አገር አቀፍ ኤግዚቢሽን ባዛርና ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፦ ከ350 በላይ ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት የሚሳተፉበት አገር አቀፍ ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽንና የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኮሚሽን አስታወቁ።

የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽንና የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኮሚሽን በጋራ ያዘጋጁትን ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

መርኃ ግብሩ ከጥር 28 እስከ የካቲት 3 ቀን 2017 "የህብረት ስራ ማህበራት ሚና ለኢትዮጵያ ብልፅግና" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ይካሄዳል።

በመርኃ ግብሩ ከ50 ሚልዮን ብር በላይ ግብይት ይከናወንበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተገለጸ ሲሆን አምራችና ሸማቾችን በማገናኘት የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ያስችላል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሺሰማ ገብረስላሴ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ በኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየሙ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ ሸማች ማህበራት ይሳተፋሉ።

በኢግዚቢሽንና ባዛሩ ከ350 በላይ የግብርናና ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት እንዲሁም ከመቶ በላይ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ይሳተፋሉ ብለዋል።

ኢግዚቢሽኑ የህብረት ስራ ማህበራት የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

መርኃ ግብሩ የተሻለ ተሞክሮ ያላቸውን የህብረት ስራ ማህበራት አሰራር በመቀመርና ልምድ በመቅሰም የህብረት ስራ ማህበራትን እድገት ወደ ተሻለ ከፍታ ለማድረስና የሀገሪቱን የብልፅግን ጉዞ ለማረጋገጥ የሚያስችል ስራ የሚከናወንበት ነው ብለዋል።

በመድረኩ አጠቃላይ የፋይናንስ ተቋማት እንደሚገኙ ገልፀው፤ ግብይቱ በዲጂታል አማራጭ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረት ስራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተጫነ አዱኛ በበኩላቸው በአዲስ አበባ ያሉ ከ120 በላይ ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት በመድረኩ እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል።

እንዲሁም ከ110 በላይ የተለያዩ የምርት አይነቶች በኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየሙ ለግብይት እንደሚቀርቡ ገልጸዋል።

ከስልሳ ሺህ በላይ ሰዎች ይጎበኙታል ተብሎ በሚጠበቀው ኤግዚቢሽን፣ባዛርና ሲምፖዚየም ከሁሉም ክልሎች የግብርና ምርቶች፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣የሌማት ትሩፋት ውጤቶች እንደሚቀርቡ ተገልጿል።

በኢግዚቢሽንና ባዛሩ ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶች እንዲቀርቡ ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል።

ዘንድሮ የሚካሄደው ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ11ኛ በአዲስ አበባ ደረጃ ደግሞ ለ4ኛ ጊዜ መዘጋጀቱ በመግለጫው ተመላክቷል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም