ለፓን አፍሪካዊነት ማበብ ወሳኝ ሚና የነበራቸው ኢትዮጵያና ሞሮኮ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ አጋርነታቸው እየጎለበተ መጥቷል- ፕሮፌሰር መሀመድ ሳዲኪ

አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2017(ኢዜአ)፦ ለፓን አፍሪካዊነት መጎልበት ወሳኝ ሚና የነበራቸው ኢትዮጵያና ሞሮኮ በጋራ ተጠቃሚነትና መሻት ላይ የተመሰረተ አጋርነታቸው እየጎለበተ መምጣቱን የሞሮኮው ናሽናል ራሊ ኦፍ ኢንዲፔንደንትስ(አር ኤን አይ) ፓርቲ ተወካይ ፕሮፌሰር መሀመድ ሳዲኪ ገለጹ።

ትናንት ማምሻውን በተደረገው የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ መክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ የፓርቲያቸውን መልዕክት ያስተላለፉት ፕሮፌሰር መሀመድ ሳዲኪ ኢትዮጵያ በብልጽግና ፓርቲ መሪነት የጀመረችውን አስደናቂ የልማት ጉዞ እንዲሁም በሀገራዊም ሆነ በአፍሪካ አቀፍ አንድነትና ሰላም ላይ ያላትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።


 

ኢትዮጵያና ሞሮኮ የጥንታዊ ታሪክ ባለቤቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ሁለቱ ሀገራት ከ1960ዎቹ ጀምሮ የፓን አፍሪካዊነት እሳቤ እንዲያብብ ወሳኝና ንቁ ተሳትፎ ነበራቸው ብለዋል።

የኢትዮ-ሞሮኮ ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት፣ የመበልጸግ ርዕይ እና ረጂም ዘመን ያስቆጠረ ታሪካዊ አጋርነት ላይ የተመሰረተ ትብብር ስለመሆኑ ጠቅሰው፤ ሁለቱ አገራት በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የጋራ ፍላጎት እንዳላቸው አንስተዋል።

ከቅርብ ዓመታት ውስጥ የሞሮኮው ንጉስ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት የኢትዮ-ሞሮኮ ፖለቲካዊ ወዳጅነት ወደላቀ ደረጃ እንዲሸጋገርና ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸው እንዲጎለብት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ አጋጣሚ ነበር ብለዋል።

በዚህም ሁለቱ ሀገራት በተለይም በግብርናው ዘርፍ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሁሉን አቀፍ የትብብር መስኮች ላይ እየሰሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የሁለቱ አገራት አጋርነትና ትብብር በደቡብ-ደቡብ ማዕቀፍ የጋራ ፈተናዎችን ለመከላከል እንዲሁም ለማህበረሰቡ የተሻለ አህጉራዊ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና አካታች የአስተዳደር ስርዓት እንዲሰፍን ያግዛል ብለዋል።

የሁለቱ አገራት የግል ዘርፍ ተዋንያን በኢኮኖሚው መስክ እመርታ የሚጫወቱት ወሳኝ ሚናም አንስተዋል።

አፍሪካ መልከ ብዙ ዕምቅ ጸጋ ቢኖራትም በነባራዊ ዐውድ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የምግብ ዋስትና፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ስራ አጥነትና መሰል ትኩረት የሚሹ ፈተናዎችን እንዳሉባት አንስተዋል።

የጋራ ፈተናዎችን ለማሸነፍ ደግሞ የጋራ አቅሞቻችንን በማቀናጀት በትብብር መስራት ግድ ይለናል ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ጊዜው አፍሪካን የፈተና ሳይሆን የዕድል ቤት ለማድረግ የምንሰራበት ነው ብለዋል።


 

ኢትዮጵያና ሞሮኮ ከኢኮኖሚያዊ ትብብር ባሻገር ፖለቲካዊ ትብብር ለማጠናከር ያላቸውን መሻት ገልፀው፤ የሁለቱ ሀገራት ገዥ ፓርቲዎች ለፖለቲካዊ ትብብሮች መጠናከር ቁልፍ የመሪነት ሚና እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።

በዚህም ፓርቲያቸው የሁለቱ ሀገራት ሁሉን አቀፍ ትብብር ይበልጥ ወደላቀ ደረጃ እንዲሻጋገር ከብልጽግና ፓርቲ ጋር በቀጣይነት ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም