የጥናትና ምርምር ስራዎች የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግና ችግሮችን ለመፍታት አቅም መሆን አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የጥናትና ምርምር ስራዎች የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግና ችግሮችን ለመፍታት አቅም መሆን አለባቸው
ሀዋሳ ፤ጥር 23/2017 (ኢዜአ):- በምሁራን የሚሰሩ የጥናትና ምርምር ስራዎች የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግና ችግሮችን ለመፍታት አቅም ከመሆን ባለፈ መንግስት ለሚነድፋቸው ፖሊሲዎች ግብዓት መሆን እንዳለባቸው ተገለፀ።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር "ብሔራዊ ጥቅሞቻችንና ቀጣናዊ ትስስር ለሚዛናዊ የህዝቦች ተጠቃሚነት" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ዛሬ ተካሄዷል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጪ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጅሀድ ናስር እንደገለፁት፤ በዩኒቨርሲቲ ምሁራን የሚያደርጉት የጥናትና ምርምር ስራዎች የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግና ችግሮችን ለመፍታት አቅም ከመሆን ባለፈ መንግስት ለሚነድፋቸው ፖሊሲዎች ግብዓት ሊሆኑ ይገባል።
በውይይት መድረኩ ላይ የሰላም ሚኒስቴርን በመወከል የተገኙት በተቋሙ የብሔራዊ መግባባት ባለሙያ ወይዘሮ ሲሳይ ብርሌ እንዳሉት ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅና ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የምሁራን ሚና የላቀ ነው።
የዛሬው ውይይትም ለሀገር እድገት ግብዓት የሚሆኑ የጥናት ውጤቶችንና አማራጭ ሀሳቦችን ምሁራን የሚያፈልቁበት አጋጣሚን የማመቻቸት ዓላማ እንዳለውና መሰል መድረኮችም በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚካሄዱ ተናግረዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ችሮታው አየለ (ዶ/ር) እንዳሉት ምሁራን ሀገርና ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የምርምር ስራዎችን መስራት ይጠበቅባቸዋል።
መድረኩ ምሁራን ለቀጣናዊ ትስስሮችና ለሀገር ግንባታ ያላቸውን አበርክቶ ለማጉላት የዳበረ ምክረ ሀሳብ ማቅረብ እንዲችሉ ታስቦ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።
በዩኒቨርሲቲው የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ተመራማሪ ዳኜ ሽብሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት በኢትዮጵያ ሰላምን፣ ልማትንና ብልጽግናን ለማምጣት ከቀጣናው ሀገራት ጋር ተባብሮና ተደጋግፎ መስራት ያስፈልጋል።
የኢትዮጵያ ሰላም ለቀጣናው ሰላምና ልማት መጠናከር የላቀ ሚና ስላለው ለተግባራዊነቱም ቀጣናዊ ትብብር ላይ መስራት የግድ እንደሚል ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የሰላም ሚኒስቴርና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወካዮችና የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተሳታፊ ሆነዋል።