የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ በዛሬ ውሎው በልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ ውሳኔዎችን አሳልፏል - ኢዜአ አማርኛ
የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ በዛሬ ውሎው በልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ ውሳኔዎችን አሳልፏል
አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2017(ኢዜአ)፦የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ በዛሬ ውሎው በልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ ውሳኔዎችን ማሳለፉን የፓርቲው የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ 2 ሺህ 100 ተሳታፊዎች በታደሙበት በደማቅ የመክፈቻ ስነ ስርዓት በትላንትናው ዕለት በይፋ ተጀምሯል።
በጉባኤው 1 ሺህ 700 የድምፅ ተሳታፊዎች እንዲሁም የ15 ሀገራት ፓርቲዎች አመራርና ተወካዮችን ጨምሮ 400 የሀገር ውስጥና የውጭ እንግዶች በተጋባዥነት መገኘታቸውም የሚታወቅ ነው።
የብልፅግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ጉባኤውን አስመልክቶ ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ ጉባኤው ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ተወካዮችን ባሳተፈና በዴሞክራሲያዊነት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለትም ጉባኤው መድረኩን የሚመሩ የፕሬዚዲየም አባላትን በመሰየም በልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ በስፋት መወያየቱንና አጀንዳዎችን መርምሮ ማጽደቁንም ተናግረዋል።
በዚህም የጉባኤው አዘጋጅ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት እና የስብሰባ ስነ-ስርዓት ደንብ ላይ በስፋት በመወያየት በሙሉ ድምፅ አጽድቋል ብለዋል።
በመቀጠልም የማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲሁም የኢንስፔክሽንና ስነምግባር ኮሚቴ ሪፖርቶች ለጉባኤው ቀርበው ሰፊ ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ መጽደቃቸውንም ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ጉባኤው በፓርቲው የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል ነው ያሉት።
ከአንደኛ ጉባኤ ማግስት በፓርቲው በተከናወኑ ተግባራት የተገኙ ውጤቶች፣ ያጋጠሙ ፈተናዎች እና ፈተናዎችን ለማለፍ የተሔደበትን ርቀት በስፋት መገምገሙንም አንስተዋል።
በዚህም የብልፅግና እሳቤ እስከ ታችኛው ህብረተሰብ ክፍል መድረሱ እና እሳቤው ባህል እየሆነ መምጣቱ የተረጋገጠበት ጉባኤ መሆኑን ገልጸዋል።
ጉባኤው በነገው ዕለትም ቀጥሎ የሚካሄድ ሲሆን የፓርቲ ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንቶችን ጨምሮ የአመራር ምርጫ ይደረጋል ብለዋል።
ለዚህም በዛሬው ዕለት አስመራጭ ኮሚቴ በመሰየም የዕለቱ ስብሰባ አሳታፊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መጠናቀቁን ተናግረዋል።
ጉባኤው ለመጪዎቹ ዓመታት የሚያገለግሉ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት እንደሆነም ጠቁመዋል።