በመዲናዋ ባለፉት ስድስት ወራት ከ113 ሺህ በላይ የሆኑ ወጣቶችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል

አዲስ አበባ፤ጥር 22/2017(ኢዜአ)፦በመዲናዋ ባለፉት ስድስት ወራት 113 ሺህ 326 ወጣቶችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ገለፀ።

ቢሮው የ2017 በጀት ዓመት የ6 ወር ዕቅድ አፈጻጸምን ከባለድርሻ አካላት ጋር ገምግሟል።

የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን በዚሁ ወቅት፤ የከተማዋ ወጣቶች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።

በከተማው በተገነባው የመጀመሪያ ዙር የኮሪደር ልማት 50 ሺህ ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ በሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማትም በተመሳሳይ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በስፖርት ዘርፉም ብቁና ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ለማፍራት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል።

በዚህም ባለፉት አራት ዓመታት በከተማው ከ1 ሺህ 300 በላይ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መገንባታቸውን ጠቅሰው፥ በሁለተኛ ዙር ኮሪደር ልማት 17 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እየተገነቡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ከዚህ ባለፈም ወጣቱን በዕውቀት የበለፀገ፤ በስነ ምግባር የታነፀ፤ ንቁና ስራ ፈጣሪ እንዲሆን የሚያስችሉ በርካታ የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች መሰራታቸውን አብራርተዋል።

ወጣቱ በማዕድ ማጋራት፣በአረንጓዴ አሻራ ልማት፣ በደም ልገሳ፣ በትራፊክ በጎፍቃድ አገልግሎትን ጨምሮ በሁሉም በጎ ተግባራት መስኮች በንቃት በመሳተፍ ማህበራዊ ተሳትፎውን እያረጋገጠ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

በቢሮው የዕቅድና በጀት ክትትል ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አበባየሁ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳሉት፥ በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ለ110 ሺህ ወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ 113 ሺህ 326 ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።

ቢሮው ወጣቶችንና የስፖርት ቤተሰቡን በማሳተፍ የ15 አቅመ ደካሞችን ቤት ማደሱንና ለ330 አቅመ ደካሞች ደግሞ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በስነ ተዋልዶ ጤና፣ በወቅታዊ ጉዳይ፣ በሰላምና ግጭት አፈታት ዙሪያ ከ1 ሚሊዮን 639ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መሰራቱንም አንስተዋል።

ዜጎች በአካልና በአዕምሮ ጎልብተው ጤናማ እና አምራች እንዲሆኑ ለማስቻል ከ4 ሚሊዮን 509 ሺህ 896 የሚበልጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማህበረሰብ አቀፍ ስፖርት ተሳታፊ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ተቋሙ በሁሉም መስክ አበረታች ውጤት ማስመዝገቡን ገልፀው፥ በግማሽ አመቱ ያልተሳኩትን ተግባራት በሁለተኛው ግማሽ አመት ስራ ጨምረው ለማሳካት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም