በክልሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል
ሀዋሳ ጥር 23/2017 (ኢዜአ ):- በሲዳማ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን የክልሉ እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ገለፀ።
የሲዳማ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ለወረዳና ቀበሌ ባለሙያዎች በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ፓኬጆች ላይ ያተኮረ ሥልጠና እየሰጠ ነው ።
በዚሁ ጊዜ የቢሮው ኃላፊ አቶ ተክሌ ጆምባ እንደገለፁት፤ በሲዳማ ክልል የወተት፣ የሥጋ፣ የዶሮ እና የዓሣ ሀብትን ጨምሮ በሰባት ፓኬጆች የአካባቢ አቅሞችን በመለየት የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብሩ እየተከናወነ ይገኛል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት አመርቂ ውጤቶች የተመዘገቡባቸው ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው የመርሀ ግብሩ ግብ ስኬታማ እየሆነ እንደሚገኝ አስረድተዋል ።
የመርሀ ግብሩ ተግባራት ከዓመት ወደ ዓመት በመጠንና በአፈፃፀም ከፍ እያሉ እንደሚገኙ የተናገሩት አቶ ተክሌ ባለፈው በጀት ዓመት በሁሉም ፓኬጆች የተመዘገበውን ውጤት ለማስቀጠል ይሰራል ብለዋል።
ለአብነትም ባለፈው በጀት ዓመት የታቀደውን 8 ሚሊዮን ዶሮዎችን ማሰራጨት ሲሆን በዚህ ዓመት ደግሞ ከታቀደው 10 ሚሊዮን እስካሁን 4 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ዶሮ ማሰራጨት ተችሏል ብለዋል።
ባለፈው በጀት ዓመት 153 ሺህ ከብቶችን ዝርያ ማሻሻል ችለናል ያሉት አቶ ተክሌ ዘንድሮ 200 ሺህ የዝርያ ማሻሻል ስራ ለማከናወን ታቅዶ 117 ሺህ ከብቶችን ዝርያ ማሻሻል እንደተቻለም ጠቅሰዋል።
በንብ ቀፎ ስርጭት፣ አርሶ አደር ማሳዎች ውስጥ በሚዘጋጁ የዓሣ ኩሬዎች እንዲሁም በሌሎች ተግባራት ውጤታማ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
ሆኖም እያደገ የሚመጣውን የህዝቡን ፍላጎት ማሟላት እንዲቻል ከዚህም በበለጠ ፍጥነትና ጥራት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በመሆኑም በባለሙያዎች ዘንድ የሚስተዋሉ የክህሎት ክፍተቶችን ለመሙላት ብሎም በመርሀ ግብሩ ፓኬጆች ላይ የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር በማሰብ ሥልጠናው መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
የዳሌ ወረዳ እንስሳት ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሻላሞ ሹራሞ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በፓኬጆች ላይ መንደሮችን በመፍጠር ሰፋፊ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
አርሶ አደሩ በአሁን ወቅት ከሌማት ትሩፋት ሥራዎች የሚያገኘው ጥቅም እያደገ በመምጣቱ በዚሁ ልክ የአመለካከት ለውጥ እያመጣ ይገኛል ብለዋል።
በአራት ፓኬጆች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት የአለታ ወንዶ ወረዳ እንስሳት ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማርቆስ ማልካቶ በተለይ የወተት ሀብት ልማት ሥራው አርሶ አደሩን የላቀ ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በወረዳው አርሶ አደሮችን በህብረት ሥራ ማህበር በማደራጀት ለይርጋለም የግብርና ምርት ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲሁም ለአዲስ አበባ ገበያ በማቅረብ ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ ማድረግም ተችሏል ብለዋል ።
ለሶስት ቀናት በሚቆየው የሥልጠና መድረክም 900 የሚሆኑ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ሲሆን የክልል፣ የዞንና የወረዳ የዘርፍ አመራሮች ተገኝተዋል።