አየር ኃይል አሁን ለገነባው ከፍተኛ ወታደራዊ የዝግጁነት አቅም የሙያተኛው ድርሻ የጎላ ነው - ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ

አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2017(ኢዜአ)፦አየር ኃይል አሁን ለገነባው ከፍተኛ ወታደራዊ የዝግጁነት አቅም የሙያተኛው ድርሻ የጎላ መሆኑን የአየር ሃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።

የኢፌዴሪ አየር ኃይል ሎጀስቲክስ የእውቅና እና የምስጋና መርሃ-ግብር በአየር ኃይል መኮንኖች ክበብ አካሂዷል።

ዋና አዛዡ በመርሃ-ግብሩ በመገኘት ለተቋሙ የግዳጅ አፈፃፀም ስኬት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ለነበራቸው ክፍሎች የእውቅና እና የምስጋና ሰርተፍኬት ሰጥተዋል።

ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የአየር ኃይል ሎጀስቲክስ የተቋሙን የማድረግ አቅም ወደ ላቀ ከፍታ ያሸጋገሩ በርካታ ተግባራት ማከናወኑን ጠቅሰው አየር ኃይሉ ለገነባው አሁናዊ ከፍተኛ የዝግጁነት አቅም የክፍሉ ሙያተኞች ድርሻ ከፍተኛ እንደነበረ ተናግረዋል ።

የአየር ኃይል ምክትል አዛዥ ለአየር ሎጀስቲክስ ብርጋዲየር ጄኔራል ነገራ ሌሊሳ በበኩላቸው ተቋሙ አዳዲስ የአቪዬሽን ትጥቆችን ከመታጠቅ ባለፈ ያሉትን ጠግኖ ወደ ግዳጅ በማሰማራት ረገድ ክፍሉ ያከናወነው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይነትም በሁሉም መስክ የጀመርናቸውን ስራዎች በላቀ የስራ ተነሳሽነት አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተሰጣቸውን ግዳጅ እና ተልዕኮ በብቃት ከመፈፀም ባለፈ ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎችን ለሰሩ ክፍሎች የእውቅና እና የምስጋና ሰርተፊኬት እንደተሰጣቸው ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም