በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ ተግባራትን እናከናውናለን-የቤንች ሸኮ ዞን አርሶ አደሮች

ሚዛን አማን፤ጥር 22/2017 (ኢዜአ)፦በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትን እንደሚያከናውኑ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የቤንች ሸኮ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ።

በዞኑ ባሉ ሁሉም መዋቅሮች የዘንድሮ የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ሥራ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።

እንደ ዞን በሸይ ቤንች ወረዳ ማዝ ቀበሌ በተጀመረው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ላይ የተሳተፉት አርሶ አደር ታደሰ ኮኒ፥ መሬት ለምነቱን ሲያጣ መርታማነቱ እንደሚቀንስ ገልጸዋል።

ይህን ለመከላከል የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በየዓመቱ እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የተፋሰስ ልማት በተከናወነባቸው አካባቢዎች ሙዝ፣ የመኖ ሣር እና ሌሎች ፍራፍሬዎችን በመትከል ተጠቃሚ ለመሆን ጠንክረው እንደሚሰሩም ጠቅሰዋል።

በተፋሰስ በሚለሙ አካባቢዎች የፍራፍሬ ችግኞችን መትከል የተራቆተ ቦታ ፈጥኖ እንዲያገግም ያደርጋል ያሉት ደግሞ አቶ በላይ ወልደየስ የተባሉ አርሶ አደር ናቸው።

ከዚህ ቀደም በአካባቢው በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የተሻለ ለውጥ ማምጣታቸውን ገልጸው፥ በየዓመቱ ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ዘንድሮ የተፋሰስ ልማት በሚሰራባቸው ዳገታማ ቦታዎች ሸንኮራ አገዳና ለአካባቢው ተስማሚ የሆኑ ሌሎች ችግኞችን ለመትከል መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።

በተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራው በግብርና ባለሙያዎች ምክረሀሳብ መሰረት ምርታማነትን የሚጨምሩና ገበያን ለማረጋጋት የሚያስችሉ የግብርና ሥራዎችን መሥራት ከሁላችንም ይጠበቃል ወይዘሮ ጣይቱ ሙሉጌታ የተባሉ ሌላዋ የተፋሰስ ልማት ሥራው ተሳታፊ ናቸው።

የቤንች ሸኮ ዞን ግብርና፣አካባቢ ጥበቃና ኅብረት ሥራ መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ጉብላ በዞኑ በ34 ሺህ 480 ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ተግባር እንደሚከናወን ገልጸዋል።

ለዚህም በ96 ንዑስ ተፋሰሶች ላይ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ዛሬ በሁሉም መዋቅሮች ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል።

በለሙ ተፋሰሶች የፍራፍሬ ችግኝ በስፋት በመትከል አርሶ አደሩ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆን መምሪያው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም አስገንዝበዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን መንገሻ የተፋሰስ ልማቱን በይፋ ሲያስጀምሩ እንደገለጹት፣የተፈጥሮ ሀብትን መጠበቅ ሰውና እንስሳትን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያድርግ ነው።

የመሬት ለምነትን ለመጠበቅና የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመረው የተቀናጀ አፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም