የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ገቢዎች ቢሮ ከ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ገቢዎች ቢሮ ከ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ
ሚዛን አማን፤ ጥር/23/2017 (ኢዜአ)፡-የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ገቢዎች ቢሮ ባለፉት ስድስት ወራት ከ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ሕይወት አሰግድ በሰጡት መግላጫ ፤ በበጀት ዓመቱ የክልሉን መንግስት የልማት ወጪ 60 በመቶውን በራስ የገቢ አቅም ለመሸፈን ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው።
የግብር ሕጎችን በማስከበርና የገቢ አሰባሰብ ሂደቱን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ባለፉት ስድስት ወራት ከተለያዩ የገቢ አርዕስቶች ከ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታውቀዋል።
የተሰበሰበው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ጠቁመዋል።
የክልሉን የገቢ አሰባሰብ ሂደት ከቴክኖሎጂ ጋር ለማጣጣም ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በ31 የታክስ ማዕከላት የሲስተም ዝርጋታ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።
በአጠቃላይ በክልሉ ውስጥ ካሉት 70 የታክስ ማዕከላት በ66ቱ ላይ ሲስተም በመዘርጋት እንዲሠሩ መደረጉን አክለዋል።
በዚህም በግማሽ የበጀት ዓመቱ 15 ሺህ የሚጠጉ የደረጃ 'ሐ' ግብር ከፋዮች ግብራቸው በ" ሲግታክስ" አሰርተው በቴሌብር አማካኝነት መክፈላቸውን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በግማሽ የበጀት ዓመቱ 186 ግብር ከፋዮችን ኦዲት በማድረግ የተገኘ 79 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።
በተመሳሳይ በገቢ ተቋም ውስጥ ሆነው በሕገ ወጥ ድርጊት የተሰማሩ 36 ባለሙያዎች ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ መወሰዱንም ጠቅሰዋል።
ደረሠኝ ሳይቆርጡ ሲያገበያዩ የተገኙ 205 የንግድ ድርጅቶች ላይ የማስተካከያ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል።
በክልሉ በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ የታቀደው 9 ቢሊዮን ብር መሆኑ ተመልክቷል።