ብልፅግና ፓርቲ ከጉባኤ እስከ ጉባኤ ያስመዘገባቸውን አመርቂ ውጤቶች ዘላቂነት የሚያረጋግጡ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል- የጉባዔው ተሳታፊዎች

አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2017(ኢዜአ)፦ ብልፅግና ፓርቲ ከጉባዔ እስከ ጉባዔ ያስመዘገባቸውን አመርቂ ውጤቶች ዘላቂነት የሚያረጋግጡ አቅጣጫዎችንና ውሳኔዎችን እንደሚያስቀምጥ የጉባዔው ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡

ብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤውን " ከቃል እስከ ባህል " በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ የአድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው።

ብልጽግና ሀገር በቀል እሳቤ ነድፎ የመጣ የመጀመሪያው ፓርቲ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት እና የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ ከጉባኤ እስከ ጉባኤ በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች እንዲሁም በዲፕሎማሲው ዘርፍ የሀገርን ቀጣይነት የሚያረጋግጡ ተጨባጭ ውጤቶችን አስመዝገቧል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛው መደበኛ ጉባኤ ትናንትን፣ ዛሬን እና ነገን የሚያስተሳስሩ ቀጣይ አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት ስለመሆኑም በጉባኤ መክፈቻ ላይ ተጠቁሟል፡፡

የጉባኤው ተሳታፊዎች በመክፈቻ መርሐ ግብር ላይ በሰጡት አስተያየት፤ ብልጽግና ፓርቲ ከጉባኤ እስከ ጉባኤ ያስመዘገባቸውን አመርቂ ውጤቶች ዘላቂነት የሚያረጋግጡ አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኃላፊ ሲሳይ ዳምጤ በሰጡት አስተያየት ፓርቲው ባለፉት ዓመታት በሁሉም መስኮች አንጸባራቂ የሚባሉ ድሎችን ማስመዝገቡን ተናግረዋል፡፡

በህዝቡ የተጠየቁ ጥያቄዎችን በመመለስ ላይ ያለ ፓርቲ መሆኑን ጠቁመው የኢትዮጵያን ብልጽግና በጠንካራ መሰረት ላይ ለማነጽ እየተጋ ያለ ፓርቲ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን የቦረዳ ወረዳ አስተዳዳሪና የጉባኤው ተሳታፊ አሸናፊ ሻሌ በበኩላቸው ብልጽግና ሰላምን፣ ልማትን እና የህዝቦችን ህብረ ብሄራዊ አንድነት ከማረጋገጥ አኳያ አመርቂ ስራዎችን መስራቱን ገልጸዋል፡፡


 

በኢትዮጵያ አስደማሚ ለውጦች እንዲመዘገቡ በማስቻልም የህዝብን ተጠቃሚነት በተግባር በማረጋገጥ ላይ ያለ ፓርቲ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በሁለተኛ መደበኛ ጉባኤው የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚስቀጥሉ ውሳኔዎች እንደሚጠበቁም  ተናግረዋል፡፡

እንደሀገር የተጀመሩ ለውጦችን ዘላቂነት ማስቀጠል የሚችሉ በሳል ውሳኔዎች እንደሚጠበቁም ጠቁመዋል፡፡

አቶ አሸናፊ ሻሌ በበኩላቸው በሁሉም መስኮች የተመዘገቡ ስኬቶች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ፓርቲው አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥ ተናግረዋል፡፡
 

ኢትዮጵያ በጀመረችው የልማት መንገድ የህዝቦቿን ተጠቃሚነት ይበልጥ ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውሳኔዎች እንደሚጠበቁ ጠቅሰው ለተፈጻሚነቱም እንደሚተጉ ገልጸዋል፡፡

ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የመጡት የጉባኤው ተሳታፊ አስራት መኩሪያ እንዳሉት ብልጽግና የፖለቲካ አካታችነትን በተግባር ያረጋገጠ ፓርቲ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

በኢትዮጵያ የብሔራዊነት ትርክት እንዲጸና ብሎም ወንድማማችነትና እህትማማችነት እንዲጠናከር አልሞ የጀመራቸው ስራዎች ውጤት ማስመዝገብ መጀመራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ከምዕራብ ሀረርጌ ዞን በዴሳ ከተማ በጉባኤው በመክፈቻው መርሐ ግብር ላይ የተገኙት ፋጡማ ጠሃ አህመዶ በበኩላቸው ብልጽግና ቃል በተግባር ያሳየ ፓርቲ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም