የሰላም መሰረት፣ የብልፅግና ተምሳሌት የሆነች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማውረስ ተግተን እንሰራለን- የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2017(ኢዜአ)፦ የሰላም መሰረት፣ የብልፅግና ተምሳሌት የሆነች ያበበች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማውረስ ተግተን እንሰራለን ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተናገሩ።

ሀገር ለማበልጸግ በዘመቻ የተጀመሩ ንቅናቄዎች ባህል ሆነው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የብልፅግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባዔ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የፓርቲው ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ገቢራዊ የተደረጉ አዳዲስ እሳቤዎችና ኢኒሸቲቮች ከዘመቻ ያለፈ ባህል የመፍጠር ልምምድና ክንውን ይፈልጋሉ ብለዋል።

ለአብነትም የጽዱ ኢትዮጵያን ንቅናቄ፣ ምርታማነት የመጨመር እና ፕሮጀክቶችን በፍጥነት የመጨረስ አዳዲስ ልምምዶች በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ባህል፣ ትዕምርትና እሴት ሆነው መከወን እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

ባህል ማድረግ አለብን ካሏቸው ጉዳዮች መካከልም ማወቅ፣ ማላቅ፣ መፍጠር፣ መፍጠን፣ ማስተሳሰር ጽንሰ ሃሳቦችን አብራርተዋል።


 

ብልፅግና ጊዜ የለኝም በሚል ስሜት የሚሰራ፣ በውጤት የሚያምን እንዲሁም ጀምሮ መጨርስን፣ ተናግሮ መፈጸምን ባህል አደርጎ እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የፓርቲው ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባዔ የማንሰራራት ዘመን የሚበሰርበት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በመጀመሪያው ጉባዔ የተገቡ ቃሎች ተፈጽመው ሪባን የምንቆርጥበት ዘመን ነው ሲሉ አመላክተዋል።

በዚህም በቀጣይ ወራት ለኢትዮጵያ ህዝብ ብስራት እናበስራለን ብለዋል።

በዚህ ዓመት የታየው የኮሪደር ልማት በሚቀጥለው ዓመት አታዩትም፤ በዚህ ዓመት ያያችሁት ፕሮጀክት በሚቀጥለው ዓመት ጨርሰን አስውበን አሳምረን አልቀን በአዲስ መልክ ታዩታላችሁ እንጂ የዘንድሮውን በሚቀጥለው ዓመት አንደግመውም ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ አዲስ የስራ ባህል መፍጠር፣ አሰራርና የተሻለ አመራር የመምረጥ የጋራ ውሳኔ ከጉባዔው ይጠበቃል ብለዋል።


 

ብልጽግና ከ15 ሚሊየን በላይ አባላት በመያዝ በአፍሪካ ግዙፉ ፓርቲ መሆኑን ገልጸው፤ ከቁጥር በዘለለ ግን አባላቱ እንደ ሻማ ቀልጠን ለትውልድ ዕዳ ሳይሆን ምንዳና ብልፅግና ለማውረስ መሰረት መጣል አለብን ብለዋል።

አዲሱ ትውልድ ልማትና ብልጽግና እንደሚሻ በማሰብ ለፍሬ መትጋት እንደሚገባ አንስተዋል።

የብልጽግና አጀንዳ ሰላምና አንድነት በመሆኑ ለሰላም፣ ለአንድነትና ለልማት እጁ የተዘረጋ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከግጭት ይልቅ መነጋገርና መሰልጠንን ማስቅደም እንደሚገባ አስገንዘበዋል።

ብልፅግና ባለፉት ዓመታት ብዙ ፈተናዎች ቢገጥሙትም ይህን ተሻግሮ ማሸነፍ የሚችል አቅም መፍጠሩን ገልጸው፤ የኢትዮጵያን ልማትና ሰላም እናረጋግጣለን ብለዋል።

በአጠቃላይ የሰላም መሰረት፣ የብልጽግና ተምሳሌት የሆነች፣ ያበበች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማውረስ ብልፅግና ተግቶ ይሰራልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም