11 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ሆነዋል

 

አዲስ አበባ፤ጥር 23/2017(ኢዜአ)፦ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የወሰዱ ዜጎች ቁጥር 11 ነጥብ 5 ሚሊዮን መድረሱን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም አስታውቋል፡፡

የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ የነዋሪዎችን የባዮሜትሪክ (የጣት አሻራ፣ የአይን አይሪስ እና የፊት ምስል) እንዲሁም የግል መረጃዎችን በመሰብሰብ አንድን ግለሰብ ልዩ በሆነ መልኩ እንዲታወቅ የሚያስችል ነው፡፡

ይህም ዘመናዊ የዲጂታል መታወቂያ ስርዓትን በመገንባት ማንነትን የማረጋገጥ ሂደት ቀልጣፋ እና ደህንነቱ የተረጋገጠ እንዲሆን ያደርጋል።

የፕሮግራሙ የስትራቴጂክ የኮሙኒኬሽን አማካሪ አቶ አቤኔዘር ፈለቀ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ ፕሮግራሙ ከተጀመረ አመታት ማስቆጠሩን ተናግረዋል።

በነዚህ አመታት ውስን በፕሮግራሙ የታቀዱ ውጥኖች ማሳካት የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል።


 

እስከ አሁን ድረስ ከ1 ሺህ በላይ በሆኑ የምዝገባ ጣቢያዎች 11 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች መታወቂያውን መውሰዳቸውን አስታውቀዋል።

ከ52 ተቋማት ጋር ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ትግበራና የአሰራር ትስስር መዘርጋት የሚያስችል ስራ መሰራቱንም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን 12 የሚደርሱ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንደ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የሕግና ፖሊሲ ክፍል ኃላፊ ጋብሬላ አብርሃም በበኩላቸው፥ በ2017 ዓ.ም የብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባ በተጠናከረ አግባብ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በዚህም በተቋሙና በምዝገባ ሂደት አጋር በሆነው ኢትዮ ቴሌኮም አማካኝነት በአገር አቀፍ ደረጃ ምዝገባ እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።


 

ይህም በከተሞች ብቻ የነበረውን ምዝገባ በገጠር አካባቢዎችም ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፥ ይህም በዓመቱ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት እንደሚያስችል ጠቅሰዋል።

ምዝገባውን በድንበር አካባቢዎችም ተደራሽ ለማድረግ በግል ተቋማት የሚከናወን ሱፐርኤጀንት የሚባል አሰራር ተግባራዊ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተግባራዊ መደረጉ ሁሉን አቀፍ፣አካታችና አስተማማኝ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችልም ተመላክቷል።

ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ዘርፈ ብዙ አስፈላጊነትን በመገንዘብ በአቅራቢያቸው በሚገኙ የመመዝገቢያ ጣቢያዎች በመመዝገብ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ እንዲሆኑም ኃላፊዎቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም