በአፍሪካ የአንድነት መሰረት እንዲጸና ልማትና ብልጽግና እንዲረጋገጥ በማድረግ ኢትዮጵያ የላቀ ሚናዋን እየተወጣች ነው - የደቡብ አፍሪካው ናሽናል ኮንግረንስ ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባል ኑዶሎ ኪቤት

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፡- በአፍሪካ የአንድነት መሰረት እንዲጸና ልማትና ብልጽግና እንዲረጋገጥ በማድረግ ኢትዮጵያ የላቀ ሚናዋን እየተወጣች ነው ሲሉ የደቡብ አፍሪካው ናሽናል ኮንግረንስ ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባል ኑዶሎ ኪቤት ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው ላይ የተለያዩ ሀገራት አህት ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች የታደሙ ሲሆን በመድረኩም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የደቡብ አፍሪካው ናሽናል ኮንግረንስ ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባል ኑዶሎ ኪቤት፤ በመልዕክታቸው በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግና እውን እንዲሆን በመስራት ላይ ላሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና አመራራቸው አድናቆታቸውን ገልጸዋል።


 

በአፍሪካ የአንድነት መሰረት እንዲጸና ልማትና ብልጽግና እንዲረጋገጥ የኢትዮጵያ ሚና የላቀ መሆኑን አስታውሰው አሁንም አጠናክራ መቀጠሏን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት ምሳሌ ብቻ ሳትሆን የአንድነትና የጥንካሬ መሰረት መሆኗንም አስታውሰዋል።

በመሆኑም የደቡብ አፍሪካ ናሽናል ኮንግረንስ ፓርቲ ለሀገራዊና አህጉራዊ ልማት መሳካት ከብልጽግና ፓርቲ ጋር በቅርበት የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካ የልማት አጀንዳዎች እንዲሳኩ አህጉራዊ ሰላም፣ የዳበረ ዴሞክራሲና ልማት እንዲረጋገጥ የጋራ ጥረታችን ይቀጥላል ሲሉም አረጋግጠዋል።

የአፍሪካ ነፃነት የሚረጋገጠው የዜጎቿ ሰላምና ነፃነት እውን ሲሆን ነው ያሉት ኑዶሎ ኪቤት፤ ለዚህ ስኬት ሀገራት ይበልጥ ተባብረውና ተቀራርበው መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም