በአፍሪካን ሰላምና ብልጽግናን ዕውን ለማድረግ የሀገራትን ተቀራርቦ መስራት ይሻል- የታንዛኒያ እና ሩዋንዳ እህት ፓርቲዎች

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፦ አፍሪካን ከውስብስብ ችግሮቿ በማላቀቅ ወደ ተሟላ ሰላምና ብልጽግና ለማሻገር የሀገራት ይበልጥ ተቀራርቦና ተባብሮ መስራትን እንደሚሻ የታንዛኒያ እና ሩዋንዳ እህት ፓርቲዎች ገለጹ።

የሁለቱ ሀገራት የፓርቲ ተወካዮች ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ያላቸውን የፓርቲ ለፓርቲ አጋርነትና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚሰሩም አረጋገጠዋል።

የብልጽግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው ላይ የተለያዩ አገራት አህት ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች የታደሙ ሲሆን በመድረኩም መልእክት አስተላልፈዋል።

የታንዛኒያው ቻማ ቻማ ፑንዱዚ ፓርቲ ዋና ጸሀፊ ኢማኑኤል ቺምቢ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሳል የአመራርነት ጥበብ ኢትዮጵያ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች ትገኛለች ብለዋል።

የታንዛንያ ፕሬዝዳንት ሳምያ ሱሉህ ሀሳን፤ የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ ስኬታማ እንዲሆን የመልካም ምኞት መግለጫቸውን መላካቸውን አንስተው ሁለቱ አገራት ለጋራ ልማትና ብልጽግና ትብብራቸውን አጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ገልጸዋል።

የሀገራቱ የረጅም ጊዜ ግንኙነት በፓርቲ ለፓርቲ ትብብርም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

ዓለማችን በአየር ንብረት ለውጥ፣ በግጭት፣ በድርቅና በምግብ እጥረት እየተፈተነች ነው ያሉት ዋና ጸሀፊው፤ አፍሪካን ከእነዚህ ችግሮች ለማውጣት አህጉራዊ ትብብርን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ የተጀመሩ ሁለንተናዊ የልማት ስራዎችና የተመዘገቡ ውጤቶች የሚደነቁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ዌላርስ ጋሳማጌራን፤ በበኩላቸው የሩዋንዳ ፕረዚዳንት ፖልካጋሜ የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ ስኬታማ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል ብለዋል።

ከሁቱ አገራት ጠንካራ ግንኙነት ባለፈ በፓርቲ እና ለፓርቲ መካከል የትብብር ግንኙነቱ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የሁለቱ እህት ፓርቲዎች መካከል ያለው አጋርነትም የፖለቲካ መስተጋብራቸውን እንዲያጎለብቱ ትልቅ ሚና የሚጫወት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

አፍሪካን ከውስብስብ ችግሮች በማላቀቅ ሰላምና ብልጽግናዋን ዕውን ለማድረግ አገራት ይበልጥ ተባብረውና ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸውም አንስተዋል።

በሩዋንዳ እና በኢትዮጵያ መካከል የሁለትዮሽ የትብብር ግንኙነቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም