በክልሉ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ከ66 ሺህ በላይ ለሆኑ ወጣቶች በተለያዩ መስኮች የስራ እድል ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ከ66 ሺህ በላይ ለሆኑ ወጣቶች በተለያዩ መስኮች የስራ እድል ተፈጥሯል
መቀሌ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፡- በክልሉ በበጀት ዓመቱ ስድስት ለ66 ሺህ በላይ ለሆኑ ወጣቶች በተለያዩ መስኮች የስራ እድል መፈጠሩን በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የወጣቶች ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በመስኖ ልማት ዘርፍ እንዲሰማሩ ባመቻቸላቸው የስራ ዕድል ውጤታማነታቸውን በማረጋገጥ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው ማደጉን በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የእንደርታ ወረዳ ወጣቶች ገልጸዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የወጣቶች ቢሮ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ውስጥ ለ66 ሺህ 784 ወጣቶች በተለያዩ መስኮች የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ገልጿል።
ውጤታማ መሆን ከጀመሩ ወጣቶች መካከል በእንደርታ ወረዳ ''የማህበረ ገነት'' ገጠር ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ፍፁምብርሃን ሰገድ አንዱ ነው።
በጊዜያዊ አስተዳደሩ በተመቻቸለት የስራ እድል በሁለት ሄክታር መሬት ላይ ቲማቲም፣ ቀይ ሽንኩርትና ቃሪያ በማልማት በዓመት ሶስት ጊዜ ምርት እየሰበሰበ መሆኑን ተናግሯል።
በወረዳው የገረብ ግባ ገጠር ቀበሌ ነዋሪው ወጣት ፀጋይ ግደይ በበኩሉ፣ ከቤተሰቡ የተሰጠውና ተጨማሪ አንድ ሄክታር መሬት በመከራየት አትክልትና ፍራፍሬ እያለማ የራሱ እና የቤተሰቡን ህይወት እየለወጠ እንደሚገኝ ገልጿል።
እያለማው ካለው ምርትም ገቢ እያገኘ መሆኑንና ዛሬ ላይ በስሩ ስድስት ወጣቶችን ቀጥሮ እያሰራ መሆኑን አመልክቷል።
ህገ-ወጥ ስደትን ከመምረጥ እዚሁ እየተመካከሩ መስራትና መለወጥ እንደሚመረጥ ወጣት ፀጋይ ተናግሯል።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የገለፀችው ደግሞ በእንደርታ ወረዳ የማህበረ ገነት ገጠር ቀበሌ የመስኖ ልማት ባለሙያ ወጣት ለምለም ገብረጨርቆስ ናት።
አሁንም ለወጣቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንቅስቃሴ ከተደረገ ወጣቱ የመስራትና የመለወጥ ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው ብላለች።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለወጣቶች በሰጠው ትኩረት በእንደርታ ወረዳ ከ3 ሺህ 600 በላይ ወጣቶች በግብርና ልማት ዘርፍ ብቻ እየሰሩ እንዲለወጡ እየተደረገ መሆኑን የወረዳው መስኖ ልማት አስተባባሪ አቶ ዓምደ ገብረ ስላሴ አስታውቀዋል።
በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ 66 ሺህ 784 ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው በጊዜያዊ አስተዳደሩ ወጣቶች ቢሮ የስራ እድል ፈጠራ ዳይሬክተር አቶ ዓብድል ዓዚዝ ዓብዱ ልቃድር ገልፀዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ የስራ ዕድሉ ከተፈጠረላቸው ወጣቶች ከ32 ሺህ የሚልቁት ሴቶች ናቸው።