የኢትዮጵያና የሩስያ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን አጋርነት ተጠናክሮ ይቀጥላል- የዩናይትድ ሩሲያ ፓርቲ

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያና የሩስያ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን አጋርነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የዩናይትድ ሩሲያ ፓርቲ ገለጸ።

"ከቃል እስከ ባህል" ከዛሬ ጥር 23 እስከ ጥር 25/2017 ዓ.ም ድረስ የሚቆየው የብልጽግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የዩናይትድ ሩስያ ፓርቲ ሱፕሪም ካውንስል ቢሮ አባልና የሩስያ ፌዴሬሽን ሴናተር አንድሬ ክሊሞቭ ፓርቲውን ወክለው መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም፤ ለብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጉባዔው ለኢትዮጵያ ቀጣይ እድገት አሻጋሪ እንደሚሆንና ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ቦታ እንደሚያስቀጥል ባለሙሉ ተስፋ ነኝ ብለዋል።

ኢትዮጰያና ሩስያ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ታሪካዊና በበርካታ መስኮች ላይ የተመሰረተ አጋርነት እንዳላቸው ጠቁመዋል።

ይህንንም አጋርነት በሁለትዮሽና ባበለብዙ ወገን በተለይም ብሪክስንና የአፍሪካ ሩስያ አጋርነት መድረክን በመጠቀም ለማጠናከር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ገዢው የዩናይትድ ሩሲያ ፓርቲ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ያለው ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር እንሰራለንም ብለዋል።

ብልጽግና ፓርቲ በቀጣይ ተጨማሪ ስኬትን እንዲጎናጸፍ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም