በደሴ ከተማ  የኮሪደር ልማት በፍጥነት እየተከናወነ ነው  - የከተማው አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ሽመልስ ጌታቸው  

ደሴ ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፡-የደሴ ከተማ አስተዳደር እየተከናወነ ያለው የአንድ ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ እየተፋጠነ እንደሚገኝ የከተማው አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሽመልስ ጌታቸው ገለጹ፡፡

የከተማ አመራር አባላትና ባለድርሻ አካላት ከቧንቧ ውሃ እስከ ወሎ ባህል አምባ እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት ተመልክተዋል፡፡

ምክትል ከንቲባው በወቅቱ እንደገለጹት፤ ከተማውን  ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ፡፡

በዚህም ህብረተሰቡን በማሳተፍ ከቧንቧ ውሃ እስከ ወሎ ባህል አምባ እየተሰራ ያለው የአንድ ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ ጥራቱን ጠብቆ በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ለልማት ስራው መፋጠን የአመራር አባላቱ  ያልተቋረጠ ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ አመልክተው፤  የልማት ስራው እስከዚህ ዓመት መጨረሻ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። 

ልማቱ ለበርካታ ዜጎችም የሥራ እድል እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለኮሪደር ልማቱ የህብረተሰቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎና አጋዥነት ውጤት እንዲመዘገብ እያረገ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጠል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ መንግስቱ አበበ በበኩላቸው፤ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ሰፋፊ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡


 

በተለይ የኮሪደር ልማቱ በተያዘለት ጊዜ በጥራት እንዲጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በህብረተሰቡ ከፍተኛ ድጋፍ እየተፋጠነ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የልማት ስራው በአመራር አባላትና ባለሙያዎች የተጠናከር ክትትል በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በደሴ ከተማ  እየተከናወነ ላለው የኮሪዳር ልማት ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተመላክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም