በጋምቤላ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት በኢኮኖሚና  በሰላም ግንባታ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል

ጋምቤላ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት  በሰላም ግንባታ፣ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የልማት ዘርፎች አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን የክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ተናገሩ ።

ቋሚ ኮሚቴዎቹ  የክልሉን ያለፉት ስድስት ወራት የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድ አፈፃፀም ገምግመዋል።

የቋሚ ኮሚቴዎች ሰብሳቢዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤  በክልሉ በበጀት ዓመቱ  የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት በሰላም ግንባታ፣ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የልማት ዘርፎች አበረታች ስራዎች ተከናውነዋል።  

የምክር ቤቱ የግብርና፣ የቆላማ አካባቢና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ገላዊት ታንገሺን ፤ በክልሉ የሌማት ቱሩፋትን ጨምሮ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ስራዎች  አፈፃፀም  ውጤታማ  መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

በተለይም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ከተረጅነት ለመላቀቅ የተጀመረውን ‘‘ኢንሸቲቭ’’ ስኬታማ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ይበል የሚያሰኙ ናቸው ብለዋል።

በክልሉ በትምህርት ለትውልድ መርሃ ግብር ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን በመገንባት የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን የተናገሩት  የምክር ቤቱ የሰው ሃብት፣ ማህበራዊ ልማትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጋትሉዋክ ጋች ናቸው።


 

እንዲሁም አዲሱን ስርዓተ ትምህርት  ተግባራዊ በማድረግ በኩልም በክልሉ ብሎም እንደ ሀገር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የታለመውን ግብ ከማሳካት አኳያ መልካም ጅምሮች መኖራቸውን ተናግረዋል።

በጤና ተቋማት የተዘዋዋሪ መድኃኒት መግዣ በጀት ውስንንት ስለመኖሩ ጠቁመው ፤ በዚህ ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አቶ ጋትሉዋክ አሳስበዋል።

ሌላው የምክር ቤቱ የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኡፓራ አጉዋ  እንደገለጹት፤ በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ረገድ  እስከ ወረዳ ስኬታማ ተግባራት ተከናውነዋል። 


 

ሆኖም ጥራቱን የጠበቀ የፍትህ አገልግሎት ለዜጎች ተደራሽ በማድረግ ረገድ ያሉት ውስነቶች  በቀጣይ ማስተካከል እንደሚገባ አመላክተዋል።

የክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች በየዘርፉ በተለያዩ አዳራሾች ትናንት የጀመሩት የስድስት ወር የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድ አፈፃፀም ግምገማ ዛሬ ተጠናቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም