በሐረሪ ክልል የተከናወነው የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት የቱሪስት ፍሰት እንዲጨመር አስችሏል- አቶ ተወለዳ አብዶሽ - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል የተከናወነው የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት የቱሪስት ፍሰት እንዲጨመር አስችሏል- አቶ ተወለዳ አብዶሽ
አዲስ አበባ ፤ ጥር 24/2017(ኢዜአ):- በሐረሪ ክልል የተከናወነው የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት የቱሪስት ፍሰት እንዲጨመር ማስቻሉን የክልሉ ባህል ቅርስ እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ ገለጹ።
ኃላፊው በሰጡት መግለጫ ከለወጡ ወዲህ በክልሉ የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት ከጁገል ዓለም አቀፉ ቅርስ መልሶ ልማት ጀምሮ የጅብ ትርዒት ማሳያ ፓርክ ግንባታዎች በዋናነት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ የተከናወኑ የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት እና እድሳት ኢንሼቲቮች የመዳረሻዎችን ህልውና ከማስጠበቅ ባለፈ የቱሪስት ፍሰቱን እንዲጨምር ያስቻሉ መሆናቸውን አመልክተዋል።
የውጪና የሃገር ውስጥ ጎብኚዎች በክልሉ መበራከታቸውንን ለአብነት አንስተዋል።
በተያዘው አመት ብቻ 4 ሺህ 991 የውጭ አገር ጎብኚዎች ወደ ክልሉ መምጣታቸውን የገለፁት አቶ ተወለዳ የቱሪስት ፍሰቱ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ37 በመቶ እድገት ማሳየቱን ጠቁመዋል።
92 ሺ 581 የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን መጎብኘታቸውንም ተናግረዋል።
በኮሪደር ልማት የተፈጠሩ ምቹ የእግረኛ መንገዶች እና የአረንጓዴ ልማቶች ለቱሪስት ፍሰቱ ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል ነው ያሉት።
በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ይበልጥ በማጎልበት የቱሪስተ ፍሰት እና ቆይታን ለማሳደግ የቱሪዝም ዘርፉ የሚፈልገውን የመሠረተ ልማቶች እና የሆቴል ቱሪዝም የማጠናከር ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በሌላ በኩል በቅርቡ ተመርቆ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የኢኮ ፓርክን በሙሉ አቅሙ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ሐረር የምትታወቅባቸውን የአብሮነት እሴቶችን ጠብቆ ለማቆየት የተለያዩ ህዝባዊ በዓላትና ሁነቶችን ወንድማማችነትን ይበልጥ አጉልቶ በሚያሳይ መልኩ መከበራቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።