ለሕዳሴ ግድብ የሚደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፦ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ህብረተሰቡ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን የግድቡ ግንባታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ገለፀ።

በግማሽ ዓመቱ 454 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ መሰብሰቡን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።

የፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍቅርተ ታምር ከኢዜአ እንዳሉት፣ ግድቡ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።

ከግድብ ግንባታ ጀምሮ ሁሉም ዜጋ በዕውቀቱ፣ በጉልበቱና በገንዘቡ ድጋፍ በማድረግ ግድቡ ትውልዱ የመተባበር፣ የአንድነትና የመቻል ተምሳሌት እንደሆነ አረጋግጧል ብለዋል።

ህብረተሰቡ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሁለንተናዊ ድጋፉን እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ ባለፉት ስድስት ወራት 454 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል ብለዋል።

ፅህፈት ቤቱ ድጋፉ ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ እንዲቀጥል ከተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ አማራጮችን የድጋፍ ማሰባሰብ ስራ እንደቀጠለ ጠቁመዋል።

በአባይ ተፋሰስ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎች የጉልበት ድጋፍ እንዲሁም የምሁራን ተሳትፎ የዕውቀት ድጋፍ ማሳያ እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

ለጋራ ጥቅምና ዓላማ በህብረት መቆም ያለውን ውጤቱ ያስተማር ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸው፤ ህብረተሰቡ የነበረውን የነቃ ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም