በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቡና ምርታማነትን የሚያሻሽሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ

ዲላ፤ ጥር 23/2017 (ኢዜአ):- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቡና ምርታማነትን ለማሻሻል  የሚያስችሉ  ተግባራት  በመከናወን ላይ እንደሚገኝ የክልሉ ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ገለጸ።

የኩታ ገጠም የቡና ልማት የመስክ ልምድ ልውውጥ በከልሉ ጌዴኦ ዞን ወናጎ ወረዳ ተካሂዷል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል ብሩ በወቅቱ እንዳመለከቱት፤ በክልሉ የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ የኩታ ገጠም የቡና እድሳት እየተከናወነ ነው።

በበጀት ዓመቱ ከ10 ሺህ ሄክታር በላይ ያረጀ ቡናን በማንሳት በተሻሻሉ ዝሪያዎች ለመተካት የነቀላና ጉንደላ ስራ በንቅናቄ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በተለይ አርሶ አደሩን በኩታ ገጠም በማደራጀት ያረጀ ቡና የማንሳት ስራን በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ለማስፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤  ምልከታውም የዚሁ አካል መሆኑን ገልጸዋል።


 

በቡና እድሳት የሚስተዋለውን የአመለካከትና የግብዓት በተለይም የተፈጥሮ ማዳበሪያና የተሻሻሉ የቡና ዝሪያዎች አቅርቦት በማመቻቸት የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ ርብርቡ መጠናከር እንዳለበት አመልክተዋል።

በዞኑ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የቡና እድሳት ስራዎች ውጤት ማምጣቱን የገለጹት የጌዴኦ ዞን ቡናና ቅመማ ቅመም ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኤርሚያስ ቼካ ናቸው።

ይህም ምርታማነትን ማሳደግ  መቻሉን ጠቁመው፤ በዞኑ በተያዘው ዓመት ከ4ሺህ 200 ሄክታር ላይ የሚገኝ ያረጀ ቡና በማንሳት በተሻሻሉ ዝሪያዎች ለመተካት ወደ ተግባር መግባታቸውን  ተናግረዋል።

ከዚህ ውስጥም 342 ሄክታር የቡና ማሳ  በኩታ ገጠም እየለማ ነው ብለዋል።

በወናጎ ወረዳ የቱማታ ጭራቻ ቀበሌ  አርሶ አደር ብርሃኑ አልማሴ በሰጡት አስተያየት፤ ባለፈው ዓመት እሳቸውን ጨምሮ 54 አርሶ አደሮች ከ27 ሄክታር መሬት ያረጀ ቡናን በማንሳት የተሻሸሉ ዝሪያዎችን በኩታ ገጠም ማልማታቸውን አንስተዋል።


 

የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀምና የአረም ቁጥጥር ጨምሮ የተለያዩ እንክብካቤዎችን በማከናወን ቡናው በአጭር ጊዜ ምርት እንዲሰጥ እየሰራን ነው ብለዋል። 

ዘንድሮም ተጨማሪ በ36 ሄክታር መሬት ላይ ያረጀ ቡና በማንሳት በተሻሻሉ ዝሪያዎች ለመተካት እየሰሩ መሆኑን  ገልጸዋል።

በልምድ ልውውጡ  በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ አመራር አባላትና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም