አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ ለተጫዋቾች ጥሪ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ ለተጫዋቾች ጥሪ አደረጉ
አዲስ አበባ ፤ጥር 23/2017(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ ለ16ኛ የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅት ለ29 ተጫዋቾች ዛሬ ጥሪ አድርገዋል።
ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ከነገ ጀምሮ ልምምድ ማድረግ እንደሚጀምሩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።
ሉሲዎቹ ከዩጋንዳ ጋር የካቲት 14 እና የካቲት 19 ቀን 2017 ዓ.ም የደርሶ መልስ ጨዋታ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከዩጋንዳ ጋር ለሚያደርገው የማጣሪያ ዝግጅት እንዲረዳ ከጅቡቲ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጋር የካቲት 5 እና የካቲት 9 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የአቋም መለኪያ ጨዋታ እንደሚያካሂድ ታውቋል።
በሞሮኮ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው 16ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ መርሃ ግብሩ በሁለት ዙር እንደሚከናወን እና 38 ሀገራት እንደሚሳተፉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ዩጋንዳን በደርሶ መልስ ካሸነፈች በሁለተኛው ዙር ከታንዛንያ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ አሸናፊ ጋር ትጫወታለች።
11 ሀገራት ከአዘጋጇ ሞሮኮ ውጪ በአህጉራዊው መድረክ ለመሳተፍ ይፋለማሉ።
በአፍሪካ ዋንጫ ላይ 12 ሀገራት ይሳተፋሉ።