በግማሽ ዓመቱ ከ12 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል - የክልሉ ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን

ዲላ፤ ጥር 24/2017 (ኢዜአ):- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በግማሽ ዓመቱ ከ12 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን የክልሉ ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ የግማሽ አመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በዲላ ከተማ አካሂዷል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሪክተር አቶ አማኑኤል ብሩ በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ በግማሽ ዓመት ከ12 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል።

በክልሉ ከ134 ሺህ ቶን በላይ እሸት ቡና ተሰብስቦ የደረቅ ቡና ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው በምርት ዘመኑ ተሰብስቦ የተከማቸ ቡናን በቀጣይ ሶስት ወራት አሟጦ ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ህገወጥ የቡና ዝውውርን ከመቆጣጠር በተጓዳኝ አቅራቢዎች ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ እንዲያቀርቡ በየደረጃው ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አንሰተዋል።

በዞኑ በግማሽ አመት ከ10 ሺህ ቶን በላይ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን ያነሱት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ቡናና ቅመማ ቅመም ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኤርሚያስ ቼካ ናቸው።

በምርት ዘመኑም ከ200 በላይ ቡና አምራቾች ከ17 ሺህ ቶን በላይ የታጠበ ቡና ማዘጋጀት መቻላቸውን ጠቅሰው ይህንንም በቀጣይ ወራት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ይህም በበጀት ዓመቱ ከ28 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም