ድሬዳዋን ይበልጥ ውብ የመኖሪያና የሥራ ተመራጭ ከተማ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ድሬዳዋን ይበልጥ ውብ የመኖሪያና የሥራ ተመራጭ ከተማ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ድሬደዋ ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፡- ድሬዳዋን ይበልጥ ውብና ፅዱ የመኖሪያ እና የሥራ ተመራጭ ከተማ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የከተማው አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤት ገለጸ።
ጽህፈት ቤቱ "ከብክነት ወደ ሀብት ምንጭነት " በሚል የሚካሄደውን የደቻቱ አሸዋማ ስፍራ ፕሮጀክት መተግበሪያ ስምምነት ዛሬ ከድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶች ምክር ቤት ጋር ተፈራርሟል።
ስምምነቱን የተፈራረሙት የድሬደዋ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር ጀማል ኢብራሂም እና የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሀሚድ አብደላ ጋር ናቸው።
ኢንጂነር ጀማል ኢብራሂም በወቅቱ እንደተናገሩት ፤ ድሬዳዋን ውብ ፣ፅዱና ማራኪ የመኖሪያና የስራ ተመራጭ ከተማ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው።
በተለይ በበጀት ዓመቱ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ይህንኑ ለማሳካት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል ።
ከዚህ ጎን ለጎን በከተማው የሚወጣው ቆሻሻ በተቀናጀ መንገድ በማፅዳትና ወደ ጥቅም በመለወጥ ከተማዋ ፅዱና ውብ የመኖሪያ ስፍራ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ዛሬ ከወጣቶች ምክር ቤት ጋር የተፈረመው ስምምነት በደቻቱ አካባቢ የሚገኘውን ስፍራ ፅዱና ውብ የንግድና የመኖሪያ ስፍራ ለማድረግ መሆኑን ተናግረዋል ።
በፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው 60 ወጣቶቹ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ስራ በመግባት የአካባቢውን ብክለት በመከላከል ስፍራው የስፖርትና የመዝናኛ ተመራጭ ስፍራ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።
በተጨማሪም ፕሮጀክቱ የአካባቢውን የተፈጥሮ ሃብት ወደ ገቢ ምንጭነት በመለወጥ ሀብቱ በዘላቂነት እንዲጠበቅ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ቀጣይ ምዕራፍ እንዳለው ጠቁመዋል።
የድሬደዋ አስተዳደር ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወጣት ሀሚድ አብደላ በበኩሉ፤ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የአስተዳደሩ ወጣቶች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባራት ውስጥ ያላቸው ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየጎለበተ መምጣቱን ተናግረዋል።
ዛሬ ወደ ተግባር የተሸጋገረው ፕሮጀክትም የዚሁ ውጤት ማሳያ መሆኑን ጠቅሷል።
በቆሻሻል ለብከለት የተጋለጠው የደቻቱ አሸዋማ ስፍራ ውብና ፅዱ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚተጉ የተናገረው ደግሞ የምክርቤቱ ፀሐፊና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ወጣት አማረ ጥላሁን ነው።