የብልፅግና ጉባዔ በፓርቲዎች ጉባዔ ታሪክ መላው ብሔር ብሔረሰብ ተወካይ ኖሮት የሚደረግ ብቸኛው ጉባዔ ነው- የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የብልፅግና ጉባዔ በፓርቲዎች ጉባዔ ታሪክ መላው ብሔር ብሔረሰብ ተወካይ ኖሮት የሚደረግ ብቸኛው ጉባዔ ነው- የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ፓርቲዎች ጉባዔ ታሪክ መላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ተወካይ ኖሮት የሚደረግ ጉባዔ የብልፅግና ጉባዔ ብቻ ነው ሲሉ የፓርቲው ፕሬዝዳንት እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
የብልፅግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባዔ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የፓርቲው ፕሬዝዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገር በቀል ዕሳቤ ነድፎ የመጣ ፓርቲ ብልፅግና መሆኑንም ተናግረዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ለ2ኛ ጊዜ ጉባዔ ያዘጋጀበት ዋናው ምክንያት ያለፈባቸውን ጉዞ በማጠቃለል አዲስ የጉዞ ጅማሮን የሚያስኬድ የተሰናሰለ ሃሳብ የሰነቀ አመራር፣ አሰራርና ደንቦች በጉባዔ መጽደቅ ስላለባቸው መሆኑንም አስገንዝብዋል።
በምክክርና ውይይት የሚፈልቅ ሃሳብም ኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት ዓመታት የምትጓዝበትን መንገድ የሚቀይስ መሆኑን ገልጸዋል።
ከጉባዔውም በጉባዔው ሂደትም ሆነ ውጤት ዴሞክራሲያዊና አሳታፊነትን እርግጠኝነቱን ለመፈተሽ የሚያስፈልግ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ፓርቲዎች ጉባዔ ታሪክም መላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ተወካይ ኖሮት የሚደረግ ጉባዔ የብልፅግና ጉባዔ ብቻ ነው ብለዋል።
ሁለተኛው የፓርቲው ጉባዔም "ከቃል እስከ ባህል" በሚል መሪ ሃሳብ በቃል የሚነገርና የሚሰነድን በልምምድ ባህል የማድረግ ትኩረት መሰነቁን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ለሃምሳና ስልሳ ዓመታት የነበረው የፓርቲ ፖለቲካ ልምምድ የምንጠላውን አብዝተን መውቀስ፣ ልናፈርስና ልንንድ የፈለግነውን ነገር በብዙ ማስረጃ መክሰስ ላይ የተመሰረተ አንጂ ልንገነባ የፈለግነውን ለውጥ ማመላከት ላይ ውስንነት ነበረብን ብለዋል።
በመሆኑም ብልፅግና ፓርቲ በኢትዮጵያ ቀደም ሲል የነበሩ ኋላ ቀር አሰራርና ልምምዶችን በማፍረስ በአዲስ እሳቤ የለውጥ ስራዎችን አስቀጥሏል ብለዋል።
የደረጀ ሃሳብ የሌለው የፖለቲካ ፓርቲ የፈለገውን በማፍረስ ለውጥ መፍጠር ቢችልም ለውጥ መምራት ካልቻለ ግን የሚያልመውን ለመትከል ይቸገራል ነው ያሉት።