አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ በክልሉ በግብርናው ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎችን ያጠናክራል - አቶ ጌታቸው ረዳ

መቀሌ፤ ጥር 24/2017(ኢዜአ)፦ አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ በክልሉ በግብርናው ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናከርና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማጎልበት እንደሚያግዝ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ገለጹ።

አዲሱን የግብርናና የገጠር ልማት ፖሊሲ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለድርሻ አካላት የማስተዋወቅ መርሀ ግብር ዛሬ በመቀሌ ከተማ ተካሂዷል።

በዚሁ ጊዜ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ፤ ፖሊሲው በክልሉ በግብርናው ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናከርና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ያግዛል ብለዋል።


 

ግብርናን ማዘመን ምርታማነትን ለማጎልበት የሚያግዙ ስራዎችን ማከናወንና ሜካናይዜሽን ላይ ማተኮር መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፖሊሲው የክልሉን እርሻ ለማጎልበት የሚደረገውን ጥረት ስለሚያጠናክር ለተግባራዊነቱ ባለድርሻ አካላት የተለየ ትኩረት ሊሰጡበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የፖሊሲ ምርምርና ጥናት መሪ ስራ አስፈፃሚ ተስፋዬ መንግስቴ(ዶ/ር) በበኩላቸው በግብርናው ዘርፍ ውጤታማ ለውጦችን ለማምጣት የግብርና ኮሜርሻላይዜሽንን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

በግብርና ዘርፍ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑንም አክለዋል።

በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የፖሊሲና የስርዓተ ምግብ ዳይሬክተር አቶ ረታ ዋጋሪ፤ ፖሊሲው ተግባራዊ በሚደረግበት ወቅት የባለድርሻ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።


 

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ብርሀነ ሀይለ የተባሉ የግብርና ባለሙያ፤ በግብርናው ዘርፍ እየታዩ ያሉት ዘርፈ ብዙ ለውጦችን ይበልጥ ለማጎልበት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማጎልበት ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

በግብርና ዘርፍ የምርምር ስራ ላይ የተሰማሩት አባዲ ግርማይ(ዶ/ር) ደግሞ፤ የግብርና ዘርፍ ለኢኮኖሚው እድገት ያለው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ የተለየ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክተዋል።

ፖሊሲው ለሀገሪቱ ዘላቂ ልማት ወሳኝ መሆኑን በመግለፅ ለተግባራዊነቱም የሁሉም አካላት ቅንጅታዊ ስራ አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የማህበራዊ ልማት ዘርፍ ሽግግር ሀላፊ ሴክሬታሪያት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም