ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ እያስመዘገበች ያለው ውጤት ለአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚያደርጋት ነው- የቱሪዝም ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ እያስመዘገበች ያለው ውጤት ለአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚያደርጋት ነው- የቱሪዝም ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ እያስመዘገበች ያለው ውጤት ለአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚያደርጋት መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሀገሪቱን እድገት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንዲያስችሉ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሰሩ ካሉ ዘርፎች መካከል ቱሪዝም አንዱ ነው።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከለውጡ ወዲህ መንግስት ለቱሪዝም ልማት በተሰጠው ተኩረት በርካታ የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች ተገንብተዋል።
በአዲስ አበባ የተጀመረው ገበታ ለሸገር ፕሮጀክትን ጨምሮ የገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶችን ለአብነት አንስተዋል።
በተጨማሪም ነባር የቱሪስት መዳረሻዎችን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በፍጥነት በማደስ ለጎብኚዎች ክፍት የማድረግ ስራም በትኩረት መከናወኑን አስታውቀዋል።
በቱሪዝም ልማት ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት ኢትዮጵያን ለአፍሪካ ሀገራትም ጭምር ምሳሌ የሚያደርጋት መሆኑን አመልክተዋል።
ለዚህም የኢጋድ አባል ሀገራት የሚመሩበት የዘላቂ ቱሪዝም ማስተር ፕላን አዲሰ አበባ ላይ ይፋ መደረጉ ትልቅ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ዘርፉ የታለመለትን አገራዊ ስኬት የበለጠ እንዲያስመዘግብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሪፎርምና መሰል የማሻሻያ ስራዎችን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል፡፡
ላለፉት 15 ዓመታት ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የቱሪዝም ፖሊሲን የመከለስ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቅርቡም አዲሱ የቱሪዝም ፖሊሲ ይፋ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል።