ብልጽግና ፓርቲ ሰላምና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል -የጉባዔው ተሳታፊዎች

አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2017(ኢዜአ)፦ ብልጽግና ፓርቲ በሁለተኛ መደበኛ ጉባኤው የኢትዮጵያን ሰላምና ልማት የሚያረጋግጡና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ የሚያስችሉ ውሳኔዎች እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል ሲሉ የጉባዔው ተሳታፊዎች ገለጹ።

ብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤውን "ከቃል እስከ ባህል" በሚል መሪ ሀሳብ በአድዋ ድል መታሰቢያ ከትናንት ጀምሮ እያካሄደ ይገኛል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ በመጀመሪያው ጉባኤ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተግባራትን ማከናወን መቻሉን በፓርቲው ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ መክፈቻ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

የጉባኤው ተሳታፊ የሆኑት መሰረት መስቀሌ በሰጡት አስተያየት ብልጽግና ፓርቲ በመጀመሪያ ጉባኤው ለህዝብ የገባውን ቃል ወደ ተግባር ቀይሮ ማሳየቱን ተናግረዋል።

ፓርቲው የህዝቦችን ህብረ ብሄራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ እና የኢትዮጵያን ተደማጭነት ያጎለበቱ በርካታ የዲፕሎማሲ ስራዎችን በማከናወን ውጤት ማስመዝገቡን አንስተዋል።

በልማት ስራዎች በተለይም በግብርናው ዘርፍ በተከናው አስደማሚ ተግባራት በሀገሪቱ ተከታታይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቅሰዋል።

በትምህርት ጥራት ማስጠበቅና በጤና አገልግሎት አሰጣጥ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተግባራት መከናወናቸውን ለአብነት አንስተዋል።

ሌላው የጉባዔው ተሳታፊ አቶ ንጉሴ ገመዳ በበኩላቸው ከፓርቲው የመጀመሪያ ጉባኤ በኋላ የአድዋ ድል መታሰቢያን ጨምሮ በርካታ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም በኮሪደር ልማት በአዲስ አበባ ከተማና በክልል ከተሞች እየተከናወነ ያለው ስራ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ገጽታ ከፍ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተግባሩ ከተሞችን ለኑሮና ለስራ ምቹ እያደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ተሳታፊዎቹ በፓርቲው ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ በኢትዮጵያ የተጀመሩ የልማት ስራዎች በፍጥነት ተጠናቀው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ የሚያስችሉ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ብለው እንደሚጠብቁም ገልጸዋል።

ብልጽግና ፓርቲው በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ የሰላምና ልማት ግንባታ ስራዎች የበለጠ ተጠናክረው የሚቀጥሉበትን ውሳኔ እንደሚያሳልፍም እንዲሁ።

ከጎረቤት ብሎም ከአለም ሀገራት ጋር ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የበለጠ የሚጠናከርበትና በኢኮኖሚ የበለጸገች አገር መገንባት የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ብለው እንደሚጠብቁም አንስተዋል።

ትናንት የተጀመረው የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ እስከ ነገ እንደሚቀጥል መገለጹ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም