ብልጽግና ፓርቲ ቃል የገባቸውን ተግባራት የፈጸመበት መንገድ እጅግ የሚደነቅ እና ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው - የደቡብ ሱዳን ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ ዋና ጸሀፊ ፒተር ላም

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፡- ብልጽግና ፓርቲ በመጀመሪያው ጉባኤ ቃል የገባቸውን ተግባራት የፈጸመበት መንገድ እጅግ የሚደነቅ እና ተሞክሮ የሚወሰድበት መሆኑን የደቡብ ሱዳን ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ ዋና ጸሀፊ ፒተር ላም ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲ እህት ፓርቲ የሆነው የደቡብ ሱዳን ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ ዋና ጸሀፊ ፒተር ላም የአጋርነትና የመልካም ምኞት መግለጫቸውን አቅርበዋል።

ብልጽግና ፓርቲ በመጀመሪያው ጉባኤ ቃል የገባቸውን ተግባራት የፈጸመበት መንገድ እጅግ የሚደነቅ እና ተሞክሮ የሚወሰድበት መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ተሞክሮ የበርካታ አፍሪካ ሀገራት ገዥ ፓርቲዎች ለህዝባቸው ቃል የገቡትን ለመፈጸም ተሞክሮ የሚወስዱበት መሆኑንም ገልጸዋል።

ብልጽግና ፓርቲ እድገትን በማረጋገጥና ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በመገንብት ያከናወናቸው ተግባራት ኢትዮጵያ በከፍተኛ የልማት መንገድ ላይ መሆኗን የሚያመላክቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይህም በፖለቲካና በኢኮኖሚ መስኮች የተመዘገበው ስኬት የሚደነቅ እንደሆነ የሚያመላክት ነው ብለዋል።


 

ዋና ጸሀፊው በአዲስ አበባ የተገነባው የኮሪደር ልማት ስራ እጅግ አስደማሚ እና የከተማዋን ገጽታ ውብ ያደረገ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።

በተጨማሪም የተያዘን ግልጽ ራእይ ወደ ተግባር መቀየር ደግሞ የበለጠ አስፈላጊ መሆኑን ትምህርት የሚወሰድበት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ነጻነት ጊዜ ጀምሮ ከጎኗ ያልተለየች ወዳጅ ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፤ የሀገሪቱ መሪዎች ድጋፍም ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።

የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት ተጠናክሮ መቀጠሉን ያነሱት ሃላፊው፤ ደቡብ ሱዳን ባለፈው አመት የናይል ቤዚን ትብብር ማእቀፍን ማጽደቋ ሌላው የሀገራቱ ወዳጅነት ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል።

በትምህርት ዘርፍ ያለውን ወዳጅነት ለማጠናከርም ከስድስት መቶ በላይ የደቡብ ሱዳን ተማሪዎች በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት እድል ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም