የወልዲያ ከተማ የመጀመሪያ ምዕራፍ የኮሪደር ልማት የፊታችን የካቲት ወር መጨረሻ ይጠናቀቃል - ኢዜአ አማርኛ
የወልዲያ ከተማ የመጀመሪያ ምዕራፍ የኮሪደር ልማት የፊታችን የካቲት ወር መጨረሻ ይጠናቀቃል
ወልዲያ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፡- በሰሜን ወሎ ዞን የወልዲያ ከተማ የመጀመሪያ ምዕራፍ የኮሪደር ልማት የፊታችን የካቲት ወር መጨረሻ እንደሚጠናቀቅ ከተማ አስተዳደሩ ገለፀ።
የመጀመሪያው ምዕራፍ ሲጠናቀቅ 15 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት እንደሚከናወን ገልጿል።
የከተማዋ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የኮሪደር ልማቱ የወልዲያ ከተማን ይበልጥ ውብ፣ ፅዱ እና ለነዋሪዎቿ ምቹ የሚያደርግና የስራ እድል የፈጠረ ፕሮጀክት ነው።
ባለፈው ሕዳር ወር የተጀመረው የመጀመሪያ ምዕራፍ የአንድ ኪሎ ሜትር ኮሪደር ልማት 35 በመቶው መድረሱን ገልፀው፤ የፊታችን የካቲት ወር መጨረሻ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።
የመጀመሪያው ምዕረፍ ኮሪደር ልማት ለ125 ሰዎች የስራ ድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸው፤ ልማቱ በሕብረተሰቡ ተሳትፎ እንደቀጠለ ገልጸዋል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ ሲጠናቀቅ 15 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሁለተኛው ምዕራፍ ኮሪደር ልማት እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ከጀነቶ በር እስከ ሸህ አልአሙዲ አደባባይ፤ ሸህ አልአሙዲ አደባባይ እስከ ስታዲየም፤ ከስታዲየም እስከ እቴጌ መናፈሻ እና ከፒያሳ እስከ ጉቦ በር የሚሸፍን መሆኑን አስታውቀዋል።
ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወጣት አለማየሁ ኃይሉና አዲሱ ንጉስ በኮሪደር ልማቱ የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ኢኮኖሚና ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዳሳደጉ ገልጸዋል።
የአካባቢው ሰላም በመሻሻሉ የኮሪደር ልማት እየተፋጠነ መሆኑን ገልጸው፤ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በከተማዋ ዕድገት የሚያሳድግና የትራንስፖርት መጨናነቅን የሚቀርፍ ስለመሆኑ ገልጸዋል።