የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ለብልጽግና ፓርቲ 2ኛ ጉባዔ የመልካም ምኞት መልዕክት ላከ - ኢዜአ አማርኛ
የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ለብልጽግና ፓርቲ 2ኛ ጉባዔ የመልካም ምኞት መልዕክት ላከ
አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2017(ኢዜአ)፦የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ለብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ የድጋፍና የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፏል፡፡
ኢትዮጵያ በብልጽግና ፓርቲ መሪነት እያስመዘገበችው ላለው ሁለንተናዊ እድገት የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ (CPC) ያለውን አድናቆት ገልጿል።
ቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጦ ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያ ተስማሚ የሆነ የእድገትና የዘመናዊነት መንገድ እንድትከተል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቅሷል፡፡
ለአብነትም በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ የዜጎችን ኑሮ በማሻሻል፣ በአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃን በማሳደግ፣ የሀገራዊ ምክክር ቅድመ-ዝግጅት በማገባደድና ማህበራዊ አንድነትን በማጎልበት ረገድ የተመዘገቡ ውጤቶች ጉልህ መሀኖቸውን ጠቅሷል።
እነዚህ ስኬቶች ኢትዮጵያን “የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት” እንድትሆን እያስቻሉ ነው ሲልም እውቅና ሰጥቷል፡፡
በቀጣይ ዓመታት ብልጽግና ፓርቲ ሀገሪቱን ወደ “አዲስና የላቀ ስኬት” መምራቱን እንደሚቀጥል ያለውን እምነት ገልጿል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል ላለው ጥልቅ ትብብር አጽንኦት በመስጠትም የሁለቱ ፓርቲዎች መሪዎች ከዚህ ቀደም የደረሱባቸውን ስምምነቶች ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝቧል፡፡
በቀጣይ የቻይናን እና የኢትዮጵያን ትብብር በሁሉም ዘርፎች በማስፋት በማንኛውም ሁኔታ የማይናወጥ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ሆኖ የበለጠ እንዲጠናከር ጥሪ አቅርቧል።
ሁለተኛው የብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ የኢትዮጵያን ቀጣይ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ የሚቀርፅበት ወሳኝ ሁነት እንደሆነ እና ለሀገራዊ ልማት ወሳኝ የሆኑ ቀጣይ ግቦችን እንደሚቀመጡ እምነት እንዳለው በመጥቀስ ለጉባኤው ስኬት መልካሙን ሁሉ ተመኝቷል፡፡