የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን እና ሀዲያ ሆሳዕና የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ17ኛ ሳምንት መርሃ ግብር የመጨረሻ ቀን ውሎ የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ከሀዲያ ሆሳዕና የሚያደርገው ጨዋታ የተመልካቾችን ትኩረት ስቧል።


የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳል።


ኢትዮጵያ መድን በሊጉ ያደረጋቸውን ያለፉት አምስት ጨዋታዎች አሸንፏል። በጨዋታዎቹ ዘጠኝ ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ሁለት ግቦችን አስተናግዷል።


ቡድኑ በ29 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።


ሀዲያ ሆሳዕና ከባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ውስጥ በሶስቱ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።


በጨዋታዎቹ ስድስት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያገናኝ አራት ግቦችን በማስተናገድ በ26 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ይዟል።


ኢትዮጵያ መድን የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ከተከታዩ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አራት ከፍ ያደርጋል። 


ተጋጣሚው ሀዲያ ሆሳዕና በጨዋታው ድል ከቀናው ደረጃውን የማሻሻል እድል ያገኛል።

በ17ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሃ ግብር ድሬዳዋ ከተማ ከፋሲል ከነማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።


ድሬዳዋ ከተማ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች አላሸነፈም። አንድ ጊዜ ሲሸነፍ አራት ጊዜ አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ አንድ ግብ ብቻ ሲያስቆጥር ሶስት ጎሎችን አስተናግዷል። 


ቡድኑ በ19 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።


ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ በበኩሉ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። አንድ ጊዜ ሲሸነፍ ሶስት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።


በአምስቱ ጨዋታዎቹ ሶስት ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ ሶስት ጎሎች ተቆጥረውበታል። ፋሲል ከነማ በ17 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።


በተያያዘ ዜና ትናንት በተደረጉ የ17ኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ጨዋታዎች ሃዋሳ ከተማ መቻልን 1 ለ 0 ሲያሸንፍ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ አንድ አቻ ተለያይተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም