ከሻይ ምርት ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት የተጀመረው ጥረት ሊጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ከሻይ ምርት ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት የተጀመረው ጥረት ሊጠናከር ይገባል
መቱ ፤ጥር 23/2017 (ኢዜአ)፡- በቡና ምርት እየተገኘ ያለውን ጥቅም ከሻይ ምርትም ለማግኘት የተጀመረው ጥረት ሊጠናከር እንደሚገባ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በአዲስ የሻይ ልማት ፓኬጅ ላይ የሁለት ቀናት የአሰልጣኞች ስልጠና በመቱ ከተማ እየሰጠ ይገኛል።
በስልጠና ማስጀመሪያው ላይ የባለስልጣኑ የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ዘርፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ደፈረስ፤ በኢትዮጵያ በቡናው ምርት እያስገኘ ያለውን ጥቅም በሻይም ለመድገም በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የሻይ ልማት በኢትዮጵያ ከተጀመረ ዘጠና ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ከዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ተጠቃሚ መሆን እንዳልተቻለ ጠቅሰዋል።
በነዚህ ዓመታት ሁሉ በሻይ ለምቶ የሚገኘው መሬት 3 ሺህ 729 ሔክታር መሬት ብቻ መሆኑን አንስተው ይህም በግል የልማት ድርጅቶች እንጂ በአርሶ አደሩ ዘንድ የተሰራው ስራ ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይ መንግስት ትልቅ ትኩረት ከሰጣቸው የልማት አቅጣጫዎች አንዱ እንደመሆኑ ባለስልጣኑም በሚቀጥሉት አምስት አመታት 100 ሺህ ሔክታር መሬት በሻይ እንዲለማ እስፈላጊ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህን ለማሳካትም በክልሎች ያለውን የማስፈጸም አቅም ለማሳደግ የአቅም ግንባታ ስራዎች በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የሻይ ልማት ለስራ ዕድል ፈጠራ፣ ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለአርሶ አደሩ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል።
በተጨማሪም የሻይ ልማት ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ትልቅ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ለልማቱ የተሰጠው ትኩረት ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድሳኒ አሚን በበኩላቸው በከልሉ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት 30 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የሻይ ችግኝ ለማልማት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
ለዚህም በክልሉ በተለይ ለሻይ ልማቱ ምቹ ሁኔታ ባላቸው ዞኖች የችግኝ ዝግጅት ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሻይ ተክል ምርት መስጠት ሲጀምር በየሁለት ሳምንቱ ለፋብሪካ የሚቀርብ በመሆኑ ከሌላው የግብርና መስኮች የበለጠ የአርሶ አደሩን ብሎም የሀገርን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድግ መሆኑንም ተናግረዋል።
በኢሉባቦር ዞን በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት 15 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ ሻይ የማልማት ስራ በትልቅ ትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቻላቸው አዱኛ ናቸው።