ፋሲል ከነማ ወደ ድል ተመልሷል 

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ17ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሃ ግብር ፋሲል ከነማ ድሬዳዋ ከተማን 2 ለ 1 አሸንፏል።

ማምሻውን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሀብታሙ ተከስተ እና አንዋር ሙራድ የማሸነፊያ ጎሎቹን አስቆጥረዋል።

ሙኸዲን ሙሳ ለድሬዳዋ ከተማ ብቸኛውን ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ውጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከነማ በሊጉ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል። በ20 ነጥብ ደረጃውን ከ14ኛ ወደ 9ኛ ከፍ አድርጓል።

ቡድኑ በውድድር ዓመቱ አራተኛ ድሉን አሳክቷል። 

በአንጻሩ በሊጉ አራተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ድሬዳዋ ከተማ በ19 ነጥብ ከ10ኛ ደረጃ 11ኛ ዝቅ ብሏል።

ድሬዳዋ የዛሬውን ጨምሮ ባለፉት ስድስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።

ቀን ላይ በተደረገ ጨዋታ የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ሀዲያ ሆሳዕናን 1 ለ 0 አሸንፏል።

ጨዋታዎቹን ተከትሎ የ17ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ተጠናቋል። የ18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከጥር 25 ቀን 2017 ዓ.ም አንስቶ ይካሄዳሉ።

ኢትዮጵያ መድን ሊጉን በ32 ነጥብ እየመራ ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ በ28 እና መቻል በ27 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

አዳማ ከተማ፣ ሃዋሳ ከተማ፣ ስሑል ሽሬ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ15ኛ እስከ 18ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም