የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳቦች የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን ብልፅግና ለማረጋገጥ ይበጃሉ- የተርኪዬ ኤኬ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር - ኢዜአ አማርኛ
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳቦች የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን ብልፅግና ለማረጋገጥ ይበጃሉ- የተርኪዬ ኤኬ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በብልፅግና ፓርቲ ጉባዔ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ያነሷቸው ሃሳቦች ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ቀጣናውና የአፍሪካን ብልፅግናን ዕውን ማድረግ የሚያስችሉ ናቸው ሲሉ የተርኪዬ ኤኬ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ዛፈር ሲራካያ አደነቁ።
የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ "ከቃል እስከ ባህል" በሚል መሪ ቃል ከተለያዩ ሀገራት የመጡ እህት ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ተጀምሯል፡፡
የተርኪዬ ኤኬ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ዛፈር ሲራካያ በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን(ዶ/ር) ጠንካራና ሁሉን አቀፍ ቁም ነገር አዘል መልዕክት አድንቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው የጠቀሷቸው ሃሳቦች መተግበር ከተቻለ ወደፊት የበለጸገች ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የበለጸገ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ብሎም የበለጸገች አፍሪካን ዕውን ማድረግ እንደሚቻል እርግጠኛ ነኝ ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃላቸውን ወደ በገቢር እንደሚለውጡ ተስፋቸውን ገልጸው፤ በብልጽግና ጉባዔ ውሳኔዎችም ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካና ለዓለም ሰላምና ልማት የሚበጁ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ እምነታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከዓለማችን ጥንታዊ ስልጣኔዎች አንዷ እንደመሆኗ በአፍሪካ የታሪክ ገጾች ውስጥ ጉልህ ታሪክ የጻፈች እንዲሁም በባህል፣ በታሪክ፣ በብዝሃነት፣ በእምነት፣ በቋንቋና ቅርስ የበለጸገችና በፈተናዎች ሳትበገር ዘመናትን የተሻገርች ምድር ናት ብለዋል።
ከኢትዮጵያ አስደናቂ ታሪኮች መካከል ለዘመናት ሉዓላዊነቷን አስከብሯ መኖሯ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ክፍለ ዓለማት የነጻናት ታጋዮች ፋና ወጊነቷ እንደሆነ ጠቅሰዋል።።
ተርኪዬና ኢትዮጵያ የነጻነት እና ሉዓላዊነት የአይበገሬነት መንፈስ እንደሚጋሩ ጠቅሰው፤ ሁለቱ ሀገራት በታሪክም ከመሰረቱ ጥብቅ ቁርኝነት እንዳላቸው አንስተዋል።
ረጁም ዘመናት ባስቆጠረው የሀገራቱ ወዳጅነት ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው በ1920ዎቹ መጀመሩን ገልጸው፤ ይህም ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት የርኪዬ የመጀመሪያውን ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮ ነበር ብለዋል።
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በንግድ፣ በባህል፣ በትምህርት እና በሌሎች መስኮች ያላቸው ትብብር በየዘመኑ እያበበና እየጎለበተ የመጣና መልከ ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶች ያስመዘገበ እንደሆነ ገልጸዋል።
ኤኬ ፓርቲ ኢትዮጵያ እንደ የፍሪካ ህብረት መገኛነቷም ልዩ ትኩረት እንደሚሰጣት እና የሁለትዮሽ የልማት ትብብርና የጋራ ተጠቃሚነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አበክሮ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካዊ መፍትሄ በሚለው መርህ መሰረት በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ተርኪዬ ያላትን ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ጠቁመው፤ ተርኪዬ ለቀጣናው ሰላምና ልማት መረጋገጥ ትብብሯን ምንጊዜም ትቀጥላለች ብለዋል።