የናይጄሪያው ኤፒሲ ፓርቲ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የናይጄሪያው ኤፒሲ ፓርቲ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፡- የናይጄሪያ ኤፒሲ ፓርቲ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ።
"ከቃል እስከ ባህል" በሚል መሪ ሃሳብ ከዛሬ ጥር 23 እስከ ጥር 25/2017 ዓ.ም ድረስ የሚቆየው የብልጽግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በድምቀት መካሄድ ጀምሯል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የናይጄሪያው ኤፒሲ ፓርቲ ምክትል ሊቀ-መንበር አልሀጅ አሊቡካር ዳሎሪ ፓርቲያቸውን በመወከል መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም ኢትዮጵያና ናይጄሪያ በርካታ ዓመታት የዘለቀ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ይህም ግንኙነት በመከባበርና በጋራ እሴት ላይ የጸና መሆኑን ተናግረዋል።
ሁለቱ ሀገራት የጋራ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው ይህም አጋርነት በተለያዩ የትብብር መስኮች የተመሰረተ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአብነትም በዲፕሎማሲ፣ በንግድና በባህል ልውውጥ ያላቸውን አጋርነት አንስተዋል።
በተመሳሳይ የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን ኤፒሲና ብልጽግና ፓርቲ የጋራ ግብ ያላቸው ፓርቲዎች ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።
ሁለቱም ፓርቲዎች ልማትን ለማረጋገጥና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እንዲሁም የበለጸገች ሀገር ለመፍጠር እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ምንም እንኳን እንደ ሀገር የተለያዩ ፈተናዎች ቢያጋጥሙን መፍትሄው ትብብር ነው ሲሉም አክለዋል።
በመሆኑም ፓርቲያቸው ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ዛሬ የሚያካሂደው ጉባኤ ልማትና አንድነትን ለማምጣት ያለንን ቁርጠኝነት በጋራ የምናወድስበት ነው ሲሉም ጠቁመዋል።