ነጋሪ 25
ይጫኑ

1

ነጋሪ 6ኛ ዓመት ቁጥር 25 ሕዳር 2016 ዓ.ም ዋጋ 15 ብር



2

ማ ስ ታ ወ ቂ ያ



3



4

አድራሻ፦ አራዳ ክፍለ ከተማ

ስልክ ቁጥር +251-11-55-00-11 +251-11-56-39-31 +251-11-56-52-21

ፋክስ ቁጥር +251-11-55-16-09 enanegari@gmail.comበኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

በየሁለት ወሩ የምትታተም መጽሔት

ማውጫ

መስከረም 2009 ዓ.ም ተመሰረተች

የችግሮቻችን መፍቻው ቁልፍ

የሕልውናመሰረት 6

12

የቅድሚያ ቅድሚያ ለሕይወት አድን

መድኃኒቶች

18



5

ዋና አዘጋጅ ገዛኸኝ ዳንጉል

ም/ ዋና አዘጋጅ የሺመቤት ደመቀ

ከፍተኛ አዘጋጅ ፍቅርተ ባልቻ

አዘጋጅ መንገሻ ገ/ሚካኤል

አርት ዳይሬክተር ነብዩ መስፍን nebiyou1st@gmail.com

ፎቶግራፍ በኃይሉ አስፋው

እርምት ባለሙያ ትዝታ ሁሴን

መልዕክት

ነጋሪያችን የተለያዩ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ይዛ ቀርባለች። በዚህ ዕትሟ አገራት በብሔራዊና በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ያለማንም ጣልቃገብነት የራሳቸውን ፖሊሲ ቀርጸው እንደሚሰሩ በማተት ብሔራዊ ጥቅም ለአገር ግንባታ ያለውን ፋይዳ በስፋት ዳሳለች። አብሮነት ለኢትዮጵያዊያን የሕልውና መሰረት ስለሆነ ለእሴቱ መጠበቅና መጎልበት ከቤተሰብ ጀምሮ ሁሉም ከፍተኛ ትርጉም ሰጥተው ሊሰሩበት እንደሚገባም አመላክታለች።

በአብይ ጉዳይዋ ከኤርትራ ነፃ አገር መሆን ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ከባሕር በርም ከቀይ ባሕር ፖለቲካም እንድትርቅና የኢትዮጵያ የቀይ ባሕርና የወደብ ባለቤትነት መብቷ እንዳይነሳ መደረጉን አስታውሳ፤ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት ኢትዮጵያ አሁን እየታየ ካለው አገራዊና ቀጣናዊ እንቅስቃሴ አኳያ የቀይ ባሕር ተሳትፎዋ ዳግም መነቃቃትና ማንሰራራት እንዳለበት እንዲሁም የባሕር በር የማግኘት ታሪካዊ እና ሕጋዊ መብት እንዳላት መረጃዎችን በጥልቀት በመዳሰስ ተንትናለች። ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ በር ማግኘት እድትችል የጀመረቻቸውን አገራዊ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች በሰላማዊ፣ በዲፕሎማሲያዊና በህጋዊ መንገድ ማስቀጠል ይኖርባታል፤ ሠማያዊ መልህቅ ስትል የቀይ ባህርን ጉዳይ “እነሆ!” ብላለች።

በመተሳሰብና በመተዛዘን አብሮ ወደፊት የመጓዝ የኢትዮጵያዊያን እሴት እየጠፋ በምትኩ ‘እኔ ብቻ እኖር’ ባይነት መስተዋሉ በዝቷል ስትል አንስታለች፡፡ ኢትዮጵያዊያን እንደ ሕዝብም ሆነ እንደ ተቋም ውጤታማ መሆንና ከፈተና ማምለጥ የምንችለው በመተጋገዝ በኅብረት መስራት ስንችል ብቻ ነው፤ ስትልም አበክራ መክራለች።

የአየር ንብረት ለውጥ የአፍሪካ ሕልውና ስጋት መሆኑን፤ የአየር ንብረት መዛባት እያስከተለ ያለውን ሁሉን አቀፍ ጉዳት ከሰብዓዊ መብቶች ጋር አያይዛ፣ መንስኤውንና ዘላቂ መፍትሄውን አመላክታለች።

በአየር ንብረት መዛባትና በሌሎች ምክንያቶች የማገርሸት አዝማሚያ ያሳየውን የወባ በሽታ ዳግም ለመግታት በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑ፤ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ላለፉት 75 ዓመታት ብቸኛው የመንግሥት የጤና ተቋማት መድኃኒት አቅራቢ ሆኖ ውጤታማ ስራ ስለማከናወኑ፤ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር፣ የምርምርና ስርፀት እና የማኅበረሰብ አቀፍ ስራዎችን ስትራቴጂ ነድፎ በተጠናከረ መንገድ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ እና የልህቀት ማዕከልነት ራዕይ ስለሰነቁት የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ ትምህርት ቤቶች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴም አቅርባለች።

ንድፈ ሃሳብን ከተግባር

26

34

የአየር ንብረት ለውጥ የአፍሪካ ሕልውና ስጋት

44

ብሔራዊ ጥቅም ለአገር ግንባታ

50

ያገረሸውን ወረርሽኝ ዳግም መግታት

56

የልህቀት ማዕከልነት ራዕይ የሰነቁት ትምህርት ቤቶች

62

ጥሎ ከማለፍ …አብሮ መጓዝ

68



6

የሕልውና መሰረት

ፖለቲካ

አብሮነት ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን



7

የሕልውና መሰረት በዶ/ር ከይረዲን ተዘራ

(የሶሻል አንትሮፖሎጂ መምህርና የብዝሃነት ተመራማሪ) መግቢያ ኢትዮጵያ የረጅም ታሪክ ባለቤት ብትሆንም በተለይ ከአገረ መንግሥት ግንባታ ጋር ተያይዞ በመንግሥታት ደረጃ ሕዝቦችን የሚያቀራርቡ እና የሚያስተሳስሩ ተግባራት ታቅደው ባለመሰራታቸው የፖለቲካ መረጋጋት እና ጠንካራ ተቋማትና አገረ መንግሥትን መመስረት ሳይቻል ቀርቷል። በዚህም ኢትዮጵያ ስር ለሰደደ ድህነትና የዚሁ መነሻ በሆነ ግጭትና የፖለቲካ ሁከት አዙሪት ውስጥ እንድትቆይ ተዳርጋለች።

በኢትዮጵያ የተፈራረቁ መንግሥታት የአገራችንን ሕዝቦች በተወሰነ ደረጃ ማኀበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት የሚያሳድጉና የሕዝቦችን ተጠቃሚነት የሚያጎሉበቱ ተግባራት ቢያከናውኑም ሂደቶቹ አካባቢያዊና የአካባቢ ማንነትና በዚሁ ዙሪያ በተቃኙ የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ ያተኮሩ መሆናቸው የልማት ተግባራቱና የመሰረተ ልማት ግንባታዎቹ ሕዝቦቹን በማስተሳሰር ለጠንካራ አገረ መንግሥት መገንባት መጫወት ያለባቸውን ጉልህ ሚና ሊጫወቱ አልቻሉም። የመንግሥታቱ ስራ የአገሪቷን የተለያዩ ሕዝቦች በብዝሃነት ውስጥ



8

ያለን አንድነት እንዲያጠነክር ሁለንተናዊ በሆኑ መልኩ ባለመተግበራቸው ብሔራዊ መግባባትና ጠንካራ ኢትዮጵያዊ አብሮነትና አንድነት ላይ የላላ ትስስር ተፈጥሯል።

ይህ ቢሆንም በአገራችን ሕዝቦች በረጅም ዘመናት የተገነቡ እና በፈታኝ ወቅቶች አንድ የሚያደርጉ እና የሚያስተሳስራቸው የጋራ የአብሮነት እሴቶች በመኖራቸው አብሮነቱና መተሳሰቡ አገርን እንደ አገር እንድትጸናና ሕዝቦቿም በክፉም በደጉም ወቅት እንዲደጋገፉ ረድተዋል። እየረዱም ይገኛሉ። ምንም እንኳን ነባሩ የአብሮነት እሴት የገጠሙንን ችግሮች እንድንፈታና በክፉ ወቅት እንድንተባበር ቢረዳንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መገፋፋት፣ መጠራጠር፣ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ ግድያዎችና መፈናቀሎች እዚህም እዚያም መሰማትና መታየት መጀመራቸው ብዙዎች ኢትዮጵያዊ የአብሮነት እሴቶቻችን የት ጠፉ? ምን ችግር ገጠመን? መነጋገርና የጋራ የአብሮነት እሴቶቻችንን አጥንተን እንጠብቅ የሚሉ ድምጾችን በስፋት ሲያስደምጡ ይሰማል። ይህ ጽሑፍም ለዚህ ጥሪ ከተሰጡና ከሚሰጡ ምላሾች አንዱ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

አገራዊ ማኅበረ-ባህላዊ እሴቶቻችን ሕዝባችንን ያጋመዱ ሰንሰለቶች ናቸው። የአገራችን ሕዝቦች ለዘመናት በኖሩባቸው ዓመታት ያዳበሯቸውን ማኅበረ-ባህላዊ እሴቶች የኢትዮጵያ ሕዝቦች የገጠሟቸውን የውስጥና የውጭ ፈተናዎች

ለማለፍ እና በውጭ ወራሪዎች ላይ ሕዝባችን ድል እንዲቀዳጅ አድርገዋል። በቅርብ ጊዜያት ያጋጠሙንን እና አሁን እያጋጠሙን ያሉትን ፈተናዎች ለማለፍ እርቅንና አንድነትን በማስተማር እየረዱ ነው። በቀጣይም ለእነዚህ እሴቶች ቦታ መስጠት አስፈላጊ ነው። እነዚህ እሴቶች ምን ያህል ለአገራችን አንድነት እንደረዱና አሁንም ነባር ማኅበራዊና ባሕላዊ እሴቶቻቸንን በማጠናከር ቅራኔዎችን ማስወገድ እና ሁሉ አቀፍ ውይይት በማድረግ ለአገረ መንግሥት ግንባታ ሊኖራቸው የሚችለውን አበርክቶ ማየቱ ጠቃሚ ነው። ይህ ጽሑፍም በአገራችን ማኅበረ ባህላዊ ዕሴቶች በተለይ የአብሮነት እሴቶቻችን ለአገራችን ዘላቂ ሰላምና እና ለሕዝቦቿ መደጋገፍና መተባበር ስላላቸው ሚና በአጭሩ ይዳስሳል።

የማኅበራዊ ዕሴቶቻችን ምንነትና ለአገር ግንባታ ያላቸው አበርክቶ

ማኅበረ-ባሕላዊ እሴት ማለት የአንድን ማኅበረሰብ ባሕሪይ የሚመሩና የሚገሩ የተለያዩ ደንቦች፣ ሕጎች፣ መርሆችና እምነቶች ሲሆኑ ሕዝቦች ጤናማ የሆነ ማኅበራዊ ሕይወት እንዲኖሩ የሚያስችሉ ናቸው። በተጨማሪም የአገር በቀል እውቀት አካል የሆኑት እነዚህ ማኅበረ- ባሕላዊ ዕሴቶች አንድ ማኅበረሰብ የዕለት ተዕለት ሕይወቱን ለመምራትና ያጋጠሙትን ተፈጥሯዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባሕላዊና መሰል ችግሮችን ለመፍታት የፈጠራቸው ጥቅል

የሚታዩና የማይታዩ እውቀቶቹን እና እምነቱን የያዘ ትውፊት ሲሆን ሕዝቦች ከተፈጥሮ እና ማኅበራዊ ከባቢያቸው ተስማምተው ለመኖር በረጅም ዘመን ሂደት የፈጠሩትና ከትውልድ ትውልድ በባሕላዊ መንገድ የሚተላለፉ ዕሴቶች ናቸው (Warren 1991፣ Hoppers, 2005)። አረጋዊያንና የሃይማኖት አባቶችን ማክበር፣ ለታናናሾች ማዘን፣ ታላቅን ማክበር፣ ከግል ፍላጎት ይልቅ ለወልና ለአብሮነት ፍላጎት ቅድሚያ መስጠት፣ ለእውነት መቆም፣ መከባበር፣ መቻቻል፣ እውነትን መናገር፣ ማስታረቅ፣ ለጋስነት የመሳሰሉት ማኅበረ- ባሕላዊ እሴቶቻችን በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች ልዩ ቦታ አላቸው። ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ሥርዓቶቻችንም እነዚህን እሴቶች በስፋት ይጠቀማሉ።

ከላይ እንደተጠቀሰው የአገራችን ሕዝቦች ለዘመናት በኖሩባቸው ዓመታት ያዳበሯቸውን ማኅበረ-ባሕላዊ እሴቶች የኢትዮጵያ ሕዝቦች የገጠሟቸውን የውስጥና የውጭ ፈተናዎችን እና ችግሮች ለማለፍ እና በውጭ ወራሪዎች ላይ ሕዝባችን ድል እንዲቀዳጅ አድርገዋል። እሴቶቻችን በቅርብ ጊዜያት ያጋጠሙንን እና አሁን እያጋጠሙን ያሉትን ፈተናዎች ለመውጣት እርቅንና አንድነትን በማስተማር እየረዱ ነው። በዚህ ረገድ የአብሮነት እሴታችን አገርን ከመጠበቅና ሕዝቦቻችንን ከማስተሳሰር እና አገራዊ ፈተናን ከመቋቋም (resilient) አቅም አኳያ ካላቸው ጉልህ ሚና አንጻር ከፍተኛ



9

አስተዋጽኦ አድርገዋል። እያደረጉም ይገኛል። አብሮነት ማለት ምን ማለት ነው? ኢትዮጵያዊ አብሮነትስ አለ? ካለስ እንዴት ይገለጻል? ቀጥለን እናያለን።

የአብሮነት ምንነት

አብሮነት ማለት በአንድ ወይም በተለያየ አካባቢ የሚኖሩ ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎች ለአንድ ጉዳይ ወይም ለሌሎች ፍላጎት መከበር መተባበር፣ መተጋገዝ፣ መደጋገፍ ተብሎ በአጭሩ ሊተረጎም ይችላል። ለምሣሌ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ መተባበርና ችግር ውስጥ የገባን አካል እንዲወጣ ማድረግ የሚል ትርጓሜ ሊሰጠውም ይችላል።

ሁለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች አንድ ላይ ሲሰባሰቡና የጋራ ግብን ለማሳካት ሲተባበሩ ስለ መተባበር እንናገራለን ማለት ነው። አብሮነት ቁሳዊም ሆነ ስሜታዊነትን ለሌሎች ማካፈልም ነው፣ ለሌሎች ድጋፍ ማድረግንና በሰዎች መካከል የጋራ ትብብርን ይሰጣል። አብሮነት በአንድ አካባቢ በሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል ያለውን የየግል ማንነት በማክበር ለጋራ ዓላማና ለወደፊት የጋራ ግብና ራዕይ በጋራ ለመቆም ከውስጥ በሚመነጭ የትብብር ስሜት እና ቅርርብ የመተግበር ቁርጠኝነት ተደርጎ ሊተረጎም ይችላል። በማኅበራዊ ሳይንስ በተለይ በሶሺዮሎጂ የትምህርት መስክ አብሮነት የእያንዳንዱ አባላት ተመሳሳይ እሴቶችን እና ተመሳሳይ መርሆዎችን እንደ ማክበር ሊታይ ይችላል። ከዚህ አንፃር ፈረንሳዊው የሶሺዮሎጂ ባለሙያ ኤሚል ዱርሃይም /Émile Durkheim/ እንደሚሉት አብሮነት በሚከተሉት መንገዶች ሊታይ ይችላል።

አንደኛ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለው አብሮነት በጋራ ፍላጎቶች ወይም ግቦች ላይ የተመሠረተ የአንድነት ስሜት ነው፣ ማኅበረሰብ እንደ አካል አንድ ሆኖ ሲወጣ ከግለሰቦች ድምር ስብስብ በላይ ነው የሚለው ዱርሃም አብሮነት አንድ ግለሰብ የአንድ ማኅበራዊ ቡድን አባል ለመሆን፣ አብሮ ለመሥራት፣ አንድ ግብ ላይ ለመድረስ ወይም በአንድ ምክንያት በጋራ ለመታገል መንቀሳቀስን ይገልፃል ይላሉ።

በተጨማሪም በማኅበረሰብ ውስጥ የሚታየው ፀንቶ የኖረ አንድነት፣ የእያንዳንዳቸው ጠንካራ የሙያ ብቃት እና የቴክኒክ የሥራ ክፍፍል ለጋራ ግብ በማዳመር ለወል ሰላምና ስኬት በተለያዩ ግለሰቦች መካከል የሚኖር እርስ

በእርስ መተማመንን ያመለክታል ይላሉ። ከላይ በተጠቀሰው መሠረት አብሮነት አንድ ግለሰብ ከሰዎች ጋር እንዴት መኖር እንዳለበት የማወቅ ጥበብ ነው፣ ማኅበራዊ ተግባር ነው፣ እንዲሁም የአንድ ማኅበረሰብ አባላትን እርስ በእርስ የሚያገናኘውን አንድነት ወይም ማኅበራዊ ትስስርን የሚያመለክትም ነው።

አብሮነት ውስጥ እንግዲህ በቡድን መኖር አለ፤ ሰላማዊ ማኅበራዊ ቅርርብ አለ፤ ዛሬም ሆነ መጪውን ጊዜ አብሮ ለመኖር መወሰንም አለ። በተጨማሪም በክፉም በደጉም ቁሳዊም ሆነ ቁሳዊ ያልሆነ ድጋፍ እና ትብብር የሚደረግለት ግለሰብም ሆነ ቡድን በተመሳሳይ መልኩ ሌላኛው አካል ችግርም ሆነ ደስታ ሲገጥመው ሊመልስ (reciprocity) አልያም ላይመልስ ቢችልም ከፍ ያለ አብሮ የመኖር ግብን እና ሰላማዊ ማኅበራዊ ከባቢን ለመፍጠር ተብሎ ከግል ይልቅ ለወል ሰላም በማሰብ የሚከወን ተግባርን ያካትታል። አብሮነት መተማመንን ይፈልጋል።

አብሮነት ይህን ያህል ከፍ ያለ ትርጉም ካለው ኢትዮጵያዊ አብሮነት ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ተተግብሮ ያውቃል ወይ? ለምንስ በተለያዩ ወቅቶች በሕዝቦች መካከል መገፋፋትን፤ ማንነትን፣ ዕምነትን፣ ብሔርና ቋንቋን መሠረት በማድረግ መጠቃቃትን አየን? የሚል ጥያቄ ይነሳል። አብሮነት በእርግጥ በአገራችን የተገነባ የሕዝቦች የወል ዕሴት ሆኖ በመተግበሩ በሠርግ፣ በለቅሶ፣ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ሲደርስ የአገራችን ሕዝቦች ዘር፣ ዕምነትና አካባቢ ሳይለዩ ሲደጋገፉ፣ ሲተባበሩ፣ የጋራ ጠላት ሲመጣ ሆ! ብለው ተነስተው አገርን ከጥቃትና ከወራሪ ሲጠብቁ እንዲኖሩ ያስቻለ ትልቅ ማኅበረ- ባህላዊ ዕሴት በመሆኑ በአገሪቱ ተተግብሮና አሁን ከእነ ውስንነቱ እየተተገበረ ያለ ነው ብሎ መናገር ይቻላል። ነገር ግን የኢትዮጵያዊ አብሮነት እሴት በረጅም ጊዜ የተገነባውን ያህል ውስጣዊና ውጫዊ በሆኑ ምክንያቶች እየተሸረሸረ፣ በሕዝቦች መካከል የነበረው መተማመን እየተመናመነ በመሄዱ መገፋፋትና ጥቃቶች እዚህም እዚያም በመበራከት ማኅበራዊ ውሉ እየላላ መሄድ ጀምሯል። ይህንን ለማስተካከል ፈጣን ተግባራዊ እርምጃ ያስፈልጋል የምንለውም ለዚያ ነው።

አብሮነት እንዲያው ዝም ብሎ ማኅበራዊ ችግርን ለመፍታት ካለው ፋይዳ አንፃር ታይቶ ብቻ አይደለም ለአገራችን ያስፈልጋል የምንለው።

ከዚያ በላይ እንደ አገር የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመፍታት እና አገራዊ ህልውናን ለማስቀጠል የሚረዳን ትልቁ ችግር መፍቻና አደጋን መቋቋሚያ ማኅበራዊ ድሮን በመሆኑም ጭምር ነው። እንዲህ ለተጋመደና ለተፈተለ ሕዝብ አንዱ አንዱን ገፍቶና አጥቅቶ የሚጨርስበትና ብቻዬን እኖራለሁ የማይልበት አገራዊ ተጨባጭነት ነው ያለው። ይህ ሳይሆን ቀርቶ መገፋፋቱ ከቀጠለ በአንድ በኩል ሁሉም በሁሉም የሚነሳበት ዕድሉ ከፍ ያለ በመሆኑ፤ በሌላ በኩል ሕዝባችን የቆመበት አገራዊ መሠረት የተፈተለውና የተገነባው በጋራ ደም እና ላብ በመሆኑ አብሮነትን መጥላት አገርን መጥላት እና ከራስ ጋር መጣላት በመሆኑ ሁሉም ይህንን የጋራ አደጋ በማየት “ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሉ በጊዜ ወደ ቀልብ መመለስ ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያዊ የአብሮነት እሴት

እንደ ሥነ ሰብ (ሶሻል አንትሮፖሎጂ) ምሁራን ባህል ዓለም አቀፋዊና አካባቢያዊ ባህሪይና መገለጫ አለው። በዚህ ረገድ አንዳንድ ባህላዊ መገለጫዎች በሁሉም አካባቢዎች ሲተገበሩና ሲገኙ አንዳንዶቹ ደግሞ በአንድ ወይም በሌላ ማኅበረ-ባህላዊ ከባቢ ይተገበራሉ፤ ይገኛሉ። ለዛም ነው ባህል ከአውድ አኳያ ዓለም አቀፋዊ (universal culture) እና አካባቢያዊ አውድ (specific culture) አለው የሚባለው። በዚህ መነሻ አብሮነት በአብዛኛው የዓለማችን አካባቢዎች በተለይ በማኅበራዊ ሕይወት እንቅስቃሴያቸው ከግል ይልቅ የቡድን እንቅስቃሴን በሚያስቀድሙ አገራትና ሕዝቦች ዘንድ የሚተገበር እሴት ነው። በተጨማሪም በጥቅሉ የማኅበራዊ ሳይንስ ምሁራን እንደሚገልጹት የሰው ልጅ ማኅበራዊ እንስሳ ነው። ይህ ማለት የሰው ልጅ በተፈጥሮው የሚፈልገውን ጉዳይ ማሳካት የሚችልበት ዋነኛ መንገዱ ማኅበራዊ መስተጋብርን በሌላ አነጋገር አብሮነትን ተጠቅሞ ነው ማለት ነው። በመሆኑም የሰው ልጅ ከግለኝነት ይልቅ የአብሮነት እሴቱ ማንነቱና ዋነኛ መገለጫው ነው። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ኢትዮጵያዊው አብሮነት የራሱ የሆኑ ልዩ ባህሪያት አሉት? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች እንደ ማንኛውም የዓለማችን ሕዝቦች አብሮነት እሴታቸው ቢሆንም ከዚህ በተለየ አብሮነትን ግዴታ አድርገው ባዳበሯቸው ማኅበረ-ባህላዊ ዕሴቶች መነሻ ምክንያቶች እና ብዝሀነት በተላበሰው ሰፊ መልክዓ ምድር



10

ብሎም ብዝሀ ምርቶቹ መተባበር እና አብሮነቱ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳዩ ሆነው ሊጎለብቱ ችለዋል። ኢትዮጵያ የተለያዩ እምነቶች፣ ባህሎች፣ ሕዝቦችና መልክዓ ምድር ያላት ስትሆን አንዳንድ ምሁራን (ዶናልድ ሌቪን፣1975) እንደሚሉት ሕዝቦቹ የየራሳቸው መገለጫ ማንነት ቢኖራቸውም ሳይነጣጠሉ እጅግ የተሳሰሩ ሆነው የተገናኙ በመሆኑ መተባበሩ ከኢኮኖሚያዊ ገፊ ምክንያቶች በተጨማሪ አንድ አካልና አንድ አምሳል በሚመስል ልክ አንዱ ለሌላው ያዝናል፣ ይተባበራል፣ በአብሮነት ሀሴት እና ሀዘኑን ያሳልፋል።

ይኸው ጸሐፊ የኢትዮጵያዊያን የአንድነት ህልውና በሶስት ተዛማጅ ሥርዓቶች ምክንያት የመነጨ መሆኑን ይገልጻል። እነሱም አንደኛ ልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ባለማቋረጥ የእርስ በእርስ ግንኙነት የማድረጋቸው ሂደት፣ ሁለተኛ በርከት ያሉ አገር አቀፍና ኢትዮጵያን መሰል የሆኑ የወል የባህል ቅርሶች በሁሉም አካባቢ መኖር (ለምሳሌ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች) እና ሶስተኛ በየጊዜው የውጭ ኃይል በአገሪቱ ላይ ጣልቃ ለመግባት በሚቃጡበት ጊዜ ለመከላከል አብረው በጋራ መቆማችው ናቸው (ዶናልድ ሌቪን ታላቋ ኢትዮጵያ 1975 39)።

እንደ ዶናልድ ሌቪን ትንታኔ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለረጅም ዘመናት ዘመናዊው የአገረ መንግሥት ምስረታ ከመከናወኑ በፊት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ይካሄድ በነበረው የንግድ እንቅስቃሴ (ሲራራ) ምክንያት ዘርና አካባቢን ሳይለይ ተጋብቷል፣ ተዋልዷል፣ በጎሳና በዘር ተጎዳኝቶ ተጋምዷል። በተጨማሪም የአገሪቱ ሕዝቦች በአብዛኛው የሚከተሏቸው የክርስትና፣ የእስልምና ብሎም ባህላዊ እምነቶች ሕዝቦቹን ከብሄራቸው በተጨማሪ በአንድ እምነት ስር እጅግ ያስተሳስራቸዋል። ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ እንደመሆኗ በአገሪቱ ያሉት የቋንቋ ቤተሰቦች ቋንቋዎች (አፍሮ እስያዊ፣ ኒሎ ሰሃራ) ሕዝቦቹን ከብሄራቸው በተጨማሪ ከሁለት ባልበለጡ የቋንቋ ቤተሰቦች ያስተሳስሯቸዋል። በየአካባቢው የምናገኛቸው አነስተኛ ገበያዎች ሕዝቦቹን ከአንድ ማንነት በላይ ሄደው አስተሳስረዋል። ለምሳሌ ወሎ አካባቢ ባቲ ገበያ የአካባቢው ነዋሪ አርጎብኛ፣ ኦሮምኛ፣ አፋርኛ፣ ትግርኛና አማርኛ ቋንቋ ተግባብቶና ተገበያይቶ በሰላም ይለያያል፤ ኅብረተሰቡ በራሱ ፌዴራላዊ ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች በየገበያዎቹ፣ አውዳመቶቹና

በእምነትና በአካባቢው የምርት እንቅስቃሴዎች በየጊዜው የአብሮነቱን እሴት ያስተሳስራል፤ የበለጠ ይጋመዳሉ። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋብቻ ሥርዓት በአብዛኛው አንትሮፖሎጂስቶች እንደሚሉት ኤግዞጋመስ ወይም ከራስ አካባቢ አልፎ ከሌላ ጎሳ ወይም ከደም ራቅ ባለ መልኩ ጋብቻ ስለሚፈጽም ኅብረተሰቡን እዳይለያይ አድርጎ አስተሳስሮታል። በአኗኗር ዘይቤም ቢሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ በሚቀራረቡ ሶስት የአኗኗር ዘይቤዎች ተከፋፍሎ ነው የሚኖረው፤ በግብርና፣ በእንስሳት እርባታ እና በእንሰት ምርት ባህል። ይህ የአኗኗር ዘይቤ ሕዝቡ አንዱ በአንዱ እንዲመረኮዝና አንዲፈላለግ ብሎም ያለ አብሮነት መኖር እንዳይችል አድርጎ ፈትሎታል ብዬ አምናለሁ። እነዚህ ታሪካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ ኩነቶች የኢትዮጵያዊ አብሮነት መገለጫ ተደርገው ሊቀርቡ ይችላሉ።

እነዚህ ማኅበረ-ባህላዊ ተቋሞቻችን የአንድነታችን ማስተሳሰሪያ ድልድዮች ናቸው። ከእነዚህ ተቋማት የሚመነጩ የአብሮነት እሴቶች የሆኑት እንደ አበልጅ፣ ዓይን አባት፣ ጉዲፈቻ፣ ጉርብትና፣ እድሮች፣ እቁቦች፣ ጌዝ፣ ወንፈል፣ ደቦ፣ መድረሳ፣ የቄስ ትምህርት ወዘተ… በረጅም የታሪክ ዘመናችን የተገነባ የአብሮነት እሴት እዲፈጠር ያደረጉ ሕዝቡን ከባዮሎጂያዊ የደም ትስስር በላይ የማኅበራዊ ትስስር ያደረጉ እሴቶች አድርጓቸዋል። ይህ የአብሮነት እሴት ታዲያ አገሪቱን ለተለያዩ ፈተናዎች የማትንበረከክ እና ችግርን የምትቋቋም ድንቅ አገር ብሎም የማኅበራዊ የመከላከል ጥንካሬ (Social Resilience) ባለቤት እድትሆን አድርጓታል።

የአብሮነት እሴታችን ሚና ለአገረ መንግሥት ግንባታ

አገር ግንባታ የተለያዩ ሰዎች የተለያየ ትርጉም የሚሰጡት፤ አንዳንድ ጸሐፍት ኖርማቲቭ የሚሉት አይነት እሳቤ ነው። ዳሩ ግን በርካታ ተመራማሪዎች የሚስማሙበት አንድ ገዢ ሀሳብ አለ። ይኸውም አገር ግንባታ ስር- ነቀል ሳይሆን ረጅም ጊዜን የሚሻ ዝግመታዊ ማኅበራዊ ሂደት (social process) ስለ መሆኑ ነው። በሕዝቦች መካከል መቀራረብንና የእኔነትን የሚፈጥሩ የብዝሃነት አላባዊያንን ማካተትና ማቀናጀት የአገር ግንባታ ሂደት ማጠንጠኛ ተደርጎ እንዲወሰድ ምሁራን አጠንክረው የሚመክሩበትም ምክንያት አንድም ከነጠላነት ይልቅ ማኅበራዊነት /ብዝሀነት/ ከአገር

መሠረታዊያን (fundamentals) ውስጥ አንዱና ዋነኛው ስለሆነ ነው። ስለሆነም Elaigwu (1983) እንደሚለው አገር ግንባታ ማለት የዜጎችን ሕይወት የሚያሻሽሉ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ፖሊሲዎችን መተግበር ብቻ ሳይሆን ይልቁንም የአንድን አገር ሕዝቦች ትስስርና አብሮነት የሚያጠናክሩ እሴቶች እውቅና እንዲያገኙና አገራዊ /ብሔራዊ/ የጋራ ማንነት የሚቆምባቸው የውሃ ልክ እንዲሆኑ ማድረግንም ይጨምራል።

እንዲሁም የሕዝቦችን ጥቅል ሕይወት ሁለንተናዊነት /ምሉዕነት/ ይወክላል ተብሎ የሚታሰበው ባህል የአገር ግንባታን ከሚያቆሙ አይነተኛ የማዕዘን ድንጋዮች ውስጥ አንዱ ነው። በሕዝቦች ውስጥ ተፈጥሮ የቆየውን የመጠራጠር ስሜት ማከም ለዘላቂ ልማትና ለአገራዊ አንድነት ወሳኝ ነው። በተጨማሪም የአገረ መንግሥት ግንባታ ዋነኛ ግብ በሕዝቦች መካከል የዓላማ እና የወደፊት ዕጣ ፈንታ ዙሪያ የተቀራረበ እሳቤና ሕዝቦች አገርን የእኔ ነው ብለው ከውስጥ እንዲያምኑና ለዕድገቱና ለሰላሙ በጋራ እንዲቆሙ ማድረግ በመሆኑ የአብሮነት እሴትን ማጠናከር ለዚህ ስኬት የማይተካ ሚና ይጫወታል። ይህንን ታላቅ አገርን በጠንካራ መሰረት ላይ የመገንባት ግብ ለማሳካት የአብሮነታችን ተግዳሮቶች የሆኑትን በተለይ ከቅርብ ግዜ ወዲህ እየታየ የመጣውን ግለኝነት፣ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች፣



11

መፈናቀሎች፣ ግድያዎች በሕዝባችን መካከል መጠራጠርን በማምጣት ነባሩን የአብሮነት ዕሴት ስለሚሸረሽር እሴቶቹን ለማዳበር የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን ይገባል።

በቀጣይ ምን መከናወን አለበት?

የአብሮነት እሴቶቻችን በረጅም ዘመናት እንደገነባናቸው ሁሉ አሁን እዚህም እዚያም የሚታዩት መገፋፋቶችና ከእኔ በላይ ላሳር አይነት የግለኝነት እሳቤዎች እንዲስፋፉ ዕድል ካገኙና የከረረው የብሔርተኝነት ስሜት መልክ ካልያዘ እየተሸረሸሩ ሄደው የአገርን ህልውና እስከመገዳደር ሊደርሱ ይችላሉ። በመሆኑም ለባህል ተቋማትና ለእሴቶቻችን መጎልበት መሰረት የሚጥሉ የሕግ ማሻሻያዎችን ማድረግና መተግበር ግድ ይለናል። ማኅበረ- ባህላዊ እሴቶቻችን እና አገር በቀል ሥርዓቶቹ በራሳቸው አካባቢ ፍትሕን ተደራሽ እንዲያደርጉ ለማድረግ የሚያስችል የሕግ ማሻሻያ ማድረግ (ያሉን ሕጎች ሕገ-መንግሥቱን ጨምሮ ሚናቸውን በሚመጥን መልኩ ቦታ እንዲሰጣቸው ቢደረግ)፣ በፖለቲካ ልሂቃኖቻችን የሚታየው ቅራኔ እና የገመድ ጉተታ መሰል ፖለቲካ ያለመተማመን ባህልን በማጎልበት አብሮነትን ስለሚጎዳ ከሽኩቻ በጸዳ መልኩ ንግግርን መሰረት ወደሚያደርግ የፖለቲካ ባህል እንዲቀየር መስራት። በተጨማሪም የአብሮነት እሴቶች እንዲሸረሸሩ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ

ችግሮችን ውጫዊ ከማድረግ ሁሉም ለችግሩ መፈጠር ያለውን አበርክቶ ቆም ብሎ መፈተሸ ( self-reflection) ያስፈልጋል።

የእምነት ተቋማትና የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች የአብሮነት እሴቶቻችን እንዲጠበቁና አንዲጎለብቱ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል።

በሌላ በኩል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እነዚህ እሴቶች እና ተቋማት ያላቸው እምቅ አቅም በተገቢው ሁኔታ ጎልቶ እንዲወጣ በትምህርት ሥርዓቶቻቸው ማካተት፣ እንደ አንድ የምርምር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ዋነኛ ተልዕኮ በማድረግ እንዲጠኑ፣ እንዲጎለብቱና ከትውልድ ትውልድ እንዲሸጋገሩ ለማድረግ እቅዶቻቸውን እንዲከልሱ ማድረግ ያሻል። ቤተሰብም እንደ ማኅበረሰብ መገንቢያ ዋነኛ መሰረት በልጅ አስተዳደግ ዘይቤ የተፈጠረውን የእሴት መሸርሸር በመፈተሽ ሕፃናት ከልዩነት ይልቅ አብሮነትን እንዲያጎለብቱ ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው።

በተጨማሪም ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ ባሉ የትምህርት ተቋሞቻችን የአብሮነት እሴቶቻችን በአግባቡ በማጥናት የትውልዱ የስብዕና ግንባታ ማድረግ ግድ ይለናል። የሥነ-ጥበብና የፊልም ስራዎች፣ ግጥምና መነባንቦች፣ ጭውውቶች፣ የስዕልና የሙዚቃ ስራዎች አገራዊ አብሮነታችንን

እንዲያዳብሩና እንዲገነቡ የሚያደርግ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል። የፖለቲካ ሥርዓታችን፣ ሕጋችን፣ ሕገ መንግሥታችን እንዲሁም የተለያዩ ደንቦች፣ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የሕዝቦችን ትስስር፣ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት በሚያስችል መልኩ እዲከወኑ በጥንቃቄ መምራት። የተለያዩ የፌዴራል ተቋማት የሰው ኃይል ስብጥር፣ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት የሰው ኃይል ግንባታ ኅብረ ብሔራዊ እንዲሆንና ተዓማኒ ሆነው አብሮነትን እንዲያጠናክሩ በጥንቃቄ መስራትና መገንባት ይገባል።

ማጠቃለያ

ኢትዮጵያዊ አብሮነት በጋራ የመኖርና ችግርና ፈተናን የመሻገር ከፍ ያለ መግነጢሳዊ ኃይል መሆኑን የተረዱ የኢትዮጵያ ውስጣዊና ውጫዊ ኃይሎች ዕሴቱን ለመሸርሸርና በሕዝቦች መካከል መተማመን እንዲጠፋ አበክረው የሚሰሩትም ለዚህ ነው። አብሮነት አገርን የተሸከመ ዋነኛ የስበት ማዕከል በመሆኑ። አብሮነት የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያን የሕልውና መሠረት ነውና ለዕሴቱ መጠበቅና መጎልበት ቤተሰብ፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከፍተኛ ትርጉም ሰጥተው ሊሰሩበት ይገባል ባይ ነኝ።



12

የችግሮቻችን መፍቻው ቁልፍ

ማህበራዊ



13

በፍቅርተ ባልቻ … ማን ነን? “እንዴት ነው ራሳችሁን የምትገልጹት? በተወለዳችሁበት ስፍራ ነው? በምትከተሉት ሃይማኖት፣ በፖለቲካዊ እሳቤያችሁ፣ በጾታችሁ፣ በብሔራችሁ ወይስ … በምን? ‘ማንነት እንዴት ነው የሚፈጠረው?’” ለሚለው ጥያቄ የተለያየ ሀሳብ እና ምላሽ ሲቀርብ ይስተዋላል። ይህን አስመልክቶ ሦስት ዋና ዋና እሳቤዎች መኖራቸው ነው የሚገለጸው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (የሶሻል አንትሮፖሎጂ) መምህር ዶ/ር ከይረዲን ተዘራ እንደሚያስረዱት፤ የመጀመሪያው (primodalism) ሲሆን ማንነት ተፈጥሯዊ እንደሆነ የሚገልጽ እሳቤ ነው። ይህም ፍልስፍና ማንነታችን አብሮን የሚፈጠር እንደሆነ ያምናል። በዚህም መሰረት ማንነታችን መሰረት የሚያደርገው (ብሔር፣ ሃይማኖት፣ አካባቢ … ላይ ይሆናል ማለት ነው። ይህን አስተሳሰብ በዋናነት የሚያቀነቅኑት ጀርመናዊያን (የጀርመን ምሁራን) ናቸው። እንደዚህ ፍልስፍና ከሆነ ማንነታችን አብሮን የሚፈጠር እና የማይቀየር ነው።

የችግሮቻችን መፍቻው ቁልፍ



14

ሁለተኛው እሳቤ (Constructivism) ነው። ይህ ፍልስፍና ማንነት በሂደት የሚገነባ እንደሆነ ያምናል። “የሰው ልጅ የሚፈልገውን ይገነባል፤ ያልፈለገውን ይተዋል። ማንነት አብሮ አይወለድም” ብሎ ነው የሚነሳው።

ሦስተኛው (Instrumenetalism) ሲሆን “ማንነት ፖለቲከኞች ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚፈጥሩት ነው” ብሎ የሚያምን እሳቤ ነው። ማንነት እየተገነባ የሚሄድ እና ቀጣይነት ያለው መሆኑን ማመን እንደሚያስፈልግ የሚመክሩት ዶ/ር ከይረዲን ሦስቱም ጽንሰ ሀሳቦች የራሳቸው ጠንካራ እና ደካማ ጎን እንዳላቸው ይጠቅሳሉ። ይህን ሀሳባቸውን ሲያብራሩም “እንደ ኢትዮጵያ ያለ ብዝሃ ማንነት ያለው ማኅበረሰብ ውስጥ እኛ ፈልገን የምናዳብረው መሆኑን ማመን ያስፈልጋል“ ይላሉ።

የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዱዓለም ደግሞ ጸሐፊያንን ዋቢ በማድረግ ማንነትን በሦስት ደረጃዎች አስቀምጠውታል። የመጀመሪያው ማንኛውም ማንነት እውቅና ይሰጠኝ የሚል መነሻ አለው፤ ይህ ማንነት በጣም ጤናማ የሚባል ጥያቄ እና እሳቤ ነው። ሁለተኛው “ፍትሃዊነት ይኑር” የሚል ነው፤ ይህ ከመጀመሪያው ጥያቄ ቀጥሎ የሚመጣ ነው፤ ይህም ጤናማ ነው። እኩልነት ላይ ከደረሰ በኋላ “እኔ የበላይ ነኝ” የሚል ጥያቄ ሲመጣ አደገኛ እና አፍራሽ የሚሆንበት ማንነት ሦስተኛው ደረጃ ነው። የማንነት ጥያቄው አገርን እና ሕዝብን የሚጎዳው እዚህ ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው።

አገራዊ ማንነት የሚገለጽባቸው ሦስት መንገዶች መኖራቸውን የመስኩ ምሁራን ይገልጻሉ። የመጀመሪያው “ብሔራዊ/አገራዊ ማንነት ቋሚ እና ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ነው” ይላል። ሁለተኛው ብሔራዊ ማንነት በፖለቲካ አመለካከት የሚገነባ እንደሆነ ይገልጸዋል። ሦስተኛው ሲቪክ ማንነት ሲሆን ይህም በጋራ መልክዓ ምድር በመኖር የሚመጣ የጋራ እይታ የጋራ ሥነ-ልቦና እና እሳቤ ነው። የዜጎች አለባበስ፣ የአኗኗር ዘይቤ የመሳሰለው የጋራ ማንነት መገለጫ ነው። ይህ ከብሔርተኝነት ጋር እንዳይጋጭብን ጥንቃቄ ማድረግ ይጠይቃል።

ዶ/ር ከይረዲን አገራዊ ማንነትን ሲገልጹ ይህ ግለሰባዊ ማንነት ከሆነ አገራዊ ማንነትስ ምንድን ነው? ብሔራዊ ማንነት (National Identity) የሚባለው”እኔ ለዚህ አገር ምንድን

ነኝ?“ ብሎ ማሰብ ነው ይላሉ። አገራዊ ማንነት ከሥነ-ልቦና እና ከውስጣችን ካለ እሳቤ ጋር የተቆራኘ እንደሆነ በአጽንኦት ይገልጻሉ። ሰንደቅ ዓላማ፣ ብሔራዊ በዓላት እና የመሳሰሉት የጋራ መገለጫዎች ናቸው። ይህ ማንነታችን የሚገለጽበት መሰረታዊ ጉዳይ ስለሆነ በዚህ ላይ ብዙ መስራት ያስፈልጋል።

ሌላው ስለማንነት ሲነሳ የማይታለፈው ነጥብ ድርብርብ ማንነት ነው። መታሰቢያ መላከ ሕይወት ገ/ክርስቶስ “ዐቃፊ ማንነት” በሚል ርዕስ በ2012 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፋቸው “ባሕላዊ ማንነት አንድ ሰው ወይም ቡድን ከቤተሰቡ፣ ከአካባቢው አብሮ ከሚኖረው ማኅበረሰብ የሚወርሰው ማንነት ነው” ሲሉ ገልጸውታል። ጸሐፊው በዚሁ መጽሐፋቸው ”እኛ ኢትዮጵያዊያን የበርካታ ማንነቶች ባለቤት ነን። በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በቆዳ ቀለም፣ በደገኝነት፣ በቆለኝነት ወዘተ … በርካታ ማንነቶች አሉን። እነዚህ ማንነቶች እርስ በእርሳቸው የሚወራረሱ ናቸው“ በማለት ድርብርብ ማንነት መኖሩን አብራርተውታል።

የማኅበረሰብ ጥናት ተመራማሪው ፕሮፌሰር ገብሬ ኢንቲሶ እንዳሉትም ”በጾታው፣ በጎሳው፣ በብሔሩ፣ በሃይማኖቱ፣ በአካባቢውና በአገሩ የሚያገኘውን ድርብርብ ማንነቶች ነው በአንድ ሰው ማንነት ውስጥ የምናገኘው። ለዚህ ነው ስለማንነት ስናወራ ስለ የትኛው ማንነት ነው?” በሚል እየነጠልን መግለጽ የሚጠበቅብን” ስለሆነም በውስጣችን ድርብርብ ማንነት አለ ማለት ነው። እነዚህ ማንነቶች የማይነጣጠሉ ናቸው። ከእነዚህ ማንነቶች አንዷን ነጥለን ስንይዝ ችግር እንደሚገጥመን የመስኩ ምሁራን ይገልጻሉ። ዕድገት እና ስልጣኔ ሲመጣ ሰው ለማንነቱ የሚሰጠው ቦታ፣ እይታው እንዲሁም ትርጉም አብሮ ይለወጣል። አሁን አድገዋል በሚባሉት የዓለም አገራት ውስጥ እየተስፋፋ ያለው እሳቤ ግላዊነት ነው። ሰው ራሱን ከማኅበረሰቡ እና ከአካባቢው ነጥሎ ይኖራል፤ ራሳችንን ነጥለን ስናይ ግላዊ ማንነታችን እያደገ ይመጣል። ይህም በማንነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል።

በአንድ የዓለማችን ክፍል በአንድ ድንበር ተከበው፣ የጋራ ሕገ-መንግሥት አጽድቀው፣ የጋራ ሰንደቅ ዓላማ ኖሯቸው የሚኖሩ ሕዝቦች የአንድ አገር ሕዝቦች ይባላሉ። “ነገር ግን እነዚህ ሕዝቦች አንድ ዓይነት ማንነት አላቸው ማለት

አይደለም” ሲል የመታሰቢያ መላከ ሕይወት መጽሐፍ ጠቅሷል። የዚህም ምክንያቱ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ሃይማኖቶች፣ የቆዳ ቀለሞች፣ ባሕሎች፣ ወዘተ … ስለሚኖራቸው ነው።

“እኛ ማን ነን?” ስንል ስነ-ልቦናዊ ገጽታ አለው። እኔ ማን ነኝ ብዬ ነው የማስበው፣ እንደ ብሔር፣ እንደ ሃይማኖት፣ እንደ ጾታ፣ እንደ የፖለቲካ አመለካከት፣ ወዘተ…። ስለዚህ ራሴ የማስበውን ነው የማደርገው ማለት ነው። ሌሎች ማን ናቸው? ብለው ነው የሚያስቡት። የሚለውን ጥያቄ ስናነሳ ማንነት ለራሳችን የሚኖረንን ምልከታ ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም እይታ እንደሚያካትት ያሳያል።

የራስ ማንነት በአንድ በኩል፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሚነጻጸር ሌላ ማንነት አለ። እኛ ራሳችን፣ እኛ ሌሎችን፣ ሌሎች እኛን የሚያዩበት መንገድ ጤናማ ሳይሆን ሲቀር ነው ችግር የሚፈጠረው። ስለዚህ ይህ ጉዳይ በጥንቃቄ መያዝ እና መታየት ያለበት ነው። የማንነትን ፋይዳ ተረድቶ በተገቢው ማጥናት ያስፈልጋል፣ ይገባልም። እንደ ዶ/ር ከይረዲን ገለጻ “በዓለም ላይም ሆነ በአገራችን ይህ ጽንሰ ሀሳብ ጥንቃቄ የሚያሻው እና ስስ ነው፣ በሁለቱም በኩል እንደተሳለ ቢላዋ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።“

ማንነት እኛ ራሳችንን የምናይበት መንገድ ነው፤ ሌሎች እኛን እንዴት እንደሚያዩንም የምንረዳበት መንገድ ነው። ስለሆነም የሁለትዮሽ ግንኙነት አለው። የፖለቲካ ባሕሪያችንን እና አብሮነታችንንም በተለያየ መልኩ ይጎዳል። በማንነት ላይ የሚሰራው ስራ ጠቃሜታው የጎላ ነው። በጥቅሉ በአገራት ላይ በጎም ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ አለው፤ ለዛም ነው “የማንነትን አጀንዳ እንደ ቀላል ጉዳይ ማየት የለብንም“ ሲሉ የመስኩ ምሁራን የሚመክሩት።

እሴቶቻችን … አስተሳሳሪዎቻችን

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በ2006 ዓ.ም “የሰላም ዕሴት ግንባታ” በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፍ ሰላማዊነት፣ አብሮነት፣ መከባበር፣ እውነተኝነት፣ ፍትሃዊነት፣ ይቅርታ፣ ሩህሩህነት፣ መልካም ምሳሌነትና በጎነት የሃይማኖቶች መሰረታዊ የጋራ ዕሴቶች መሆናቸውን ያስረዳል። ይኸው መጽሐፍ እነዚህ የሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ዕሴቶች ለግለሰብ፣



15

ለቤተሰብ፣ ለማኅበረሰብ፣ ለአገር፣ ለዓለም ያላቸውን ፋይዳ እና ጠቀሜታም በዝርዝር አስፍሯል።

ባሕላዊ ማንነትና ብዝሃነት የአንድ አገር ሕዝቦች ብዝሃ ባሕል የማንነት መገለጫዎች፣ ለዜጎች ታላቅ ሀብትና የማኅበራዊ ስብዕና መሠረቶች ናቸው፡፡ እነዚህን ከጥፋት በመታደግ፤ ማጎልበትና ለዘለቄታዊ ልማት መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡

በ2008 ዓ.ም ይፋ የሆነው የኢትዮጵያ ባሕል ፖሊሲ “አንድ የፖለቲካና የምጣኔ ሀብታዊ ማኅበረሰብ በመፍጠር ሂደት ውስጥ ወሳኝ ሚናና ድርሻ ያላቸው በተለያዩ የፎክሎር ቅርፆችና ትውፊቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የቆዩ የሰላም፣ የፍትሕ፣ የእውነት፣ የእኩልነት፣ የሰብዓዊነት፣ የአንድነት፣ የመተሳሰብ፣ የነፃነት፣ የመቻቻል፣ አብሮ የመኖር እና የመሳሰሉትን የአገሪቱን ባሕላዊ እሴቶች በማጥናት ለሰላምና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ ለዴሞክራሲያዊ ብሔራዊ መግባባት፣ ለልማትና ለዕድገት ግብዓት እንዲውሉ ይደረጋል“ ሲል የባሕላዊ እሴቶችና አገር በቀል እውቀቶችን እንዴት እና ለምን መጠቀም እንዳለብን አብራርቷል።

ከኅብረተሰቡ መካከል እውቅናና አክብሮት የተቸራቸውን የሃይማኖት አባቶች፣ የአገረሰብ

መሪዎችና አዛውንቶች፣ ወጣቶችና ሴቶች መርጦ በባሕላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችና እውቀቶች ላይ በማሰልጠን ለማኅበረሰባቸው አገልግሎት እንዲሰጡ መስራት ወሳኝ መሆኑንም የባህል ፖሊሲው አመላክቷል።

“አስተሳሳሪዎቻችን እሴቶቻችን ናቸው። በጋራ እሴቶቻችን እርስ በእርስ እንተሳሰር። እንደ ሸረሪት ድር የሚያስተሳስሩ ወሳኝ ነገሮች ናቸው። ዘመን የቆጠሩ እና ሰላማችንን የሚያጸኑ ናቸው። ስለሆነም በእነዚህ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ አለብን። አሉታዊ እና አዎንታዊ ጎኖች አሉ። አሉታዊውን ትተን አዎንታዊው ላይ ማተኮር አለብን።“ ሲሉ ስለ እሴቶቻችን የሚያብራሩት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲው መምህር ዶ/ር ሮባ ጴጥሮስ ኢትዮጵያዊያን ለሕዝባቸው እና ለሉዓላዊነታቸው ሟች ናቸው። ኢትዮጵያዊው አትሌት አበበ ቢቂላ በአንድ ወቅት “አገሬ ኢትዮጵያ ሁልጊዜ በቁርጠኝነት እና በጀግንነት እንደምታሸንፍ ዓለም እንዲያውቅ እፈልጋለሁ“ ማለቱን ያስታውሳሉ። ከዚህ የአበበ ቢቂላ ንግግር ኢትዮጵያ ለነጭ ቦታ (ፊት) የማትሰጥ ቁርጠኛ አገር መሆኗን ዓለም እንዲያውቅ መፈለጉን እንረዳለን።

በባሕላዊ ተቋማት ውስጥ የተሸሸጉ እሴቶች አሉ። ደቦ፣ እድር፣ እቁብ… ከእነዚህ እሴቶች መካከል ይጠቀሳሉ። “50 ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ጌጡ“ የሚለውም ብሂል



16

ይህን እሴት ይገልጸዋል። በሶማሌ “አንድ ጣት ብቻዋን ፊት አታጥብ“ ይባላል። በአንድ ጣት መብላት፣ እጅን መታጠብ አይቻልም፤ አንድ ጣት ብቻዋን ምንም አትሰራም። ይህ አባባል አብሮነታችንን ከሚያጎለብቱ እሴቶቻችን ሌላው መገለጫ ነው።

ጥይት የሰው ልጅን እንደሚገድል ሁሉ እስክሪብቶም ትውልድ ገዳይ በመሆኑ “እስክሪብቶ ከጥይት ይበረታል“ ይባላል። እነዚህ ሁሉ አቃፊ ማንነቶች እያሉ ከአገረ መንግሥት ግንባታ ጀምሮ የተገነቡ ትርክቶች አንዱን አሸናፊ፣ ሌላውን ተሸናፊ አድርገው ስም እያወጡ ይገልጹ ነበር። ነገር ግን ከአገረ መንግሥት ግንባታ ጀምሮ ያሉ መልካም ልምምዶች ለምን ጎልተው አልወጡም? ቢባል ምላሹ “የፖለቲካ ነጋዴዎች እነዚህ መጥፎ ገጽታዎች ጎልተው እንዲወጡ ስለሰሩ ነው“ ይላሉ ዶ/ር ሮባ።

“የሚያስተሳስሩን ተዘንግተው በሚያለያዩን ላይ አትኩረናል“ ሲሉ በዚህ ሀሳብ ላይ ያላቸውን ስምምነት የሚገልጹት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ “ኢትዮጵያዊያን ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ በጋራ የምንገለጽባቸው ማንነቶች ጎልተው ወጥተው እንዲታወቁ እና ማኅበረሰቡ በባለቤትነት እንዲይዛቸው፣ እንዲጠብቃቸው እንዲንከባከባቸው ለማስቻል እንዲሰራበት እንፈልጋለን“ ብለዋል።

ሽማግሌዎች በየአካባቢው አሉን፣ እነዚህ ሽማግሌዎች ለእርቅና ለሰላም መንፈሳዊ አድባር ናቸው። አባቶቻችን ሕግና ፍትሕን፣ እርቅን በአዕምሯቸው ይዘው ይዞራሉ። በእውነት ማፈላለግ ላይ በጣም ወሳኝ ስራ ይሰራሉ። በጨለማ የተሰራን ነገር ያጋልጣሉ፤ እውነትን ሲያፈላልጉ ጎበዞች ናቸው።

ዶ/ር ሮባ ለዚህ ማሳያ ሲያቀርቡ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ “የአገር ሽማግሌዎች ጥፋት እንደፈጸመ የተጠረጠረውን ሰው ጉድጓድ ይቆፍሩና ጉድጓድ ውስጥ ይከቱታል፤ ማንም በሞት ፊት ቀርቦ የሰራውን ነገር መደበቅ አይችልም። ስለሆነም እውነቱን ይናገራል፣ ጥፋተኛ ከሆነ ጥፋተኛነቱን ያምናል። ሽማግሌዎቹም ተገቢውን ፍትሕ ይሰጣሉ“ ዶ/ር ሮባ እነዚህን የመሳሰሉት አገር በቀል እሴቶቻችን እና ልማዶቻችን ወደ ሕዝቡ ወጥተው እንዲታወቁ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል። ምክንያቱም እሴቶቻቸን የኅብረ ብሔራዊነታችን፣ የአንድነታችን መቀነቶች፤ የኢትዮጵያዊነታችን ውበት እና ድምቀቶች ናቸው።

“በትንሹም በትልቁም እንጋጫለን። የግጭቱ ምንጭ የጋራ ማንነታችን መላላት መስሎ የሚታይበት ወቅት አለ። ስለሆነም ኢትዮጵያዊያን በተለያየ መልክ፣ ቋንቋ፣ አካባቢ ውስጥ ብንኖርም የጋራ ሕልውናችን መሰረት

የሆኑ ነገሮችን ለይተን ትስስራችንን እንዲያጠብቁ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል።“ ሲሉ የችግሩን ምንጭ እና መፍትሔውን ያብራሩት የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታው “ሞት አይቀርም፣ ስም አይቀበርም“ የሚለው ኢትዮጵያዊው ብሂል ትልቅ ትርጉም እንዳለው በማውሳት፤ አባባሉ ሰው ከሕይወቱ በላይ ለስሙ እንደሚጨነቅ እና ማኅበረሰቡ ለታማኝነት የሚሰጠውን ትልቅ ቦታ የሚያመላክት መሆኑን ማሳያ ጠቅሰዋል።

“የጋራ እሴቶቻችንን በመተው በተናጠል እውነት ላይ እየታጠርን ነው። የራሱን እንጂ የጋራ የሆነው ነገራችንን የመፈለግ ባሕላችን ወርዷል፤ ሌላውን የማዳመጥ እና የመቀበል ችግር እየተስተዋለ ነው። እንደ አገር የሚያስተሳስሩን በርካታ እሴቶች ቢኖሩም እየተውናቸው፣ እየጣልናቸው ነው።“ ሲሉ ለጋራ እሴቶቻችን ትኩረት መንፈጋችንን የሰላም ሚኒስትሩ አመላክተዋል።

የጋራ የሆነውን እውነት፣ ተውን፤ የጋራ የሆነውን ፍላጎት እና ሀሳብ ማድመጥ አቆምን እኔ የምለው ብቻ ትክክል ነው ማለት ጀመርን። አንተም ጋር ጥሩ ነገር አለ፤ እኔም ጋር ጥሩ ነገር አለ። ብንደማመጥ፣ የጋራ እናደርገዋለን ብንል፣ አገር መገንባት እንችላለን። ለምሳሌ፡- እኔ ብቻ ልክ ነኝ የሚለው አስተሳሰብ የአመለካከት ችግር ነው። የሌላውስ ሀሳብ እንዴት አይደመጥም? የኔ ሀሳብ ብቻ የበላይ የሚሆነው ለምንድን ነው? ብለን ሁላችንም ራሳችንን መጠየቅ አለብን።



17



18

ለሕይወት አድን መድኃኒቶች

ማኅበራዊ

የቅድሚያ ቅድሚያ በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት እና በኢትዮጵያ ዜና

አገልግሎት ትብብር የተዘጋጀ



19

ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የያዘችውን ጤናማና አምራች ዜጋ የማየት ራዕይ ማሳካትና መምራት የሚያስችሉ የልማት ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችን እና ዕቅዶችን ነድፎ በመተግበር ሰፊ መሰረት ያለው፤ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ልማትን የማፋጠንና ድህነትን የማስወገድ ዓላማ ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል - የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት።

ጤና በዋናነት ከሚጠቀሱት የልማት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም ለአገር ዕድገትና ለኅብረተሰብ ደህንነት መረጋገጥ ወሳኝ ከሆኑት ማኅበራዊ የልማት ዘርፎች እንዲሁም፤ በአገር ደረጃ በተነደፈው የሁለተኛው የ10 ዓመት የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ ነው።

ላለፉት 75 ዓመታት አምስት ሺህ ለሚጠጉ የመንግሥት የጤና ተቋማት ብቸኛው መድኃኒት አቅራቢ ሆኖ የዘለቀው ይህ ተቋም በእነዚህ ዓመታት በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፤ በማከናወን ላይም ይገኛል። ከእነዚህ መካከል ከአገሪቷ ስፋት አንጻር ለጤና ተቋማት ወቅቱን የዋጀ የአቅርቦት ሰንሰለት ሥርዓት መዘርጋት ዋነኛው ነው።

የቅድሚያ ቅድሚያ በየሺመቤት ደመቀ



20

አገልግሎቱ የመድኃኒት አቅርቦቱን በሁለት መልኩ ይከውናል። አንደኛው በጤና ሚኒስቴር ጥያቄ ለጋሽ አካላት የሚያመጡትና አገልግሎቱ ለዜጎች በነፃ የሚያቀርባቸው የቲቢ፣ የወባ እና የኤች አይ ቪ/ኤድስ መድኃኒቶች የተካተቱበት ሲሆን ሌላው ደግሞ የመድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት በጀት ይዞ በመግዛት ወጪውን በሚሸፍን የተወሰነ ትርፍ ለሽያጭ የሚያቀርብበት አግባብ ነው።

የመድኃኒት አቅርቦት ስራ ትልቅ ቴክኖሎጂ ይፈልጋል የሚሉት የአገልግሎቱ የግዥ አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ንጉሴ በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት የመድኃኒት አቅርቦት ስራውን ከ70 በመቶ በላይ ማሳካቱንና በቀጣይም በአዋጅ የተቋቋመበትን ዓላማ መሉ በሙሉ ለማሳካት እየተሰራ እንደሆነ ይናገራሉ።

ከመድኃኒት ልየታ የሚጀምረው የመድኃኒት ግዥ ሥርዓት የልየታ ስራው ከተገልጋዩ ጋር በጋራ የሚከናወን ነው። የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ባለፉት ሦስት ዓመታት ይህንኑ ስራውን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የሚገዙ መድኃኒቶችን ዝርዝር አዘጋጅቷል። በዚህም ከሦስት ዓመት በፊት 1 ሺህ 270፣ ባለፈው ዓመት 1 ሺህ 20 እና በተያዘው ዓመት 877 መድኃኒቶችን በመዘርዝር ይዟል።

አቶ ሰለሞን የሚለዩ መድኃኒቶች ቁጥር እያነሰ የመጣበትን ምክንያት ትኩረት ማድረግ እና የዜጎች የጤና ችግር ለሆነው የሕክምና አገልግሎት የሚውሉ ዋና ዋና መድኃኒቶች ማካተት ስለሚያስፈልግ ነው ሲሉ ያብራራሉ።

ከእነዚህ መድኃኒቶች አብዛኞቹ ከውጭ አገራት የሚገቡ ናቸው። መንግሥት የአገር ውስጥ አቅርቦቱን ለማሻሻል እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ እንዳለ ሆኖ ባለፉት ዓመታት ግን የአገር ውስጥ ድርሻ እየቀነሰ ነው። ባለፈው ዓመት የአገር ውስጥ ድርሻ ከስምንት በመቶ ያልበለጠ ነበር። አጠቃላይ ሁኔታው ሲታይ በቂ አቅራቢ ያላቸው መድኃኒቶች 29 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው። እነዚህ የግዥ ኤጀንሲ ባወጣው መመሪያ እና መስፈርት መሰረት አምስት እና ከዚያ በላይ አቅራቢ አላቸው ማለት ነው። የተቀሩት መድኃኒቶች ውስን አቅራቢና ምንም አቅራቢ የሌላቸው ናቸው። በአንድ በኩል በአገር ውስጥ መድኃኒት አይመረትም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከውጭም አቅራቢ የላቸውም ማለት ነው። ይህን

ተግዳሮት ለመፍታት አገልግሎቱ የአገር ውስጥ አምራቾችን እንዲሁም የውጭ አቅራቢዎችን መልካም ዕድሎችን ተጠቀሙና አብረን እንስራ ሲል ጥሪ እያቀረበ ይገኛል።

በመድኃኒት አቅርቦት ሥርዓት ውስጥ ትልቁን ሚና የሚጫወተው የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ቢሆንም የሽግግር ዕቅዱ /Phar- maceutical supply transformation plan በእሱ ብቻ የሚሳካ አይደለም፤ ከዚህ አኳያ ዘመናዊ የግዥ ሥርዓት መተግበር፣ አገልግሎትን ማቀላጠፍ፣ በቴክኖሎጂ የማገዝ ዋና ዋና ዓላማዎች አሉ።

አገልግሎቱ መድኃኒት ያቀርባል ማለት ዜጎች መቶ በመቶ መድኃኒት ያገኛሉ ማለት አይደለም። የመድኃኒት አቅርቦት አስተዳደር ሰንሰለት ነው፤ ሚና ያላቸው አካላት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል። ለአብነት ከመድኃኒት ግዥ ጀምሮ እስከ ጤና ተቋም ድረስ ያለው የመረጃ ሥርዓት መጠናከር አለበት። የጤና ተቋማት መድኃኒት የመጠየቅ፣ ሪፖርት የማድረግ፤ መደበኛ መድኃኒት ከሆነ በቂ በጀት የመያዝና ግዥ የመፈጸም ስራዎች መቀላጠፍ አለባቸው። ከዚህ አንጻር ክፍተቶች አሉ፤ የመረጃ ሥርዓትን ማጠናከር ያስፈልጋል።

አገልግሎቱ ተደራሽነቱን ለማረጋገጥ 19 ቅርንጫፎች አሉት፤ በእነዚህ ስር ያሉ የጤና ተቋማት ደግሞ ያላቸው ቅንጅት የላላ ነው፤ ይህ ጠንካራ መሆን አለበት። የወባ መድኃኒትን ብንወስድ ባለፉት ጥቂት ወራት ወደ 570 ሺህ አካባቢ የወባ ታካሚ ቁጥር አለ፤ ሪፖርቱ ጉድለት ሊኖርበት መቻሉ እንዳለ ሆኖ ሦስት እጥፍ የሚሆን መድኃኒት ደግሞ ለጤና ተቋማት ተሰራጭቷል። አሁንም ግን ዜጎች የወባ መድኃኒት እጥረት እየገጠማቸው ነው፤ እዚህ አካባቢ መናበብ ያስፈልጋል፣ ክትትል ያስፈልጋል። ይህ ለጤናው ዘርፍ እንደተሰጠው አይነት ትኩረት ለመድኃኒት አቅርቦትም በዚያው መጠን ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ማሳያ ነው።

የአሥር ዓመት ዕቅዳችንን በሦስት ከፍለን እየሰራን ነው የመጀመሪያውን ሦስት ዓመት ጨርሰናል ሰባቱ ዓመት የሚሆነው ከአፍሪካ ፈጣን ምላሽ ሰጪ የሆነ የመድኃኒት አቅርቦት ሥርዓት መዘርጋት ነው፤ ይህንን እንደ ራዕይ ይዘን እየሰራን ነው። ተልዕኳችን ተደራሽነትን



21



22

ማረጋገጥ፣ በተመጣጣኝ ዋጋ ቀጣይነት ባለው አግባብ ማድረስ ነውና ለዚህ የሁሉም አካላት ሚና ትልቅ ነው።

የአቅርቦት ሰንሰለቱ ዋና ዋና ችግሮች…

የአገር ውስጥ የመድኃኒት ምርት በጣም አነስተኛ ነው የሚሉት አቶ ሰለሞን ምክንያቶቹን ሲገልጹ “በአገራችን ሳቢ የሆነ ኢንቨስትመንት ፖሊሲ የለም እንዳይባል አለ፤ በተለይ የኢንቨስትመንት ፖሊሲያችን ከሌሎች አገራት ያነሰ አይደለም ይልቁንም ከአንዳንዶቹ የተሻለ ነው። እንደ ማሳያ የፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ ሲባል የራሱ የኢንዱስትሪ ፓርክ ተዘጋጅቷል። ይህም ብቻ አይደለም የአገር ውስጥ ገቢ፣ የታክስና የግዥ ሥርዓቱም ቅድሚያ ለአገር ውስጥ ይሰጣል። በአገር ውስጥ ለሚመረቱ መድኃኒቶች እስከ 25 በመቶ የዋጋ ከለላ አለ፤ ይህ ከውጭ ከሚገቡት ጋር ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ ነው”።

ይህም ሆኖ ግን አሁንም ችግሮች አሉ። የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በተናጠል እና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመስራት፤ ጤና ሚኒስቴርም እንደ ዋነኛ ባለቤት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ሰፊ ውይይቶችና ምክክሮች ተካሂደዋል። በዚህም ሰፊው እና ትልቁ የመድኃኒት አቅርቦት ተግዳሮት ተደርጎ

የተወሰደው የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ችግር ነው። ምንም እንኳን መድኃኒቶች በአገር ውስጥ ይመረቱ ቢባልም ጥሬ ዕቃው የሚመጣው ከውጭ ነው። እናም የዶላር አቅርቦት በሌለበት የጥሬ ዕቃው ግዥ የማይታሰብ በመሆኑ ዕቅዱን ከምኞት የማያልፍ እንዲሆን አድርጎታል።

ይህ ለዜጎች ጤና ቁልፍ የሆነ ጉዳይ በሚመለከታቸው አካላት ሊደገፍ ይገባል። የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎቱ “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” እንዲሉ እንደ ግዥ ተቋም ከውጭም ይግባ በአገር ውስጥም ይመረት ስራው መድኃኒት መግዛትና ማቅረብ ነው። ይሁንና እዚህ ላይ ያለውን አጋርነት እና ሚና በመጫወት በአጠቃላይ ለአገሪቷ ከሚያስፈልገው የመድኃኒት አቅርቦት 60 በመቶው በአገር ውስጥ እንዲመረት ለማድረግ የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተደጋጋሚ ውይይት በማድረግ ዋነኛው የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ችግር እንዲፈታ ውሳኔ ተላልፏል። ይህም መድኃኒቱ ያለው ጠቀሜታ እና የሚጨምረውን እሴት መሰረት የሚያደርግ 55 በመቶ ድረስ የጥሬ ዕቃ መግዣቸውን በዶላር የማመቻቸት ኃላፊነት በዋናነት የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ጋር በመሆን እየሰራ ይገኛል። በዚህም ከዚህ ቀደም በአገር



23



24

ውስጥ ማምረት ያልተቻሉ ሁሉንም መድኃኒቶች ጨምሮ ከመቶ በላይ የመድኃኒት አይነቶችን ለማምረት ከአምራቾች እና ከማኅበራቸው ጋር እየተሰራ ይገኛል። እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ ይህ ከሆነ እና ከውጭ ያለውን የመድኃኒት አቅርቦት መሰረት ማስፋት ከተቻለ ችግሩን በሂደት መፍታት ይቻላል። በቀጣዩ ዓመትም አሳሳቢውን የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት የሚያቃልል እመርታዊ ለውጥ ይመጣል።

እንደ አጠቃላይ አሁን ያለው የመድኃኒት አቅርቦት ደረጃ እንደየመድኃኒቱ አይነት የሚለይ ነው የሚሆነው። በጤና ፕሮግራም የኤች. አይ.ቪ፣ የቲቢ… መድኃኒቶች ሰው ሰራሽ ችግር ካልሆነ በቀር የአቅርቦት ችግር የለባቸውም። ነገር ግን በመደበኛ መድኃኒቶች ላይ አሁንም የፋይናንስ ችግር አለ። ይህም ችግር ሁለት መልክ አለው፤ አንደኛው የጤና ተቋማት የራሳቸውን በጀት ይዘውና የሚፈልጉትን መድኃኒት በግልጽ አስቀምጠው የመግዛት ሲሆን ሌላው አገልግሎቱ ራሱ ባስቀመጠው የክምችት መጠን መሰረት ሁሉንም መድኃኒቶች ለመግዛት የሚያጋጥመው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ነው። ያም ሆኖ በጤና አገልግሎቱ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያላቸው መሰረታዊና ሕይወት አድን የሆኑት የደም ግፊት፣ የስኳር፣ የአዕምሮ ጤና… መድኃኒቶች ግን የውጭ አቅራቢም ስለሌላቸውና ትኩረት የተሰጣቸው በመሆኑ የአቅርቦት ችግር የለም። ሌሎቹ ላይ ግን የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በመለየት ማቅረብ ያስፈልጋል። ሁሉንም ማቅረብ ቢቻል ጥሩ ቢሆንም የማይቻልባቸው ምክንያቶች

ግን ብዙ ናቸው፤ ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል አሁንም ዋነኛው የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ችግር ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፖሊሲ በግልፅ እንዳስቀመጠው የመድኃኒት ግዥ የቅድሚያ ቅድሚያ ከተሰጣቸው መዘርዝሮች ተርታ ነው። ስለሆነም በሂደት የሚፈቱት እንዳሉ ሆነው የመድኃኒት አቅርቦት የሕይወት ጉዳይ ነውና የቅድሚያ ቅድሚያ የመስጠቱን ስራ መተግበር ለነገ የሚባል አይደለም። ትልቁ መፍትሄ ትልቁን የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ችግር መፍታት ነው።

ሌላው መፍትሄ…

“ከአቅራቢዎቻችን ጋር መወያየት፣ ከሌሎች ባለድርሻ አካላትም ጋር መምከር ያስፈልጋል” በመስከረም 2016 አጋማሽ በአዲስ አበባ የተካሄደው 3ኛው ዓለም አቀፍ የሕክምና ግብዓት አቅራቢዎች ጉባዔ ዓላማም ይኸው ነው። በአቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ የሌሉ ዋናዋና መድኃኒቶችን አቅርቦት ለማግኘት እና በአገር ውስጥ የመድኃኒትና የሕክምና መሣሪዎች አምራቾችን መፍጠር፤ ብሎም አዳዲስ አምራቾች እንዲመጡና በዘርፉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ማድረግ።

ኢትዮጵያ ከኢንቨስትመንት አንጻር የኢንቨስትመንት ፖሊሲ አላት፤ ከመሬት ታክስ አላት፤ ከግዥ አንጻር ግን አገር ውስጥ የሚመረት መድኃኒት እስከ 25 በመቶ የዋጋ ልዩነት አለው። ይህም ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረተው መድኃኒት 35 በመቶ እና ከዚያ በላይ እሴት ጨምሮ የተመረተ ከሆነ ኢትዮጵያዊ

ምርት ተብሎ ይገለጻል። ከውጭ ከሚመጣው መድኃኒት ጋር በግዥ ውድድር በሚደረግበት ጊዜ 25 በመቶ የዋጋ ልዩነት ቢኖረውም እንኳን መንግሥት እሱን እገዛለሁ እያለ ነው። የዚህ ፖሊሲ አቅጣጫ በራስ አቅም ራስን መቻል ነው። ጤነኛ ዜጋ ማፍራት ለሚለው የተሻለ ተደራሽ፣ የተሻለ አቅርቦት የሚኖረው ራሳችን መድኃኒት ስናመርት ነው። መንግሥት በፖሊሲ፣ በአዋጅ ደንግጎ እስከ 25 በመቶ የዋጋ ልዩነት ቢኖርም እንኳ ከፍሎ ለመግዛት እየሰራ ቢሆንም ቅሉ በአፈጻጸም እንደሚታየው አብዛኛዎቹ አገር ውስጥ የሚመረቱት እሴት የሚጨምሩት የሚያደርጉት ከ35 በመቶ በታች ስለሆነ ይህንን ፖሊሲ እየተጠቀሙበት አይደለም።

አዲስ እየተሻሻለ ባለው አዋጅ ይህንን ለማሻሻል ዝግጅት ተደርጓል። ገንዘብ ሚኒስቴር እንደየሴክተሩ በተለያየ ጊዜ የሚያሻሽለው ሆኖ ከ35 በመቶ ዝቅ ብሎ እንዲጀምርና የአገር ውስጥ አምራቾች በዚህ ተደግፈው ራስን ወደ መቻል እንዲወስዱን፤ ጤነኛ ማኅበረሰብ በመፍጠር የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እየተሰራ ነው፤ በዚህ ረገድ መንግሥት ፖሊሲውን ለማስተካከል ብዙ ቢሄድም ስራ ላይ ግን አልዋለም።

በአንፃሩ መካሄድ ከጀመረ ሦስተኛ ዓመቱን የያዘው ይህ ጉባዔ ባለፉት ዓመታት ያመጣውን ለውጥ ብንመለከት ከምናቀርባቸው መድኃኒቶች በቂ አቅራቢ የነበራቸው ከ20 በመቶ የማይበልጡ የነበሩ ሲሆን አሁን ቢያንስ በአሥር በመቶ ማሳደግ ችሏል። ነገር ግን አሁንም



25

በቂ አቅርቦት እንዲኖር በተለይ ትላልቅ ገበያ ያላቸው ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ለመስራት ግልጽ የሆነ ነገር የሌላቸውን ተቋማት ጭምር ይጋብዛል። ያለውን ግንኙነት ማጠናከር፣ አዳዲሶችን ኢንቨስት እንዲያደርጉ መሳብ፣ የአገሪቷ ኢንቨስትመንት ፖሊሲ ምን ይመስላል የሚለውን ማሳየት ያስፈልጋል። ለንግድም ለአገልግሎት መስጫም በቂ የሆኑ ቅንጅታዊ ስራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግ ማሳየትም እንዲሁ። በዘንድሮው ጉባዔ ላይ የቀረበውም ገለፃ አንዱ ይህ ነው። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ትኩረት ምንድን ነው? የሚለውን ጭምር ለማቅረብ ተሞክሯል። በዚህም ብዙዎቹ አገር ውስጥ መጥተው ለማምረት ፍላጎታቸውን እያሳዩ ይገኛሉ። ጉባዔውን የተወሰኑት አቅራቢዎች በአካል፣ ገሚሱ በተወካዮቻቸው አማካኝነት ቀሪዎቹ ደግሞ በያሉበት አገር ሆነው ተሳትፈዋል።

አገልግሎቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት…

የኅብረተሰቡን ጤና ለማሻሻል የሚያግዙ የመድኃኒት እና የሕክምና መገልገያዎችን ማቅረብ እንዲያስችለው የአቅርቦት ሰንሰለት አስተዳደሩን በማዘመንና በማጠናከር በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት ለጤና አገልግሎቱ የሚያስፈልጉ ጥራታቸው፣ ፈዋሽነታቸው እና ደህንነታቸው የተረጋገጡ መሰረታዊ መድኃኒቶችንና የሕክምና መገልገያዎችን በበቂ መጠን፤ በተመጣጣኝ ዋጋ እና ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማቅረብ የ2014 በጀት ዓመት አፈፃፀሙን በየደረጃው በመገምገም የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን ለማስቀጠል፤ ደካማ አፈጻጸሞችን ለማረም የሚያስችሉ መፍትሄዎችን በመለየትና ለበጀት ዓመቱ ዕቅድ በግብዓትነት በመውሰድ ነው ወደ ትግበራ የገባው። የጤና ተቋማትን ፍላጎት ለማሟላት በ2015 በጀት ዓመት ከ41,656,678

ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን የመድኃኒት፣ የኬሚካል እና ሪኤጀንቶት፤ የሕክምና መገልገያና መሣሪያዎችን በግዥና በዕርዳታ ወደ መጋዘን እንዲገቡ ያደረገ ሲሆን 37,159,508,754.53 ብር ዋጋ ያላቸው የመደበኛ እና የጤና ኘሮግራም መድኃኒቶች፣ ሪኤጀንቶች፣ የሕክምና መገልገያዎችና መሳሪያዎች ለጤና ተቋማት ተሰራጭተዋል።

አገልግሎቱ በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል በነበረው ግጭት ጉዳት ለደረሰባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች አገልግሎት የሚውሉ መድኃኒቶች፣ የሕክምና መሳሪያዎች እና የሕክምና መገልገያዎች የፀጥታ ችግር በነበረባቸው አካባቢዎች ጭምር ማሰራጨት ችሏል። በዚህ ረገድ በትግራይ ክልል በግጭቱ ወቅት በተለያዩ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች በኩል እንዲሁም የሰላም ስምምነት ከተደረገ በኋላም አገልግሎቱ በራሱ የሕክምና ግብዓቶች እንዲሰራጩ አድርጓል።



26

ማህበራዊ

ንድፈ ሃሳብን ከተግባር

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ እና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ትብብር የተዘጋጀ



27

ንድፈ ሃሳብን ከተግባር

መግቢያ

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ሦስት መሰረታዊ ምሰሶዎች አሉት። መማር ማስተማር፣ ምርምርና ስርጸት (ለኅብረተሰቡ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ ማድረግ) እና የማኅበረሰብ ተሳትፎ ስራዎችን ማከናወን። ዩኒቨርሲቲው እነዚህን አገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ተግባራት ከምስረታው ጀምሮ ሲያከናውናቸው እስከአሁን ዘልቋል። አሁን ደግሞ እነዚህን ተግባራቱን በተለየና በተጠናከረ መንገድ መከወን የሚያስችሉትን ስትራቴጂዎችና

ስልቶች በመንደፍ በመተግበር ላይ ይገኛል። ከዚህ የአሰራር ሥርዓቱ አኳያ በዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት የሚመራው የማኅበረሰብ አገልግሎትና ኢንተርፕራይዝ ልማት ተጠቃሽ ነው።

ይህ ዘርፍ በርካታ ተግባራት አሉት። የኢንተርፕራይዝ ዳይሬክተር፣ የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር፣ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ሊንኬጅ እና ኢንተርፕረነርሺፕ ዳይሬክተር፣ የተቀናጀ የሐረማያ ሐይቅ ተፋሰስ ጽሕፈት ቤትም ይገኛሉ።

ማኅበረሰብ ተኮር በሆኑት በግብርና ውጤታማነት፣ በትምህርት ጥራት፣ በተፈጥሮ ሀብት፣ በሕግ

በጌታቸው ሠናይ



28

አገልግሎት፣ በጤና እና በተለያዩ የመሰረተ ልማቶች ላይ እየሰራ ይገኛል። ዩኒቨርሲቲና ኢንዱስትሪዎችን በማያያዝ የኢንዱስትሪዎችን ችግር በጋራ ለመፍታት ይንቀሳቀሳል። ተማሪዎች አብረው የሚሰሩበትን ሁኔታዎች ያመቻቻል። ይህን ዘርፍ የሚመሩት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ይስሀቅ የሱፍ የሰጡት ማብራሪያ እንዲህ ቀርቧል።

የኢንተርፕራይዝ ልማት አስፈላጊነት

ኢንተርፕራይዝ የተሻሻሉ ምርጥ ዝርያዎች የሚባዙበት አንዱ ማዕከል ነው። በተገቢው መንገድና በጥንቃቄ የተባዙት ምርጥ ዘሮች ለማኅበረሰቡ በሁለት መልኩ እንዲደርሱ ይደረጋል። አንደኛው ራሳቸውን ሳይችሉ የቆዩና ተደራጅተው ሥራ በመስራት ኑሯቸውንና አካባቢያቸውን መለወጥ ለሚፈልጉ ወጣቶችና አርሶ አደሮች ድጋፍ የሚደረግበት ነው። ሁለተኛው አቅም ያላቸውና ምርጥ ዘሮቹን በመግዛት ቴክኖሎጂውን መጠቀም ለሚችሉ አካላት የሚዳረስበት መንገድ ነው።

ከግብርና አኳያ በርካታ አስተዋጽኦ እየተደረገ ይገኛል። ከአገሪቷ ከፍተኛ ሀብት አንዱ

የእንሰሳት ሀብት። ግብርና ስንል ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። የኢትዮጵያ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው ዝቅተኛ መሬት (Lowland) ነው። የግጦሽ መሬት በብዛት ይስተዋላል። ይህም ለቤት እንስሳት እርባታ ሰፊ ድርሻ አለው። ዩኒቨርሲቲው በዝቅተኛ መሬት ያለውን የእንስሳት ሀብትና እድል ለመጠቀም የሚያስችል ምርምርና ጥናት በማካሄድና የጥናቱን ውጤት በማጋራት ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የማድረግ ስራዎች ሲያከናውን ቆይቷል። በሌሎችም መልክዓ ምድር የሚገኙትን በማጥናት የሰብል ምርጥ ዘር በማውጣት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ የሚችሉ ስራዎችን አከናውኗል።

ዩኒቨርሲቲው በ1948 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹን 11 ተማሪዎች ተቀብሎ ትምህርት መስጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለአገር ፋይዳ ያላቸውን የምርምር ተግባራት አከናውኗል። በተለይም ከተፈጥሮ ጋር የተሳሰሩ ዕውቀቶችን፣ ቴክኖሎጂዎችን፣ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎችን ማፍለቅና ማስተላለፍ መቻሉ እንደ አንድ ጠንካራ ስኬት ይታያል። ኢትዮጵያ በግብርና ምርምር ያላት አቅም እንዲጎለብት፣



29

ጠንካራ የምርምር ሥርዓት እንዲኖራት ከመጀመሪያው ጀምሮ ሲሰራና ሲያስተባብር መቆየቱ መጪውን ዘመን በራሱ መንገድ ቢቀጥል እጅግ የላቀ ውጤት ማስመዝገብ የሚያስችለው ልምድ ማካበቱን ያመላክታል።

ለኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ዕድገት የራሱን ታላቅ አሻራ ማስቀመጡም የሚዘነጋ አይደለም። በግብርና በኩል በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመጥር ተመራማሪዎችንና ሳይንቲስቶችን አፍርቷል።

ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት በኢንተርፕራይዝ ልማት ዘርፍ በኩል አሰራሩን እያዘመነና እያሰፋ በመምጣት ላይ ይገኛል። ከእነዚህ መካከል አንዱ እንስሳት ሳይንስ ዲፓርትመንት ነው። በዲፓርትመንቱ ሁለት የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ስድስት ማስተር፣ አራት ፒኤችዲ መርሃ ግብሮች አሉት። እነዚህ መርሃ ግብሮች ውጤታማ እንዲሆኑ ንድፈ ሃሳብን ከተግባር የሚያጣምሩ ሰፊ የእርሻ ቦታ፤ የወተት ላሞች፣ ፍየሎች፣ በጎች፣ አሳማዎች፣ ዶሮ ማርቢያና የከብቶች ማድለቢያ ቦታዎች አሉት። እነዚህ ለመማር ማስተማር፣ ለምርምር እና ለማኅበረሰብ አገልግሎት እንዲውሉ በማድረግ የተሻሉ ዝርያዎችን ማባዣ ማዕከሎች ሆነው እያገለገሉ ናቸው።

የዩኒቨርሲቲዎች ራስን መቻል ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸውን ለመቻል የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ስራዎችን ያከናውናሉ። በዚህም ዩኒቨርሲቲው የተወሰነውን ወጪ ለመሸፈንና

ራሱን ለመቻል እየሰራ ይገኛል። ለዚህ ኢንተርፕራይዝ ሁለት ጥቅሞች አሉት። አንደኛው የእንስሳት ተዋጽኦዎችን በማምረት፣ ሕብረተሰቡን በማይጎዳ ዋጋ በመሸጥ ለዩኒቨርሲቲው ትርፍ ማስገኘት ነው። ወተት እስከ ቅርብ ጊዜ በሊትር 25 ብር ይሸጥ ነበር። በርግጥ በአካባቢው ያለው ገበያ ስድሳ ብር ሲያስገባ ተቋሙም ወደ 40 ብር ከፍ አድርጎታል።

ዩኒቨርሲቲው በትንሹ ትርፍ ማግኘት መቻሉ ለራሱ መቋቋሚያ ይረዳዋል። በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው አንድ እርምጃ ወደፊት በመራመድ ፍቃድ በማውጣትና ቅጥር ግቢው ውስጥ ብቻ ሳይሆን ሌሎች አካባቢዎችም የንግድ እንቅስቃሴ በማድረግ ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ አቅዷል። ይህም ለዩኒቨርሲቲው ስራ ማስኬጃ ማግኘት የሚያስችለው ይሆናል።

ዩኒቨርሲቲው ደረጃውን የጠበቀ ትልቅ ተሽከርካሪ ማደሻ (Garage) እየተሰራለት ነው። ጠንከር ያለ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይታመናል። በአገራችን ትልልቅ ተቋማት ሲኖሩ ዋጋን ማረጋጋት ይችላሉ። አንድ አገልግሎት የሚሰጥ ዘርፍ መቶ በመቶ ለግለሰቦች ሲሰጥ ትርፍ ላይ ብቻ ያተኩሩና ማኅበረሰቡ ላይ ዋጋ ይጨምራሉ። ለዚህ ነው ኢንተርፕራይዝ ማኅበረሰቡን ማዕከል ያደረገ ስራ ስለሚሰራ የመቋቋሙ ጥቅም ከፍተኛ ነው የሚባለው። የውጪውን ገበያ በማረጋጋት ለራሱ ትርፍ ማግኘት ይችላል።

ለኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ዕድገት የራሱን ታላቅ አሻራ

ማስቀመጡም የሚዘነጋ አይደለም። በግብርና

በኩል በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመጥር ተመራማሪዎችንና

ሳይንቲስቶችን አፍርቷል።



30

ተማሪዎች ሲመረቁ ስለ ኢንተርፕራይዝ ማወቅ አለባቸው። እንደቀደመው ጊዜ “የመንግሥት ሰራተኛ እሆናለሁ” ብለው ማሰብ የለባቸውም። በአፍሪካ አንድ ጥናት ተሰርቶ ነበር። በጥናቱ ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ከሚመረቁ ተማሪዎች አብዛኛዎቹ የመንግሥት ሰራተኛ የመሆን ምኞት እንዳላቸው ታይቷል።

አዳዲስ የሰብልና የእንስሳት ምርጥ ዘሮችን በተለያዩ መልኮች የሚያመነጨው ተቋሙ አዲስ ቴክኖሎጂ ወደ ኅብረተሰቡ ይዞ ከመውጣቱ በፊት “ምን ዓይነት ተጽዕኖ ይኖረዋል?” ሲል ይመረምራል። በመጀመሪያ በተቋሙ ውስጥ ይሞከራል። ለአርሶ አደሩ ማቅረብ እንዲቻል “ምን ምን ግብዓቶች ቢያሟሉ የተሻለ ውጤት ያስገኛል?” ተብሎ ይጠየቃል። ኢንተርፕራይዙ የቴክኖሎጂ ማራቢያ መንገድ፤ ለተቋሙም ትርፍ ማግኛ ስልት ነው። የአካባቢውን ገበያ ማረጋጊያ ተደርጎም ይወሰዳል።

በአሁኑ ወቅት 89 ዓለምአቀፍ ፕሮጀክቶች አሉ። እነዚህ ፕሮጀክቶች በአንድም ሆነ በሌላ

መልኩ የኅብረተሰቡን ችግር ለመፍታት የሚሰሩ ናቸው። በየሩብ ዓመቱ የዳሰሳ ጥናት ይደረጋል። ቴክኖሎጂዎቹ የተሰጡት በሰዓቱ ነው? እጥረታቸው ምንድን ነው? ኅብረተሰቡ እንዴት አያቸው የሚለውን ግምገማ እናደርጋለን። ሁሌም ቴክኖሎጂ ስንሰጥ ጥያቄው ከማኅበረሰቡ ይነሳል። ለማኅበረሰቡ የሚቀርቡት ችግሮችን መሰረት በማድረግ ነው። በተደረገው የተጽዕኖ ፈጣሪነት የዳሰሳ ጥናት በየዓመቱ ከ80 በመቶ በላይ ውጤት ተገኝቷል።

ንድፈ ሃሳብ በተግባር ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ያገኙትን የንድፈ ሃሳብ እውቀት በተግባር የሚመራመሩበት ነው። የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ደግሞ በከብቶች፣ በዶሮዎች፣ በፍየልና በጎች ላይ ምርምር በማድረግ ውጤታማ ስራዎችን የሚያካሂዱበት፤ ለአገር ጠቃሚ የሆኑ የምርምር ግኝቶችን የሚያገኙበት ነው።

ለአብነት የወተት ላም እርባታ በቀን 500 ሊትር

ወተት ያመርታል። የወተት ምርቱን በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ይቀርባል። የተሻሻለ ምርት የሚሰጡ ጊደሮችን በማውጣት አቅም ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በተመጣጣኝ ዋጋ በግዥ እያቀረበ ይገኛል። አቅም ለሌላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ በድጋፍ ይሰጣል። በአካባቢው የወተት ላሞችና ጊደሮች የአቅርቦት ጥያቄ በጣም ከፍተኛ ነው። ሆኖም በአገራችን የጊደሮች አቅርቦት ዝቅተኛ ነው። በዚህ መሠረት አሁን ያለውን ፍላጎት ለማሟላት አዳጋች ሲሆን ይስተዋላል።

ዩኒቨርሲቲው በቀን 500 ሊትር ወተት በማምረት ለግቢውና ለውጪው ተጠቃሚ ማኅበረሰብ እንዲውል ያደርጋል። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተፈጠረ ያለውን የወተት እጥረት ለማቃለል የ64 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ተቀርፆ ወደ ስራ ተገብቷል። ይህ ፕሮጀክት እንዲሳካ የተለያዩ ተቋማትና የመንግሥት አካላትን ድጋፍ ይጠይቃል።

ዩኒቨርሲቲው አጽንኦት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች



31

መካከል ተማሪዎች በንድፈ ሃሳብ ብቻ ታንጸው መውጣት የለባቸውም፤ ጥበቡን መያዝ ይኖርባቸዋል፤ ይህ ተማሪዎች አንድ የተግባር ልምምድ የሚያደርጉበት መስክ ነው፤ የሚሉት ይጠቀሳሉ። ትምህርታቸው በሳምንት ሦስት ሰዓት (ክሬዲት) ከሆነ ሁለቱ ንድፈ ሃሳብ፣ አንዱ የተግባር ልምምድ ይሆናል። በመሰረቱ ንድፈ ሃሳብ ብቻ ሲሆን ነገሮችን ውጭ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ማገናዘብ ሊከብድ ይችላል።

በዩኒቨርስቲው የእንሰሳትና የሰብል ልማት እንዲሁም የኢኮኖሚክስና ቢዝነስ ዘርፎች የተግባር ልምምድ የሚካሄድባቸው መስኮች ናቸው። ተማሪው የማኅበረሰቡን ችግር ተረድቶ ለመፍታት እንዲንቀሳቀስ በማንኛውም ሙያ ሲሰለጥን የተግባር ልምምድ ያደርጋል። ለአብነት በጤና፣ በሕግ …. እንደ ሙያው ዓይነት ወጥቶ ይሰራል። የሕግ ተማሪዎች በሳምንት ሁለት ቀናት ወደ ኅብረተሰቡ በመቅረብ የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱበትን የተግባር ልምምድ ያደርጋሉ። ገና ከጅምሩ የማኅበረሰቡን

ችግር መገንዘብ የሚችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል ማለት ነው። የዚህ ዓይነቱ የተግባር ልምምድ በትምህርት ከቀሰሙት ንድፈ ሃሳብ ጋር አገናዝበው ችግሩን ለመፍታት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። የማኅበረሰቡ ችግሮች ሰፊ ናቸው። ገንዘብ፣ ጊዜና ጉልበት ይፈልጋሉ። ያደጉት አገራት ከእኛ የሚሻሉት ማኅበረሰቡ በእርሻ ዘርፍ ያለበትን ችግር ተደራጅተው ለመፍታት በመቻላቸው ነው። በሌላው አገር ገበሬ ሀብታም ነው። ኢንተርፕራይዙ ለወጣቶች አንድ የተግባር መለማመጃ ቦታ ነው። ከዩኒቨርሲቲው ለተግባር ልምምድ ሲላኩ እዚያው የሚቀጠሩበት ሁኔታም አለ።

ዶሮዎች እንቁላል ይጥላሉ፣ የወተት ላሞች ይታለባሉ። ተማሪዎች ይማሩባቸዋል። የዶሮ እርባታ ላይ በየዓመቱ ከስድስት እስከ 10 የሚሆኑ የፒኤችዲ እና የኤምኤስሲ ተማሪዎች ጥናት ይሰራሉ። የወተት ላሞች እርባታ፣ የከብቶች ማድለቢያ ላይም ይሰራሉ። ተሞክሮ ውጤታማ ሲሆን ወደ ኅብረተሰቡ ይቀርባል። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢንተርፕራይዞች ለማስተማርም ለምርምርም አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ኢንተርፕራይዝ ጥቅሙ በጣም ሰፊ ነው።

የዩኒቨርሲቲው የከብቶች ማድለቢያ ማዕከል በርካታ ተግባራት አሉት። ለተማሪዎች አገልግሎት፣ ለሥጋ አቅርቦት የሚውሉ ከብቶችን በማድለብ ለሽያጭና ለዩኒቨርሲቲው ያቀርባል። አንዳንዴም ተቋሙ ከብቶች ገዝቶ በማድለብ ለማኅበረሰቡ እንዲደርሱ ያደርጋል። ይህም ብቻ አይደለም የተደራጁ ወጣቶች የሚደገፉበትም አንዱ ስልት ነው። ባለፉት ሦስት ዓመታት ለተደራጁ 50 ወጣቶችና ለ800 ግለሰቦች ድጋፍ ተደርጓል። በተቋሙ የተደረገው ድጋፍ በገንዘብ 30 ሚሊዮን ብር ይሆናል። ከእርሻው ጋር የተያያዙ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ምርጥ ዘሮች ውስጥ ከ20 እስከ 25 በመቶው የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ውጤቶች ናቸው። በተጨማሪም የሰብል ምርት ለማሻሻልና ውጤታቸው ከፍተኛ የሚሆን ዝርያዎችን ለማግኘት ታላላቅ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። እንዲሁም የዶሮ እርባታ ጣቢያችን እንቁላል ለሕብረተሰቡ ቀጥታ ያቀርባል። በአካባቢው ለሚገኙ ሴት አርሶ አደሮች በተለይ ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ የዶሮዎች አቅርቦት ያደርጋል። በዓመት ሦስት ሺህ ያህል ዶሮዎችን ለማኅበረሰቡ ያደርሳል።



32

ዩኒቨርሲቲው ንብ ማነቢያም አለው። በየዓመቱ ከ25 እስከ 30 ያህል የንብ ቀፎ ከንብ ጋር ለአርሶ አደሩ ድጋፍ ያደርጋል። የእንስሳት መኖ ከእርባታ ሥራው 60 በመቶ ያህሉን ወጪ ይወስዳል። ትልቁ ወጪ መኖ ነው። ይህን ወጪ መቀነስ ከተቻለ “ትርፍ ይጨምራል” ማለት ነው።

በአገር ደረጃ ከግጦሽ መሬት የሚገኘው የእንሰሳት መኖ ምርት በሄክታር አንድ ቶንና በታች ነው። የተሻለ ምርት የሚሰጡ የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮች በሄክታር እስከ 20 ቶን ውጤት ሊያስገኙ ይችላሉ። በዚህ ሁኔታ የእንስሳት መኖ ማምረት ይቻላል። አምና ከአራት እስከ አምስት ሄክታር መሬት በእንሰሳት መኖ ለምቶ፤ 800 ሺህ ብር የሚገመት የእንሰሳት መኖ ተመርቷል። ዘሩም ለአርሶ አደሩ ይሰራጫል። በተለይ በሐረማያ ሐይቅ ተፋሰስ ውስጥ ያሉ አርሶ አደሮች የመሬት ጥበት ስላለባቸው ማቻቻል እንዲችሉ የመኖ ምርጥ ዘር ተሰጥቷቸው ይተክላሉ።

ሌላው የአየር ንብረት ለውጥ ትልቁ ጉዳይ ነው። እንስሳት የሚያመነጩት ግሪን ሀውስ ጋዝ ወደ አካባቢው ይረጫሉ። ይህ ከአመጋገባቸው ጋር የተያያዘ ነው። ደካማ አመጋገብ ካላቸው ችግሩ ይከሰታል። ለዚህ ደግሞ እንስሳቱን በአግባቡ በመመገብ የአየር ብክለት መጠንን መቀነስ አይከብድም።

በአሁኑ ወቅት ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከግብርና ጋር ተያይዞ በርካታ ተግባራትን የሚያከናውነው እንደዚህ ዓይነት ችግሮችን በጥናትና ምርምር ለመፍታት ነው። ተማሪዎችና ተመራማሪዎች ጥልቀት ያለው ምርምር በማካሄድ ችግሮችን ለመፍታት የሚችሉና በተግባር የተፈተኑ የመፍትሄ ሃሳቦች ከምርምራቸው ያወጣሉ፤ ወደ ተግባር እንዲተረጎም ይደረጋል።

ከተፈጥሮ ሀብት ጋር በተያያዘ እ.አ.አ 2010 በአካባቢው የከርሰ ምድር ውሃ እየጠፋ ነበር። አሁን 75 በመቶ የከርሰ ምድር ውሃው ተመልሷል፤ ወደ ድሬዳዋ የሚጎርፈው ደራሽ ጎርፍ እንዲገታና አካባቢው መልሶ እንዲያገግም የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው። ከአገራችን ሕዝቦች መካከል 80 በመቶ የሚሆነው አርሶ አደር ነው። በአገሪቷ ለእንስሳት እርባታ የሚመች መሬት አለ። ይህን መሬት በተገቢው መንገድ

ለመጠቀምና ውጤታማ ተግባር ለማከናወን ምርምርን መሰረት ያደረገ መፍትሄ እየቀረበ ነው። ዩኒቨርሲቲውም በትንሽ መሬት ላይ የቤት እንስሳት የማርባትና ውጤቶችን ለኅብረተሰቡ በብዛት በማቅረብ ትምህርት እንዲቀስም እየተደረገ ይገኛል። በተለይ ወጣቶችን አሰልጥኖ የስራ ዕድል በመፍጠር ለኅብረተሰቡ ጥሩ የእንስሳት ውጤቶችን ማቅረብ እንደሚችሉ እምነት ተጥሎበታል።



33

በተጨማሪም ተደራጅተው የሚመጡ ወጣቶችን መደገፍ ብቻ ሳይሆን በእርሻ ቦታ ስልጠና እንዲወስዱ ይደረጋል። ከዩኒቨርሲቲው ሲወጡም በሥልጠና ያገኙትን ዕውቀት በተግባር በመተርጎም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። እዚህ ላይ አጽንኦት የሚሰጠው የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ጉዳይ መታየቱ ነው።

ለእንስሳት እርባታ ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው ከፍተኛ ወጪ የሚወጣው ለመኖ ነው። ሰዎች ቢሰለጥኑ ጥሩ ውጤት ያስመዘግባሉ፤ ይቻላልም። የእንስሳት መኖ ዘር ተከማችቶ የሚገኘው አንድ ማዕከል ላይ ነው። በአገር ደረጃ የሚያከፋፍሉት አዲስ አበባ፣ አዳማ አካባቢ የሚገኙ ማዕከሎች ናቸው።

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ለምስራቁ የአገሪቷ ክፍል እያከፋፈለ ይገኛል። ተቋሙ ይህ ዘላቂ ይሆናል የሚል እምነት አለው። በዚህ ሥርዓት ውስጥ ኢንቨስት አድርገው ዘሩን ለማቅረብ የሚችሉ ወጣቶች መኖር እንዳለባቸው ይታመናል። ይህም የበለጠ ችግሩን ያቃልላል የሚል እምነት አለ። ለዚህም ሲባል የተደራጁ አክሲዮኖች አሉ። ከግብርና ግብዓት ጋር በተያያዘ በርካታ ተግባራት ይከናወናሉ። ከእነርሱ ጋር በመገናኘትና በመደገፍ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ ነው። የእንሰሳት መኖ በጥሩ ሁኔታ አምርተው ለገበያ በማቅረብ የራሳቸውን ገቢ በመፍጠር የሻለ ሕይወት መምራት እንደሚችሉ እሙን ነው።



34

ፖለቲካ

ሠማያዊ መልህቅ



35

ሠማያዊ መልህቅ

በጌታቸው ያለው

እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን አቆጣጠር 2018 በጅቡቲ የተካሄደውን ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ለመዘገብ ሁለት ደርዘን ያህል ጋዜጠኞች ወደዚያው አቀኑ፤ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የውጭና የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች በቀይ ባሕር የወደብ ከተማዋ ጅቡቲ ተገኝተው ሰሞነኛውን ጉዳይ ሲዘግቡ ሰነበቱ። ቆይታቸው ከኢትዮጵያው የዱር ቡና ላኪ ኮስካል እስከ ቻይናው ግዙፍ የኮንስትራክሽን ማሽነሪ አምራች ኩባንያ (XCMG)

የተሳተፉበትን ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት (DIF) መታዘብ አስችሏቸዋል።

በዓለም አቀፉ የንግድ ትርዒት መክፈቻ የጅቡቲው ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ መንግሥታቸው ለቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ትብብር ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ቁርጠኛ መሆኑን ይፋ በማድረግ የፖሊሲ ማዕቀፎችን በማሻሻል፣ ነፃ የንግድ ቀጣናዎችን በማቋቋም፣ የወደብ ልማትን ጨምሮ በአገሪቱ ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት ምኅዳር ለመፍጠር የሚያግዙ እርምጃዎችን እየወሰደ ስለመሆኑ ሲናገሩ ተደምጠዋል።



36

በወቅቱ የጋዜጠኞቹ ቡድን የዶራሌህ ሁለገብ ወደብ (Doraleh Multipurpose Port) ጨምሮ የጅቡቲውን ግዙፍና ቅንጡ ኬምፐንስኪ ሆቴል፣ የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዲሁም የቀይ ባሕር ውብ ደሴቶችን የመጎብኘት ዕድል አግኝቷል።

ከሣምንቱ በአንዱ ቀን በቀይ ባሕር ከሚገኙ የመዝናኛ ሥፍራዎች አንዷ ወደሆነችው ደሴት ለማቅናት ጋዜጠኞቹ የስራ ቁሳቁሳቸውን ሸክፈው ወደ ወደብ በምትወስዳቸው መለስተኛ አውቶቡስ ተሳፍረው ለጉዞ ተሰናዱ። ጉብኝቱን ያሰናዳው የጅቡቲ የቱሪዝም መሥሪያ ቤት ለጉዞው የሚያስፈልገውን ለማሟላት ጋዜጠኞችን የያዘችው ተሽከርካሪ በአንድ የከተማዋ መንገድ ዳር ለአፍታ እንድትቆም አደረገ።

ይህን አጋጣሚ መጠቀም የፈለጉ ሦስት የካሜራ ባለሙያዎች የከተማዋን ምሥል ለመያዝ ከመኪና ወርደው ውብ ነው ያሉትን የከተማዋን ገፅታ በካሜራቸው መያዝ ይጀምራሉ። በተለይ ሁለቱ ተሽከርካሪው ከቆመበት ስፍራ ራቅ ብለው በባሕር ዳርቻው ወደ ተንጣለለ ግዙፍና ያማረ ቅጥር ግቢ ተጠግተው ቀረጻቸውን ይቀጥላሉ። በዚህ መሃል ከየት መጡ ሳይባል ድንገት ከተፍ ያሉ የጅቡቲ የደህንነት ፓትሮሎች ሁለቱን የካሜራ ባለሙያዎች በቁጥጥር ሥር ያውሏቸዋል። ብዙም ርቆ ያልሄደው ሦስተኛው የካሜራ ባለሙያ ፈጥኖ ጋዜጠኞቹን ወዳሳፈረችው መለስተኛ አውቶቡስ ገብቶ ይቀመጣል።

ከደህንነት አባላቱ አንዱ ወደ ተሽከርካሪው በመምጣት የገባው የካሜራ ባለሙያ እንዲወጣ ይጠይቃል። መልስ የሰጠው አልነበረም፤ ሁሉም በዝምታ ተውጧል። የካሜራ ባለሙያውን መለየት ባለመቻሉ ከውጭ የገባው ሰው እንዲወጣ በድጋሚ ቢጠይቅም ሁሉም ጭጭ አለ። በዚህ ጊዜ ጋዜጠኞቹ ከተሽከርካሪዋ እንዲወርዱ ትዕዛዝ አስተላለፈ፤ ይሄኔ ከአንዱ ጥግ አንድ ሰው “በቃ ውረድልን” ሲል በጩኸት ተናገረ፤ አማራጭ አልነበረውምና የካሜራ ባለሙያው ከነካሜራው ወረደ። ሦስቱ የካሜራ ሙያተኞች በደህንነት አባላቱ ታጅበው የቀይ ባሕር ዳርቻን ታኮ ወደተገነባውና ከደቂቃዎች በፊት ሲቀርጹት ወደ ነበረው ግዙፍ ቅጥር ግቢ ገቡ።

የተቀሩት ጋዜጠኞች የካሜራ ባለሙያዎቹ እንደሚመለሱ በተስፋ ቢጠባበቁም የውሃ ሽታ ሆኑ። ጉዳዩን የሚመለከታቸው ሁሉ እንዲያውቁት ተደረገ። ከሠዓታት ቆይታ በኋላ የካሜራ ባለሙያዎቹ ሲመለሱ ካሜራዎቻቸው

ተወረሱ። ጉዳዩ የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ከፍተኛ የደህነነት ኃላፊዎች ጋር ደረሰ። ከብዙ ቆይታ በኋላ የጋዜጠኞቹ ቡድን በሦስት የአገሪቱ የፀጥታ ፓትሮሎች ታጅቦ ራቅ ወዳለ የባሕር ዳርቻ አመራ። ከደቂቃዎች የመኪና ጉዞ በኋላ በስተቀኝ የጅቡቲ፤ በስተግራ በኩል ደግሞ የአሜሪካ ግዙፍ የጦር ካምፖች ወደሚገኙበት ቦታ ደረሰና ወደ ጅቡቲ የጦር ካምፕ በመግባት በካሜራዎቹ የተቀረጸው ምስል በባለሙያዎች እንዲጠፋ ተደርጎ ለባለቤቶቹ ተመለሱ።

ወስዶ መላሹ ትዕይንት በዚህ ሲቋጭ የክስተቱ ታዳሚ የነበርነው ጋዜጠኞች የዚያ ሁሉ ውጣ ውረድና ግርግር ምክንያት የካሜራ ባለሙያዎቹ አፍንጫው ሥር ተጠግተው ሲቀርጹት የነበረውና ምንም የጽሁፍ መግለጫ የማይታይበት



37

የተንጣለለ ውብ ቅጥር ግቢ የጅቡቲ ፕሬዚዳንት ቤተ-መንግሥት መሆኑን ተረዳን። እናም በዕለቱ ወደ ደሴቲቷ ታስቦ የነበረው ጉብኝት በቀጣዩ ቀን ተደረገ።

በወቅቱ የተመለከትኳቸው ግዙፍና ዘመናዊ የጅቡቲ፣ የአሜሪካ እና የቻይና የጦር ካምፖች ከፈጠሩብኝ አግራሞት ባሻገር፤ አገራቱ ባሕር አቋርጠው በጅቡቲ ስላቋቋሟቸው የጦር ካምፖች ሳስብ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጂኦ- ፖለቲካ ምን ያህል እንደተገለለች እያሰላሰልኩ ቁጭት ውስጥ እገባለሁ።

በምሥራቅ አፍሪካ ጫፍ እና በባብ-ኤል-መንደብ ሁነኛ ስፍራ ላይ የምትገኘው ጅቡቲ የዓለም ጂኦ-ስትራቴጂካዊ ዓምድ ከሆነች ሰነባብታለች።

በዚህም በርካታ ኃያላን አገራት በትንሿ የአፍሪካ ቀንድ አገር ላይ ወታደራዊ መልህቃቸውን ጥለዋል። እዚህ ላይ ጅቡቲን ጨምሮ የቀይ ባሕር አካባቢ ለምን የጂኦ-ፖለቲካዊ ስትራቴጂ ፍጥጫ ማዕከል ሊሆን ቻለ የሚለው ሰፊ ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም አሁን እየታየ ካለው ቀጣናዊ እንቅስቃሴ አኳያ የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ተሳትፎ ዳግም መነቃቃትና ማንሰራራት እንዳለበት አመላካች ነው።

የቀይ ባሕር ጂኦ-ፖለቲካዊ መነሻ ስለ ቀይ ባሕር ለዘመናት ብዙ ተብሏል፤ ብዙ ተጽፏል። እንዲያም ሆኖ ስለዚህ ስትራቴጂያዊ ባሕር በትንሹ መጠቃቀሱ አይከፋም። ቀይ ባሕር በእስያና በአፍሪካ መካከል የሚገኝ የውኃ

አካል ሲሆን የሜዲትራኒያን ባሕር እና የሕንድ ውቅያኖስን ያገናኛል። የቀይ ባሕር ጠቅላላ የገፅታ ስፋት 438 ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር እና 2 ሺህ 250 ኪ.ሜ. ርዝማኔ እንዳለው መረጃዎች ያሳያሉ። ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ሱዳን፣ ግብፅ፣ የመን፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ እስራኤል እና ዮርዳኖስ የቀይ ባሕርን ዳርቻ ይጋራሉ።

ቀይ ባሕር አውሮፓ እና እስያን በስዊዝ ካናል በኩል የሚያገናኝ ወሳኝ የንግድ የውኃ መስመር ነው። የዓለም የኢኮኖሚ የደም ሥር ሲሆን በመጪዎቹ አሥርት ዓመታትም አሁን ካለው ተፈላጊነት በላይ ጠቃሚ ሆኖ እንደሚቀጥል ይታመናል። ይህ የውኃ አካል በዓለም ላይ ከሚገኙ 10 እጅግ ወሳኝ ከሚባሉ ጂኦ-ስትራቴጂያዊ አካባቢዎች በቀዳሚነት ይጠቀሳል።



38

በቀይ ባሕር ደቡባዊና ሰሜናዊ ክፍል የሚገኙት የባብ ኤል-መንደብ እና የስዊዝ ካናል ሰርጦች 10 በመቶ እና ከዛም በላይ የሚሆነው የዓለም ንግድ በየዓመቱ የሚተላለፍባቸው ቁልፍ የውኃ መስመሮች ናቸው። ይህ ደግሞ በአፍሪካ ሰሜናዊ ምሥራቅ የባሕር ጠረፍ እና በዓረብ ልሣነ ምድር (ባሕረ ገብ መሬት) ላይ የሚገኙት የቀይ ባሕር አገራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ጂኦ- ፖለቲካዊ ጠቀሜታ እንዲኖራቸው መነሻ ሆኗል።

ይህ ብቻ አይደለም በነዳጅ ኃብታቸው ከበለፀጉት የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ወደ አውሮፓና አሜሪካ በአብዛኛው ነዳጅ የሚተላለፈው በዚሁ የውኃ መስመር ነው። እነዚህ አገራት ያላቸው ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ከሌሎች ታሪካዊ ዳራዎች ጋር ተዳምሮ ጂኦ-ፖለቲካዊ ተፈላጊነታቸው ከፍ እንዲል መነሻ ሆኗል። እነዚህ አገራት 620 ሚሊዮን ሕዝብ እንዳላቸው የሚገመት ሲሆን ይህ አሀዝ እ.ኤ.አ በ2050ዎቹ መጀመሪያ ላይ ወደ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን እንደሚደርስ ይጠበቃል። አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርታቸውም አሁን ካለው 1 ነጥብ 8 ትሪሊዮን ወደ 6 ነጥብ 1 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚያድግ የምጣኔ ኃብት ጠቋሚዎች ያሳያሉ።

ይህ ሁሉ ተዳምሮ በቀይ ባሕር አካባቢ የዓለም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ ፍላጎት እየጨመረ እንዲመጣ አድርጎታል። በአንፃሩ ይህ ሁኔታ አካባቢውን ለግጭቶች እና ለፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች ተጋላጭ እንዲሆን ያደረገ ክስተትም ሆኗል።

የቀጣናዊ ሽኩቻ ገፅታ

የቀይ ባሕር ቀጣና በታሪክ ግጭትና ጦርነት ከማይለያቸው የዓለማችን አካባቢዎች ተጠቃሽ ነው። አሁን አሁን በቀይ ባሕር አካባቢ የሚስተዋሉት ግጭት ጠማቂዎች የተለያዩ ቢሆኑም በውክልና ጦርነት (Proxy War) እና በቀጣናዊ ሽኩቻ (Regional Rivalries) ያተኮሩ ናቸው።

ቀደም ሲል በሶማሊያ የባሕር ዳርቻ ይስተዋል የነበረው የባሕር ላይ ዘረፋና ውንብድና የቀይ ባሕር አካባቢ ዋነኛ የፀጥታ ችግር ሆኖ እንዲቆይ አድርጎታል። ይሁን እንጂ እ.ኤ.አ በ2008 ገቢራዊ በተደረገው ግዙፍ ዓለም አቀፍ የባሕር ኃይል ዘመቻ የባሕር ላይ ዘረፋን ሥጋት ወደማይሆንበት ደረጃ ዝቅ ማድረግ ተችሏል። ነገር ግን በየመን የተቀሰቀሰው ግጭት የባሕር ላይ ውንብድናን ተክቶ የቀይ ባሕር ቀጣና ዋነኛ ያለመረጋጋት መንስኤ ሆኖ ቀጥሏል።

በተለይ እ.ኤ.አ በ2012 ከዓረቡ ዓለም አብዮት መምጣት ጋር ተያይዞ የመንን ለረጅም ዓመታት የመሯት ዓሊ አብዱላህ ሳላህ ከሥልጣን መወገድ የመናዊያንን ወደለየለት ፖለቲካዊ አመፅ እና የእርስ በርስ ጦርነት እንዲገቡ አድርጓቸዋል። በዚህም የመንና የቀይ ባሕር ቀጣና እስካሁን ሰላምና መረጋጋት ርቋቸው እየታመሱ ቀጥለዋል። ጦርነቱ በየመን ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ከመፍጠሩ ባሻገር በቀይ ባሕር የመርከቦች ዝውውር ላይም ስጋት ፈጥሯል።

በባሕረ ሰላጤው አገራት መካከል ያለው ቀጣናዊ ሽኩቻ በሁለቱም የቀይ ባሕር ዳርቻዎች ላይ የፖለቲካ ውጥረት እንዲፈጠር አድርጓል። በተለይ በምሥራቅ አፍሪካ ወደቦችና ወታደራዊ ማዕከሎችን ለማግኘት የሚደረገውን ሩጫ ይበልጥ እንዲባባስ ማድረጉን የብሩኪንግስ ድረ- ገፅ በጉዳዩ ላይ ይፋ ያደረገው ዘገባ ያሳያል።

በቅርቡ ኒውዮርክ ካስተናገደችው 78ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ በተጓዳኛ በርካታ አገራት የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ውይይቶች ማካሄዳቸው አይዘነጋም። በወቅቱ ቀልብ መሳብ ከቻሉት የጎንዮሽ ውይይቶች መካከል የጅቡቲና የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ውይይት ይጠቀሳል። ሁለቱ አገራት ለሰባት ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን ግንኙነታቸውን ዳግም “አድሰናል” ሲሉ ተደምጠዋል። የኢራንና የጅቡቲ ግንኙነት ወደነበረበት መመለስ የባሕረ ሰላጤው አገራት ከምሥራቅ አፍሪካ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንደሚሹ ማሳያ እንደሆነ በአፍሪካ ቀንድ ዙሪያ የሚወጡ መረጃዎች ያስረዳሉ።

እንዲያም ሆኖ በምሥራቅ አፍሪካ ከፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች መጠናከር ጀርባ ያለው የአገራት ሽኩቻ ቀጣናውን ወዴት ያደርሰዋል? የሚለው ለበርካቶች እንቆቅልሽ እንደሆነ ቀጥሏል። ከሽኩቻው ባሻገር በምሥራቅ አፍሪካ ያለው የባሕረ ሰላጤው አገራት ቅጥ ያጣ መሻት ከወዴት የመነጨ ነው? ብሎ የሚጠይቅ ባይኖርም ጉዳዩን ትንሽ ፈታ አድርጎ ማየቱ ጠቃሚ ይሆናል።

ከሽኩቻው በስተጀርባ

የአፍሪካን ቀንድ ከባሕረ ሰላጤው አገራት ጋር የሚያቆራኙ በርካታ ቀለበቶች እንዳሉት ይታወቃል። ከመልክዓ ምድራዊ ቅርርብ እስከ ባህላዊና ኃይማኖታዊ እንዲሁም ምጣኔ ኃብታዊ ትስስሮች መጥቀስ ይቻላል። ለብዙ ሺህ



39

ዓመታት በእነዚህና በሌሎች የጋራ መስተጋብሮች ተጋምደው ኖረዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የግንኙነቶቹ መሰረቶች ኢኮኖሚያዊ እና ጂኦ-ስትራቴጂያዊ እየሆኑ ስለመምጣታቸው አሳማኝ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል። በተሻለ ምጣኔ ኃብታዊ መደላድል ላይ የነበሩት የባሕረ ሰላጤው አገራት እ.ኤ.አ በ2008 የተከሰተው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ዝቅጠት (Economic Recession) የምግብ ዋስትናቸውን ክፉኛ ስለተፈታተነውና ከዚህ ጋር ተያይዞ ያጋጠማቸው የምግብ ዋጋ መጨመር አገራቱ የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥን ዓብይ አጀንዳቸው አድርገው እንዲሰሩበት አድርጓል።

ለዚህ አማራጭ ያደረጓቸው የሰሜንና የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ሲሆኑ ግብፅ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን ተመራጭ ሆነው ቀረቡ። በእነዚህ አገራት ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን በኪራይና በግዥ በመያዝ የምግብ ዋስትናችንን ያረጋግጣል ያሉትን ሁሉ እያከናወኑ ይገኛሉ። የባሕረ ሰላጤው አገራት በአፍሪካ ቀንድ ቅጥ ያጣ መሻት መነሻው የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሆነ ልብ ይሏል።

በኃብት የናጠጡት የባሕረ ሰላጤ አገራት እ.ኤ.አ ከ2015 ጀምሮ በቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ በሪልስቴት ዘርፍ እብደት የተሞላበትና ጥድፊያ

የበዛበት የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት አድርገዋል። እነዚህ አገራት በጅቡቲ፣ በኤርትራ፣ በሶማሊያ፣ በሱዳን እና በየመን ስትራቴጂያዊ ቦታዎችን በመያዝ አዳዲስ የባሕር ወደቦች እና ወታደራዊ ማዕከላት እንዲስፋፉም ጥረዋል።

የባሕረ ሰላጤው አገራት የቀይ ባሕር ቀጣናዊ ሥርዓትን እንደገና ለመወሰንና በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ወሳኝ ተዋናይ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሰላ ሽኩቻ ሲያደርጉም ይስተዋላል። አገራቱ በተለይም የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በቀንዱ አካባቢ ያሉ አዳዲስ የንግድ ወደቦች በአፍሪካ እየሰፋ የመጣውን የሸማቾች የመግዛት አቅም ታሳቢ ያደረገ ተጽዕኖ ፈጣሪነት የመያዝ ከፍ ያለ ፍላጎት አላት።

ይህ ደግሞ በቀጣናው እያደገ የመጣው የመልማት ፍላጎት በቀይ ባሕር እና በምዕራብ ሕንድ ውቅያኖስ የባሕር መስመር መፃኢ ዕጣ ፈንታን ለመቅረፅ ዕድል ይፈጥርላታል። በተለይ ቻይና በአካባቢው የምታደርገው የንግድ ልውውጥ በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ምክንያት እያደገ ሲሄድ እነዚህ አገራት በሚኖራቸው ተጽዕኖ ፈጣሪነት ልክ ተጠቃሚ መሆንን ይሻሉ።

ይህ አካሄድ አንዳንድ የአፍሪካ መንግሥታትን በጊዜያዊነት የጠቀመ ስለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ።

የታላላቅ ኃይሎች ፍጥጫ ቀይ ባሕር ካለው ከፍ ያለ ጂኦ-ፖለቲካዊ ስትራቴጂ አኳያ ዓለም አቀፍ ኃይሎች ወታደራዊ ይዞታቸው ለማድረግ መንቀሳቀሳቸው የሚያስገርም አይደለም። በአሁኑ ወቅት በቀይ ባሕር አካባቢ በሚንቀሳቀሱ አገራት ከደርዘን በላይ የባሕር ኃይል ማዕከላት ይገኛሉ። ለአብነት ጅቡቲ የአሜሪካን፣ የፈረንሣይን፣ የኢጣሊያን፣ የጃፓን እና የቻይናን የባሕር ኃይል ተቋማት በማስተናገድ ለውጭ ወታደራዊ ኃይል መገኘት ቁልፍ መልህቅ ሆናለች።

መስከረም 14 ቀን 2016 ዓ.ም የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን በጅቡቲ የሚገኘውን ካምፕ ሌሞኒየርን (የአሜሪካ የጦር ካምፕ) የመጎብኘታቸው ምክንያት ምንም ይሁን ምን የቀይ ባሕር ጉዳይ እንደሆነ ግልጽ ነው። ካምፕ ሌሞኒየር ለአሜሪካ በባህረ ሰላጤው፣ በዲያጎ ጋርሺያ ደሴት እና በሕንድ ውቅያኖስ ለሚኖራት የባሕርና የአየር ኃይል እንደ ቁልፍ አገናኝ ሆኖ ያገለግላታል። በተለይም ካምፑ አራት ሺህ የአሜሪካና አጋር ወታደሮችን በማስተናገድ በአፍሪካ የአሜሪካ ዕዝ ዋና የኦፕሬሽን ማዕከል ሆኖ ያገለግላል። ይህ ሁሉ ጋጋታ እንግዲህ የቀይ ባሕር ጂኦ-ስትራቴጂያዊ ስበት ያመጣው መሆኑን ማስተዋል ይገባል።



40

በተመሳሳይ ቻይና እ.ኤ.አ. በ2008 የፀረ-ባሕር ውንብድና ዘመቻን ከተቀላቀለች በኋላ ከ26 ሺህ በላይ ወታደሮቿን በቀጣናው አሰማርታለች። እ.ኤ.አ. 2017 የቻይና ሕዝባዊ ጦር ኃይል (People’s Liberation Army-PLA) በጅቡቲ የሎጂስቲክስ ቤዝ መስርቶ በአፍሪካ ቀንድ የቻይና የባሕር ኃይል እና የሰላም ማስከበር ሥራዎችን እንዲሁም የአደጋ ጊዜ ተልዕኮ እየተወጣ ይገኛል። ከዚያ አለፍ ሲልም የቻይና ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭን (ሰሞኑን 3ኛውን ዓለም አቀፍ ጉባዔ በቻይና አካሂዷል) ለመጠበቅ ወሳኝ ከሆኑ ስትራቴጂያዊ አካባቢዎች አንዱ የቀይ ባሕር ቀጣና በመሆኑ ጭምር ነው።

ሌላዋ ኃይል ሩሲያ በቀይ ባሕር ፖለቲካ እና ወታደራዊ ስትራቴጂያዊ ጨዋታ ውስጥ ተጠቃሽ አገር ናት። ሩሲያ ጨዋታውን ከፍ ለማድረግ ከሁለትዮሽ ግንኙነት ባሻገር በሩሲያ- አፍሪካ ጉባዔ አማካኝነት የተለየ ሚና እንዲኖራት እየጣረች ነው። ሞስኮ ከ20 በላይ ከሚሆኑ የአፍሪካ አገራት ጋር የወታደራዊ ትብብር ስምምነቶችን የተፈራረመች ሲሆን በጅቡቲ የራሷን ጦር ሰፈር ለማቋቋም ስትደራደርም ተስተውላለች።

የሩሲያው የኑክሌር ኩባንያ ሮሳቶም ከ18 የአፍሪካ አገራት ጋር የኑክሌር ትብብር ስምምነት ተፈራርሟል። በተጨማሪም እ.ኤ.አ. በ2020 የሩሲያ የጦር መርከቦችን ለማስተናገድ የባሕር ኃይል ሎጂስቲክስ ቤዝ ማቋቋም የሚያስችል ስምምነት ከሱዳን ጋር ተፈራርማለች።

የባሕረ ሰላጤው አገራትም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በቀይ ባሕርና በአፍሪካ ቀንድ ተሳትፏቸውን እያሳደጉ መጥተዋል። ላቅ ያለ ምጣኔ ኃብታዊ አቅም ያላቸው የባሕረ ሰላጤው አገራት በአፍሪካ ቀንድ ያሳደሩት ፍላጎት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጎልቶ እየታየ ነው። ይህ ደግሞ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በቀይ ባሕር የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የስትራቴጂ ተሳትፎ የቆዩ ግምቶችን እያፋለሰ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ይገኛል።

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኳታር እና ቱርክ የንግድ ወደቦችን እና በአፍሪካ ቀይ ባሕር ጠረፍ ላይ ያሉ ወታደራዊ ማዕከሎችን ጨምሮ የተጽዕኖ አቅማቸውን ለማስፋት እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ። የመካከለኛውን ምሥራቅ ፉክክር በትልቁ የቼዝ ሰሌዳ (የአፍሪካ ቀንድ) ላይ እየተጫወቱበት ይገኛሉ። ይህ ደግሞ ከታላላቅ ኃይሎች ፍላጎትና ፍጥጫ ጋር ተዳምሮ የጂኦ-ፖለቲካ መልክዓ ምድሩን ይበልጥ አወሳስቦታል።

የአዳዲስ ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ መዋዕለ ንዋይ ፍሰት በቀይ ባሕር ምሥራቅና ምዕራባዊ ዳርቻዎች ላይ የጂኦ-ፖለቲካዊ ለውጦች እያመጣ ይገኛል። ለምን? ብሎ ደፍሮ የጠየቀ ባይኖርም ሁኔታው በቀይ ባሕር ምዕራባዊ ዳርቻ ለሚገኙ የአፍሪካ መንግሥታት የውጭ ኃይሎች በአዲስ መልክ ብቅ እንዲሉ አድርጓል። በቀይ ባሕር የኃያላኑ ተሳትፎና ፍጥጫ አሁን ላይ ጨዋታ

ቀያሪ ዓይነት አንድምታ ባይታይበትም አዎንታዊ እና መርዛማ (Tonic and Toxin) ገፅታ ይዞ ስለመምጣቱ በርከት ያሉ ማሳያዎችን አንስተው የሚሞግቱ ተንታኞች በዝተዋል።

ኢትዮጵያ እና የቀይ ባሕር ፎረም ኢትዮጵያ ለዘመናት የቀይ ባሕር ባለቤት በመሆን በቀጣናው ተገቢ ሚናዋን ስትጫወት ቆይታለች። እንዲያም ሆኖ በተለያዩ ምክንያቶች ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ፖለቲካ ከተገለለች ዓመታትን አስቆጥራለች። እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን አቆጣጠር 1993 ኤርትራ ነፃ አገር መሆኗ ሲታወጅ ኢትዮጵያ ከባሕር በርም ከቀይ ባሕር ፖለቲካም እንድትርቅ ሆኗል። በወቅቱ የነበሩ የውስጥና የውጭ ጫናዎች ኤርትራ እንድትገነጠል ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ የቀይ ባሕርና የወደብ ባለቤትነት መብት እንዳይነሳ ሆኖ እንዲዳፈን ተደርጓል።

በወቅቱ በኢትዮጵያ የነበረው መንግሥት አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን የቀይ ባሕር በር በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛና ሰፊ አገር ለሆነችው ኢትዮጵያ አንዳች መተንፈሻ ያላስቀረ ታሪካዊ ስህተት መፈጸሙ ተስተውሏል።

ኢትዮጵያ በአፋር ቡሬ ወደ ቀይ ባሕር ያላት ርቀት 80 ኪሎ ሜትር እንኳ የማይሞላ ሆኖ ሳለ ከወደብ እና ከቀይ ባሕር ፖለቲካ ተገልላ የቅርብ- ሩቅ መሆኗ የሚያስተዛዝብ ጭምር ነው። የቀይ ባሕር ጉዳይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ



41

ኢትዮጵያን የሚመለከታት ቢሆንም ከ“ቀይ ባሕር ፎረም” ጭምር የተገለለች ሆናለች።

በደህንነት ጉዳዮች ላይ ለመተባበር እና የቀይ ባሕር አካባቢን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚል ዓላማ ያለው እ.ኤ.አ በ2020 በሳዑዲ ዓረቢያ አጋፋሪነት የተመሰረተው ይኸው ፎረም አራት የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) አባል አገራት ማለትም ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያን በአባልነት አካቷል። በዓባይ ውኃ አጠቃቀምና በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ በምታንጸባርቀው የከረረ አቋም ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ ያለችው ግብፅም የፎረሙ አባል ናት። ቀሪዎቹ የፎረሙ አባል አገራት የመን፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እና ዮርዳኖስ ናቸው።

የቀይ ባሕር ፎረም ትኩረት የሚያደርግባቸው ጉዳዮች ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከባህል፣ ከአካባቢ እና ከደህንነት ጋር የተያያዙ ናቸው። ስብስቡ ከተመሰረተባቸው 12 ዓላማዎች አንዱ በቀጣናው የሚከሰቱ ሽብርተኝነት፣ የባሕር ላይ ውንብድና እና ሕገ-ወጥ ንግድን መከላከል ነው። በአባል አገራት የሚከሰቱ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀለኞችን እና ሕገ-ወጥ ስደትን መከላከልም ከፎረሙ ዓላማዎች መካከል ይጠቀሳል። በስብስቡ በተካተቱ አገራት ንግድና ኢንቨስትመንትን ማስተዋወቅ ሌላው ዓላማው ሲሆን የቀይ ባሕር ፎረም በቀጣናው የሸቀጦች፣ የአገልግሎቶች እና የገንዘብ እንቅስቃሴን እንዲሁም የባሕር ላይ

ንግድን የማሻሻል ትልምም አለው።

የቀይ ባሕር ፎረም በይፋ ከሚነገሩለት ዓላማዎች ባሻገር ዓለም አቀፉ የጂኦ-ስትራቴጂ ፉክክር የሚንጸባረቅበት ነው። እንደ አብዛኞቹ የፖለቲካ ተንታኞች እይታ የጂኦ-ስትራቴጂ ሽኩቻው የቀዝቃዛውን ጦርነት ዳግም መምጣት እያመላከተ እንደሆነ ነው የሚያምኑት። በዚህ የውድድር ማዕቀፍ ውስጥ እንግዲህ አንዱን

አቅርቦ ሌላውን አግልሎ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆኖ ለመውጣት አገራት ሲተራመሱ ይታያሉ።

የፎረሙን ዓላማ ስኬታማ በማድረግ በኩል የማይናቅ አስተዋፅኦ ያላት ኢትዮጵያ ቀድሞውኑ የባሕር በር እንዳይኖራት ለዘመናት ሲጥሩ የነበሩ ታሪካዊ ጠላቶቿ አሁንም ከቀይ ባሕር ስብስብ እንድትርቅ የሸረቡት ሴራ ለጊዜው የተሳካላቸው ይመስላል። ግን ደግሞ በቀጣናው ዘላቂ ስላምና የጋራ ብልጽግና ለማረጋገጥ አግላይ አካሄድ የትም እንደማያደርስ በመገንዘብ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሚናቸው ከፍ ያለ የአካባቢው አገራትን ማቀፍ እንደሚገባ የበዙ የጂኦ-ፖለቲካ ተንታኞች ይመክራሉ።

የተነቃቃው የኢትዮጵያ

የባሕር በር ጥያቄ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የባሕር በር ጉዳይ ዋነኛ የመነጋገሪያ ርዕስ እየሆነ መጥቷል። ኢትዮጵያ የባሕር በር እንደሚገባት በመንግሥት ደረጃ ይፋዊ ጥያቄ መነሳቱ ደግሞ ጉዳዩ ይበልጥ ትኩረት እንዲስብ አድርጓል። ጥያቄው ድንገት ገንፍሎ የመጣ ሳይሆን ለዘመናት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ሲያነሱት የቆየ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት መንበር እንደመጡ በፓርላማ ተገኝተው ባሰሙት የመጀመሪያ ንግግራቸው የወደብ ልማት ጉዳይ መንግሥታቸው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራበት መናገራቸውን ማስታወሱ ለዚህ በቂ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል። እናም ሰሞነኛው በቀይ ባሕር የራስ በር ጥያቄ በኢትዮጵያ በኩል መነቃቃት ማሳየቱ አስገራሚ ሊሆን አይችልም።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ምናልባትም መንበረ ሥልጣኑን ከመረከባቸው አስቀድሞ ስለጉዳዩ የቆየ ግን ደግሞ የተለየ ሃሳብ እንዳላቸው ያመላከቱበት ነበር ማለት ይቻላል፤ በስሎና ጎልብቶ ይፋ የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን የጠቆመም ጭምር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህን ብቻ ሳይሆን አትዮጵያ የብሪክስ (BRICS) አባል አገር መሆን እንዳለባት ከ13 ዓመታት በፊት የገለጹ መሆኑ ሲታወስ በኢትዮጵያ እና በአህጉሩ ጉዳይ ያላቸው የፀና የከፍታ አቋም የት ድረስ እንደሆነ ያመላክታል።

ለሦስት አስርት ዓመታት ከስሞ የቆየውን የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዳግም እንዲደራጅ ማድረጋቸውም ፍንጭ ሰጪ ነበር። በወቅቱ ዜናው ሲሰማ በርካቶችን አስገርሟል። ያለ ባሕር በር የባሕር ኃይል እንዴት ይታሰባል? የሚል ፌዝ አዘል ጥያቄም

የባሕር በር ባለቤትነት ሁለንተናዊ

እይታውም ከፍላጎት ባሻገር

በሕግና በጥናት በማስደገፍ

ላይታጠፍ የተነሳውን ጥያቄ ዳር

ማድረስ የመንግሥትና የምልዓተ-

ሕዝቡ የዘመኑ የቤት ሥራ ይሆናል።

የፖለቲካ፣ የታሪክ፣ የምጣኔ ኃብት

አቅም፣ የዲፕሎማሲና የሕግ

ዝግጅት ያስፈልጋል።



42

ተደምጧል። ዳሩ ሃሳብን ወደ እውነታ የመለወጥ ውጥን ሂደት ስለመሆኑ ብዙዎች በጊዜው አለመረዳታቸውን አሁን ልብ ይሉት ይሆናል።

እናም ይህ ጥያቄ አሁን ላይታጠፍ በይፋ ተነስቷል። ለመሆኑ ኢትዮጵያ ለምታነሳው የባሕር በር የይገባኛል ጥያቄ ታሪካዊና ሕጋዊ መሰረት አላት? ገፍታ እየሄደችበት ያለው የይገባኛል ጥያቄ የቱን ያህል ውጤት ያስገኝላታል?

ኢትዮጵያ አሁን ያላት 120 ሚሊዮን ሕዝብ እ.ኤ.አ በ2030 ወደ 145 ሚሊዮን እንደሚያድግና በ2050 ደግሞ ቁጥሩ ከ205 ሚሊዮንና ከዚያም በላይ እንደሚደርስ የዘ-ዎርልድ ካውንትስ (The World Counts) የሥነ-ሕዝብ ትንበያ ያሳያል።

በዓለም የባሕር በር ከሌላቸው 44 አገራት በሕዝብ ብዛት ኢትዮጵያ ቀዳሚ ናት። እንዲያም ሆኖ የዚህን ያህል ከፍተኛ ቁጥርና እየጨመረ የሚሄድ የሕዝብ ብዛት ያላት አገር የባሕር በር ማግኘት አለመቿሏ በፖለቲካም ይሁን በምጣኔ ኃብት ረገድ ሊፈጥር የሚችለው አገራዊና ቀጣናዊ ጫና በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

የኤርትራ ከኢትዮጵያ መገንጠል ጋር ተያይዞ የሚበዛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄዎችን ሲያነሳ ቆይቷል። የመገንጠሏ ምክንያቱ በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት ትክክል ሊሆን ይችላል አልያም በወቅቱ በህወሓት እና በኤርትራ ሕዝቦች ነፃ አውጪ ግንባር (ሻዕቢያ) መካከል የተፈጠረው ስምምነት ምናልባትም የኃይል ሚዛን ውጤት ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ጉዳዩ አሁንም በአከራካሪነቱ ቀጥሏል። ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያን ያለ አንዳች የባሕር በር መተንፈሻ ከርችሞ ያስቀረ ኢ-ፍትሃዊ ውሳኔ በመሆኑ ነው።

ኢትዮጵያ ምንም እንኳን በተደጋገመ የውጭ ኃይሎች ወረራ ወደቦቿን በቅኝ ገዢዎች የማጣት ፈተና ቢያጋጥማትም መሪዎቿ ለአገራቸው ያለውን ጠቀሜታ በውል ተገንዝበው ለባሕር በር ከመታገል ወደኋላ ያሉበት ጊዜ አልነበረም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም ያደረጉት ይህንኑ ነው።

በእርግጥም ኢትዮጵያ ለምታነሳው የይገባኛል ጥያቄ ታሪካዊና ሕጋዊ መሰረት ያላት ስለመሆኗ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች አሉ።

ከዚህ አንፃር ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ታሪካዊ መብት አላት። በተመሳሳይ ይህን እውነታ የሚያጠናክሩ ሕጋዊ መሰረቶች አሉ። እዚህ ላይ በዋናነት ሊነሳ የሚገባው እ.ኤ.አ በ1981 የፀደቀውና በ1994 ሥራ ላይ የዋለው የባሕር ላይ እንቅስቃሴዎችን የሕግ ማዕቀፍ አስመልክቶ የተዘጋጀው የተባበሩት መንግሥታት የባሕር ሕግ ኮንቬንሽን (UNCLOS) ነው።

ለባሕር በር ተደራሽ የመሆን መብት እና የመተላለፍ ነፃነት (The Right of Access to the Sea and Freedom of Transit) የዚሁ ህግ አካል ነው።

የኮንቬንሽኑ ክፍል 10 ከአንቀጽ 124 እስከ 132 የባሕር በር የሌላቸው አገራት ለባሕር ተደራሽ የመሆን መብትን ይመለከታል።

በኮንቬንሽኑ አንቀጽ 125 በተለይ ለባሕር ተደራሽ የመሆን እና የመተላለፍ ነፃነትን የሚመለከት ነው። በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ የባሕር በር እንደሌላት አገር ይህን መብት የመጠቀም ዕድል ቢኖራትም በሁለቱ አገራት መካከል በየጊዜው

በሚፈጠረው ግጭት ምክንያት ገቢራዊ ማድረግ አልተቻለም።

ኮንቬንሽኑ ወደብ የሌላቸው አገራት በቅርበት የሚገኙ ወደቦችን የመጠቀም መብቶችን እውቅና እና የመተላለፍ ነፃነት ይሰጣል። የሕግ ማዕቀፎችንም ያረጋግጣል። እናም ኢትዮጵያ ያነሳችው የይገባኛል ጥያቄ ሕጋዊም ታሪካዊም መሰረት ያለው ነው ሲባል ውሃ በሚያነሳ ምክንያት ነው።

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ባሕር ላይ የራሷ የሆነ በር ማግኘት እድትችል የጀመረቻቸውን አገራዊ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች በሰላማዊ፣ በዲፕሎማሲያዊና በሕጋዊ መንገድ ማስቀጠል ይኖርባታል። ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ጂኦ-ፖለቲካን ከዓለም አቀፍ ዓውድ አንፃር በውል ተገንዝቦ ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ የሚያስችሉ ሥራዎች ሊሰሩ ይገባል።

የባሕር በር ባለቤትነት ሁለንተናዊ እይታውም ከፍላጎት ባሻገር በሕግና በጥናት በማስደገፍ ላይታጠፍ የተነሳውን ጥያቄ ዳር ማድረስ የመንግሥትና የምልዓተ-ሕዝቡ የዘመኑ የቤት ሥራ ይሆናል። የፖለቲካ፣ የታሪክ፣ የምጣኔ ኃብት አቅም፣ የዲፕሎማሲና የሕግ ዝግጅት ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያዊያን ልሂቃን ከሕግና ከታሪካዊ ዳራዎች ጋር የሚጣጣሙ ብሎም ውስብስቡ የውኃ ፖለቲካ ከሚፈጥረው ጫና እና ውጥረት የሚያላቅቁ ጥናትና ምርምሮችን በማከናወን ምሁራዊ አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል። የውስጥ ሰላማቸውን በማስጠበቅና በማጠናከር ለአገራቸው ብሎም ለቀጣናው የሚጠበቅባቸውን ሚናም መወጣት ይኖርባቸዋል።



43



44

ማህበራዊ

የአየር ንብረት ለውጥ

የአፍሪካ ሕልውና ስጋት



45

የአየር ንብረት ለውጥ

የአፍሪካ ሕልውና ስጋት

አፍሪካ በቆዳ ስፋቷ እና በሕዝቧ ብዛት በዓለማችን በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትቀመጣለች። በተፈጥሮ ሀብትም ሆነ በተስማሚ የአየር ሁኔታዋ የታወቀች ብትሆንም በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በፖለቲካዊ ችግሮቿ ምክንያት ግን የሚገባትን ያህል ዕድገት ላይ አልደረሰችም።

ለዚህ በምክንያትነት ከሚጠቀሱት ጉዳዮች መካከል ለምሣሌ ለረዥም ጊዜ አህጉሪቷን ቀይዶ ይዞ የቆየው የቅኝ አገዛዝ ሥርዓት እና ሥርዓቱ ከተወገደ በኋላ ተንሰራፍቶ የቆየው የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ፣ ያንንም ተከትለው የመጡት የእርስ በእርስ ጦርነቶች እንዲሁም አህጉሪቷ በምትገኝበት ስልታዊ የመሬት አቀማመጥ እና ካላት እምቅ የተፈጥሮ ሀብት የተነሳ በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት የሚካሄዱ ግጭቶች ይገኙበታል።

እነዚህ ሁሉ ችግሮች በስፋት የሚጠቀሱ እና ዘወትርም መፍትሔ ሲፈለግላቸው የኖሩ ናቸው። እንደ ዕድል ሆኖ አንዳንዶቹ ችግሮቿ ሲፈቱ፣ ሌሎቹ ረገብ ሲሉ እና ሲያገረሹ እስካሁን ዘልቀዋል። ከእነዚህ ችግሮች ባልተናነሰ ሁኔታ የአህጉሪቷ ፈተና የሆነው ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ ነው።

በማሕተመ ብሩ



46

የአየር ንብረት ለውጥ የረጅም ጊዜ የሙቀት ለውጦች እና የአየር ሁኔታን ይመለከታል። እነዚህ ለውጦች ተፈጥሯዊ ሊሆኑ ይችላሉ። ከ1800ዎቹ ጀምሮ ግን ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች እንደ ከሰል፣ ዘይት እና ጋዝ ያሉ ከቅሪተ አካላት የሚገኝ የማገዶ አይነቶችን (Fossil Fuels) በማቃጠል ለአየር ንብረት ለውጥ መከሰት ዋነኛ ምክንያት ሆነዋል። የሚቃጠሉ የቅሪተ አካል ነዳጆች በምድራችን ላይ እንደተጠቀለለ ብርድ ልብስ የሚያገለግሉ የግሪንሃውስ ጋዝ ልቀቶችን ያመነጫሉ፣ የፀሐይን ሙቀት በመያዝም የሙቀት መጠንን ይጨምራሉ።

የአየር ንብረት ለውጥን ከሚያስከትሉ የግሪንሃውስ ጋዝ ልቀቶች ምሣሌዎች ካርቦን ዳይኦክሳይድ እና ሚቴን ይገኙበታል። እነዚህም መኪናን ለመንዳት ቤንዚን በመጠቀም ወይም ሕንፃን ለማሞቅ የድንጋይ ከሰል መጠቀም፣ ደኖችን ማጽዳት ካርቦን ዳይኦክሳይድን ሊለቁ ይችላሉ። የቆሻሻ መጣያ ቦታዎች የሚቴን ልቀት ዋነኛ ምንጮች ናቸው። የኃይል ማመንጫዎች፣ ኢንዱስትሪዎች፣ ትራንስፖርት፣ ሕንፃዎች፣ ግብርና እና የመሬት አጠቃቀም ዋና ዋና የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ምንጮች ናቸው።

ለአሁኗ ዓለማችን ስጋት ሆኖ የሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥ የተከሰተው በዋናነት በኢንዱስትሪ የበለጸጉት አገራት በተለይም አሜሪካ እና ቻይና በሚለቁት ከፍተኛ መጠን ያለው ካርቦን ነው። ወደ ከባቢ አየር ከሚለቀቀው የካርቦን መጠን ውስጥ አፍሪካ ከ2 እስከ 3 በመቶ የሚሆነውን ብቻ የምትጋራ ቢሆንም በዚህ ሳቢያ በሚደርሰው የአየር ንብረት ለውጥ የሚደርሰው ዘርፈ ብዙ ጉዳት ዋናዋ ገፈት ቀማሽ ግን አፍሪካ ናት።

በአስጊ ሁኔታ እየተባባሰ ያለው ይህ የአየር ንብረት ለውጥ ከወዲሁ ካልተገታ አፍሪካ ላይ በተለያየ መልኩ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። በመሆኑም የአፍሪካ አገራት መሪዎች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በዘርፉ የተሰማሩ ዓለምአቀፍ እና አገር አቀፍ ተቋማት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት ይኖርባቸዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ እና ሠብዓዊ መብቶች

ሰፋ ባለ መልኩ ሲታይ የአየር ንብረት ለውጥ በሰው ልጆች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት በዓለም ዓቀፍ ሕግጋት የተደነገጉ ሠብዓዊ መብቶችን የሚያሳጣ ክስተት ነው፡፡ ይህን በተመለከተ

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ዓለም አቀፍ የሠብዓዊ መብቶች ተማጋች ተቋም እንደገለጸው ይህ ዓለም ዓቀፍ ችግር በሚከተሉት መልኮች በአጠቃላይ የሰው ልጆች ላይ ችግር ይፈጥራል፡፡

በሕይወት የመኖር መብት ሁላችንም በሕይወት፣ በነጻነት እና በደህንነት የመኖር መብት አለን። ነገር ግን የአየር ንብረት ለውጥ በዚህች ፕላኔት ላይ ያሉ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት እና ደህንነት አደጋ ላይ ይጥላል። በጣም ግልጽ የሆነው ምሣሌ እንደ አውሎ ንፋስ፣ ጎርፍ እና ሰደድ እሣት ባሉ ከአየር ሁኔታ ጋር በተያያዙ ክስተቶች የሚደርሰው ጉዳት ነው። ነገር ግን የአየር ንብረት ለውጥ ለሕይወት ስጋት የሚሆንባቸው ሌሎች በርካታ የማይታዩ መንገዶች አሉ። ከ2030 እስከ 2050 ባለው ጊዜ ውስጥ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በዓመት 250,000 ሰዎች እንደሚሞቱ የዓለም ጤና ድርጅት ትንበያ ያሳያል።

የጤንነት መብት ሰዎች ሁሉ ከፍተኛውን የአካል እና የአዕምሮ ጤና ደረጃ የማግኘት መብት አላቸው። እንደ አይ.ፒ.ሲ.ሲ ገለጻ ከአየር ንብረት ለውጥ ዋና ዋና የጤና ተጽዕኖዎች ለጉዳት፣ ለበሽታ እና

ለሞት የሚዳርገው ኃይለኛ የሙቀት ማዕበል እና የእሣት አደጋን ይጨምራል። በድሃ ክልሎች በምግብ ምርት መቀነስ ምክንያት ለተመጣጠነ የምግብ እጥረት የመጋለጥ ዕድልን ይጨምራል። ከምግብ እና ከውሃ እንዲሁም ከቬክተር ወለድ በሽታዎች ለሚመጡ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድልንም ይጨምራል። በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሰዎች በተለይም ሕፃናት በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ለአሰቃቂ ሁኔታዎች ሲጋለጡ ከጭንቀት በኋላ በሚመጡ ችግሮች ሊሰቃዩ ይችላሉ።

መኖሪያ ቤት የማግኘት መብት ሁላችንም ለራሳችን እና ለቤተሰባችን የመኖሪያ ቤትን ጨምሮ በቂ የኑሮ ደረጃ የማግኘት መብት አለን። ነገር ግን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ እንደ ጎርፍ እና ሰደድ እሣት ያሉ ከፍተኛ የአየር ሁኔታ ክስተቶች የሰዎችን መኖሪያ ቤቶች እያወደሙ አፈናቅለዋቸዋል። ድርቅ በአካባቢ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ለውጦችን ሊያመጣ ይችላል፤ የባሕር ከፍታ መጨመር በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የመኖሪያ ቤት ስጋት ላይ ጥሏል።



47

ለመጠጥ እና ለንጽሕና አገልግሎት የሚውል ንጹህ ውሃ የማግኘት መብቶች እንደ በረዶ መቅለጥ፣ የዝናብ መጠን መቀነስ፣ የሙቀት መጠን መጨመር እና የባሕር ከፍታ መጨመር የአየር ንብረት ለውጥ የውሃ ሃብቶችን ጥራት እና መጠን እየጎዳ መሆኑን ያሳያሉ። ቀድሞውኑ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሰዎች ደህንነቱ የተጠበቀ ሊሆን የሚችል የውሃ ወይም የንጽሕና ምንጭ አያገኙም። የአየር ንብረት ለውጥ ይህንን ያባብሰዋል። ይህም የሰዎችን ጤነኞች ማድረግ የሚያስችለው ንጹሕ ውሃ የማግኘት እና የንጽሕና አጠባበቅ መብትን ጥያቄ ምልክት ውስጥ ያስገባዋል።

በአየር ንብረት ለውጥ በእጅጉ የሚጎዳው ማነው? የአየር ንብረት ለውጥ በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎችንም ሆነ እንስሳትን ያለምንም ልዩነት ተጎጂ ሊያደርግ የሚችል አቅም እንዳለው የማይካድ ሃቅ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን በመላው ዓለም የሚገኙ ሕዝቦች ተመሳሳይ ወይም እኩል የኢኮኖሚ፣ የእውቀት፣ የቴክኖሎጂ እና የመሳሰሉ እሴቶች ይዞታ ስለሌላቸው ሁሉም እኩል ተጎጂ ይሆናሉ ማለት አይቻልም፡፡ በተለይ

ደግሞ ጉዳቱን የመከላከል ጉዳይ ሲታሰብ ከላይ በተገለጹት ምክንያቶች አንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች ብሎም ከአንድ ሕብረተሰብ ውስጥ የተወሰኑት ክፍሎች በችግሩ ይበልጥ ተጎጂ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚገልጸው በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ ከተጠቁት መካከል ብዙውን ጊዜ ለአየር ንብረት ለውጥ አነስተኛ አስተዋፅኦ የሚያደርጉት የሕብረተሰብ ክፍሎች በለውጡ ምክንያት ከፍተኛውን ጉዳት ያስተናግዳሉ። ይህ የሆነበት ምክንያት ከአየር ንብረት ጋር ለተያያዙ አደጋዎች በመጋለጣቸው ብቻ ሳይሆን የእነዚያን ክስተቶች ተጽዕኖ በሚያጎሉ ፖለቲካዊ፣ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ጭምር ነው። በተለይም የቅኝ ግዛት ዘላቂ መዘዞች እና በአገራት መካከል ያለው እኩል ያልሆነ የሀብት ክፍፍል ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ከሚያስከትላቸው አሉታዊ ተጽዕኖዎች ጋር መላመድ እንዳይችሉ አድርጓል።

ተጋላጭ ከሆኑት የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል ደግሞ ሴቶች እና ልጃገረዶች በተፈጥሮ ሃብቶች ላይ የበለጠ ጥገኛ በሚያደርጓቸው ስራዎች ላይ ስለሚጠመዱ እና የመሬት ባለቤትነት፣ የገንዘብ

ወይም የእውቀት ሃብቶችን በማግኘት ረገድ ባለባቸው ውስንነት ምክንያት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ለሚከሰቱ ችግሮች ይበልጥ ተጋላጭ ይሆናሉ።

የአየር ንብረት ለውጥ ስለምን የአፍሪካ ስጋት ሆነ? ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ መዘዞች ከሌሎች የበለጠ ተጎጂ ትሆናች፡፡ በእርግጥ የአየር ንብረት ለውጥ ለመላው ዓለም ወይም ለሁሉም የሰው ልጆችና ፍጥረታት በሙሉ ስጋት ነው፤ ነገር ግን ከላይ በተገለጹት ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ቴክኖሎጂያዊ ክፍተቶች ምክንያት ከሌላው ዓለም በበለጠ አፍሪካን ለአደጋ ተጋላጭ የማድረግ ባህሪይ ስላለው አህጉሪቱን ከሌሎች በበለጠ ሁኔታ ቢያሳስባት የሚደንቅ አይሆንም።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ፕሮግራም (ዩኔፕ) እንደገለጸው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ ተጋላጭነት ዋነኛ መንስኤ በአህጉሪቱ እየታየ ያለው ዝቅተኛ የማኅበራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ነው። የአየር ንብረት ለውጥ ዓለም አቀፋዊ ቢሆንም ድሀ አገራት ግን ተመጣጣኝ ባልሆነ ሁኔታ ለጉዳቱ ተጋላጭ



48

ናቸው። ምክንያቱም ለውጡን ለመቋቋም ወይም ለመላመድ የሚያስፈልጓቸውን ቁሳቁስ እና አገልግሎቶችን መግዛት የሚያስችል አቅም ስለሌላቸው እና ከከፋ የአየር ንብረት ተጽዕኖዎች ለማገገም ስለሚቸገሩ ነው፡፡ በአፍሪካም ይህ ነው እየሆነ ያለው።

በዓለም ላይ እየተከሰተ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ ከሌላ የዓለም ክፍል በተለይ አፍሪካን ሊያሳስባት የሚችልበት ምክንያት ሲታይ አንደኛ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገራት መካከል ከዓለማችን 95 በመቶ የሚሆነውን በዝናብ ላይ የተመሰረተ የግብርና ስራ የሚያከናውኑ ናቸው። ሁለተኛ በጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት እና የስራ ስምሪት ውስጥ ያለው የአየር ሁኔታ- ተኮር ተግባራት መካከል የእንስሳት እርባታ እና ዓሣ ማጥመድን ጨምሮ የግብርና ድርሻ ተጋላጭነትን በማባባስ ለኪሳራ እና ለምግብ ዋስትና እጦት ያጋልጣል። በሌላ በኩል ደግሞ ለአየር ንብረት ለውጥ በጣም ተጋላጭ ከሆኑት 10 የዓለም አገራት መካከል ሰባቱ የአፍሪካ አገራት መሆናቸው ስጋቱን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል።

የመፍትሔ ሃሳቦች እንደ አፍሪካ ያሉ ታዳጊ አገራትም ሆኑ ሌላው ዓለም ከለይ የተዘረዘሩትን የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳቶች ለመከላከል የተለያዩ ተቋማት የተለያዩ የመፍትሔ ሐሳቦችን ይሰነዝራሉ፡፡ እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም የመሳሰሉ ድርጅቶች ከሰነዘሯቸው ሀሳቦች መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

የሙቀት መጨመርን ማስቆም ከ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ እየጨመረ ያለውን የዓለም ሙቀት ለማስቆም የተቻላቸውን ሁሉ ያድርጉ። ከ2050 በፊት ወይም በ2050 የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀትን ወደ ፍፁም ዜሮ ለመቀነስ የበለፀጉ አገራት በፍጥነት ይህን ማድረግ አለባቸው። እ.ኤ.አ በ2030 የዓለም ልቀቶች በ2010 ከነበረው በግማሽ ያህል መሆን አለባቸው።

አረንጓዴ የኃይል ምንጮችን ልማት ማፋጠን

በተቻለ ፍጥነት የነዳጅ ዘይት (ከሰል፣ ዘይት እና ጋዝ) አለማምረትና አለመጠቀም እንደ አንድ መፍትሔ ይሰነዘራል። እነዚህን ካርቦን አመንጪ የኃይል ምንጮች ምርትና አጠቃቀምን ለማስቆምም የቅሪተ አካል ነዳጅ ድጎማዎችን መግታት አስፈላጊ ነው። ብዙ ሃብታም አገራት

የአየር ንብረት ለውጥ የመከላከል ስምምነት እንዲተገበር እንደሚሹ ይናገራሉ። ነገር ግን በተመሳሳይ ጊዜ አዳዲስ የድንጋይ ከሰል፣ የዘይት እና የጋዝ ክምችቶችን ለማግኘት በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር የግብር ከፋዮችን ገንዘብ ያጠፋሉ። እነዚህ መንግሥታት የካርቦን ዋጋን ከገበያ በቀረጥ ዋጋ እያወጡ እንጂ የአየር ንብረት አደጋን ማስታገስ የለባቸውም። የቡድን 20 አገራት የነዳጅ ፍለጋ እና የምርት ድጎማዎችን በ2018 የሚከለክልበትን የጊዜ ሰሌዳ ማውጣት አለባቸው።

የአፍሪካ ዝቅተኛ የካርቦን ኢነርጂ ሽግግርን ማፋጠን የአፍሪካ መንግሥታት፣ ባለሃብቶች እና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት አፍሪካ እምቅ ዝቅተኛ የካርቦን ልዕለ ኃያል አገር እንድትሆን ለማስቻል የኢነርጂ ኢንቨስትመንትን በተለይም ታዳሽ ኃይልን ማሳደግ አለባቸው። በ2030 ለሁሉም አፍሪካዊያን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ለማቅረብ በአስር እጥፍ የኃይል ማመንጫዎች መጨመር ያስፈልጋል። ይህም ድህነትን ይቀንሳል፣ ዕድገትን ይጨምራል።

የካርቦን ንግድን ማስፋፋት የአየር ንብረት ለውጥን ሸክም ፍትሃዊ በሆነ

መልኩ ለመጋራት በጋራ መስራት አስፈላጊ ነው። ይህም ማለት የበለፀጉ አገራት በማደግ ላይ ባሉ አገራት ታዳሽ ኃይል እንዲያገኙ እና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር እንዲላመዱ የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ ማድረግ አለባቸው። በተጨማሪም ጉዳት ለደረሰባቸው እና በአየር ንብረት ቀውስ ምክንያት ለሚደርስ ጉዳት ካሳን ጨምሮ መፍትሔ መስጠት አለባቸው።

ይህ በአግባቡ ከተተገበረ አገራት የተፈጥሮ ካፒታላቸውን ወደ ሀብት መቀየር ይችላሉ። ለምሣሌ በመካከለኛው አፍሪካ የሚገኘው የኮንጎ ተፋሰስ 70 በመቶ የሚሆነው የአፍሪካ ደኖች መገኛ ሲሆን ይህም በዓለም ላይ ትልቁ የካርበን ማስቀመጫ ሆኖ ያገለግላል። እነዚህ ደኖችም ከ25 እስከ 30 ቢሊዮን ቶን ካርቦን ይይዛሉ ተብሎ ይገመታል። በፕላኔታችን ላይ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ብዝሃ ሕይወት ለማግኘት በጣም አስፈላጊ ከሆኑ ቦታዎች አንዱ ነው። በመሆኑም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ ጋር፣ ክልሉ ይህንን ንብረት በአገር ውስጥ፣ በአገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ ገቢ ምንጮች መተርጎም ይኖርበታል።

የዓለም ባንክ በኮንጎ ተፋሰስ የደን ልማትን



49

ለመደገፍ ቁርጠኝነት ያሳየ ሲሆን ይህን እውን ለማድረግ ከሚያስችሉ ተግባራት መካከል እንደ የመካከለኛው አፍሪካ የደን ተነሳሽነት፣ የደን ካርቦን አጋርነት ተቋም፣ የደን ኢንቨስትመንት ፕሮግራም፣ ዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም፣ PROGREEN እና REDD+ ካሉ መንግሥታት እና አጋሮች ጋር፣ የአካባቢውን ተወላጅ ማኅበረሰቦች እና የተፈጥሮ ሃብቶችን ግልፅ እና ውጤታማ አጠቃቀም ማስተዋወቅን የመሳሰሉት ይገኙበታል። ተጨማሪ የአየር ንብረት ፋይናንስ ለመጠቀም የአፍሪካ አገራት በካርቦን ገበያ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ማረጋገጥ በቀጣይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው።

የታቀዱ የከተማ ማስፋፊያ አዳዲስ ሞዴሎችን መተግበር አፍሪካ በዓለም ፈጣን የሆነው የከተማ መስፋፋት የሚታይባት እንደመሆኗ ደህንነቱ የተጠበቀና ቀልጣፋ የሕዝብ ማመላለሻ እና ብዙ ያልተበከሉ ከተሞችን ለማዳበር ዕድሎች አሏት። የምጣኔ ሀብት መጠን እና እየጨመረ የሚሄደው የከተማ ገቢ ታዳሽ ኃይል ለማቅረብ እና ሁለንተናዊ የመሠረታዊ አገልግሎቶችን ተደራሽነት ለማስፋት የሚያስችል አቅም አላቸው። የአፍሪካ ከተሞችን እያደጉ ካሉት

የዓለም አቀፍ የከተማ ኔትወርኮች፣ የ”C40” ከተሞች ቡድንን ጨምሮ፣ እውቀትን ለመለዋወጥ፣ አቅምን ለማጎልበት እና ፋይናንስ ለማቅረብ አዳዲስ ዕድሎችን ሊከፍት ይችላል። መንግሥታት፣ የባለብዙ ወገን ኤጀንሲዎች እና የዕርዳታ ለጋሾች ተባብረው የከተሞችን የብድር ብቃት በማጠናከር ለንጹሕ ኢነርጂ ፈጠራ አጋርነት መፍጠር አለባቸው።

ለአየር ንብረት-ምቹ ግብርናን (Climate Smart Agriculture) ማሳደግ ካለፉት አስርት ዓመታት ወዲህ አገራት ለከፋ የምግብ ዋስትና ቀውስ ተዳርገዋል። ይህም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአስደናቂ ሁኔታ እየጨመረ የመጣው የኢነርጂ እና የማዳበሪያ ዋጋ እንዲባባስ አድርጎታል። በምላሹ የዓለም ባንክ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት የምግብ ምርትን ለማበረታታት፣ የምግብ ሥርዓቱን ለውጥ የመቋቋም አቅምን ለማሳደግ፣ ንግድን ለማሳለጥ፣ የእሴት ሰንሰለትን ለማዳበር እና ተጋላጭ ቤተሰቦችን ለመደገፍ 17 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እያደረገ ነው። የዚህ ጥረት አካል የሆነው የምዕራብ አፍሪካ የምግብ ሥርዓት መቋቋም ፕሮግራም 4 ሚሊዮን ሰዎችን በማዳረስ በአየር ንብረት ምቹ ግብርና

ምርትን ያሳድጋል።

እ.ኤ.አ ከ2020 ጀምሮ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት የማዳበሪያ ዋጋ በሦስት እጥፍ በመጨመሩ የምግብ ምርት እጥረት እና የምግብ ዋጋ መጨመር ስጋት አለ። ፈጣን እርምጃ ካልተወሰደ በቀጣናው የምግብ ዋስትና እጦት እንዲጨምር በማድረግ ከ100 ሚሊዮን በላይ አፍሪካዊያንን የምግብ እጥረት ውስጥ ሊከት ይችላል። የማዳበሪያውን ችግር ለማቃለል በቀጣናው ግልጽና ቀልጣፋ የማዳበሪያ ገበያ ለማልማት፣ የአፈር ፍላጎትን በተሻለ ለመረዳትና ዘላቂ የግብርና አሰራሮችን በመከተል ምርታማነትን ለማሳደግና የአርሶ አደሩን ገቢ በዘላቂነት ለማሳደግ በመንግሥትና በማዳበሪያ ኢንዱስትሪ መካከል ትብብርን ይጠይቃል። በአየር ንብረት-ምቹ ግብርና ላይ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶችም ለቀጣናው አገራት ከፍተኛ የምግብ ዋስትና ዝግጁነት፣ ጠንካራ የእሴት ሰንሰለቶች እና የተቀናጀ የመሬት ገጽታ አያያዝ ጥቅማጥቅሞችን እያገኙ ነው።

የአየር ንብረት ለውጥን እንደ አዲስ መደበኛ ተግባር (New Normal) መቁጠር የአፍሪካ አገራት በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ኢንቨስት ማድረግ እና ዝቅተኛ የካርቦን ዕድገትን ወደ ዘላቂ ልማት መደገፍ አለባቸው። ለምሣሌ እንደ መሪ አጋር እና ትልቁ ፋይናንስ ምንጭ የዓለም ባንክ የአፍሪካን ዝቅተኛ የካርቦን ተከላካይ ሽግግርን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አሳይቷል። በምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ ከሐምሌ 2021 እስከ ሰኔ 2022 ባሉት ጊዜያት ለ92 ፕሮጀክቶች 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የአየር ንብረት ፋይናንስ ተደርጓል። ክልሉ ትራንስፎርሜሽን እና ፈጠራን የሚያበረታቱ አረንጓዴ፣ ተቋቋሚ እና አካታች ኢንቨስትመንቶችን አቅርቧል። ጠንካራ የአየር ንብረት እርምጃ እና የአየር ንብረት ፋይናንስ መጨመር አገራት ሙሉ አቅማቸውን እንዲገነዘቡ እየረዳቸው ነው።

የዚህ ጥረት አካል የሆነው የዓለም ባንክ እንደ አፍሪካዊው ታላቁ አረንጓዴ ግንብ ያሉ የለውጥ ፕሮግራሞችን በመደገፍ የመሬት አቀማመጥን በማደስ፣ የተሻሻሉ የምግብ ሥርዓቶችን እና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችሉ መሠረተ ልማቶችን በመጠቀም የሰዎችን ኑሮ ማሻሻል ላይ ያተኮረ ነው።



50

ብሔራዊ ጥቅም ለአገር ግንባታ

ፖለቲካ



51

በብሔራዊ እና በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ አገራት የራሳቸውን ስልት ይከተላሉ። የውጭ አገራትን ፖሊሲ ለመቋቋምም የየራሳቸውን ፖሊሲ ቀርጸው በጋራ ይሰራሉ። አገራት የራሳቸውን ፖሊሲ ያለማንም ጣልቃገብነት፣ ያለማንም እርዳታ ቀርጸው ሲሰሩ ለአገር ግንባታቸው ጥሩ ይሆናል ሲሉ የመስኩ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

በማደግ ላይ ያሉ አገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በዓለም አቀፍ ሥርዓት ላይ ተጽዕኖ ማሳደር አይችሉም። በዓለም አቀፍ ደረጃ ለራሳቸው የሚከራከሩበት አቅም የላቸውም። አንዳንዶቹ አንጻራዊ የሆነ ተጽዕኖ የማሳደር አቅም ይኖራቸዋል። ከዚህ በተቃራኒው ያደጉት አገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በሌሎች አገራት ላይ ጭምር ተጽዕኖ ያደርጋሉ። “በውስብስቡ ዓለም አቀፍ ሥርዓት ውስጥ የአንዲትን አገር ብሔራዊ ጥቅም እንዴት ማስጠበቅ እንችላለን? እንዴትስ በዚህ ገበያ ውስጥ ተፎካካሪ የሆነች፣ ፍላጎቷን ያወቀች፣ ፍላጎቷን መሸጥ የምትችል፣ ከዚህ ገበያ የምታገኘውን ጥቅም የምታሳድግ ማድረግ እንችላለን?“ ሲሉ ሃሳባቸውን

በፍቅርተ ባልቻ



52

በጥያቄ የገለጹት የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ባለሙያው ዶ/ር መሃመድ እድሪስ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ወሳኝ መሆኑን በአጽንኦት ይገልጻሉ። ብሔራዊ ጥቅም ሁሉም ዓለም አቀፋዊ ሂደቶች የሚያተኩሩበት ነው። እጅግ መሰረታዊው ነጥብ አገረ መንግሥት መንግሥት ሆኖ እንዲቀጥል የሚያደርገው ምን ዓይነት ብሔራዊ ጥቅም ሲኖረው ነው? በአገር ውስጥ እና በውጭ ካሉ አካላት ጋር ድርድር ውስጥ የሚገባው ምንን ለማስጠበቅ ነው? ለምንድን ነው መንግሥት የውስጥ እና የውጭ አቅሙን አስተባብሮ የሚሰራው? ወዴት ለመሄድ ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች የሚመልስልን ብሔራዊ ጥቅሙ ምንድን ነው? የሚለው ነው። አገራት ይህን ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚያከናውኑት ተግባር፣ የሚዘረጉት መሰረተ ልማት ፋይዳውን ይነግረናል። ለምን ስለ ብሔራዊ ጥቅም እናወራለን? “ብሔራዊ ጥቅም ለአገር ግንባታ ወይስ አገር ግንባታ ለብሔራዊ ጥቅም ነው?“ የትኛው ይቀድማል የሚለው ሀሳብ እስካሁን መቋጫ አላገኘም። ሆኖም አገር ግንባታ ለብሔራዊ ጥቅም የሚለው ይሻል ይሆናል ይላሉ ዶ/ር መሃመድ። እንደ እርሳቸው ገለጻ በአንድ አገር ላይ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ በመጀመሪያ ደረጃ ዋነኞቹ ተዋንያን እነማን እንደሆኑ መለየት፣ በመቀጠል የተዋንያኑ ፍላጎት ምን እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል። ብሔራዊ ጥቅም እጅግ በጣም ውስን፣ አንገብጋቢ፣ አገራዊ፣ መንግሥታት የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ኃይላቸውን ሳይቀር ጥቅም ላይ የሚያውሉበት መሰረታዊ ፍላጎታቸው ነው። የሁሉንም ዜጎች ጥቅም ያማከለ ነው፤ እንደማሳያ ሰላምን ማንሳት ይቻላል፣ የሁሉም ሕዝቦች ጥያቄ እና ፍላጎት ነውና። ስለዚህ ስለ አንድ አገር ብሔራዊ ጥቅም ስናወራ በመሰረታዊነት ሦስት መለኪያዎች አሉ ይላሉ ዶ/ር መሃመድ። የመጀመሪያው አስፈላጊነት፣ ሁለተኛው ስምምነት ሲሆን ሦስተኛው የውጭ ተቀባይነት ናቸው። የመጀመሪያው መለኪያ አንድ ጉዳይ ለዚያች አገር ብሔራዊ ጥቅም ያለው አስፈላጊነት (relevance) ነው። “አጀንዳው እጅግ መሰረታዊ የሆነ የማሻገር አቅም አለው ወይ? በማኅበረሰቡ ውስጥ አጀንዳ ሆኖ ለዘመናት የዘለቀ ነው ወይ? እየተንሸራሸረ ነበር ወይ? የአጀንዳው ማኅበራዊ ይዘት መስተጋብር

ስር ነቀል በሆነ መልኩ የሚቀይር፣ የሚያሻግር ነው ወይ? ለአዳዲስ መብቶች ዕድል የሚሰጥ ነው ወይ? ለሚሉት ጥያቄዎች የሚሰጠው ምላሽ አስፈላጊነቱን ያስረዳናል“ ይላሉ ዶ/ር መሃመድ። ከዚህ የምንረዳው ሁሉም አጀንዳ ብሔራዊ ጥቅም መሆን እንደማይችል ነው። ብሔራዊ ጥቅም የሁሉም ዜጎች ጥቅም ነው። በጥቅሉ ብሔራዊ ጥቅምን በሦስት ከፍሎ ማየት እንደሚቻል ዶ/ር መሃመድ ይገልጻሉ፤ ያለፈ፣ የአሁን እንዲሁም የወደፊት። “አገራቱ የትናንት ጥያቄያቸውን፣ የዛሬ ፍላጎታቸውን ዓለም የሚፎካከርበትን ጉዳይ፣ የነገ ጥያቄያቸውን መሰረት አድርገው ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ መስራት ይጠይቃቸዋል“ ሲሉ ይመክራሉ። እንድንለወጥ የሚያስገድዱን ዓለም አቀፋዊ የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳዎች አሉን። በመሰረታዊነት ቋሚ ወይም የማይቀያየሩ የሚመስሉ ብሔራዊ ጥቅሞች ቢኖሩም የብሔራዊ አጀንዳው የመቀየር ፈጣን ዕድገት እንዳለው ልብ ማለት ያስፈልጋል። ባደጉት እና ባላደጉት አገራት ብሔራዊ ጥቅም መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። ለእኛ ተቀዳሚ (መሰረታዊ የሆኑት) የብሔራዊ ጥቅም ጉዳዮች ለሌሎች አገራት ላይሆኑ ይችላሉ። ከሌሎች አገራት ብሔራዊ ጥቅም ጋር ያለው መስተጋብር፣ የአገራችንን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚመች ነው ወይ? እንደ ዶ/ር መሃመድ ገለጻ “ያደጉት አገራት

ብሔራዊ ጥቅማቸውን ማስጠበቅ የሚችሉት ይህ ኢ-ፍትሃዊ የሆነ ዓለም መቀጠል እስከቻለ ድረስ ብቻ ነው።“ ይህም በመሆኑ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ያላደጉትን አገራት ብሔራዊ ጥቅም እንዴት ነው ማስጠበቅ የሚቻለው? የሚለውን ማጤን መሰረታዊ ነጥብ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ የአንዲት አገር ብሔራዊ ጥቅም እንዴት ነው መከበር የሚችለው? የሚለውን ከውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አንጻር (Foreign Relation Per- spectives) በቅጡ ማየት እና ሙያዊ ትንታኔ እየሰጡ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። በዓለም ላይ ያለው ሥርዓትም ባለበት ለመቀጠል ትግል የሚያደርግ ነው። የዓለም ኃላያላን አገራት አሁን ያላቸውን የፖለቲካ ሚዛን አስጠብቀው ለመቀጠል የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም። በትላልቅ ኩባንያዎቻቸው፣ በድርጅቶቻቸው አማካኝነት ደህንነታቸውን እና ብሔራዊ ጥቅማቸውን ማስጠበቅ ይሻሉ። የተለያየ መልክ እና ገጽታ ተላብሰው በማደግ ላይ የሚገኙትን አገራት (exploit) ይበዘብዛሉ። ስለዚህ ይህን አሸንፎ ለመውጣት እጅግ ከባድ ትግል ይጠይቃል። ስለሆነም በማደግ ላይ ያሉ አገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሳይንሳዊ እና ብልሃት የተሞላበትን አካሄድ መከተል ይጠበቅባቸዋል። ያላደጉት አገራት ሁልጊዜም በሽግግር ውስጥ ናቸው። እንደ በምግብ እህል ራስን መቻል፣ ዴሞክራሲ፣ ደህንነት (security) ያሉትን ጉዳዮች



53

ብሔራዊ ጥቅማቸው አድርገው ሊሄዱ ይችላሉ። በዓለም ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ከዚህ ቀደም የነበሩትን የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳዎች ይዘን መቀጠል እንደማንችል ያሳያል። አሁን የሳይበር ጥያቄ፣ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ከቴክኖሎጂ እንዲሁም ከሳይንስ፣ ከምርምር ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ከአገራት ብሔራዊ ጥቅም ጋር በእጅጉ እየተቆራኙ መጥተዋል። እዚህ ላይ ማኅበረሰብን እና አገርን ነጣጥሎ ማየት እንደማይቻል፤ በማኅበረሰብ እና በአገር ፍላጎት መካከልም ቅደም ተከተል እንደማይቀመጥ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። አዋጭ እና ስኬታማ የሚያደርገው መንገድ የሁለቱንም ፍላጎቶች በአንድነት አጣምሮ ማስፈጸም ነው። በዓለማችን አሁን ላይ ውስብስብ የሆኑ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሁነቶች ይከወናሉ። በዚህ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን እንዴት አስጠብቃ መሄድ ትችላለች የሚለው ትልቅ አጀንዳ ነው። በኢትዮጵያ ደረጃ ብሔራዊ ጥቅም የሁሉም ሕዝቦች ጥቅም ተብሎ ሊወሰድ ይችላል። አንድ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያ ውስጥ በመኖሩ የግድ የሚያገኘው እና የሁሉም ሕዝቦች ጥቅም ነው። ይህን ስንል በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያለን ተወዳዳሪነት ወሳኝ እንደሆነ ማየት ያስፈልጋል። ብሔራዊ ጥቅም እኛ ስለፈለግነው፣ የእኛ ጥቅም ለጎረቤት አገሮች እና ለዓለም አቀፍ ሥርዓት ስጋት ከሆነ በዋናነት ሌላ አጀንዳ ውስጥ ይከተዋል።

ስለሆነም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ስናስብ ኢትዮጵያ ያለችበትን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ ማየት ይጠይቃል። ችግሮቹ እና መውጫ መንገዳቸው … አዎንታዊ የሰላም ግንባታ የሰላም ሚኒስትር ተግባር እና ኃላፊነት ነው። ከዜጎች ጋር መግባባት ላይ ለመድረስ ለውይይት መነሻ ከሚሆኑ ጉዳዮች መካከል አገራዊ ማንነት፣ አገራዊ እሴቶች እና ብሔራዊ ጥቅም እንደሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያምናል። ለአገራዊ ሰላም ግንባታ ሂደቱ ብሎም ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ለሚሰራው ስራ እንዲያግዝ በማሰብ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀትና በማካሄድ ላይ ይገኛል። ትኩረታቸውን አገራዊ ማንነት፣ ባሕላዊ እሴቶች እና ብሔራዊ ጥቅም ለአገር ግንባታ በተሰኙት ርዕሶች ላይ አድርገው በተካሄዱ የውይይት መድረኮች ላይ የተለያዩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። በእነዚህ መድረኮች በአገራችን ማንነታችንን፣ ባሕላዊ እሴቶቻችንን ለብሔራዊ ጥቅም እንዴት ማዋል እንደሚገባ ሰፊ ውይይቶች ተካሂደዋል ማብራሪያዎችም ተሰጥተዋል። በየርዕሰ ጉዳዮቹም ላይ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር እየተስተዋሉ ያሉ ጥንካሬዎች እና ድክመቶች እንዲሁም የወደፊት የቤት ስራዎች ተመላክተዋል። በአገራችን ለሚፈጠሩ ችግሮች አንዱ ምንጭ

አገራዊ ማንነት (National Identity) ላይ የጋራ ግንዛቤ ያለመኖር ስለመሆኑ ተጠቁሟል። አገራት የማንነትን ጉዳይ በአግባቡ ካላስተዳደሩ ሊረጋጉ እንደማይችሉ እየታየ ነው የሚሉት ዶ/ር ከይረዲን የሶቭየት ኅብረትና የዩጎዝላቪያ መፍረስ ዋነኛው ምክንያት ማንነትን በአግባቡ ካለመያዝ ጋር የተቆራኘ መሆኑን ነው ያነሱት። ጠንካራ አገራዊ ማንነት የገነባች አገር የተረጋጋች፣ ሰላሟ የተጠበቀ ይሆናል። ጠንካራ አገራዊ ማንነት እንዲኖር ደግሞ ሕዝቡ እርስ በእርሱ ተቀራርቦ አንዱ የሌላውን ማንነት ማክበር ይጠበቅበታል። እንደ ግለሰብ፣ እንደ ቡድን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ፍላጎት አለ። ይህን ፍላጎት በአግባቡ ተቀብሎ ለማስተናገድ መስራት ያስፈልጋል። በዚህ መንገድ መጓዝ ሲቻል በአገር ውስጥም ሆነ በአገራት መካከል የሚከሰተው ግጭት ይቀንሳል። ይህን አስመልክቶ ዶ/ር ከይረዲን ሲናገሩ”ጠንካራ አገራዊ ማንነት ለተረጋጋ ሰላም ወሳኝ ነው፣ ስለሆነም እዚያ ላይ መስራት ያስፈልጋል። አገር በቀል ተቋማት (Indigenous Institutions) አሉ። እነዚህ ተቋማት በሰዎች አስተሳሰብ ላይ ይሰራሉ (መድረሳዎች፣ ቄስ ትምህርት ቤቶች፣ የገዳ ሥርዓት …) ፤ በመንግሥት ደረጃ በተመሳሳይ አገራዊ ማንነትን ለማጎልበት በስፋት መስራት ያስፈልጋል” ብለዋል። በየትኛውም ዓለም ማንነት የህልውና ጉዳይ ስለመሆኑ ”በዓለማችን ታሪክ የማንነት ጉዳይ



54

ለዘመናት ለብዙ ጦርነቶች እና አለመግባባቶች ምክንያት ቢሆንም በአሁኑ ዘመን ማንነቶችን አቻችሎ፣ ተከባብሮ፣ በአንድ አገር በርካታ ቋንቋዎችን በመናገር የመኖር ባሕል በስፋት እየተለመደ መጥቷል” ሲሉ በመጽሐፋቸው ያሰፈሩት መታሰቢያ መላከ ሕይወት ናቸው። ጸሐፊው ”በአንድ አገር የሚኖሩ ሕዝቦች በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ዕድገት ጉዞ በሚጀምሩበት ጊዜ ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ ሲሄዱ ባቡር፣ መንገድ፣ ከተሞች እየለሙ ሲሄዱ በሕዝቦች መካከል የሚኖረው መቀራረብም እየተጠናከረ ይሄዳል” የሚለውን ሀሳብ እንደመከራከሪያ ነጥብ አንስተዋል። ፖሊሲያችን እና ሕገ-መንግሥቱ የጋራ ማንነትን መገንባት ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ይጠይቃል። በተያያዘም የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 88”… የሕዝቦችን ማንነት የማክበርና በዚሁ ላይ በመመርኮዝ በመካከላቸው እኩልነት፣ አንድነትና ወንድማማችነትን የማጠናከር ግዴታ አለበት” ሲል ደንግጓል። በማኅበረሰቡ ዘንድ አገር በቀል ሕጎች አሉ። እነዚህን ሕጎች ወደ ፖሊሲ ማዕቀፍ እንዴት እንደምናመጣቸው ማሰብና መሰራት አለበት። ልዩነቶቻችን በሕግ፣ በፖሊሲ መታቀፍ አለባቸው። የሕግ ማዕቀፎቻችን አንድነት አንድነት የሚሸቱ መሆን አለባቸው። የህልውናችን መሰረት የሆኑ እና እጃችን ላይ ያሉ እሴቶችን ማየት አለብን። ኢትዮጵያዊያን እርስ በእርሳቸው ተጋብተዋል፣ ተዋልደዋል፣ ተሳስረዋል። በርከት ያሉ የጋራ ሀብቶች (ቅርሶች) አሉ፤ እነዚህ ቅርሶች አንዱን ከሌላው ጋር የሚያስተሳስሩ ናቸው። ኢትዮጵያዊያን ተለያዩ ሲባል በአገር ላይ ጥቃት ሲቃጣ በጦርነት ወቅት አንድ ይሆናሉ። ችግር ሲመጣ አብረው ይነሳሉ። የዚህ ምክንያቱ ለዘመናት የዘለቀ የተሳሰረ ማንነታቸው ነው። የኢትዮጵያ ሕዝቦች ተሰባጥረው በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ተወራራሽ የባሕል እሴቶቻቸውን በማጎልበት በመቻቻልና በመከባበር ለአገር ልማትና ብልጽግና በጋራ እንዲቆሙ ለማስቻል በትኩረት መስራት ያስፈልጋል። ቁሳዊ ያልሆኑ ኢትዮጵያዊነትን የሚያሳዩ እሴቶችን ለአሁኑ እና ለተከታዩ ትውልድ ለማስረከብ መስራት ካልተቻለ ኢትዮጵያዊ ማንነትን አጽንቶ ማቆየት ”ላም አለኝ በሰማኝ …” አይነት ነው የሚሆነው። ባሕል የቀድሞውን ስልጣኔ እንደፈጠረ ሁሉ የዛሬውን የልማት ጥረትም ማገልገል ይጠበቅበታል፤ የነገውንም ትውልድ የመቅረጽ ሚና ይኖረዋል፡፡ እነዚህን ልማታዊና ማኅበራዊ ፋይዳዎች እውን ለማድረግ የሚያስችል ስልት

ነድፎ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባት በአገራችን እዚህም እዚያም እየተከሰቱ ላሉ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት ይጠቅማል። እሴቶቻችን የህልውናችን መሰረቶች ናቸውና አንድ በሚያደርጉን ነጥቦች ላይ ትኩረት ሰጥተን መስራት ይኖርብናል። በሐኪም የታዘዘ መድኃኒት ለህመሙ ፈውስ ስለሆነ እየመረረም ቢሆን ይዋጣል። ”በኢትዮጵያ አንዱ የገነባውን ሌላው ያፈርሳል፤ ተሃድሶ ህመም ቢኖረውም መታደስን መልመድ አለብን” የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ዶ/ር ሮባ ምክረ ሀሳብ ነው። አብሮነታችንን ለማጽናት አንደኛው መንገድ ተቋማትን ጠንካራ እና ቀጣይ እንዲሆኑ ማስቻል ነው። በኢትዮጵያ ላልይበላ፣ አክሱም፣ ፋሲለደስ፣ የሐረር ግንብ ወዘተ… የጋራችን እንደሆኑ ለልጆቻችን ማስተማር አለብን። እነዚህ አኩሪ ታሪኮች በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተቱ በማድረግ ለሁሉም ዜጎች ግንዛቤ መፍጠር እና ማስረጽ ይጠይቀናል። ይህን ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መለወጥ የውጭ አገራትን ከመናፈቅ የሚላቀቅ፣ ብሎም አገር ወዳድ ትውልድ ማፍራት የሚያስችል ትልቅ እርምጃ ይሆናል። ዶ/ር ሮባ ”ዜጎች ከብሔራቸው እየወጡ ከሌሎች ብሔሮች ጋር መላመድ አለባቸው። የባሕል ርቀቱን መቀነስ ያስፈልጋል ካልሆነ ርቀት መሄድ አንችልም። ከድሬደዋ እና ከሐረር ብዙ ትምህርት መውሰድ ይቻላል” ሲሉ ይመክራሉ። የአገር ግንባታችን በሂደት ላይ ያለ ነው፣ ጀምረነዋል፤ እያስነጠሰን፣ እያመመንም ቢሆን ፍጻሜው ያማረ እንዲሆን መስራት ይጠበቅብናል። አንድን ዛፍ ትዕግስት ኖሮን ወቅቱን ጠብቀን ከተንከባከብነው ዝናብ ይዘንባል ይለመልማል፣ ፍሬም ያፈራል። ስለዚህ መጠበቅ፣ መታገስ፣ የሚችል ትውልድ እንገንባ። የሚፈጠረው ችግር ሁላችንንም የሚጎዳ ነውና ለሚፈጠሩ ችግሮች ተጠያቂው እከሌ ነው ከማለት ቀደም ብሎ ችግሩ እንዳይፈጠር ማድረግ የሚቻልባቸውን መንገዶች በመከተል መከላከል ያስፈልጋል። ትውልዱ የሚጠይቅ እና ምክንያታዊ እንዲሆን ብዙ መስራት ይጠይቃል። አገራዊ እሴቶቻችንን በአግባቡ መጠቀም ያልቻልነው ለምንድን ነው? የሁላችንም ጥያቄ ነው። በአገራችን 50 ዩኒቨርሲቲዎች አሉ። የሃይማኖት ተቋማት ለማኅበረሰቡ ያላቸውን አበርክቶ የሚያጠና ዩኒቨርሲቲ ግን የለንም። ይህም ለጉዳዩ የሰጠነው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን ያሳያል። ክርስትናን እና እስልምናን

አስቀድመን የተቀበልን፣ የሰው ዘር መገኛ የሆነች አገር ያለችን ነን፤ ይሁንና ”ሰው የዘራውን ያጭዳል” እንደሚባለው ባልሰራናቸው የቤት ስራዎቻችን ምክንያት አሁን እየገጠሙን ለሚገኙ ችግሮች ተዳርገናል። ሲጠቃለል ኢትዮጵያ ካላደጉ አገራት መካከል ነች። በምግብ ራሷን አልቻለችም፣ ከድህነት ወለል በታች ያሉ ዜጎች አሉ። ያለነው በድህነት ውስጥ ነው፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሯዊ አደጋዎች (ረሃብ፣ ድርቅ፣ በመሳሰሉት…) እየተጠቃን ነው። በቀጣናችን ከ10 በላይ አገራትን እናዋስናለን ናይል ብዙ አገራትን ያካልላል። የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ነን። ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማስከበር የምንነሳው ይህን የቀጣናችንን ሁኔታ ታሳቢ አድርገን ነው። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ፣ በአፍሪካም ደረጃ ያላትን ቦታ የሚመጥኑ የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳዎች (Assparations) ያስፈልጉናል። ወደ ውስጥ ብቻ የመመልከት አባዜ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላትን አትራፊነት፣ ያላትን ተወዳዳሪነት ልትይዝ የሚገባትን ቦታ እንዳያሳጣት ትልልቅ ጉዳዮችን አጀንዳዎቻችን ማድረግ ያስፈልጋል። ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማስጠበቅ የምናደርገው እንቅስቃሴ እነዚህን ነጥቦች ታሳቢ ያደረገ እና ከፍ ያለ እሳቤ የያዘ እንዲሆን መስራት ያስፈልጋል። እዚህ ላይ ሰላም ቁልፍ ጉዳያችን ይሆናል፤ ቀጣናዊ ትስስሩም ኢትዮጵያዊ እሳቤ እንዲኖረው የሚያደርግ የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳ መቅረጽ ይጠበቅብናል። በዚህ መልኩ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ ተፎካካሪ እና ተወዳዳሪ ማድረግ እንችላለን። በየትኛውም አገር ላይ የማይገሰሱ የሚባሉ የአገራት ሉዓላዊነት እና የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳዎች አሉ። ቀደም ሲል ሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች ነበሩ። አሁንም በተመሳሳይ ሰላም፣ እኩልነት፣ ዴሞክራሲ ብሔራዊ ጥቅሞቻችን ናቸው። መንግሥት በአገሪቷ ያሉትን ባሕላዊ እሴቶች ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ በማዋል የዜጎችን ፍላጎት ማስታረቅ ይችላል። ”ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ ውስጥ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ስንገልጻት በዓለም አቀፍ ደረጃ ባላት ተሳትፎ ጠንካራ አድርገን የምንወስድበት በጣም ብዙ ማሳያዎች አሉ” የሚሉት ዶ/ር መሃመድ። ኢትዮጵያ የሚደረጉባት በጣም ብዙ ጫናዎችም ምንጫቸው ይህ ነው



55

ባይ ናቸው። ዜጎች አገር የሚመሰርቱት እና የሚገነቡት ጥቅማቸውን ለማስከበር ነው። ”ብሔራዊ ጥቅም ሳይከበር ምንም ዓይነት የቡድን ጥቅም ሊከበር አይችልም” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተውም ይገልጻሉ። እንደ እርሳቸው ገለጻ ከምንም በላይ የአንድን ቡድን ጥቅም ለማስከበር የሚደረጉ ጥረቶች የራሳቸው ቅደም ተከተል ሊኖራቸው ይገባል። ”ብዙዎቹ ግጭቶቻቸን እየመነጩ ያሉት ይህን ቅደም ተከተል ካለመጠበቅ ነው። ጦርነቶቻችን፣ ግጭቶቻችን በሙሉ የሚመነጩት ከብሔራዊ ጥቅም ዝቅ ብለን በምናነሳቸው ጉዳዮች ነው። ባላደገ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ባላመጣ አገር ውስጥ ለብቻው ተነጥሎ ሊያድግ የሚችል ቡድን አይኖርም” ሲሉም አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል። ከዚህ የምንረዳው ብሔራዊ ጥቅም ባልተከበረበት አገር ውስጥ የሚከበር የቡድን ጥቅም አለመኖሩን ነው። ዜጎች፣ ተቋማቶቻችን፣ ሲቪል ሰርቪሱ፣ … ወዘተ እኔ የቆምኩት ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር ነው ብለው የሚረዱ እና ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ ከሆነ አጀንዳዎቻችንን ከፍ ማድረግ እንችላለን። በዚህ ሂደት ውስጥ የቤተሰብ፣ የግለሰብ ሚና ቁልፍ ነው። ብሔራዊ ጥቅምን ቀስ በቀስ (በሂደት) እንጂ በአንድ ጊዜ ማሳካት አይቻልም። መንግሥት የአገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ነው የሚሰራው የሚለውን እምነት ስናሳድር እና ግንዛቤ ስንፈጥር ቀስ በቀስ ወደ ስኬት እናመራለን።

የአገር ግንባታ እና አገራዊ ጥቅም (State Build- ing and State Interest) ቀጣይነት ያላቸው አጀንዳዎች ናቸው። አገር በመገንባት እና በማዘመን የጋራ የሆኑ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። የእኛ ዘመን ከቀደመው ዘመን ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ይህ ትውልድ ምን ይባላል? ከዚህ አንጻር የራሳችንን አሻራ የምናስቀምጥበትን ቀጣይነት ያለው ስራ መስራት ትልቁ የቤት ስራችን ልናደርገው ይገባል። የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም በበኩላቸው”ብዙ ጊዜ የግል እና የቡድን ፍላጎት እና ጥቅሞች ትልቁን ቦታ በሚይዙበት ጊዜ ትልቁ አገራዊ ሁኔታ ይረሳል አልያም አንሶ ይታያል። ይህ ትልቅ ፈተና ነው። ትውልዱ (Self centered) ከሆነ ሌላው ግድ የማይሰጠው ይሆናል። ለአገር እና ለመላው ሕዝብ የሚለውን ነገር ይተዋል። በዚህ ምክንያት ግጭት ይፈጠርና አገር የጭቅጭቅ እና የብጥብጥ ማዕከል ትሆናለች” ሲሉ አተያየታቸውን ሰንዝረዋል። በተለይ በዚህ ዘመን ያለው ተግዳሮት አገሮች ብሔራዊ ጥቅማችንን እናስከብራለን በሚል የሚወስዱት እርምጃ ሌሎች አገሮችን ማፍረሱ እንደሆነ አንስተዋል። በቅርብ ጊዜ በእኛም አገር ላይ ሲደርስ የነበረው ተጽዕኖ መነሻው ይኸው ነው። ለእኛ የሚቆረቆሩ መስለው ፍላጎታቸውን በእኛ ላይ ለመጫን ብዙ ችግሮችን እንድንሸከም አድርገዋል። ይህ ተጽዕኖ ለብሔራዊ ጥቅማችን መከበር በራሱ ፈተና እንደሆነም አመላክተዋል። በዓለምም፣ በቀጣናውም፣

በአገራችንም በሚከናወኑት ጉዳዮች ውስጥ ብሔራዊ ጥቅማችንን ታሳቢ አድርገን መስራት ይጠይቀናል። ስለሆነም አንዱን ትተን ሌላውን ሳንል፣ ሁለቱንም በአንድነት ይዘን መጓዝ ይኖርብናል። ”አውሮፓዊያን እና ያደጉት አገራት ስለ ዛሬ እና ስለ ነገ አስበው እየሰሩ ነው። እኛ ደግሞ የትናንትናን ታሪክ መልቀቅ ነው ያቃተን። በትናንትናው ታሪክ ላይ ተቸንክረን ነገን ረስተን፣ በትናንትናው ታሪክ እየተወዛገብን ነው ያለነው፤ አሁን እዚህ ላይ ቆም ብለን ማሰብ አለብን”። ”በኢትዮጵያ የምንገነባው ማንነት መሰረቱን መደመርን፣ ወንድማማችነትን፣ እህትማማችነትን፣ አብሮነትን አድርገን፤ ግባችንን ደግሞ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት፤ ይህን እሳቤ ይዘን ነው ስለ አገረ መንግሥት ግንባታ የምንነጋገረው” ያሉት አቶ ብናልፍ የብሔር ማንነት አያስፈልግም ብለን ውድቅ በማድረግ የሚመጣ አገራዊ አንድነት እንደማይኖር በመግለጽ በዚህ እሳቤ መነሻነት ጠንካራ አገረ መንግሥት ለመገንባት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል። ይህ ለውይይት፣ ለአስተያየት፣ ለክርክር ክፍት መሆኑን፤ በቀጣይም የብሔራዊ መግባባት አጀንዳ ወደ ፊት መምጣት አለበት፤ ለአገራዊ አንድነታችን ቅድሚያ ሰጥተን መነጋገር አለብን፤ አካታች ብሔራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆንም ሁላችንም የሚጠበቅብንን እንወጣ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።



56

ማህበራዊ

ያገረሸውን ወረርሽኝ

ዳግም መግታት

በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ትብብር የተዘጋጀ



57

ያገረሸውን ወረርሽኝ

ዳግም መግታት

ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት በትንኝ የሚተላለፉ በሽታዎች በስፋት መከሰት መጀመራቸው እየተነገረ ነው። በአገራችን እንደ ዲንጊ ፊቨር፣ ቺክንጉኒያና ቢጫ ወባ በአብነት ቢጠቀሱም አሁንም በርካታ አፍሪካዊያን ሕፃናትን ለሕልፈት እየዳረገ የሚገኘው ትልቁ የጤና ችግር የወባ በሽታ ነው።

ወባ በቀይ ደም ወይንም በጉበት ውስጥ በጥገኝነት የሚኖሩ፣ የሚያድጉ፤ የሚራቡ፣ በዓይን የማይታዩና በእጅ የማይዳሰሱ ፕላስሞዲየም በመባል የሚታወቁ ረቂቅ ተህዋስያን አማካኝነት የሚመጣ በሽታ ነው። በሰዎች አካል ውስጥ በመራባትና በማደግ ለበሽታው የሚያጋልጡት አራት የወባ ተህዋስያን ዝርያዎች አሉ። እነሱም ፕላስሞዲየም ፓልሲፓረም፣ ፕላስሞዲየም ቫይቫክስ፣ ፕላስሞዲየም ማላሪያ እና ፕላስሞዲየም ኦቫሌ ይሰኛሉ።

ተህዋስያኑ ያላቸው ቅርጽ፣ እድገት፣ የትውልድ ብዛት፣ ለመራባት የሚወስዱት የጊዜ ፍጆታ፣ የበሽታው የጥቃት መጠን፣ የሚያሳዩት የግርሻ አይነትና ወቅት በመድኃኒቶች የመጠቃት ዝንባሌ፣ በአካል ውስጥ የሚያደርሱት የጉዳት አይነት የተለያየ ነው። ከእነዚሁ የወባ ተህዋሲያን ዝርያዎች መካከል በአገራችን በዋናነት በኅብረተሰቡ ላይ ጉዳት የሚያደርሱት ፕላስሞዲየም ፓልሲፖረምና

በመንገሻ ገ/ሚካኤል



58

ፕላስሞዲየም ቫይቫክስ የሚባሉት ናቸው።

ወባን መከላከል የሚቻል ቢሆንም፤ ሚሊዮኖችን ለሕመምና ለሕልፈተ ሕይወት መዳረጉን እንደቀጠለ ነው። በሽታው በርካቶችን ከሥራ አስተጓጉሎ ምርታማነት እንዲቀንስ ከማድረጉም በላይ የመከላከሉ ተግባር አገራችንን ለከፍተኛ ወጪ እየዳረጋት ይገኛል።

መንግሥት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ባደረገው ርብርብ በወባ በሽታ ምክንያት ያጋጥም የነበረውን የጤና እክልና ሞት በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ተችሎ እንደነበረ ይታወቃል። በዚህም በወረርሽኝ ደረጃ ይከሰት የነበረውን የወባ በሽታ ከመከላከል ባሻገር በሽታውን በ2030 የማጥፋት ዘመቻ ተካሂዶ አበረታችና ተስፋ ሰጪ ውጤት ማግኘት ተችሏል። በዚህም ኢትዮጵያ በወባ በሽታ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ከ40 በመቶ በታች ማውረድ ከቻሉ የአፍሪካ አገራት አንዷ መሆን ችላለች።

ይሁንና እ.ኤ.አ ከ2020 ጀምሮ በኮቪድ- 19 ወረርሽኝ ሳቢያ ባጋጠመው የመድኃኒት የአቅርቦት እጥረት፣ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥና በአንዳንድ አካባቢዎች አጋጥሞ በነበረ የፀጥታ ችግር ምክንያት የወባ ወረርሽኝ ዳግም አገርሽቷል። ይህን ችግር ለመሻገርና ኢትዮጵያ የወባ በሽታን ለማጥፋት ተቃርባ ወደነበረችበት ደረጃ ላይ መድረስ የሚያስችል ጠንካራ የሦስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ተነድፎ ወደ ሥራ ተገብቷል፤ ለተግባራዊነቱም የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው። ለስትራቴጂክ ዕቅዱ ተፈጻሚነት ድጋፍ ማድረግን ዓላማው ያደረገ ዓለም አቀፍ ጉባዔም በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በቅርቡ ተካሂዷል። በዚህ ጽሑፍ በጉባዔው የቀረቡ ሪፖርቶች፣ የጉባዔው አካል የነበረው አውደ- ርዕይ እና የሁሉንም ትኩረት የሳቡ አዳዲስ የወባ መከላከያ ቴክኖሎጂዎች በወፍ በረር ይዳሰሳሉ።

ወባን ለመቆጣጠር ያስቻሉ አሰራሮችን በአፍሪካ መተግበር

ወባ በቀይ ደም ወይንም በጉበት

ውስጥ በጥገኝነት የሚኖሩ፣

የሚያድጉና የሚራቡ፣ በዓይን

የማይታዩና በእጅ የማይዳሰሱ

ፕላስሞዲየም በመባል የሚታወቁ

ረቂቅ ተህዋስያን አማካኝነት

የሚመጣ በሽታ ነው። በሰዎች

አካል ውስጥ በመራባትና በማደግ

ለበሽታው የሚያጋልጡት አራት

የወባ ተህዋስያን ዝርያዎቸ

ፕላስሞዲየም ፓልሲፓረም፣

ፕላስሞዲየም ቫይቫክስ፣

ፕላስሞዲየም ማላሪያ፣

ፕላስሞዲየም ኦቫሌ ይሰኛሉ።



59

በጉባዔው ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል በአፍሪካ ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የወባ በሽታን የመከላከልና የመቆጣጠር የአሰራር ሥርዓትን ማጎልበት የሚለው አንዱ ነው። በዓለም 100 የሚጠጉ አገራት ውስጥ የወባ በሽታ ተወግዷል አልያም ቀንሷል፤ ወባ በማኅበረሰቡ ዘንድ የጤና ስጋትና የኢኮኖሚ ተግዳሮት ወደማይሆንበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ለዚህ ውጤት ዋነኛው ምክንያት ማኅበረሰቡ በየአካባቢው ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ የሆኑ ቦታዎችን አስቀድሞ ማዳፈንና ማፅዳት እንዲሁም የወባ ትንኝ ዕጮችን ማጥፋትና ሌሎች የቁጥጥር እርምጃዎችን መውሰድ መቻሉ ነው። በሌሎች አገራት የወባ በሽታን በተሳካ ሁኔታ መከላከልና መቆጣጠር ያስቻሉ አሰራሮች በአፍሪካ አገራትም በመተግበር ላይ ናቸው።

በአዲስ ፈጠራና ግኝት የወባ ትንኝን መቆጣጠር

ዋና ትኩረቱን የወባ ትንኝ ቁጥጥር ላይ አድርጎ

የመከረውና በቅርቡ በኢትዮጵያ የተካሄደው 9ኛው ዓለም አቀፍ የወባ ትንኝ ቁጥጥር ጉባዔ ላይ የወባ ትንኝን ለመቆጣጠርና ለማጥፋት የሚረዱ የተለያዩ አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶች ቀርበዋል።

በወባ ቁጥጥር አውድ ውስጥ ዋነኛው የመቆጣጠሪያ ዘዴ ለወባ ትንኞች መራቢያ ምቹ የሆኑ ውኃ ሊያቆሩ የሚችሉ ቦታዎችን ማጥፋት ነው። እንዲህ ዓይነቱ የውኃ አካላት አያያዝ የሚካሄደው የወባ ትንኝ እንቁላል ወይም ዕጮች እድገትን በመከላከልና ጎልማሳ ትንኞች እንዳይፈጠሩ በማገድ ነው። የዚህ ስልት ዋነኛ ዓላማው የወባ ስርጭትን መከላከልና መቆጣጠር ነው።

ከዓለም አቀፉ ጉባዔ ጎን ለጎን በተካሄደው ኤግዚቢሽን ከቀረቡት የወባ በሽታ መከላከያ አማራጮች አንዱ የወባ ትንኝ ከዕጭነት አልፎ ወደ በራሪ ነፍሳትነት ሳይቀየር በአጭሩ እንዲገታ የሚረዳ ነው። ይህ አዲስ ምርት ለገበያ የቀረበው ሱሚላርቭ በሚል ስያሜ ነው። ምርቱ ባለ

5 ነጥብ 5 ሴንቲ ሜትር ስፋት ያለው ክብ የፕላስቲክ ዲስክ ሲሆን፤ አገልግሎቱም የወባ ትንኝ ዕጭ ተፈልፍሎ ወደ ትንኝነት እንዳይለወጥ በአጭሩ የሚገታ ነው፤ የወባ ትንኞች እንዳይራቡ በማድረግ የወባ በሽታን ይከላከላል።

የሱሚላርቭ ዲስክ ከ40 እስከ 500 ሊትር የሚሆን ውኃ ውስጥ በማስቀመጥ መጠቀም የሚቻል ሲሆን፤ ዲስኩ ከውኃው ስር በመቀመጥ ለረጅም ጊዜ ኬሚካሎችን በመርጨት የወባ ትንኝ መራባትን ይከላከላል። ይህ ምርት ለረጅም ጊዜ ውኃ ውስጥ ተቀምጦ የወባ ትንኝን የሚያጠፋ ኬሚካል ከመርጨት በተጨማሪ ውኃውን መቀየር ቢያስፈልግ እንኳ አገልግሎቱ አይቋረጥም፤ ይህ ማለት ማቆሪያው ውስጥ ያለውን ውኃ ደጋግመን እየቀየርን ዲስክ ሳንቀይር መጠቀም ያስችለናል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የሱሚላርቭ ዲስክ በአገራችን ሙከራ ተደርጎበታል። አዋሽ አካባቢ ሙከራውን ያደረገው የጅማ ዩኒቨርሲቲ ነው። የሙከራው ውጤትም እጅግ አበረታች



60

ነው። ለ31 ቀናት በተካሄደው የመስክ ሙከራ የሱሚላርቭ ዲስክ የተደረገባቸው የውኃ ጀሪካኖች ውስጥ የተቀመጡ የወባ ትንኝ ዕጮች አንዳቸውም ተፈልፍለው ወደ ወባ ትንኝነት ሳይለወጡ ቀርተዋል። ይህ ምርት በአገራችን ቢሰራጭ የወባ ትንኝ መራባትን በቀላሉ መከላከል የሚያስችል ነው።

ፍሉዶራ ፊዩዥን፡-

ፍሉዶራ ፊዩዥን ሁለት አይነት የኬሚካል ውህዶችን በመቀላቀል የሚረጭ ጸረ-ወባ ትንኝ ኬሚካል ሲሆን፤ በተለይም በተለምዶ በሚረጩ ኬሚካሎች አልጠፋ ያሉ የትንኝ ዝርያዎችን ለማጥፋት እንደሚያስችል የተመሰከረለት ነው። ምርቱ በ16 አገራት የተሞከረ ሲሆን እስከ 12 ወራት ድረስ አካባቢን ከትንኝ መከላከል ያስችላል። ምርቱ በተለይም በቤት ውስጥ ርጭት የወባ ትንኞችን ለማጥፋት አሁን ካሉት ኬሚካሎች የተሻለ ውጤት ማስመዝገብም ችሏል።

በአዲስ ቅርፅ ለገበያ የቀረበ የጸረ-ወባ ኬሚካል መርጫ መሳሪያ

በጎይዘፐር ግሩፕ በአዲስ ቅርፅ ለገበያ የቀረበ የጸረ-ወባ ኬሚካል መርጫ መሳሪያ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ስያሜው አይ.ኬ ቬክተር ኮንትሮል ስፕሬየር (IK Vector Control Spryer) በመባል ይታወቃል። ይህ የኬሚካል መርጫ መሳሪያ ከተለምዶው የተለየ ገጽታ ተላብሶ ነው የቀረበው። መሳሪያውን ከተለመደው የፀረ-ወባ ኬሚካል መርጫ መሳሪያ ለየት የሚያደርገውና የላቀ ፋይዳው ኬሚካል የተረጨበት ስፍራ ሙሉ ለሙሉ በኬሚካል እንዲሸፈን እንዲያደርግ ተደርጎ መፈብረኩ ነው።

ከዚህም ባሻገር ለአያያዝ ቀላልና አመቺ፣ አካባቢን የማይበክል፣ በቀላሉ ለመጠቀምና ለመጠገን የሚያስችል ጠንካራ መሆኑ ከሌሎች መሰል ምርቶች የተሻለ ሆኖ መቅረቡ ነው።

የወባ ትንኞችን የመግደል አቅም ያጎለበተው አጎበር-ኦሊሴት ፕላስ፡-

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር ብዙዎችን ከወባ በሽታ በመከላከልና በመታደግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። አጎበር እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የወባ በሽታ አስተላላፊ ትንኞች (የወባ ትንኝ) ሰዎችን እንዳይነክሱ አልጋን ጨምሮ መኝታቸውን በመጋረድ ራሳቸውን ከወባ ትንኝ ብሎም ከበሽታው ይከላከሉ ነበር። አሁን ለተመራማሪዎች ምስጋና ይድረሳቸውና አጎበር ሰዎች በወባ ትንኝ እንዳይነደፉ ከመከላከል ባለፈ የማጥፋት ሁለገብ ፋይዳ እንዲኖረው ተደርጓል። የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር “በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” እንዲል ሀገራዊ ብሂሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፀረ-ወባ ትንኝ ኬሚካል ተነክሮ ጥቅም ላይ እንዲውል በመደረጉ የወባ ትንኞችን መከላከል ብቻ ሳይሆን የማጥፋት አቅም እንዲኖረው በመደረጉ ሰዎችን ከወባ በሽታ በአያሌው እየታደገ ነው። ቀደም ሲልም የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር በፀረ- ወባ ትንኝ ኬሚካል ይነከር አልነበረም እንዴ፤ ታዲያ ይህ አዲሱ ኦሊሴት ፕላስ የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር ምን አዲስ ነገር ይዞ ቀረበ? የሚል ጥያቄ ካጫረባችሁ አጎበሩን ልዩ የሚያደርገው



61

እንደ ቀድሞው ከተመረተ በኋላ የፀረ-ወባ ትንኝ ኬሚካል የሚነከር ብቻ ሳይሆን ኬሚካሉ ከአጎበሩ ስሪት ጋር አብሮ ተዋህዶ መመረቱ ነው። ይህ የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር በተደጋጋሚ ቢታጠብ እንኳን ከአጎበሩ ክር ጋር አብሮ ተዋህዶ የተመረተው የፀረ-ወባ ትንኝ ኬሚካል የወባ ትንኞችን መግደሉን ሳያቋርጥ ለረጅም ጊዜ ማገልገሉ ሌላው የተለየ የሚያደርገው ጉዳይ ነው። ከፍተኛ ውጤት እንዳስገኘ የሚነገርለት ይህ የፀረ-ወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር በቀላሉ አልጠፋ ያሉ የትንኝ ዝርያዎችን ሳይቀር የመከላከል እቅም ስላለው ልዩ ያደርገዋል። ከዚህም ባሻገር በሰውና በሌሎች እንስሳት ላይ ጉዳት የማያደርስ ስለመሆኑም በዓለም የጤና ድርጅት የተመሰከረለት ነው።

የወባ ዕንቁላል ሲፈለፈል ትንኙን ተባዕት ብቻ የሚያደርግ የቴክኖሎጂ ውጤት- ኦክስቲክ

ቴክኖሎጂው የወባ ትንኝ ማራቢያ የፕላስቲክ ሳጥን (ኦክስቲክ) ሲሆን፤ ይህ ደግሞ ከሌሎች የወባ በሽታ መከላከያ ዘዴዎች የተለየ ነው።

ልዩ የሚያደርገው ደግሞ ሳጥኑ ውስጥ የወባ ትንኝ እንቁላል ተሞልቶ የሚመጣ ሲሆን፤ እንቁላሎቹ ሲፈለፈሉ ሁሉም ተባዕት (ወንድ) የወባ ትንኝ ሆነው ነው። እነዚህ ወንድ የወባ ትንኞች ከሌሎች የወባ ትንኞች ጋር ሲራቡ የሚፈለፈሉት ዕጮችም እንዲሁ ሙሉ በሙሉ ወንድ ትንኞች ይሆናሉ። በዚህም ሴት የወባ ትንኞች ቁጥር እየቀነሰ ይመጣና በመጨረሻም ይጠፋሉ። ይህ አዲስ የቴክኖሎጂ ውጤት በአሁኑ ወቅት በብራዚል በሙከራ ላይ የሚገኝ ሲሆን በቅርቡም ሙከራውን በተመሳሳይ በጎረቤት ጅቡቲ ለማካሄድ ከሀገሪቱ መንግሥት ፈቃድ እየተጠበቀ መሆኑን የቴክኖሎጂው አምራች ድርጅት ይፋ አድርጓል።

የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶች ለገበያ መቅረባቸው እጅግ አበረታች ነው። ሆኖም በሽታን መከላከል ላይ ትልቅ ለውጥ ማምጣት የሚቻለው በክትባት እንደሆነ በበርካቶች የዘርፉ ተመራማሪዎች ይታመናል። ለመሆኑ በሙከራ ላይ የሚገኘውና ተስፋ የተጣለበት የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት ከምን ደረሰ?

ተስፋ የተጣለበት የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት

የወባ በሽታ መድኃኒቶች እና የወባ ትንኝ ለመቆጣጠር የሚወሰዱ እርምጃዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በሽታው እንዲቀንስ አድርገዋል። ሆኖም ይህ ተስፋ ሰጪ ውጤት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቀንሶ ታይቷል። በመሆኑም የወባ በሽታን በዘላቂነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የበሽታው መከላከያ ክትባት አስፈላጊነት ከምንጊዜውም በላይ ተረጋግጧል።

በመሆኑም ገዳይ ከሆኑ ተላላፊ በሽታዎች መካከል አንዱ የሆነውን የወባ በሽታ መከላከል የሚያስችል የመጀመሪያው ክትባት ይፋ ተደርጓል። ክትባቱ በየዓመቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናትን ከበሽታው ሊታደግ እንደሚችል ታምኖበታልም። የዓለም ጤና ድርጅት በታዳጊ አገራት ውስጥ የወባ በሽታን ለመከላከል ትልቅ ተስፋ የተጣለበትን ይህን የመጀመሪያውን ክትባት አፅድቆታል። ፍቱንነቱና ውጤታማነቱ የተረጋገጠው ይህን የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት ተደራሽ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራው እየተከወነ ነው።



62

ማህበራዊ

የልህቀት ማዕከልነት ራዕይ

የሰነቁት ትምህርት ቤቶች በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ እና በኢትዮጵያ ዜና

አገልግሎት ትብብር የተዘጋጀ



63

የልህቀት ማዕከልነት ራዕይ

የሰነቁት ትምህርት ቤቶች በመንገሻ ገ/ሚካኤል

በ1939 ዓ.ም የተመሠረተው የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ በጤና አገልግሎት መልካም አሻራ በማሳረፍ በስኬት ጎዳና እየተጓዙ ከሚገኙ ሆስፒታሎችና የሕክምና ኮሌጆች በግንባር ቀደምነት የሚጠቀስ ነው። የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ በሆስፒታልነት ብቻ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን ከኢትዮጵያ ሚሊኒየም በኋላ የሕክምና ኮሌጅ በመክፈት በርካታ የጤና ባለሙያዎችን በማፍራት ላይ ይገኛል።

የሕክምና ኮሌጁ በቅድመ እና ድህረ ምረቃ እንዲሁም በተለያዩ የስፔሻሊቲ ፕሮግራሞች በየዓመቱ በርካታ ባለሙያዎችን በማስመረቅ ለሀገሪቷ በጤና ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው። በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የአካዳሚክና ምርምር ምክትል ፕሮቮስት በሚል ስያሜ የተዋቀረው ኮሌጁ በስሩ ሦስት ትምህርት ቤቶችን ይዟል የነርሲንግ፣ የሕክምና እና የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤቶችን። በተለያዩ ፕሮግራሞች ማስተማር፣ ጥናትና ምርምር ማካሄድና የማኅበረሰብ አገልግሎት መስጠት ለአካዳሚክ እና ምርምር ኮሌጁ የተሰጡ ዋና ዋና ተልዕኮዎች ናቸው። ይህ ጽሑፍ የትምህርት ቤቶቹን አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ ይዳስሳል።



64

የነርሲንግ ትምህርት ቤት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ ከሚገኙት ሦስት ትምህርት ቤቶች መካከል ነርሲንግ ትምህርት ቤት አንዱ ነው። በኢትዮጵያ የነርስ ትምህርት ቤቶች ከቀደምቶቹ አንዱ ነው። ከ1964 ዓ.ም በፊት የተመሰረተው ኮሌጁ በመጀመሪያ ነርሶችን በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ዘመኑ በደረሰበት የነርስ ሙያን በዲፕሎማ በማሰልጠን ይታወቃል። በመላ ኢትዮጵያ የሕክምና ኮሌጅ ከተመሰረተ በኋላ ግን በመጀመሪያ ዲግሪ ማሰልጠን ብቻ ሳይሆን በሁለተኛ ዲግሪ የነርሲንግ ትምህርት ይሰጣል። በአሁኑ ወቅት በሁሉም ፕሮግራሞች በድምሩ 220 ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል። በትምህርት ቤቱ ስር በመጀመሪያ ዲግሪ አምስት፤ በሁለተኛ ዲግሪ ደግሞ ስድስት ትምህርት የሚሰጥባቸው ፕሮግራሞች ይገኛሉ። በመጀመሪያ ዲግሪ የሚሰጡ የትምህርት መስኮች የሚከተሉት ናቸው። እነርሱም የቀዶ ሕክምና ነርሲንግ(Surgical Nursing) ፣ ኦፕሬሽን ቲያትር ነርሲንግ (Operation The- atre Nursing) ፣ የሕፃናት ነርሲንግ (Pedi- atrics Nursing ) ፣ የጨቅላ ሕፃናት ነርሲንግ( Neonatal Nursing ) እና የድንገተኛ እና ጽኑ ህሙማን ነርሲንግ( Emergency and Critical care Nursing) ናቸው። በሁለተኛ ዲግሪ ደግሞ የሚሰጡት የትምህርት መስኮች ካርዶቶራሲክ፣ ካርዶቫስኩላር፣ ፓራሜዲክስ፣ የድንገተኛ እና ጽኑ ህሙማን ነርሲንግ፡ የጨቅላ ሕፃናት ነርሲንግ እና ኦንኮሎጂ ነርሲንግ ናቸው። ክሪቲካል ኬር ነርሲንግ እና ኒኦናታል ነርሲንግ የተሰኙት የትምህርት ዘርፎች ደግሞ በሁለቱም መርሃ ግብሮች የሚሰጡ ናቸው። ትምህርት ቤቱ ኒኦናታል ነርሲንግ፣ ኦንኮሎጂ ነርሲንግ እና ክሪቲካል ኬር ነርሲንግ በሁለተኛ ዲግሪ (በማስተርስ) ደረጃ ማስተማሩ ከሌሎች ተመሳሳይ ተቋማት የተለየ ያደርገዋል። የነርሲንግ ትምህርት ቤት የሬዚደንስ ፕሮግራም በማስጀመር በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ትምህርት ክፍል እንደሆነ የሚናገሩት የትምህርት ቤቱ ዲን ረዳት ፕሮፌሰር ፈይሳ ለሜሳ ቀደም ሲል በፅንሰ ሃሳብ ብቻ ይሰጥ የነበረውን የማስተርስ ፕሮግራም በአሁን ወቅት ከታካሚዎች ጋር በመሆን በተግባር የተደገፈ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን አብራርተዋል። በዚህም ከትምህርት ቤቱ የሚመረቁ ነርሶች በችሎታ፣ በእውቀት፣ በአመለካከት ብቁ ሆነው እየወጡ ነው ይላሉ።

እንደ ካርዶቶራሲክና ፓራሜዲክስ የመሳሰሉ የማስተርስ ፕሮግራሞች በመስጠትም በሀገሪቱ ብቸኛው ትምህርት ቤት ነው። የፓራሜዲክስ ተማሪዎች ይበልጥ ትኩረት የሚያደርጉት በቅድመ ሆስፒታል ሕክምና ሲሆን ይህም አደጋ ከተከሰተበት ቦታ እስከ ሆስፒታል ድረስ ምን ዓይነት ሕክምና ያስፈልጋል የሚለውን የሚያጠቃልል ነው። እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለጻ ተማሪዎቹ ከኮሌጁ ከሚያገኙት እውቀት በተጨማሪ ለአራት ወራት ወደ ኖርዌይ በመሄድ ልምምድ እንዲያደርጉ ይደረጋል። በሀገር ውስጥም በውጭም በቀሰሙት እውቀት በአቤት ሆስፒታል፣ በእሳት አደጋ መከላከል ዙሪያ በሚሰሩ ተቋማት እንዲሁም ጠብታ በመሳሰሉት የአምቡላንስ አገልግሎቶች በመግባት የላቀ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ነው። የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ ነርሲንግ ትምህርት ቤት ከመማር ማስተማር በተጓዳኝ የማኅበረሰቡን ችግሮች የሚፈቱ የጥናትና የምርምር ስራዎችን ያከናውናል። የነርሲንግ ሙያን የሚያሳድጉ፣ የሕክምና አገልግሎት ጥራትን የሚያሻሽሉ እና እንደ ካርዲያክ፣ ካንሰር፣ ስኳር የመሳሰሉ ተላላፊ

ያልሆኑ በሽታዎችን ስርጭት መቀነስ የሚያስችሉ ርዕሰ ጉዳዮች በጥናት እና ምርምሩ ትኩረት የሚደረግባቸው ዘርፎች ናቸው። የትምህርት ቤቱ በ2013 ዓ.ም ከ30 በላይ ጥናቶች በዓለም አቀፍ የምርምር መጽሔት (ጆርናል) ያሳተመ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት 80 ጥናቶችንና ምርምር ስራዎችን ለማሳተም አቅዶ እየሰራ ነው። የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በሚያዘጋጀው ዓመታዊ ጥናት ጉባኤ የሚቀርቡ የጥናት ውጤቶችን በታዋቂ የምርምር መጽሔቶች (ጆርናሎች) ላይ በማሳተም በኮሌጁ ከሚገኙት ሦስት ትምህርት ቤቶች የነርሲንግ ትምህርት ቤት ቀዳሚ በመሆን መመረጥም ችሏል። የነርሲንግ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ትምህርታቸው በሚያጠናቅቁበት እና በእረፍት ጊዜያቸው በተለያዩ የጤና ተቋማት ተመድበው ማኅበረሰቡን በነፃ ያገለግላሉ። የማኅበረሰቡን የጤና ችግሮች በመለየት በሁሉም ዲፖርትመንቶች የሚገኙ ተማሪዎች የራሳቸውን እንቅስቃሴ ያደርጋሉ። ተማሪዎቹ በኮልፌ አካባቢ ለሚገኙ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች መጸዳጃ ቤቶች ከራሳቸው በማዋጣትና ከሌሎችም ባለድርሻ



65

አካላት ገንዘብ በማሰባሰብ የነዋሪዎችን ችግር መፍታታቸውን ረዳት ፕሮፌሰር ፈይሳ ለአብነት ጠቅሰዋል። የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የነርሲግ ትምህርት ቤት በኖርዌይ ከሚገኘው ኦስሎ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በ2017 የፒ.ኤች.ዲ ፕሮግራም ለመጀመር እቅድ ይዞ እየሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል። ትምህርት ቤቱ የመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራሞችን በመቀነስ በማስተርስ ፕሮግራም ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት የላቀ ትምህርት መስጠት እንደሚፈልግ የሚናገሩት ዶ/ር ፈይሳ በቀጣይ ትምህርት ቤቱን ወደ ነርሲንግ ልህቀት ማዕከል ከፍ ለማድረግ እየሰራን ነው ብለዋል። ትምህርት ቤቱ ከሚያከናውናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት አንፃር ለቢሮና ለማስተማሪያ የሚሆኑ በቂ ክፍሎች አለመኖር፤ እንዲሁም ለጥናትና ምርምር የሚሆን በቂ በጀት አለማግኘት በዋነኝነት የሚጠቀሱ ተግዳሮቶች ናቸው። በትምህርት ቤቱ የሚስተዋለው የቦታ ጥበት በማስተማር ሂደቱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን ረዳት ፕሮፌሰር ፈይሳ ገልጸው፤

ለጥናት እና ምርምር የሚመደበው በጀት አነስተኛ መሆኑም የጥናት ስራዎችን በአግባቡ ለመከወን ማነቆ እንደሆነባቸው ነው የተናገሩት።

የሕክምና ትምህርት ቤት የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የሕክምና ትምህርት ቤት በተለያዩ ፕሮግራሞች ያስተምራል፣ ጥናት ያካሂዳል። የሕክምና አገልግሎትም ይሰጣል። ትምህርትን በተመለከተ በቅድመ ምረቃ ፣ በ20 ስፔሻሊቲ ፕሮግራም እና በ24 ሰብ ስፔሻሊቲ ፕሮግራሞች ትምህርት ይሰጣል። ከቅድመ ምረቃ ተማሪዎች ጀምሮ ጥናትና ምርምር ያካሂዳል። ዶክተር ማርያማዊት አስፋው የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የሕክምና ትምህርት ቤት ዲን ናቸው። እንደ እርሳቸው ገለጻ ትምህርት ቤቱ የውስጥ ደዌን፣ የማህፀንና ፅንስ ሕክምና ስፔሻሊቲን፣ በሕፃናት ሕክምና የሬዚደንስ ፕሮግራምን፤ የዓይን፣ ከአንገት በላይ ሕክምናን ጨምሮ በርካታ የሬዚደንሲ ፕሮግራሞች በማስተማር ላይ ይገኛል። የጥርስ ሕክምና እና የመንጋጭላ ኦፕራሲዮን የሚሰሩ



66

ሐኪሞችን ቀጥታ በራሱ አወዳድሮ በመቀበል ትምህርት እየሰጠም ነው። ዶ/ር ማርያማዊት እንዳሉት በትምህርት ቤቱ በኦፕራሲዮን ክፍሉ የንቅለ ተከላ ሰብ-ስፔሻሊቲ ፕሮግራም ትምህርት ይሰጥ የነበረ ቢሆንም አሁን ተቋርጧል። ለንቅለ ተከላ ሕክምና የሚያስፈልጉ አቅርቦቶች በቀላሉ በሀገር ውስጥ ስለማይገኙና በግዥም የሚገኙበት ዕድልም አነስተኛ መሆኑ እንደዋነኛ ምክንያት ይጠቀሳል። ነገር ግን እንደ አገር ተፈላጊ ከሆኑ የሕክምና አገልግሎቶች አንዱ ነው ይላሉ። በዚህ ሕክምና ዘርፍ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በአገራችን ቀዳማይ ተቋም ነው። የእናቶች ጤና እና አገልግሎቱን የላቀ ለማድረግ የተለያዩ የትምህርት ፕሮግራሞች ይሰጣሉ። ትምህርት ቤቱ ከማኅበረሰብ አገልግሎት ጋር ተያይዞ ከቅድመ ምረቃ እስከ ድህረ-ምረቃ ያሉ ተማሪዎች ነፃ የሕክምና አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ያደርጋል። ለምሳሌ በየዓመቱ ከአንገት በላይ ሕክምና፣ የዓይን ሕክምና፣ የሴቶች ቅድመ ካንሰር ምርመራ ላይ የማኅበረሰብ አገልግሎቶችን ይሰጣሉ። እንደ ዶ/ር ማርያማዊት ገለጻ ከትምህርት ቤቱ ቀጣይ የትኩረት መስኮች ዋነኛው በትምህርት ጥራት ላይ መስራት ነው። በኮሌጅ ደረጃ የሚገኘው ትምህርት ቤት ራሱን የቻለ ዩኒቨርሲቲ የመሆን ራዕይ አለው። የትምህርት ሥርዓቱ ሲሻሻል የሕክምና አገልግሎቱም በዛው ልክ ይሻሻላል። “የእኛ ተማሪዎች ትልልቅ ቦታዎች ላይ የመግባት እድላቸው ሰፋ ያለ ነው፤

ይህን ጠንካራ ጎን በማስቀጠል የሚጎድሉትን ለመሙላት በትኩረት እንሰራለን”። እንደ ሀገር ተግባራዊ ለማድረግ የተያዘውን የፕሮግራም አክሪዲቴሽን ለማሳካት የኢፌዲሪ ትምህርትና ሥልጠና ባለስልጣን፣ ከሕክምና ማኅበርና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ ይሰራል። ዶ/ር ማርያማዊት አያይዘውም የበጀት እጥረት የሕክምና ትምህርት ቀዳሚው ችግር መሆኑን መጥቀስ ተገቢ ነው ይላሉ። ዘርፉ በጣም ብዙ ፈላጊ ያለው በመሆኑ በክፍያ ማነስ ሳቢያ ከፍተኛ የመምህራን ፍልሰት እያጋጠመ ስለመሆኑ ይናገራሉ። መንግሥት ችግሩን ለማቃለል ሰራተኞቹን በተለያዩ መንገዶች ሊደጉማቸው ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የሕብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ ከሚገኙ ሦስት ትምህርት ቤቶች አንዱ ነው። ኮሌጁ ሲመሰረት የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ክፍል ሆኖ ነው የተቋቋመው። መጋቢት 2001 ዓ.ም ሆስፒታሉ በአዋጅ ወደ ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅነት ሲያድግ የሕብረተሰብ ጤና ትምህርት ክፍል በሥሩ ሁለት ዲፓርተመንቶችን ይዞ ወደ ትምህርት ቤት አደገ። ዲፓርትመንቶቹም ኢፒዲሞሎጂ እና ሥነ-ተዋልዶ ጤና (Repro- ductive Health)፣ የስነ ምግብ ሳይንስ (Nu- trition) ፣ሄልዝ ፕሮሞሽን እና ሄልዝ ሰርቪስ ማኔጅመንት ናቸው። የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት ተወካይ እና የኢፒዲሞሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር አማን የሱፍ እንዳሉት ትምህርት ቤቱ ዋና ስራው ከመማር ማስተማሩ በተጨማሪ የማኅበረሰቡን የጤና ችግር መለየት ነው። የበሽታን ስርጭትና በመንስኤው ዙሪያ መረጃ በመሰብሰብና በመተንተን የኅብረተሰቡን የጤና ችግር በመለየት ለፖሊሲ አውጪዎች የመፍትሄ ሃሳቦችን በማቅረብ ጉልህ ድርሻም አለው። ትምህርት ቤቱ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በፊልድ ኢፒዲሞሎጂ (Masters of Public Health in Field Epidemiology/ በማስተርስ ፕሮግራም ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል። የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅን ጨምሮ በሀገሪቱ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች በስፔሻሊቲ ደረጃ የሚሰጥ ሲሆን ፕሮግራሙ በሀገር አቀፍ ደረጃ በጤና ሚኒስቴር የሚመራ ነው። እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለጻ ትምህርት ቤቱ በተጨማሪም በ Masters of public health in epidemiology፣ Masters of public health-General (MPH)፣ Masters of Public health in Nutrition ፕሮግራሞች ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ይገኛል። በዚህ ዓመት Masters of public health in health com- munication and promotion ለመጀመሪያ ጊዜ ጀምሯል። በፒኤችዲ ፕሮግራምም በፐብሊክ ሄልዝ ማስተማር ጀምሯል። ትምህርት ቤቱ የሚሰጣቸውን የትምህርት ፕሮግራሞች በየጊዜው እያሰፋ በመሄድ ላይ ይገኛል። የኮሌጁ የሕክምና ተማሪዎች በንድፈ ሃሳብ ያገኙትን እውቀት ቀደም ሲል ወራቤ፤ አሁን ደግሞ ወደ ሱሉልታ ሄደው የማኅበረሰቡን



67

የጤና ችግር በተግባር እንዲለዩ እየተደረገ ነው። በዚህም ተማሪዎች ባላቸው አቅምና ጊዜ ማኅበረሰቡን ለማስተማር ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመለየት ፕሮጀክት ቀርጸው ትምህርት የመስጠት፣ መፍትሄውን የማስቀመጥ ተግባራትን እንደሚያከናውኑ ረዳት ፕሮፌሰር አማን ያስረዳሉ። ትምህርት ቤቱ ከሚሰጣቸው ፕሮግራሞች በተጨማሪ ለሕክምና ትምህርት ቤት የሕክምና ተማሪዎች፣ የስፔሻሊቲ ተማሪዎች እና የሰብ ስፔሻሊቲ ተማሪዎችን መመረቂያ ጽሑፋቸውን በማማከር ጉልህ ድርሻ እንዳለው ረዳት ፕሮፌሰሩ ይገልጻሉ። ትምህርት ቤቱ ከኅብረተሰብ ጤና ጋር ተያይዞ በሚካሄዱ ሀገር አቀፍ ጥናቶች ላይም የድርሻውን እያበረከተ ይገኛል። እንደ ሌሎቹ ትምህርት ቤቶች የበጀት እጥረት በጥናትና ምርምር ስራዎቹ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው። በቂ የመማሪያ ክፍሎችና ቢሮዎች አለመኖሩም የትምህርት ቤቱ ሌላው ተግዳሮት ነው።

ረዳት ፕሮፌሰር አማን አክለውም “የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታልን ወደ ሕክምና ዩኒቨርሲቲ፤ የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤቱን ወደ ኢንስቲትዩት የማሳደግ ራዕይ አለን። ፕሮግራሞቹን ስፋትና ጥልቀት እንዲኖራቸው በማድረግ የምርምር ማዕከላት እንዲኖሩን እንሻለን። በተለይ በተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች፤ በሕብረተሰቡ የሚከሰቱ ድንገተኛ ወረርሽኝና አደጋዎች የላቀ የትምህርት ማዕከል ማድረግ እንፈልጋለን። የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ ሦስቱም ትምህርት ቤቶች የሚጋሩት አንድ ራዕይ አላቸው። እሱም ሜዲካል ኮሌጁ ወደ ዩኒቨርሲቲ አድጎ ማየት ነው። ያላቸውን አቅም አሟጠው በመጠቀም በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወደዳሪ፣ ብቁ የጤና ባለሙዎችን ማፍራት ነው። የሀገሪቷን የጤና ሥርዓት የሚያሻሽሉ፣ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በበለጠ ትጋት በመስራት የማኅበረሰቡን የጤና ችግሮች ማስወገድ ነው።



68

ማህበራዊ

ጥሎ ከማለፍ … አብሮ መጓዝ



69

ጥሎ ከማለፍ … አብሮ መጓዝ

በቆንጂት ተሾመ

እ.ኤ.አ 1980፤ ምሩጽ ይፍጠር በሞስኮ ኦሎምፒክ በ10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ አሸንፎ ሁለተኛ የወርቅ ሜዳልያ ለማሸነፍ የአምስት ሺህ ሜትር ሩጫ ውድድር ላይ ነው። ምሩጽ የመጨረሻው ዙር ላይ ደርሷል። ርቀቱ ሊጠናቀቅ 300 ሜትር ሲቀር ሁሌም አፈትልኮ በመሮጥ እንደሚያሸንፍ ይታወቃል። ይህንን አስቀድመው የተረዱት ተፎካካሪዎቹ ወደፊት ማምለጫ ቦታ እንዳያገኝ ዙሪያውን አጥር ሰርተው መንገድ ዘጉበት። በቅርብ ርቀት ከፊት ለፊቱ እየሮጠ የሚገኘው የሀገሩ

ልጅ መሐመድ ከድር ምሩጽ ወደፊት ከሚያፈተልክበት ሰዓት ሲዘገይበት ወደኋላው ዞሮ ፈለገው። ወዲያውኑም መውጫ ቀዳዳ በማጣት መቸገሩን ተረዳ። እናም እሱን ለማሳለፍ የራሱን መንገድ ለመልቀቅ ወሰነ። ራሱን ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ በስተቀኙ በኩል ወዳለው አውሮጳዊ ሯጭ በመጠጋት ምሩጽ በስተግራው እንዲያልፍ ክፍተት ፈጠረለት። “ና ወደፊት እለፍ” ሲልም በእጁ ምልክት ሰጠው።

ምሩጽ ለአፍታም ሳያመነታ ያገኛትን ቀጭን መንገድ ተጠቅሞ ወደፊት ተፈተለከ። ተቀናቃኞቹ



70

አጥሩን ጥሶ ማለፉ አስደንግጧቸው ሊከተሉት ሞከሩ። አልደረሱበትም። ምሩጽ ውድድሩን በአሸናፊነት አጠናቀቀ። ለሀገሩም ለራሱም ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ ያስገኘበትን ልዩ ታሪክ ሰራ።

ይህ ከሆነ ከ38 አመት በኋላ…

እ.ኤ.አ በ2018ቱ የስዊዘርላንድ ሉዛን የዳይመንድ ሊግ የአትሌቲክስ መድረክ በወንዶች አምስት ሺህ ሜትር ፉክክር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች እንደ ሁልጊዜው ለድል ተጠብቀዋል።

በውድድሩ የመጨረሻው ዙር ላይ አንደኛው ኢትዮጵያዊ አፈትልኮ ወደ ፊት መሮጥ ሲጀምር…አጠገቡ የነበረው የሀገሩ ልጅ ተከትሎት እንደሚሮጥ ማንም የተጠራጠረ አልነበረም። የሆነው ግን ፍጹም ያልታሰበ እና ማንም ያልገመተው ነበር።

ወደፊት የሚሮጠውን የሀገሩን ልጅ ተከትሎ ይሮጣል የተባለው ኢትዮጵያዊ ሯጭ እግሩን ሳይሆን እጁን ለመሰንዘር ፈጠነ። ወደፊት የሚገሰግሰውን የአጋሩን ቁምጣ በመጎተት ሊያስቀረው ሞከረ። ኢትዮጵያዊያኑ ሯጮች ልቀቀኝ…አልለቅም…ትግል ጀመሩ። ይህ ክስተት አስደንጋጭ የሩጫው ትርዒት ሆኖ የዓለምን ትኩረት ሳበ።

ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች ተያይዘው ከወደቁበት ለመነሳት ሲዳክሩ፤ ከኋላቸው የነበረው ኤርትራዊ ሯጭ ደርሶ አልፏቸው ሄደ። የውድድሩም አሸናፊ ሆነ። ያኔ መነጋገሪያ ርዕስ የሆነው “ኢትዮጵያዊያኑ ምን ሆኑ?” የሚለው ጥያቄ ነበር። ቀድሞ በመረዳዳት ተቀናቃኞቻቸውን ከኋላቸው አስከትለው በአንድነት ሆነው ፊት በመምራትና በማሸነፍ የሚታወቁት የኢትዮጵያ ልጆች ዛሬ አንዱ ሌላውን ጥሎ ለማለፍ ሲሞክር መታየታቸው “ምን አግኝቷቸው ነው?” አሰኝቷል።

እነዚህ በሁለት የተለያዩ ዘመናትና ትውልዶች መካከል የተፈጠሩ ክስተቶች የሩጫ ውድድር ታሪኮች ብቻ አይደሉም። በቀደመውና በአሁኑ ትውልድ መካከል ያለውን የኅብረተሰብ ሥነ- ልቦና በትክክል ሊያስረዱልን የሚችሉ ማሳያዎች እንጂ። በመተሳሰብና በመተዛዘን አብሮ ወደፊት የመጓዝ የኢትዮጵያዊያን እሴት እየጠፋ በምትኩ ‘እኔ ብቻ እኖር’ ባይነት መስተዋሉ በዝቷል።

በልቦና ውቅር ላይ ሰፊ ትንተና በመስጠት የሚታወቁት ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው፤ ዛሬ ላይ ደብዝዞ ቢታይም፤ የቀደመውን ኢትዮጵያን በዓለም መድረኮች ሁሉ ውጤታማ ያደረገውን የአትሌቶቻችንን በትብብር የመሮጥ ባህል በየተሰማራንበት ሙያና ሕይወት ውስጥም ልንከተለው እንደሚገባ ይመክራሉ። “ኢትዮጵያዊያን እንደ ሕዝብም ሆነ እንደ ተቋም ውጤታማ መሆንና ከፈተና ማምለጥ የምንችለው በመተጋገዝ በኅብረት መስራት ስንችል ብቻ ነው” የሚል እምነት አላቸው።

በጋራ በምንኖርባት ዓለም በተናጥል እኔ ብቻ ነጥሬ ልውጣ የሚል የልቦና ውቅር የገነባ ሰውም ሆነ ማኅበረሰብ እየበዛ ከመጣ፤ ሀገር የምታተርፈው፤ ሕዝብም የሚጠቀመው እንደሌለም የ”እነሆ መንገድ ለኢትዮጵያ” መጽሐፍ ደራሲው ፕሮፌሰር ዳንኤል ይናገራሉ።

የፕሮፈሰሩ ስጋት በእርግጥ ስጋት ብቻም አይደለም። በግብርም ነፍስ ዘርቶ ታይቷል። በብዙው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ዘንድ የነበረው በመተሳሰብና በመረዳዳት የመኖር እሴት እየደበዘዘ ጭካኔና ራስ ወዳድነት ገዝፈው የታዩባቸው ጥፋቶች ተከስተዋል። ለዘመናት የተገነባው መተማመን በቀላሉ ተንዶ የሰብዓዊና ቁሳዊ እንዲሁም የማኅበራዊ እሴቶች ውድመት አስከትሏል።

በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ታዲያ ሀገርና ሕዝብ እንዴት ጸንተው መቀጠል ይችላሉ? በእርግጥም የቀደመው በመተሳሰብና በመረዳዳት በጋራ

አንድን ሀገር ወይም ሕዝብ በጽኑ መሰረት ላይ እንዲገነባ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው በማኅበረሰቡ ዘንድ የዳበሩ የጋራ

እሴቶች መኖር እንደሆነ ይታመናል።



71

የመቆም፣ በልዩነቶች ውስጥ በአንድነት የመራመድ የመሳሰሉ ኢትዮጵያዊ መገለጫዎች የት ሔዱ? ብለን የምንጠይቅበት ዘመን ላይ መሆናችንን የሚያስረዱ በርካታ አስደንጋጭ እና አሳዛኝ ክስተቶችን አስተናግደናል።

ለዘመናት በአብሮነት የተሻገረ፣ የውጭ ጠላቶችና የተፈጥሮ ፈተናዎች ያልበገሩት ጠንካራ የማኅበረሰብ ሥነ-ልቦና እንዴትና ለምን ትንንሽ በሚባሉ መሰናክሎች ሊሸረሸር ቻለ? እንዴትስ አለመተማመንና መጨካከን ቦታ አገኘ? የሚሉ ብዙ ጥያቄዎችን እንድናነሳ የሚያስገድዱ ክስተቶችን በዚህ ትውልድ ውስጥ ተመልክተናል።

የአብሮነት ማገሮች መላላት

አንድን ሀገር ወይም ሕዝብ በጽኑ መሰረት ላይ እንዲገነባ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው በማኅበረሰቡ ዘንድ የዳበሩ የጋራ እሴቶች መኖር እንደሆነ ይታመናል።

የማኅበረሰብ የጋራ እሴቶች ከሆኑት መካከልም ብርቱ የሀገር ፍቅር፣ መተማመን፣ መረዳዳት፣ የራስን ባሕልና ሃይማኖት የመውደድና የሌላውንም የማክበር፣ የሀገርና የሕዝብ ጠላትን ያለ ልዩነት በትብብር የመጋፈጥና የማሸነፍ ታላቅ ወኔ…የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው። የእነዚህ እሴቶች በጥንካሬ መቆየት በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው መስክ የሚመጣውን ጫና መቋቋምና ማሸነፍ እንደሚቻል ለማሳያነት



72

የሚጠቀሱ ምሳሌዎች አሉ።

የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያዋ ትግስት ባዘዘው “ታላቁ የአድዋ ድል የተገኘው በወቅቱ የነበረው ማኅበረሰብ የጠንካራ ማኅበራዊ እሴት ባለቤት ስለነበረ ነው” ትላለች። “ይህም ኢትዮጵያዊያን የጋራ ታሪክ ባለቤት ሆነን እንድንቆይ አድርጎናል። በእርግጥ ይህ የአድዋ ድል ዛሬ ላይ የልዩነት ሰበዝ የሚመዘዝበት መሆኑንም ተመልክተናል” ስትልም አክላለች።

“የኢትዮጵያ ሕዝብ የአድዋ ድል በፈጠረለት በጋራ የጀግንነት ታሪኩ ኃያል ሆኗል። ይህ ኃያልነቱ ራስ ምታት የሆነባቸው አካላት ደግሞ በጋራ የጀግንነት ታሪኩ ውስጥ መከፋፈልን የሚፈጥሩ ትርክቶችን ያመጣሉ። አንድ ከሚያደርጉን ታሪኮች የበለጠ ሊነጣጥሉን የሚችሉ ትንንሽ ጉዳዮችን ያነሳሉ” በማለትም በማኅበረሰቡ መካከል መጠራጠርና መጨካከን እንዲፈጠር ካደረጉ ምክንያቶች መካከል አንደኛው የሕዝቦች የጋራ እሴቶች መነካት እንደሆነ ነው ያስረዳችው።

ሌላ ማሳያ እንመልከት… የትራፊክ አደጋዎች!

ኢትዮጵያ በርካታ የትራፊክ አደጋ ከሚመዘገብባቸው የዓለማችን ሀገሮች

ከቀዳሚዎቹ ተርታ የምትሰለፍ ናት። ይህም “ኢትዮጵያዊያን የምንታወቅበት የመተሳሰብ እና ለሌላው ቅድሚያ የመስጠት እሴቶች በየጊዜው እየላሉ ለመገኘታቸው ማሳያ ነው” የሚሉት የአመራር ፍልስፍና መምህርና “የስሜት ልህቀት” መጽሐፍ ደራሲው ዶክተር መክብብ ጣሰው ናቸው።

ዶክተር መክብብ አብዛኞቹ የትራፊክ አደጋዎች የሚደርሱት በአሽከርካሪዎች ጥፋት መሆኑን መረጃዎች እንደሚያሳዩ በመጥቀስ፤ “ይህ የሆነው ደግሞ እኔ እቀድም የሚል… ለሌላው ቅድሚያ ለመስጠት ያለመፈለግ…ስሜት በመንገሱ የተነሳ ነው” ይላሉ። “ለሌሎች ቅድሚያ ማሰብና መጠንቀቅ ለራስም እንደሚጠቅም መረዳት ባለመቻላችን ኢትዮጵያዊያን ተያይዘን እየጠፋን ነው” ሲሉም ይናገራሉ።

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የማኅበረሰብ እሴቶች እየተናዱ መገኘታቸው እርግጥ መሆኑን የገለጹልን የማኅበረሰብ ሳይንስ ባለሙያና የሕይወት ክህሎት መምህሩ ብርሃኑ ራቦም እንዲሁ ማሳያዎችን ይጠቅሳሉ።

“የማኅበረሰብ ጠንካራ ስነልቦና በመገንባት ረገድ ትልቅ መሰረት የሆኑት እንደ ዕድር፣ ዕቁብ፣



73

የቤተ ዘመድ ማኅበራት… የመሳሰሉት ማኅበራዊ ተቋማት ዛሬ ላይ የቀደመውን አይነት ሚና የላቸውም” ነው የሚሉት የክህሎት መምህሩ።

በእርግጥ እነዚህ ማኅበራዊ ተቋማት ጭራሹን አልጠፉም። ነገር ግን አሁን ያሉትም ቢሆኑ በብሔርና በሃይማኖት ወይንም በፖለቲካ መስመር ተመሳስሎሽ ያላቸው ሰዎች የሚገኙባቸው መሆናቸውን ነው ብርሃኑ ራቦ የሚገልጹት። ቀድሞ ኅብረተሰቡ ያለ ሃይማኖትም ሆነ ጎሳ ልዩነት በጋራ የሚገኝባቸው ማኅበራዊ ተቋማት ጥንካሬያቸው እየላላ መምጣቱን እንደ ቀላል ነገር ልናየው እንደማይገባም ያሳስባሉ።

መምህር ብርሃኑ ምክንያቱን እንዲህ ያስረዳሉ “እንደ ትንሽና ተራ ነገር የምንመለከተው የእነዚህ ማኅበራዊ ተቋማት መዳከም የጋራ እሴት ያለው ማኅበረሰብ እንዳይፈጠር ያደርጋል። በሕዝብና በሀገር ህልውና ላይም ስጋትን የሚያሳድር ነው”።

ጠንካራ የማኅበረሰብ እሴቶች ሀገርን የማጽናት ሕዝብንም የማስተሳሰር ኃይል እንዳላቸው ከታመነበት፤ ጠቀሜታቸው የፖለቲካውንም ሆነ የኢኮኖሚውን ቀውስ የመታደግ አቅም ካላቸው ስለምን እንዲፈርሱ ጦር ይሰነዘርባቸዋል? ይህ እንዲሆን የሚፈልግስ ማን ነው? ስትል ትጠይቃለች የማኅበረሰብ ሳይንስ ባለሙያዋ ትዕግስት ባዘዘው፤ አያይዛም “የራሳቸውን ጥቅምና ፍላጎት ለማሳካት የሚሹ ኃይሎች ናቸው” በማለት ጥያቄውን ትመልሳለች።

“እነዚህ ኃይሎች እንዳንድ ኃላፊነት የጎደላቸው የውጭ መንግሥታትም ሊሆኑ ይችላሉ። ሥልጣን ለመያዝ የሚሹ የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ተፋላሚዎች፤ አሁን ደግሞ ማኅበራዊ አንቂ የሚባሉት ሊሆኑ ይችላሉ። በጥቅሉ የማኅበረሰቡን እሴቶች በመናድ የራሳችንን ጥቅም እናተርፋለን ብለው የሚያስቡ አካላት ሁሉ ናቸው” ስትልም ታስረዳለች።

ምናልባት ኅብረተሰቡ ራሱ ይፈልገው እንደሆነስ?

ጥያቄው ትዕግስትን ሳያስገርማት አልቀረም።

“እንዴት? ማኅበረሰቡ ለዘመናት በመተሳሰብና በመቻቻል የኖረበት ማኅበራዊ ሐብቱ እንዲፈርስ ይፈልጋል? እኔ ፍላጎት አለው ብዬ አላምንም! ይህ ፍላጎት በኅብረተሰቡ ዘንድ

ባለመኖሩ እኮ ነው ኢትዮጵያ አሁንም ድረስ እንደ ሀገር መቆየት የቻለችው” ስትል ነው ሃሳቧን ከረር አድርጋ የገለጸችው። በእርግጥ ኅብረሰተቡ ፍላጎት የለውም ብሎ ሁኔታውን በዝምታ ማየት አይገባም። ትኩረት ሊሰጣቸውና ሊሰሩ የሚገባቸው ስራዎች አሉ ትላለች የማኅበረሰብ ሳይንስ ባለሙያዋ።

የልቦና ውቅር ለውጥ

በኢትዮጵያ በበርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች ዘንድ ለዘመናት የቆየው የመረዳዳትና አብሮ የመኖር እሴት ይበልጥ እንዲጎለብት ካስፈለገ የልቦና ውቅር ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ይመክራሉ።

“ብዙዎቻችን ተባብሮ ለመስራት የልቦና ውቅር ለውጥ ያስፈልገናል። አንዳችን ለአንዳችን አስፈላጊ መሆናችን ላይ መሰራት አለበት። አንድን ቤት ‘ቤት’ የሚያሰኙት መሰረቱ፣ ጣሪያ እና ግድግዳው እንደሆኑ ሁሉ እኛም ሁላችን ተደጋግፈን ለአገራችን በርትተን መቆም አለብን”

እንዲህ ያለውን የልቦና ውቅር ለውጥ ለማምጣት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደማይቻል የሚገልጹት ፕሮፈሰር ዳንኤል፤ “ለውጡን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማምጣት ከተፈለገ ደግሞ በቅድሚያ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሚባሉ ለምሣሌ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን የልቦና ውቅር መለወጥ እንደሚገባ ነው የጠቆሙት። ምክንያቱም “የኪነ ጥበብ ሰዎች በብዙዎች ዘንድ ተሰሚነትና ተቀባይነት ስላላቸው ተጽዕኗቸው ፈጣን ስለሆነ”።

ዶክተር መክብብ ጣሰው በበኩላቸው “አሁን አሁን በሀገራችን እያታየ ያለው እኔ እበልጥ፣… እኔ ብቻ ጀግና፣… እኔ ብቻ አሸናፊ፣… እኔ ብቻ የበላይ፣… አይነት ስሜቶች በፍጥነት መገራት ካልቻሉ እርስ በርስ መጠፋፋቱ በቀላሉ የሚቆም አይደለም” ይላሉ።

መፍትሔውንም እንዲህ ያስቀምጣሉ…

“በዋናነት ሰዎች ማድረግ ያለብን ‘እኔ ብቻ’ ከማለት መቆጠብ፣ ሌሎችም መሰል ስሜት እንዳላቸው ማሰብና ያንንም ማክበር ነው። ሌሎች ከሌሉ እኛም እንደማንቆም ማወቅ ይኖርብናል። ይህ የልቦና ውቅር የሚገነባው ደግሞ ሁሉም ሰው የስሜት ልህቀት እንዲኖረው ሲያደርግ ነው”

በኢትዮጵያ በበርካታ የማኅበረሰብ

ክፍሎች ዘንድ ለዘመናት የቆየው

የመረዳዳትና አብሮ የመኖር እሴት

ይበልጥ እንዲጎለብት ካስፈለገ የልቦና

ውቅር ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ

ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ይመክራሉ።



74

ዶክተር መክብብ የስሜት ልህቀትን ሲተረጉሙት “አንድ ሰው ከግለሰብ፣ ከቡድን፣ ከኅበረተሰብ ጋር ባለው ግንኙነት ወቅት የራስንም ሆነ የሌሎችን ስሜት ማወቅና መረዳት እንዲሁም መቆጣጠርና መምራት መቻል ነው” ይላሉ።

በስሜት የሚመራ ማኅበረሰብ ውድቀቱ ቅርብ እንደሆነ በማስረዳት “የስሜት ልህቀት” ባለቤት መሆን ፍቱን አማራጭ ስለመሆኑ ያሰምሩበታል። ይህ የስሜት ልህቀት በየዕለቱ በሚደረግ ልምምድ ሊዳብር የሚችል ተሰጥኦ እንደሆነም ይገልጻሉ።

የጣልነውን ማንሳት

የተሸረሸረውን የማኅበረሰብ እሴት እንዴት መገንባት እንችላለን? ለሚለው ጥያቄ “መልሱ ቀላል ነው” የሚሉት የሕይወት ክህሎት መምህሩና የማኅበረሰብ ሳይንስ ባለሙያው ብርሃኑ ራቦ፤ “ለመፍትሔው ሩቅ መሔድና መመራመር አያስፈልገንም። የራሳችን የሆነውን፤ ግን ደግሞ የጣልነውን ማኅበራዊ እሴታችንን ማንሳት ነው” ይላሉ።

“ሽምግልናን ንቀናል፤ እንደ ዕድርና ዕቁብ፣

ፅዋ መጠጣት የሚባሉትን ማኅበራዊ እሴቶቻችንን ጥለናል። ነገር ግን እነዚህ ናቸው፤ እንደ ሕዝብ እንደ ሀገር ፀንተን እንድንቆም ያደረጉን። በዕድር… በማኅበር… ውስጥ ሁሉም ሃይማኖትና ብሔር አለ። ሁሉም ብሔርና ሃይማኖት ውስጥ ደግሞ የመረዳዳትና የመተዛዘን አስተምህሮት አለ። ሁሉም በራሱ ቀለም አንድ ላይ ሲሆን የሚፈጥረው ውበትና ጥንካሬ ጠላትን ያስደነግጣል፤ ያሸንፋልም። ይህንን ማወቅ አለብን። ስለዚህ ዋነኛው መፍትሔ ወደቀደመውና ወደጣልነው ማንነታችን መመለስ ነው” ሲሉም አበክረው ይመክራሉ።

የማኅበረሰብ ሳይንስ ባለሙያዋ ትዕግስት ባዘዘውም የተሸረሸረውን የማኅበረሰብ እሴታችንን መልሶ በመገንባቱ አስፈላጊነት ነው የምታምነው።

“በቅድሚያ እነዚያ የምንኮራባቸው ውብ እሴቶቻችን ለምንና በማን እንደተሸረሸሩ መረዳት ከቻልን እንደገና መጠገኑ አይከብደንም” ባይ ናት። ግን ደግሞ ጥገናው

ተመልሶ በማይናድ መልኩ መሰራት እንዳለበት ትመክራለች።

ለዚህ ደግሞ የሃይማኖት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች (በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥም እንዲካተት በማድረግ)፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር ወዳድ ግለሰቦች… ማኅበራዊ እሴቶቻችን እንዲጠበቁ ቢሰሩ መልካም ውጤት እንደሚገኝ ትገልጻልች። በተጨማሪም በኢትዮጵያ የማኅበራዊ እሴቶችን የሚጠብቅ ተቋም እንዲኖር ቢደረግ የተሻለ እንደሆነ ጠቁማለች።

የእሴቶቹ ባለቤትና ጠባቂ በዋናነት ማኅበረሰቡ ቢሆንም፤ እንደ የማኅበረሰብ ሳይንስ ባለሙያዋ ትዕግስት እይታ፤ የእሴቶች ጠባቂ ተቋም ቢኖር እሴቶቹን ሊነካ የሚፈልግ ወይም የሚሞክር አካል ቢኖር በሕግ አግባብ መከላከልና ተጠያቂ ማድረግ ይቻላል። በዚህም የኢትዮጵያን ማኅበራዊ እሴቶች ማንኛውም አካል በፈለገው ሁኔታ ለማፍረስ የማይደፍራቸው ይሆናሉ። በሒደቱም ጠንካራ የማኅብረሰብ ሥነ-ልቦና ያለው ሕዝብና ሀገር ጸንተው እንዲቆዩ ማድረግ ይቻላል።



75



76




የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም