በክልሉ በስድስት ወራት ውስጥ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በስድስት ወራት ውስጥ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ
ጋምቤላ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ከተለያዩ የገቢ አርዕስቶች ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።
ክልሉ የገቢ አቅም አሟጦ በመጠቀም ወጪዎችን በራስ አቅም ለመሸፈን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ቢሮው ገልጿል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ቸንኮት ዴቪድ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በተያዘው በጀት ዓመት ከ2 ቢሊዮን 963 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዷል።
በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ከአንድ ቢሊዮን 486 ሚሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ የዕቅዱን 91 ነጥብ 66 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።
ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም ከ437 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ ተናግረዋል።
የክልሉ ገቢ አቅም አሟጦ በመሰብሰብ ወጪዎችን በራስ የመሸፈን አቅምን በማሳደግ የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ፍላጎቶችን ለማሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
የታክስ አስተዳደር ስርዓቱን በማዘመን ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ በቀላሉ ግብር የሚከፍልበትን አሰራር በወረዳዎች የማስፋት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
በቀጣይ ግማሽ በጀት ዓመት ለግብር ከፋዮች አዲሱን ልዩ መለያ /Qr Code/ ደረሰኝ ተግባራዊ በማድረግ ጥረት እየተደረገ ነውም ብለዋል።
ግብር ለህዝቡ የሚበጁ መሰረተ ልማቶችን ለማከናወን ያለውን ሁለንተናዊ ፋይዳ ጠቅሰው፤ ማህበረሰቡ ግብሩን በወቅቱ በመክፈል ሀገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።