በክልሉ ልማትን የሚያጠናክሩ መረጃዎች ተደራሽ በማድረግ የተመዘገቡ ውጤቶችን የሚያጎለብቱ ተግባራት ይቀጥላሉ

ቦንጋ፤ ጥር 24/2017(ኢዜአ)፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የወል በሆነ መልኩ ልማትና ዕድገትን የሚያጠናክሩ መረጃዎች ተደራሽ በማድረግ የተመዘገቡ ውጤቶችን የሚያጎለብቱ ተግባራት እንደሚቀጥሉ የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው የበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የተግባር አፈጻጸም ላይ የመከረ መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሄዷል።

በዚህ ወቅት የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ የሺዋስ ዓለሙ፣ ቢሮው የመረጃ ተደራሽነትን ለማስፋት የመገናኛ ብዙሃን እና የኮሙኒኬሽን መዋቅሩን በማስተባበር በርካታ ስራዎችን ማከናወኑን ተናግረዋል።

ለአብነት ክልሉ ያሉ የልማት አቅሞች በማስተዋወቅ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝምና በሌሎች ሀብቶች እንዲመጡና ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረጉን ጠቅሰዋል።

እንደአገር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመቻቹ የተለያዩ ኢንሼቲቮችን ለህዝብ ለማስተዋወቅና ሀሳቡን ለማስረፅ በተከናወነው ስራ ተስፋ ሰጪ ለውጥ መምጣቱንም ጠቁመዋል።



በተለይም የወል በሆነ መልኩ ዕድገትንና ልማትን የሚያጠናክሩ መረጃዎች ተደራሽ በማድረግ ረገድ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በመተባበር በተደረገው ጥረት የተመዘገቡ ውጤቶችን የሚያጎልበቱ ተግባራት እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

በቀጣይም በዋና ዋና የልማት አጀንዳዎች፣ ሰላምን በሚገነቡና የሕዝቦች ትስስርን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ በተቀናጀ መንገድ እንደሚሰራመ አቶ የሺዋስ አብራርተዋል።

በመድረኩ የተሳተፉ የመገናኛ ብዙሃንና የኮሙዩኒኬሽን አመራር አባላት በሰጡት አስተያየት፤ከለዉጡ ወዲህ መንግስት ያመቻቸውን የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት በመጠቀም በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።



በቀጣይም የአገሪቱ የልማትና ብልፅግና ጉዛ የተሳካ እንዲሆን ህብረተሰቡን በማንቃትና እውነታውን በማሳወቁ ረገድ የሚጠበቅባቸውን አንደሚወጡ ገልጸዋል።

ለአንድ ቀን በተካሄደው የምክክር መድረኩ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ተወካዮች፣ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የኮሙዩኒኬሽን ሥራ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም