ነጋሪ 28
ይጫኑ

1

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም



2

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ማ ስ ታ ወ ቂ ያ



3



4

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

አድራሻ፦ አራዳ ክፍለ ከተማ

ስልክ ቁጥር +251-11-55-00-11 +251-11-56-39-31 +251-11-56-52-21

ፋክስ ቁጥር +251-11-55-16-09 enanegari@gmail.com

በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በየሁለት ወሩ የምትታተም መጽሔት

ማውጫ

መስከረም 2009 ዓ.ም ተመሰረተች



5

ድረ-ገፅ www.ena.et/web/negari

ውድ አንባቢያን ሠላም ለእናንተ ይሁን! ነጋሪ ዛሬም በማኅበራዊ፣ በፖለቲካዊ እና በኢኮኖሚያዊ መስኮች ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ አገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ ጉዳዮችን ሰንዳለች።

በዚህ ዕትሟ ድንቅነሽ/ሉሲ ከተገኘች ዘንድሮ ግማሽ ምዕተ ዓመት ማስቆጠሯን አስመልክቶ በአሜሪካው አሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ የቅድመ ሰው ዘር አመጣጥ ጥናት ተቋም በኩል የፈረንጆቹ 2024 ‘የድንቅነሽ ዓመት’ ተብሎ ተሰይሟል። በቅርቡ በአዲስ አበባ የተካሄደውን የሰው ዘር አመጣጥ ጥናት ጉባዔ ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ኹነቶች እየተዘከረም ይገኛል። ለመሆኑ ድንቅነሽ ለኢትዮጵያም ሆነ ለጥንተ ሰብዕ ምርምር ዘርፍ መጎልበት ምን ትሩፋት አመጣች? ነጋሪ ምላሽ አላት።

ነጋሪ በዓቢይ ጉዳይዋ ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ መሆኗ በተለያየ መልኩ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገቷን የሚገድብና ሁለንተናዊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎቿ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥር መሆኑን፤ በተለይ በአገሪቷ እየጨመረ ያለውን የሕዝቧን ቁጥርና የኢኮኖሚ ዕድገቷን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት አስፈላጊነትን ከባሕር ሕግ ስምምነት፣ ከዓለምአቀፋዊ ዳራዎችና አሁናዊ ሁኔታዎች አንፃር በመዳሰስ ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት እያደረገች ያለውን ጥረት እንዲሁም ልትወስዳቸው የሚገቡ እርምጃዎችን ታስቃኛለች።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዓለም ፊቱን ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ እያዞረ መምጣቱን በጎዳናዎች የሚርመሰመሱ ተሽከርካሪዎች ማሳያ መሆናቸውንና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሽያጭ በከፍተኛ ደረጃ ዕድገት እያሳየ መሆኑን በማጣቀስ፤ ኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የተለየ ትኩረት የማድረጓን ምክንያት፣ የዓለምን የፖለቲካ- ኢኮኖሚ እየፈተነ ያለው የነዳጅ ጉዳይ፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የጋዝ አማቂ ልቀትና የአየር ብክለትን በመቀነስ ያላቸውን አይነተኛ ድርሻ፣ ዓለምአቀፉን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አጀማመርና የእስካሁን ሂደት ከኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ኢኒሼቲቭ ጋር በማያያዝ የሚተነትን ፅሁፍም ይዛለች -ነጋሪ።

“እኔ በፓለቲካ ምሕዋር ውስጥ ብኖርም ዓይን ያወጣሁ ፖለቲከኛ ግን አይደለሁም። መጻፍ ብችልም ጥሩ ተመራማሪ ምሁር ነኝ አልልም። መናገር ብችልም ለሚገባው ተገቢ ቃላት መርጬ መናገር አልችልም” የሚለው አንጋፋው ፀሃፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ ‘ባሕል ምንድን ነው? ኪነ-ጥበብስ?’ ይለናል፤ . . . ምላሹን ነጋሪ በውስጥ ገጿ ይዛለች።

ነጋሪ መላውን ዓለም ጠባብ መንደር ያደረገው የዘመኑ የዲጂታል ቴክኖሎጂ እጅግ የላቀ ደረጃ ላይ ከመድረሱ ባሻገር ተለዋዋጭነቱም እየበዛ በመምጣቱ ዜጎችን ከዚህ ፈጣን ለውጥ ጋር እያበቁ አገር መገንባት ለነገ የማይባል ወሳኝ ጉዳይ ሆኗል። የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎች ዘመኑ የሚጠይቀውን ዕውቀትና ክህሎት ቀስመው በዓለም መድረክ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል ተግባራዊ ከሆኑ ሥራዎች መካከል አንዱ ስለሆነው የአምሥት ሚሊዮን ኮዶሮቸ ኢኒሼቲቭ የሥልጠና ዕድል ፋይዳ እና አሁናዊ የኢኒሼቲቩ ሂደት የምትለው አላት። ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮችም በነጋሪ ተዳሰዋል።

መልካም ንባብ!

ዋና አዘጋጅ አብዱራህማን ናስር

ም/ ዋና አዘጋጅ የሺመቤት ደመቀ

ከፍተኛ አዘጋጅ ፍቅርተ ባልቻ

አዘጋጅ መንገሻ ገ/ሚካኤል

አርት ዳይሬክተር ነብዩ መስፍን nebiyou1st@gmail.com

ፎቶግራፍ አሸናፊ ገ/ሥላሴ በኃይሉ አስፋው እርምት ባለሙያ ትዝታ ሁሴን

መልዕክትስታርት አፕ ለኢትዮጵያ ልዕልና

06 ኢትዮጵያ የምትቆጣጠረው

የባሕር በር ለቀጣናው ልዕልና

26 የማክሮ ኢኮኖሚ

ማሻሻያው ቀጣይ ጉዞ 42

ዓመተ-ድንቅነሽ 56

ዘመናዊ የአቅርቦት ሠንሰለት ለቀልጣፋ

አገልግሎት 66

አረንጓዴ አማራጭ 72

ትኩረት የሚሻው የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና

90 የፅናት ተምሣሌት …

98 አለርት ከትላንት እስከ ዛሬ

112 ባሕል እና ኪነ-ጥበብ

118 የተገልጋይ እርካታን

ለማሳደግ 130

“ትውልድ ይማር፣ ይሠልጥን፣ከዓለም

ይፎካከር” 138



6

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ስታርት አፕ

ኢኮኖሚ



7

ለኢትዮጵያ ልዕልና

መነሻው ስታርት አፕ በ18ኛው እና 19ኛው ክፍለ ዘመን ከአሜሪካ እንደመጣ መረጃዎች ያመላክታሉ። ‘ስታርት አፕ’ የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የሆነው በ1851 በጋዜጣ መጣጥፍ ላይ ነው። በጊዜው ቃሉ አዲስ ንግድን ወይም ድርጅትን ለመግለፅ ነው ጥቅም ላይ የዋለው። በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የስታርት አፕ ፅንሰ ሀሳብ በሂደት ቅርፅ መያዝ ጀመረ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የአሜሪካ መንግሥት በምርምር እና በልማት ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ አውጥቷል። ይህም ከጊዜ በኋላ በስታርት አፕ ለገበያ የበቁ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆነ።

በአንዱንሰው ሺፈራው



8

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ዘመናዊው የስታርት አፕ ሥነ- ምህዳር በ1970 እና 1980ዎቹ ቅርፅ መያዝ ጀመረ። ይህ ወቅት ከፍተኛ የዋጋ ንረት እና የወለድ ምጣኔ የታየበት የኢኮኖሚ ቀውስ የተከሰተበት ነበር። ይሁን እንጂ ወቅቱ ለስታርት አፕ በጣም ጥሩ አጋጣሚ ሆኗል። እንደ አፕል እና ማይክሮሶፍት ያሉ በርካታ ጠቃሚ ኩባንያዎች መመስረት እና ስኬት ሌሎች የራሳቸውን ንግድ እንዲጀምሩ ተነሳሽነትን ፈጥሯል። ዘመናዊው ስታርት አፕ መፈጠር የጀመረው እስከ 1990ዎቹ መጨረሻ ድረስ ሲሆን፤

የመጀመሪያው እርምጃ ስታርት አፖች ከምርታቸው ገንዘብ እንዲያገኙ የሚያስችላቸው አዳዲስ የንግድ ሞዴሎችን ማዘጋጀት ነበር። ሁለተኛው እርምጃ ጥሩ ሀሳብን ወደ ስኬታማ ንግድ መቀየር የሚያስችለውን የገንዘብ ድጋፍ ያደረገው የቬንቸር ካፒታል (Venture Capital) መጨመር ነው። ቬንቸር ካፒታል ለጀማሪ ኩባንያዎች እና የረጅም ጊዜ የዕድገት አቅም ላላቸው አነስተኛ ንግዶች የሚቀርብ የፋይናንስ ዓይነት ሲሆን፤ ከባለሀብቶች፣ ከኢንቨስትመንት ባንኮች እና

ከፋይናንሺያል ተቋማት የሚገኝ ነው። ትልቅ ምርት ከመገንባት ይልቅ፣ ትልቅ ኩባንያ ለመገንባት የበለጠ ፍላጎት ያለው አዲስ የሥራ ፈጣሪ መፍጠር ሦስተኛው እርምጃ ነበር። እነዚህ ሥራ ፈጣሪዎች በጊዜው ስኬታማ ጅምር፣ ጠንካራ ቡድን፣ አሳማኝ እይታ እና ጤናማ የንግድ ሞዴል እንደሚያስፈልግ ተረድተዋል። እ.ኤ.አ. በ1970ዎቹ እና 1980ዎቹ የስታርት አፕ ፅንሰ- ሀሳብ በአሜሪካዊያን ሥራ ፈጣሪዎች እና እንደ ቢል ጌትስ እና ስቲቭ ጆብስ ባሉ ሥራ



9

ፈጣሪዎች የበለጠ ዳብሯል። ስታርት አፕ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም አዲስ የንግድ ሥራ ሊሆን እንደሚችል አምነዋል። አዳዲስ ንግዶችን ለመፍጠር ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥራቸው እየጨመረ በመምጣቱ ስታርት አፖች በሁሉም የዓለም ማዕዘኖች ይገኛሉ። የቬንቸር ካፒታል አቅርቦት መኖር፣ የገበያ ግሎባላይዜሽን እና የስራ ፈጠራ ተወዳጅነት እየጨመረ መምጣት የስታርት አፖች ቁጥር ለመጨመሩ በምክንያትነት

የሚጠቀሱ ናቸው። የጀማሪ ኢንዱስትሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እድገት እያሳየ በመምጣት አሁን በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ከአራት ሺህ በላይ ስታርት አፖች እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ። አብዛኛዎቹ በሲሊኮን ቫሊ፣ በኒውዮርክ ከተማ እና በቦስተን የተመሰረቱ ሲሆኑ፣ ስታርት አፕ በመላ አሜሪካ ቁጥራቸው እየጨመረ ይገኛል። ስታርት አፕ ምንድን ነው? በርካታ ሙያተኞች ለስታርት አፕ የተለያዩ ብያኔዎችን ሲሰጡት ይስተዋላሉ። በዴንማርክ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የስታርት አፕ ውድድር አሸናፊ የሆነው የኪዩቢክ መስራች ቅዱስ አስፋው ስታርት አፕን ″ለሰዎች ሕይወት፣ ለኅብረተሰብ ጠቃሚ የሆነ ምርት ወይም አገልግሎት የሚያመጣ ነው። ስታርት አፕ ተሞክሮ በማይታወቅ መንገድ አንድን ሥራ ሰርቶ ያንን ሥራ ለማሻሻል የሚያበቃ ዓይነት መፍትሄ ሲኖረው ነው″ ይለዋል። የራይድ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ሳምራዊት ፍቅሩ ደግሞ “ስታርት አፕ አንድን ሀሳብ መሬት ላይ አውርዶና ተግብሮ ውጤት ያስመዘገበ፤ መስራት መቻሉን ያረጋገጠ ማለት ነው። ለእኔ ስታርት አፕ ሲባል ድርጅት መሆን የለበትም

እውነት ለመናገር ስታርት አፕ ሃሳብ (አይዲያ) ሊሆን ይችላል። ነገር ግን መሬት ወርዶ ትንሽ ውጤት ያሳየ ሃሳብ” በማለት ትገልጸዋለች። የመድኃኒት አይ.ቲ ሶሉሽን መስራችና ሥራ አስኪያጅ በአምላክ አለማየሁ በበኩሏ ስታርት አፕ ማለት ችግሮችን ለመፍታት ኢኖቬቲቭ የሆኑ ነገሮችን ተጠቅመው በተለያየ ዘርፍ የሚመሰረቱ ኩባንያዎች መሆናቸውን ነው የገለጸችው። እነዚህም ኩባንያዎች በተቀመጠው መስፈርት መሰረት እስከ አምስት ዓመት ባለው የዕድገት ጊዜያቸው ምናልባት አንዳንዴም ከዚያም ሊያልፍ ይችላል። በጥቅሉ ስታርት አፕ በኢኖቬቲቭ ሃሳቦች ላይ የተነሱ ችግሮችን ያጠቃለለ ተብሎ ሊገለፅ እንደሚችል ታክላለች። በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የኢኖቬሽን እና ስታርት አፕ ልማት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰላምይሁን አደፍርስ የስታርት አፕን ምንነትና ስያሜ ሲገልፁ ”ስታርት አፕ መጀመር ማለት አይደለም። ብዙ ቢዝነሶች ሊጀመሩ ይችላሉ። ጀማሪ ቢዝነሶች ሊኖሩ ይችላሉ። ግን ስታርት አፕ ናቸው ማለት አይደለም። ስታርት አፖች አዲስ ሆነው ሊጀምሩ ይችላሉ። ስለሆነም ጀማሪ የሚለውም የሚገልፀው ቃል አይደለም። ስራ



10

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ፈጣሪ የሚለውም ሙሉ ለሙሉ የሚገልፀው አይደለም። ስራ ፈጠራ ሰፊ አውድ አለው፤ በዚያ ውስጥም ብዙ ዓይነት ቢዝነሶች ሊኖሩ ይችላሉ። ስታርት አፕ ለየት ያለ ባህርይ ስላላቸው ቢዝነሶች ነው የሚያወራው። አቻ ቃል በማውጣት ባህርይውን መግለፅ አይቻልም። ከዚህ በፊትም የነበረ ዓይነት ቢዝነስም ስላልነበረ ልክ እንደ ቴሌቪዥን፣ እንደ ሬዲዮ እንግሊዝኛውን እንዳለ ወስደን ነው የሄድነው። ግሎባል ተርም ስለሆነ መጠሪያው ‘ስታርት አፕ’ ቢሆን የተሻለ ነው” ብለዋል። ስታርት አፕ በዋናነት መሰረት የሚያደርገው በአጭር ጊዜ ማደግ የሚችሉ፤ በከፍተኛ ስጋት ውስጥ የሚያርፉ፣ ፈጠራ ወይም ኢኖቬቲቭ የሆኑ ስለመሆናቸውም ይገልጻሉ። አብዛኛውን ጊዜ ስታርት አፖች እያደጉ የሚሄዱበት ደረጃ ዓለም አቀፍ ነው። ስታርት አፖች በተለያየ ጊዜ የሚያገኙትን ኢንቨስትመንት ወደ ሥራቸው እያስገቡ፣ እያደጉ የሚሄዱና በተለያየ ደረጃ የሚያልፉ ናቸው። አቶ ሰላምይሁን “ስታርት አፖች በከፍተኛ ደረጃ እርግጠኛ መሆን በማይቻልበት፣ እርግጠኝነት በሌለበት ሁኔታ ውስጥ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ፣ ችግር ወደ ቀጣይ ደረጃ የሚወስዳቸው እንጂ ለእያንዳንዱ ችግር መንግሥት

ካላገዘን የሚል ዓይነት የቢዝነስ ቅርጽ ያለው አይደለም። አዲስ ነገር ይፈጥራሉ፤ ደረጃቸውን ከፍ ያደርጋሉ“ ይላሉ። ስታርት አፕ ከንድፈ ሀሳብ ተነስቶ የተለያዩ ደረጃዎችንና የዕድገት እርከኖችን አልፎ ወደ ካፒታል ገበያና ሕዝብ እስከሚቀርቡ ድረስ የሚሄድ ረዥም ጉዞ ያለው የቢዝነስ ዓይነት ነው። ስታርት አፕን ብዙዎች ይጀምሩታል፤ ከዳር የሚያደርሱት ግን የተወሰኑት ናቸው። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የተሳካላቸው ዓለም አቀፍ ባይሆኑም ዩኒኮርን (ገቢያቸው አንድ ሚሊዮን ዶላር የደረሰ) ተብለው ባይጠሩም ከሌላው በተሻለ የሚያድጉበት የቢዝነስ ዕድል እንዲሁም የቢዝነስ ኤኮ ሲስተሙን የመቀየር አቅም ያላቸው ስለመሆኑ ነው አቶ ሰላምይሁን የገለጹት። አሁናዊ የስታርት አፕ ዓለም አቀፍ ሃቆች በዓለም ላይ ከሚገኙት የስታርት አፕ ዘርፎች ቀዳሚውን ድርሻ የሚይዘው ፊንቴክ ነው። ፊንቴክ የሚለው ቃል “ፋይናንስ” እና “ቴክኖሎጂ” ከሚሉት ቃላት የተፈጠረ ሲሆን ሰዎች ወይም ንግዶች በዲጂታል መንገድ ተደራሽ እንዲሆኑ፣ ገንዘባቸውን እንዲያስተዳድሩ ወይም ስለ ገንዘባቸው ግንዛቤ እንዲያገኙ

እና የፋይናንስ ግብይቶችን እንዲያደርጉ የሚያስችል ማንኛውንም መተግበሪያ፣ ሶፍትዌር ወይም ቴክኖሎጂ የሚመለከት ነው። ይህ ዘርፍ በስታርት አፕ ኢንዱስትሪ ውስጥ የ7 ነጥብ 1 በመቶ ድርሻ አለው። ላይፍ ሳይንስ እና ጤና አጠባበቅ 6 ነጥብ 8 በመቶ፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ 5 ነጥብ 0 በመቶ፤ ሌሎች ዘርፎች ደግሞ ቀሪውን ድርሻ ይይዛሉ። በቅርቡ ይፋ የሆኑ መረጃዎች ዩናይትድ ስቴትስ በስታርት አፖች ቁጥር ቀዳሚ እንደሆነች፤ ሕንድ እና ዩናይትድ ኪንግደም በቅደም ተከተላቸው ቀጣዮቹን ደረጃዎች ስለመያዛቸው ይናገራሉ። ዓለም በስታርት አፕ የደረሰበት ደረጃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ከሆኑ ስታርት አፖች መካከል የአማዞን መስራች ጄፍ ቤዞስ፣ የፌስ ቡክ መስራች ማርክ ዙከርበርግ፣ የማይክሮሶፍት መስራች ቢልጌትን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። በአገረ አሜሪካ ስማቸው በስታርት አፕ ከሚጠቀሱ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መካከልም ሣራ መንክር አንዷ ነች። ሣራ “ግሮ ኢንተለጀንስ” የሚባል ስታርት አፕ መስራች ናት። በመረጃ በመደገፍ የግብርናውን ዓለም ለማላቅ በቁርጠኝነት የሚሰራው ”ግሮ ኢንተለጀንስ“ የአርቴፊሻል



11

ኢንተለጀንስን ኃይል እና የላቀ ትንታኔ በመጠቀም የምግብ ዋስትናን፣ ዘላቂነት እና የገበያ ተለዋዋጭነት በሚቀየርበት መንገድ ላይ የሚሰራ፤ ዓለም አቀፍ የምግብ አቅርቦት ሰንሰለት ውጤታማ እንዲሆን የሚታትር ተቋም ነው። የግብርና እና የአየር ንብረት አዝማሚያዎችን ለመተንበይ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የሚጠቀመው የግሮ ኢንተለጀንስ መስራች እና የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሣራ መንክር ዛሬ በስታርት አፕ አንቱታን ካገኙ መካከል ትጠቀሳለች። ስኬታማ የኢትዮጵያ ስታርት አፖች ጅማሮ በኢትዮጵያ ስታርት አፕ እንደ አሁኑ ሳይታወቅ ሥራ ፈጣሪ ኢትዮጵያዊያን እንደነበሩ የገለጹት አቶ ሰላምይሁን ችግሮችን አልፈው የወጡትን ብቻ የምናይ ሆኖ እንጂ ከ30 እና 40 ዓመታት በፊት የነበሩት እንደ ‘ዳን ቴክኖ ክራፍት’ ያሉት የስታርት አፕ ዓይነት ባሕርይ ያላቸው ተቋማት እንደሆኑና ወደ ሊፍት ኢንጂነሪንግ ገብተው ትልልቅ ኩባንያ የፈጠሩት ከምንም ተነስተው እንዳልሆነ በመጥቀስ በየጊዜው ስታርት አፖች መከሰታቸውን፤ ነገር ግን የሚታወቁትና ሰው የሚያያቸው በብዙ ችግሮችና መከራ ውስጥ ካለፉ በኋላ እንደሆነ አንስተዋል።



12

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

በነበርኩበት ጊዜ አብዛኛው ስራዬ በቴሌቪዥን በምናያቸው ቴክኖሎጂዎች ነበር። በአንድ አጋጣሚ ምዕራብ አፍሪካ ውስጥ በአንድ ፕሮጀክት ላይ ተሳትፌ ፕላስቲክ ቆሻሻ እያነሳን እንዴት ብሎኬት ሰርተን ትምህርት ቤት መገንባት እንችላለን የሚል ዓይነት ፕሮጀክት ነበር። ያን ፕሮጀክት አንዱ ያቋቋምኩት እኔ ነበርኩ። እና በዚያ የተነሳ ሕይወቴ ተለወጠ። የሰው ልጅ ሕይወት የሚሻሻለው በብልጭልጭ ነገር አይደለም፤ በቀላል ነገሮች ቆሻሻ አውጥተን፣ ያንን ቆሻሻ ጥቅም ላይ አውለን የሰዎችን ኑሮ ማሻሻል እንደምትችል ስታይ ይሄንንማ በዚህች ፕሮጀክት ላጠናቅቀው አልችልም፤ እንዴት ዓለም አቀፍ ማድረግ እንችላለን፤ እንዴት ከትምህርት ቤት ውጭ ሌሎች ነገሮችን መገንባት እንችላለን የሚል ዓይነት ስሜት ተሰማኝና ዕድሉ ሲያጋጥመኝ ከዩኒሴፍ ወጥቼ ኪዩቢክን መሰረትኩ”። በስታርት አፕ ብዙ ፈተናዎችን አልፈው ለስኬት ከደረሱት መካከል ራይድ ሌላው ተጠቃሽ ነው። የራይድ መስራች እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆነችው ሳምራዊት ፍቅሩ በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በተዘጋጀው የSTRIDE Ethiopia 2024 Expo ምርጥ እንስት ሥራ ፈጣሪ (Entrepreneur) በመሆን ሽልማት ተበርክቶላታል።

በኢትዮጵያ አሁን ስለ ስታርት አፕ በስፋት መነገር ጀምሯል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የስታርት አፕ ሽልማቶችን ያሸነፉ ኢትዮጵያዊያንም ብቅ ብለዋል። ለዚህም በዓለም አቀፉ የስታርት አፕ ሽልማት (Global Start up Award 2024) የኢትዮጵያን ስም በዓለም ያስጠራው የኪዩቢክ መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቅዱስ አስፋውን መጥቀስ ይቻላል። ቅዱስ ከወዳደቁ ፕላስቲኮች ለቤት መስሪያ የሚሆን ብሎኬት የሚያመርተውን ኪዩቢክን ከመመስረቱ በፊት በኢንተርናሽናል ዴቨሎፕመንት፣ በግሉ ዘርፍ በተለያዩ አገራት ሰርቷል። አብዛኛው ሥራውም ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮረ ነበር። በጉግል (Google) የመስራት ዕድልም አጋጥሞታል። የጉግል ቆይታውን ሲገልፅ “ጉግል በምሰራበት ጊዜ አሁን የምናውቃቸውን ምርቶች ጉግል ማፕ፣ ጉግል ፋይናንስ የምንላቸውን ከእንግሊዝኛ ውጭ 40 በሚሆኑ ቋንቋዎች እንዴት ለውጠን ለሌላም ገበያዎች ማቅረብ እንችላለን? በሚል ኢኒሼቲቭ ላይ ነበር የምሰራው። ከዚያም በኋላ ማማከር ላይ ሰርቻለሁ። ማማከር ላይ በምሰራበት ጊዜም በጣም ትልቅ ትምህርት አግኝቻለሁ፤ ኮንሰልታንት ስትሆን ለዛ ድርጅት

ሠራተኛ አይደለህም። እየሄድክ እየለዋወጥክ፣ ድርጅቶችን እንዴት ማሻሻል ትችላለህ፣ እዚያ የሚሰሩ ሰዎች ድርጅታቸውን እንዴት ምርታማ ማድረግ ይችላሉ ብለህ ነው የምታስበው። ያን በምታደርግበት ጊዜም ብዙ ሰው ስራ ላይ ያለውን ባሕሪይ ትማራለህ። ድርጅቶች እንዴት እንደሚያስቡ፣ ራሳቸውን እንዴት እንደሚያደራጁ ብዙ ትማራለህ። እና ያ ትልቅ ጥቅም ነበረው” ይላል። ቺሊ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ሊባኖስን፣ ማላዊ፣ እና ሴራሊዮንን ጨምሮ ስደተኞች፣ ጦርነትና በሽታ ባለባቸው ከ40 በላይ በሆኑ አገራት መስራቱን የሚገልጸው ቅዱስ፤ በስራ ላይ በነበረባቸው አገራት የብዙ ሰዎች ፍላጎት በአገራቸው መኖር፣ ከተረጂነት መውጣትና ሰርቶ ማግኘት፣ ለልጆቻቸው እንክብካቤና ጤንነት መጠበቅን እንደሆነ መረዳቱን ይናገራል። በዚህ ላይ በአገሩ ላይ የመስራትና ሰዎችን የመርዳት ፍላጎቱ ታክሎበት የሰዎችን ክብር ማፅናት “Build Dignity”ን ዓላማው ያደረገውን ኪዩቢክን ለመመስረት አነሳሳው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የዓመቱ ምርጥ ስታርት አፕ በሚል ለሽልማት የበቃው ኪዩቢክ የተወጠነበትን አጋጣሚ ሲያስታውስም ”ዩኒሴፍ ውስጥ



13

ሳምራዊት ራይድን ስትጀምር የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ታስታውሳለች “ስጀምር ደመወዜን ቆጥቤ በ40 ሺህ ብር ሀይብሪድ ዲዛይንስን ያቋቋምኩት አንድ ኮምፒውተር እና በዚያን ጊዜ የኢንተርኔት ሞደም አለች እሷን ዶንግል ይዤ ነው። እኔ ሃሳብ (Idia) ነበረኝ። ነገር ግን በዚያ ጊዜ አይዲያ ኖሮህ ብቻ መስራት አይቻልም፤ ፈቃድ (Licens) ያስፈልጋል። ላይሰንስ ለማውጣት ቢሮ መከራየት አለብኝ። ስለዚህ በጣም ትንሽዬ ቢሮ ተከራይቼ፣ ላይሰንስ አውጥቼ፣ ሀይብሪድ ዲዛይንስ የሚባለውን አቋቁሜ ነው የጀመርኩት። 40 ሺህ ብር በዚያን ጊዜ ብዙ አልነበረም። ጠረጴዛ፣ ወንበር . . . ከገዛሁ በኋላ አይዲያዬን ይዤ ገባሁ”። ሌላዋ ባለስኬት በጤናው ዘርፍ ያለውን አገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ በማገዝ አገልግሎቱን ማላቅ (የተሻለ ማድረግ) ላይ የሚሰራው የመድኃኒት አይ.ቲ ሶሉሽን መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ በአምላክ አለማየሁ ናት። እጅግ ተፈላጊ በሆነው የጤና ዘርፍ ስኬታማ ሥራዎችን ሰርታለች። በአምላክ ″ከዚህ በፊት በነበረን ሜዲካል ኮንሰልታንሲ እና የሜዲካል ትራቭል ላይ በሚሰራው ካምፓኒያችን ከብዙ የውጭ ሀገር ሆስፒታሎች ጋር

የመስራት ዕድል ነበረን። ሕንድ፣ ቱርክ፣ ዱባይ፣ እስራኤል፣ ታይላንድ፣ እንደ እነዚህ ካሉ ሀገሮች ጋር። አሁን ያለውን የቴክኖሎጂ ዕድገት፣ ኤ.አይ፣ ሮቦቲክ የሆኑ ቀዶ ሕክምናዎችን መስራት፣ እነዚህ በሚሰጧቸው አገልግሎቶች የሕክምናውንም ዘርፍ ለማሳደግ ረድቷቸዋል፤ እና ይሄ ነገር ለምንድን ነው ኢትዮጵያ ውስጥ መሆን የማይችለው ብለን መጥተን አየነው። አሁን ባለንበት የቴክኖሎጂ ዘርፍ ደግሞ ባለንበት የቴክኖሎጂ ጊዜ ትልቁ የሰው ልጅ ሀብት ዳታ ነው። ይሄን ዳታ ደግሞ በሥነ-ሥርዓት ለሚያስፈልገው ማዋል ራሱ እንደ ትልቅ ዋጋ ያለው (Asset) ነው። ለአንድ ሀገር ትልቅ ችግር የሚፈታ ነው። እና በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ባየንበት ጊዜ ብዙ ሰዎች የሚቸገሩበት ጉዳይ ሆኖ ያገኘነው አንደኛ የት፣ ምን ዓይነት የሕክምና አገልግሎት ማግኘት እችላለሁ። ከሐኪሞች ጀምሮ ሆስፒታሎች ምን ዓይነት አገልግሎት ይሰጣሉ። ምርመራዎችን የት አገኛለሁ። መድኃኒቶችን የት አገኛለሁ የሚሉት ናቸው። ይሄን ለመፍታት ተነሳን። በቀጣይነት ደግሞ ይሄንን እየሰራን በነበረበት ወቅት የእነዚህን የጤና ተቋማት የሕክምናም ሆነ የአገልግሎቶቻቸውን ዳታ ምን ያህል የተደራጀ፣ ጊዜውን በዋጀ

በሆነ ቴክኖሎጂ እየደገፉን ነው የሚለውን አየን ትልቅ ክፍተት ነበረው። እሱን ለመደገፍ ደግሞ የተለያዩ ሶፍትዌሮች ለሆስፒታሎች፣ ለፋርማሲዎች፣ ለላቦራቶሪዎች ማበልፀግ ጀመርን። መነሳት የቻልነው ከዚህ ነው” ስትል አብራርታለች። የስታርት አፕ ፈተናዎች በቀደመው ጊዜ ስታርት አፕን የሚደግፉ ፖሊሲዎች አለመኖራቸው፤ ዘርፉ ለአገር ሊያበረክት በሚችለው ፋይዳ ላይ የነበረው ግንዛቤ አለመዳበር ምክንያት ስታርት አፖች ብዙ ፈተናዎች ሲገጥሟቸው ቆይቷል። የገጠሟቸውን ፈተናዎች በፅናት በመጋፈጥ አልፈው ለስኬት የበቁ የመኖራቸውን ያህል ተስፋ የቆረጡም አይታጡም። አሁን ላይ ፈተናዎችን አልፈው ለስኬት የበቁት ስታርት አፖች ምን ገጠማቸው እንዴትስ ተወጡት? ቅዱስ በኪዩቢክ ምስረታ ወቅት ፍርሃት ውስጥ ገብቶ እንደነበር አልሸሸገም። “በጣም ፈርቻለሁ፤ የሦስት ልጆች አባት ነኝ። የእነሱን የኑሮ ሁኔታ ማበላሸት አልፈልግም፤ ኃላፊነት አለብኝ፤ ደግሞም መብላት፣ መጠጣት መኖር አለብኝ። እና በየወሩ ደመወዝ አግኝቼ ከምኖርበት ሕይወት ወጥቼ፣ መቼ እንደሚከፈለኝ እና መቼ ገንዘብ እንደሚኖረኝ የማላውቅበት ዓይነት ሁኔታ ውስጥ መግባት



14

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ለራሴም ለቤተሰቤም በጣም ከባድ ነበር። የምኖረውም ለልጆቼ ነው። ልጆቼ ምንድን ነው የሚፈልጉት ብዬ አርቄ ሳስበው የእነሱን ሕይወት በእኔ ዕድሜ በሚደርሱበት ጊዜ ዓለምን እና የእነሱን ሕይወት አባታችን እንዴት አድርጎ በተሻሻለ መልክ ለማድረግ ሞከረ የሚለውን ዓይነት ስሜት እንዲሰማቸውም እፈልጋለሁ። እና የአየር ንብረት ለውጥ የሚባለው ነገር ብዙ ሰው ሊያየው አይፈልግም እንጂ እያየነው ነው። እንደ ዱባይ ዓይነት በረሀ በውሃ እየተጥለቀለቀች ነው። በእኛም አገር ያለ ወቅቱ በዘነበ ዝናብ ድርቅ እያየን ነው። ይሄ አገራችን ውስጥ ብቻ የሚካሄድ ነገር አይደለም።

በዓለም ላይ የምናየው ነገር ነው እና ዓይናችንን ጨፍነን ምንም ሳናደርግ ኑሮን ብንቀጥል እኔ ላልጎዳ እችላለሁ፤ ግን ልጆቼን፣ የሌሎችን ልጆች ምን ዓይነት አደጋ ውስጥ ነው የምከተው፤ ያንን ሌላ ሰው እንዲፈታው መጠበቅ የለብኝም የሚል ዓይነት ስሜት ደግሞ አለኝ። እና ይሄ ስራ አልተሳካም እንበል፤ ልጆቼ አንድ ቀን ሲያስቡት አባቴ ሞክሯል የሚል ዓይነት ስሜት እንዲኖራቸው ነው የምፈልገው። እናም እኔ ያየሁት ይሳካል ወይ የሚለውን አይደለም፤ ባይሳካም ውጤት አምጥቻለሁ የሚል ዓይነት ስሜት ነው የተሰማኝ። የአንድ ሰው ሕይወት ባሻሽል፣ አንድ ሰው ይሄን ነገር አይቶና

ተነሳስቶ ሆኖ በተሻለ መልክ አቅርቦ ሰራው ብንል ለእኔ ትልቅ ውጤት ነው ያመጣሁት ብዬ ነው የማየው። እና ባይሳካም ደስ ይለኛል የሚለው መልስ ለራሴ መመለስ ስችል ኃላፊነቱን ወስጄ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሰናል” ይላል። ሥራውን ሲጀምር የብቸኝነት ስሜት እንደተሰማው የሚገልፀው ቅዱስ አንድ ድርጅት ሲቋቋም የድርጅቱ ራዕይ ያለው በመስራቹ ጭንቅላት ውስጥ ብቻ መሆኑ ሥራውን የበለጠ አስጨናቂ ያደርገዋል ይላል “አንድ ድርጅት በምታቋቁምበት ጊዜ የድርጅቱን ዓላማ እና መንገድ የምትቀርፀው አንተ ነህ። ስለዚህ ብቸኝነት አለው።



15

ለምን አንተ ብቻ ነህ ያንን መንገድ፣ ያን ዓላማ የምታየው። ለሌላው እንደምትፈልገው ተንትነህ ብትነግረው የምታየው ግን አንተ ብቻ ነህ ምክንያቱም ገና አልተሰራም። ትልቅ ድርጅት ውስጥ ስትሰራ አጠገብህ ሰው አለ፤ አሁን ጠዋት ተነስቼ የማወራውም ከእኔ ጋር ነው፤ የማስበው፣ የምወያየው ለብቻዬ ነው። ለጊዜው ደስ ይላል፤ ለምን ክፍተት ኖሮ በርታ ብለህ በራስህ መንገድ በራስህ ፔስ (ፍጥነት) መስራቱ ደስ ይላል። አንድ ወቅት ላይ ግን ሁልጊዜ ለብቻህ ማውራት ደስ አይልም . . . ያም ሆኖ ግን ዕድለኛ ነበርኩ፤ ይሄንን ሁኔታ ያሳለፉ ጓደኞቼ፣ ልጆቼ ከእነሱ ጋር የምወያይባቸው ጊዜያት ደግሞ ያጠነክሩኝ ነበር። የምሄድበት መንገድ አዲስ እንዳልሆነ፣ ትክክል እንደሆነ የሚያረጋግጡልኝ ሰዎች ነበሩ። አንዳንድ ሀሳቦቼን ማስተካከል እንዳለብኝ የሚመክሩኝ ነበሩ፤ ያ ለሥራዬ ትልቅ ሚና ተጫውቷል” የራይድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሳምራዊት ራይድን ለስኬት በማብቃት ሂደት ብዙ ውጣ ውረዶችን ማሳለፏን ነው የምትናገረው “እኔ የተማርኩት ትምህርት ኮምፒዩተር ሳይንስ ነው። I am a computer coder፣ ስለዚህ ኮድ አድርጌ፣ ዴቨሎፕ አድርጌ፣ የመጀመሪያውን ፕሮዳክት አወጣሁ። ለመሸጥ

ሞከርኩ። በዚያን ጊዜ በጣም ልጅ ነኝ። የሠራሁትን ሥራና እኔን ሲያመጣጥኑኝ በእነሱ አስተሳሰብ አ ል ተ መ ጣ ጠ ን ኩ ኝ ም ፤ ሲስተሙን ቢወዱትም በነፃ ብሰጣቸውም የተወሰነ ጊዜ ላይሰንሱ የመጠቀሚያ ጊዜው እንዲያልፍ አደረኩባቸው። ከሦስት ወር በኋላ ሄጄ ክፈሉኝ ስላቸው መክፈል አልፈለጉም። እና ቃል በቃል ያሉኝ የማልረሳው ‘ሲስተሙ በጣም አሪፍ ነው። ለድጋፍ ስንጠራ አንቺ ነሽ የምትመጪው። ለሥልጠናም አንቺ ነሽ የምትመጪው። ኮዱንም አንቺ ነሽ የፃፍሽው። እኛ ብር ከፍለንሽ አንቺ ብትሞቺስ። በቃ! አለቀ ብራችን ቀለጠ!’ ብር ከከፈላችሁኝ እኮ የሠው ኃይል እጨምራለሁ ብዬ አልኳቸው ለእነሱ ግን አልተዋጠላቸውም። ስለዚህ የተለየ ቦታ ለመሸጥ ሞከርኩኝ፤ ተቀባይነት ማግኘት አልቻለም”። ለተስፋ መቁረጥ እጅ ያልሰጠችው ሳምራዊት በሂደት ፈቃድ የማይፈልግ፣ ከድርጅት ጋር የማትነካካበት አዲስ ነገር ለመስራት ተነሳች “ችግሮችን መቀበል ጀመርኩ። ከሰዎች ሁሉ፣ ከጓደኞቼም እንዲሁም ከሌሎች አጋሮቼም መቀበል ጀመርኩኝ። የታክሲው ችግር አንድ ዓይነት እየሆነ መጣ። እዚህ ላይ እኮ እንዲህ ያጋጥመኛል የሚል ነገር ሰማሁኝ ‘በተለይ ሌሊት፣ ማታ፣

መሸት ሲል በጣም ያስፈራናል። በተለይ እንደ ሴት ብቻችንን ላዳ ታክሲ ውስጥ በጣም ያስፈራናል’ የሚያስፈራችሁ ምንድን ነው? ስል ‘ሰውዬውን አላውቀውም!’ ስለዚህ ዶክመንትድ አይደለም ማለት ነው። እና ለምን ይሄንን ችግር አልፈታም በሚል “ራይድ”ን ጀመርኩኝ። አራት ወር ሙሉ ከቢሮዬ አልወጣሁኝም። እስከ ሌሊቱ ሰባት፣ ስምንት ሠዓት እያመሸሁ ሰራሁኝ፤ ከአራት ወር በኋላ ሲስተሙን ጨረስኩኝ”። በዚህ መልኩ የተጀመረው ራይድ ጉዞውም በፈተናዎች የታጀበ ነበር። ”ሁለተኛ ቨርዥን ከላዳዎቹ ጋር ጀመርን፣ ልክ ሜትር ታክሲ ከቀረጥ ነፃ ተፈቀደ ሲባል ሁሉንም ፕሮሰስ ላይ ነበርን። ስብሰባ በመጥራት፣ ኤስ.ኤም.ኤስ በመላክ፣ ዶክመንቴሽናቸውን በማዘጋጀት፣ ስፔስፊኬሽን በማዘጋጀት፣ ሌሎችም. . . ምንም የቀረንበት ሂደት አልነበረም። በመጨረሻ 751 ዘ-ሉሲ ሜትር ታክሲዎች ሲመጡ ተፈራርመን የሞባይል መተግበሪያውን ላውንች አደረግን። ራይድ እያደገ፣ ሰውም እያወቀው መጣ። ከታክሲዎቹ ጋር ደግሞ ሌላ ቻሌንጅ መጣ። እኛ አፕሊኬሽኑን ለአንድ ዓመት በነፃ ከሰጠናቸው በኋላ ሁለትና ሦስት ሥራ ይሰሩ የነበሩት በአፕሊኬሽን 14 እና 16 መሥራት፣ ገቢያቸውን



16

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

እጥፍ ማድረግ ጀመሩ። ከአንድ ዓመት ማላመድ በኋላ ኮሚሽን ልንጀምር ነው ስንል ሌላ ብጥብጥ ተነሳ። ለምን ኮሚሽን እንከፍላለን፤ እኛ በሰራነው እናንተ ለምን ታገኛላችሁ ዓይነት ጥያቄ መጣ፤ እኛም እኮ ወጪ አለብን፣ ብዙ ደንበኛ እያመጣን ነው፣ ብዙ ሰው እንድታገለግሉ እያስተዋወቅን ነው . . .፤ አስረዳን ትንሽ ስትራግል ማድረግ ጀመርን”። ራይድን ማስቀጠል ብርቱ ጥረትን የጠየቀ ነበር። ኮድ ሦስት ተሽከርካሪዎችን ራይድ ለማሰራት ሕጉ እንደማይከለክላቸው በማረጋገጥ ሥራው ተጀመረ። በወቅቱ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን የስምሪት አገልግሎት የምንሰጠው እኛ ነን፤ በቴክኖሎጂ የስምሪት አገልግሎት የሚባል ነገር የለም፤ ሙሉ በሙሉ መዘጋት አለበት አለ። “ከባድ ነበር ይመጡና ያሽጉብናል፤ ሄደን ተከራክረን ስናስከፍት ድጋሚ ያሽጉታል። እኛ እንደ ስታርት አፕ ትግል አድርገን፣ ሁለት ጊዜ ኢንቨስትመንት ሬዝ አድርገን ነው የመጣነው። እና ቴክ ኦፍ በምናደርግበት ሠዓት መዘጋት አለበት ብለው መጥተው ዘጉት። ከእነሱ ጋር ፍርድ ቤት መመላለሱ በጣም ውድ ነበር። በጣም ብዙ ገንዘብ ነው ያወጣነው። በዚያን ጊዜ ራይድ አራት ዓመት ያህል ስትራግል አድርጎ እንደ ስታርት

አፕ ሁለተኛውን ኢንቨስትመንት አግኝቶ ቴክ ኦፍ የሚያደርግበት ጊዜ ነበር። እውነት መንግሥት እንዲህ ያደርጋል? አልጠበቅንም። ምክንያቱም ”አይዲያ ፋይናንሲንግ“ (Idea Financing) ብሎ ንግድ ባንክም በዚያ ጊዜ ጀምሮ ነበር። ወጣቶችን እንደግፋለን፣ ሥራ ፈጣሪ ሴቶችን አንደግፋለን ተብሏል። እንግዲህ እኔ በዚያ ጊዜ ወጣትም ነኝ፣ ሴትም ነኝ። ሁሉንም ነገር አሟላለሁ። መደገፍ ሲገባቸው እንዴት ዲስከሬጅ ያደርጋሉ። የሚወራው እና በተጨባጭ ያለው አልተመጣጠነልኝም። በጣም ከባድ ጊዜ ነበር ያሳለፍነው። በጊዜው በጣም ብዙ ሰዎች ቀጥረናል። እነሱን ልናባርር ነው። ወደ 7 ሺህ አሽከርካሪ ደርሰናል። ተበድሮ መኪና የገዛውንስ ውሃ ላይ ልንጥለው ነው? እንዴት ነው የሚሆነው፣ ከባድ ነበር! እግዚአብሔር ይመስገን፣ ዛሬ አድገን እዚህ ደረጃ ላይ ደርሰናል” ትላለች ሳምራዊት አስቸጋሪውን ጊዜ እያስታወሰች። እንደ ሌሎቹ ሁሉ የስታርት አፕ ጉዞ ፈተናዎችን እያለፈ የመጣው የመድኃኒት አይ.ቲ ሶሉሽን ሥራውን ሲጀምሩት በጥናት ነበር። መስራቿ በአምላክ ይህን ትላለች፤ ”ሥራውን በምንጀምርበት ጊዜ የራሳችንን ጥናት ለማድረግ ሞከርን። እንደ

ንግድ ሀሳብም ብቻ ሳይሆን ለእኛ ትልቁ ጉዳይ የነበረው እነዚህን ችግሮች እንዴት ዲጂታላይዝ አድርገን እንፍታ የሚለው ነበር፤ ይሄንን ጥናት ማድረጉ በራሱ ጊዜ ወስዶብናል። ሁለተኛ በፖሊሲው በኩል ያለው፣ ምን ላይ ብንሰራ ፈቃድ ይኖረናል፣ የሚለው ሌላው ጉዳያችን ነበረ። በወቅቱ ገበያውን ስንቀላቀል በአንድ አካታች በሆነ ሲስተም ላይ የመጀመሪያ ካምፓኒ ነበርን። እና በትልቅ ደረጃ ቻሌንጅ የነበረን አጋሮችን ማግኘት ነበረብን፤ ሆስፒታሎች፣ ፋርማሲዎች ወደ እኛ ፕላት ፎርም እንዲቀላቀሉ፣ ሀሳቡን ይደግፉታል፤ ነገር ግን ተግባራዊ የመምሰል ነገሩ አዳጋች ነበር። ይሄንን ደግሞ ሰርቶ ማሳየቱ ጊዜ ወስዶብን ነበር። በጥቅሉ ሁሌም አዲስ ነገር መጀመር ቀላል አይደለም። የመጀመሪያ ሆኖ መንገዱን መጥረግ የራሱ ፈተና አለው። በቢሮ ደረጃ ሁሉንም ፋሲሊቲ በማሟላት ደረጃ እንደ ዕድል ሆኖ እኔ በግሌ ይሄንን ነገር ሳቋቁም የመጀመሪያ ካምፓኒ ስላልሆነ ቀድሞ የነበረ የሥራ ልምድ አግዞኛል አድርጎኛል። በዙሪያችን የነበሩ ባለሙያዎች ይሄንን ደግፈውናል። ተጨማሪ ሆኖ ያገኘነው የቴክኒካል፣ ወይም የሶፍትዌር ዴቨሎፐሮችን ማግኘት ነበረ። እና አሁንም ድረስ በኩራት የምንናገረው



17

ትልቁም አሴታችን በጣም ጥሩ ፕላትፎርሞችን ነው የገነባነው። እነዚህ ፕላትፎርሞች ደግሞ የተገነቡት ሀገር ውስጥ በተማሩ በኢትዮጵያዊያን ሶፍት ዌር ዴቨሎፐሮች፣ እዚሁ በሀገር ውስጥ ነው ዴቨሎፕ ያደረግነው። በጣም አድቫንስድ የሆኑ ሶፍት ዌሮችን ማበልፀግ የሚችሉ ሶፍትዌር ኢንጂነሮች አገኘን። ይሄ አጋዥ ሆነልን ማለት ነው። የራሱ የነበሩ ችግሮችን ወደ መልካም ዕድል እየቀየርን ነው የቀጠልነው“። ስኬቶቻቸው . . . የኪዩቢክ መስራች ቅዱስ አስፋው ሥራውን ተማምነውበት ኢንቨስት የሚያደርጉ አጋሮችን ለማግኘት ብዙ ስለመድከሙ ነው የሚናገረው። “ከጓደኛ እስከ ዘመድ፣ አብሬአቸው ከሰራኋቸው ስለ እኔም ከሰሙ በሩቁም ሥራዬን ያዩ ብዙ ሰዎችን፤ ከ800 በላይ ኢንቨስተሮችን ነበር ያወራሁት”። በሥራ አጋጣሚ በተለያዩ ሀገራት የመስራት ዕድል የነበረው ቅዱስ በስታርት አፕ በቶሎ ሰርቶ አንድ ቦታ ላይ መድረስ እንዲሁም ገበያው ስታርት አፕ ለጀመረው ኪዩቢክ በቂ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ በመረዳቱ ኪዩቢክ ለሚያመርታቸው ብሎኬት ዓይነት ምርቶች ከሚያስፈልገው ፕላስቲክ

ጀምሮ ኮንስትራክሽን አለ ወይ፣ የኮንስራክሽን ገበያው ምን ይመስላል፣ የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ጥናቶችን አድርጓል። ሂደቱን ተከትሎ ፕላስቲክ ወደ ማሰባሰብ ሥራ ከመግባቱ አስቀድሞ ከአዲስ አበባ ከተማ የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ጋር ሊሰራ ስላሰበው ሥራ በቅርበት መከረ። በዝቅተኛ ዋጋ ሊሰሩ የሚችሉ ቤቶችን መስራት ላይ እንደሚያተኩር በመግለፅም ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት በቅርበት መነጋገር ቻለ። “ዝም ብለህ ዓይንህ ጨፍነህ፣ መንግሥት ይረዳኛል ብለህ ከገባህ ተበሳጭተህ ነው የምትወጣው። ነገር ግን ለእነሱ ምን ልጠቅም እችላለሁ፤ እነሱ ደግሞ ምን ሊረዱኝ ይችላሉ ብለህ ‘ዊን-ዊን-ሶሉሽን’ ትጠቀማለህ”። በዚህ ሁኔታ የተጀመረው የኪዩቢክ ሥራ ዛሬ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ችሏል። ቅዱስ ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ኪዩቢክ ማለት ቅዱስ ነበር። ዛሬ ኪዩቢክ 70 ሠራተኞችን የሚያስተዳድር ድርጅት ለመሆን በቅቷል። በአዳማ ኢንደስትሪያል ፓርክ ውስጥ ፋብሪካ ለመክፈት በቅቷል። ኪዩቢክ በሐረር፣ በአዳማ፣ እና በአዲስ አበባ የቆሻሻ ፕላስቲክ ለቀማ እየሰራ ይገኛል። ቅዱስ ይህን ሲገልፅ “በጣም ደስ የሚሉ ዓይነት የግንባታ ፕሮጀክቶችን እያካሄድን ነው።

የማኅበረሰቡን አቅም ያገናዘቡ ቤቶች፣ የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች፣ . . . እንደዛ ዓይነት ፕሮጀክቶች፤ ሰዎችን የሚጠቅሙና የሚያግዙ ፕሮጀክቶች ላይ እየተሳተፍን ነው። ጀመርን ለማለት ይከብደኛል። ምክንያቱም ዓላማችን ኢትዮጵያ ፀድታ፣ ከፕላስቲክ ቆሻሻ ነፃ ሆና፣ ለዓለም ትልቅ ምሣሌ ሆና እንድትገኝ ስለምንፈልግ፣ ገና አልጀመርንም የሚል ስሜት ነው ያለኝ”። ራይድ አሁን ለ85 ሺህ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። አገልግሎቱን በአዲስ አበባ፣ በቢሾፍቱ እና በአዳማ ያሰፋ ሲሆን ከኢትዮጵያ ውጭ በጅቡቲ በመስራት ላይ ይገኛል። ዋና ሥራ አስኪያጇ ሳምራዊት “ራይድን የኢትዮጵያ ዩኒኮርን (የሐብት መጠኑ አንድ ቢሊዮን ዶላር የደረሰ) ማድረግ ነው የምንፈልገው፤ ኢትዮጵያ በቡናዋ፣ በሯጮቿ እንደምትጠራው ራይድም በዚህ ልክ እንዲታወቅ የማድረግ ትልም አለን። በዓለም ላይ እንዳሉት የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ፌስ ቡክ፣ ጉግል. . . እኛም እንደዚህ ዓይነት ዩኒኮርኖችን መፍጠር ነው የምንፈልገው፤ ከእነዚህ መካከል ራይድ አንደኛው እንዲሆን ነው የምንፈልገው” ትላለች። ለዚህም ከ2017 ዓ.ም በሚጀምረው የአምስት ዓመት ስትራቴጂያቸው በአፍሪካ



18

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

በተለይ ምስራቅ አፍሪካ ገበያ ውስጥ የመግባት ዕቅድ ይዘው እየሰሩ ስለመሆኑ አብራርታለች። ራይድ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ለውጧል፤ ሥራ ላልነበራቸው የሥራ ዕድል፤ ሥራ ላላቸው ደግሞ ተጨማሪ ገቢ ፈጥሯል። “አሁን መኪና ዕዳ ሳይሆን ብዙ ብር የሚያመጣ እንዲሆን አደረግነው ማለት ነው። ኢኮኖሚው ውስጥ ከመቶ ቢሊዮን ብር በላይ ተኝቶ የነበረን እቃ ብድግ አድርገን ወደ ኢኮኖሚው አስገባነው። መንግሥት ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ታክስ መሰብሰብ ቻለ። ስለዚህ የራይድ ተጽዕኖ ትንሽ አይደለም። በጣም ትልቅ ነው። የሰው ሕይወት ቀይሯል። ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ፈጣን ገቢ (ፋስት ካሽ) የሚገኝበትን የስራ ዕድል ፈጥሯል። መኪና አሁን ወጪና ኪሳራ (Liability) ሳይሆን፣ ፕሮፊት ወይንም ደግሞ ገቢ የሚያመነጭ ማሽን ሆኗል” ነው ያለችው ሳምራዊት። አገልግሎቱን በዌብሳይት፣ በአፕሊኬሽኖች እና በጥሪ ማዕከላት እየሰጠ የሚገኘው የመድኃኒት አይ.ቲ ሶሉሽን በቅርቡ በቴሌግራም ጀምሯል። እነዚህን በመጠቀም በጤና ዘርፍ የት ምን ዓይነት አገልግሎት ማግኘት እንችላለን ለሚለው ምላሽ ይገኛል።

የመድኃኒት አይ.ቲ ሶሉሽን መስራቿ በአምላክ ይህንን ስትገልጽ “ለምሣሌ አምሥት የሚጠጉ ዋና መለያዎች አሉን። የእያንዳንዱን ሆስፒታል በእኛ ፓርትነር ሆስፒታሎች ፕሮፋይል ላይ ተቀምጦ ምን ዓይነት አገልግሎት ይሰጣሉ፣ መገኛቸው፣ በስራቸው ምን ምን ዓይነት ዶክተሮች አሉ። ከነሙሉ ፕሮፋይላቸው ላብራቶሪያቸው ምን ይመስላል፣ ፋርማሲያቸው ውስጥ ሄጄ ምን መድኃኒት ማግኘት እችላለሁ የሚለውን ማግኘት ይችላሉ። በተጨማሪ በእኛ ፕላትፎርም አንደኛው ጥቅም ካሉበት ሎኬሽን አንፃር ነው ሆስፒታሎቹን የሚዘረዝርላቸው። በዚህ መሰረት በአቅራቢያዬ ያለ ሆስፒታል የቱ ነው፣ ምን አለው የሚለውንም ዳታ ማግኘት ይቻላል”። ሐኪሞችን በያዘው ምድብ ደግሞ የሕክምና ባለሙያዎች በሁለት መልክ ተዘርዝረው ይቀመጣሉ። አንደኛው በስፔሻሊቲያቸው ሲሆን፤ ሁለተኛው በስማቸው መሰረት ነው። አንድ ታካሚ እንደዚህ ዓይነት ስፔሻሊስት ሀኪም ሊያይህ ይገባል፤ ወይም ዶክተር እከሌ ይይህ ተብሎ ሪፈር ሲደረግ በመተግበሪያው ላይ በቀላሉ ማግኘት ያስችላል። በሐኪም የታዘዙ ምርመራዎችን ለማድረግ በተለይም ከተለያዩ

አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ ለሚመጡ ታካሚዎች አዳጋች ለሚሆነው ችግር መፍትሄ ያበጀው በቀላሉ በአቅራቢያቸው ያለ የዲያግኖስቲክ ወይም የላቦራቶሪ ማዕከል ምን ዓይነት ምርመራዎችን ይሰጣል የሚለውን ማየት የሚችሉበት ነው። በቀላሉ የሐኪሙን ትዕዛዝ ፎቶ በማንሳትና በመድኃኒት አይ.ቲ ሶሉሽን መተግበሪያዎች በማስገባት ምርመራውን የት ማግኘት እንደሚችሉ በግልፅ ማየት ያስችላል። ይህ የብዙዎችን ሕይወት ያቀለለ የስታርት አፕ ውጤት ነው። በቀደመው ጊዜ በሐኪም የታዘዘን መድኃኒት ፈልጎ ማግኘት አድካሚ ነበር። የመድኃኒት አይ.ቲ ሶሉሽን የትኛው መድኃኒት፣ የት ይገኛል የሚለውን መረጃ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ለተጠቃሚው በማድረስ ረገድ ውጤታማ ስራ መስራት ችሏል። ሌላው በመድኃኒት አይ.ቲ.ሶሉሽን የሚሰጠው የሜዲኬሽን ዴሊቨሪ ሲስተም (Medication Delivery System) ነው። “የሜዲኬሽን ዴሊቨሪ ሲስተም ታካሚዎች በተለይም ደግሞ ለድንገተኛ (Emergency Care) ትልቅ ሃሳብ ነው ብለን ያመጣነው ነገር ነው። ካሉበት ሆነው የታዘዘላቸውን መድኃኒት ማግኘት ይችላሉ። ተጨማሪ አዲስ ያመጣነው፣ በሀገራችን



19

የመጀመሪያ የሚሆነው የኢ- ቡኪንግ ሲስተም (E-booking System) ማለትም አንድ ታካሚ ያለበት ሆኖ የመረጠውን ሐኪም እንዲያገኝ፣ የሐኪሙን ፕሮግራም አይቶ በዛ መሰረት በሚሄድበት ጊዜ የወረፋ መጨናነቅን ለማስቀረት ይረዳል። ታካሚዎች ወረፋ ሞልቶ ያገኙና የመጉላላት ችግር ሲፈጠር አየን። ስለዚህ ለምን አንድ ታካሚ ቀደም ብሎ ቡክ አድርጎ፣ በዚያ ሠዓት ሄዶ መስተናገድ አይችልም አልን፤ ይሄ በጤና ተቋማት ላይ የምናየውን አላስፈላጊ መጨናነቅ ጊዜ በመቆጠብ ጭምር ችግሮችን ፈትቶ አግኝተነዋል”።

የዓመቱ ዓለም አቀፍ ስታርት አፕ ዓለም አቀፍ የዓመቱ ስታርት አፕ (The 2024 Global Start Up of the Year) በመባል የሀገርን ስም በዓለም አቀፍ መድረክ ማስጠራት በእጅጉ ያስደስታል። የኪዩቢክ መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቅዱስ አስፋው በደቡብ አፍሪካ እና በዴንማርክ በተካሄዱ የስታርት አፕ ውድድሮች አሸናፊ ሆኗል። ይህ ፈተናዎችን እየተጋፈጡ በስታርት አፕ ስኬት ለማስመዝገብ የሚታትሩ ወጣቶችን የሚያበረታታ ነው። “ግሎባል ስታርት አፕ አዋርድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ80 ከሚበልጡ ሀገራት ከ10 ሺህ

በላይ ስታርት አፖችን አወዳድሮ የሚሸልም ድርጅት ነው። ቅዱስ በዴንማርክ ስለነበረው ሽልማት ሲገልፅ “አንድ ሰው ‘ኢትዮጵያን ወክለህ አፕሊኬሽን ሙላ!’ አለኝ። እንዴ! ምንም እኮ የለኝም ስል ‘ችግር የለውም! ዋናው ሀሳቡ ነው!’ አለኝ። ዓላማውን በማየት ነው እንደ ቀልድ ነው ያመለከትነው። እና ትዝ ይለኛል፣ የፈረንጆች ገና ዕለት ኢሜል ደረሰኝ ‘የኢትዮጵያ ወኪል ሆነሀል!’ ተባልኩ። ምስራቅ አፍሪካን ወክዬ አሸነፍኩ። ምንም ሽልማት የለውም። ዝግጅት የለውም። ግን ደረጃው እንዴት አድርገን የአፍሪካ አንደኛ ለመውጣት ተብሎ የሚታይ



20

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ነገር ስለነበረ ገረመኝ። ለምን ገና እየጀመርኩ ነው። ማሸነፋችን ከተገለጸ በኋላ ንግግር ሳደርግ መልዕክት ያስተላለፍኩት ለቡድኔ፣ ለሌሎችም ስታርት አፖች፣ እኛ ባሸነፍንበት ዘርፍ ላላሸነፉት አምስት ስታርት አፖችም ጭምር ነበር፤ ትልቅ ደስታ ነበር የተሰማኝ። ሽልማቱ ትልቅ ተስፋ ነው የሰጠን”። ምርጥ አፍሪካዊ የቢዝነስ ባለ ራዕይ ሽልማት የራይድ መስራች እና ሥራ አስኪያጅ ሳምራዊት ፍቅሩ የአፍሪካዊ ቢዝነስ ባለ ራዕይ ሽልማት አሸናፊ ለመሆን በቅታለች። እ.ኤ.አ በ2021 የአፍሪካ ሬናይሰንስ ኤንድ ዲያስፖራ ኔትወርክ (African Renaissance And Diaspora Network) በተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም በተዘጋጀው ሽልማት ሳምራዊት ፍቅሩ ለበርካቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ምርጥ አፍሪካዊ የቢዝነስ ባለ ራዕይ (Best African Business Visionary) ተብላ ተሸልማለች። ሳምራዊት በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና በሌሎች ባለድርሻ አካላት ጥምረት የስትራይድ ኢትዮጵያ 2024 ኤክስፖ ሲካሄድ ምርጥ ስታርት አፕ በሚል መሸለሟም ይታወሳል። እነዚህ ኢትዮጵያዊ ስታርት አፖች

በቀጣይ የላቀ ደረጃ ላይ ለመድረስ ታትረው እየሠሩ ነው። ነገ ትልቅ ደረጃ ለመድረስ የዓመታት ስትራቴጂክ ዕቅዶቻቸውን ነድፈው ትጋታቸውን ቀጥለዋል። ለበርካቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር፤ የኢትዮጵያ ዩኒኮርን (የሐብት መጠኑ አንድ ቢሊዮን ዶላር የደረሰ) እንደሚሆኑ ተስፋ ከሚጣልባቸው መካከል ሊጠቀሱ የሚችሉም ናቸው። የስኬታማ ስታርት አፖቹ ቀጣይ ጉዞ ኪዩቢክን ገደብ የለሽ በሚሆን ዓይነት መልክ እንደመሰረተው የሚገልጸው ቅዱስ “መቼም ቢሆን ከፕላስቲክ ቆሻሻ ብሎኬት የሚያመርት ፋብሪካ ነን ብዬ አይደለም የማየው። ዓለምን እንዴት ማፅዳት እንችላለን፤ እንዴት አድርገን የሰዎችን ኑሮ ማሻሻልና ማቃለል እንችላለን በሚል ዓይነት መንገድ ነው፤ እና ከ10 ዓመት በኋላ የምንሆነው ድርጅት በጣም የተለየ ሊሆን ይችላል ብዬ ነው የማየው” ይላል። “ራሳችንን ዩኒኮርን ብለን በቀጣይ እዛ ላይ እንሰራለን። እኛ ብቻችንን አንችልም፤ መንግሥትም ይሄንን ሊረዳ ይገባል ብዬ ነው የማስበው። ስለ እኛ አይደለም፣ ከአሁን በኋላ የሀገር ሆኗል። የሕዝብ ነው። ራይድ የእናንተ ነው፤

የሁሉም ሕዝብ ነው። ስለዚህ መንግሥትም በሄደበት ሁሉ ራይድን ማስተዋወቅ አለበት። በአፍሪካ፣ በሌሎች ሀገራትም ስናስፋፋ ቢዝነስ ዲፕሎማሲው ላይ መሰራት መቻል አለበት። እንደዚህ ዓይነት ድጋፎች ያስፈልጋሉ። እሱን ካደረግን ራይድ በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ ቦታ ይደርሳል ብዬ አስባለሁ” - የራይድ መስራች እና ሥራ አስኪያጅ ሳምራዊት ፍቅሩ። የመድኃኒት አይ.ቲ ሶሉሽን መስራቿ በአምላክ እንደ ኩባንያ ትልቁ ግባቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የጤና አገልግሎት ጥያቄ መመለስ፣ ሥራቸውን ወደ አፍሪካ በማስፋፋት ወደ ሌሎች ሀገሮች ይዞ መሄድ እንደሆነ ነው የምትገልፀው። “ጤና የአንድ ማኅበረሰብ ጥያቄ ብቻ አይደለም። የአንድ ክልል ብቻ ጥያቄ አይደለም። ቴክኖሎጂ ደግሞ የማይፈታው ችግር የለም ብለን እናምናለን። የጤናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ በመደገፉ ባደጉት ሀገራት ከኢኮኖሚ ባለፈ ምን ያህል ለውጦችን ማምጣት እንደቻለ አይተናል። ያንን ለውጥ ማምጣት ነው አንደኛው ግባችን። ከኢትዮጵያ እየወጣ ያለውን የሜዲካል ቱሪዝም ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ግባችን ነው። ይሄ ደግሞ አሁን ዘርፉ ላይ፣ ሥራው ላይ ያሉትን በቴክኖሎጂ



21

መደገፍ ሌላው የእኛ ትልቁ ግብ ነው። ሌላው ኢትዮጵያ ላይ በቀጣይ ዓመታት የዩኒኮርን ካምፓኒዎች መመስረት የሚቀር አይመስለኝም” ስትል አስተያየቷን አክላለች። ለጀማሪ ስታርት አፖች . . . ሳምራዊት ጀማሪ ስታርት አፖች ሁሌም ጥረታቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ትመክራለች። ግባቸውን አስቀምጠው ለስኬት መትጋት እንዳለባቸው ታነሳለች። ለዚህም በጥረቷ ገፍታ ባለመሄዷ ምክንያት ጀምራ ለስኬት ባላበቃቻቸው ሥራዎቿ ካጋጠማት ውድቀት መማሯን ለአብነት ትጠቅሳለች። ከቀደመው ውድቀቴ ተምሬ ራይድን ስኬታማ ማድረግ ችያለሁ ስትል ታብራራለች። የመድኃኒት አይ.ቲ.ሶሉሽን መስራችና ሥራ አስኪያጅዋ በአምላክም በችግሮች ውስጥ አዳዲስ ሃሳቦች ያሉ በመሆናቸው በትንሹም ቢሆን መሞከር ጥሩ መሆኑን ነው የምትመክረው። አንድ ቢዝነስ ሲቋቋም ለሃሳቡ ከሚኖር ፍላጎት የተነሳ ብዙ ነገሮች አይታዩም፤ ጉዳዩን ማሳካት ላይ ትኩረት ይደረጋል፤ ያ በሚሆንበት ጊዜ ተጨማሪ አማካሪዎችን መያዝ፣ በሙያው ውስጥ ያሉ ባለሙያዎችን ማካተት፣

ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ብቻ ማማከር ያስፈልጋል። ለብዙ ስታርት አፖች መውደቅ ምክንያቱ የማይመለከታቸውን ሰዎች ምክር መቀበል ሊሆን ይችላል ትላለች። “በታሰበው ሥራ ላይ የሚያተኩሩ ትምህርትና ሥልጠናዎች ያስፈልጋሉ፤ ጊዜው አሁን ላለው ትውልድ ደጋፊ ነው። ከዩቲዩብ እስከ ትላልቅ ድርጅቶች ኢንተርፕሪነርሺፕ ብዙ ነገሮችን፣ መማር ማየት የሚያስችል ነው። እነዚህ ጉዞውን ሊያቀሉት ይችላሉ” ኪዩቢክን እውን በማድረግ ሂደት የተለያዩ አጋዦች እንደነበሩትና ዕድለኛም እንደሆነ የሚገልፀው ቅዱስ አስፋው፤ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መስራቱም ምቹ መደላድል እንደፈጠረለት ገልጿል። “አብዛኞቹ ስታርት አፖች ከኮሌጅ ወጥተው፣ ብዙ ኤክስፖዥር ሳይኖራቸው ነው የጀመሩት። እኔ ትንሽ አቅም ኖሮኝ ነው የጀመርኩት። አብረውኝ የሰሩና ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሰው እኔን ወደላይ ለመጎተት አቅም የነበራቸው አጋዦች ነበሩኝ። ብዙ የዚህ ዓይነት ዕድል የሌላቸው የስታርት አፕ መስራቾች አሉ። ሁሉንም ነገር እንደ ችግር ካየነው ችግር ሆኖ ነው የሚቀረው። ተስፋ ከሌለ ሶሉሽን ፕሮቫይደር መሆን በጣም ከባድ ነው፤ ስትሞክር እንቅፋት የማይቀር ነው። ሁኔታዎችን በራዲካል



22

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ኦፕቲሚዝም (Radical Optimism) ማየት አለብን። ወጣት ደግሞ መቻል እና መቋቋም የሚችል ሰው ነው። ወጣት መሆን ደስ የሚያሰኘው ነገር ራሱን አይገድብም፤ ክሬቲቭ፤ አንድን ችግር ለመፍታት በብዙ ዓይነት መንገድ የሚያይ ነው። ስለዚህ ወጣትነትን አንደ ጥቅም (Advantage) መጠቀም ይኖርብናል፤ ለወጣቶች ያለኝ ምክር ይህ ነው”። የመንግሥት ትኩረት - ለስታርት አፕ መንግሥት ለስታርት አፕ የሰጠው ትኩረት የሚያበረታታ ስለመሆኑ ስታርት አፖች

አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የኪዩቢክ መስራቹ ቅዱስ “አሁን የመጣው የስታርት አፕ አክት በጣም የበሰለ ነው። እውነት የሆኑትን ችግሮች አይተው፣ ችግሩን እንዴት እንፍታው ብለው ስላዩት ነው። ዋናውና ትልቅ ገደብ የሆነው ሃሳብን ወደ ተግባር ለማስገባት ቢሮ ያስፈልጋል መባሉ ነው። ቢሮ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? ጉግልን ብናይ በአንድ የዘመድ ጋራጅ ውስጥ ነው የተጀመረው። አሜሪካ ውስጥ ቢሮ ከሌለህ ማቋቋም አትችልም ቢባሉ ኖሮ አሁን የደረሱበት ደረጃ ይደርሳሉ ወይ የሚለው ትልቅ ጥያቄ ነው” ካለ በኋላ፤ የሚያስደስተው



23

ነገር በመንግሥት ስታርት አፕን በተመለከተ ከዚህም በላይ ብዙ ማሻሻያዎችና እርማቶች አሉ መባሉ ትልቅ ብስለት ነው ሲል አክሏል። የራይድ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ሳምራዊት ፍቅሩ መንግሥት አሁን ለስታርት አፕ የሰጠውን ትኩረት በአዎንታ እንደምታየው ነው የገለፀችው። “እኔ የነበረብኝን ቻሌንጅ እንዳለ ትኩረት ሰጥተውታል ብዬ አስባለሁ። አሁን ገንዘብ ማግኘት (Access to Finance) ነው ትንሽ አስቸጋሪ የሚሆነው። እሱን እየሰሩበት ነው ብዬ አምናለሁኝ። አንድ ስታርት አፕ ብር ቢፈልግ ድርጅቱን ለማስፋፊያ አይዲያ ፋይናንሲንግ (Idea Financing) ብለው ባንኮቹ መደገፍ አለባቸው። እና እሱ ላይ ጠንክረው መስራት አለባቸው ብዬ አስባለሁ። የባንኮችም ትብብር ያስፈልጋል፤ እኔ የቢሮ ኪራይ መክፈል አቅቶኝ የተደበቅኩበት ጊዜ አለ። አሁን ቢሮ አያስፈልግም ይሄ ደስ ይላል። የንግድ ፈቃድ አያስፈልጋቸውም። ዝም ብለው መስራት ይችላሉ። ትልቅ ነገር ነው”። ኢንኩቤሽን ሴንተሮች ስታርት አፕ ላይ ያሉ ወጣቶች ሃሳቦቻቸውን ወደ አዋጭ ንግድ ለመቀየር እንዲችሉ ሥራዎቻቸውን እንዲሰሩባቸው

የተመቻቹ ቦታዎች ናቸው። ኢንኩቤሽን ሴንተሮችን ለማቋቋም በመንግሥት በኩል ያለው ተነሳሽነት የሚያበረታታ ስለመሆኑም ሳምራዊት አንስታለች። በተለያዩ ቦታዎች ለኢንኩቤሽን ሴንተር የማቋቋም ሃሳብ መኖሩ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው። አሁን ለስታርት አፖች ብዙ ነገሮች በተቻለ አቅም ክፍት መደረጋቸው መልካም ነው። “እኛ እነዚህን ፕላትፎርሞች ስንሰራ ወደ ሁለት ዓመት ወስዶብናል፤ አሁን አገልግሎታችንን ወደ ሕዝቡ ባመጣንበት ጊዜ በሀገር ደረጃ በጣም ደጋፊ የሆኑ ፖሊሲዎች፣ ከመንግሥትም ከተለያዩ አካላትም ትላልቅ ድጋፎች በስታርት አፕ ዙሪያ እየተደረጉ ነው። ይሄ ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት እኛ ስራ ስንጀምር ከነበረበት ጊዜ በፍፁም የሚነፃፀር አይደለም። ከመንግሥት ድጋፍ ማግኘት ማለት እንደኛ ላሉ ካምፓኒዎች ትልቁን ሸክም ያቀላል። ለምሣሌ በታክስ ደረጃ፣ በቢሮ ደረጃ፣ በፖሊሲዎች ደረጃ ስታርት አፖች ላይ ትልቁ ነገር ብዙ ጊዜ ኢኖቬቲቭ የሆኑ አዲስ ሃሳቦችን ነው ይዘው የሚነሱት። አዲስ ሃሳብ፣ አዲስ የሥራ ፈጠራ በአዲስ ፖሊሲ ሊደገፍ ይገባዋል። ከዚህ በፊት እኛ በምንሰራበት ጊዜ አይዲያል ኢኖቬቲቭ ለሆኑ ተቋማት ለየት ያለ ድጋፍ

አልነበረም” ስትል መንግሥት ለስታርት አፕ የሰጠው ትኩረት መልካም ጅምር መሆኑን የገለጸችው የመድኃኒት አይ.ቲ ሶሉሽን መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ በአምላክ አለማየሁ ነች። በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢኖቬሽንና ስታርት አፕ ልማት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰላምይሁን አደፍርስ በበኩላቸው መንግሥት ስታርት አፕ፣ ኢኖቬሽን፣ ምርምር፣ ዲጂታላይዜሽን፣ ሳይበር ሴኪዩሪቲን አደራጅቶ ሲይዘው በዋነኛነት ውጤታማ እንደሚሆን አብራርተዋል። “ከመንግሥት አንፃር ፖሊሲ ከወጣ ሁለት ዓመት ሆኖታል። ፖሊሲው ሲወጣ ስታርት አፕ እዛ ውስጥ አለ፤ መንግሥት ፍላጎቱን ቢገልፅም ወደ ተግባር መግባት ግን ቀላል አይደለም። ሕግ ይፈልጋል፣ የስታርት አፕ አዋጅ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ሲንከባለል የቆየ አዋጅ ነው። ቱኒዚያ ስትጀምር እኛም ጀምረን ነበር። እነ ናይጄሪያ ከእኛ በኋላ ነው ያወጡት። አዋጁ አስፈላጊ ነው። ፖሊሲ ፍላጎትን ነው የሚገልፀው። ፍላጎት አለኝ ከማለት ያለፈ ፍላጎቱ ምን እንደሆነ፣ ምን ዓይነት ስትራቴጂ ብከተል ይሻላል ከማለት ባለፈ የማስፈፀሚያ መሣሪያ አይደለም። ሕግ ይፈልጋል፣



24

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ፋይናንስ ይፈልጋል፣ ሕግን በተመለከተ አዋጅ ይፈልጋል”። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከሚጠበቅበት ተግባራት አንዱ የስታርት አፕ ማኅበር እንዲመሰረት ማገዝ ነው። ”የስታርት አፕ ኮሚዩኒቲ በተለያየ ጊዜ የተለያየ ቢሆንም መረጃዎችን ከዛ ነው የምናገኘው። ራንደምሊ አላዘጋጀንም። ስናደራጅ ስንደግፍ የነበሩት ናቸው ተሰብስበው ወደ ኤግዚቢሽን የመጡት“ ብለዋል። በዩኒቨርሲቲዎች ደረጃ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች እንደ ጅምር (Early Stage) ተማሪን መሰረት ያደረጉ ስታርት አፕ መፍጠሪያ መሆን እንዳለባቸውና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የመግባቢያ ስምምነት (ኤም.ኦ.ዩ) በሁለቱም ሁነት መፈራረም ስለመጀመሩ ጠቅሰዋል። ሁሉም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ልክ ለሥራ እንደሚያመለክተው ለስታርት አፕ ጉዞ እዛ ሆኖ ሲጀምር ማየት አለበት ይላሉ። “አርሊ ስቴጅ መፍጠሪያ እንዲሆኑ ነው ዩኒቨርሲዎችን በተለይ የፈለግነው። አስተማሪዎች ምርምርን መሰረት ያደረጉ ስታርት አፖችም እንዲፈጥሩ ይፈለጋል። ታፍ ቴክ የሚባል አለ (Tough Tech) አለማችን እየገጠሟት ያሉ ችሮችን በሳይንስ፣ በምህንድስና እና

በመሳሰሉት የሚፈታ ቴክኖሎጂ ነው። አሁን የዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ውጭ ካሉ ስታርት አፖች ጋር እየተሳሰሩ ላይሰንሳቸውን እየሰጡ ኮሜርሺያላይዜሽን ቀላል የሆነበት መንገድ አለ። ዲፕ ቴክ የሆኑ፣ ተማራማሪዎችን የሚያካትት ሲሆን ደግሞ ተመራማሪዎች መስራች (Founder) ሆነው የሚወጡበት ሁኔታ መኖር አለበት ብለን፤ ዩኒቨርሲቲም እንደዛው ነው። ዩናይትድ ኔሽን ጋርም ቲምቡክቱ የሚባል ፕሮግራም አለ። በቲምቡክቱ ማዕቀፍ ይህን ለመስራት እየሞከርን ነው። የሚፈልገው ነገር ቀላል አይደለም። እንደዚህ ዓይነት ቢዝነሶች በተለይም ዩኒቨርሲቲዎች በዚህ መስመር እንዲይዙ ከተደረገ በእርግጠኝነት ወሳኝ የሚባሉ አቅሞች ከዩኒቨርሲቲ ይወጣሉ” በማለት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ይህንን ለማሳካት በስፋት እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል። ከማን ምን ይጠበቃል ስታርት አፕ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርስ መንግሥት ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ይጠበቃል። እንዲሁም በጤና፣ በትምህርት እና በሌሎችም የተለያዩ ዘርፎች መሬት የወረደ ፖሊሲ ያስፈልጋል። በግሉ ዘርፍ ባለሀብቶች ከውጭ አገራት እየገቡ መሆኑን ተከትሎ

ዛሬም የኢትዮጵያዊያን ሃሳብ እየተደገፈ ያለው በባለሀብቶች ነው ያለችው በአምላክ አለማየሁ በአንጻሩ በአገር ውስጥ በንግዱ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ኢኖቬቲቭ የሆኑ ወጣቶችን መደገፍ ላይ ውስንነቶች ይታያሉ ትላለች። ስታርት አፕን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ በሚደረገው ጥረት የትምህርት ሥርዓቱ ለስታርት አፕ ትኩረት መስጠት እንዳለበትም ታነሳለች። ”በትምህርት ሥርዓታችን ውስጥ እየተሻሻሉ ያሉ ነገሮች እንዳሉ ሆኖ፤ ተማሪዎችን ለኢኖቬሽን የሚያበቃ ሥርዓት መዘርጋት፤ ከዚያም ባለፈ ዲጂታል ሊትረሲ (Digital Litracy) በማኅበረሰቡ ዙሪያ የቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም፣ ችግሮችን እንዴት በቴክኖሎጂ መፍታት ይቻላል የሚለውን በማኅበረሰቡ ዘንድ ማስረጽ በእነዚህና በሌሎችም መንገዶች እየተደገፈ መሄድ አለበት፤ ስታርት አፖች መስራታችን ብቻ በቂ አይደለም። ለቴክኖሎጂ ቅርብ የሆነ ማኅበረሰብ እንዴት እንፍጠር? ማኅበረሰቡ አጠቃቀሙን እንዴት ይረዳ? የሚለው ሚዲያውን፣ የትምህርት ዘርፉን በሌሎችም ዘርፎች ያሉትን የሚመለከት ነው። በተለይ በትምህርት ዘርፉ ላይ ኢኖቬቲቭ የሆነ ትውልድ መፈጠር አለበት።



25

ተማሪዎች እንዴት ኢኖቬቲቭ ይሁኑ፣ እንዴት ኢንተርፕሪነር የሆኑ ልጆችን እናብቃ፣ ታለንት እንዴት እናውጣ የሚለው ላይ መስራት መቻል አለብን“ ስትል የመድኃኒት አይ.ቲ ሶሉሽን መስራቿ አስተያየቷን ሰጥታለች። በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የኢኖቬሽን እና ስታርት አፕ ልማት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰላምይሁን አደፍርስ በበኩላቸው ስታርት አፕ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርስ ሁሉም በጋራ መስራት እንዳለበት አንስተዋል። መንግሥት የአንበሳውን ድርሻ ወስዶ የተለያዩ ተግባራትን በመከወን ላይ ነው። “ካፒታል ማርኬት አካባቢ፣ በኢንቨስትመንቱ በኩል የሚሞከሩ ነገሮች አሉ። ሥርዓተ ምህዳሩን የሚያነቃንቅ ባለሀብትን የሚያበረታታ፤ ግሎባል ኢንቨስተሮችም እንዲመጡ ይጠበቃል። ኢኮሲስተም ቢውልደርስ የምንላቸው፤ ኢንኩዩቤሽን፣ አክስለሬሽን እነዚህን የሚደግፉ ተቋማትም ኃላፊነት ለመውሰድ ፍላጎት እንዲኖራቸው፤ በለጋሾች ገንዘብ ብቻ ሳይሆን እዚሁ ስታርት አፖችን በመፍጠር ዘላቂ የሆነ ሥርዓተ ምህዳር አንዲፈጠር መንግሥት ዋና ሚና አለው። ለሁሉም የቁጥጥር እና የማበረታቻ ፓኬጆች መኖር አለባቸው። ይሄንን

መንግሥት ነው የሚያቀርበው። ኢኮሲስተም ቢውለደሮች ወይንም ኢንኪዩቤሽን፣ አክስለሬሽን እነዚህ ስታርት አፕ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት የሚባሉት አቅማቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ማደግ አለበት። በተቻለ መጠን በለጋሾች ከሚመራው አካሄድ ወደራሳቸው ስትራቴጂ መጥተው ይሄን ያህል ስታርት አፕ እዚህ ያመርታሉ ማለት አለበት። ለስታርት አፕ ሥልጠና መስጠት ብቻ በቂ አይደለም። ሰባት እና ስምንት ዓመት ለሚያደርጉት ጉዞ የተለያየ ዓይነት የኢንቨስትመንት ፓኬጅ ማቅረብ፣ ዕድሎች መፍጠር እና መምራት አለባቸው” ነው ያሉት። ይህን ማድረግ የሚያስችል አቅም ለመፍጠርም ከአውሮፓዊያን ቢዝነስ ኔትወርክ እና ከጂ.አይ. ዜድ ጋር ደረጃ የማውጣት ሥራ እየተሰራ መሆኑን አክለዋል። ስታርት አፕ ላይ ማስተርካርድን ጨምሮ በርካታ ኢንቨስትመንት ስለመኖሩ ያነሱት አቶ ሰላምሁን በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ፕላትፎርሞች፣ ኢንኩዩቤሽን ሴንተሮች ሊኖሩ እንደሚገባና መስፈርቶችን የሚያሟሉ መሆን እንዳለባቸው፤ ስታርት አፕን በፋይናንስ መደገፍ እንዲሁም ወደ ራስ ገዝ እየሄዱ ከመሆናቸው አንፃር ከሚሸጡት ገቢ ማግኘት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት። ዩኒቨርሲቲዎች

ምርምር ካልሸጡ፣ ካልሰሩ፣ ካላማከሩ፣ ከኢንደስትሪዎች ጋር ካልተሳሰሩ፣ ምርትና እና አገልግሎቶቻቸውን ካላወጡ መዝለቅ አይችሉም ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ ስታርት አፕ ዩኒቨርሲቲዎችም ዕውቀታቸውን ለገበያ ይፋ የሚያደርጉበት ሥርዓት (Platform) አመልክተዋል። እናም ጥሩ የኢንኩዩቤሽን ላቦራቶሪዎች እንዲኖሯቸው፣ ለተማሪዎች ወጥነት ያላቸው ውድድሮች እንዲፈጠሩ፤ ሁልጊዜም የሚኖሩና ተማሪዎችም ግብ አድርገው የሚሄዱባቸው ውድድሮች፣ የድጋፍ ፕሮግራሞች እንዲኖሯቸው ይጠበቃል ብለዋል። ከመሰረተ ልማት አንፃር እንደ አይ.ሲ.ቲ ፓርክ፣ ቡራዩ የተሰጥኦ ማበልፀጊያ ማዕከል (ትምህርት ቤት) የመሳሰሉት በአገሪቷ በስፋት ተደራሽ ማድረግ ይገባል። ጊዜው የተደራጀ የመረጃ ሥርዓት መኖር ግድ የሚልበት ነው። በአጠቃላይ ጊዜው የዲጂታል አገልግሎትን የሚጠይቅ ነው። በመሆኑም ሁሉም ባለድርሻ አካል በሚገባው ልክ መንቀሳቀስ ከቻለ ሥርዓተ ምህዳሩ አሁን ካለበት ደረጃ ወደ ቀጣዩ ግሎባላይዜሽን መሻገር ይችላል።



26

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የምትቆጣጠረው

ፖለቲካ



27

የባሕር በር ለቀጣናው ልዕልና

ዓለማችን ተፈጥሮ ከለገሳት በርካታ ሀብቶች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰውና የዓለምን ሦስት አራተኛ የሚሸፍነው የውሃ ሀብት ነው። ይህም ማለት በውሃ የተሸፈነው የዓለማችን ክፍል በጠቅላላው 71 በመቶ ገደማ ሲሆን ትላልቅ ወይንም ሰፋፊ ውቅያኖሶችና ባሕሮችን ይይዛል። እነዚህ ውቅያኖሶችና ባሕሮች ድንበር ተሻጋሪና በርካታ አገራትን የሚያዋስኑ ናቸው። የዓለም ትልቁ የውሃ አካል ፓስፊክ ውቅያኖስ አስያ፣ ኦሽንያ፣ ደቡብ አሜሪካና ሰሜን አሜሪካን፤ አትላንቲክ ውቅያኖስ አውሮፓን፣ አፍሪካን፣ ሰሜን አሜሪካን እና ደቡብ አሜሪካን እንዲሁም ሜዲትራኒያን ባሕር አውሮፓ፣ አፍሪካና

በፈትሂ ማህዲ ወዚር (ዶ/ር) (በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የውጭ ግንኙነትና ሠላም ጉዳዮች

ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ)



28

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

አስያን የሚያዋስኑ ሲሆን ቀይ ባሕር ደግሞ አፍሪካን ከአስያ በመለየት በስዊዝ ቦይ በኩል ከህንድ ውቅያኖስ ጋር ይገናኛል። የዓለም አገራትን ተፈጥሯዊ አቀማመጥ ስንመለከት ከፊሉ የባሕር አዋሳኝ ድንበር ሲኖራቸው የተወሰኑት ደግሞ ዕድል ያልቸራቸው የባሕር ድንበር እንዲሁም የባሕር በር የሌላቸው ናቸው። ይህን ተፈጥሯዊ ወይም በታሪክ ሂደትና በተለያዩ ምክንያቶች የባሕር በር መዳረሻ የተነፈጉ/ ያልተቸሩ አገራት የባሕር ድንበር ካላቸውና በቀጣናው ወይም በአቅራቢያ ከሚገኙ አገራት ጋር በትብብር በመቀናጀት ፍትሃዊና ምክንያታዊ በሆነ እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ መጠቀም እንዲችሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ አገራት ተስማምተዋል። ምክንያቱም ከላይ በከፊሉ የተጠቀሱት ውቅያኖሶችና ባሕሮች ተፈጥሮ ለዓለም ሕዝብ የቸረቻቸው የጋራ ፀጋዎች በመሆናቸው ነው። አገራት እነዚህን ዓለም አቀፋዊ የጋራ ፀጋዎች ፍትሃዊና አካታች በሆነ መልኩ መጠቀም እንዲያስችላቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባሕር ሕግ (United Nations Convention on the Law of the Sea – UNCLOS)

አውጥቷል። ስምምነቱ እ.አ.አ በ1982 በሞንቴጎ ቤይ-ጃማይካ ተቀባይነትን አግኝቶ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈረመ ሲሆን በቂ ቁጥር ያላቸው አገራት ስምምነቱን ካጸደቁት በኋላ በይፋ ተግባራዊ መሆን የጀመረና በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም ሰፊ ተቀባይነት ያለው የባሕር ሕግ ስምምነት ነው። ይህ ስምምነት በአጠቃላይ የባሕር እና የባሕር ዳርቻዎችን በተመለከተ በርካታ ጉዳዮችን የሚያካትት የባሕር ዞኖች (የባሕር ዳርቻ አገራት የሚቆጣጠሯቸውን የተለያዩ የባሕር ክልሎች፣ የግዛት ባሕር፣ ተቀራራቢ ዞን ወይም ክልል፣ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን፣ ወዘተ. . .)፣ የባሕር ሀብቶች እንደ ዓሣ፣ ዘይት፣ ጋዝ እና ሌሎችንም እንዴት ማስተዳደር እንደሚቻል፣ የባሕር ላይ መጓጓዣዎችን የሚቆጣጠሩ ሕጎች፣ የባሕር አካባቢን ከብክለትና ከመጥፋት ጥበቃ፣ የባሕር ላይ ምርምር፣ የባሕር ላይ ግጭቶችን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። በአጠቃላይ ስምምነቱ ተፈጥሮ የለገሰችውን፣ ዓለምአቀፋዊና የጋራ ፀጋ የሆነውን የውሃ ሀብት በተመለከተ የአጠቃቀም፣ የአስተዳደር፣ የጥበቃና የባሕር ላይ ግንኙነቶችን የሚመለከቱ ሰፊ ጉዳዮችን አካቷል። የዚህን የባሕር ሕግ ስምምነት



29

አንቀጽ 69 ንዑስ አንቀጽ 1 እስከ 5 ስንመለከት የባሕር በር የሌላቸው አገራት ፍትሃዊና የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ እንዴት የባሕር በር ማግኘት እንደሚችሉ ይደነግጋል። በተጨማሪም አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ የባሕር በር የሌላቸው አገራት በስምምነት የተደረገ የተለየ የአገልግሎት ክፍያ ከሌለ በስተቀር ለተገለገሉበት ባሕር ምንም ዓይነት የትራፊክ ታክስ ወይንም ሌላ ክፍያ እንደማይጠየቁ በድንጋጌው አስቀምጧል፡፡ ይህ ማለት የባሕር በር የሌላቸው አገራት በአካባቢያቸው ካለው ባሕር የተፈጥሮ ሀብት እኩል የመጠቀም መብት እንዳላቸው ይደነግጋል ማለት ነው፡፡ ይህም፤ ዓሣ ማጥመድንና በባሕር ውስጥ የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶችን ፍለጋ ጨምሮ ሌሎች ከባሕር ተፈጥሮ ጋር የተያያዙ ሀብቶችን ተጠቃሚነት መብት ያካትታል፡፡ እነዚህን ዓለምአቀፋዊ ዳራዎች ግንዛቤ ውስጥ በማስገባትና ዓለምአቀፍ የውሃ ሕግ መርሆዎችን መሰረት በማድረግ ፍትሃዊና ምክንያታዊ የባሕር በር አጠቃቀምን ማስፈን፣ ትብብርን ማጠናከርና የጋራ ዕድገትን መጎናፀፍን በርካታ ጠቀሜታዎች ለአገራት እንደሚያበረክት መገንዘብ አስፈላጊ ይሆናል። ምክንያቱም ዓለምአቀፍ የውሃ

ሕግ መርሆዎችን መሰረት ማድረግ ፍትሃዊና ምክንያታዊ የባሕር በር አጠቃቀምን ለማስፈን፣ ለአገራት ዕድገትና ለዓለም ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ስለሚታመንበት ነው። የባሕር ዳርቻ ወይንም የባሕር በር የሌላቸው አገራት በተለይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገታቸውን ለማፋጠንና ከተቀረው ዓለም ጋር የንግድ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር የባሕር በር ማግኘታቸው እጅጉን አስፈላጊ ነው። ዓለምአቀፍ ተሞክሮዎችን ለአብነት ብንመለከት በርካታ አገራት ከጎረቤቶቻቸው ጋር ስምምነቶችን በማድረግ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ለምሣሌ በላኦስ እና በ ቬትናም (Laos and Vietnam ) በደቡብ አፍሪካና በሌሶቶ (South Africa and Lesotho) እንዲሁም በኡዝቤኪስታን እና በካዛኪስታን (Uzbekistan and Kazakhstan) መካከል የተደረጉ ስምምነቶችን ብቻ መጥቀስ ይቻላል። ላኦስ፣ ሌሶቶና ኡዝቤኪስታን የባሕር ዳርቻ ያልነበራቸው አገራት የነበሩ ሲሆኑ ዓለምአቀፍ የውሃ ሕግ መርሆዎችን መሰረት በማድረግ ከጎረቤቶቻቸው አገራት ጋር ስምምነት በመፈፀም የባሕር በር ለማግኘት ችለዋል። በአገራቱ መካከል የተደረጉት

ስምምነቶች፤ ስምምነቱን ተግባራዊ ላደረጉት ስድስቱም አገራት በርካታ ጠቀሜታዎችን ስለማስገኘቱ በርካታ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል። ነገር ግን ወደብ ያልነበራቸውና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ጎረቤት አገራትን በመጠቀም የባሕር በር ካገኙ አገራት አንጻር የተገኘውን ጠቀሜታ ጠቅለል ባለ መልኩ ስንመለከተው አገራቱ ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ልማት ማምጣት አስችሏቸዋል። ይህ ብቻም አይደለም አገራቱን ለዓለም ገበያ በቀላሉና በተቀላጠፈ ሁኔታ መድረስ እንዲችሉም አድርጓቸዋል፤ አገራቱ የንግድ ዕድገት ማስመዝገብ ችለዋል፣ በዓለም ገበያ ላይ መሳተፍና ገቢና ወጪ ምርቶችን በቀላሉ፣ በተቀላጠፈና በተመጣጣኝ ዋጋ ማስገባትና ወደ ውጭ መላክ ችለዋል፣ የስራ ዕድል ፈጥረዋል፣ ኢንቨስትመንትን ማበረታታትም አስችሏቸዋል። የባሕር በር ለውጭ ኢንቨስትመንት ማራኪ፤ እንዲሁም በባሕር ዳርቻ ያሉ አገራትን መጎብኘት ለቱሪስቶች እጅግ ሳቢ በመሆኑም የቱሪዝም ዕድገትን ማምጣት ችለዋል። ዓለምአቀፍ የውሃ ሕግ መርሆዎችን መሰረት በማድረግ የባሕር ዳርቻ ወይንም የባሕር በር የሌላቸውን አገራት ከቀጣናቸው ወይም ከጎረቤት



30

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

አገራት ጋር በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ማግኘታቸው በርካታ ጠቀሜታዎችን የሚያስገኝና ዓለምአቀፍ የሕግ መሠረትና ድጋፍ ያለው ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ተፈጥሮ ለመላው የዓለም ሕዝብ በፀጋነት የለገሰቻቸውን የውሃ ሀብቶች ሁሉምንም አገራት በተቻለ መጠን እኩል ተጠቃሚ በማድረግ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲፈጠር ማድረግ ይገባል። ከላይ በምሣሌነት የተጠቀሱት አገራት በትብብርና በቅንጅት እየሰሩ፣ የጋራ ጥቅሞቻቸውን እያስከበሩ፣ የድንበር አለመግባባቶችን እየቀነሱ እንዲሁም በቀጣናቸው ያለውን የውሃ ሀብት በጋራና በትብብር እያስተዳደሩ የባሕር ሀብቶችን በዘላቂነት መጠቀምና ክልላዊ ትብብርን ማጠናከር ችለዋል። በተጨማሪም አገራቱ የባሕር በሮቻቸው የሽብርተኞች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ሽብርተኝነትን በጋራ በመከላከል፣ ሰብዓዊ ዕርዳታዎች በባሕር በሩ በቀላሉ እንዲጓጓዙ በማድረግ፣ የውሃ ሀብቶችን ዘላቂ እና ቀጣዩን ትውልድ ታሳቢ ባደረገ መልኩ በመጠቀም እንዲሁም በባሕር በር አጠቃቀም ላይ የሚከሰቱ ግጭቶችን በመቀነስ በቀጣናቸው፣ በአህጉራቸውና በዓለምአቀፍ ደረጃ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ

የሚደረገውን ጥረት በማገዝ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛሉ። የባሕር ዳርቻ ወይም የባሕር በር የሌላቸውን ታዳጊ ወይም ያላደጉ አገራትን (Land locked developing countries) የኢኮኖሚ ዕድገት ሁኔታ ስንመለከት ባሉባቸው ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች ላይ የባሕር በር የሌላቸው መሆናቸው “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ ተጨማሪ ችግሮችን ይፈጥርባቸዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (United Nations office of

the high representative for the least developed countries, landlocked developing countries and small island developing States) እ.አ.አ በ2013 ባወጣው ሪፖርት የባሕር በር የሌላቸው ታዳጊ አገራት የባሕር በር ካላቸው አገራት የዕድገት ደረጃቸው በአማካይ 20 በመቶ ዝቅ ያለ እንደሆነ በጥናቱ አመላክቷል። ይህም ማለት አገራቱ የባሕር በር ስለሌላቸው ብቻ 20 በመቶ የሚሆነውን ዕድገታቸውን አጥተዋል። የባሕር በርን ከአገራችን ሁኔታ ስንመለከት ኢትዮጵያ የባሕር



31

በር የነበራትና በታሪክ አጋጣሚ በተፈጠረ ክስተትና ስህተቶች ምክንያት የባሕር በር አልባ እንድትሆን የተደረገች አገር ነች። አገሪቱ ከቀይ ባሕር ያላት ርቀት ከ60 ኪሎ ሜትር የማይበልጥ ሆኖ ሳለ ነገር ግን የባሕር በር መዳረሻ የላትም። በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ከተቀረው ዓለም ጋር የንግድ ልውውጥ ለማድረግ በጎረቤት አገር ጅቡቲ የሚገኘውን የባሕር ወደብ ነው የምትጠቀመው። 95 በመቶ የሚሆነው የገቢና የወጪ ሸቀጥም በዚሁ ብቸኛ በሆነው የጅቡቲ ወደብ ነው የሚንቀሳቀሰው። ለዚህ ወደብ አገልግሎት ኢትዮጵያ በዓመት

ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለጅቡቲ የምትከፍል ሲሆን ላለፉት 30 ዓመታትና ከዛ በላይ አገልግሎቱን በዚሁ መንገድ እያገኘች ትገኛለች። ይህ በየዓመቱ የሚፈፀመውን ክፍያ ኢትዮጵያ ለተለያዩ የልማት ሥራዎች ብታውለው በኢኮኖሚና በሁለንተናዊ ዕድገቷ ላይ ሊያመጣ የሚችለውን አዎንታዊ ተጽዕኖ መገመት አይከብድም። ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ መሆኗ በተለያዩ መንገዶች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገቷን የሚገድብና ሁለንተናዊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎቿ ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥር ነው። በተለይ ጉዳዩን በአገሪቷ እየጨመረ በመሄድ ላይ ያለውን የሕዝቧን ቁጥርና የኢኮኖሚ ዕድገቷን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ስንመለከተው የኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት እጅጉን አስፈላጊ ነው። የባሕር በር ያላቸው አገራት የውጭና የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንት የመሳብ ትልቅ አቅም ያላቸው ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ። የኢትዮጵያ የሕዝብ ብዛት ከ120 ሚሊዮን በላይ ሲሆን በቀጣይ ዓመታት ከፍተኛ ዕድገት እንደሚያሳይ ትንበያዎች ያመላክታሉ። የሕዝብ ብዛቱ እ.አ.አ በ2035 ወደ 150 ሚሊዮን እንዲሁም በ2050 ወደ



32

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

204 ሚሊዮን እንደሚያድግ የሚጠበቅ ሲሆን ለዚህ አምራች የሰው ኃይል የሥራ ዕድል መፍጠር የግድ ይላል። ይህ ካልሆነ በአገሪቷ እንዲሁም በቀጣናው ላይ ተዛማች ተጽዕኖ (Spillover effect) በመፍጠር የበኩሉን አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠሩ አይቀሬ ነው። ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት የንግድ ልውውጥን ለማስፋፋትና ለማቀላጠፍ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል። አገሪቷ የምታመርታቸውን ምርቶች ተወዳዳሪ በሆነ ዋጋ፣ ፈጣንና በተቀላጠፈ ዘዴ ወደ ዓለም ገበያ ማድረስ እንድትችል ይረዳል። ይህም የምርቶቿን የውጭ ምንዛሬ ማግኛ አቅም ይጨምራል። ከውጭ አገራት የሚገቡ ምርቶችን በቀጥታ በራሷ የባሕር በር በኩል ማስመጣት ደግሞ የሎጂስቲክስ ወጪን ስለሚቀንስ በሸቀጦችና ግብዓቶች ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ከፍተኛ ዋጋ ወይም ወጪን ይቀንሳል። ይህ ደግሞ ለሸማቹ ሕዝብ ተመጣጣኝና የተስተካከለ ዋጋ ስለሚያስገኝ ሊከሰት የሚችለውን የኑሮ ውድነት መቆጣጠር ያስችላል። የባሕር በር ማግኘት የአገሪቷ የኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲስፋፋ አይነተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። የማምረቻ መሳሪያዎችን፣ ጥሬ ዕቃዎችንና ሌሎች የኢንዱስትሪ

ግብዓቶችን በቀላሉ፣ በቅናሽ ዋጋና በተቀላጠፈ ዘዴ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ የበለጠ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያን ምርቶች በባሕር በኩል በተቀላጠፈና ተወዳዳሪ በሆነ ዋጋ ወደ ውጭ በመላክ የኢንዱስትሪ ዕድገትን ያፋጥናል። በሌላ በኩል በባሕር ዳርቻ የሚገነቡ የቱሪስት መስህቦች ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ተጨማሪ ዕድል ይፈጥራሉ። የአምራች ኢንዱስትሪውና የቱሪዝም ዘርፎች መስፋፋት ለኢኮኖሚው ከሚያበረክተው ጠቀሜታ በተጨማሪ ከፍተኛ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ያደርጋል። ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት (ዓለም አቀፍ ተቋማትም በሪፖርታቸው እንዳረጋገጡት) አሁን ባለው በብቸኛው የጅቡቲ ወደብ ብቻ መቀጠል አዳጋች እየሆነ ነው። ግዙፍ ኢኮኖሚ እየገነባችና በጠቅላላ አገራዊ ምርቷ (GDP) በምስራቅ አፍሪካ አንደኛ እንዲሁም በአፍሪካ አምስተኛ ደረጃ ላይ ለምትገኘው ኢትዮጵያ፣ የጅቡቲ ወደብ ከኢኮኖሚ ዕድገትና ፍላጎቷ ጋር መሄድ የሚችልበት ደረጃ ላይ አይደለም፤ ይህም በቀጣዮቹ ዓመታት በሁለት

አሃዝ (Double digit growth) በማደግ በ25 ዓመታት ውስጥ ጠቅላላ አገራዊ ምርቷን (GDP) ወደ 4 ነጥብ 8 ትሪሊዮን ዶላር በማድረስ ከዓለም 14ቱ ግዙፍ ኢኮኖሚዎች ተርታ ለመድረስ የምታደርገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳረፉ አይቀርም። የባሕር በር የኢትዮጵያን ጂኦ- ፖለቲካዊ አቋም ከማጠናከር አንጻርም ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል። በተለይ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ውስጥ ንቁ ተሳታፊና ተጽዕኖ ፈጣሪ እንድትሆን ትልቅ እገዛ ያደርጋል። በርካታ ኃያላን አገራት (ፈረንሳይ፣ አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ጀርመን፣ ኢጣሊያ፣ ስፔን፣ ቻይና እና ሌሎችም) በጎረቤታችን ጅቡቲ የጦር ካምፕ በመገንባት በቀጣናው የሚከሰተውን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በመቃኘት የአገሮቻቸውን ጥቅም ለማስከበር ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ። አሁን ያለንበት ዓለምአቀፍ ነባራዊ ሁኔታ በፍጥነት የሚቀያየርና ዘርፈ ብዙ መገለጫዎች ያሉት፤ ፈርጀ ብዙና መጠነ ሰፊ ትስስር የሚስተዋልበት፤ ዓለም ታሪካዊ የብዝሀ ቀውስ (Poly-Crisis) ውስጥ እያለፈች ያለችበት መሆኑ፣ ከፍ ያለ የጂኦ-ፖለቲካ ውጥረትና የበላይ ነን የሚሉ አገራት ፉክክር ያለበት፣ የአየር



33

ንብረት ለውጥ አደጋዎች የሚስተዋሉበት፣ እየጨመረ የሚሄድ አለመመጣጠንና የኢኮኖሚ ዋስትና ማጣት፣ ኃያላን አገራት ገንዘብን ወይንም ከረንሲን፣ ኃይልን፣ ምግብን፣ ማዳበሪያን፣ መድኃኒቶችና ክትባቶችን እንደ መሣሪያ (weaponazation) መጠቀማቸውና ቀውሱን ማባባሱ፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ፈርጀ ብዙ ተጽዕኖ እና የድህነት ፈተናዎች ይጠቀሳሉ። እነዚህ ምክንያቶች ዓለም የብዝሃ ቀውስ ዘመን ውስጥ እንደምትገኝ ጥቂት ማሳያዎች ናቸው። ይህ ጉዳይ በአገራት ላይ በርካታና ውስብስብ ችግሮችን የሚያመጣ ሲሆን ባሕሪያቶቹም በዋናነት ኢ-ተገማች፣ በጊዜና በቦታ ያልተገደበ፣ መፍትሔው አንድ ያልሆነ፣ ለዓለም አቀፍ ፖለቲካና አስተዳደር ፈተና የሆነ፣ አማራጭ እውነታን የሚፈልግ መሆኑና ዓለምአቀፍ ተቋማት ውሳኔ ላይ መድረስ እንዳይችሉ ማድረጉ (ብዙ ጉዳዮች በይደር የሚታለፉ በመሆናቸው) ተጠቃሽ ናቸው። ይህ ዓለምአቀፋዊ ሁኔታ አገራችን አማራጭ የባሕር በር ለማግኘት እያደረገች ባለው ጥረት ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የበኩሉን ተጽዕኖ ማሳረፉ አይቀርም። ምክንያቱም ዓለም

ከባለ አንድ ወደ ባለ ብዙ ዋልታነት ለመለወጥ የምታደርገው ሽግግር ገና ያለየበት ሁኔታ መሆኑ፤ ባለ ብዙ ዋልታ ዓለም እንዲኖር በሚሹ ኃያላን አገራት መካከል ያለው ፉክክር እያየለ የመጣበት፣ ቀጣናዊ የበላይነትን ለመያዝ ጥረት የሚደረግበትና ጥንድ የበላይነት ሁኔታዎች እየታዩ ያሉበት ሁኔታዎች በመኖራቸው ነው። በተጨማሪም ድህረ እውነትና የመረብ ዘመን አገራት ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ ያለ ሲሆን እውነትን ከውሸት መለየት በማይቻልበት ዓለም አገራት ዜጎቻቸውን በአግባቡና በሰላም ለማስተዳደር ፈተና እየሆነባቸው ይገኛል። እነዚህ ዓለማዊና ቀጣናዊ ሁኔታዎች በአገራችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖዎች የመፍጠር አቅም ያላቸው ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል የዓለምአቀፉ የጂኦ-ኢኮኖሚክስ፣ ጂኦ- ፖለቲካና ጂኦ-ስትራቴጂ ሽኩቻና ሀሳብ ተጠቂ መሆን፣ በቀይ ባሕር ላይ ከዚህ በፊት በተለየ ሁኔታ ፉክክር ያየለበት መሆኑ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩ (የንግድ መርከቦች በአሸባሪዎች መጠቃታቸው)፣ የተፈጥሮ ሃብትና የንግድ መስመር የመቆጣጠር ፉክክር ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው። ይህ ሁኔታ የአገራችንን የባሕር

በር ማግኘት የግድ የሚል በመሆኑ ኢትዮጵያ በቀጣናዋ ካሉ አገራት እና “ኃያላን” ነን ከሚሉ አገራትና ቡድኖች ጋር ሚዛኑን የጠበቀ ወዳጅነትና ግንኙነት (በሁለትዮሽና በባለብዙ) እንዲሁም ትብብር መፍጠር ይጠበቅባታል። ኢትዮጵያ ብቸኛና ዋነኛ የሸቀጦቿ መግቢያና መውጫ በሆነውና በራሷ ቁጥጥርና አስተዳደር ስር ባልሆነው የጅቡቲ ወደብ ላይ ጥገኛ ሆና መቀጠሏ አስተማማኝ አይደለም፤ አግባብም አይሆንም። የተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፍላጎት ባላቸው ኃያላን አገራት መካከል ድንገተኛ ግጭት ቢፈጠርና እየተገለገልንበት ያለው የጅቡቲ ወደብ አገልግሎት ቢቋረጥ በአገሪቷ ላይ ሊደርስ የሚችለውን የህልውና አደጋ መገመት አይከብድም። ቁልፍና ዋና ዋና መሠረታዊ፤ የዜጎችን ሕይወት ለማስቀጠል የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ወደ አገር ውስጥ ማስገባትና ወደ ውጭ አገራት መላክም የማይቻል ይሆናል። ማዳበሪያ፣ ነዳጅ፣ የፋብሪካ ግብዓቶች፣ የምግብ ዘይትና መሰል ሸቀጦች በጣት ለሚቆጠሩ ወራት ወደ አገር ካልገቡ የዜጐች ሕልውና አደጋ ላይ መውደቁ ሳይታለም የተፈታ ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ በአካባቢዋ



34

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ማለትም በቀጣናው፣ በተለይ በቀይ ባሕር ላይ በማንኛውም አካል የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ ከሌሎች አገራት በላይ የሚያሳስባት የህልውናዋ ጉዳይ ነው። ስለዚህም ኢትዮጵያ በቀጣናው ባይተዋር እንዳትሆንና የነቃ ተሳትፎ እንድታደርግ ከብቸኛው የጅቡቲ ወደብ ባለፈ ሌሎች ተጨማሪ አማራጭ የባሕር ዳር መዳረሻዎችን ሠላማዊና የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መንገድ ከጎረቤት አገራት ማግኘቷ በእጅጉ ወሳኝ፣ ለነገ

ይደር የሚይባልና ልዩ ትኩረትና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ መገንዘብ ተገቢ ይሆናል። እንግዲህ ከላይ ከተዘረዘሩት ምክንያቶችና ሌሎች በዚህ ጽሁፍ ባልተዘረዘሩ ምክንያቶች ኢትዮጵያ የምታስተዳድረው የባሕር በር እንዲሁም ወደብ መኖሩ የአገሪቷን ብሎም የቀጣናውን ኢኮኖሚ ከማሳደግና ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግናን ከማጎናጸፍ አንጻር አስፈላጊ ነው። በጥቂቱ የተገለጹት ዓለምአቀፍ ተሞክሮዎችም የሚያሳዩት

የባሕር በርን ከጎረቤት አገራት ሰላማዊና ፍትሃዊ የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ በስምምነት ያገኙ አገራት በርካታ ጠቀሜታዎችን ማግኘት ችለዋል። ነገር ግን የኢትዮጵያ አማራጭ የባሕር በር ወይም የወደብ ፍላጎት ለረዥም ዓመታት አገራዊ አጀንዳ ሳይሆን ቆይቷል። በተለይ ላለፉት ሦስት አሥር ዓመታት የኢትዮጵያን የባሕር በር ፍላጎት ጥያቄን ማንሳት ተገቢና አስፈላጊ እንዳልሆነ እንዲሁም ወዳልተፈለገ ግጭት ሊያመራ እንደሚችል ተደርጎ እንዲወሰድ፣

ኢትዮጵያ ከሁሉም አጎራባች አገራት ጋር በባሕል፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት እንዲሁም በደም የሚተሳሰሩ ዜጐች ያሏትና ከአገራቱ ጋር ከጥንት እስከ አሁን በዘለቀ መቀራረብና መተባበር በሠላም የኖረች አገር ነች። የአገራችን ታሪክ እንደሚያሳየው በአስገዳጅ ሁኔታና አገራዊ ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ በተደረገ ዘመቻ የተስተዋሉ ጥቂት በጣት የሚቆጠሩ ግጭቶች ካልሆኑ በቀር ኢትዮጵያ ከሁሉም ጎረቤቶቿ ጋር ግጭትን በማስወገድ

በሰላምና በወዳጅነት ለዘመናት ዘልቃለች።



35

በዝምታ ተዳፍኖ እንዲቆይና እንዲታለፍ ተደርጓል። የለውጡን መንግሥት ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት ዳግም አገራዊ አጀንዳ ሆኖ እንዲነሳ ተደርጓል። ኢትዮጵያ አማራጭ የባሕር በር ለማግኘት እንዲያስችላት በቀጣናው ለሚገኙ ጎረቤት አገራት ጥያቄዎቿን ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማቅረብ መጀመሯ ይታወቃል። ጥያቄው መነሳቱ ከላይ በተገለጹት አገራዊ፣ ቀጣናዊ እንዲሁም ዓለምአቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎች

አንፃር ትክክልና አግባብነት ያለው ነው። ዋናው ቁልፍ ጉዳይ ጥያቄው የመነሳትና ያለመነሳቱ ሳይሆን ጥያቄው ምላሽ የሚያገኝበት፣ የሚስተናገድበትና የሚተገበርበት ወይም ተፈጻሚ የሚሆንበት መንገድ ነው። በተጨማሪም የባሕር በር ፍላጎቱ በአጭር ጊዜ ባይመለስ እንኳን ቀጣዩ ትውልድ ሊያሳካው ስለሚችል ጥያቄው አሁን መነሳቱ ተገቢ እንዲሆን ያደርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፈው ዓመት



36

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በተዘጋጀ ልዩ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ሰፊና ዝርዝር ማብራሪያ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት ጥያቄ ፍፁም ሠላማዊ በሆነ መልኩና ጎረቤት አገራትን በጋራ ተጠቃሚ በሚያደርግ ሁኔታ መሆኑን አስረድተዋል። ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥና ራሷን ብቻ ሳይሆን አጎራባች አገራትን ጭምር የሚጠቅም፣ ሰላማዊና ትብብርን የሚያጎላ፣ አለመግባባቶች ቢፈጠሩ በድርድርና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንደሚፈታ፣ ጎረቤት አገራት የኢትዮጵያ ፀጋ የሆኑትን እንደ ዓባይ ግድብ፣ ኢትዮጵያ አየር መንገድና ኢትዮ ቴሌኮም ከመሳሰሉ ሀብቶቿ ድርሻ መውሰድ እንደሚችሉ፣ በአካባቢው ሠላምን፣ ደህንነትንና የጋራ ልማትን በማስጠበቅ በጋራ የሚኖር አንድ ማኅበረሰብ ለመገንባት እንደሚረዳ ገልፀዋል። ይህን ተከትሎ በርካታ ዝርዝር ማብራሪያዎች፣ ገለፃዎችና መልዕክቶች በተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ መገናኛ ብዙኃን በመንግሥትና በዘርፉ ዕውቀት ባካባቱ ባለሙያዎች ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በተደጋጋሚ ገለፃ ተደርጓል።

የኢትዮጵያን አማራጭ የባሕር በር ፍላጎት ጥያቄ ማቅረብን ተከትሎ ምላሽ ከሰጡት መካከል የሶማሌላንድ ራስ ገዝ አንዷ ስትሆን እ.አ.አ 2014 (Jan, 01, 2014) አዲስ አበባ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር የመግባቢያ ሰነድ (Memorandum of Understanding) ፈርማለች። ይህን ተከትሎም አገራት የተለያዩ መግለጫዎችን ሲሰጡ ይስተዋሉ ነበር። በተለይ ጎረቤት አገር ሶማሊያ የአገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነቴ ተሸርሽሯል በማለት አፍራሽና የሁለቱን አገራት ዲፕሎማሲ በሚጎዳ መልኩ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች። ይህ ሊሆን የቻለው የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ አስፈላጊነትና ለቀጣናው ሊያበረክት የሚችለውን ሁለንተናዊ ጠቀሜታ በአግባቡ ካለመረዳት፣ የመግባቢያ ስምምነቱን ይዘት በሚገባ ባለመገንዘብ፣ ዓለምአቀፍ የባሕር ሕጎችና ተሞክሮዎችን በአግባቡ ካለመረዳት፣ ጉዳዩን አገራዊ አጀንዳ በማድረግ ለውስጣዊ የፖለቲካ ችግሮች ሽፋን ለማዋል ካለ ፍላጎት፣ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት፣ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ያለውን የቆየ ታሪካዊ ግንኙነትና ትስስር ባለመገንዘብና መሰል ምክንያቶች የመነጨ እንደሆነ ይገመታል።



37

“ኢትዮጵያ ከሁሉም አጎራባች አገራት ጋር በባሕል፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት እንዲሁም በደም የሚተሳሰሩ ዜጐች ያሏትና ከአገራቱ ጋር ከጥንት እስከ አሁን በዘለቀ መቀራረብና መተባበር በሠላም የኖረች አገር ነች። የአገራችን ታሪክ እንደሚያሳየው በአስገዳጅ ሁኔታና አገራዊ ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ በተደረገ ዘመቻ የተስተዋሉ ጥቂት በጣት የሚቆጠሩ ግጭቶች ካልሆኑ በቀር ኢትዮጵያ ከሁሉም ጎረቤቶቿ ጋር ግጭትን በማስወገድ በሰላምና በወዳጅነት ለዘመናት ዘልቃለች።” በታሪኳ በጎረቤት አገራት ላይ በኃይል ወይም በጉልበት ወረራ ያካሄደችበት ጊዜ የለም። ሊወራት የመጣን የውጭ ጠላት የመመከትና ሉዓላዊነቷን የማስጠበቅ ካልሆነ በቀር። በመሆኑም በኢትዮጵያና በቀጣናው በሚገኙ አገራት መካከል ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶችና ትስስሮች በተቻለ መጠን ሚዛናቸውን በጠበቀ መልኩ ለበርካታ ዘመናት ቀጥለዋል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከሶማሊያ ጋር ያለው ግንኙነት በተለይ ኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ኃይል ወደ ሶማሊያ ግዛቶች በመላክ ሽብርተኝነትን በመዋጋትና በመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ

አበርክታለች። የአገሪቷ መንግሥት እንደ መንግሥት ሆኖ እንዲቆም ኢትዮጵያ ያበረከተቻቸው አስተዋፅኦና ውለታ እጅግ ብዙ ነው። የመከላከያ ሠራዊታችን ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ በአገሪቷ ሠላም በማስጠበቅና የአገሪቷን ሕልውና አደጋ ላይ ከሚጥሉ አሸባሪ ኃይሎች ታድጓል። ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ብቻ ሳይሆን በቀጣናው፣ በአህጉሩ እንዲሁም በዓለምአቀፍ ደረጃ ሠላም አስከባሪ ሠራዊቷን በማሰማራት ለዓለም ሠላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተች፣ እያበረከተች ያለች አገር ናት። በአሁኑ ጊዜ ከሶማሊያ በተጨማሪ በደቡብ ሱዳን፣ በመካከለኛው አፍሪካ፣ በጊኒ፣ በሱዳን የሠላም አስከባሪ ሠራዊት በማሰማራት የማይተካ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች። ከዚህ መረዳት የሚገባው ወይም ጥያቄ የሚያጭረው ጉዳይ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሠላም ለማስፈን አይተኬ ሚና እየተጫወተች በሌላ በኩል የባሕር በር ፍላጎቷን ለማሳካት ሠላማዊ ባልሆነ መንገድ እንዴት ልትንቀሳቀስ ትችላለች? የኃይል አማራጭ የመጠቀም ፍላጎት የላትም፤ ታሪክም ይህንኑ ነው የሚያሳየው። ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት ቅድሚያ የሚሰጥ የውጭ ግንኙነት

ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ የአፍሪካ ቀንድ ሠላምና ደህንነት አስተማማኝ እንዲሆን ትጉህ ተሳትፎ በማድረግ እንደምትገኝ የአደባባይ ምስጢር ሆኖ ሳለ ይህን እውነታ ወደ ጎን በመተው ያልተፈለገ ውዥንብር መፍጠር ተገቢ አይደለም፤ መፍትሄም አያመጣም። ከላይ ከተዘረዘሩት ነጥቦች በመነሳት በጥቅሉ ኢትዮጵያ ነባራዊ አገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለምአቀፍ ሁኔታዎችን፣ የዕድገትና የልማት ፍላጎት እንዲሁም መጪውን ትውልድ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የባሕር በር ፍላጎቷ በሠላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ በመንቀሳቀስ ላይ ትገኛለች። ይሁንና የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ በአንድ ጀንበር ምላሽ የሚያገኝ አይደለም፤ ከባድ ይሆናል ተብሎ ሊታሰብ ይችላል ነገር ግን የማይቻል አይደለም። በጎረቤት አገራት መካከልና በቀጣናው የሚስተዋሉ ነባራዊና በፍጥነት የሚቀያየረው የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ውጥረቶች የባሕር በር ስምምነቶችን በሚፈለገው ፍጥነት ተግባራዊ እንዳይሆኑ ሊያደርጉ ይችላሉ። ስለዚህ ስኬቱን ለማምጣት መንግሥት የጀመረውን ሠላማዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።



38

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ከጎረቤት አገራት ጋር የሚደረጉ ድርድሮች በዓለምአቀፍ ሕግና ፖለቲካ እንዲሁም በሌሎች ውስብስብ ጉዳዮች ላይ የተመሰረተ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። የአገሪቷን የመደራደርና ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም በሚገባ ማጎልበት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ በረዥም ዓመታት ያካበተቻቸውና ያከማቸቻቸውን ውስጣዊ አቅሞች በተለይ ለስላሳ/ ገር ኃይሏን (soft power) በመጠቀም በዲፕሎማሲው ረገድ በተለይ ከጎረቤት አገራት ጋር ያለውን ሁለንተናዊ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር

ይጠበቅባታል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ዓለም እያለፈችባቸው ያሉትን ዘርፈ ብዙ፣ ውስብስብ፣ አስቸጋሪ፣ በፍጥነት ተለዋዋጭና ኢ-ተገማች ሁኔታዎችን በመቋቋም በቀጣናው ሠላም፣ መረጋጋት፣ አንድነትና የጋራ ብልፅግና እንዲመጣ የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ መቀጠል ይጠበቃል። አፍሪካዊ ችግሮች በአፍሪካዊያን እንዲፈቱና የአፍሪካ ኅብረት ጥንካሬና ተሰሚነት እንዲጎላ ከአባል አገራት ጋር የበለጠ በመቀራረብ መስራት በዚህም



39

የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤዎች የበለጠ እንዲገኑ በማድረግ ለባሕር በር ጥያቄና ሌሎች ጉዳዮቿ መፍትሄ እንድታገኝ የበኩሉን አዎንታዊ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል። ኢትዮጵያ ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅሟን በሚያስጠብቅ፣ በጀመረችው የሰጥቶ መቀበል መርህ፣ የጋራ ተጠቃሚነትና ብልፅግናን በቀጣናው በሚያረጋግጥ መልኩ የባሕር በር የማግኘት ጥረቷን አጠናክራ መቀጠል ይኖርበታል። የኢትዮጵያን አማራጭ የባሕር በር ፍላጐት የአገሪቱን ብሔራዊ

ጥቅም በሚያረጋግጥና በተፈለገው አግባብ እንዲሳካ ውጤታማ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማድረግ ተጽዕኖ መፍጠር ይገባል። ነገር ግን የውጭ ግንኙነት ዲፕሎማሲው በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማና የተሳካ ተጽዕኖ መፍጠር እንዲችል የውስጣዊ አገራዊ ሠላም፣ አንድነትና ጥንካሬ የግድ ነው። ውስጣዊ አንድነትና ጥንካሬ ለውጭ ግንኙነት ዲፕሎማሲያችን ትልቅ አቅም የሚፈጥርና አጋዥ ኃይል ነው። ስለዚህ ብሔርን ጎሳን ሃይማኖትን ወ.ዘ.ተ መሠረት የሚያደርጉ ግጭቶች፣ ጽንፈኝነት ወይንም ጫፍ የረገጠ አስተሳሰብ፣ የትናንት እስረኛ መሆንና ወደፊት አለማየት፣ ነጠላ ትርክት፣ ያልተገደበ ጥቅምና ክብር መፈለግ፣ በአገር ህልውና መደራደር፣ በተቋምና በመርህ አለመመራት፣ የፖለቲካ ገበያና የጥቅም ትስስር፣ የቁርጠኝነትና ጽናት ባሕል አለመዳበር፣ ለሕግና መርህ ተገዢ አለመሆን፣ ሌብነትና ሙስና እንዲሁም ብልሹ አሰራሮች፣ ያልዳበረ የዴሞክራሲ ባሕል፣ የውጭ ጣልቃ ገቦች ሰለባ መሆን አገራዊ አንድነትን፣ ውስጣዊ ጥንካሬና አቅምን (National Unity & Strength) የሚሸረሽሩ፣ የአገር ሉዓላዊነትን፣ ብሔራዊ ጥቅምና አገራዊ ገፅታን የሚጎዱ

ተግባራትና ልማዶችን ማስወገድ ያስፈልጋል። የእነዚህ ችግሮች መፈታት በአገሪቷ ሠላም እንዲሰፍን፣ የተረጋጋችና ውስጣዊ አቅሟ እንዲጎለብት፣ ጥንካሬና አንድነት እንድትፈጥር ወሳኝ ሲሆኑ ይህ ደግሞ የውጭ ግንኙነት ዲፕሎማሲ የሚጠበቀውንና የሚፈለገውን ተጽዕኖ በቀላሉ እንዲያመጣና ብሔራዊ ጥቅሟ እንዲረጋገጥ ያስችላል። መንግሥት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ዕቅድ ነድፎ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል። በተለይ የፖለቲካ ሪፎርም በማድረግ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት አካታችና ሁሉንም የአገሪቷን ዜጎች አሳታፊ አድርጓል በሚባል ደረጃ በመንቀሳቀስ ላይ ነው። አካታች ፖለቲካን ለመፍጠር አገራዊ ፓርቲ ማቋቋም መቻሉ፣ በመደመር ጽንሰ ሀሳብ የሚመራ የእርቅ፣ የይቅርታ፣ የመግባባትና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጎለብቱ ሥራዎች መከናወናቸው፣ ስብራትን መጠገን፣ መሻገር፣ ለቀጣዩ ትውልድ የሚጨነቅና የሚያስብ የሚሉ ሃሳቦች በሥራ ላይ መዋላቸው፣ በተለያዩ ጊዜያት የእስረኞች በምሕረት መፈታት፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመንግሥት የሥልጣን እርከኖች ተመድበው ተሳትፎ



40

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ማድረጋቸው፣ የተለያዩ ሃሳቦች መስተናገዳቸውን፣ እንዲሁም ይህም ብቻ አይደለም፤ ቤተ እምነቶችን ማስታረቅ፣ ከኤርትራ ጋር ሰላም ለመፍጠር የተደረገው ከፍተኛ ጥረትና ውጤቱ (የኖቤል ሽልማት)፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ነጻና ገለልተኛ እንዲሆኑ መደረጉ፣ አገራዊ አሰባሰቢ ገዢ ትርክት እንዲፈጠር እየተደረገ ያለው ጥረት፣ የሽግግር ፍትሕና አገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋምና ወደ ትግበራ መገባቱ ወ.ዘ.ተ መጥቀስ ይቻላል። ከፖለቲካ ሪፎርሙና ምህዳሩን ከማስፋት ጋር በተያያዘ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር ቁልፍ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ በጋራ የመሥራት ባሕልን ማዳበርና ማጠናከር ለአገሪቷ የውስጥ ጥንካሬና አንድነት የበለጠ አቅም መፍጠሩ አይቀርም። የፖለቲካ ፓርቲዎች የሃሳብ፣ የአመለካከትና የፖለቲካ አጀንዳ ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ የአገሪቷን ሉዓላዊነት፣ የሕዝብ ደኅንነትና ብሔራዊ ጥቅምን ለሚመለከቱ አገራዊ ጉዳዮች ልዩ ትኩረት በመስጠት ወደ አንድ የጋራ አቋም መምጣት እጅግ ጠቃሚ ይሆናል። የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄና ፍላጎት የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ፍላጎትና መሻት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ጉዳይ ሲሆን የተፎካካሪ ፓርቲዎች አቋምም ከዚህ የተለየ

ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም። በመሆኑም የአገሪቷን በሠላማዊ አማራጭ የባሕር በር ፍላጐት እንዲሳካ ለሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ጠቀሜታ ይኖረዋል። ከለውጡ በኋላ ላለፉት ዓመታት አገራዊ የውስጥ አንድነትን የሚያጠናክሩ፣ ሠላምና የተረጋጋ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተግባራት ተከናውነዋል በመከናወን ላይም ናቸው፤ ዋና ዋናዎቹ የገበታ ፕሮጀክቶች (ገበታ ለአገር፣ ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለትውልድ) ያስገኟቸው ውጤቶች፣ ከፍተኛ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉ፣ በግብርና ዘርፍ ተዘርዝረው የማያልቁ በርካታ ሥራዎች ተሠርተው ተጨባጭ ውጤት ማምጣታቸው (የሌማት ትሩፋት፣ የከተማ ግብርና፣ የስንዴ ልማት፣ የሩዝ፣ የወተትና ማር ምርቶች፤ የአሳማ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች… ወዘተ)፣ የወጪ ንግድ መጨመር፣ በምስራቅ አፍሪካ ትልቁን GDP መያዝ መቻሉና ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ መቻሉ፣ ውጤታማ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችና ትግበራቸው፣ አገራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርምና ያመጣቸው

ውጤቶች፣ ተቋማት ግንባታ ላይ የተሰሩ ስራዎች፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርና ያመጣቸው ውጤቶች፣ በቱሪዝም ዘርፍ የተሰሩ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች፣ አገራዊ ፕሮጀክቶች እንደ ዓባይ ግድብ፣ ድልድይ፣ ወዘተ፣ የኮሪደር ልማት፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች መጠናከር፣ የወንዝ ዳር ልማትና የከተሞች ውበት ጽዳትና ሌሎች በርካታ ተግባራትን አብነት መጥቀስ ይቻላል። በማኅበራዊ ልማትም የአቅመ ደካሞችን ቤቶች ማደስና አዲስ መገንባት፣ የተማሪዎች ምገባ፣ ለአቅመ ደካሞች የከተማ መመገቢያ ማዕከላት መቋቋም፣ የአብርሆት ቤተ መፅሐፍት፣ ለታዳጊ ሕጻናትና ወጣቶች መዝናኛና መጫወቻ ቦታዎች ግንባታ፣ ለዓይነ ስውራን የተገነባው ማዕከል፣ የመደመር መጽሃፍ ሽያጭ ገቢን ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ማዋል፣ በክልሎች የተገነቡ የሕዝብ ዳቦ መጋገሪያ ፋብሪካዎችና ሌሎችም። እንግዲህ ከላይ በከፊልና ጠቅላል ባለ መልኩ የተጠቀሱት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተግባራት ሁለንተዊ ብልፅግናን ለመጎናፀፍ፣ ብሔራዊ አንድነትን፣ ሠላማዊና የተረጋጋ ሁኔታን በመፍጠር ላልተጠናቀቀው አገረ መንግሥት ግንባታና ጠንካራ ወይም አይበገሬ ውስጣዊ አቅም ፈጠራ



41

ለማምጣት እንደሚያስችሉ ይታመናል። እነዚህ ሁሉ ተደምረው አገራዊ አቅም በመሆን የውጭ ግንኙነት ዲፕሎማሲ ሥራዎቻችን ላይ የበኩላቸውን ሚና ይጫወታሉ። ደካማ አገራዊ አቅምን፣ ውስብስብ ውስጣዊ አገራዊ ችግሮችና ያለፈ ታሪክን መሰረት በማድረግ በቀላሉ ተጽዕኖ መፍጠር ከባድ መሆኑ የታወቀ በመሆኑ ከላይ በጥቂቱ የተጠቀሱት ጉዳዮችን አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሁለተኛዋ ትልቅ የሕዝብ ብዛት ያላትና በርካታ ተፈጥሯዊና ማኅበራዊ እምቅ ጥሪትና አቅሞች ያሏት መሆኗ ይታወቃል። እነዚህን ፀጋዎች በአግባቡ ማወቅና በፍትሃዊነት ማስተዳደርና መጠቀም ከተቻለ በቀላሉ ወደ ባለፀጋነት መቀየር እንዲሁም አገሪቷን ከድህነት ማላቀቅና ለቀጣናውና ለመላው ዓለም ሊጠቅም የሚችል ሀብት ማፍራት ይቻላል። ኢትዮጵያ ያላት በርካታ ገር ኃይል (Soft Power) ዲፕሎማሲያዊ ተጽዕኖ ለመፍጠር ምቹ ሁኔታን ይፈጥርለታል። የሕዝቦቿ ማኅበራዊ ትስስር ደርዝ፣ የቀጣናው ስትራቴጂያዊ አስተባባሪ መሆኗ፣ ብዝሃ ባሕል ቋንቋና ሃይማኖት ያሏት መሆኗ፣ ፈጥኖ ለማደግና ለመለወጥ ፍላጎት ያለው እንዲሁም አስቻይ

መሪነትና ስትራቴጂ ትርክት መኖሩ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያለው አቋምና ቁርጠኝነት እንዲሁም እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች፣ ውስጣዊም ይሁን ውጫዊ ግጭቶችን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረገው ጥረት እንደ አስቻይ ምቹ ሁኔታ የሚጠቀስ ነው። በዓለምአቀፍ ተቋማት ውስጥ ያላት ተሳትፎና ተደማጭት (በተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ፣ የካሪቢያን እና የፓስፊክ አገራት እንዲሁም የአውሮፓ ኅብረት ፓርላሜንታዊ ምክር ቤት /ACP- AU፣ ፓን አፍሪካን ፓርላመንት፣ አፍሪካ ኅብረት እና ሌሎች)፣ ድንበር ተሻጋሪ ሃብቶችን በሠላማዊ መንገድ ለመጠቀም የሚደረጉ ድርድሮችና አገራዊ ሀብትን ማካፈል (ኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት መደረጉ)፣ ለጎረቤት አገራት የሚሰጡ ትምህርት ዕድሎች፣ ለስደተኞች በሯን ክፍት በማድረግ ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጓም ይጠቀሳል። ከዓለምአቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ያለው መልካም ግንኙነት፣ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ያለ የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ ዕድገት ላይ ትኩረት መደረጉ፣ ለቁልፍ መሰረተ ልማቶች የተሰጠ ትኩረትና ሌሎችንም በመጠቀም ራስን ከመቻል አልፎ ለሌሎች አገራት በመትረፍ ከዕርዳታ ተቀባይነት

ወደ ሰጪነት በመቀየር እና የንግድ የበላይነትን በማረጋገጥ በቀጣናው እንዲሁም በዓለምአቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪነት አቅሟን በመጨመር አማራጭ የባሕር በር ጥያቄዋን የበለጠ ቀላልና በፈጠነ ዘዴ እውን ማድረግ ትችላለች። በመጨረሻም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚገዳደሩ፣ ብሔራዊ ጥቅሟን በእጅጉ የሚጎዱ፣ አገራዊ አንድነትና ሠላምን የሚያውኩና አገራዊ ጥቅምን የሚፈታተኑ ውስጣዊም ይሁን ውጫዊ አካላትን ለማስቆም፣ ለመከላከልና አስፈላጊ የሕግ ማስከበር ሥራዎችን ፀጥታና ሕግ በሚያስከብሩ ተቋማቷ በኩል አስፈላጊ እርምጃዎችን መውሰድ ተገቢ ይሆናል። በዚህ ፅሁፍ በዝርዝር የተመላከቱት ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ኢትዮጵያ ጠንካራ ሠራዊት በመገንባት በቀጣናው ኃያል መሆን እንደሚኖርባት አስገዳጅ ሁኔታን እንደሚፈጥር መገንዘቡ ተገቢ ነው። ለዚህም ከፍተኛ ተቋማዊ ሪፎርም ያደረጉ፣ ብቁና አስተማማኝ እንዲሁም ዘመኑን የዋጁ የፀጥታና የደህንነት ተቋማት ግንባታን አገሪቷ የጀመረችውን ጥረት ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ አጠናክራ መቀጠል ይኖርባታል።



42

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ኢኮኖሚ

የማክሮ ኢኮኖሚ



43

መንደርደሪያ ኢትዮጵያ በኋላ ታሪኳ ጦርነትን ጨምሮ ያለፈችባቸው ውስብስብ የፖለቲካ ሂደቶችና የአገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ዛሬ ላይ ለያዘችው መልከ ብዙ ቁመናዋ አበርክቶው ከፍተኛ ነው። ይህንን የፖለቲካ ሃዲድ የተከተለው የአገሪቱ ኢኮኖሚም በተዋረሱ በርካታ ሳንካዎች በመታጀብ ብርቱና አድካሚ ጉዞን እንዲያዘግም አስገድዷል። በወቅቱ መሰራት ኖሮባቸው ሳይሰሩ ያደሩ ውዝፍ የቤት ሥራዎች አንደ አገር ልንደርስ ከሚገባን ቦታ በእጅጉ ከልክለውናል። በተለይም የእልፍ የተፈጥሮ ኃብትና የወጣት ኃይል ባለቤት ሆነን ድኅነትን ማሸነፍ አለመቻላችን አግራሞትን ይጭራል። ለዚህ በርካታ መነሻዎች ቢኖሩም ገቢራዊ ያደረግናቸው የዕድገት

በበረከት ሲሳይ

ማሻሻያው ቀጣይ ጉዞ



44

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ሞዴሎችና ውጥኖችን የመፈጸም አቅማችን አናሳ መሆን የራሱ አስተዋጽኦ አድርጓል። በተጓዳኝም፤ ቀድመው ከበለጸጉ አገራት የዕድገት መንገዶች ለራስ በሚመች አኳኋን ለመቀመር የሄድንበት መንገድም በስኬት የታጀበ አለመሆኑ ሌላው ስብራት ነው። ሌላው ቢቀር ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ አንስቶ ለአብነትም፤ የነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝና የእርሱን ፍኖት የተከተሉ የዘርፉ ባለሙያዎችን ሂስ አዘል ምክረ ሐሳቦች ቸል ያልንባቸው የታሪክ እጥፋቶችም የሚያስቆጩ ናቸው። የእነዚህ ድርብርብና የተንከባለሉ ፈተናዎች ዳፋ ዛሬ ለገባንበት የኢኮኖሚ ቅርቃር ምክንያት ከመሆን በዘለለ ለመጪው ትውልድ እንዳይተርፉ የዛሬን እልህ አስጨራሽ ጥረታችንን መገበር አስፈልጓል። እንዲያም ሆኖ፤ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት መረጃ እንደሚያሳየው ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በኢትዮጵያ በአንጻራዊነት የተሻለ የኢኮኖሚ ዕድገት ተመዝግቧል። ያም ሆኖ በተለይም በግብርናው ዘርፍ ምርታማነትን በመጨመር፣ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን በማነቃቃትና በመሰል ዘርፎች የተሻለ አፈጻጸም በማስመዝገብ ያልተቋረጠ ዕድገት ማስመዝገብ ተችሏል። ይሁንና በተለይም

ከለውጡ መንግሥት ዋዜማ አንስቶ የነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት የተነቃቃው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል። በዚህ አውድ ውስጥ ያለፈው የለውጡ መንግሥት፤ በወቅቱ የተረከበው የኢኮኖሚ ሁኔታ በጥቅሉ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ይስተዋልበት እንደነበር ገምግሞታል። ዕድገቱ በመንግሥት ከፍተኛ ወጪ በተስፋፋ የመሠረተ-ልማት አማካይነት የተመዘገበ በመሆኑ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት የፈጠረ፣ አስተማማኝ የሥራ ዕድል በተፈለገው መጠን በቋሚነት መፍጠር የተሳነው፣ ከፍተኛ የብድር ጫና የፈጠረ መሆኑን በውስንነት አንስቷል። እነዚህን መዋቅራዊ ችግሮች በዘላቂነት በመፍታት በአገሪቱ ቀጣይነትና ጥራት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት እውን ለማድረግ በማለም በ2011 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ምዕራፍ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ወደ ሥራ አስገብቷል። የኢኮኖሚ ማሻሻያው በተለይም የማክሮ ኢኮኖሚ የፋይናንስ መረጋጋትን ለማረጋገጥ በዋናነት ጥብቅ የፊስካል ፖሊሲ ገቢራዊ አድርጓል። በዚህም በዋና ዋና ዘርፎች ላይ አበረታች ውጤቶች ቢገኙም ቀሪ በርካታ ሥራዎች ሊሰሩ እንደሚገባ ተመላክቷል። አገሪቱ

ያለባትን የኢኮኖሚ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ደግሞ መንግሥት ከሰሞኑ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አድርጓል። የፖሊሲ ትግበራው፤ ማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትንና ዘላቂነትን የሚደግፍ ዘመናዊና ጤናማ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማዕቀፍ መመሥረት፤ ፈጠራን የሚያበረታታ ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ ዘርፍ ከባቢና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ፣ የአገር ውስጥ ምርትና ምርታማነት አቅምን ማጠናከርና ጥራት ያለው አገልግሎት በብቃት ለማቅረብ የመንግሥትን አቅም ማሳደግ የሚሉ ጥቅል ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደርጋል። የአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግብይት ተመን



45

በገበያ ሥርዓት እንዲወሰንም አድርጓል። የፖሊሲ እርምጃዎቹ ከአጠቃላይ አገራዊ የረጅምና የመካከለኛ ዘመን የልማት ዕቅዶች ጋር ተጣጥመው የሚከናወኑ በመሆናቸው በመጀመሪያው የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርኃ- ግብር የተስተዋሉ ቀሪ ሥራዎችን በምልዓት በመሥራት የዕዳ ክምችትን በማቃለል፣ የወጪ ገቢ ንግድ ሚዛን በመጠበቅ፣ የበጀት ጉድለትን በመሙላት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን በማስፋት፣ የዋጋ ንረትን በማቃለል ትልቅ እመርታ እንደሚኖራቸው ታምኗል። በዚህም በሚቀጥሉት አራት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአማካይ በ8 በመቶ ያህል

እንደሚያድግ፤ የዋጋ ንረት ወደ 10 በመቶ ዝቅ እንደሚል፤ የታክስ ገቢ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ 11 በመቶ እንደሚደርስ፤ የመንግሥት ዕዳ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ወደ 35 በመቶ ዝቅ እንደሚል፤ የወጪና የገቢ ንግድ ዋጋ ወደ 20 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያድግ፤ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ወደ 8 ቢሊዮን ዶላር ከፍ እንደሚል፤ ዓለም አቀፍ የመጠባበቂያ ክምችት ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል። ያም ሆኖ፤ ይህ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ያለምንም ተጽዕኖ ገቢራዊ እንደማይሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

(ዶ/ር)ን ጨምሮ በርካታ የመስኩ ምሁራን ተናግረዋል። በተለይም በመጀመሪያዎቹ የትግበራ ጊዜያት ላይ ተጽዕኖው ሊበረታ እንደሚችልና ይህም በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የዚህ ገፈት ቀማሽ እንደሚሆኑ አይቀሬ በሚመስል አኳኋን አስቀምጠውታል። እነዚህ ሥጋቶች ምንድን ናቸው? እንዴትስ ይፈታሉ? የሚሉ ወሳኝ ተጠየቆች ላይ በመንተራስ ጉዳዩን በዚህ ጽሑፍ ለመዳሰስ ተሞክሯል። ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ሥርዓትና የአገራት ተሞክሮ ምንም እንኳን የማክሮ ኢኮኖሚ



46

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ማሻሻያው በርካታ ጉዳዮችን በውስጡ የያዘ ቢሆንም ዋነኛ ማዕከሉ ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረጓ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ታዲያ ለዚህ ሥርዓት ኢትዮጵያ ቀዳሚ አገር እንዳልሆነች ሁሉ ይህንን ሥርዓት ተግባራዊ ያደረጉ የቀደሙ አገራት ተሞክሮ መዳሰስ ለመማሪያነት ሳይጠቅም አይቀርም። እንደሚታወቀው በታሪክ የበርካታ አገራት የመገበያያ ገንዘብ የንግድ መለኪያ ሆኖ ያገለገለው ወርቅ ነበር። ኋላ ላይም በተለይ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ ወርቅ ከዶላር ጋር እየተተመነ ዶላር ዓለም አቀፍ የንግድ መፈጸሚያ ዋነኛ ገንዘብ የሆነበት አሰራር ተበጅቶ ነበር። ይህ አሰራር በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም አገራት ብድር መክፈል ሲያዳግታቸውና የነዳጅ ዋጋ መጨመርን ተከትሎ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጠጣር ከ1970 ጀምሮ እንዲያከትም ሆኗል። ይህ ከወርቅ ጋር በተያያዘ ሥራ ላይ ይውል የነበረው የመገበያያ ገንዘብ ዋነኛ መለያው መንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲው ማዕከላዊ ሥፍራን የያዘበት ነበር። ይህም በተለይ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1930ዎቹ የዓለም የኢኮኖሚ ቀውስ በተፈጠረበት ወቅት

የእንግሊዙ የኢኮኖሚ ጠበብት ጆን ማይናርድ ኬኔይዥያ (ኬኔይዥያኒዝም) ያቀረበው የፖሊሲ እርምጃ አይነት መሆኑ ነው። በኬኔይዥያኒዝም ኅልዮት መሰረት የመንግሥት ወጪ መጨመር አጠቃላይ የኢኮኖሚውን ውጤት የተሻለ ያደርገዋል የሚል ነበር። እንዲያም ሆኖ የመገበያያ ገንዘብ በወርቅ መለካት ማቆም አጠቃላይ ኢኮኖሚውን እንዴት ነው መቆጣጠር የሚቻለው በሚለው ጉዳይ ላይ ጥያቄ ማስነሳቱን ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚገልጹት። ይህን ተከትሎ አገራት በተለይም የገበያ ሥልት የኢኮኖሚው ማዕከል እንዲሁም የመንግሥትን ኃብት ወደ ግል ማዞር አማራጭ መፍትሄ አድርገው መውሰድ ጀመሩ። እነዚህም በአሁኑ ጊዜ በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሬ ሥርዓትን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮችን የሚያካትተው የነጻ ገበያ የኢኮኖሚ ሥርዓት መሰረታዊያን ተብለው የሚወሰዱ መሆናቸውን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት። አገራት የመገበያያ ገንዘባቸው ዋጋ ዋነኛ የንግድ አጋር ከሆኗቸው አገራት ጋር በመንግሥት እንዲተመን (fixed curren- cies) አንዳንዶች ደግሞ በገበያ ላይ የተመሰረተ (free floating)

አንዳንዶች ደግሞ ሁለቱንም ለማቀላቀል (hybrid) የሞከሩ ስለመኖራቸውም መረጃዎች ያትታሉ። የመስኩ ምሁራን በተለይም በተቃራኒ በቆሙ በሁለቱ መንገዶች ላይ የተለያዩ አመለካከቶችን ሲያራምዱ ይታያሉ። ለአብነትም ውስን የውጭ ምንዛሬ ተመን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና የውጭ ንግድ ሥራን አያበረታታም ሲሉ፤ በአንጻሩ በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሬ ተመን ለእነዚህ ለሁለቱ መፍትሄ ነው ይላሉ። በዚህ መነሻነት በተለይም ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ለአብነት በቻይና በተወሰነ መልኩ ገቢራዊ ከሆነ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጠጣር ከ2005 ጀምሮ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አዎንታዊ ለውጦች ማምጣት ችሏል። በተለይም የቻይና መገበያያ ገንዘብ ከአገሪቱ ዋነኛ የንግድ አጋር አካላት ጋር ያለውን ዋጋ ዝቅ በማድረግ አገራቱ ከቻይና ጋር ያላቸው የንግድ ግንኙነት እንዲጠናከር አድርጓል። ያም ብቻ ሳይሆን የቻይና የውጭ ንግድ ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ እንዲሆን በማድረግ አገራት የቻይና ምርት ምርጫቸው እንዲሆን አድርጓል። ይህንን በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሬ ተመን ቻይና አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ላላት መጠነ ሰፊ የንግድ ልውውጥና



47

የአገሪቱን ኢኮኖሚ በፍጥነት እንዲያድግ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። ያም ብቻ ሳይሆን ቻይና በዚህ የገበያ መር የገንዘብ ተመን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሏትን ሌሎች ተጓዳኝ ሥራዎች በአግባቡ መስራቷ ከሥርዓቱ ተጠቃሚ እንድትሆን አድርጓታል። በሌላ በኩል በተለይም በማደግ ላይ ያሉ የአፍሪካና ሌሎች የእስያ አገራት ይህንን ሥርዓት ገበያ አድርገው ያልተሳካላቸውም አሉ። በዚህ ረገድ በአፍሪካ ጋና እና ዚምባብዌ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመንን በአግባቡ ገቢራዊ ባለማድረጋቸው እስከ ቅርብ ጊዜ የዘለቁ ችግሮችን ለማስተናገድ ተዳርገዋል። ምሁራኑ እንደሚያስቀምጡት በተለይም በአፍሪካ የተከሰቱት ችግሮች ዋነኛ ማጠንጠኛቸው አገራቱ ያሉበት የኢኮኖሚ ችግር መሆኑን ይስማሙበታል። በተለይም የግብርናና የአምራች ዘርፉ ምርታማነት ጠንካራ አለመሆን፣ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ትክክለኛ የገንዘብ ፖሊሲ አውጥቶ አለመተግበርና ከአገራቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ ሁሉን አቀፍና የአገራትን የውስጥ አቅም መጠቀም የሚያስችል አገር በቀል የኢኮኖሚ ልማት ፖሊሲ ተግባራዊ አለማድረግ ገበያ

መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ውጤታማ እንይሆን ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ይላሉ። ጎን ለጎንም አገራቱ ያሉበት አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሁኔታ በተለይም የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ በገበያ ላይ የተመሰረተው የውጭ ምንዛሬ በሚፈለገው መልኩ ውጤት እንዳያመጣ ማድረጉን ያስቀምጣሉ። ሁለቱም አገራት ላይ በተለይም ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ንረት መቆጣጠር አለመቻላቸው ትልቅ አደጋ መደቀኑ ይጠቀሳል። የአምራች ኢንደስትሪ ዘርፋቸው ጠንካራ ካለመሆኑ ጋር በተያያዘ በተለይም ከውጭ የሚገቡ እቃዎች ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየታቸውና ሌሎች ምርትና አገልግሎቶች ላይ የነበረው የዋጋ መናር ኢኮኖሚያቸውን በእጅጉ ፈትኖባቸዋል። ይህም በኋላ ላይ በተለይም ዚምባብዌን ለከፍተኛ የዋጋ ግሽበት መዳረጉ ይታወሳል። ይህ የዋጋ ግሽበት በሌሎች የማክሮ ኢኮኖሚ መሰረታዊያን ላይ የደረሱ አሉታዊ ተጽዕኖዎች ኢኮኖሚያቸውን በእጅጉ እንዲንገዳገድ በር ከፍቷል። ከዚህ ጋር አብሮ የሚነሳው በተለይም በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ላይ ዜጎች ለከፋ ችግር እንዳይዳረጉ ገቢራዊ የነበሩ ድጎማዎች ቀጣይነት አለመኖር

ሌላው ለገጠሟቸው ችግሮች የሚጠቀሱ ምክንያቶች ናቸው። በመሆኑም ገቢራዊ የተደረጉ ገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሬ ተመን ለችግሮች እልባት ከመሆን ይልቅ በአገራቱ የነበሩ የኢኮኖሚ ችግሮች ይበልጥ እንዲስፋፉ ማድረጉን ነው ምሁራኑ የሚያስረዱት። እነዚህ ተሞክሮዎች በቅርቡ ወደዚህ ሥርዓት ለገባችው ኢትዮጵያ ነገሮችን ለማንጸሪያ ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው። የአገራቱን አካሄድ በመንተራስ ኢትዮጵያ ከዚህ በገበያ ላይ ከተመሰረተ የውጭ ምንዛሬ ተመን ጋር በተያያዘ ምን ሊገጥማት ይችላል? የሚለውን እንቃኛለን። ከፊታችን ያለውን ድልድይ እንዴት እንሻገረው? የማክሮ ኢኮኖሚ ገቢራዊ መደረጉን ተከትሎ በኢትዮጵያ ስለሚገኘው ጥቅምና በአንጻሩ ስለሚኖረው አሉታዊ ተጽዕኖ በርካታ የመስኩ ባለሙያዎች ሥጋታቸውን በስፋት ሲገልጹ ተስተውሏል። በተለይም የአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚስተዋሉበትን ችግሮች ከግምት በማስገባት ሊያስከትላቸው የሚችሉ ተጽዕኖዎች በብዙዎች ዘንድ ሥጋትን ጭሯል። ቀዳሚ ሥፍራውን የሚይዘው ከንግድ ሚዛን ጉድለት ጋር በተያያዘ የዋጋ ንረት በቀዳሚነት ያነሳሉ።



48

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

የአገሪቱ የአምራች ዘርፍ በሚገባው ልክ አለማደጉን ተከትሎ አገሪቱ አሁንም ከውጭ በሚገቡ እቃዎች ላይ ጥገኛ መሆኗን በማንሳት አዲሱ ፖሊሲ ለዋጋ ንረት ተጋላጭ እንደሚያደርጋት፤ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ሥርዓቱ (free floating) ከውጭ የሚገቡ እቃዎች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ስለሚኖረው በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል ተጋላጭ እንደሚያደርገው ይጠቅሳል። ስለዚህም ፍላጎትን ተደራሽ የሚያደርግ በአገር ውስጥ ምርት ላይ የተመሰረተ በቂ አቅርቦት በሌለበት ሁኔታ

ሥርዓቱ ተግባራዊ መደረጉ በዋጋ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖራል የሚል ሥጋትን ጭሯል። ያም ብቻ ሳይሆን አገራዊ ምርት በሚፈለገው ደረጃ ካላደገና ፍላጎቱን ተደራሽ ማድረግ ካልቻለ አሁን ላይ ያለው የውጭ ምንዛሬ ተመን ከዚህ በላይ እንዲጨምር እንዲያውም እንዳይተነበይ በሚያደርግ ደረጃ ሊደርስ እንደሚችል ያላቸውን ሥጋት ይጠቅሳሉ። ይሁንና ምርትና ምርታማነት በማሳደግ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ጠንካራ የገንዘብ ፖሊሲና የወለድ መጠንን በአግባቡ በማስተዳደር ለመምጣት የሚንደረደረውን ችግር ከወዲሁ



49

መግታት እንደሚቻል የመስኩ ባለሙያዎች ምክረ ሃሳባቸውን ይሰጣሉ። በተመሳሳይ ከብር የመግዛት አቅም መዳከም ጋር በተያያዘ በተመሳሳይ የአገልግሎትና የእቃዎች ዋጋ ሊጨምር ስለሚችል ይህም ጫናው ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ። ይህም የኋላ ኋላ የዋጋ ግሽበት በማስከተል አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ በማሳደር የታሰበው ለውጥ ላይመጣ ይችላል የሚል ስጋታቸውን የመስኩ ምሁራን ያስቀምጣሉ። ከዋጋ መጨመር አንጻር ከጅማሮው ምልክቶች መኖራቸው ምናልባት የዚህ ዓመት ዋነኛ ተግዳሮት ሊባል የሚችለው ጉዳይ ይኸው ይመስላል። በእርግጥ መንግሥት ይህንን በተለይም ከዋጋ ንረት ጋር ሊከሰት የሚችለውን አይቀሬ ተግዳሮት ለማቃለል የራሱን እርምጃ እንደሚወስድ አሳውቋል። በተለይም ዝቅተኛ ተከፋይ የሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች የሚደርስባቸውን ተጽዕኖ እንዲቋቋሙ የደመወዝ ማሻሻያ እንደሚደረግ ባሳወቀው መሰረት ከመስከረም 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ አድርጓል። ይህም በተለይ በከተሞች አካባቢ በኪራይ ቤት

የሚኖረው ሠራተኛ ተጋላጭ እንዳይሆን ከለላ የሚሰጥ ነው። ከቤት ኪራይ ጋር በተያያዘ ከፖሊሲው ተግባራዊነት አስቀድሞ መንግሥት አላግባብ የኪራይ ዋጋ ጭማሪን ለመከላከል የሄደበት ርቀትም ሌላው የሚበረታታ ተግባር ነው። በሌላ በኩል በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች በልማታዊ ሴፍቲኔት እንዲታቀፉ በማድረግ ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስ ትኩረት እንደሚደረግ ተገልጿል። ይህም ምንም እንኳን ዜጎች በቂ ገቢ ባይኖራቸውም መንግሥት የመተማመኛ ድጋፍ ማድረጉ ማኅበራዊ ችግርን የሚያቃልል እርምጃ ነው። ከዚህ ጎን ለጎን በነዳጅ፣ በማዳበሪያ እና በምግብ ዘይት ላይ የሚደረገውን ድጎማ ለማስቀጠል መንግሥት ውሳኔ ማሳለፉ በጥቂቱም ቢሆን መታየት የጀመሩትን የዋጋ ጭማሪዎች ለመቋቋም ሁነኛ መፍትሄዎች ናቸው። በነዳጅ ዋጋ ላይ የሚደረገው ድጎማ በበርካታ ዘርፎች ላይ ሊያስከትል የሚችለውን የዋጋ ንረት ከወዲሁ በመግታትና በመቆጣጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ይህም ያለ ትራንስፖርት የሚጓጓዝ ምንም አይነት ሸቀጥ ባለመኖሩና ዋጋውንም የመወሰን ኃይል ስላለው የንግዱ ማኅበረሰብ አላግባብ

ዋጋ እንዳይጨምር ምክንያት ከሚያሳጡ ተግባራት መካከል ተጠቃሽ ነው። ከማዳበሪያ ጋር ተያይዞ የተደረገው ድጎማም የግብርናውን ምርት በመጨመር በኋላም፤ በምርቶች ላይ ሊመጣ የሚችለውን የዋጋ ንረት ለማስቀረት ሁነኛ መፍትሄ ነው። በአጠቃላይ በመንግሥት የሚደረጉት ድጎማዎች ለሁሉም በሚባል ደረጃ እፎይታ የሚሰጡ እርምጃዎች ናቸው። የዋጋ ንረት ከፖሊሲ ትግበራ ጋር በተያያዘ ወዲያውኑ ሊያጋጥም የሚችል አጣዳፊ ችግር ከመሆኑ ጋር በተያያዘ መፍትሄዎቹም በዚያው ልክ ሊፈጥኑ ይገባል። የተለያዩ የአገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው እነዚህን ድጎማዎች የተሻለ አውድ እስከሚፈጠር ድረስ አጠናክሮ ማስቀጠሉ የምርጫ ጉዳይ አለመሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። ከድጎማ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ማንኛውንም አይነት ሕገ-ወጥ ተግባራትን በጥብቅ ዲሲፕሊን በመከላከል ለውጤታማነቱ መትጋትም ሌላው ዋነኛ ጉዳይ ነው። ሌላው በባንኮች እና በትይዩ ገበያ መካከል ያለው ልዩነት መጥበብም በተወሰነ መልኩ መረጋጋት የታየበት ሲሆን በቀጣይ ልዩነቱ ይበልጥ እንዳይሰፋ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። ምንም እንኳን የዋጋ



50

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ንረት ተቀዳሚ ተግዳሮትና ይህንን ተከትሎ የችግሮችን መወሳሰብ ለማስቀረት ዋነኛ ትኩረት ቢሆንም ሌላው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በድምሩ እንዲሁም በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሬ ተመን የታለመለትን ግብ እንዲመታ መሰራት ከሚኖርባቸው በርካታ ሥራዎች መካከል የተወሰኑት እንዲህ ተቃኝተዋል። የጋራ ትብብር የሚጠይቁ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ሰፊ ሀሳብ የያዘ የአገሪቱ ቀጣይ ወሳኝ አቅጣጫ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል። ይህ ማሻሻያ ውጤታማ እንዲሆን በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ እንዲሁም በኅብረተሰቡ የጋራ ትብብር መሰራት ያለባቸው በርካታ ሥራዎች መኖራቸውን መገንዘብ ይገባል። በተለይም መንግሥት ዋነኛ የፖሊሲ አመንጪና አስፈጻሚ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የመሪነት ሚና ሊጫወትባቸው የሚገቡ ዐበይት ጉዳዮች መኖራቸውም የሚሸሸግ አይደለም። መንግሥትም ሆነ የመስኩ ባለሙያዎች ከፖሊሲ ማሻሻያው ጋር በተያያዘ ‘ሊያጋጥሙ የሚችሉ’ ተብለው የተለዩ ችግሮችን ማቃለልም ሆነ በሂደት ማስቀረት የሚቻለው በተወሰኑ ዘርፎች ላይ ትኩረት ማድረግ ሲቻል ነው።

ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲው ተግባራዊነት አስቻይ አውድ በሚፈጥሩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረጉ የሚያጠያይቅ አይደለም። ከታች በጥቂቱ ለመዘርዘር የተሞከሩት በራሳቸው ምሉዕ ያልሆኑ፤ ነገር ግን ፈረንጆቹ እንደሚሉት ልንዘነጋቸው የማንችላቸው ትልልቅ ተግዳሮች (Elephant in the house) በመሆናቸው አስፈላጊው ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል። ነገር ግን እነዚህ ችግሮች እንዴት ይፈቱ፣ ከማን ምን ይጠበቃል የሚሉና ሌሎች ተጠየቆች ይበልጥ ሊታሰብባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ሲሆኑ ችግሮቹን የመፍታት አስፈላጊነትና ሥራው መቼ ይጀመር በሚለው ጉዳይ ልዩነት ይኖራል ተብሎ አይታሰብም። ያም ብቻ ሳይሆን በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ለመረባረብ ‘መቼ’ ለሚለው ጥያቄ ከ’ዛሬ’ ውጪ አማራጭ አለመኖሩንም ልብ ይሏል። ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት ማረጋገጥ በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በአግባቡ ተግባራዊ እንዳይሆንና የታሰበው ለውጥ እንዳይመጣ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በፈተናው ውስጥ ያለው ኢኮኖሚ ይበልጥ እንዲወሳሰብ መደላድል ይፈጥራሉ። በተለይም በማክሮ

ኢኮኖሚ የማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ ዋነኛ ትኩረት ከሚሰጠው ዘርፍ መካከል ምርትን ማስፋትና ተኪ ምርትን የማስፋት ሂደት በእጅጉ ያስተጓጉለዋል። የአገር ውስጥ አምራቾችን በተለየ ሁኔታ የሚያበረታታው ይህ ማሻሻያ እንዲህ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት አምራቾች ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይከውኑ እንቅፋት ይፈጥርባቸዋል። በሌላ በኩል የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብ በዚህም ሂደት የቴክኖሎጂ ሽግግርን እውን ለማድረግ፣ ምርትና ምርታማነት ለመሳብ፣ የሥራ ዕድል የመፍጠር እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል። ለየትኛውም አይነት የምርት እንቀስቃሴ የሰላማዊ አውድ አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ ከመሆኑ አንጻር አሁን ያለው የጸጥታ ችግር ትልቅ እንቅፋት የሚፈጥር በመሆኑ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው። ከዚህ በዘለለ እንዲህ አይነት የግጭት አውዶች ለሕገ- ወጥ ተግባራት መበራከት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስላላቸው ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን በማበራከት በመንግሥት ገቢ አሰባሰብ ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል። በተጨማሪም የማክሮ ኢኮኖሚ



51

ማሻሻያው በተሟላ መልኩ ተግባራዊ እንዳይሆን በማድረግ የተያዙ የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅዶች እንዳይከወኑ ያደርጋል። በዚህ ሳቢያም በጊዜ መፈታት ያለባቸው ችግሮች በይደር እንዲቀመጡና ያልታሰቡ አዳዲስ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ። መልካም አስተዳደር ማስፈን በርካታ የኢኮኖሚ ምሁራን እንደሚስማሙበት በመልካም አስተዳደርና በኢኮኖሚ እድገት መካከል ቀጥተኛ ቁርኝት አለ። የዓለም ባንክ እንደሚያስቀምጠው መልካም አስተዳደር የሚለካው የአንድ አገር የአስተዳደር መርሆን የመተግበር አቅምና በዚህም የኢኮኖሚ እድገት እውን ለማድረግ የሚያስችል አውድ የመፍጠር ብሔራዊ አቅም መሆኑን ያብራራል። መልካም አስተዳደርን ለመለካት ባንኩ ካስቀመጣቸው ስድስት መስፈርቶች መካከል ምናልባት ካለንበት አገራዊ አውድ በመነሳት የመንግሥት የመፈጸም አቅም፣ የምርትና አገልግሎት ጥራት ጉዳይ፣ ሙስናን መከላከል የሚሉት ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸው ሁሉንም የሚያስማማ ይሆናል። የመንግሥት የመፈጸም አቅም በቀጥታ የመንግሥት ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት ውጤታማ ማድረግን ከግምት

ያስገባል። ከዚህ አንጻር መንግሥት በሲቪል ሰርቪስ ዘርፍ እያደረጋቸው የሚገኙ የሪፎርም ሥራዎች ሊጠናከሩ የሚገባ መሆኑን ያስገነዝባል። መንግሥት በተቋማቱ ብቁ የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትና እርስ በርስ ያለው ቅንጅታዊ አሰራርና የመናበብ ሂደትን ለማጠናከር የሚሄድበትን ርቀት ይበልጥ ማጠናከር ይገባል። ጎን ለጎንም በመንግሥትም ይሁን በግል ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶች እና ምርቶች ጥራትን መሰረት እንዲያደርጉ ማስቻል ሌላው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው። ከዚህ ጋር አብሮ ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ የአንድ አገር የመፈጸም አቅም ሊያድግ የሚችለው ሙስናና ብልሹ አሰራርን መቅረፍ ሲቻል ነው። በተለይ ይህንን መሰል ከአሰራር ጋር ተያይዘው የሚነሱ ብልሹ አሰራሮችን መቅረፍ የሚያስችል የዲጂታል ሥርዓት ሊጠናከር ይገባል። በአሁኑ ጊዜ እየተዘወተረ ያለውን በተለያዩ ዘርፎች አገልግሎቶችን በዲጂታል ሥርዓት የማስደገፍ ሂደት ይበልጥ በማስፋት ከወረቀት ንክኪ ነጻ የሆኑ አገልግሎቶችን ማጠናከር ለነገ የማይባል የቤት ሥራ ነው። ይህም በመንግሥት ተቋማት ላይ ያለውን አመኔታ በመጨመር ለዜጎች ለሕግ-ተገዥ



52

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

የመሆን እድልን በመፍጠር ጤናማ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት መሰረት እንደሚጥል ነው የሚታመነው። ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የአገሪቷን የግብርና እና የአምራች ዘርፍ ፍላጎት ተደራሽ ለማድረግ ምንም እንኳን አሁን ላይ ተጨባጭ ለውጥ ቢያስመዘግቡም በርካታ ቀሪ የቤት ሥራዎች ከፊት ለፊት አሉ። በተለይ የግብርናውን ዘርፍ ሜካናይዝድ በማድረግ አገሪቱ ከውጭ የምታስገባቸውን የምግብ ፍላጎቶች በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሄደበት ያለው ርቀት ይበልጥ ሊጠናከር የሚገባው ጉዳይ ነው። በስንዴ እና በሩዝ ምርት እየተመዘገቡ ያሉትን ውጤቶች በሌሎች የግብርና አይነቶችም በመድገም አገሪቱ ምርቶችን ከውጭ በማስገባት ተገቢ ላልሆነ ወጪ የምትዳረግበትን ዕድል ማጥበብ ይገባል። በአንጻሩ፤ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡትን የግብርና ምርቶች በብዛትና በጥራት በማምረት አገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝቷን ማሳደግ ይጠበቅባታል። ማሻሻያው የውጭ ንግድ በእጅጉ የሚያበረታታ መሆኑን ከግምት በማስገባት የዘርፉ ተዋንያን ይህንን እድል ለመጠቀም ዝግጁነቱ እንዲኖራቸው የማድረጉ ሥራም

አብሮ ሊሰራ የሚገባው ጉዳይ ነው። በሌላ በኩል በአምራች ዘርፉ በተመሳሳይ በተለይም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት የሚደረጉ ጥረቶች ይበልጥ ሊጠናከሩ ይገባል። ከውጭ ምንዛሬ ተመን መሻሻል ጋር ተያይዞ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች የዋጋ ጭማሬ እንደሚኖራቸው አያጠራጥርም። በመሆኑም እነዚህን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋና ጥራት የሚተካ ተኪ ምርት አገር ውስጥ ማዘጋጀት ከተቻለ ተጽዕኖዎችን ማቃለል ይቻላል። የአገር ውስጥ ምርት አቅም በሚፈለገው መጠን ባለማደጉ



53

ምክንያት የአገሪቷ የውጭ ንግድ ሚዛን የተሟላ አይደለም። በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት የተኪ ምርቶች ዓመታዊ አፈጻጸም ከ2 ቢሊዮን ዶላር ጥቂት ዘለል ያለ እንደነበር አብነት መጥቀስ ይቻላል። ይህንን አሃዝ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በእጥፍ ማሳደግ ያስፈልጋል። ለዚህም የ”ኢትዮጵያ ታምርት”ን አይነት እንቅስቃሴ በስፋት በማንቀሳቀስ እንዲሁም ለዘርፉ የሚቀርቡ ድጋፎችና ምቹ አውድ የመፍጠር ሥራዎችን በማጎልበት ዘርፉን ማጠናከር ይገባል። የአገራት የአምራች ኢንዱስትሪ ያደገው ለአምራች ዘርፉ የተለያዩ

ከለላዎች (Protectionism) በመስጠት መሆኑን ከግምት በማስገባት አምራቹ ይበልጥ የሚበረታታበትን መንገድ ማፈላለግ ተገቢ ይሆናል። የአገር ውስጥ ምርት የመጠቀም ልምድ ቀስ በቀስ እንዲጎለብት የማድረግ ሥራም ከዚህ ጋር አብሮ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ነው። በተለይም አልባሳትና መሰል መሰረታዊ መገልገያዎች የአገር ውስጥ አምራቾች በቀላሉ ሊሰማሩባቸውና ሊያተርፉባቸው የሚችሉባቸው ዘርፎች በመሆናቸው ሸማቹም በእጅጉ ሊጠቀም ይችላል። የአገር ውስጥ ተጠቃሚነት

በጎለበተ ቁጥር አምራች ዘርፉ ይበልጥ በመጠናከር ምርቶች በብዛትና በጥራት የመመረት ዕድላቸው ይጨምራል፤ በዚህም የሥራ ዕድል ፈጠራው ይሰፋል፤ ዘርፉም ለአጠቃላይ አገራዊ ምርት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ይጨምራል። ጎን ለጎንም ከዚህ ቀደም ውጤታማ ያልሆንባቸውን የማዕድን ዘርፍ ልማት ከግምት ያስገባ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ምርትና ምርታማነትም በእጅጉ ሊታሰብበት ይገባል። በጥቅሉ ኢኮኖሚውን ወደተሻለ መስመር የሚመሩና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የፈጠራ ሥራን ማስፋት የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን ይበልጥ ማጠናከር ተገቢ ነው። በአገሪቷ በአራቱም አቅጣጫ ልንጠቀምባቸው የሚገቡ በርካታ የማዕድናት ክምችቶቸ መኖራቸው ይታወቃል፤ እነዚህን አልምቶ በመጠቀም ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ግኝቱን ማስፋት ሊሰመርበት ይገባል። ይህም የኢትዮጵያን የውጭ ንግድ መሰረት በማስፋት (Export Diversification) ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖረው የመስኩ ባለሙያዎች ይመክራሉ። ጠንካራ የፊስካል ፖሊሲ መተግበር



54

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

በመጀመሪያው የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በትኩረት ከተሰራባቸው ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች አንዱ ጠንካራ የፊስካል ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ ነው። ከዚህ አንጻር አበረታች ውጤቶች ቢመዘገቡም አሁንም በርካታ ቀሪ ሥራዎች አሉ። በተለይም መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተግባራዊ ለማድረግ በቀጣይ ዓመታት የሚያገኘውን ከፍተኛ ኃብት በአግባቡ መጠቀም ሌላው ትልቅ ኃላፊነት ነው። በተለያዩ ዘርፎች የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ውጤማነታቸው የተጠናና አዋጭ መሆናቸው ተለክቶ ለትግበራ እንዲዘጋጁ የማድረግ ሂደት አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። የካፒታል ፍሰቱ ጥራትን፣ ውጤታማነትንና የመፈጸም አቅምን ከግምት ያስገባ መሆኑን የማረጋገጥ ሥራ ቀጣይነቱን ማረጋገጥ ይሻል። በሌላ በኩል፤ መንግሥት ሰፊውን ሕዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ እንደ መስኖ ግድብ ሥራዎች፣ የኃይል ማመንጫ ግድቦች፣ መንገዶችና የትምህርትና የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽ የማድረግ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችን በማከናወን ላይ ይገኛል። እነዚህን ፕሮጀክቶች በተፈለገው ጥራት ለኅብረተሰቡ በአግባቡ ተደራሽ ለማድረግ የካፒታል

አቅሙን ማሳደግ አለበት። ያም ብቻ ሳይሆን እያደገ ለሚመጣው የሕዝብ ቁጥር ተመጣጣኝ መሰረት ልማቶችን ለመገንባት አሁን ከሚመድበው በጀት በላይ መመደብ ይኖርበታል። ይህ የሚሳካው ደግሞ የአገር ውስጥ የኃብት ማሰባሰብ አቅም ማጠናከር ሲቻል ብቻ ነው። በሌላ በኩል መንግሥት የበጀት ጉድለት ሲያጋጥመው በተደጋጋሚ ከብሔራዊ ባንክ በመበደር የሚሞላበት አካሄድ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግበት ተገልጿል። ይልቁንም የግምጃ ቤት ሰነድ እየሸጠ የሚያጋጥመውን ጉድለት እንዲሞላ የሚያበረታታ አካሄድ እየተፈጠረ ነው። ይህ አካሄድ በተለይ በገበያ ላይ ከሚፈለገው በላይ በርካታ ጥሬ ገንዘብ እንዲሰራጭ በማድረግ የዋጋ ግሽበት እንዲፈጠር ሲያደርግ የቆየውን ከለውጡ በፊት የነበረውን ከብሔራዊ ባንክ ያለገደብ የመበደር አሰራር የሚያስቀር ነው። ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር ተያይዞ በዜጎች ላይ የሚመጣውን ጫና ከግምት በማስገባትና የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ በማይጎዳ ሁኔታ የኃብት አሰባሰብ አቅምን ማጠናከር ያስፈልጋል። ይህም ብድር መክፈልን ጨምሮ የተለያዩ ወጪዎችን በራስ አቅም ለመሸፈን እንደሚረዳ

ነው በመስኩ የተካሄዱ ጥናቶች የሚያመላክቱት። እንደ መውጫ ኢትዮጵያ በከፍተኛ መጠን እያደገ ካለው የሕዝብ ቁጥሯ ጋር ሊስማማ የሚችል የኢኮኖሚ ዕድገት ያስፈልጋታል። ይህም ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፉን ተለዋዋጭ የጂኦ-ፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታን ታሳቢ ያደረጉ የተለያዩ ተጽዕኖዎችን የሚቋቋም ኢኮኖሚ መገንባት የዛሬና የነገ የቤት ሥራ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ የዕድገት አካሄድም ሁነኛ መፍትሄ ነው። መንግሥት ገቢራዊ ያደረገው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ከዚህ አንጻር በተለይም ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ኃብት አሟጦ በመጠቀም የተሻለ ልማት እንዲመዘገብ ከፍተኛ አበርክቶ ሊያስመዘግብ ይገባል። የዕድገት ምንጮችን በማስፋት ኢትዮጵያ ከዓለም ተለዋዋጭ ሁኔታ ጋር በመጓዝ ትርፋማ የምትሆንበትን አካሄድ አጥብቆ መያዙ አዋጭ ነው። በርካታ አገራት አንድም የሚከተሉት የዕድገት ሞዴል ከውስጣዊ ሁኔታቸው ጋር ያልተገናዘበ መሆኑና የዕድገት ምንጮች ውስን መሆን ለገጠሟቸው ችግሮች የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል።



55

ኢትዮጵያ ምንም እንኳን የራሷን የዕድገት ሞዴል በመቀመር ረገድ ችግሮች ባይስተዋሉባትም ከመፈጸም ጋር በተያያዘ የተለያዩ የተዋረሱ ችግሮች ባለቤት ነች። የዕድገት ምንጭን ማስፋት ዛሬም ያልተሻገርነው ሌላው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው። በመሆኑም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ የለውጥ እንቅስቃሴዎች አዎንታዊ ተጽዕኗቸው ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ የጋራ ርብርብ ማድረግን ይጠይቃል። ለዚህም ከመንግሥት ጎን ለጎን ባለኃብቱም ዋነኛ የዕድገት ሞተር የሚሆንበት ተጨማሪ ዕድል ተከፍቷል። ገበያ ላይ የተመሰረተው የውጭ ምንዛሬ ተመን ባለኃብቱ ከአገር ውስጥ ባሻገር የውጭ ንግድ ላይ ተሳትፎ እንዲያደርግ የሚያበረታታ ነው። ይህንን ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ባለኃብቱ ዋነኛ የኢኮኖሚ ተዋናይና መሪ የሚሆንበትን ዕድል ዳግም ማረጋገጥና አልቆ ማስቀጠል ይገባል። ሕጋዊነትን ያከበረ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በአራቱም የአገሪቷ አቅጣጫ ማጠናከርና አገርና ሕዝብ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሥርዓት ማበጀት ሌላው ጉዳይ ነው። ሕገ-ወጥነት ባለበት አውድ ውስጥ የተሳካ ሥራ መሥራት ስለማይቻል መንግሥት ችግሮቹን ለመቅረፍ ከሚያደርጋቸው ጥረቶች

ባልተናነሰ የኅብረተሰቡ ተሳትፎም ወሳኝ ይሆናል። ኢትዮጵያ ካሉባት የኢኮኖሚ ስንጥቃቶች የመውጣቷ ነገር አጠያያቂ አይደለም፤ ጥያቄው መቼ ነው የሚለው ጉዳይ በመሆኑ አሁን ያለነው ትውልድ ለዚህ ቀን መቃረብ የራሳችንን ጠጠር የመወርወር ግዴታ ተጥሎብናል። በተለይም ዘመኑ ወደ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ሥርዓት ሽግግር የሚደረግበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚከናወኑ ተግባራት እጅግ ወሳኝ ሆነው ይታያሉ። ይህም ወደፊት እየገሰገሰ ባለው ፈጣን የዓለም የዕድገት ባቡር ላይ መሳፈር እንደሚያስችለን ሁሉ የሚጠበቅብንን ካልሰራን ወደኋላ የመቅረታችንን ዕድልም አብረን አዝለን የምንዞር መሆኑን ልብ ይሏል። በመሆኑም የኢትዮጵያን ቀጣይ ወደ ተስፋ ጉዞ እንከን የለሽ ለማድረግ ሳይሆን የሚገጥሟትን ፈተናዎች አልፋ ስኬት እንድትጎናጸፍ ማድረግ የሁሉንም የጋራ ጥረት ይሻል። የማሸነፍን የድል መንፈስ ከቀደሙ አባቶች ገድል በመውረስ፤ የዛሬውና የመጪው ትውልድ ስንክሳር በኢኮኖሚውም መስክ በአንጸባራቂ ስኬቶች ይታጀቡ ዘንድ ልባዊ ምኞቴ ነው።



56

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ማኅበራዊ

ዓመተ-ድንቅነሽ



57

ዓመተ-ድንቅነሽ

ጭላፊ… በ1960ዎቹ አጋማሽ ኢትዮጵያ የለውጥ አብዮት በተገላገለች ማግሥት ነው። አብዮቱ ግና ከመወለዱ ኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም ዕድሜ-ልካቸውን ለሀገር የኖሩ ባለውለታ ልጆቿን በሽርፍራፊ ደቂቃዎች ውስጥ ቀርጥፎ በላባት። በዚህ ዕለት ‘ደርግ’ 60ዎቹን ድንቅ ልጆቿን በግፍ ጨፈጨፈ። በማግሥቱ ኅዳር 15 ቀን 1967 ዓ.ም ግን በሐሩራማው የታችኛው አዋሽ ሸለቆ ልዩ የምሽት ድባብ ይነበባል። በተለይ በአፋሯ የሐዳር መንደር። የቅድመ ሰው ዘር አመጣጥ ተመራማሪዎቹ ‘ዘ-ቢትልስ’ በሚሰኝ የሮክ ሙዚቃ ባንድ የተዜመን “ሉሲ በባለ አልማዝ ሠማይ ስር’ የሚል ትርጓሜ ያለው የእንግሊዝኛ ሙዚቃ ይኮመኩማሉ።

በአየለ ያረጋል



58

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

በተለይ ከስዊድናዊ ቤተሰብ የሚወለደው አሜሪካዊ ወጣት ተመራማሪ ዶናልድ ካርል ጆሐንሰን (የዛሬው ፕሮፌሰር) በሐሴት ፈንጠዝያ ተውጧል። ዘመን አይሽሬ ክብርና ዝና ያገኘበት የሰው ዘር ቅሪተ አካል ግኝት ባለቤት ሆኗልና። ይባስ ብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረ ቅሪተ-አካል! የአፋር የምርምር ቡድን አባላቱ አሜሪካዊው ዶናልድ ጆሀንሰን፣ እንግሊዛዊቷ ማሪ ሊኪ፣ ፈረንሳዊያኑ ማውረስ ታይብ

እና ይቨንስ ኮፐንስ ናቸው። በጆሯቸው ከሚያስተጋባው ለስላሳ ሙዚቃ በመነሳት ቅሪተ አካሏን ‘ሉሲ’ ሲሉ ሰየሟት። ከቀናት በኋላም አንድ የኢትዮጵያ የባሕል ሚኒስቴር ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊ በግኝቱ ‘ድንቅነት’ በመገረም ቅሪተ አካሏን ‘ድንቅነሽ’ የሚል አቻ ሥያሜ ሰጧት። ዘንድሮ የድንቅነሽ ቅሪተ-አካል ከተገኘ 50ኛ ዓመቱን አስቆጠረ። ዓመቱም ‘የድንቅነሽ ዓመት’ በሚል ተሰይሞ እየተዘከረ ነው። ነገረ- ሉሲ (ድንቅነሽ)



59

ሉሲ በጥንተ-ሰብዕ ምርምር ዓለም የአውስትራሎፒቲከስ አፍረንሲስ ቤተሰብ ናት። ሉሲ አንድ ሜትር ከ40 ሴንቲ ሜትር ርዝመት ያላት ናት። የቅሪተ አካሏ 40 በመቶው አካል ክፍሏ ነው የተሰባሰበው። የሉሲ (ድንቅነሽ) ራስ ቅል ከዛሬዎቹ ዝንጀሮዎች የሚመሳሰል፣ ጥፍሯ ቆልማማ፣ ባለ ትልቅ አገጭ እና ቆማ መራመድ በመቻሏ ጥንተ ሰብዕ ዘር መሆኗ ተረጋገጠ። ድንቅነሽ/ሉሲ ከተገኘች እነሆ ዘንድሮ ግማሽ ምዕተ ዓመት ተቆጠረ። በአሜሪካው አሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ የቅድመ ሰው ዘር አመጣጥ ጥናት ተቋም በኩል የፈረንጆቹ 2024 ‘የድንቅነሽ ዓመት’ ተብሏል። በቅርቡ በአዲስ አበባ የተደረገውን የሰው ዘር አመጣጥ ጥናት ጉባዔ ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ኹነቶች እየተዘከረ ነው። ለመሆኑ ድንቅነሽ ለኢትዮጵያም ሆነ ለጥንተ ሰብዕ ምርምር ዘርፍ መጎልበት ምን ትሩፋት አመጣች? “ባለ አከርካሪዎች” የተሰኘው የማንይንገረው ሸንቁጥ መጽሐፍ እንደሚያትተው ሉሲ በሁለት እግሯ የምትንቀሳቀስ ኤፕ (ቺምፓንዚ) መሰል ፍጡር ነበረች። ድንቅነሽ (ሉሲ) በሴት ጾታ የምትጠራው ደግሞ ‘የዳሌዋ አጥንት’ በመገኘቱ እንደሆነ

ተመራማሪዎች ይገልጻሉ። ከአንድ ዓመት በፊት (ሰኔ 2015 ዓ.ም) በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ይፋ በሆነው መረጃ ደግሞ ሉሲ በመሬት ላይ ቆማ መራመድ ብቻ ሳይሆን በዛፍ ላይም ትኖር ነበር። ለዚህ ማስረጃም በዲጂታል መንገድ(3D) በመጠቀም የሉሲ የጉልበት መገጣጠሚያ መተጣጠፍና መዘርጋት ይችል ነበር የሚለውን በማረጋገጥ ነው። እናም ድንቅነሽ በሁለት እግሮቿ ‘መሽቀንጠር’ም፤ በእጆቿ ዛፎች ላይ ‘መንጯለል’ም መክሊት ነበራት ማለት ነው። የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት ያፀናችው - ‘ድንቅነሽ’ በየዘመናቱ ኢትዮጵያን የጎበኙ አሳሾች ‘ድንቅ ምድር’ ብለዋታል። በእርግጥ ኢትዮጵያ የ13 ወር ፀጋ፣ የጥንት ሥልጣኔ አውድማ፣ ነቅዓ-ግዮን፣ ባለ ፊደል፣ ቅኝ ያልተገዛች አፍሪቃዊት ምድር፣ የቡና እና ሌሎች አዝርዕት መገኛ …. በመሆኗ ልዩ እና ድንቅ መልክ አላት። በሥነ-ሰብዕ አመጣጥ መለኮታዊ እሳቤ ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት እንደሆነች ይነሳል። ዓባይ ሸለቆ ‘የሥልጣኔ መነሻ፣ የፍጥረተ ዓለም መጀመሪያ ነው’ የሚል ሳይንሳዊና ትውፊታዊ ትርክት አለ። ባለቅኔው (ቀደሰ)

ዓለማየሁ ሞገስ (ረዳት ፕሮፌሰር) ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ የሰው ዘር ቅሪተ አካል ሉሲ (ድንቅነሽ) ከመገኘቷ በፊት “የሰው ዘር የተፈጠረው በኢትዮጵያ በዓባይ ሸለቆ ነው፤ የግብፅን መንግሥት የመሰረቱ ጠቢባንን ያስተማሩትም ኢትዮጵያዊያን ናቸው” ብለው ነበር። ከ30 ዓመት በኋላ ሉሲ በአፋር ክልል ሐዳር ውስጥ ተገኘች። ሊቁ ዓለማየሁም በተመሳሳይ ጥናት በዓባይ ሸለቆ ጥናት ለማድረግ የሚያስተምሩበትን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጠይቀው ትብብር ባለማግኘታቸው በቁጭት እንደቀሩ ጽፈዋል። ዶክተር ኃይሉ ወልደሚካኤል የተባሉ ሰው ‘አብሮነት በኢትዮጵያ’ በተሰኘ መጽሐፋቸው “የዓባይ ሸለቆ የዓባይ ወንዝ ውጤት ነው። የዓባይ ሸለቆም የመጀመሪያው የሰው ልጅ የተደራጀ ማኅበራዊ ሥርዓት የፈጠረበት፣ የሰው ልጅ የተፈጥሮን ሕግ ግንዛቤ ያገኘበት፣ የሃይማኖት፣ የፖለቲካ፣ የሥነ ምግባርና የሳይንስ ሥርዓት ምስጢር የለየበትና ያደራጀበት ነው” ብለዋል። የሉሲ ቅሪተ አካል፣ የራሚደስ ቅሬተ አካል (4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ ያለው) እና ሌሎች የቅድመ ሰው ዘር ቅሪቶች የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት



60

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

አጽንተዋል። በዝግመተ-ለውጥ ወይም በሳይንሱ ዓለም የሰው ዘር አመጣጥ ምርምር ደግሞ ‘ድንቅነሽ’ ምድረ ቀደምትነቷን አፀናች። ዕውነተኛ የሰው ዘር ምንጭነቷንም አረጋግጣለች። ድንቅነሽ በስምጥ ሸለቆ ተጨማሪ የቅድመ ሰው ዘር ምርምሮች እንዲጠናከሩ ምክንያት ሆናለች። ለምሣሌ ድንቅነሽ ከሞተች ከሁለት መቶ ዓመት በኋላ የኖሩ የድንቅነሽ ቤተሰብ አባላት እንደሆኑ በጥናት የታመነባቸው የጥንት ሰው ዘሮች ቅሪተ አካላት ተገኝተዋል። ከዛሬ ግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ምድር የተገኘው የሉሲ ቅሪተ-አካል በቅድመ ሰው ዘር አመጣጥ ጥናት ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን የዘርፉ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። የሉሲ ቅሪተ አካል መገኘት ደግሞ የኢትዮጵያን ምድረ-ቀደምትነት ያጸና አጋጣሚ ብቻ ሳይሆን በሰው ዘር አመጣጥ ሳይንሳዊ ጥናት ማዕከል እንድትሆን አይተኬ ሚና ተጫውቷል፡፡ የዛሬው የ81 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆሀንሰን የዘርፉ የጥናት መስክ ትኩረት እንዲያገኝ ትልቅ ውለታ ውለዋል። በቅርቡ የግኝታቸውን 50ኛ ዓመት መታሰቢያ ለመዘከር አዲስ አበባ የነበሩትን ፕሮፌሰር ጆሀንሰን ኢዜአ አነጋግሯቸው

ነበር። “የሉሲን የወርቅ ኢዮቤልዩ ለማክበር በመብቃቴ ልዩ ደስታ ይሰማኛል” ነበር ያሉት። የድንቅነሽ መገኘት የሰው ዘር አመጣጥ ጥናት ላይ የእሳቤ ለውጥ ማምጣቱን ያወሳሉ። በሌላ በኩል ለኢትዮጵያ እውነተኛ የሰው ዘር ምንጭነቷ ተጨማሪ ማረጋገጫ መሆኑን ይናገራሉ። “ኢትዮጵያ ከስድስት ሚሊዮን ዓመት በፊት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የሰው ዘር መኖሪያነቷን፣ ስለ እኛ ምንነት፣ ከየት መጣን እንዲሁም ውስጠ መነሻችን የት ነበር ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ማረጋገጫ ነው” ይላሉ። ፕሮፌሰር ጆሃንሰን ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ ከረገጡበት ከ1960ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ሰርክ ወደ ኢትዮጵያ ተመላልሰዋል። “ኢትዮጵያ ሁለተኛ ቤቴ ናት። “ኢትዮጵያ አንዴ ከመጣህ የግድ ትመላለሳለህ” ይላሉ። “ታይቶ የማይጠገብ” በሚሉት በኢትዮጵያ መልክዓ ምድር ይደመማሉ። የሀበሻን ምግብ እና ባሕል ይወዳሉ። ባሳለፍነው ሐምሌ 2016 ዓ.ም መጨረሻ በተካሄዱ 50ኛ ዓመት የዝክረ-ሉሲ መርኃ-ግብሮች ከ34 አገራት የተውጣጡ የዘርፉ ተመራማሪዎች ጥንታዊ ቅርሶችና የቅሪተ-አካል ክምችቶችን ጎብኝተዋል። ጎብኚዎቹ ኢትዮጵያ በሰው ዘር ምንጭነቷ ብሎም

በዳበረ ጥንታዊ ቀደምት ታሪኳ ‘’ምድረ ቀደምት’’ የሚለው መጠሪያ ኢትዮጵያን በልክ ይገልጻታል ነበር ያሉት። በአሜሪካው ስቶክተን ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ሕይወት ትምህርት ክፍል ተመራማሪዋ ፕሮፌሰር ማርጋሬት ሌዊስ፤ ከፈረንጆቹ አቆጣጠር 1997 ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በአፋር አካባቢ ምርምሮችን ያደርጋሉ። በጥንተ የእንስሳት ቅሪተ አካል ምርምር የሚያደርጉት ፕሮፌሰሯ፤ ሉሲን ጨምሮ የቅድመ ሰው ዘር ቅሪተ አካሎች የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት የሚያረጋግጡ እንደሆኑ ይገልጻሉ። “ኢትዮጵያ በብዙ ነገር ምድረ ቀደምት መሆኗ ዕሙን ነው፡ ፡ ሉሲ ስለ ሰው ዘር አመጣጥና ምንጭ የነበረን እሳቤ ቀይራለች፡ ፡ የእኔ ምርምር በሉሲ አካባቢ በነበሩ ግዙፍ እንስሳት ዙሪያ ያተኮረ ነው። ምርምሮቹ ስለ ሉሲ ምንነትና አካባቢው የጥንት መልክና አኗኗር ይነግረናል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሰው ዘር አመጣጥ ስብስቦችን፤ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ስለ ሁላችንም የሰው ዘሮች አመጣጥ ታሪክ የሚነግረን ነው” ይላሉ። በአሜሪካው ኢንዲያና ዩኒቨርሲቲ የሰው ዘር አመጣጥ ተመራማሪው ታንዛኒያዊ ፕሮፌሰር ጃክሰን ጃው፤ “በሥነ-



61

ምድር ጥናት ቀደምትነት የጊዜ ዑደትና የዕድሜ ቅደም ተከተል አኳያ ኢትዮጵያ ቀደምት የሰው ዘር መገኛ ናት” ሲሉ ይገልጻሉ። ኢትዮጵያ እስከ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ ያላቸው ቅሪተ-አካላት የተገኙባት አገር መሆኗ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ቀደምት የሚያደርጋት ታሪኮች ባለቤትም እንደሆነች ያነሳሉ። “የቅድመ ሰው ዘር 6 ሚሊዮን ዓመት ወደኋላ አስቆጥሯል፡ ፡ እስከ አሁን እስከ 4 ነጥብ 5 ወይም 3 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ ያላቸው ቅሪተ-አካሎች በኢትዮጵያ ተገኝተዋል፡፡ ስለዚህ ምድረ-ቀደምት የሚለው መጠሪያ ትርጉም ይሰጣል” ብለዋል። ስፔናዊው ኢግናሲዮ ላሳጋባስተር (ዶ/ር) በእንግሊዙ ሊቨርፑል ዩኒቨርሲቲ የሰው ዘር አመጣጥ ከፍተኛ ተመራማሪ ነው። የድንቅነሽ ቅሪተ-አካል ለእርሱና መሰሎቹ ተመራማሪዎች በዘርፉ ጥናት እንዲሰማሩ መነሳሳት ፈጥራለች። “ስለ ሉሲ፣ ስለ ሰላም ቅሪቶች ስናይ ከአንድ ዘር የተመዘዝን ወንድማማች ሰዎች እንደሆንን ያስተምሩናል፡፡ ቅድመ አያቶቻችን ከኢትዮጵያ እንደሚመዘዙ ያሳያል፡፡ ስለዚህ በትክክል ኢትዮጵያ ምድረ

ቀደምት ናት፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ በምስራቅም ሆነ በደቡብ አፍሪካ ለምርምር የሚጠቅሙ ሌሎች ቅሪተ-አካሎች ተገኝተዋል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያን እነዚህ ቅሪተ- አካሎች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች የአርኪዮሎጂካል ኃብቶችም ምድረ ቀደምት ያሰኟታል” ይላል፡፡ በሌላ በኩል በታንዛኒያው የዳሬሠላም ዩኒቨርሲቲ የአርኪዮሎጂስት ትምህርት ክፍል ተመራማሪዋ ማሪየም ቡንዱላ (ዶ/ር) በሀገራቸው ታንዛኒያ ሚሊዮን ዓመት ያስቆጠሩ ቅሪተ አካሎች ቢኖሩም ኢትዮጵያን እንደማይስተካከሉ ያምናሉ። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ቅርሶቿን ያደራጀችበትን መንገድ ያደንቃሉ። “ቅርስ ከትውልድ ትውልድ በተሸጋገረ ቁጥር እኛ ከየት እንደመጣንና ስለ ሀገራችን ቀደምት ታሪክ ያስተምረናል፡፡ ስለዚህ እናንተ እንዴት ታሪክና ቅርሳችሁን እንደጠበቃችሁና እንዳደራጃችሁ ያየነው ነገር የሚያኮራ ነው፡፡ ይህ ለቀጣይ ትውልድ ጠብቆ ለማስተላለፍ ይበጃል፡፡ ስለዚህ መንግሥት የሰራው ነገር ትልቅ ነገር ሆኖ የእናንተ ትውልድም ይህን ቅርስ መጠበቅ አለበት ብዬ አስባለሁ’’። የኬንያ ብሔራዊ ሙዚየም ባልደረባ እና የሦስተኛ ዲግሪ



62

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ተማሪዋ ኬንያዊት ርብቃ ሙሪዩኪ፤ ኢትዮጵያ ቅርሶቿን ያደራጀችበትን አግባብ አድንቀዋል። ቅርስን ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ማሻገር ትውልዱ በታሪኩ እንዲኮራ ብቻ ሳይሆን ከትናንት ማንነቱ እንዲማርበት የሚያስችል እንደሆነ ገልጻለች። ሌላው ወጣት የዩጋንዳ ሙዚየም ባልደረባ እና የመከረሪ ዩኒቨርሲቲ የአርኪዮሎጂ ትምህርት ክፍል ተማሪው ክሪስ ሰሲዩቡንጎ ነው። ኢትዮጵያ በታሪኳ በአፍሪካ ቀደምት የሥልጣኔ ሀገር እና የዳበረ ታሪክ ያላት እንዲሁም የመላው አፍሪካዊያን የነጻነት ቀንዲል መሆኗን ይናገራል። “ኢትዮጵያ መምጣት ሁሌም እመኝ ነበር። ሉሲን ጨምሮ የቅድመ ሰብዕ ዘር ቅሪተ አካሎችን በማየቴ ደስተኛ ነኝ” ነበር ያለው። ድ ን ቅ ነ ሽ - የ ድ ን ቅ ሳይንቲስቶች መነሻ ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆሃንሰን ‘ድንቅነሽ የለወጠችው ስለ ጥንተ- ሰብዕ እሳቤ ብቻ አይደለም’ ይላሉ። ኢትዮጵያ በዝግመተ ለውጥ እሳቤ ሳይንስ ዓለም ስሟና ክብራ እንዲናኝ አስችሏል። ይልቁንም ስመጥር የዘርፉ ተመራማሪዎች የኢትዮጵያን ሸለቆዎች እንዲያስሱ ምክንያት ሆናለች። እንደ ፕሮፌሰር ዶናልድ

ጆሃንሰን ድንቅነሽ አንቱታን ያተረፉ አያሌ ኢትዮጵያዊያን ሳይንቲስቶች እንዲወጡም መነሳሳት ፈጥራለች። ዛሬም በዘርፉ ወጣት ተመራማሪዎች ቢበዙ ኢትዮጵያን ለተቀረው ዓለም ይበልጥ ለማሳወቅ ይበጃል የሚል እምነት አላቸው። “ኢትዮጵያ ውስጥ ምርመር ስጀምር በቅድመ ሰው ዘር አመጣጥም ሆነ በቅሪተ አካል ቁፋሮ ማንም ኢትዮጵያዊ ተመራማሪ ምሁር አልነበረም። ዛሬ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልደው አስደናቂ ምርምር በማድረግ ቅሪተ አካል ያገኙ ወጣት ተመራማሪዎች ሞልተዋል። ወጣቶች ኢትዮጵያዊያን በሰው ዘር አመጣጥ ጥናት እንዲሰማሩ እመክራለሁ። ምክንያቱም ስለ ኢትዮጵያም ሆነ ስለተቀረው ዓለም ምንነት ለመረዳት ያግዛልና” በሰው ዘር አመጣጥ ጥናት አንቱታን ካተረፉ ሳይንቲስቶች መካከል አንዱ ፕሮፌሰር ዮሐንስ ኃይለሥላሴ ናቸው። በአሜሪካው የአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ የቅድመ ሰው ዘር ጥናት ተቋም ዳይሬክተር እና ተመራማሪ ናቸው። (በነገራችን ላይ የዚህ ምርምር ተቋም መስራች ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆሃንሰን ናቸው)። ፕሮፌሰር ዮሐንስ ከሉሲ

(ድንቅነሽ) ዕድሜ በዕጥፍ የምትቀድመዋን ‘አርዲ’ የተሰኘችዋን የስድስት ሚሊዮን ዓመት ቅሪተ አካል ኢትዮጵያ ውስጥ ያገኙ ሳይንቲስት ናችው። በግኝቶቻቸውም ስማቸው በዕውቅ የሳይንስ መጽሔቶች የፊት ገጽ ላይ ናኝቷል። ከድንቅነሽ ቅሪተ አካል እርሳቸውና መሰል ኢትዮጵያዊያን ተመራማሪዎች በጥናትም ሆነ የጥናት ፕሮጀክት በመምራት በዘርፉ ለዓለም ትልቅ አበርክቶ አግኝተዋል። ፕሮፌሰር ዮሐንስ አሁንም ተተኪ



63

ሳይንቲስቶችን ለማፍራት ጥረት እያደረጉ ስለመሆኑ ይገልጻሉ። ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያዊያን ምሁራንን በማፍራት አመርቂ ውጤት ስለመገኘቱም እንዲሁ። “ጥናቶችን ማካሄድ ብቻ ሳይሆን የግኝት ባለቤቶች ናቸው። ሉሲ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዓመቷ ነው። እኔ ግን የስድስት ሚሊዮን ዕድሜ ያላት ቅሪተ አካል አግኝቻለሁ። በሰው ልጅ ቅድመ ታሪክ መስክ እኔን ጨምሮ ብዙዎቻችን ቅሪተ አካል አግኝተናል። አሁን ሌሎቹ እንደ ተባባሪ ሳይሆን በዘርፉ

የምርምር መሪዎች አድርገው ነው የሚያዩን። አሁን እንዴት ተተኪ እናፍራ የሚለውን ነው እየሰራን ያለነው። በአጠቃላይ በሁለት አሥርት ዓመታት ውስጥ የምሁራን ቁጥር ዕድገት አበረታችና አመርቂ ነው ማለት እንችላለን“። ከድንቅነሽ ግኝት በኋላ በተለይም አዋሽና ኦሞ ሸለቆዎች የዝግመተ ለውጥ ምርምሮች እንዲጠናከሩ አድርገዋል። ለምሣሌ የሆሞ ኤሬክተስ ቅድመ ታሪክ አሻራዎች በመልካ ቁንጥሬ መካነ ቅርስ



64

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ግቢ ይገኛሉ፡፡ ሆሞ ኤሬክተስ እሣት የሞቀበት ሳይቀር የተጠቀመባቸው የድንጋይ መሳሪያዎችም አሉ፡፡ የድንጋይ ዘመን የቴክኖሎጂ ውጤቶች መሆናቸው ነው፡፡ ለምሣሌ አሣ፣ ጉማሬ፣ የፈረስ ዝርያ፣ ቀጭኔና የቀንድ ከብት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት እንደጎበኘሁት በመልካ ቁንጥሬ መካነ ቅርስ መካከል 65 የቁፋሮ ስፍራዎች ይገኛሉ። አራት ዓይነት ሙዚየሞች አሉት፡፡ የመጀመሪያው የአፍሪካ ቅድመ ታሪክ ቤተ-መዘክር ሲሆን በአፍሪካ ውስጥ ትልልቅ ሥራ የሠሩ ታዋቂ አርኪዎሎጂስቶች፣ ጂኦሎጂስቶችና ሌሎችም የዘርፉ ባለሙያዎችን ያስቃኛል፡ ፡ ከእነዚህም ድንቅነሽ (ሉሲ) ን ያገኟት ዶናልድ ጆንሰን እና በመልካ ቁንጥሬ ቀደምት ሰዎችና እንስሳት የእግር አሻራ ያገኘችው ማሪ ሊኪ እና ቤተሰቦቿ ይጠቀሳሉ፡፡ ሁለተኛው የሥነ- ምድር እና የመሬት ፍንዳታ ቤተ-መዘክር ሲሆን ከሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባልጩ ከሚባለው የእሣተ ገሞራ ፍንዳታ የነበረበት አካባቢ የተሰበሰቡ ሹል መገልገያ ድንጋዮች ቤተ-መዘክር ነው፡፡ ሦስተኛው የፖሊአንትሮፖሎጂ ቤተ-መዘክር ነው፡፡ እኛ ሰዎች ከማምቧቸት ጀምረን በዝግመተ ለውጥ ሒደት ዛሬ

ያለንበትን ደረጃ የሚዋጅ ነው፡ ፡ የአራተኛው ስያሜ መልካ ቁንጥሬ ሲሆን በመካነ ቅርሱ ካሉ የቁፋሮ ቦታዎች የተሰባሰቡ የእንስሳት ቅሪተ አካሎችና የእጅ መሣሪያዎች የሚገኙበት ነው፡፡ የሮም ዩኒቨርሲቲ የአርኪዮሎጂ ተመራማሪዎች የሰው ዘርና የእንስሳት የእግር አሻራ (foot print) አግኝተዋል፡፡ የአሻራ ምልክት ከታንዛኒያ በስተቀር ሌላ ቦታ አልነበረም፡፡ ድንቅነሽ ለኢትዮጵያ ቱሪዝም አዲስ ገጽ ቱሪዝም ለኢትዮጵያ የማይናቅ ምጣኔ ሀብታዊ ድርሻ አለው። ዳሩ ከሀገሪቷ ቱሪዝም ዕምቅ አቅም አኳያ ገና ያልተነካ ዘርፍ ይሰኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ለዘርፉ ማነቆ የነበሩ የቱሪስት መሰረተ ልማቶች እየተሻሻሉ መምጣታቸው (የገበታ ለሀገር እና የገበታ ለትውልድን ጨምሮ) ዘርፉን ለማነቃቃት ወሳኝ ድርሻ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። የኢትዮጵያ የቅድመ ሰው ዘር መገኛነት ደግሞ ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት ጉልህ ሚና ተጫውቷል። ድንቅነሽ ቅሪተ- አካሏ ከኢትዮጵያ አልፎ በመላው ዓለም እየተዘዋወረች ኢትዮጵያን አስተዋውቃለች። የሉሲን ቅሪተ-አካል 50ኛ ዓመት መታሰቢያ ምክንያት በማድረግ በወርኀ ሐምሌ 2016 ዓ.ም አዲስ



65

አበባ ውስጥ የምርምር ጉባዔ እና ዐውደ ርዕይ ተካሂዷል። ከ34 ሀገራት የተውጣጡ ከ240 በላይ የቅድመ ሰው ዘር ተመራማሪዎች ታድመውበታል። በጉባዔው በቅድመ ሰው ዘር አመጣጥ (ፓሊዮአንትሮፖሎጂ) ዘርፍ ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት የሚያጠናው የአሜሪካው አሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሰው ዘር አመጣጥ ምርምር ተቋም ምሁራን ይገኙበታል፡ ፡ ፕሮፌሰር ዮሐንስ “ጉባዔው ከዚህ በፊት ከተካሄዱ ጉባዔዎች በተለየ ድምቀትና ከፍታ የተከበረ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ጉባዔው እና የምሁራኑ ጉብኝት ከሳይንሳዊ ፋይዳው ባሻገር የኢትዮጵያን ገፅታ ለመገንባት ብሎም የቱሪዝም ሀብቶችን ለተቀረው ዓለም ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ፋይዳ እንደነበረው ነው ያብራሩት። በተለይም ተመራማሪዎቹ በአድዋ ድል መታሰቢያ፣ በብሔራዊ ቤተ-መዘከር እና በአንድነት ፓርክ ጉብኝት ማድረጋቸውን የኢትዮጵያን ታሪክና ቅርስ ሀብት እንዲመለከቱ በማድረግ የቱሪዝም ፀጋዎቿን እንድትሸጥ አስችሏታል። በእርግጥ ጎብኚዎቹም በተመለከቱት ነገር መደነቃቸውን አልሸሸጉም። በ1999 ዓ.ም በኢትዮጵያ ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና በአሜሪካው

ሂውስተን የተፈጥሮ ሳይንስ ሙዚየም ስምምነት መሠረት ሉሲ በአሜሪካ የአምሥት ዓመት ቆይታ አድርጋለች። በወቅቱም ድንቅነሽ በሂውስተን፣ በቴክሳስ፣ በሲያትልና በካሊፎርኒያ ተዘዋውራ ከ350 ሺህ በላይ ሰዎች ሲጎበኟት፣ ከአንድ ነጥብ አምሥት ሚሊዮን በላይ ዶላር ገቢ እንዳስገኘች መግለጹን ያስታውሷል። በተመሳሳይ እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር በጥቅምት 2021 በተካሄደውና ከ192 በላይ ሀገራት በተሳተፉበት ዱባይ ኤክስፖ 2020 ላይ ኢትዮጵያ ራሷን ለማስተዋወቅ ይዛቸው ከቀረበቻቸው ቁሶች መካከል አንዷ ድንቅነሽ ነበረች። በኤክስፖው ድንቅነሽ ለመንፈቅ ዓመት በዱባይ ቆይታለች፤ ሀገሯንም አስተዋውቃለች። በእርግጥ ሉሲ ከሀገር ውጭ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ በየዕለቱ ከሚጎበኙ የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል አንዷ ናት። በወርኅ የካቲት 2011 ዓ.ም የ”ጉዞ ሉሲ ለሠላምና ለፍቅር” ፕሮጀክት ከተገኘችበት አፋር ክልል ጀምሮ በመላው ኢትዮጵያ ተዘዋውራ ትውልዱ በሀገር ሠላምና ፍቅር እንዲነግሥ የማድረግ ንቅናቄ ምልክት ተደርጋለች። መሰናበቻ! ጆን ማርቲኔዝ (ዶ/ር) የሚባሉ

የውጭ ሀገር ዜጋ በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው (LinkedIn) ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባሕልና መልክዓ ምድር ሰርክ ይጽፋሉ። ስለ ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምትነት መተረክ እንደማይሰለቻቸውም እንዲሁ። በዶክተር ማርቲኔዝ ጽሑፍ እንሰናበት። “ምንም ያህል ስለ ኢትዮጵያ ብጽፍ አይበቃኝም። ስለ እርሷ የሚሰማኝን ነገር ሁሉ በቅጡ መግለጽ ይሳነኛል። ዘለዓለም ጊዜ ቢሰጠኝም አይበቃኝም። . . . ከጥንት እስከ ዘመናዊ ዘመነ መንግሥታት ህልቆ ቢስ ታሪኳ ቢወራ ተዝቆ አያልቅም። በአፍሪካ ውስጥ አስደናቂዋ እና የማይታመን ታሪክ የሆነ ልዕለ ተፈጥሮ የመሰለ ውበት የተቸራት ሀገር፤ የአፍሪካዋ ልብ ናት - ኢትዮጵያ። መልክዓ ምድሯ፣ ተራሮቿ፣ ጫካዎቿ እና ሣር ምድሯ . . . ከፈጣሪዋ የተቸራት ድንቅ ምድር። . . . መሰረታችን፣ የሰው ዘር መገኛ፣ የአፍሪካ ትናንት እና ነገ ማስተሳሰሪያዋ ልብ - ኢትዮጵያ ናት። መሰረታችሁን እና ሕይወት የሰጠቻችሁን ሀገር ጎብኟት። ለነጋችሁ ትናንታችሁን እሹ። . . . እግዚአብሔር የፍጥረት እና የእስትንፋስ መጀመሪያዋን ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ይጠብቅ” አሜን!



66

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ማኅበራዊ

በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት እና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ትብብር የተዘጋጀ

ዘመናዊ የአቅርቦት ሠንሰለት



67

ለቀልጣፋ አገልግሎት

ኢትዮጵያ በጤና ዘርፍ የያዘችውን ጤናማ እና አምራች ዜጋ የማየት ራዕይ ለማሳካትና ለመምራት የሚያስችሉ የልማት ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ዕቅዶችን ነድፎ በመተግበር ሰፊ መሰረት ያለው ፈጣን፣ ቀልጣፋና ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ልማትን የማፋጠንና ድህነትን የማስወገድ ዓላማ ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል - የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት። ጤና ከሁሉም የአገሪቷ የልማት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም ለአገር ዕድገትና ለኅብረተሰብ ደህንነት መረጋገጥ ወሳኝ ከሆኑ ማኅበራዊ የልማት ዘርፎች አንዱና በአገር ደረጃ በተነደፈው የሁለተኛው የ10 ዓመት የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ ነው።



68

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

አገልግሎቱ የኅብረተሰቡን ጤና ለማሻሻል የሚያግዙ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎችን ማቅረብ ያስችል ዘንድ የአቅርቦት ሰንሰለት አስተዳደሩን በማዘመንና በማጠናከር በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት ለጤና አገልግሎቱ የሚያስፈልጉ ጥራታቸው፣ ፈዋሽነታቸውና ደህንነታቸው የተረጋገጡ መሰረታዊ መድኃኒቶችንና የሕክምና መገልገያዎችን በበቂ መጠን፣ በተመጣጣኝ ዋጋና ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማቅረብ የቀደመውን በጀት ዓመት አፈፃፀም በመገምገምና ጠንካራና ደካማ ጎኖችን እንዲሁም መፍትሄዎችን በመለየት ለበጀት ዓመቱ ዕቅድ

በግብዓትነት በመውሰድና በማቀድ ተግባራቱን አከናውኗል። የመድኃኒትና የሕክምና ግብዓቶችን ወደ ተጠቃሚው ለማድረስ የሚወስደውን የጊዜ ክፍተት ለማስተካከል የአቅርቦት ሰንሰለት ሥርዓቱን ለማዘመን መንግሥት በትኩረት እየሰራበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጉልህ ስኬቶች እየተመዘገቡ ነው። የመድኃኒትና የሕክምና መሳሪያዎችና ግብዓቶችን አቅርቦት ችግር ለመቅረፍም እንደ አገር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል። በዚህ ረገድ የአቅርቦት ሥርዓቱን ለማሳደግና ሂደቱንም ቀልጣፉ የማድረግ ሥራዎች ተሰርተዋል። በተለይ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተበጣጠሰ የነበረውን



69

የመረጃ ሥርዓት ወደ አንድ የተቀናጀ (Digitalized) የአሰራር ሥርዓት ያሳደገበት ሲሆን፤ እንደ አገር በቅርቡ ተግባራዊ የሆነው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያም ለዓመታት ለግዥ ሥርዓቱ ፈተና የነበረውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመፍታት መልካም ዕድል የፈጠረለት ሆኗል። የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የጤና ተቋማትን ፍላጎት ለማሟላት በ2016 በጀት ዓመት በመደበኛ በጀት የ8 ቢሊዮን ብር፣ ለክትባት 8 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ሌሎች የጤና ፕሮግራም ግብዓቶችን ጨምሮ ከ34 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሕክምና ግብዓቶች ግዥ ፈፅሟል። እነዚህም በመደበኛ በጀት፣ ከአገር ውስጥ አምራቾች፣ በጤና ፕሮግራም ግዥ፣ በተለያዩ አጋር ድርጅቶች የተገዙ እና በእርዳታ የተገኙ የሚገኙባቸው ሲሆን፤ በግዥ የገባ የክትባት መድኃኒትም ድርሻ አለው። በበጀት ዓመቱ በመደበኛ እና በጤና ኘሮግራም በድምሩ የ29 ቢሊዮን 184 ሚሊዮን 314 ሺህ 496 ከ26 ብር ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶች፣ ሪኤጀንቶች፣ የሕክምና መገልገያዎችና መሣሪያዎች ለጤና ተቋማት ተሰራጭተዋል፡፡ የሕይወት አድንና የመሰረታዊ መድኃኒቶች አቅርቦት አፈፃፀም በመደበኛ

81 ነጥብ 5 በመቶ እና በጤና ኘሮግራም 94 ነጥብ 6 በመቶ ነው። የሕክምና ግብዓቶች አቅርቦት የመገኘት ምጣኔ እንደ አገር ከላይ የተገለጸው ቢሆንም የአንዳንድ ቅርጫፎችና ጤና ተቋማት በቂ በጀት ይዞ አለመግዛት፣ የጤና ተቋማት ቀደም ብለው ለወሰዱት የዱቤ ግዥ ክፍያ አለመፈፀም እንዲሁም በአንዳንድ የአገሪቷ አካባቢዎች ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት አቅርቦቶቹ በተመሳሳይ ሁኔታ የመገኘት ምጣኔ እንዳይኖራቸው አድርጓል። በመሆኑም አገልግሎቱ በአገር አቀፍ፣ በቅርጫፎቹ እና በጤና ተቋማት መካከል ያለውን የአፈፃፀም ልዩነት ለማጣጣም አልሞ እየሰራ ይገኛል። አገልግሎቱ የመድኃኒት አቅርቦቱን ለማሻሻል ካስቀመጠው ዕቅድ የአገር ውስጥ አምራቾችና አቅራቢዎችን በማበረታታት የሕይወት አድን መድኃኒቶችን ፍላጎት በአገር ውስጥ አምራችች ለሟሟላት መጠነ ሰፊ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ በዚህ መሰረት በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት አምራቾቹ ከ4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶችን ለመግዛት የተዋዋሉ ሲሆን ከተገባው የአቅርቦት ውል ውስጥ የ2 ቢሊዮን 277



70

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ሚሊዮን 130 ሺህ 956 ብር ዋጋ የሚያወጡ መድኃኒቶችን አቅርበዋል አፈፃፀማቸውም 36 በመቶ ነው። አፈጻጸሙ በ2015 በጀት ዓመት ከነበረው ሥምንት በመቶ አንፃር ዕድገት ያሳየ ሲሆን ለዚህም ለአምራቾቹ 55 በመቶ የሚሆን የምርት አቅርቦት ጥምርታ የውጭ ምንዛሬ መፈቀዱ በዋነኝነት ይጠቀሳል። የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአገሪቷ የፀጥታ ችግር በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለወረርሽኝ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን አቅም በፈቀደ መልኩ ለማቅረብ ከፍተኛ ርብርብ ማድረጉ፤ የጤና ተቋማትን የቀጥታ ስርጭት (Last Mile Delivery) ለማጠናከር የሚያገለግሉ ተሽከርካሪዎች ማቅረቡ፤ የመድኃኒት ብልጫና ጉድለት ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑና በፍጥነት ማጠናቀቅ መቻሉ፣ አጭር የመጠቀሚያ ጊዜ ያላቸው እና ዝቅተኛ እንቅስቃሴ ያላቸውን ግብዓቶች ከቅርንጫፍ ወደ ቅርንጫፍ በማዘዋወር ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ብክነት መቀነስ መቻሉ፣ ከባለድርሻ አካላትና አጋር ድርጅቶች ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከሩ፤ የመድኃኒት ብክነትንና እጥረትን ለመቀነስ በየወሩ የክምችት መረጃ ትንተና በመስራት

ክትትል መደረጉ፤ በተቋሙ መጋዘኖች ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ለመከላከል የሚያስችሉ ቁሳቁሶች ማሟላት እና የአጠቃቀም ሥልጠናዎች መስጠቱ እና ሌሎችም በጥንካሬ የሚጠቀሱ ተግባራቱ ናቸው። በአንፃሩ የአገር ውስጥ አቅራቢዎች መድኃኒቶችን በገቡት ውል፣ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ አለማቅረባቸው፤ ቅርንጫፎች የሽረት ጊዜያቸው የተቃረቡ መድኃኒቶችን በመሸጥና ለመንግሥት ጤና ተቋማት በማሰራጨት ጥቅም ላይ እንዲያውሉ መመሪያ ቢተላለፍም ተግባራዊ አለማድረጋቸው፤ የኮንትራት አስተዳደር ሥርዓት ሲስተም (CMS) ዘላቂነት ባለው መልኩ ጊዜውን ጠብቆ አለመጠቀም፤ Zero Demurrage initia- tive’ን በተፈለገዉ መልኩ አለማሳካት፤ ከባንኮች እና ከአቅራቢዎች የሚፈለጉ ሰነዶችን በሚፈለገው ፍጥነትና በተሟላ መልኩ አለማቅረብ፣ የኮንትራት አስተዳደር ሲስተም (CMS) በሚፈለገው ልክ አለመተግበሩና የሚፈለጉ መረጃዎችን በተሟላ መልኩ አለማግኘት፤ LC ለመክፈት የውጭ ምንዛሪ እጥረት መከሰት፤ በአንዳንድ አካባቢዎች በጸጥታ መደፍረስ ሳቢያ ግብዓቶችን በየብስ ትራንስፖርት ለማድረስ



71

አለመቻልና በአየር ትራንስፖርት መድኃኒቶችን ለማጓጓዝ ከፍተኛ ወጪ መጠየቁ፤ የስርጭት ተሽከርካሪዎች ተደጋጋሚ ብልሽት፣ በአገልግሎት ብዛት ማርጀትና ለረጅም ጊዜ በጥገና ላይ መቆየት፤ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የመድኃኒት አቅርቦት እጥረትና ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት፤ ጤና ተቋማት የዱቤ ውል ጊዜያቸውን ጠብቀው ክፍያ መፈጸም አለመቻላቸው፤ የአገር ውስጥ አምራቾች በአቅርቦት ውላቸው መሰረት አምርተው ማቅረብ

አለመቻል፤ ለመድኃኒቶችና ሌሎች ተያያዥ ግብዓቶች ግዥ የሚውል ገንዘብ ከጤና ሚኒስቴር እና ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ወቅቱን ጠብቆ ወደ አገልግሎቱ አለመተላለፍ፤ ከፍተኛ የሆነ የተቆራረጠ የግዥ ጥያቄ መኖሩ መድኃኒት በወቅቱ ገዝቶ ለማቅረብ ፈታኝ መሆኑ፤ የአቅራቢዎች ውል በገቡበት ዋጋ ለማቅረብ ፍቃደኛ አለመሆን፣ ውል መሰረዝና በአንዳንድ ግብዓቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መጠየቅ፤ የመድኃኒቶች ስርጭት የአገልግሎት ተከፋይ

ተሰብሳቢ ሂሳቦች በወቅቱ ከጤና ሚኒስቴር መሰብሰብ አለመቻል፤ የመረጃ ልውውጥ ከፍተኛ ችግር መኖር፣ ተናቦ ያለመስራትና የወጥነት ችግር፤ መደበኛ የግዥ ትዕዛዞች በEFDA ለማፀደቅ ረጅም ጊዜ መውሰዳቸውና የኬሚካል ግብዓቶች የግዥ ትዕዛዝ ለማፅደቅ በEFDA መዘግየት መፈጠሩ እና ግብዓቶች አጭር የመጠቀሚያ ጊዜ ይዘው ወደ ማከማቻ መጋዘን መግባት አገልግሎቱን የፈተኑ ችግሮች ናቸው።



72

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ኢኮኖሚ

አረንጓዴ አማራጭ



73

የፕላኔታችንን ሥር ነቀል ለውጥ የሚወክሉ ሦስት አጫጭር ቃላት - የአየር ንብረት ለውጥ። እነዚህ ቃላት ከቁጥራቸው በላይ የገዘፉና ብዙ የተባለላቸው ናቸው። ዓለም ስለ እነዚህ ቃላት አብዝቶ ተነጋግሯል፣ መክሯል፣ ጽፏል። አሁን አሁን የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክቶ የሚፃፉ መጣጥፎች እንደ እውነተኛ የወንጀል ታሪክ (True Crime-story) በስፋት የሚነበቡ ሆነዋል። እርግጥ ነው የበዙት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ታሪኮች በአርክቲክ እና በአንታርክቲካ የምድራችን ገፆች በሚከሰቱት ለውጦች ላይ ያተኮሩ ናቸው። ከዚህ ሻገር ካለም የአውሮፓና የአሜሪካ የአየር ንብረት ስለሚኖረው ተጽዕኖ ሲነገር ነው የሚደመጠው። በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የከፋ ጉዳት ሰለባ የሆኑት የአፍሪካ አገራት ጉዳይ ግን አርክቲክ እና

በጌታቸው ያለው



74

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

አንታርክቲካን አስመልክተው በሚነገሩ ትርክቶች ሲዳፈኑ ይስተዋላል። ያም ተባለ ይህ ግን በሁሉም የምድራችን አካባቢ የሙቀት መጠን በአስፈሪ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። ድፍን ዓለም በለውጡ ጫና ስጋት ይገባው ጀምሯል። ይህ እውነት አሁን ዓለምን አረንጓዴ አማራጮችን ማስፋት ግድ የሚላት ጊዜ ላይ አድርሷታል። እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1961 ስዊዘርላንድ ውስጥ የተመሰረተው ዓለም አቀፉ የተፈጥሮ ፈንድ (The World-Wide Fund for Nature-WWF) ከዓመታት በፊት ያሳተመው ጽሑፍ በወቅቱ ዓለምን ያነጋገረ ነበር። በረሃማነትን በመከላከል እና የሰው ልጅ በተፈጥሮ አካባቢ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ በመቀነስ ላይ የሚሰራው ይኸው ድርጅት ዓለም ትኩረቱን በ2020 የቶኪዮ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ ባደረገበት ወቅት “ኦሊምፒክ በ2048 ምን ሊመስል ይችላል” በሚል ርዕስ ይዞት የወጣው ጽሑፍ የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። “ፕላኔታችንን ማውደም ከቀጠልን ኦሊምፒክ በ2048 ምን ሊመስል ይችላል…?” በሚል ተጠየቅ የተዘጋጀው መጣጥፉ የአየር ንብረት ለውጥ የሚፈጥረውን ምስቅልቅል የኦሊምፒክ ጨዋታዎችን

በማሳያነት ወስዷል። አንባቢያን ጽሑፉን ሲያነቡ ወደፊት ሊፈጠር ስለሚችለው አስፈሪ ሁኔታ እንዲያስቡ አድርጓል። መጣጥፉ ለማሳያነት ከተጠቀማቸው ምስሎች መካከል ሁሉም ተወዳዳሪ አትሌቶች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አድርገው መሮጥ ግድ ሲሆንባቸው ነው። በአሃዛዊ ማስረጃ የተደገፉት እነዚህ ምስሎች የአየር ንብረት ለውጥ አደጋን መግታት ካልተቻለ ስፖርታዊ ውድድሮች ምን ሊመስሉ እንደሚችሉ ትንቢታዊ ምልከታውን አስፍሯል። ያም ሆኖ በብዙ የዓለም ክፍሎች የአየር ብክለት ደረጃ በአደገኛ ሁኔታ ከፍተኛ ሆኖ እንደሚቀጥል እየተገለጸ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣው አዲስ መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም ላይ ከ10 ሰዎች ዘጠኝ ያህሉ ከፍተኛ የብክለት መጠን ያለው አየር ይተነፍሳሉ። በተጨማሪም ሰባት ሚሊዮን ያህል ሰዎች በተበከለ አየር ውስጥ ለጥቃቅን ቅንጣቶች በመጋለጥ ወደ ሳንባ፣ ልብና የደም ሥር (Cardiovascular System) ዘልቀው በመግባት ስትሮክ፣ የልብ ሕመም፣ የሳንባ ካንሰር፣ ሥር የሰደደ የሳንባ ምች በሽታዎች እና በመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን በመጠቃት ለሞት ይዳረጋሉ።

“የምንወዳቸውን ስፖርቶች ለማስቀጠል እና በጋራ እንድንሰባሰብ ከፈለግን ፕላኔታችንን ለመጠበቅ በጋራ ልንሰራ ይገባል” ሲል የዓለም የጤና ድርጅት ምክረ ሃሳቡን አስቀምጧል። ይህ እንግዲህ የአየር ንብረት ለውጥ ከጤና አኳያ የሚያደርሰው ጉዳት ሲሆን በአንፃሩ በዓመት 24 ቢሊዮን ቶን ጤናማ አፈር ከምድር ገጽ እንደሚጠፋ ጥናቶች ያሳያሉ። ምድራችን ላይ ካለው አፈር ግማሹ ባለፉት 150 ዓመታት በደን ጭፍጨፋ፣ ልቅ በሆነ ግጦሽ፣ ዘላቂነት በጎደለው ግብርና እና የመሬት አጠቃቀም እንዲሁም በብክለት እና ከአየር ንብረት ቀውስ ጋር ተያይዞ ጠፍቷል። ለአየር ንብረት ለውጥ የበዙ መንስኤዎች ያሉ ሲሆን የነዳጅ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች በካይ ጋዞችን በማመንጨት አሉታዊ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ የሚጠቀሱ ናቸው። እነዚህ በካይ ጋዞች የአየር ንብረት ለውጥ በማስከተል የሰው ልጅ ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች እንዲጋፈጥ አድርገውታል። በዚህም ከተፈጥሮ ምንጮች፣ ከዘመናዊ የሳተላይት እና ሌሎች መሣሪያዎች የተወሰዱ ሣይንሳዊ መረጃዎች ዓለማችን ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት እየሞቀች ስለመሆኗ በማያሻማ



75

ማስረጃ ያሳያሉ። በዓለም ታሪክ የምድር የአየር ንብረት ለውጥ የነበረ ቢሆንም አሁን ያለው የሙቀት መጨመር ግን ባለፉት 10 ሺህ ዓመታት ውስጥ ባልታየ ፍጥነት መሆኑ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል። የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎች በሰው ልጆች ላይ የሚያደርሱት ጉዳት እጅግ አስፈሪነት መሰማት ከጀመረ ዋል አደር ብሏል። በተለይ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ወዲህ ያለው የለውጥ መጠን ከሺህ ዓመታት በፊት ታይቶ የማይታወቅ እንደሆነ ነው የምርምር ውጤቶች የሚያስረዱት። አብዛኛዎቹ የአየር ንብረት ለውጦች ምድራችን

የምትቀበለውን የፀሐይ ኃይል መጠን በሚቀይሩት በመሬት ምህዋር ላይ ባሉ በጣም ትንንሽ ልዩነቶች ምክንያት ነው። በዋናነት ግን የሰው ልጅ ሥልጣኔ ከመጀመሩ ጋር ተያይዘው በመጡ ነባራዊ ሁኔታዎች እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ። ተሽከርካሪዎች በየዓመቱ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ቶን ያህል የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት (Greenhouse Gases-GHGs) በአብዛኛው በካርቦን ዳይኦክሳይድ መልክ ወደ ከባቢ አየር ይለቃሉ። አንድ የነዳጅ ተሽከርካሪ በየዓመቱ ከ5 እስከ 9 ቶን ያህል አማቂ የጋዝ ልቀት (GHG) ወደ ከባቢ አየር እንደሚለቅ ጥናቶች ያሳያሉ። ይህ የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ



76

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ ያደርጋል። የብክለት መቆጣጠሪያ መሳሪያዎች የተሽከርካሪን የካርበን ዳይኦክሳይድ ልቀት እምብዛም መቀነስ እንደማይችሉ ምርምሮች ያስረዳሉ። ይልቁንም ነዳጅ ቆጣቢ አልያም ብዙም ካርበን አመንጪ ያልሆኑ እንደ ኢታኖል ያሉ የኃይል አማራጮችን መጠቀም እንዲሁም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም ልቀቱን ለመቀነስ ጠቃሚ አስተዋጽኦ አላቸው። በአየር ንብረት ለውጥ የበይነ መንግሥታት ፓነል (The Inter- governmental Panel on Cli- mate Change-IPCC) የአየር ንብረት ለውጥን፣ አንድምታውን እና ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን አስመልክቶ ለፖሊሲ አውጪዎች በየጊዜው ሣይንሳዊ ግምገማዎችን ያቀርባል። በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን፣ የወደፊት ስጋቶችን እና የመላመድ እንዲሁም የመቀነስ አማራጮችን በየጊዜው እየገመገመ ያቀርባል። የዓለም የሙቀት መጠን ከሁለት ዲግሪ ሴልሺየስ በታች እንዲገደብ እንደ ካርቦን ዳይኦክሳይድ ያሉ የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀቶችን በፍጥነት የመቀነስ ሥራንም ይቆጣጠራል። የበይነ መንግሥታት ፓነሉ

በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ከተሽከርካሪ የሚለቀቀው የካርቦን ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን በማውሳት የካርቦን ልቀት እና የነዳጅ አጠቃቀምን ለመቀነስ መንግሥታት ፖሊሲ ከመቅረጽ ባለፈ ሥራ ሊሰሩ እንደሚገባም ያስገነዝባል። ኢትዮጵያ ይህን ተገንዝባ አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም የሚያስችሉ እርምጃዎችን በመውሰድ የሚደነቅ ሥራ እየሰራች ትገኛለች። በተለይ ሐምሌ 2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው አገራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የተራቆተ መሬት በዕጽዋት እንዲሸፈን በማድረግ የአየር ንብረት ለውጥ ሚዛንን ለመጠበቅ እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠቃሽ ነው። የችግሩን ስፋትና ጥልቀት እንዲሁም ከዓለም የነዳጅ ዋጋ ማሻቀብና መውረድ ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ጭምር ታሳቢ በማድረግ አሁን ላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አማራጭ ተስፋ ይዘው ብቅ ብለዋል። ዓለምም ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ፊቱን ማዞሩ እየተስተዋለ ነው። ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪን አስመልክታ



77

የያዘችው አቋም ምን ይመስላል…? በዚህ ጽሑፍ የሚቃኝ ይሆናል። የዕድገት አዝማሚያዎች እ.ኤ.አ በ2023 ከተሸጡ አምስት ተሽከርካሪዎች መካከል አንዱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ እንደሆነ ዓለም አቀፍ የኢነርጂ ኤጀንሲ መረጃ ያሳያል። በዚያው ዓመት ብቻ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሽያጭ 14 ሚሊዮን ደርሷል። በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አጠቃላይ ቁጥር ወደ 40 ሚሊዮን መድረሱን እ.ኤ.አ በ2023 የወጣው የግሎባል የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሽያጭ መጠቆሚያ (Global EV Outlook-GEVO-2023) ያሳያል። በ2024 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሽያጭ ጠንካራ ሆኖ በመቀጠል ከቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው በ25 በመቶ ብልጫ ማሳየት ችሏል። እነዚህ አዝማሚያዎች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ገበያ እያደገ መሄዱ ብቻ ሳይሆን ዕድገቱ ጠንካራ ሆኖ እንደሚቀጥል ያመለክታሉ። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ምርትና ሽያጭ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ ቢሆንም ሽፋኑ ግን በጥቂት ዋና ዋና በሚባሉ

ገበያዎች ላይ የተከማቸ ነው። የቻይና፣ የአውሮፓና የአሜሪካ ገበያዎች ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ። ለአብነት በዚሁ ዓመት ከተመዘገቡት አዳዲስ ተሽከርካሪዎች በቻይና ከሦስቱ አንዱ፣ በአውሮፓ ከአምሥቱ አንዱ እንዲሁም በአሜሪካ ከአሥሩ አንዱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ናቸው። እነዚህ አገራት ከጠቅላላ የተሽከርካሪ ሽያጭ ሁለት ሦስተኛውን ይወክላሉ። ይህም ማለት በእነዚህ ገበያዎች ውስጥ ያለው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሽግግር ከዓለም አቀፋዊ አዝማሚያዎች አንፃር ትልቅ እመርታ የሚታይበት መሆኑ ነው። በተጨማሪ ቻይና እ.ኤ.አ በ2023 ከአራት ሚሊዮን በላይ ተሽከርካሪዎችን ወደ ውጭ የላከች ሲሆን ይህም በዓለም ላይ ግዙፍ የኦቶሞቲቭ ላኪ አገር አድርጓታል። ከእነዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ያህሉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መሆናቸው የዕድገቱ አዝማሚያ ወዴት እያመራ እንደሆነ አመላካች ነው። በአዳጊ ገበያ እና በማደግ ላይ ባሉ ኢኮኖሚዎች (Emerg- ing Market and Develop- ing Economies-EMDEs) የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች

ሽያጭ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ቀጥሏል። ትንበያዎች እንደሚያሳዩት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቁጥር እ.ኤ.አ በ2040 ከ254 እስከ 937 ሚሊዮን ሊደርሱ እንደሚችሉ ነው። ይህም ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የሚደረገው ሽግግር በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ ስለመምጣቱ አሁናዊ አዝማሚያው ይጠቁማል። የነዳጅ ፓለቲካ እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ዕድገት አሁን ከደረሰበት ደረጃ ከመድረሱ በፊት ከነዳጅ አምራቾችና ሻጮች፣ ከመደበኛ ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያዎች፣ ከጋራዥ ባለቤቶች፣ ከደላላዎች ብሎም ከፖለቲከኞች የገጠመውን ቀላል የማይባል ፈተና ማለፍ ነበረበት። ዕድገቱ አልጋ በአልጋ አልነበረም። ይህን ጉዳይ እ.ኤ.አ በ2006 የተሰራን አንድ ዘጋቢ ፊልም በመዳሰስ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ዕድገት ፈተና እና የነዳጅ ፖለቲካን እንመልከት። ዘጋቢ ፊልሙ who killed the Electric Car? በግርድፍ ትርጉሙ ‘የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪውን ማን ገደለው?’ እንበለው። ፊልሙ በዘመናዊው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ዕድገትና መክሰም ዙሪያ የተወሳሰቡ ትዕይንቶችን



78

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

የሚያሳይ ነው። ኃያል ስሜታዊነት እና የነዳጅ ፖለቲካ ምስቅልቅልነት የሚንጸባረቅበት ጠንካራና በጣም አሳማኝ ዘጋቢ ፊልም ነው። በክሪስ ፔይን ዳይሬክት የተደረገው ይኸው ዘጋቢ ፊልም በአሜሪካ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪን አፈጣጠር፣ የገበያ ሁኔታ እና መክሰምን የሚዳስስ ሲሆን በተለይ በ1990ዎቹ አጋማሽ ጄኔራል ሞተርስ የሰራቸው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ዕጣ ፈንታ ላይ ያጠነጠነ ነው። ፊልሙ የዚህን ቴክኖሎጂ ዕድገትና አጠቃቀም በመገደብ የአውቶሞቢል አምራቾችን፣

የነዳጅ ኢንዱስትሪን፣ የአሜሪካን ፌዴራል መንግሥት፣ የካሊፎርኒያን ግዛት መንግሥት፣ የኤሌክትሪክ እና የሃይድሮጂን ተሽከርካሪዎችን እና ሸማቾችን ሚና ይዳስሳል። በተጨማሪ ፊልሙ ስለ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ታሪክ፣ ስለ ዘመናዊ ዕድገቱ እና ስለ ግብይቱም ያስቃኛል። በካሊፎርኒያ የአየር ብክለትን በመቀነስ የአካባቢ ጥራት እና የሕዝብ ጤናን ለማሻሻል የተቋቋመው የአየር ኃብቶች ቦርድ (California Air Re- sources Board-CARB) እ.ኤ.አ. በ1990 ዜሮ የጋዝ ልቀት ተሽከርካሪዎች (Ze- ro-Emission Vehicle-ZEV)



79

ገቢራዊ እንዲሆኑ የሚያደርግ ውሳኔ ያሳልፋል። ውሳኔውም በአሜሪካ የሚገኙ ግዙፍ የመኪና አቅራቢዎች ካሊፎርኒያ ውስጥ በነዳጅ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን ሽያጭ ለመቀጠል ከፈለጉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን እንዲያቀርቡ የሚያስገድድ ነበር። ከአውቶሞቢል አምራቾች በደረሰበት ክስ እና ብርቱ ጫና እንዲሁም ከነዳጅ ኢንዱስትሪው ያጋጠመው የማያቋርጥ ፍጥጫ ይባስ ብሎ በጆርጅ ደብሊው ቡሽ አስተዳደር የተቀነባበረ ሴራ ቦርዱ ቀደም ሲል ያሳለፈውን ውሳኔ በመቀልበስ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መፃኢ ዕድል ላይ አሉታዊ ጥላ ሲያሳርፍ ፊልሙ ያሳያል። በዚህ ውሰኔ ሳቢያ በወቅቱ በክሪስለር፣ በፎርድ ሞተር ኩባንያ፣ በጄኔራል ሞተርስ (GM)፣ በሆንዳ፣ በኒሳን እና በቶዮታ ዲዛይን ተደርገው የተመረቱ አምሥት ሺህ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እንዲወድሙና ገሚሶቹም ለሙዚየሞችና ለዩኒቨርሲቲ የምርምር ተቋማት እንዲለገሱ ተደርገዋል። ዘጋቢ ፊልሙ የአውቶሞቢል እና የነዳጅ ኢንዱስትሪዎች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪን ለማክሰም ምክንያት ያሏቸውን

ጉዳዮች ለመዳሰስ ሞክሯል። በዋናነት የነዳጅ ኩባንያዎች በነዳጅ ላይ ያላቸውን ሞኖፖሊ ያሳጣናል የሚለው ስጋት አንዱ ነው። ሌላው የመደበኛ ተሽከርካሪ ኩባንያዎች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አነስተኛ ወጪ ብቻ የሚፈልጉ መሆናቸውና በነባሩ ተሽከርካሪ ላይ ብልጫ በመውሰድ ለገቢ ኪሳራ ይዳርገናል ከሚል ስጋት የመነጨ መሆኑን አሳይቷል። የአየር ብክለት፣ የነዳጅ ጥገኝነት፣ የመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ እና የዓለም ሙቀት መጨመር አንድምታ በፊልሙ የተዳሰሰ ቢሆንም ከላይ የተወሰነውን አሉታዊ ውሳኔ ማስቀረት ግን አልቻለም። በአጭሩ በፖለቲከኞች ጭምር የሚደገፈው ግዙፉ የነዳጅ ኢንዱስትሪ ከአካባቢ ጥበቃ ይልቅ የገንዘብ ፍላጎቶችን በማስቀደም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መስፋፋትን አጥብቆ ይቃወማል። ‘የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪውን ማን ገደለው…?’ የሚለው ዘጋቢ ፊልም ከተሰራ ከአምሥት ዓመት በኋላ ክሪስ ፔይን ዳግም Revenge of the Electric Car የሚል ሌላ ዘጋቢ ፊልም ሰርቶ ለዕይታ አብቅቷል። ክሪስ ፔይን የፊልም ሠራተኞቹን ከኒሳን፣ ከጄኔራል ሞተርስ እና ከሲልከን ቫሊ የቴስላ ሞተርስ

በሮች ጀርባ ወስዶ ዓለም አቀፍ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን የማንሰራራት ታሪክ የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም ሰርቷል። በፊልሙም ከነዳጅ ይልቅ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከብክለት የፀዱና የአዲሱ ትውልድ ፈጣንና ምቹ ተሽከርካሪዎች ስለመሆናቸው አሳይቷል። ፊልሙ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ያለአግባብ መወገዳቸውን የሚተርክና አራት ጉምቱ የፈጠራ ሰዎች ማለትም ኢሎን ማስክ፣ ካርሎስ ጎስን፣ ቦብ ሉትዝ፣ እና ‘ተገደሉ’ የተባሉትን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ‘ከሞት’ ለመመለስ ከባድ ጥረት ያደረጉ መካኒኮችን ትዕይንት ለእይታ አብቅቷል። ከጄኔራል ሞተርስ ኪሳራ እስከ ቴስላ ሞተርስ ስታርት አፕ ጥረት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ዳግም እንዲያንሰራራ የተወሰደው ጣፋጭ በቀል በፊልሙ ተተርኳል። አሁን የዓለም የነዳጅ እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የፖለቲካ አካሄድ ተቀይሮ አዲስ መልክ ይዟል። የአየር ንብረት ለውጥ እየፈጠረ ያለው ጫና አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተከትሎ የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ቅነሳ የተለየ ትኩረት አግኝቷል። ይህን ለማሳካት ደግሞ በነዳጅ የሚንቀሳቀሱ



80

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ተሽከርካሪዎች አጠቃቀም ላይ ቅነሳ እንዲደረግ ዓይነተኛ አማራጭ ሆኖ ቀርቧል። በዚህ የተነሳ ግዙፍ የመኪና አምራች ኩባንያዎች ሁሉም በሚባል ደረጃ አዳዲስ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሞዴሎችን ለማምረት ቀን ከሌት ሲጥሩ ይታያሉ። ምርጥ ለመሆን እና በዓለም ዙሪያ ያሉ ሸማቾችን ቀልብ ለመሳብ ሩጫ ላይ ናቸው። እንዲያም ሆኖ ከድጎማ እና ከታሪፍ ፖለቲካ ጋር ተያይዞ አሁንም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በዓለም ዙሪያ የፖሊሲ አውጪዎችን ትኩረት እንደሳቡ ቀጥለዋል። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዓለም ፊቱን ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ እያዞረ መምጣቱን በየጎዳናው የሚርመሰመሱ የበዙ ተሽከርካሪዎች ማሳያ ናቸው። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሽያጭም በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ነው። እንደ ኖርዌይ፣ አይስላንድ፣ ስዊድን፣ ኔዘርላንድስ እና ቻይና ያሉ አገራት ደግሞ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በስፋት ከሚጠቀሙ አምስት የዓለማችን አገራት ቀዳሚዎቹ ናቸው። በምድራችን እ.ኤ.አ በ2024 ከተሸጡት የመንገደኞች ተሽከርካሪዎች መካከል 10 በመቶ

የሚሆኑት በሙሉ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መሆናቸውን የዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ መረጃ ያሳያል። ይህ ከአምሥት ዓመታት በፊት ከነበረው በ10 እጥፍ የበለጠ ነው። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በካይ የጋዝ ልቀትን የማያመነጩ በመሆናቸው በነዳጅ ከሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ይልቅ ተመራጭ እየሆኑ መጥተዋል። የእነዚህ ተሽከርካሪዎች በስፋት አገልግሎት ላይ መዋል የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እየተደረጉ ካሉ ጥረቶች በጣሙን ጠቃሚ እርምጃ እንደሆነ ነው የሚነገረው። የዓለምን ሙቀት መጨመር ወደ 1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺዬስ ዝቅ ለማድረግ እና ብዙ ጎጂ ተጽዕኖዎችን ከአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል ከዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ግቦች ጋር በማጣጣም እ.ኤ.አ በ2030 የመንገደኞች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሽያጭ ከ75 እስከ 95 በመቶ ያህል እንዲሆኑ ምክረ ሃሳብ ቀርቧል። ከነዳጅ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚደረገው ሽግግር በመንግሥታትም ሆነ በግዙፍ ኮርፖሬሽኖች ለረጅም ጊዜ ሲታሰብበት የቆየ ብርቱ ጉዳይ ነው። ጉዳዩ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ

እና አካባቢያዊ ጥቅሞችን ታሳቢ ያደረገ ዕመርታዊ ለውጥ ስለመሆኑም በምክንያትነት ያስቀምጣሉ። በቴክኖሎጂ እና በዘርፉ መሠረተ ልማት በኩል የሚስተዋሉ መሰናክሎች እየተቀረፉ መምጣታቸው ደግሞ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚደረገው ሽግግር በሚቀጥሉት አሥርት ዓመታት ውስጥ ጎልቶ እንዲታይ መደላድሉን ፈጥሯል። በጥቅሉ ዓለም ነዳጅ ከሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች እየተላቀቀች ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እየሄደች ነው። ኢትዮጵያም ከዚህ ማዕቀፍ ውጭ አለመሆንን መርጣ ወደዚያው እያመራች ነው። ዝም ብሎ ማምራት ብቻ ግን አይደለም። እንደ አገር ዕቅድ ነድፋ በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ ዘርፉ በተጨባጭ መሬት የሚያርፍበት ሥራም እየተሰራ ነው። ከዚህ አኳያ በሁለተኛው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕቅድ የትራንስፖርት ዘርፍ ትልም ውስጥ ታዳሽ ኃይል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪን አስመልክተው በአንድ ወቅት ያነሱት ሃሳብ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ በብዙ መልኩ ለኢትዮጵያ



81

የሚያስፈልጋት ቴክኖሎጂ ስለመሆኑ አስምረውበታል። ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ ተሸከርካሪ የተለየ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። ኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የተለየ ትኩረት ማድረጓ ምክንያቱ ምንድን ነው? የሚለውን አንኳር ጉዳይ እዚህ ላይ ማንሳቱ ተገቢነት አለው። አንድም ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ፀጋ የታደለች አገር መሆኗ ተጠቃሽ ነው። ዓመቱን ሙሉ የፀሐይ ብርሃን የምታገኝ በመሆኗ የፀሐይ ኃይል አቅርቦት ከፍተኛ የሆነባት አገር ናት። ውኃን መሰረት ያደረገው ሃይድሮ ኤሌክትሪክና የታዳሽ ኃይል አቅሟም ሰፊ ነው። ይህ ዕምቅ ኃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋል አለበት የሚለው እሳቤ የትኩረቱ አንዱ መነሻ ነው። ሌላው የዓለምን የፖለቲካ- ኢኮኖሚ እየፈተነ ያለው የነዳጅ ጉዳይ ነው። በየጊዜው የሚያሻቅበው የነዳጅ ዋጋ የዓለምን ገበያ ብቻ ሳይሆን የኃይል ሚዛንን በማናጋት ፖለቲካዊ አንድምታውም በዛው ልክ ጫና ሲፈጥር ይስተዋላል። በእስራኤል እና በሃማስ ታጣቂ ቡድን መካከል ከወራት በፊት የተፈጠረው ግጭት ተባብሶ ከቀጠለ የነዳጅ ዋጋ አሁን

ካለው 78 ዶላር በበርሚል ወደ 150 ዶላር ሊደርስ እንደሚችል የዓለም ባንክ ማስጠንቀቁን ልብ ይሏል። እንደ ዓለም ባንክ ማስጠንቀቂያ ከሆነ ግጭቱ ከቀጠለ እና ነገሮች ወደ ከፋ ሁኔታ የሚለወጡ ከሆነ በ1970ዎቹ ከነበረው ዓለም አቀፍ የነዳጅ ቀውስ (Oil Shock) ጋር ተመሳሳይ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ማሳሰቡ የነዳጅን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ የሚያሳይ ነው። በተለይ ችግሩ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በመልማት ላይ ያሉ አገራት የነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ በአገራዊ ኢኮኖሚያቸው ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ ግልጽ ሆኖ የሚታይ ነው። የዚህ ቀውስ ሰለባ ላለመሆን ኢትዮጵያም ዓለምም አማራጭ ያሉትን ሁሉ መጠቀማቸው በጎ መሆኑ አያጠያይቅም። የኢትዮጵያ የ2016 ዓ.ም የነዳጅ ፍላጎት አራት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሲሆን አጠቃላይ አገራዊ የነዳጅ አቅርቦት በየዓመቱ በአማካይ 10 በመቶ ጭማሪ አለው። በተጠናቀቀው የ2016 ዓመትም አገሪቷ ለነዳጅ ያወጣችው ወጪ ከ4 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ነው። ይህም ከኤክስፖርት ግኝቷ በላይ መሆኑን ነው የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ባሬዮ ሀሰን የሚያስረዱት።



82

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ነዳጁ ወደ አገር ውስጥ ከገባ በኋላ በትይዩ ገበያ (ጥቁር ገበያ- Black Market) የሚዘዋወርበት አጋጣሚ ሰፊ በመሆኑ የጥራት ችግር ያጋጥመዋል። ይህንን የትራንስፖርት ዘርፉ ሲጠቀምበት ደግሞ የአካባቢ ብክለቱ የከፋና የካርቦን ልቀቱንም ከፍተኛ ያደርገዋል ነው የሚሉት። “ይህንን ችግር ለመግታት የውጭ ምንዛሬ ችግራችንን፣ አገሪቱ እፎይታ እንድታገኝ ከማድረግ አኳያም ዓለም እየሄደበት ያለው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ትግበራ አማራጭ ነው” ይላሉ። ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በስፋት የመጠቀሟ ጉዳይ በመንግሥት ልዩ ትኩረት አግኝቶ እየተሰራበት መሆኑን አብራርተዋል። በትራንስፖርት ዘርፍ የ10 ዓመት ዕቅድ ላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በሰፊው ጥቅም ላይ ለማዋል በአየር፣ በየብስና በባሕር ላይ የሚሻሻሉ ነገሮችን በማሻሻል የአገራዊ ታዳሽ ኃይል አጠቃቀምን የማስፋት ሥራ ተጀምሯል። ይህ ሲደረግ ደግሞ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶች መሰረት የተደረጉ ሲሆን የአየር ብክለትን መከላከል የዚህ አንዱ አካል ተደርጎ የሚሰራበት መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ግልጽ አድርገዋል። ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ስትራቴጂ ነድፋ ይፋ

አድርጋለች። ይህን ስታደርግ ግን ቀደም ሲል የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ጥቅም ላይ አውለው ስኬታማ ያልሆኑ እንደ ሕንድ ያሉ አገራት ውጤታማ ያልሆኑበት አካሄድ እንዳይገጥማት ይህንን ታሳቢ ያደረገ ሥራ በመሥራት፤ በሌላ በኩል የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪን ጥቅም ላይ በማዋል ቀድመው ከሄዱ እንደ ቻይና ካሉ አገራት በጎ ልምድ በመውሰድ የሁለቱም ተሞክሮ ተቀምሮ አገራዊ ስትራቴጂ ተደርጎ እንዲወሰድ ተደርጓል። በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽክርካሪ ገበያ በከፊል ከላይ የተጠቀሱት ፈተናዎች ሲገጥሙት ተስተውሏል። ያም ሆኖ አሁን በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ከቴስላ እስከ ቢ.ዋይ.ዲ (Build Your Dreams-BYD)፣ ከbz4x እስከ ቮልስ ዋገን ID-4, ID-6, ID-7 ያሉ የአሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በስፋት መታየት ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። ይህም ኢትዮጵያ በእርግጥም ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ በስፋት እየገባች ስለመሆኗ ማረጋገጫ ነው። መንግሥት በመስኩ እየተከተለ ያለው ፖሊሲም ከሕዝብ ጤንነትና ከአካባቢ ደህንነት አኳያ ተመዝኖ ይህንኑ የሚያበረታታ ነው። አስቻይ ሁኔታዎች መንግሥት የኤሌክትሪክ

ተሽከርካሪዎች በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ሲነሳ ይህን ማስፈጸም የሚያስችል መመሪያ አስፈላጊነትን አልዘነጋም። ይህን አስመልክቶ የፌዴራል መንግሥት አስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 ላይ ለትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የተሰጠው ኃላፊነት አለ። ይህም የትራንስፖርት ዘርፉ ለአካባቢ ተስማሚና ታዳሽ ኃይልን የሚጠቀም እንዲሁም ከአየር ብክለት የፀዳ እንዲሆን አድርጎ የመምራት ኃላፊነት ነው። የትራንስፖርት ዘርፍ ዕቅዱ በአዋጅ ለትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ከተሰጠና ሥራውን ከጀመረ ሦስተኛ ዓመቱን አስቆጥሯል። ይህን መነሻ በማድረግ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ስታንዳርድ ያላት አገር እንድትሆን ማድረግ ተችሏል። በአገር አቀፍ ደረጃ በደረጃዎች ኤጀንሲና በብሔራዊ ምክር ቤቱ አማካኝነት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ስታንዳርድ ጸድቋል። ከዚህ ቀደም ነዳጅ ሲጠቀሙ የነበሩ ተሽከርካሪዎች ወደ ኤሌክትሪክ የሚቀየሩበት ስታንዳርድም ፀድቋል። የእነዚህ ስታንዳርዶችና የአዋጁ መነሻ ለሥራው አስቻይ ሁኔታን



83

የሚፈጥሩ መሆናቸውን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ባሬዮ ሀሰን ባሬዮ አብራርተዋል። ከስትራቴጂውና ከስታንዳርድ በሻገር መንግሥት በታክስ በኩል ይህንን ዘርፍ የሚደግፍ አሰራር ዘርግቷል። ለአብነትም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ሙሉ በሙሉ ከውጭ የሚያስገባ ሰው 15 በመቶ የጉምሩክ ታክስ ብቻ እንዲከፍል ተደርጓል። ሌሎች ታክሶችን እንዲከፍል አይገደድም። ይህ ደግሞ ከነዳጅ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች አንፃር ሳቢ ሁኔታን የሚፈጥር ነው። በተመሳሳይ በአገር ውስጥ የሚገጣጠሙና የሚመረቱ ከሆነ ከታክስ ነፃ ይደረጋሉ። እንደ ሚኒስትር ዴኤታው

ገለፃ በዚህ በኩል አገራዊ ዕቅዱ እንደሚሳካ ማሳያዎች አሉ። በማሳያነትም በ10 ዓመት ውስጥ 148 ሺህ የቤት አውቶሞቢሎችን፣ 4 ሺህ 855 አውቶቡሶችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ታቅዶ በአጠቃላይ 80 ሺህ የሚሆኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ገብተዋል። አራት የሚሆኑ የመገጣጠሚያ ፋብሪካዎች ሥራ የጀመሩ ሲሆን የመኪና መለዋወጫዎችን የሚያመርቱና የሚያቀርቡ በርከት ያሉ ጋራዦችም ሥራ ጀምረዋል። ኢትዮጵያ በመጪዎቹ አሥር ዓመታት 376 ሺህ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ይኖሯታል የሚል የጥናት ግኝት በቅርቡ ይፋ ሆኗል። ለዚህ ደግም 2 ሺህ 300



84

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎች እንደሚያስፈልጉ ይኸው ጥናት አመላክቷል። በእርግጥ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎች በብዛት እንደማይገኙ አሽከርካሪዎች በቅሬታ የሚገልጹ ሲሆን ሚኒስትር ዴኤታውም የቅሬታውን ትክክለኛነት ተቀብለው፤ አሁን መንግሥት ጉዳዩን ገምግሞ በሰጠው ትኩረት መሰረት ሥራዎች እየተሰሩ ስለመሆናቸው አመላክተዋል። በመንግሥት የፌዴራል መዋቅሮች ውስጥ ዓለም እየሄደበት ያለው ፐብሊክ ቻርጀሮችን በማስፋፋት የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ ጥረት እየተደረገ ነው። በተለይ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎችን ለመገንባት ምቹ ሁኔታ የፈጠረ በመሆኑ በቀጣይ የሚሰሩ ሥራዎች ይኖራሉ ብለዋል። የቻርጂንግ መሰረተ ልማት መስፋፋት አስፈላጊ ነው። ቻርጀሩ ውድ አይደለም፤ ለማግኘትም ሰፊ ጊዜ የሚወስድ አይደለም። የሚያስፈልገው ቁርጠኝነት ብቻ ነው። በዚህ ረገድ የመንግሥት አቋም ጽኑ መሆን ትግበራውን የሚያፋጥን ይሆናል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን 80 ሺህ የሚጠጉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ይገኛሉ። በግልጽ

የሚታወቁና የተመዘገቡ 65 ቻርጅ ማድረጊያዎች አሉ። ሁሉም አስመጪዎች ቻርጀር እንዲተክሉ በመመሪያ ግዴታ ተጥሎባቸዋል። ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የሚያስገባ ማንኛውም አስመጪ ቻርጀር መትከል አለበት። ቻርጅ ማድረጊያ ሳይተክል ተሽከርካሪ አያስመጣም፤ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን የሚገጣጥም ከሆነ ደግሞ ሁለት ቻርጀር የግድ ሊኖረው ይገባል። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በቤት ውስጥ ቻርጀር ቻርጅ የሚደረጉ ናቸው። ነገር ግን ከሚወስደው ጊዜ አንፃርና የቤቱ ሁኔታ ምቹ ስለማይሆን በተለይ በአዲስ አበባ ቦታዎቹ ተለይተው በአጭር ጊዜ ውስጥ የቻርጀር ፍላጎቱን የሚያሟላ ሥራ እንደሚሰራ ሚኒስትር ዴኤታው አረጋግጠዋል። አሁን ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪን ቻርጅ አስመልከቶ የታሪፍ መመሪያ አዘጋጅታ ወደ ሥራ ገብታለች። የሚተከሉት ቻርጀሮች ፈጣንና ያልተቋረጠ የኃይል አቅርቦት ያስፈልጋቸዋል። ለዚህ ደግሞ የውኃ ኃብትና የኤሌክትሪክ ኃይል የተሰጣቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የቴክኒክ ኮሚቴ አቋቁመው እንቅስቃሴ ጀምረዋል። መንግሥት የቻርጀር ስታንዳርድ ራሱን ችሎ እንዲዘጋጅ አድርጓል።



85

በዚህም ፈጣን ቻርጀር የት ቦታ መጠቀም እንደሚገባ ሦስት ደረጃዎች እንዲወጡ ተደርጎ ወደ ትግበራ ተገብቷል። “ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ትግበራ ሲገባ ማንዋል አዘጋጅተን ነው የተጀመረው። ስታንዳርድ ካፀደቅን በኋላ ወደ መመሪያ እየቀየርን ነው። በመመሪያ የሚመለሱ ግራውንድ ላይ ቼክ የሚደረጉ በተለይ ከቮልስ ዋገን መኪና ትግበራ ጋር በውጭ አገር ያለውን ተሞክሮ ወስደን፣ አገር ውስጥ የገቡትን ሁኔታ አይተን፣ የጋራዦችን ዝግጁነት ተመልክተን፣ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ትስስር ለመፍጠር ጥረት አድርገን ነው” ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው ያስረዳሉ። የኢትዮጵያ ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት ይህንን ሥራ ወስዶ ሰርቶ ማሳያ አዘጋጅቶ ሀይብሪድ (Hybrid Cars) እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ እየሰራ ይገኛል። ጥገና ላይ ክፍተት እንዳይፈጠር ዩኒቨርሲቲዎች በሥርዓተ ትምህርታቸው ውስጥ አካተው እየሰሩ ነው። ለምሣሌ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን በማስተርስ ደረጃ ለመስጠት ወደ ትግበራ ገብቷል። አዳማ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ትግበራ በመግባት ዘርፉ በዕውቀት እንዲመራ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ

ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመሆን 1 ሺህ 311 ኢንዱስትሪዎች ለዚህ የሚሆን አስፈላጊ ግብዓት እንዲያቀርቡና ከነዳጅ ጥገኝነት ለመላቀቅ ውስጣዊ አቅም እንዲፈጠር መንግሥት በትኩረት እየሰራ ስለመሆኑ ሚኒስትር ዴኤታ ባሬዮ ሀሰን ግልጽ አድርገዋል። የሽግግሩ ሂደት ኢትዮጵያ አሁን ያሉት ተሽከርካሪዎቸ ወደ ታዳሽ ኃይል እንዲሸጋገሩ የመቀየሪያ ስታንዳርድ አፅድቃለች። በአገሪቷ እስከአሁን ተሽከርካሪዎችን በዕድሜ ከገበያ የማውጣት ሂደት አልነበረም። ከዚህ በኋላ ግን ተግባራዊ እንዲሆን መመሪያው ተጠናቆ ስታንዳርዱ ጸድቋል፤ መተግበሩም አይቀርም። የአፍሪካ የመንገድ ኮንቬንሽን (Africa Road Convention) እንዲሁም የቪየና ኮንቬንሽንን (Vienna Convention) የመሳሰሉ እንደ አገር የተፈረሙ ሕጎችም መተግበር አለባቸው። እነዚህ ተግባራዊ የሚደረጉት ለዓለም አቀፉ ስታንዳርድ ተብሎ ብቻ ሳይሆን ለዜጎች ጤና መጠበቅ ከማሰብ ጭምር ነው። ነዳጅ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች ወደ ኤሌክትሪክ የማይቀየሩበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ጋራዦችና ተቋማትም በዚህ ረገድ እየሄዱበት ነው። የቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት የቤንዚን የነበረን

ተሽከርካሪ ወደ ኤሌክትሪክ ቀይረው በተግባር አሳይተዋል። በዚህ ረገድ አቅም እየተገነባ በመሆኑ በሂደት ተግባራዊ የሚሆንበት ዕድል ሰፊ ነው። ዕድሜን መሰረት ያደረገ የተሽከርካሪዎች ትግበራ እንዲኖር መመሪያ ተዘጋጅቷል። በቅርቡ ፀድቆ ወደ ተግባር እንደሚገባም ይጠበቃል። ከደረጃ 1 እስከ 3 ባሉ፣ በልዩ አውቶቡስ ላይ ለምሣሌ ልዩ አውቶቡስ ከ7 ዓመት በኋላ ልዩ አውቶቡስ ሆኖ አይቀጥልም። አዲሱ የመንገድ ትራንስፖርት የስምሪት የብቃት ማረጋገጫና የምዝገባ መመሪያ ቁጥር 894/2015 ፀድቋል። መመሪያው ይህንንም ያዛል። በሂደት ወደ ሚገባቸው ምድብ እየወረዱ ይሄዳሉ። ሽግግር ማድረግ ያለባቸውም ስታንዳርዱን ተጠቅመው ከነዳጅ ወደ ኤሌክትሪክ የሚደረገውን ሽግግር የሚያከናውኑ ይሆናል። የሽግግሩን ሂደት ከሚፈትኑት ጉዳዮች መካከል ከገንዘብ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከፋይናንስ ተቋማት የሚያጋጥሙ መሰናክሎች ይጠቀሳሉ። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የገዙ ሰዎች ከፋይናንስ ተቋማት የብድር አገልግሎት እያገኙ አይደለም የሚል ቅሬታ በስፋት ይቀርባል። ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የባንክ እና የኢንሹራንስ ተቋማት እይታ ትክክለኛ አልነበረም።



86

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ኢንሹራንስ እንዲገቡ የማይፈቅዱባቸው ሁኔታዎች ነበሩ። ይህም በመንግሥትና በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተደረገው ሰፊ ጥረትና ርብርብ ጥሩ መሻሻል አሳይቷል። በዚህ ሂደት ውስጥ ግን ተጨማሪ ሥራ የሚፈልጉ ጉዳዮች እንዳሉ መገንዘብ ይገባል። ዜሮ በሚባል ደረጃ ባይሆንም መፈታት ባለበት ልክ ተፈቷል ሊባልም አይችልም፤ ጥረቱን አጠናክሮ መቀጠል የሽግግር ሂደቱንም ማፋጠን ያስፈልጋል። የተሽከርካሪ ገበያ ይታወቃል። እንደ ቋሚ ስቶክ ታይቶ የሚበደሩበት ቢዝነስ የሚያሰፉበት ሆኖ ሳለ፤ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪን በዚህ እይታ ያለማየት ችግር ይስተዋላል። በቶሎ ይበላሻል የሚል እሳቤ በመኖሩ። ባትሪው

ችግር አለበት የሚል የተሳሳተ ግንዛቤም አለ። እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ስለመሆኑ ተጠቃሚዎች ማረጋገጥ ችለዋል። በአዲስ አበባ እየተሰራ ያለው የኮሪደር ልማት ለፓርኪንግ እና ቻርጅ ማድረጊያ ቦታዎች እንዲሁም የመንገድ ሥራዎች ሽግግሩን ለማፋጠን የሚረዱ መሆናቸውን ልብ ይሏል። ዕድሜን መሰረት ያደረገ ምዝገባ በመመሪያው መሰረት ተግባራዊ ሲደረግ ዕድሜ ጠገብ ተሽከርካሪዎችን ከአገልግሎት ለማስወጣት ያለመ ሳይሆን በቴክኖሎጂ ታግዘው ተጨማሪ ዓመታትን እንዲያገልሉ ለማስቻል ነው። ዝግጁነት ካለ፣ መመሪያውን ተቀብለው ተግባራዊ የሚያደርጉ ከሆነ፣ አንድም ልቀትን ለመቀነስ፤ ሁለትም አደጋን መከላከልን

ታሳቢ ከማድረግ ባለፈ ሽግግሩ እነሱን ከአገልግሎት ውጭ የሚያደርግ አይሆንም። የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ቀደም ሲል የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ በኢትዮጵያ ገበያ የነበረው ምልከታ የተዛባ እንደነበር ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። ከላይ ለማንሳት እንደተሞከረው ልክ እንደ ዓለም አቀፉ ገበያ ሁሉ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ፍላጎት ከግንዛቤ ማነስ፣ ከደላላዎች ፍላጎት አንፃር፣ ከነዳጅ አቅራቢዎችና ሻጮች እንዲሁም ከጋራዥ ባለቤቶች የሚንፀባረቅ አሉታዊ አተያይ ነበር። ለረጅም ዓመታት በነዳጅ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ተሽከርካሪዎችን ሲጠቀም የቆየው የንግዱ ማኅበረሰብና ለግል አገልግሎት



87

የምንጠቀምባቸው አነስተኛ ተሽከርካሪዎችን ገዝቶ በመሸጥ ሂደት ውስጥ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪን የተቀበለበት አግባብ ሙሉ በሙሉ ቀና እና በጎ ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም። ከነበረው ተሞክሮ ብናይ አንዳንድ ጊዜ ቴክኖሎጂ አሻሽሎ ያመጣቸውን የአውቶሞቲቭ ውጤቶች ገበያ ላይ ውጤታማ ለማድረግ በንግዱ ማኅበረሰብ እና በተጠቃሚው መሃል ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች አሉ። ምርቱ ጉዳት እንዳለው የማጥላላትና የማንኳሰስ ሁኔታዎች ነበሩ። ከነዳጅ አቅርቦት ጋር የተያያዘ የሥራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ወገኖች ከመደበኛ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚደረገው ሽግግር በአንድ ጊዜ የሚሳካ እንዳልሆነ ሁሉ በአንድ ጀንበር በጋዝ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ወጥተው በኤሌክትሪክ የሚተኩ አስመስሎ በማሰብ በጎ ጎኑን ከመመልከት ይልቅ አሉታዊ ሊያውም የሌሉትን አጉልቶ በማሳየት በማኅበረሰቡ ዘንድ የተፈጠረው ብዥታ ቀላል አይደለም። መንግሥት በተለይ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ከውጭ በማስመጣትና አገር ውስጥ በመገጣጠም ለገበያ

የማዋል ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶችን በማበረታታት ይህንን አስተሳሰብ መለወጥ የሚያስችል ሥራ ሰርቷል። አሁን ኢትዮጵያዊያን ባለሃብቶች ቀደም ሲል በነዳጅ ሲሰሩ የነበሩ ተሽከርካሪዎችን በርካታ ጥቅሞችን በሚያስገኝ መልኩ ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ወደሆነ ተሽከርካሪ ለመቀየር የተፈጠረውን ዕድል ተጠቅመው ወደ ሥራ ገብተዋል። ከእነዚህ ባለሃብቶች መካከል የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ ይህንን ዕድል በመጠቀም ዘርፉን በማስፋት በርካታ ፕሮግራሞችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በተለይ ለሕዝብ ማጓጓዣ አገልግሎት የሚውሉ ሙሉ በሙሉ ተገጣጥመው ያለቀላቸውን ተሽከርካሪዎችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት እና በከፊልና ሙሉ በሙሉ የተበታተኑትን ገጣጥሞ ለተጠቃሚዎች ገበያ ላይ የማዋል ሥራ ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ እየሰራ ይገኛል። በዚህም እስካሁን በርካታ ቁጥር ያላቸውና እያንዳንዳቸው ከ15 ሰው በላይ መጫን የሚችሉ መለስተኛ አውቶቡሶችን አገር ውስጥ በመገጣጠም ለገበያ አውሏል። አገር አቋራጭ (Cross Country) ወይም የከተሞች (Inter-City) የተሰኙ አውቶቡሶችንና የከተማ ሕዝብ

ማመላለሻ አውቶቡሶችን ደብረብርሃን በሚገኘው የቢኬ የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካው በመገጣጠም ላይ ይገኛል። ጎልደን ድራጎን ባስ በዓለማችን ከታወቁ የሕዝብ ማጓጓዣ ትራንስፖርት ማምረቻ ተቋማት አንዱ ነው። የቻይናዋ ፉጂያን ግዛት መዲና በሆነችው ሺያመን ከተማ የሚገኝና በቻይና የአገር ውስጥ ገበያ እና በሌሎች የዓለም ዓቀፍ ገበያዎች ውስጥ ከፍተኛ ተወዳዳሪ የሆነ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ ነው። የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ እህት ኩባንያ የሆነው ሜታል ኢንጂነሪንግ ከቻይናው ኩባንያ በተሰጠው ሙሉ የቢዝነስ ስምምነት ውክልና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ማምረቱን ተያይዞታል። የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የቢዝነስ አቅጣጫ ይህ የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ከሚያስገኘው ትርፍ ይልቅ ማኅበረሰብ ተኮር እንዲሆን ማድረጉ ከመንግሥት ፖሊሲ ጋር እንዲጣጣም ያደርገዋል። የግሩፑ እህት ኩባንያ የጎልደን ድራጎን ባስ የልዩ አገልግሎት ዋና ሥራ አሥኪያጅ አቶ ኃይሉ ግዛው መንግሥት በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ማስመጣትና ማምረት ሥራ ለተሰማሩ ባለሃብቶች ድጋፍ እያደረገ ስለመሆኑ ይናገራሉ።



88

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

“በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ የንግዱ ማኅበረሰብን ጨምሮ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን አስመጥቶ መሸጥ በአገር ውስጥ በከፊልና ሙሉ በሙሉ የተበተኑ በከፊል የሚገጣጠሙ (Semi Knocked Down- SKD) ተሽከርካሪዎችን ባነሰ ዋጋ ገበያ ላይ ለማዋል የሚያስችል የማበረታቻ የፖሊሲ ድጋፍ መንግሥት እያደረገ ነው“ ብለዋል። በዚህም ተሽከርካሪዎቹ በተለይ ደግሞ በፖሊሲ ተደግፎ ከ10 ሰው በላይ የመጫን አቅም ያላቸው ተሽከርካሪዎች ከታክስ ክፍያ ነፃ እንዲሆኑ መደረጉ፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ዋነኛ አካል የኃይል ሰጪው የባትሪ ቻርጅ ማሽን ወደ አገር ውስጥ ሲገባ ከቀረጥ ነፃ እንዲሆን ማበረታቻ መሰጠቱ ተገቢነት አለው ይላሉ። በዘርፉ ከተሰማሩ የንግዱ ማኅበረሰብ ጎን ለጎን በየጊዜው ሁኔታዎች በፈቀዱ አቅም ማኅበረሰቡ ስለ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መረጃና ግንዛቤ እንዲኖረው ድጋፍ በመስጠት ረገድ መንግሥት እያደረገ ያለው ድጋፍ ቀላል እንዳልሆነም አንስተዋል። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ገበያ ስናሰማራ የማኅበረሰባችን ጥያቄ ሆኖ የቀረበው የቻርጂንግ አገልግሎት በምን ያህል መጠን እና እንዴት

እንገኛለን የሚል ነበር ያሉት አቶ ኃይሉ፤ “የእኛ ድርጅት ለገበያ ከማቅረብ ጎነ ለጎን የኃይል መሙያ መሣሪያ አገር ውስጥ በበቂ ሁኔታ አስገብቷል። በየደረጃው ከሚገኙ የክልል፣ የአዲስ አበባና የፌዴራል መንግሥት ጀምሮ የተቀናጀ የልማት ሥራ ለመስራት የመመሪያዎችን ተግባራዊ መሆን እየጠበቀ ነው፤ በዚህ ረገድ መንግሥት ጥሩ ድጋፍ እያደረገልን ነው” ሲሉ አክለዋል። ፋይዳው ኢትዮጵያ ከወጭ ንግድ ከምታገኘው የውጭ ምንዛሬ አብላጫውን ለነዳጅ ግዥ እንደምታውለው ይታወቃል። የተሽከርካሪ መለዋወጫ ዕቃዎችን ጨምሮ ሌሎች ኦፕሬሽናል ወጪዎች እንዳሉ ሆነው ተሽከርካሪዎች እያረጁ በሄዱ ቁጥር የሚጠይቁት የነዳጅን ያህል ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ አገራዊ ወጪውን ይበልጥ የሚያንረው ይሆናል። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የነዳጅ ወጪውን ሙሉ ለሙሉ የሚያስወግድና ከኤሌክትሪክ አኳያ ሲነፃጸር አምሥት በመቶ ያህል ወጪ የማያስወጣ መሆኑ ሲታሰብ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አዳጊ አገራት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ፋይዳው የጎላ ይሆናል። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ፈርጀ

ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት በመስኩ የተደረጉ ምርምሮች ያሳዩ ሲሆን ተጠቃሚዎችም ይህንኑ ነው የመሰከሩት። በተለይ የጋዝ አማቂ ልቀትንና የአየር ብክለትን በመቀነስ ረገድ አይነተኛ ድርሻ እንዳላቸው ይታመናል። ከአየር ብክለት ጋር ተያይዞ በከተሞች የሚፈጠሩ የጤና ችግሮችን የሚቀንሱ ሲሆን አገራትን በነዳጅ ላይ ካላቸው ጥገኝነት የሚያላቅቅ ነው። ከዚህ ሻገር ሲልም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከድምጽ ብክለት (Noise Pollution) የፀዱ በመሆናቸው አካባቢንና ማኅበረሰብን አያውኩም። ከነዳጅ ተሽከርካሪዎች ይልቅ የጥገና ወጪያቸው በጣም ዝቅተኛ መሆኑም ተመራጭ ያደርጋቸዋል። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቴክኖሎጂ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ ሲደረግ በቂ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተከናውነዋል። በመስኩ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ተሽከርካሪዎቹን አምርተው ወደ ኢትዮጵያ ከሚልኩ አገራት ጋር በተደረገ ግንኙነት የሙያ ሥልጠና ተሰጥቷቸው በአገር ውስጥ የመገጣጠም ሥራ ላይ ችግር ሲያጋጥም የመጠገን ብቃት እንዲኖራቸው ተደርጓል። ይህ ደግሞ የዕውቀት ሽግግር ከማስገኘቱ ባሻገር ለዜጎች የሚፈጥረው የሥራ ዕድል ቀላል



89

አይደለም። ሌላው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በነዳጅ ከሚሰሩ መደበኛ ተሽከርካሪዎች አንፃር የጥገና ወጪያቸው ዝቅተኛ ነው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለጥገናና ለሰርቪስ የሚጠይቁት ወጪ በነዳጅ ከሚሰሩት ተሽከርካሪዎች ቢያንስ 30 በመቶ ያነሰ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ነዳጅ የማይጠቀሙ በመሆናቸውና የነዳጅ ማቃጠያ ሞተር (Internal Combus- tion Engines-ICE) እና ከዚህ ጋር ተያያዥ የሆኑ መለዋወጫ ዕቃዎችን ብዙም የማይፈልጉ በመሆናቸው ነው። በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሞተር ውስጥ ወደ 20 የሚጠጉ ተንቀሳቃሽ ክፍሎች ብቻ ያሉ ሲሆን በመደበኛ ተሽከርካሪዎች ግን በመቶዎችና በሺህ የሚቆጠሩ ተንቀሳቃሽ ክፍሎች ይገኛሉ። ይህ ደግሞ ለጥገና እና መለዋወጫ የሚያስፈልጋቸው ወጪ ከፍ እንዲል ያደርገዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እንዲገቡ ለማበረታታትና በነዳጅ የሚሰሩት ደግሞ በብዛት እንዳይገቡ ተስፋ ለማስቆረጥ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ መደንገጉ በአዎንታ የሚታይ ነው። ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ማገድ በዓለም

የንግድ ድርጅት ሕግ መሰረት የማይቻል በመሆኑ የአገሪቱን የቀረጥ ሥርዓት በመጠቀም ምጣኔ ሃብትን ለማሳደግ የሚጠቅሙትን ማበረታታት፤ ጎጂ የሆኑትን ደግሞ እንዳይስፋፉ የማድረጉን ሥራ መንግሥት ሊሰራ ይገባል። ይህን ሲያደርግ ከምጣኔ ሃብታዊና አካባቢያዊ ፋይዳው አንፃር ታይቶ በመሆኑና በተለይ ኢትዮጵያ ከጀመረችው የአረንጓዴ ልማት ኢኒሼቲቭ ጋር እንዲጣጣም በሚያደርግ መልኩ መሆኑ ተመራጭ ያደርገዋል። በትራንስፖርት ዘርፍ ያለውን ልቀት ለመቀነስ ከነዳጅ ወደ ኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች በተቻለ ፍጥነት የመቀየር ጊዜው አሁን ነው። በዚህ ረገድ አገሪቷ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ እንድትሸጋገር የረዥም ጊዜ የመንግሥት ድጋፍ ያስፈልጋል። ዓለማችን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱትን ድርቅ፣ ረሃብ፣ ጎርፍ፣ የሙቀት መጨመርና ሌሌች ቀውሶች ለመከላከል ብክለት አመንጪ ያልሆኑ እንደ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አረንጓዴ አማራጮችን መተግበር ምርጫ ሳይሆን ግዴታ አርጋ ልትወስደው ይገባል።



90

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ማኅበራዊ

ትኩረት የሚሻው

በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ትብብር የተዘጋጀ



91

የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና

ዓለም አቀፉ የመሠረታዊ ጤና ክብካቤ ተቋም ወጣትነት ከፍተኛ የአካል፣ የአዕምሮ እንዲሁም የማኅበራዊ ግንኙነት ለውጦች የሚከሰቱበት፤ አፍላ ስሜትን በመቆጣጠር የወላጅ ምክርን ለመቀበል ያለመቻል አዝማሚያ የሚታይበትና አንዳንድ ለጤና አደገኛ የሆኑ ባሕሪያትን መልመድ የሚጀመርበት ወቅት ነው ይለዋል። የጤና ባለሙያዎችም በወጣትነት ዕድሜ ላይ በሆርሞን አለመስተካከል ሳቢያ በስሜታዊነት ወይም ባለማገናዘብ የሚወሰን ውሳኔ ይበዛል ይላሉ።

ስለሆነም ወጣትነት የተለየ ትኩረት፣ ክትትልና የማያቋርጥ ድጋፍ የሚሻ የዕድሜ ክልል እንደሆነ ይገለፃል። የአንድን አገር ሁለንተናዊ ዕድገት እውን ለማድረግ ወጣቶች ጤናማና ብቁ ተተኪ ትውልድ

በመንገሻ ገ/ሚካኤል



92

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

እንዲሆኑ ተገቢው ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል። በዚህ ጽሑፍ በጤና ሚኒስቴር ከአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና አጠባበቅ ጋር በተያያዘ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን እንዳስሳለን።

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም አቀፍ ደረጃ የወጣቶች ቁጥር ሁለት ቢሊዮን ደርሷል። እንደ ድርጅቱ መረጃ አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ለተለያዩ የሥነ-ተዋልዶ ችግሮች ይጋለጣሉ። በአፍላ ዕድሜ የግብረ ስጋ ግንኙነት መጀመር፣ ስለ ቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት በቂ እውቀት አለመኖር፣ ያልተፈለገ እርግዝና፣ ደህንነቱ ያልተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ፣ ኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ እና ሌሎች በግብረ ሥጋ

ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች (ኢንፌክሽኖች) ተጋላጭ መሆን እንዲሁም ያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ በአፍላ ዕድሜ ልጅ ከመውለድ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ችግሮች ተጠቃሾች ናቸው።

ከአካላዊ ችግር በተጨማሪ ሥነ-ልቦናዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችም ይከሰታሉ። ለእነዚህ ችግርች እንደ መንስኤ የሚጠቀሰው ደግሞ በቂ ግንዛቤ አለመኖር፣ የአገልግሎቱ ምቹ እና ተደራሽ አለመሆን እንዲሁም መሰል በአገልግሎት ሰጪና ተጠቃሚዎች መካከል ያሉ ክፍተቶች ናቸው።

በኢትዮጵያ አፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች 42 በመቶ የሚሆነውን የኅብረተሰብ ክፍል ይሸፍናሉ።



93

ወጣቶች ከሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች በተለየ ሁኔታ ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጭ ናቸው የሚለው የጤና ሚኒስቴር፤ አብዛኞቹ ወጣቶች ስለ ጾታዊ ግንኙነትና ሥነ-ተዋልዶ ጤና ያላቸው ግንዛቤ ያልዳበረ በመሆኑ ለችግር አጋላጭ ተግባራት ውስጥ ይሳተፋሉ ይላል። በከተማ እና ገጠር በሚኖሩ ወጣቶች መካከል ስለ ኤች.አይ.ቪ ምርመራ እና በበሽታው ዙሪያ ያላቸው ግንዛቤ ሰፊ ልዩነት አለው። ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 19 ዓመት የሚሆናቸው 37 በመቶ ሴቶች እና 43 በመቶ ወንዶች የአልኮል መጠጥ የሚወስዱ ሲሆኑ፤ 57 በመቶ የሚሆኑ ወንዶች ደግሞ ጫት ይቅማሉ። እንዲሁም ከ15 እስከ 19 ዓመት ከሚሆናቸው አፍላ ወጣት ሴቶች መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት የደም ማነስ እና 23 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ዝቅተኛ ክብደት ያላቸው ናቸው።

በጤና ሚኒስቴር የሥነ-ተዋልዶ፣ የቤተሰብ ዕቅድ፣ የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ጤና ባለሙያ የሆኑት አቶ ሰኚ ዱፌራ፤ አፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ለከፍተኛ የጤና ችግሮች እና ለችግር አጋላጭ ባሕሪያት የተጋለጡ ቢሆኑም የጤና አገልግሎቶች ተደራሽነት እና ተጠቃሚነት ሽፋን ዝቅተኛ ነው ይላሉ። በአገሪቷ ከሚገኙ የሕክምና ተቋማት

ለወጣቶች የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡት 56 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው የሚሉት አቶ ሰኚ፤ ጤና ሚኒስቴር ከ10 እስከ 24 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ይገልፃሉ። የወጣቶችን ጤና መጠበቅ የሚያስችሉ ስትራቴጂዎች ተነድፈው እየተተገበሩ ነው፤ የተለያዩ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ዕቅዶችም ወጣቶችና አፍላ ወጣቶችን ያማከሉ እንዲሆኑ ተደርጓል።

ጤና ሚኒስቴር የወጣቶችና አፍላ ወጣቶችን ጤና ለማሻሻል ሁለት የሥነ-ተዋልዶ ጤና ስትራቴጂዎች (ከ2006-2015 እና ከ2016- 2020) በመተግበር በኤች.አይ.ቪ እና በሌሎች የሥነ-ተዋልዶ ጤና ላይ ውጤታማ ሥራዎች ሰርተዋል። ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ሦስተኛው የወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ጤና የአምሥት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ በትግበራ ላይ ይገኛል። ይህ ስልታዊ ዕቅድ ሁሉን አቀፍ የወጣቶችና አፍላ ወጣቶች የጤና ችግሮችን የሥነ ተዋልዶ ጤና፣ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከል፣ የአደንዛዥ ዕፅ መጠቀምና የአዕምሮ ጤና፣ የሥርዓተ ምግብ፣ ፆታን መሠረት ያደረገ ትንኮሳና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች፣ ቴክኖሎጂና የወጣቶችና ጤና

በሰብዓዊ ምላሽ ወቅት ጉዳዮችን በማካተት በዋናነት የጤናውን ዘርፍ የአምሥት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ መሠረት አድርጎ መዘጋጀቱን አቶ ሰኚ አብራርተዋል።

በሁለተኛው የጤና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድና በመካከለኛ ዘመን የጤና ዕድገትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ ውስጥ የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና ስትራቴጂ የሥነ-ተዋልዶ ጤና ስትራቴጂዎች ተካተዋል። በስትራቴጂው ከተቀመጡ ዓበይት ተግባራት መካከል የተሟላ የጾታዊ ግንኙነትና የሥነ- ተዋልዶ ጤና መረጃ፤ ምክር እና አገልግሎቶችን ማስፋፋትና የሥነ-ልቦና ማኅበራዊ ድጋፍ ተደራሽ ማድረግ፤ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ስልቶችን፤ ወጣትን ማዕከል ያደረጉ ምቹ እና ፈጠራ ተኮር ተግባራትንና ውጤታማና ሰው-ተኮር አገልግሎቶችን ለማሻሻል አዳዲስ ስልቶችን በማስተዋወቅ፣ በማላመድና በመሞከር እንዲተገበር ድጋፍ ማድረግና ማመቻቸት የሚል ይገኝበታል።

እንዲሁም ጤናማ የአኗኗር ባሕሪን ለአፍላ ወጣቶች ማስተዋወቅ (ለምሣሌ ጤናማ አመጋገብ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ ትንባሆ፣ አልኮል ወይም አደንዛዥ ዕፅ



94

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

አለመጠቀምን. . . ወዘተ ማበረታታት)፤ ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን፣ ጎጂ ልማዶችን (ያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ ጠለፋ) ለመከላከል፤ መለየት እና ማከም የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመተግበር በስትራቴጂክ ዕቅዱ የወላጅነት/የአሳዳጊነት ችሎታ ማጎልበቻ ፕሮግራምን መተግበር እና የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች የሕይወት ተሞክሮ/ክህሎት ሥልጠናዎችን ተደራሽነት ማስፋፋት፤ የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤናን ከትምህርት ቤት የጤና ፕሮግራሞች ጋር ማቀናጀትና ማጠናከር የሚሉት ዋና ዋና አንኳር ተግባራት ናቸው።

በአፍላ እና በጉርምስና ዕድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶችን ማዕከል ያደረጉ የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽነትና ጥራት ማሻሻል፣ በተለይም ለተጠቂነት ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ አካላት እንደ አካል ጉዳተኞች፣ ላገቡ ሴቶች፣ በገጠር አካባቢ ለሚኖሩ፣ በድህነት ውስጥ ለሚገኙ እና በቂ ትምህርት ለሌላቸው የአፍላ ዕድሜ ወጣቶች የበለጠ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል።

ሚኒስቴሩ ወጣቶች ለተለያዩ የጤና እክሎች ተጋላጭ የሆኑባቸውን አካባቢዎች በመለየት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው የሚሉት አቶ ሰኚ፤ በከፍተኛ

የትምህርት ተቋማት፣ በወጣት ማዕከላት፣ በልማት ኮሪደሮች፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በሥነ- ተዋልዶ ጤና ወጣቶችንና አፍላ ወጣቶችን ያማከሉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም እነዚህ አካባቢዎች ለጤና ተቋማት ተደራሽ አልነበሩም የሚሉት ባለሙያው የጤና አገልግሎት ሽፋኑን ለማሻሻል በንቅናቄ መልኩ እየተሰራ ነው። በእነዚህ ወጣቶች ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑባቸው አካባቢዎች ሉፕ የተባለ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ሽፋን ለማሳደግ በንቅናቄ እየተሰራ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በአፍላ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶችን የሥነ-ተዋልዶ ጤና ለማሻሻል የሚወሰዱ ውጤታማ እርምጃዎች የተለያየ አደረጃጀትና የተቀናጀ አቀራረብን ይጠይቃሉ። በተጨማሪም አድሎአዊ ያልሆኑ አገልግሎቶችን ለማዳረስ፣ ትክክለኛ አሰራርን የጠበቀ ሕክምና እንዲኖር፣ ከአስተዳደግ ሁኔታ፣ ከባሕል እና ከዕድሜ አንፃር ተስማሚ የሆኑ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ያስችላል።

በሌላ በኩል ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ የጤና ችግሮችን ከ15 እስከ 19 ዓመት ዕድሜ ክልል በሚገኙ ሴቶች ላይ መከላከል የሚቻል

ቢሆንም፣ ሞት እና የጤና መጓደሎችን እያስከተሉ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ ሕግ መሰረት ከ18 ዓመት ዕድሜ በታች ጋብቻ ባይፈቀድም እስከ 40 በመቶ ያለ ዕድሜ ጋብቻ ይፈፅማሉ። እነዚህ ሴቶች ከወሊድ ጋር ተያይዞ በጤናቸው ላይ ጉዳት ስለሚደርስ ልጅ እንዲወልዱ አይመከርም የሚሉት ባለሙያው፤ ዕድሜያቸው ለጋብቻ ሳይደርስ ያገቡ ታዳጊ ወጣቶች ካገቡ በኋላም ቢሆን ወሊዳቸውን እንዲያዘገዩ ማድረግ እንዲቻል የንቅናቄ ሥራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል። የአፍላ ወጣቶችን እርግዝናና ያለ ዕድሜ ጋብቻ ለመከላከል እ.ኤ.አ በ2030 አሁን ካለበት 13 በመቶ በግማሽ ለመቀነስ ግብ ተጥሎ እየተሠራ መሆኑን አክለዋል።

ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ሌላው የወጣቶች ፈተና መሆኑን አቶ ሰኚ ይናገራሉ። ፆታን መሰረት በማድረግ ማንኛውንም በአካል፣ በሥነ-ልቦና፣ በወሲብ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ወይም ያደረሰ “ጥቃት” የሚባል ሲሆን ድርጊቱን ለመፈፀም የሚደረጉ ተግባራትን በሚመለከት በቤት ውስጥም ሆነ በውጭ የሚፈጸሙ ማስፈራራት፣ ማስገደድ፣ ያለአግባብ ማገድ እና ነፃነትን መቀነስ፣ ድብደባ፣ የእጅ እልፊት፣ የወሲብ ትንኮሳ፣ አስገድዶ መድፈር፣ በሴቶች አካል



95

መነገድ፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ ግርዛት፣ ስድብ እና ማዋረድ፣ በጭካኔ መያዝ፣ ጠለፋ እና የሀይል ጋብቻ የመሳሰሉት ናቸው። እነዚህ ጥቃቶች በተለይም በሴት ወጣቶች ላይ በስፋት ይስተዋላሉ የሚሉት አቶ ሰኚ ይህንን ጥቃት ለማስቆም ጤና ሚኒስቴር ከተለያዩ የፌዴራል እና የክልል ባለ ድርሻ አካላት በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

አሁን አሁን አዕምሮን የሚያነቃቁ አደንዛዥ ዕፆች የሚጠቀሙ ወጣቶች ቁጥር እየጨመረ ነው። ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር ተያይዘው በሚከሰቱ ችግሮች ዋነኛ ተጠቂዎች ወጣቶች ናቸው። አነቃቂ አደንዛዥ ዕፆች በሚወሰዱበት ጊዜ በዋናነት

አዕምሮ ላይ ተጽዕኖ በመፍጠር በአካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ተግባሮች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። አደንዛዥ ዕፅ የሚጠቀሙ ወጣቶች ለኤች. አይ.ቪ፣ ለጉበትና ለሌሎች ተላላፊ በሸታዎች የመጋለጥ ዕድላቸው የሰፋ ነው።

ጤና ሚኒስቴር ወጣቶችን ከአደንዛዥ ዕጽ ተጋላጭነት ለመከላከል አገር አቀፍ የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና ካውንስል ኣቋቁሞ እየሰራ ይገኛል። በሁሉም ክልሎች ካውንስል አቋቁመናል የሚሉት አቶ ሰኚ፤ የካውንስሉ አባላት ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመሆን በዋናነት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በወጣቱ ጤና ላይ የሚያደርሷቸውን ጉዳቶች



96

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ለመቀነስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በስፋት እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል። ከሱስ ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉትን ችግሮች ለመቀነስ ከክልል ጤና ቢሮዎች፣ ከወረዳ ጤና ተቋማት ጋር ውጤታማ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በአገሪቱ በርካታ የወጣት ስብዕና ግንባታ ማዕከላት የተገነቡ ቢሆንም ማዕከላቱ ከጤና አገልግሎት አሰጣጥ አኳያ ጉድለት ያለባቸው ናቸው ይላሉ አቶ ሰኚ። የስብዕና መገንቢያ ማዕከላት የተለየ ትኩረት እና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ገልፀው በቀጣይ ከሕክምና አገልግሎት ጋር የማቀናጀት ሥራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

የወጣቶችን ጤና የመጠበቅ

ተግባር የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ ትብብር ይፈልጋል፤ በአንድ ዘርፍ ብቻ ተሰርቶ የሚያልቅ አይደለም የሚሉት አቶ ሰኚ፤ ከሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ፣ ከትምህርትና ከፍትሕ ሚኒስቴሮች እንዲሁም ከሌሎች መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች በጋራ እየሰራን ነው ብለዋል። ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ከአበባ ልማት ድርጅቶች በጋራ እየሰሩ እንደሆነ በመጥቀስ።

የወጣቶች ችግሮች በዕድገት ወቅት የሚከሰቱ በሚገባ ካለመረዳት፣ አርቆ ካለማሰብና ከስሜታዊነት እንዲሁም ከዕድሜ እኩዮች በሚፈጠር

ግፊትና ከማኅበራዊ ኑሮ ልምድ ማጣት ጋር የተያያዙ ናቸው። ስለሆነም በጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጅ የወጣቶች ሥነ- ተዋልዶ ጤና ፕሮግራምን በማካተት ወጣቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው የተሻለ ሕይወት በመምራት ጤናማና ብቁ ተተኪ ትውልድ እንዲሆኑ ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ ያሻል። ወጣቶች ጤንነታቸው አደጋ ላይ እንዳይወድቅ በማኅበር ተደራጅተው በበርካታ የሥነ- ተዋልዶ ጤና ችግሮቻቸው ዙሪያ እንዲወያዩና ጤናማ የባሕሪ ለውጥ በማምጣት ራሳቸውን ከአደጋ መከላከል እንዲችሉ ማድረግም ያስፈልጋል።



97



98

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ማኅበራዊ

የፅናት ተምሣሌት …



99

የፅናት ተምሣሌት …

ትውልድና ዕድገቷ አዲስ አበባ በተለምዶ ኦሎምፒያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። ዕድሜዋ 31፤ ለቤተሰቧ አራተኛ ልጅ ስትሆን፤ አራት እህትና ወንድሞች ያሏት በእናቷ መልካም አስተዳደግ እና እንክብካቤ ልጅነቷን ያሳለፈች መሆኗን ትናገራለች። የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በተለያዩ የግል ትምህርት ቤቶች ተከታትላለች። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች ወደ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ አምርታ ከዘጠኝ ዓመት በፊት እሷ “ወንዶች የሚበዙበትና (Male dominated) የሴቶች ቁጥር የሚያንስበት” ባለችው የሲቪል ምህንድስና (Civil Enginering) የትምህርት መስክ ተመርቃለች። “እናታችን ’አልችልም‘ የሚል ስሜት ውስጣችን እንዲኖር አላደረገችም። ይልቁንም በምርጫችን እንድንማር፣ በምርጫችን እንድንወስን እያበረታታች ስላሳደገችን

በፍቅርተ ባልቻ



100

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ለወንዶች የተተወውን ይህን ሙያ ስቀላቀለ የተለየ ስሜት በውስጤ አላደረም“ በማለት የእናቷ የአስተዳደግ መርህ ብርታት እንደሆናት ትገልጻለች። በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ የሴት ተማሪዎችን የሕይወት ተሞክሮ ስትሰማ በብዙ ውጣውረዶች ውስጥ አልፈው እንደመጡና ሴቶች ላይ የተለያዩ ጫናዎች እንደሚደረጉ ተረድታለች። ባለታሪካችን ወ/ሪት ማህሌት ኃብተማርያም ትባላለች። “የዩኒቨርሲቲ ሕይወት ድግግሞሽ ስላላው ስልቹ አደረገኝ“ የምትለው ማህሌት ይህ ስሜት በዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሳለች በከተማዋ እንደ ፒዛ እና፣ በርገር ያሉ ምግቦች አለመኖራቸውን (የገበያውን ክፍተት) በማየቷ ከእናቷ ባገኘችው 25 ሺህ ብር መቀሌ ውስጥ ምግብ ቤት ከፍታ እንድትሰራ ምክንያት ሆናት። ሥራዋን የጀመረችው ከአዲስ አበባ በመጣ አንድ ኢጣሊያዊ ምግብ አብሳይና ሌሎች ሠራተኞችን በማሰባሰብ ነው። ያኔ በቂ ገንዘብ ስላልነበራት ተመጋቢዎችን በፕላስቲክ ሰሀኖች አስተናግዳለች፤ አቅሟን በዕቁብ እና በሌሎች መንገዶች በማጠናከር ምግብ ቤቷን ታዋቂ ከማድረግ ባሻገር እዚያው መቀሌ ውስጥ ሁለተኛ ቅርንጫፍ በመክፈት እየሰራች ሳለ አገሯን

የመጎብኘት ፍላጎት እንዳደረባት ታወሳለች። “ወደ ላሊበላ ሄድኩኝ፤ ለአስጎብኚዬ ወጣት ምን እንደምሰራ ነገርኩት፤ ለምግብ ቤት የሚሆን አንድ ቤት ጨረታ እንደወጣ፣ በከተማዋ የምግብ ቤት እጥረት እንዳለ ነገረኝ። ይህን ስሰማ እዛም ለመስራት ጓጓሁኝ“ ስትል ስራዋን ከመቀሌ ወደ ላሊበላ ያዘዋወረችበትን አጋጣሚ ታስታውሳለች። የመቀሌ ምግብ ቤቶቿ ውጤታማ ቢሆኑም እነሱን ዘግታ ላሊበላ ከተመች። በዚያ የተወሰኑ ዓመታት ሰራች፤ ወደ አዲስ አበባ እየተመላለሰች ለመስራት ብትሞክርም ስላልተመቻቸላት ሥራውን የሚያስተዳድር ሰው ቀጥራ ለሁለት ዓመት እንደሰራች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተከሰተ፤ ተከታትሎም በሰሜኑ የአገሪቷ አካባቢ የተቀሰቀሰው ጦርነት ሥራዋን እንድታቋርጥ አስገደዳት። ምግብ ቤቷን ወደ ላሊበላ ካዘዋወረች በኋላ አዲስ አበባ መጥታ በፋሲሊቲ ኮንስትራክሽን እና ማኑፋክቸሪንግ ሥራ የተሰማራችው ምህረት ለዚህም ወደ ኮንስትራክሽን የመምጣት ፍላጎት እንዳላት የተረዱት የጓደኛዋ አባት ምክንያት እንደሆኗት ትገልጻለች። “ሙያውን አስተማሩኝ፤ ከልጃቸው ጋር በመሆን ሥራውን

ጀመርን፤ አንድ ሁለት እያልን ጉዟችንን ቀጠልን” ትላለች። የፋሲሊቲ ኮንስትራክሽን ሙያ የተለያዩ ሥራዎችን ባህሪይ ታሳቢ በማድረግ ምቹ፣ ተስማሚ እና ጥራታቸውን የጠበቁ አገልግሎቶች እንዲሰጡ፣ ምርት እንዲያመርቱ ለማስቻል የሚሰራ የኮንስትራሽን ሥራ ነው። የገበያውን ክፍተት በማየት ለቤት እና ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ የእንጨት ውጤቶችን ያመርታሉ። ማህሌት የድርጅቱ ሊቀመንበር ነች። ሦስት ሆነው በ10 ሺህ ብር የጀመሩት ሥራ ካፒታል አሁን 10 ሚሊዮን ብር ደርሷል። የምርቶቻቸው ተደራሽነት እስከ አሁን በአዲስ አበባ ብቻ መወሰኑን፤ ሥራቸውን ከትንሽ ተነስተው መጀመራቸው ጊዜያቸውን እየወሰደባቸው መሆኑን የምትናገረው ማህሌት፤ ዘመኑን የሚዋጅ ቴክኖሎጂ መጠቀም እንደሚኖርባቸው ገልጻለች። “ድርጅታችን አብዛኛውን ሥራ በማሽን ስለሚያከናውን የጉልበት ወጪ ይቀንሳል፣ ጊዜ ይቆጥባል፣ በዚያው ልክ ለደንበኛችንም ዋጋ ይቀንስለታል። በዚህ መልኩ ከሠራን ዘመኑ ዓለም የተሳሰረችበት በመሆኑ ኢ-ኮሜርስን መቀላቀል እንችላለን። በቀጣይ ወደ ጎረቤት አገራት ኬንያ፣ ሱዳን፣ . . . እያልን



101

ወደ ውጭ አገራት ምርቶቻችንን ኤክስፖርት የማድረግ ትልም አለን” ብላለች ሩቅ አሳቢዋ። ዓለም አቀፍ መረጃዎች እ.ኤ.አ 2022 ዓ.ም የዓለም ሕዝብ ብዛት 7 ነጥብ 95 ቢሊዮን መድረሱን መረጃዎች ያመላክታሉ። ከዚህ ውስጥ የሴቶች ቁጥር 3 ነጥብ 95 ቢሊዮን ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ’Gender Ratio In The World’ በሚል ርዕስ ይፋ ያደረገው ሰነድ እንደሚያሳየው ወንዶች ከዓለም ሕዝብ 50 ነጥብ 25 በመቶ፤ ሴቶች ደግሞ 49 ነጥብ 75 በመቶ ናቸው። በዓለም ባንክ ‘Women’s

Business and the Law 2022’ ሪፖርት መሰረት 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ሴቶች በኢኮኖሚ መስክ ከወንዶች እኩል የመሳተፍ ዕድል አላገኙም፤ በ178 አገራት ያለው የሕግ ማዕቀፍ ኢኮኖሚያዊ ተሳትፏቸውን ገድቦታል። ሪፖርቱ አያይዞም 23 አገራት እ.ኤ.አ በ2021 ሴቶችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ በሕጎቻቸው ላይ ማሻሻያዎች ማድረጋቸውን ጠቅሷል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ዘርፍ The World’s Women 2020: Trends and Statistics በሚል ርዕስ ይፋ

ያደረገው መረጃ ደግሞ ወደ ሥራ የሚሰማሩበት ዕድሜ ላይ ከደረሱ ወንዶች 74 በመቶው ሥራ ላይ ሲሆኑ፣ በአንጻሩ የሴቶች ቁጥር 47 በመቶው ብቻ መሆናቸውን አረጋግጧል። በአንፃሩ ክፍያ የሌላቸውን የቤት ውስጥ ሥራዎችን በስፋት ይሰራሉ፤ ይህም በሴቶች ላይ ጫና ያሳድራል። በቀን ውስጥ ሴቶች ለቤት ውስጥ ሥራዎች የሚያውሉት ጊዜ በአማካኝ 4 ነጥብ 2 ሠዓት ሲሆን፣ ወንዶች 1 ነጥብ 7 ሠዓት ብቻ ነው። በሰሜን አፍሪካ እና በምዕራብ እስያ ያለው ክፍተት ከዚህ የላቀ ሲሆን፣ ሴቶች ከወንዶች



102

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ሰባት እጥፍ የሚበልጠውን ሠዓታቸውን ለቤት ውስጥ ሥራዎች እንደሚያውሉ ጽሑፉ ያሳያል። እ.ኤ.አ በ2020 በዓለም አቀፍ ደረጃ ሴቶች በምክር ቤቶች (ፓርላማዎች) ያላቸው ወንበር 25 በመቶ ብቻ ነው። የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ ዕድገት እያሳየ ቢሆንም በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢንጂነሪንግ፣ በሂሳብ የትምህርት መስኮች ከሚመረቁት መካከል ሴቶች 35 በመቶ ብቻ ናቸው፤ በሳይንሳዊ ጥናት እና ምርምር ላይም ጥቂት ተሳትፎ ነው ያላቸው። የዓለምን እኩሌታ የሕዝብ ቁጥር የሚይዙት ሴቶች በአብዛኞቹ አገራት በፖለቲካ መስክ ያላቸው ተሳትፎ ከቁጥራቸው አንጻር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ለዚህም በምክንያትነት የሚጠቀሱት አግላይ የሆኑ ሕጎችና ድርጊቶች፣ የሥርዓተ ጾታ ልዩነት በተለይም በትምህርት እውቀታቸውን ለማሳደግ፣ ጤንነታቸውን ለመጠበቅ ዕድል አለማግኘታቸው፣ ድህነት ተጽዕኖውን በእጅጉ የሚያሳርፈው በሴቶች ላይ መሆኑን የሚተነትነው፤ ጥናት እና ምርምሮችን በመሥራት ይፋ የሚያደርገው Congressional Research Service የተባለ ተቋም ‘Statistics on Women in National Governments

Around the Globe‘ በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ 2023 ለንባብ ያዋለው መረጃ ነው። ተቋሙ እ.ኤ.አ 2023 በዓለማችን በሕግ አውጪ መዋቅሮች ወንበር (legislative seats) ያላቸው ሴቶች ቁጥር 26 ነጥብ 7 በመቶ ብቻ መሆናቸውንም ጠቅሷል። የሕግ ማዕቀፎች ምን ይላሉ? የወንዶች እና የሴቶች እኩልነት ከኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ተጠቃሚነት ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው። ሴቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ መደረጉ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ብሎም ሌሎች መብቶቻቸው እንዲከበሩ መደላድል እንደሚሆን እሙን ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥን ዓላማ ያደረጉ በርካታ ፕሮግራሞችና ስልቶች ተግባራዊ ሲደረጉ ቆይተዋል፣ አሁንም እየተደረጉ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያዘጋጀው ስምምነት ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። በሴቶች ላይ የሚደረግ ማንኛውንም አድሏዊ ልዩነት ለማስወገድ የተደረገው ይህ ስምምነት (The Convention on the Elimination of all forms of Discrimination against Women /CEDAW) በተባበሩት

መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ እ.ኤ.አ 1979 ተቀባይነት አግኝቶ በ1981 በሥራ ላይ ውሏል። ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ድርጅት (International Labour Organization) እንደሚገልጸው፤ ሴቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ ማብቃት ኢኮኖሚን ያነቃቃል፣ የአገር ኢኮኖሚ ያሳድጋል፣ የቤተሰብን ምርታማነት እና የኑሮ ሁኔታ ያሻሽላል፤ ይህም በውጤቱ ደህንነታቸው የተጠበቀ ልጆችን ለማሳደግ ያስችላል። ሁሉም ሴቶች በራሳቸው የመወሰን፣ የፈለጉትን የመምረጥ፣ ከጾታዊ ጥቃት ነጻ የመሆን፣ የመማር፣ በአገራዊ ጉዳዮች የመሳተፍ እና የመወሰን፣ ለተመሳሳይ ስራ ተመሳሳይ ክፍያ የማግኘት መብታቸው መጠበቅ እንዳለበት (The Fourth UN World Conference on Women of September 1995) በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኮንፈረንስ ላይ ቀርቦ ከስምምነት ላይ ተደርሷል። እ.ኤ.አ (11th July 2003) በተካሄደው የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ የማፑቶ ፕሮቶኮል (Maputo protocol) ጸድቆ ወደ ስራ ተገብቷል። ይህ ፕሮቶኮል በአንቀጽ 13 ላይ በአፍሪካ ሴቶች ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ ደህንነት እና መብቶች



103

ቅርብ እንዲሆኑ በማድረግ ሴቶችን ለማብቃት መስራት (Empowerment of women) ተገቢ ስለመሆኑ በዘላቂ የልማት ግቦቹ ተመላክቷል። በሌላ በኩል እ.ኤ.አ (4th February 2015) የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ አጀንዳ 2063 ጸድቋል። ይህ አጀንዳ የአፍሪካን ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያመላክት ፍኖተ ካርታ ነው። የአፍሪካ ሴቶች በግብርናው መስክ ተሳትፈው ተጠቃሚ የሚሆኑበትንና ጤንነታቸውን መጠበቅ የሚችሉበት ብሎም የትምህርት ዕድል የሚያገኙባቸውን፣ ለሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ቅርብ እንዲሆኑ መስራት በአጀንዳው ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ናቸው። የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ አገራት የጋራ ገበያ (The Common Market for Eastern and Southern Africa /COMESA) እ.ኤ.አ በ2016 የሥርዓተ ጾታ ፖሊሲ አዘጋጅቷል። ሥርዓተ ጾታን በፖሊሲዎች፣ በመዋቅሮች፣ በፕሮግራሞች እንዲሁም በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ውስጥ አካቶ በመተግበር (Mainstream) የሴቶችን እኩልነት ለማስፈን ብሎም ለማብቃትና ማኅበራዊ ዕድገት ለማምጣት መሰራት እንዳለበት

ላይ ትኩረቱን አድርጓል። የመንግሥታቱ ድርጅት ዘላቂ የልማት ግቦች (UN Sustainable Development Goals /SDGs) ከሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ጋር በቀጥታ የተሳሰሩ ናቸው። በተለይ አምስተኛው ግብ የሥርዓተ ጾታን እኩልነት እና የሴቶችን ተጠቃሚነት አስመልክቶ “በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ማናቸውንም ዓይነት መድልዎ እና ማግለል ማስቆም፣ በቤት ውስጥ ለሚሠሩ እና ክፍያ ለሌላቸው ሥራዎች እውቅና መስጠት፣ የቤት ውስጥ ሥራዎች የሚፈጥሯቸውን ጫናዎች ለማቅለል የሚረዱ የሕዝብ አገልግሎቶችና መሰረተ ልማቶችን ማቅረብ፣ በቤተሰብ ውስጥ ያለን ኃላፊነት በጋራ መወጣት የሚያስችሉ አማራጮችን ማበረታታት ማስተዋወቅ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል“ ሲል ዘርዝሯል። ከኢኮኖሚያዊ መብቶቻቸው ጋር በተያያዘም የራሳቸውን ኃብት እንዲያፈሩ፣ በኃብቶቹም ላይ የማዘዝ መብት እንዲኖራቸው፣ የመሬት ባለቤት እንዲሆኑ የሚያስችሉ የማሻሻያ እርምጃዎችን መውሰድ፤ የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸውን በማሻሻል፣ በተለይም ለኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ

በፖሊሲው ተመላክቷል። ኮሜሳ ሴቶችን ለማብቃትና በኢኮኖሚ ራሳቸውን ለማስቻል በጀት በመመደብ እየሰራ ሲሆን፣ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ሴቶች በገንዘብ ችግር ምክንያት የሚገጥማቸውን ተግዳሮት እንዲወጡ ብድር እንዲያገኙ ያመቻቻል። የምስራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ (East African Community /EAC) በበኩሉ እ.ኤ.አ 2018 የሥርዓተ ጾታ ፖሊሲ አዘጋጅቷል። ይህም ሴቶች በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ያላቸውን ሚና ማዕከል ያደረገና ሴቶችን የማብቃት ስትራቴጂ ያቀፈ ነው። በአነስተኛ ንግድና ቢዝነስ ከተሰማሩት መካከል አብዛኞቹ ሴቶች እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ። እነዚህ በአነስተኛ ንግድ የተሰማሩ ሴቶች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች አገራት በሚፈጥሩት ክፍለ አህጉራዊ ትስስር አማካኝነት ማቃለል ሥራቸውን የተሳካ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑ በፖሊሲው ተመላክቷል። ለመረጃ ቅርብ እንዲሆኑና በሚሠሩት ሥራ ምን ማሟላት እንደሚጠበቅባቸው አስቀድሞ ግንዛቤ በመፍጠር የሚያጋጥሟቸውን ውጣ ውረዶች መቀነስ እንደሚቻል የጠቆመው ፓሊሲው የሥርዓተ ጾታ ትንተና በመሥራትና



104

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ለሕግ አውጪዎች መረጃውን በመስጠት የማሻሻያ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ጫና ማሳደር አስፈላጊ መሆኑን ይመክራል። በመካከለኛው ምስራቅ፣ በሰሜን አፍሪካ እና ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት መሻሻሎች ቢኖሩም ሴቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት እና የፈጠራ ችሎታቸውን በተጨባጭ ለማሳየት ከሕግ ማዕቀፍ ጋር ተያያዥ የሆኑ ማነቆዎች መኖራቸው አልቀረም። በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ ልማዶችና ለሴቶች ሚና የሚሰጠው ቦታና ግምት ማነቆ እየሆነ ያለው ደግሞ በማደግ ላይ ባሉ አገራት ብቻ ሳይሆን ባደጉት እና በበለጸጉት አገራት

ጭምር ነው። የዓለም ባንክ ሰነድ ከሕግ ማዕቀፍ ጋር የተያያዙ ችግሮችን በመፍታት፣ የትዳር አጋሮቻቸው ሴቶች ከቤት ወጥተው እንዲሠሩ የሚስማሙበትን ሁኔታ በማመቻቸት፣ በሥራ አካባቢ በሴቶች ላይ ለሚደረጉ ጫናዎች እልባት በመስጠት ሴቶች በኢኮኖሚው መስክ በስፋት መሳተፍ የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚቻል ያስረዳል። ከላይ የተጠቀሱት እና ሌሎችም ዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፎችና ሰነዶች ሴቶችን ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ለማድረግ፣ መብቶቻቸውንም ለማስከበር በሚሠሩ ሥራዎች ላይ የራሳቸውን አዎንታዊ ተጽዕኖ

ስለማሳረፋቸው በእርግጠኝነት መግለጽ ይቻላል። የሴቶችን ተጠቃሚነት እና ሁለንተናዊ ተሳትፎ በተመለከተ መሻሻሎች ቢኖሩም አሁንም ድረስ በወንዶች እና በሴቶች መካከል ያለው ልዩነት (Gender gap) እንደቀጠለ በመሆኑ በቀጣይ ብዙ መስራት እንደሚጠይቅ ጥናቶች ያመላክታሉ። በኢትዮጵያ ምን መልክ አለው? በኢትዮጵያ ሥርዓተ ጾታ፣ የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ምን ይመስላል ያልን እንደሆነ ምላሹ በአገራችን ያለው ገጽታም ከተቀረው የዓለም ክፍል የተለየ አይደለም ነው። በቀደመው ጊዜ ሴቶች በማጀት ሆነው ልጆችን እና



105

ቤተሰብን ከመንከባከብ ባሻገር በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በማኅበራዊው መስኮች ንቁ ተሳትፎ አልነበራቸውም። የአገራችን ብሂል ”አንድ እጅ ብቻውን አያጨበጭብም” እንዲል፤ ከጠቅላላው ሕዝብ 50 በመቶውን ድርሻ የሚይዙት ሴቶች ተሳትፎ ሳይኖራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ለውጥ ማምጣት የሚታሰብ አለመሆኑን ያስረግጣል። በመሆኑም መንግሥት የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማጎልበት በርካታ ጥረቶች አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል። በዚህም መሰረታዊ የሆኑትን የሴቶች መብቶች ሕገ-መንግሥታዊ መሰረት ማስያዝ፣ ወደ ተግባር መለወጥ የሚያስችሉ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ ፕሮግራሞችና ፓኬጆችን ቀርጾ በየደረጃው በመፈጸም ላይ ይገኛል። የሴቶች ፖሊሲ መውጣቱ፣ በፌዴራልና በክልል መንግሥታት የሴቶች ጉዳይ አደረጃጀት መዋቅር መዘርጋቱ፣ በገጠር የሴቶች የመሬት ባለቤትነት መረጋገጡ፣ የቤተሰብ ሕግ መጽደቁ፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ በደሎችን ለመግታት በሚያስችል መልክ መሻሻሉ ከተደረጉ ጥረቶች ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ።

ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በመነሳት የራሷን የሕግ ድንጋጌዎች አዘጋጅታ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል። ከዚህ አንጻር የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 25 እና 35 የሰዎች እኩልነት እና የሴቶች መብቶች ላይ ትኩረት አድርጓል። አንቀጽ 25 ”ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው፤ በመካከላቸውም ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በሕግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል። ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት አላቸው” ሲል ስለ እኩልነት ደንግጓል። አንቀጽ 35 ”ሴቶች በበታችነትና በልዩነት በመታየታቸው የደረሰባቸውን የታሪክ ቅርስ ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህ ቅርስ እንዲታረምላቸው በተጨማሪ የድጋፍ እርምጃዎች ተጠቃሚ የመሆን መብት አላቸው። በዚህ በኩል የሚወሰዱት እርምጃዎች ዓላማ በፖለቲካዊ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ መስኮች እንዲሁም በመንግሥት እና በግል ተቋሞች ውስጥ ሴቶች ከወንዶች ጋር በእኩልነት ተወዳዳሪና ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ እንዲቻል ልዩ ትኩረት ለመስጠት ነው” በማለት ለሴቶች ልዩ ድጋፍ (Affirmative action) ሊደረግላቸው እንደሚገባ ግልጽ

አድርጓል። ይኸው የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ ስለ ኢኮኖሚያዊ መብቶቻቸውም ”ሴቶች ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደር፣ የመቆጣጠር፣ የመጠቀምና የማስተላለፍ መብት አላቸው። በተለይም መሬትን በመጠቀም፣ በማስተላለፍ፣ በማስተዳደርና በመቆጣጠር ረገድ ከወንዶች ጋር እኩል መብት አላቸው። ሴቶች የቅጥር፣ የሥራ ዕድገት፣ የእኩል ክፍያ እኩል መብት አላቸው። ሴቶች በብሔራዊ የልማት ፖሊሲዎች ዕቅድና በኘሮጀክቶች ዝግጅትና አፈጻጸም፣ በተለይ የሴቶችን ጥቅም በሚነኩ ኘሮጀክቶች ሐሳባቸውን በተሟላ ሁኔታ እንዲሰጡ የመጠየቅ መብት አላቸው” ሲል ደንግጓል። ማኅበራዊ መብቶቻቸውን አስመልክቶም ”ሴቶች ከጐጂ ባሕል ተጽዕኖ የመላቀቅ መብታቸውን መንግሥት ማስከበር አለበት። ሴቶችን የሚጨቁኑ ወይም በአካላቸው ወይም በአዕምሯቸው ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ሕጐች፣ ወጐችና ልማዶች የተከለከሉ ናቸው” ብሏል። በሌላ በኩል የአስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 916/2008 የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የወል ሥልጣንና ተግባር



106

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ላይ እያንዳንዱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ፖሊሲዎች፣ ሕጎች፣ የልማት ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች በሚያዘጋጅበት ወቅት የሴቶች ጉዳይ መካተቱን እንዲያረጋግጥ ኃላፊነት ሰጥቷል። የሴቶችን መብቶችና ጥቅሞች ለማስከበር የሚረዱ የተለያዩ የፖሊሲ ማዕቀፎች ተዘጋጅተዋል፤ ተሻሽለዋልም። ከዚህ ጋር በተያያዘ በ1986 ዓ.ም ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየውና በቅርቡ ማሻሻያ የተደረገበት ብሔራዊ የሴቶች ፖሊሲ ተጠቃሽ ነው። በተደረገው ማሻሻያም “ብሔራዊ የሥርዓተ-ጾታ እኩልነትና ሴቶች ማብቃት ፖሊሲ“ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ፖሊሲው ምን ላይ አተኩሯል? የኢትዮጵያ መንግሥት የሥርዓተ-ጾታ እኩልነት ለማስፈን መጠነ ሰፊ የሕግ እና የፖሊሲ ማሻሻያዎችን አድርጓል። የሴቶችን ብሔራዊ ፖሊሲ በ1986 ዓ.ም በማዘጋጀት ወደ ስራ ገብቷል። በተጨማሪም ሴቶችን የተመለከቱ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ስምምነቶችን በመፈረምና በማጽደቅ የአገሪቱ የሕግ አካል በማድረግ በርካታ ተግባራትን እየፈጸመ ይገኛል። ያምሆኖ ሴቶችን በሁሉም ዘርፎች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ በማድረግ በኩል አሁንም ሰፊ ልዩነቶች ይስተዋላሉ።

በጤና እንዲሁም በትምህርትና ሥልጠና ዘርፎች የሥርዓተ-ጾታ ክፍተት መኖሩን እንደማሳያ የሚጠቅሱት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሙያ አቶ ይሁኔ ወርቁ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የሥርዓተ-ጾታ እኩልነትን ለማስፈን አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳላቸው ገልጸዋል። ሴቶች ”በኢኮኖሚው ውስጥ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ሥርዓተ-ጾታ ላይ ያለውን ክፍተት ማስተካከል ይጠይቃል” ይላሉ። በአመራር እና በውሳኔ አሰጣጥ ላይ የሥርዓተ-ፆታ ክፍተቶች እንዳሉ መረጃዎችም ያሳያሉ። በሥራ ላይ የነበረው ብሔራዊ የሴቶች ፓሊሲ ከአገሪቷ ሕገ- መንግሥትና ከቤጂንግ የድርጊት መርሀ ግብር ቀድሞ በ1986 ዓ.ም የተቀረፀና ምንም ዓይነት ማሻሻያ ሳይደረግበት ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ነው። የነበረው ፖሊሲ የሴቶችን መብት በማስከበር፣ በየደረጃው በሚካሄዱ የልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ንቁ ተሳታፊ፣ ከትሩፋቱም ፍትሃዊ ተቋዳሽ እንዲሆኑ ከማስቻል አኳያ ሰፊ ክፍተትና ውስንነት የሚስተዋልበት ነው። ይህም በአፈፃፀም ላይ ከፍተኛ ጫናና እንቅፋት እየፈጠረ ስለመሆኑ ሚኒስቴሩ ጠቅሷል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሴቶች ፖሊሲ ከዓለም አቀፉ ነባራዊ

ሁኔታ ጋር ተጣጥሞና በሴቶች የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ በሚያስችል መልኩ የተሻሻለ ስለመሆኑ ተነግሯል። ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ እና አስፈጻሚ አካላት ጋር በየደረጃው ውይይት ሲደረግበት ቆይቷል። በውይይቱ ወቅት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ ሙና አህመድ አገሪቷ ከፖሊሲው በኋላ ከተቀበለቻቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችና የልማት ዕቅዶች ጋር የተዋሃደና ጊዜውን የዋጀ ፖሊሲ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል። የሴቶች መብት እንዲጠበቅና ተሳታፊነትና ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥራዎች እየተሠሩ ቢሆንም አሁንም ቀሪ ሥራዎችን ለማከናወን የፖሊሲው መከለስ ትልቅ አቅም እንደሚሆን ነው የተናገሩት። ይሁንና አጠቃላይ የፖሊሲው ዝግጅት የተጠናቀቀ ቢሆንም አሁንም በሚመለከተው አካል ጸድቆ ወደ ትግበራ አልገባም፤ ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሴቶች ፖሊሲ በቅርቡ ፀድቆ ተፈፃሚ እንደሚሆን የሚኒስቴሩ አንድ የሥራ ኃላፊ ለዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ገልፀዋል። የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ



107

ባገናዘበና የሴቶችን ፍላጎቶችና ጥያቄዎች ማዕከል ባደረገ፣ የሥርዓተ ፆታ እኩልነትን ባረጋገጠ አግባብ ከነበሩ ክፍተቶችና ስኬታማ ተሞክሮዎች ትምህርት በመውሰድ ፓሊሲውን እንደገና መፈተሽና መከለስ አስፈልጓል። አቶ ይሁኔ ከሥርዓተ ጾታ ጋር በተያያዘ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ከዓለም አቀፍና አህጉራዊ ስምምነቶች እንዲሁም ከአገራዊ ዕቅዶች ጋር ለማጣጣም፤ የሥርዓተ-ጾታ እኩልነትን ተግባራዊ ለማድረግ ክፍተቶች በመፈጠራቸው ብሔራዊ የሥርዓተ-ጾታ እኩልነትና ሴቶች ማብቃት ፖሊሲ ማዘጋጀት ማስፈለጉን ገልፀዋል። ብሔራዊ የሴቶች እና የሥርዓተ- ጾታ እኩልነትና ሴቶች ማብቃት ፖሊሲው ራዕይ በሁሉም ዘርፍ የሥርዓተ-ጾታ እኩልነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን ማየት ሲሆን ተልዕኮው የሥርዓተ-ጾታ እኩልነት መዛባት የሚያስከትሉ መሰረታዊ መንስዔዎችን ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ፣ በማስተባበርና ተጠያቂነትን በማስፈን የሥርዓተ-ጾታ እኩልነት ማምጣት ነው። በኢኮኖሚያዊ፣ በማኅበራዊ፣ በፖለቲካዊና በባሕላዊ መስኮች የሥርዓተ ጾታ እኩልነት ማምጣትና በሁሉም ዘርፍ የበቁ ሴቶችን የመፍጠር

ዋና ዓላማም አንግቧል። ሴቶችን በኢኮኖሚ ማብቃት፤ በማኅበራዊ አገልግሎቶች እኩልነትና ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ፤ የሥራ ጫና መቀነስ፤ የመሪነትና ውሳኔ ሰጪነት ተሳትፎ ማሳደግ፤ የሥርዓተ- ጾታ እኩልነትን በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢንጂነሪንግና በሂሳብ ዘርፎች ማስፈን፤ በቤት ውስጥና ያለ ክፍያ ለሚሰሩ የእንክብካቤ ሥራዎች እውቅና መስጠት ከፖሊሲው ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል ናቸው። በጽሑፋችን መግቢያ ታሪኳን ያጋራችን ወ/ሪት ማህሌት “የሰለጠነችበት ሲቪል ምህንድስና (civil Enginering) ወንዶች የሚበዙበት (male dominated)፣ የሴቶች ቁጥር የሚያንስበት የትምህርት መስክ እንደሆነ ትናገራለች። መረጃዎችም የሚያሳዩት በተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት መስኮች ከሚማሩ ውስጥ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ወንዶች ሲሆኑ፤ በርካታ ሴቶች በማኅበራዊ ሳይንስ የትምህርት መስኮች ውስጥ ናቸው። ይህ በእነዚህ ወንዶች በሚበዙባቸው የትምህርት ዘርፎች ሴቶችም በስፋት እንዲሰለጥኑ በፖሊሲው ትኩረት ማግኘቱ ተገቢ ስለመሆኑ ማሳያ ነው። ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ

ሚኒስቴር፣ የክልል አደረጃጀቶች፣ የልማት ድርጅቶች፣ ሲቪል ማኅበራትና የሴቶች መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ የግሉ ዘርፍ፣ የመገናኛ ብዙሀን አካላት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፖሊሲውን ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ጉልህ ሚና ያላቸው ፈጻሚ አካላት ስለመሆናቸው ተጠቅሷል። ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ባለፉት ዓመታት በመንግሥት የተለያዩ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችንና ፓኬጆችን በመንደፍና ተግባራዊ በማድረግ ሴቶችን ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም ችግሮቹን በሚፈለገው ደረጃ በመፍታት ረገድ ውስንነቶች እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ። ሴቶችን በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በማኅበራዊ መስኮች ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ ብዙ እየተሰራ ቢሆንም አሁንም ማነቆዎችና ችግሮች አልተለዩትም። በቀድሞው የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር (2009 ዓ.ም) የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ሴቶች የልማትና ለውጥ ስትራቴጂ ሰነድ የአገራችን ሴቶች የሚገኙበትን ሁኔታ፣ የተሠሩ፣ እየተሠሩ ያሉ እና በቀጣይ በትኩረት መከናወን ያለባቸውን ቁልፍ ጉዳዮችን ተንትኗል። የሴቶችን



108

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተከናወኑ በርካታ ሥራዎች የተመዘገቡ ውጤቶች ቢኖሩም ወደ ላቀ ደረጃ ከማሸጋገር አኳያ ያለው የአመለካከት ችግር፣ በየደረጃው ያለው አመራር ቁርጠኝነት ማነስ፣ በሁሉም አካላት የአቅም ውስንነት መኖር፣ የተጠያቂነት አሰራር አለመጠናከር፣ ሥራ አጥነትና ለሴቶች ተስማሚ አገልግሎቶች አለመስፋፋት ቁልፍ ችግሮች መሆናቸውን አመላክቷል። Global Majority E-Journal, Vol. 11, June 2020) Closing the Gender Gap በሚል ርዕስ ያስነበበው ጽሑፍ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ሦስት መመዘኛዎችን (Reproductive health, Empowerment, and Economic status) መሰረት በማድረግ በ188 የዓለም አገራት በተሰራ ዳሰሳ ኢትዮጵያ 173ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ያስረዳል። በመሆኑም በአገራችን የሥርዓተ ጾታ ልዩነት በተለይም ደግሞ ጾታዊ ጥቃት ሴቶች ላይ እያስከተለ ያለውን አካላዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ እና ማኅበራዊ ጠባሳ ለማጥፋት መረባረብ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ትልቁና ቁልፍ የቤት ሥራቸው ሊያደርጉት ይገባል። የኢትዮጵያ የአሥር ዓመት የልማት ዕቅድ (2013-2022)

ሰነድ ላይ ”በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው የተዛባ አመለካከት፤ የሥራ ዕድሎች በቂና ዘላቂ አለመሆናቸው፤ የሚሰጡ የሙያና የክህሎት ሥልጠናዎች ማነስ፣ የሴቶች የመደራደርና የመወሰን አቅም ማነስ፤ በዋና ዋና የውሳኔ ሰጪነት ቦታዎች ተሳትፎና ውክልና ማነስ፤ ወደ አመራርና ውሳኔ ሰጪነት የማምጣት ችግር፤ የመንግሥት ተቋማት የሴቶችን፣ የሕፃናትንና የወጣቶችን ጉዳይ የዋና ሥራቸው አካል አድርገው አለመሥራት የታዩ ዋና ዋና ተግዳሮቶች ናቸው” በማለት የችግሮቹን ስፋት አመላክቷል። አያይዞም ”የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ በተወሰዱ እርምጃዎችና በተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች በፌዴራል ደረጃ የሴቶችን ውሳኔ ሰጭነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 38 ነጥብ 8 በመቶ፣ በሕግ ተርጓሚው 20 ነጥብ 6 በመቶ፣ በከፍተኛ የአሥፈጻሚ አካላት ደረጃ 50 በመቶ፣ በመካከለኛ አመራርነት ቦታ 22 በመቶ ማድረስ ተችሏል” ሲል አስፍሯል። ባለፉት ዓመታት በተሰሩ የግንዛቤና የንቅናቄ ሥራዎች በሕብረት ሥራ ማኅበራት ከተደራጁ ጠቅላላ የሕብረት ሥራ አባላት መካከል የሴቶች ድርሻ 30 ነጥብ 5 በመቶ ደርሷል። በተመሳሳይ በጥቃቅንና አነስተኛ

ልማት ዘርፍ በመደራጀት ከተፈጠረው የሥራ ዕድል ውስጥ 41 በመቶ የሚሆነው የሴቶች ድርሻ ነው። በግብርና ዘርፍ የሴቶች የቴክኖሎጂ አጠቃቀም 27 ነጥብ 4 በመቶ የደረሰ ቢሆንም ከወንዶች ጋር ሲነጻጻር በ52 በመቶ ያንሳል፤ በግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት የሴቶች ተጠቃሚነት 23 በመቶ ሲሆን ይህም አሃዝ ከወንዶች ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው። እነዚህን ቁጥሮች እንደማሳያ አነሳን እንጂ በሌሎችም መስኮች የሴቶች ተሳትፎ አነስተኛ ነው። ከአገሪቷ ሕዝብ 50 በመቶው ሴቶች እንደመሆናቸው ቀደም ሲል የተጠቀሱት መረጃዎች የሚያሳዩአቸው መሻሻሎች ቢኖሩም በቂ ሥራ ተሠርቷል በሚያስብል ደረጃ ላይ አለመድረሱን ነው። በመሆኑም በቀጣይ ሴቶች ተጠቃሚነታቸው፣ ውክልናቸውና ተሳትፏቸው እንዲረጋገጥና በአገር ልማት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል። ተምሣሌት … ሴቶች ስለራሳቸው ያላቸውን የተዛቡ አመለካከቶች በመቅረፍ ለችግሮቻቸው በቀዳሚነት የመፍትሔ አካል



109

ሆነው መንቀሳቀሳቸው ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ብሎም መብታቸውን ለማስከበር ለሚደረገው ጥረት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። ስለራሳቸው ያላቸውን የበታችነት አስተሳሰብ መቀየር፣ በራስ መተማመን ማጎልበትና በአካባቢው በሚካሄዱ የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ እንቅስቃሴዎች በንቃት መሳተፋቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተጠቃሚነታቸውን እውን ለማድረግ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው። ባለታሪካችን ማህሌት ለዚህ ጥሩ ማሳያ የምትሆን ጠንካራ እና የጽናት ተምሣሌት የምትሆን ሴት ናት። ከእርሷ የሕይወት ተሞክሮ ብዙ ትምህርት መውሰድ ይቻላል። በትምህርት ዓለም በዩኒቨርሲቲ ደረጃ እያሉ የራስን ሥራ ለመጀመር መነሳት በራሱ ትልቅ የሥነ- ልቦና ጥንካሬ መገለጫ ነው። ዕቅድን ወደ ተግባር ለመለወጥ ብዙዎች በሚቸገሩበት በዚህ ወቅት በድፍረት ለብቻ ሆኖ ከትምህርት ጎን ለጎን የራስን ሥራ መሥራት በራሷ የመተማመን ድፍረቷን ያሳያል። በዚህ ሳትገደብ ሁኔታዎችና ወቅቶች የሚፈጥሩባትን ተግዳሮቶች በመቋቋም ከአንደኛው ወደ ሌላኛው ሥራ እየቀያየረች

ለመሥራት መንቀሳቀሷም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ብዙዎችን ለኪሳራና ለሥነ-ልቦና ቀውስ ሲዳርግ እርሷ ችግሩን ተቋቁማ ስኬታማ መሆኗም የጥንካሬዋ መገለጫ ነው። በወ/ሪት ማህሌት የሕይወት መንገድ ውስጥ የእናቷን ሚና በግልጽ ማየት ይቻላል፤ ጥንካሬን፣ በራስ መተማመን፣ ድፍረትን ስላስተማሯት ለስኬት በቅታለች። ይህን እውነታ “እናቴ ‘የተገላበጠ ድስት አያርም‘ ትለን ነበር። መውደቅን አውቃለሁ፤ ሰው ሲወድቅ እዛው የወደቀበት ቦታ መቆም እንደማይኖርበትም ከሕይወት ልምዴ ተምሬያለሁ። ለዚህም ነው የተለያዩ ሥራዎችን እየሞከርኩ እዚህ ደረጃ የደረስኩት። አሁንም ብዙ እንደሚቀረኝ ነው የሚሰማኝ“ በማለት ነው የገለጸችው። ባለታሪካችን ለሴት ወይም ለወንድ ብቻ ተብለው በልማድ ስለተለዩ የሥራ መስኮች ባነሳችው ሃሳብ”እኩልነት የሚለው ቃል ዝም ብሎ ጣል የሚደረግ አይደለም። በተለያዩ የሥራ መስኮች በተጨባጭ ለወንዶች፣ ለሴቶች እየተባለ ሲሰራ ይታያል፣ ይህ መስተካከል ያለበት ነው። ሥራ ለመቀጠር ለምዝገባ የሄደች ሴት ‘ብየዳ፣ ወይም መካኒክ በሚለው የሥራ መደብ መስራት እፈልጋለሁ’ ስትል የምትስተናገደው ለሴት

ጥሩ ነው ብለሽ ነው? የሚል አስተያየት ነው የሚያጋጥማት። ይህ መታረም ያለበት አመለካከት ነው” ትላለች። ሴቶች በሥራ ገበታቸው ላይ ብዙ አይነት ፈተናዎች እ ን ደ ሚ ገ ጥ ሟ ቸ ው የምትገልጸው ማህሌት የራስን ቀይ መስመር ማበጀት እንደሚያስፈልግ ትመክራለች። “ሴት በመሆኔ በጣም ብዙ መልካም አጋጣሚዎችን ባገኝም በማሠራት ሂደት ላይ በጣም ብዙ ትግል አልፌያለሁ፣ አሁንም እያለፍኩ ነው” ብላለች። አሁን ካለችበት ወደተሻለ ስኬት ለመድረስ የበለጠ የመስራት ውጥን እንዳላትም እንዲሁ። አንዲትን ሴት በኢኮኖሚ ማቋቋም ማለት በሥሯ ያሉ ብዙ ሰዎችን መጥቀም እንደሆነ የምትገልጸው ማህሌት ሴትን ማገዝ ማኅበረሰብን ማገዝ ስለመሆኑ የራሷን ተሞክሮ እንደ ማሳያ ታቀርባለች። ከድርጅቷ የሚወጣውን ተረፈ ምርት ለእንጀራ መጋገሪያ (ማገዶ) ስለሚሆን እናቶች ያለምን ክፍያ ወስደው ይጠቀሙበታል። ድርጅቱ በቋሚ እና በኮንትራት ቅጥር የሚሠሩ ሴት አናጺዎችን ጭምር ያካተተ የባለሙያዎች ስብስብ አለው። ባለሙያዎቹ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እርስ በእርስ በመመካከርና በመፍታት ይደጋገፋሉ። ይህም



110

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ማህሌትን በእጅጉ ያስደስታታል። በክልሎች በተለይም ከከተማ ራቅ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ሴቶች በርካታ ጫናዎችን ተቋቁመው ሕይወታቸውን ይገፋሉ የምትለው ማህሌት፤ ከተሜዎቹ ከእነዚህ ሴቶች ተሞክሮ ሊወስዱ እንደሚገባ ትመክራለች። “ለእኔ እዚህ መድረስ ምክንያቱ አይዞሽ፣ በርቺ እየተባልኩ በማበረታቻ ማደጌ ነው፤ በዚህ ረገድ ወላጆች እና ማኅበረሰቡ በታዳጊ ሴቶች ላይ የሚሠራው ሥራ አመለካከት እና ስብዕናን በመቅረጽ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው“ ትላለች። ሁሉም ሰው የማደግና የመሻሻል ዕድል ማግኘት ይሻል፤ መንግሥትም ይህን ዕድል ለዜጎቹ ማመቻቸት ቀዳሚ ተግባሩ ነው። “ፖሊሲዎች ሲቀረፁ፤ ከዝግጅት ጀምሮ በጉዳዮቹ ላይ ተሞክሮ ያላቸው ዜጎችና ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ቢሰጡባቸው ፖሊሲዎች ወደ ትግበራ ሲገቡ አፈጻጸማቸው ውጤታማ ይሆናል“ ስትል ማህሌት አስተያየቷን ሰንዝራለች። መውጫ መንገዶች ልማት ዕውን ሊሆን የሚችለው የማኅበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ አቅም በማጎልበት፣ የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎችም መሰረታዊ አገልግሎቶችን ተደራሽነት በማረጋገጥ ነው። በሥርዓተ ጾታ

ላይ ሚዛናዊ ያልሆነ ግንኙነት (Gender gap) ባለበት ሁኔታ ልማትን ማረጋገጥ አዳጋች ይሆናል። ሚዛናዊ ያልሆነ ግንኙነት ሰዎች ሐብት፣ ንብረት፣ ትምህርት፣ ጤና ወዘተ. . . በማግኘት የሚጠበቅባቸውን ሚናና ኃላፊነት በአግባቡ እንዳይወጡ ያደርጋል። ስለሆነም የአንድን አገር ልማት ለማፋጠን በሰዎች መካከል ያለውን ማንኛውንም ዓይነት ሚዛናዊ ያልሆነ ግንኙነት ደረጃ በደረጃ መቀነስ ያስፈልጋል። ድህነትን ለማስወገድ በሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ማጎልበት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ሴቶች በቤታቸው፣ በአካባቢያቸው፣ በአገርም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ወሳኝ ሚና አላቸው። ሴቶች ያልተሳተፉበትና ተጠቃሚ የማይሆኑበት ማናቸውም ዓይነት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፓለቲካዊ፣ ባሕላዊና አካባቢያዊ እንቅስቃሴዎች፤ በግማሽ ጉልበት፣ በግማሽ እውቀት፣ በግማሽ ጥረት ላይ የተመሰረቱ ያደርጋቸዋል። ሴቶች የማኅበረሰቡ የጀርባ አጥንቶች ከመሆናቸው ባሻገር ቤተሰባዊም ሆነ አገራዊ ዕድገትን አስተማማኝ ማድረጊያ መሰረቶችም ናቸው። የትኛውም

ዓይነት የልማት እንቅስቃሴ እውን ሊሆን የሚችለውም ሴቶችን ባማከለና እኩል ተጠቃሚነታቸውን ባረጋገጠ መልኩ ሲከወን መሆኑ እሙን ነው። የሴቶችን አቅም በማጎልበት ተሳታፊነታቸውን ሚዛናዊ ማድረግ፤ በፖለቲካው መስክም የውሳኔ ሰጪነት አቅማቸውን በማሳደግ ተሳታፊነታቸውን ማረጋገጥ ከችግሮቻችን መውጫ መንገዶች መሆናቸው አጠያያቂ አይደለም። ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት በሚደረገው ጉዞ ሴቶችን ለማሳተፍ መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች የስዊድን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እ.ኤ.አ በ2009 ይፋ ባደረገውና ‘Women’s Economic Empowerment: Key Issues and Policy Options/Sida Policy‘በሚል ርዕስ ባዘጋጀው ጽሑፍ እንደሚከተለው ተንትኗቸዋል። ”የሴቶችን አቅም ስናሳድግ ሰርተው የሚያገኙትን ክፍያ ማሳደግ ያስችላል። ከሥነ- ተዋልዶ ጋር የተያያዙ ኃላፊነቶችን ቀለል የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀምና የወንዶችን ሚና በማሳደግ በሴቶች ላይ ያለውን ጫና መቀነስ፣ መሬትና መኖሪያ ቤትን ጨምሮ ሐብትና ንብረቶች አስመልክቶ የሴቶችን መብት ከወንዶች እኩል ማድረግ፣



111

የፋይናንስ ሥርዓቱ ውስጥ ሴቶች በስፋት እንዲሳተፉ ማስቻል፣ ስለ ሥርዓተ ጾታ ግንዛቤ በመፍጠር ሴቶች ማኅበራዊ ጥበቃ እንዲያገኙና ቀውስ በሚያጋጥም ጊዜ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ትኩረትም እንዲያገኙ መስራት” ናቸው። ጽሑፉ አያይዞም ሴቶችን ከወንዶች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ በሲቪል ማኅበራትና በፖለቲካው በጋራ በመንቀሳቀስ እየመጣ ያለው መሻሻል መፈተሹ አስፈላጊ ስለመሆኑ ምክረ ሀሳብ አቅርቧል። ”ለሴቶች ልዩ ድጋፍ በማድረግ (Affirmative action) ሴቶች በሚካሄዱ ምርጫዎች እኩል ተወዳድረው ወደ አመራርነት እንዲመጡና ብቁ መሪዎች መሆናቸውን እንዲያሳዩ ማድረግ፣ የትምህርት ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ ማገዝ የሚሉትን ዘርዝሯል። በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ ልማዶች ሴቶች ከወንዶች እኩል ወደ ኃላፊነትና የመሪነት ቦታዎች እንዳይመጡ ማነቆ መሆናቸውንም አመላክቷል። እንደመፍትሔ ያቀረበውም እነዚህን ልማዶች ለመለወጥ በተከታታይ ሰፊ ሥራዎችን መስራት እንዲሁም የሕግ ማሻሻያዎችን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ነው። የሰሜን አውሮፓ እና ስካንዲኒቪያን አገራት እ.ኤ.አ

በ1960ዎቹ ጀምሮ ሴቶችን በትምህርት እና በኢኮኖሚ መስክ እንዲሳተፉ ማድረጋቸው ወደ ሕግ አውጪ መዋቅሮች እንዲቀላቀሉ መንገድ ጠርጓል። በወንዶችና በሴቶች መካከል ሙሉ እኩልነት ለማስፈን ወንዶችና ሴቶች በልማድ በማኅበረሰቡና በቤተሰብ ውስጥ የነበሯቸው ሚና ላይ ያለውን አረዳድ፣ እሳቤ ማጤን ጠቃሚ ነው። የአንድን አገር የተሟላ ዕድገት፣ የዓለምን ደህንነትና የሰላም ተልዕኮ እውን ለማድረግ ወንዶችና ሴቶች በልማድ በኅብረተሰብና በቤተሰብ ውስጥ የነበሯቸውን ሚናዎች መለወጥ ይጠይቃል። በኢትዮጵያ መንግሥት፣ ኅብረተሰቡና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሰጡት ትኩረትና ዘርፈ ብዙ ምላሾች የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየጎለበተ በመምጣቱ በሁሉም መስኮች የድርሻቸውን ለመወጣት ጥረት በማድረግ ላይ ስለመሆናቸው በየመስኩ እያስመዘገቡት ያለው ውጤት አስረጂ ነው። አገራችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ በምታደርገው ሂደት ሴቶችን በየደረጃው ይበልጥ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ ብሎም የመሪነት ሚናቸውን እንዲወጡና በተደራጀ አግባብ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ በትኩረት መስራት

ይጠይቃል። የሕግ ማዕቀፎች፣ አዋጆች፣ ፖሊሲዎች፣ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች፣ ለሥርዓተ ጾታና ለሴቶች ተጠቃሚነት ትኩረት በሰጠ መልኩ እንዲዘጋጁና እንዲተገበሩ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ፤ በየደረጃው ያለውን የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎና ውሳኔ ሰጪነት ለማሳደግ በቂ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ የመንግሥት ኃላፊነት ነው። ሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች የሥርዓተ ጾታን ጉዳይ ተቋማዊ በማድረግ በሁሉም ሥራዎቻቸው ውስጥ ማካተት ይኖርባቸዋል። የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተቀናጀ መልኩ መንቀሳቀስና ድጋፍ ማድረግ፣ እኩልነታቸውን ማመንና መቀበል፣ ለሴቶች ተገቢውን ክብርና ቦታ መስጠት ከኅብረተሰቡና ከማኅበረሰብ አደረጃጀቶች የሚጠበቁ የቤት ሥራዎች ናቸው። የኃይማኖት አባቶችና ተቋማት በሴቶች የእኩልነት መብቶች ዙሪያ ተከታዮቻቸውን ማስተማር፣ የተዛቡ አመለካከቶችን ማረቅ፣ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችንና ጥቃቶችን በማስቆም አርዓያ ሊሆኑ ይገባል።



112

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ማኅበራዊ

አለርት

(በአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ትብብር የተዘጋጀ)



113

አለርት ከትናንት እስከ ዛሬ

በልዕልት ዘነበወርቅ ስም የተሰየመው ለሥጋ ደዌ በሽታ ሕሙማን ሕክምና መስጫ እና መንከባከቢያ ይሆን ዘንድ በ1924 ዓ.ም በንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለሥላሴ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረና ከበርካታ ዓመታት በኋላ በ1965 ዓ.ም ስያሜው ተቀይሮ አለርት (መላው አፍሪካ የሥጋ ደዌ የቲቢ መከላከያ እና ትምህርት መስጫ ማዕከል) የሚሰኘው የሕክምና ማዕከል በኢትዮጵያ የስጋ ደዌ በሽታን በማከም ጉልህ አሻራ ያሳረፈ ተቋም ነው። አሁን አለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚል ስያሜ ያገኘው ይህ ሆስፒታል በስጋ ደዌ ሕክምና ብቻ ሳይወሰን በየጊዜው አገልግሎቱን በማስፋት ሁሉን አቀፍ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።

በመንገሻ ገ/ሚካኤል



114

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

በአገራችን የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለሥጋ ደዌ ሕሙማን ተብሎ የተቋቋመ የመጀመሪያው የሥጋ ደዌ ማዕከል ነው። የሥጋ ደዌ በሽታ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ እንደ ፈጣሪ ቁጣ ተደርጎ በመወሰዱ የበሽታው ተጠቂዎች ማኅበራዊ መብቶቻቸውን ተነፍገው ‘አብያተ ክርስቲያናትን መጎብኘት፣ ከወንዝ ውሃ መጠጣትና ጤናማ ሰዎችን መንካት አይችሉም’ በሚባልበት ዘመን ለአገልግሎት የተከፈተው

ይህ ማዕከል፣ በወቅቱ በማኅበረሰቡ ዘነድ የነበረውን አመለካከት በመቀየር በሥጋ ደዌ ሕሙማን ላይ ይደርስ የነበረውን መገለል እና መድሎ በማስቀረት ያበረከተው አስተዋፅኦ የላቀ ነው። ከአዲስ አበባ በስተ ደቡብ ምዕራብ የሚገኘው ይህ ሆስፒታል የሥጋደዌ ታማሚዎች በማዕከሉ ሕክምና ከተደረገላቸው በኋላ የተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን

እንዲያገኙ ሲያደርግ ቆይቷል። ታካሚዎቹ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ ቤተ-ክርስቲያን እና መስጊድ ተገንብቶላቸው ካህናትና ሼክ ተመድበውላቸው፤ ለልጆቻቸውም ትምህርት ቤት አገልግሎቶችን ሲያገኙ ቆይተዋል። በአሁኑ ወቅት በሆስፒታሉ ዙሪያ የሰፈሩት ከአገሪቷ የገጠር አካባቢዎች ለሕክምና መጥተው መኖሪያቸውን በዚያ ያደረጉ ማኅበረሰቦች መሆናቸውን የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና



115

ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ሺመልስ ገዛኸኝ ይናገራሉ። እነዚህ የማኅበረሰብ አባላት አሁን ከአድልዎና መገለል ነፃ የሆኑበት ደረጃ ተደርሷል የሚሉት ዶ/ር ሽመልስ፣ የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አድሎና መገለል እንዳይኖር በሠራው ሥራ የሥጋደዌ ታካሚ ቤተሰብ ነኝ ብሎ ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበት ሁኔታ መፍጠር ተችሏል ይላሉ። ሆስፒታሉ ከሕክምና ባሻገር የሥጋደዌ ሕሙማን በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ በርካታ ሥራዎች ሰርቷል። በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ተደራጅተው የሚሠሩበትን ዕድል በማመቻቸት የኢኮኖሚ አቅማቸውን አዳብረው የላቀ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ከውጭ አገር ዕቃዎችን ከቀረጥ ነፃ ማምጣትን ጨምሮ በተለያየ የንግድ ሥራዎች ላይ ሲሳተፉ በመንግሥት የሚደረጉላቸው ድጎማዎች መኖራቸውን የገለፁት ዶ/ር ሽመልስ፣ የሥጋደዌ ታካሚዎች ሕክምና አግኝተው ካገገሙ በኋላ ቤተሰብ መስርተዋል። በመንግሥት በሚወጡ አዋጆች ተካቶ ከነቤተሰባቸው ነፃ ሕክምና እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል። እነዚህ ውጤቶች የተገኙት የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ላለፉት

90 ዓመታት ባደረገው ከፍተኛ ጥረት መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል። የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከሥጋደዌ ባሻገር በቆዳ እና በዓይን ሕክምና የረዥም ጊዜ የዳበረ ልምድ ያለው ተቋም ነው። ሆስፒታሉ ከቆዳ ሕክምናዎች ጋር በተያያዘ ትልቅ ልምድ አለው የሚሉት ዶ/ር ሺመልስ፤ በዚህ የሕክምናው ዘርፍ በአገር ደረጃ ከሚገኙ የቆዳ ሕክምና ስፔሻሊስቶች “በዚህ ማዕከል ያልሠለጠነ ይኖራል ብዬ አልገምትም፤ በአገሪቷ የሚገኙ የተለያዩ የቆዳ ሕክምና የሚሰጡ ማዕከላት የአለርት ውጤቶች ናቸው” ይላሉ። ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ ከቆዳ በሽታዎች ጋር በተያያዘ ትልቅ ልምድ ያለው በመሆኑ ከአገር ውስጥ አልፎ ከተለያዩ አገራት የሚመጡ የሕክምና ባለሙያዎች ሥልጠና የሚወስዱበትና ጥናትና ምርምሮች የሚካሄድበት ተቋም ነው። በተመሳሳይ በዓይን ሕክምና አገልግሎቱ በአገሪቷ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሕክምና የሚሰጡ በሙያው አንቱ የተባሉ የሕክምና ባለሙያዎች የሚገኙበት ተቋም ነው። የድንገተኛና ፅኑ ሕክምና፣ የአጥንት፣ የሣምባ

ነቀርሳ እና የፕላስቲክ ሰርጀሪ ሕክምናዎችም ሆስፒታሉ የሚታወቅባቸው የሕክምና ዘርፎች ናቸው። ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ ትልቅ የፕላስቲክ ሰርጀሪ ዲፓርትመንት እንዳለው የሚናገሩት ዶ/ር ሺመልስ፤ እንደ አገር ከባድ የሚባለው የፕላስቲክ ሰርጀሪ ሕክምና የሚሰጠው በአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆፒታል እንደሆነ ያረጋግጣሉ። ወደፊትም ሆስፒታሉ በዚህ ዘርፍ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል። የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሲቋቋም ሕክምና መስጠት ብቻ ሳይሆን ሥልጠናም እንዲሰጥ ታስቦ የተገነባ ነው። የትልቅና አንጋፋ ሥልጠና ማዕከል ባለቤት የሆነው ሆስፒታሉ በሕክምና ዘርፍ በርካታ ባለሙያዎችን በማሠልጠንም ቀዳሚ ተቋም ነው። ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ ከሕክምና አገልግሎት በተጨማሪ እንደ ሌሎች መሰል ተቋማት በስፔሻላይዜሽን ሕክምና ዘርፎች ሐኪሞችን በማሠልጠን የአገሪቷን የጤና አገልግሎት እንቅስቃሴ በመደገፍ ያበረከተው አስተዋፅኦ ጉልህ ነው። በተለይም ከሥጋደዌ ሕክምና ጋር ተያይዞ ለበርካታ ባለሙያዎች ሥልጠና በመስጠት ለዘርፉ ሕክምና ዕድገት ጉልህ



116

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ሚና ተጫውቷል የሚሉት ዶ/ር ሺመልስ በኢትዮጵያ የሥጋደዌ ሕክምና አገልግሎት ለሚጀምሩ የሕክምና ተቋማት እንደ ሞዴል ሆኖ ሲያገለግል መቆየቱን አክለዋል። ከዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት / World Health Organization/ “የአፍሪካ ማሠልጠኛ ማዕከል” የሚል እውቅና ያገኘው የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በአፍሪካ ደረጃም ጉልህ አስተዋጽኦ ያለው ተቋም ነው። የመላው አፍሪካ የቲቢና የሥጋ ደዌ ሕክምና ማሠልጠኛ ማዕከል ሆኖ ሲያገለግል የቆየው ይህ ተቋም ከበርካታ የአፍሪካ አገራት ለሚመጡ ባለሙያዎች ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል፤ ከ14 የአፍሪካ አገራት የመጡ የጤና ባለሙያዎች ሥልጠና ያገኙ ሲሆን፤ ከዚህ ባገኙት እውቀት እና ልምድ እንደ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ ባሉ አገራት ተመሳሳይ ማዕከላት መገንባት ችለዋል። የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በመንግሥት ልዩ ትኩረት እያገኘ በመምጣቱ ተቋሙ ለወደፊት ብዙ ተስፋ ሰንቋል ይላሉ ዶ/ር ሺመልስ። ሆስፒታሉ እንደ አገር የመጀመሪያ የሆነውን የአደጋ (Trauma) ሕክምና መስጫ፤ አንድ ሺህ አልጋ የሚይዝ፣ 17 የቀዶ ሕክምና ክፍሎች ያሉት ትልቅ ማዕከል እየገነባ በመሆኑ

ወደፊት በርካታ ሥራዎች የሚከወኑበት ማዕከል ነው። ይህ ማዕከል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ የመጡትን በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱና ለሕመም፣ ለአካል ጉዳት እና ለሞት ለሚዳርጉ አደጋዎች የሚሰጠውን ሕክምና በማሻሻል ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው ተስፋ ተጥሎበታል። ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ የአገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን ለማሳደግ የተለያዩ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እያደረገ ነው። ከእነዚህም የፕላስቲክ ደርማቶሎጂ ማዕከል የሚሆነው ባለ 15 ወለል ሕንፃ ግንባታ ይገኝበታል። በሌላ በኩል ለሕፃናት የሚሰጡ የሕክምና አገልግሎቶችን ማሻሻልና ማዘመን የሚያስችል ባለ ስምንት ወለል ሕንፃ የሕፃናት ሆስፒታልም እየገነባ ይገኛል። ሆስፒታሉ ባለፉት 90 ዓመታት የሥጋደዌ ማዕከል ብቻ ከመሆን ተነስቶ ወደ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ያደገበት ሂደት ትልቅ ስኬት የሚሉት ዶ/ር ሺመልስ፤ ቀደም ባለው ጊዜ እንደ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት (NGO) ስለሚታይ፣ በነጮች ይመራም ስለነበር በእርዳታ ብቻ ይንቀሳቀስ እንደነበረ አንስተዋል። አሁን ከመንግሥት በሚያገኘው ድጋፍ የተለያዩ የማስፋፊያ

ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ማድረግ ችሏል። ሆስፒታሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጽዱ ጤና ተቋም ፕሮጀክት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ከተመረጡ ሁለት ጤና ተቋማት አንዱ ነው። የደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድን በዘመናዊ መንገድ ማሻሻል፣ የሕክምና ቁሳቁስና ሕንጻ እድሳት፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ለአገልግሎት ማብቃት፣ እንዲሁም የአቅጣጫ ጠቋሚ ምልክቶችን በቅጥር ግቢው ውስጥ በማኖር አለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ከኢንፌክሽን የፀዳና ለተገልጋዮቹ ምቹ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል። ይህ ተቋም በተመረጡት የተለያዩ የሕክምና ዘርፎች የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ ሲሆን በሚቀጥሉት አምሥት ዓመታት እንደ አህጉር ትልቅ የድንገተኛ አደጋ ሕክምና (Trauma) ማዕከል የመሆን ራዕይ ሰንቋል። ማዕከሉ የድንገተኛና የአጥንት እንዲሁም የጀርባ እና የነርቭ ቀዶ ሕክምናዎች የሚያጠቃልል ነው። አገልግሎቱን ለመጀመር መንግሥት ከሶሪያ መንግሥት ባገኘው ገንዘብ የሕክምና ግብዓት ግዥ እየተካሄደ ነው። እንደ አህጉር የፕላስቲክ ሰርጀሪ፣ የዓይን እና የቆዳ ሕክምና የልህቀት ማዕከል መሆን ሌላው የተቋሙ ራዕይ ነው። እስከ አሁን



117

በፕላስቲክ ሰርጀሪ ከዛምቢያና ዚምባብዌ እየመጡ ሥልጠና የሚወስዱ ባለሙያዎች መኖራቸውን የጠቆሙት ዶ/ር ሺመልስ፤ ይህን የሥልጠና አገልግሎት በማሳደግ በአፍሪካ ዕውቅ የፕላስቲክ ሰርጀሪና ሕክምና የሚሰጥበት ተቋም ለመሆን እንሰራለን ብለዋል። ይህም ብቻ አይደለም ሆስፒታሉ ስፔሻላይዝድ የሕፃናት ሕክምና ማዕከል የመሆን ዕቅድም አለው። የሕፃናት ሕክምና ማዕከሉ መሰረታዊ የሆኑትን ሕክምናዎች ብቻ ሳይሆን ሪፈራል የሕፃናት ሕክምና መስጠት የሚያስችል ነው። ራሱን የቻለ የሕፃናት የዓይን ሕክምና ማዕከል ግንባታ የተጠናቀቀ ሲሆን በአንድ ዓመት ውስጥ ሥራ ይጀምራል ተብሏል። የሕፃናት የካንሰር፣ የኩላሊት እና ከባድ የሚባሉ የሕፃናት ቀዶ ሕክምናዎች ሪፈራል ማዕከል የመሆን ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ዶ/ር ሺመልስ አብራርተዋል። ተቋሙ በተጨማሪ በሌላ አገር የማይሰጡ የሕክምና ማዕከላትን በማስጀመር የሜዲካል ቱሪዝምን የማሳደግ በዚህም የልህቀት ማዕከላቱ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ የማድረግ፤ ቀልጣፋና ጥራታቸውን የጠበቁ አገልግሎቶች ለመስጠት ሆስፒታሉን የማዘመንና ወደ ዲጂታላይዜሽን የመቀየር ሥራ

እያከናወነ ይገኛል። በዓመት እስከ 500 ሺህ ታካሚዎችን የሚያስተናግደው ይህ ግዙፍ የሕክምና ተቋም ባቀደው ልክ እንዳይሰራ የታካሚዎችን ፍሰት ለማስተናገድ የሚበቃ መሰረተ ልማት አለመኖር ተግዳሮት ሆኖበታል። ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች ቢኖሩም ሆስፒታሉ የአልጋ እጥረት፣ የቦታ ጥበት፣ የመሰረት ልማት አለመስፋፋት በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳርፈዋል። የተቋሙ ሥራ ስፋት ያለው በመሆኑ ይህንኑ የሚመጥን ተጨማሪ በጀት እንደሚፈልግ ዶ/ር ሺመልስ ሳይጠቅሱ አላለፉም። የሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ዙሪያው ግልጽ የሆነና ድንበር የሌለው በመሆኑ ተጨማሪ ፕሮጀክቶችን ለማስፋፋት ተቸግረናል የሚሉት ዶክተሩ ለሆስፒታሉ በተሰጠው የይዞታ ካርታ ውስጥ ከመቶ በላይ አባወራዎች ይኖራሉ፤ እነዚህ የሥጋደዌ ታካሚዎች ጎጆ ቤት ሰርተው የሚኖሩ ሲሆኑ ከሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ እንዲወጡ ማድረግና ሌላ መሰረተ ልማት መዘርጋት አልተቻለም። በቀጣይ ሆስፒታሉ ከክፍለ ከተማው ጋር በመነጋገር ዲጂታል ካርታ ለማውጣት እየተሰራ እንደሆነም አብራርተዋል።



118

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ባሕል እና ኪነ-ጥበብ

ማኅበራዊ



119

እንደ መግቢያ እኔ በፓለቲካ ምሕዋር ውስጥ ብኖርም ዐይን ያወጣሁ ፖለቲከኛ ግን አይደለሁም። መጻፍ ብችልም ጥሩ ተመራማሪ ምሁር ነኝ አልልም። መናገር ብችልም ለሚገባው ተገቢ ቃላት መርጬ መናገር አልችልም። ታዲያ! እኔ ማን ነኝ? ራሴን የሥነ- ጽሑፍ ሰው አድርጌ እቆጥረዋለሁ። ይምረርም-ይጣፍጥ..፣ ይወደድም-ይጠላ...፣ ይከበርም-ይናቅ...፣ ዘመን ተሻጋሪም ይባል ወቅታዊ...፣ ዕድሜዬን በሙሉ ያገባደድሁት በዚህ ሙያ ላይ ተሰማርቼ ነው። እናም! ቀጥዬ የማቀርባትን ወረቀት ሥራዬ ብዬ ከያዝሁት ሙያ፤ አንፃር አንብቡልኝ ወይ ገምግሙልኝ። (ምንም እንኳ ሥራዬ ሥራ የሌለው ሥራ ቢሆንም... )

በጸሀፌ-ተውኔት አያልነህ ሙላቱ



120

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ይህች አጭር ጽሑፍ በውስጧ የያዘችው የራሴን ሃሳቦችና አመለካከት ብቻ ነው። እንደ ምሁራን ጥናቶች በነጮች መረጃ ወይንም ዋቤ መጻሕፍት የተጨናነቀች አይደለችም። የተወሰዱ ሃሳቦችም ቢኖሩ “ምንጩ ከእኛ ነው” ብዬ ስለማምን ልጠቅሳቸው አልፈለግሁም። የሚጠበቅብኝ የራሴን አቋም በራሴ ሃሳብ እንድገልፅ እንጂ “እገሌ እንዳለው” እያልሁ የሌሎችን ሃሳብ እንዳስተጋባ ወይንም እንድኮርጅ አይደለም። እናም! ጽሑፌ ብዙ ጥቅስ የላትም። ከጠቀሰችም የጠቆመችው የአገር ቤት ምሁራን ሥራዎችን ብቻ ነው።

ባሕል ምንድን ነው? ባሕል የሰው ልጅ በረጅም ዘመን ታሪኩ ተፈጥሮን ለማወቅ፣ ለመቋቋም፣ ለመቆጣጠርና የራሱን ሕልውና ለማረጋገጥ፣ ባደረገውና በሚያደርገው ትግሉ የፈጠረውና የሚፈጥረው በየጊዜው እያደገ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የኖረና የሚኖር አጠቃላይ የቁሳዊና መንፈሳዊ ቅርሶች ክምችት ነው። ባሕል ሰውን ከሌሎች እንስሳት የለዩት የማሰብ፣ የመፍጠርና የማምረት ችሎታ ውጤት ነው። እንደማናቸውም ነባራዊና ሕሊናዊ ክስተቶች ሁሉ ባሕልም ለዲያሌክቲካዊ ሕግ ተገዥ ስለሆነ አንድ ባሕል ይፈጠራል፣ ያድጋል፣ ይሞታል።

ሊቁ እና በአገር በቀል እውቀት የተካኑት፤ ተሰማ ሀብተ ሚካኤል ግጽው፤ ከሣቴብርሃን ተሰማ የአማርኛ መዝገበ ቃላት በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 517 ላይ ስለ ባሕል ምንነት የሚከተለውን ብለዋል። “ባሕለ ሀገር” ለሚለው የሰጡት ትርጉም “የአገር ልማድ፣ ወግ፣ ሥርዓት፣ አስተዳደር፣ የሕዝብ ልማድ” የሚል ሲሆን፤ ባሕላተ ቃላት ለሚለው ደግሞ ” የንባብ ሐረግ አካሄድ፣ በተውላጠ ስም፣ በቅጽል፣ በቦዝ አንቀጽ፣ በመስተዋድድ፣ በመስተፃምር፣ በቃል አጋኖ የሚነገር ንባብ” ይሉታል። ከዚህ በኋላ ባሕል የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ በዚህ መልክ ይበይኑታል። “ባህል፣ አባባል፣ አነጋገር፣



121

አለው። በኀብረት መሥራትንና በጋራ መረዳዳትን አጣምሮ የያዘ ነው። ዓለም አቀፋዊነትንና ብሔራዊነትን ያዋሀደ ነው። ፍጹም ሰብዓዊ፣ ታማኝና እውነተኛ ከመሆኑም ሌላ በሕዝብ መዝባሪዎች ላይ እርቅ የለሽ አቋም አለው። ምንጊዜም ዝግጁና ንቁ ነው። አመለካከቱ ብሩህና በነባር ዕውቀት ላይ የታነፀ ሳይንስን መሠረት ያደረገ ነው። የባሕልን አጠቃላይ ገጽታ ለማየትና ምንነቱን ለመገንዘብ፣ በየኀብረተሰቡ የዕድገት ደረጃ ላይ ያለውን ባህሪይ በማወቅ፣ እድገቱንና የእድገቱን ምንጭ መረዳት በእጅጉ ያስፈልጋል። የባሕልን ጥናት በተጨባጭ ሁኔታ አቀናብሮ ለማቅረብ፣ የባሕልን አመጣጥ፣ አመሠራረትና እድገት ለመገምገም የሚቻለውም በባህል ዕውቀት ላይ ተመሥርቶ፣ የኀብረተሰቡን የቁስ አካላዊና የመንፈሳዊ እድገትን በመመርመር ብቻ ነው። ይህን በምናደርግበት ወቅት የባህልን ጥንታዊ ትርጉሞች እንዳለ እንጥላቸዋለን ማለት አይደለም። በእነዚህ ነባር ትርጉሞች ውስጥ የሚገኙትን የእውነትነት ንጥረ ነገሮች መሠረት በማድረግ የባሕልን ትርጉም እናዳብራለን። ባሕል የሰው ልጅ በተከታታይ በማኅበራዊ ተግባሩ ሂደት

ልማድ፣ ሕግ፣ ወግ…” ካሉ በኋላ እንደገና ባሕል ብለው “አገባብ፣ አሰካክ፣ የመጻፍ ባሕል፣ ልዩ ልዩ መንገድ የሚመራ፣ የቋንቋ ባሕል በየወገኑ በእየ ሀገር የሚነገር…፤ ቋንቋ ሥር መሠረቱ አንድ ኾኖ ሳለ በጥቂት የሚለያይ፣ የግዕዝ፣ ዐረብ፣ የሴም ቋንቋዎች ሲሆኑ ባሕላቸው አንድ ነው። ባሕል የግሥ አነጋገር አገሳሥ አመዳደብ ነው” በማለት ይደመድማሉ። በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በአስኳላ ምሁራን የተዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ በገጽ 235 ላይ “ባሕል የኅብረተሰብ የአኗኗር ዘዴ፣ ወግ፣ ልማድ፣ እምነት ነው“ ይላል። ሁለቱ መዝገበ ቃላት ስለ ባሕል የሰጡትን ትርጉም በአዕምሯችን ይዘን ባሕልን በዚህ ጽሑፍ በጥቂቱ ለማየት እንሞክር። ባሕል በታሪክ የተወሰኑ የሕዝብ ችሎታዎች፣ ዕውቀቶች፣ አመለካከቶች፣ አስተሳሰቦች፣ ዝንባሌዎችና ስሜቶች አጠቃላይ ድምር ውጤት ሲሆን፣ ባሕሪውም እነዚህን የባሕል ውጤቶች በምርት ቴክኒክና በሕዝባዊ አገልግሎቶች፣ በሕዝብ የትምህርት ደረጃ፣ ማኀበራዊ ኑሮን በሚያደራጁ፣ ማኀበራዊ ተቋማትን በሚቆጣጠሩ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ እድገቶች፣ በኪነ-ጥበብና በሥነ- ጽሑፍ ሥራዎች ውስጥ መሠረት

መጣልና ቁስ-አካላዊ ማድረግ ነው። በእርግጥ እነዚህን ባሕላዊ ውጤቶች ወደ ቁስ አካላዊነት ለመለወጥና በተለይም የሕዝባዊው ባሕል አካል ለማድረግ የሚጠይቀው ትግል ቀላል አይሆንም። ከየሥርዓተ ማኀበሩ የሚወረሱት ኋላቀር ባሕሎች ትግሉን የበለጠ ውስብስብና ከባድ ያደርጉታል። በዚህ ወቅት በኪነጥበብ ባለሙያው ፊት የሚደቀነው ዓቢይ ተግባር የባሕል ግንባታው ጉዳይ ይሆናል። ሕዝባዊው ባሕል ከኅብረተሰቡ ጓዳ የሚወጣ ስለሆነ፣ ብሔራዊ ቅርጽ አለው፣ ይህም ብቻ አይደለም። ዴሞክራሲያዊ ይዘቱ የጠነከረ ነው። በዚህም መሠረት ብሔራዊው ባሕል ከባሕል ዓለም አቀፋዊ ይዘት ጋር በኅብር የሚዋሀድ እንጂ የሚቃረን አይደለም። ይህም በቅርጹ ብሔራዊ የሆነው ባሕል በይዘቱ ዓለማቀፋዊ ይሆናል። የሕዝባዊ ባሕል እጅግ በጣም ጠቃሚ ባሕርይው አዲሱን ሰው መፍጠር መቻሉ ነው። ይህም አዲስ ሰው አዲስ የሥነ- ምግባር ገጽታዎች ይኖሩታል። አዲሱ ሰው ለሰፊው ሕዝብና ለዴሞክራሲ ግንባታ በቆራጥነት ከመቆሙም በላይ ግለሰባዊነትን ለኀብረተሰቡ የማስገዛት ችሎታ



122

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ውስጥ ያከማቸው የቁስ አካላዊና የመንፈሳዊ እሴቶች አጠቃላይ ድምር መሆኑን ገልፀናል። ባሕል የኀብረተሰብ እንቅስቃሴና እድገት ውጤት ነው ሲባል የምርት ኃይሎችና የምርት ግንኙነቶች ከታላላቆቹ የቁስ አካላዊ እሴቶች አንዱ መሆናቸውን እንረዳለን። ስለዚህ ስልተምርት በአጠቃላይ የባሕል ወሳኝ መሠረት ነው። ባሕል መላውን የማኀበራዊ ኑሮ ማለትም ከምርት ጀምሮ እስከ ርዕዮተ ዓለም መስኮች ድረስ ያሉትን አቅጣጫዎች ያቅፋል። ባሕል የምርት ግንኙነት ነፀብራቅ እንደመሆኑ የእርሱ መለወጥ ባሕልንም ይለውጠዋል። የማኅበረ-ኢኮኖሚው ቅንብር መሻሻል ባሕሉን ጭምር ያሳድገዋል። በዚያም ላይ ባሕል እንደ ማኀበራዊ ኑሮ ብዙ አቅጣጫዎች ያሉት ስለሆነ፣ ከመሠረቱና ከላዕላይ መዋቅሩ ለውጥ አንፃርና ከሚሻሻለው የቀን-ተቀን ኑሮ ጎን የባሕሉም ወሳኝ አቅጣጫዎች በዚያው መጠን አብረው በእድገት ይለወጣሉ። በተለይም ደግሞ በምርትና በኢኮኖሚ ውስጥ የሚከናወኑት ለውጦች፣ በሕዝቡ ባሕሪያት፣ አመለካከቶች፣ አስተሳሰቦች፣ ዝንባሌ፣ ንቃተ ሕሊና፣ የፈጠራ ችሎታና ቋንቋ ላይ ፈጣን ውጤት አሏቸው። ስለሆነም ባሕል የሰው ልጅ

ተፈጥሮን ለመቋቋም ብሎም በቁጥጥሩ ሥር ለማዋልና የራሱን ሕልውና ለማረጋገጥ ባደረገው የረጅም ጊዜ ትግል የፈጠረውና ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ የቁስና የመንፈስ ቅርስ ክምችት ነው። በሰው የተፈጠረው ባሕል ደግሞ ሰውን መልሶ ይፈጥረዋል። በኀብረተሰቡ ውስጥ ተዋህዶ እንዲኖርና ሕልውናው እንዲረጋገጥ የሚያደርገው ባሕል ነው። የአንድ ኀብረተሰብ ጥንካሬ በእያንዳንዱ ግለሰብ ጥንካሬና ግለሰቦችን በሚያስተሳራቸው ሥርዓት ትክክለኛነት ላይ ይመሠረታል። የግለሰቡን ጥንካሬ የሚወስነው ደግሞ ባሕሉ ነው። የሰው ልጆች እድገት ብሩህ ፈለግ የሚተለመውም በሰፊው ሕዝብ የፈጠራ ሥራ ላይ ተመስርቶ ነው። የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አቢይ ተልዕኮ፣ ሰፊው ሕዝብ አዲሱን ታሪካዊ የሆነውን የራሱን ኀብረተሰብ እንዲፈጥር ማነሳሳት ሲሆን፣ ይህም አዲሱ ታሪካዊ ፈጠራ የባሕል ግንባታ ነው። በእርግጥም የባሕል ፈጣሪው ሰፊው ሕዝብ ነው። ዴሞክራሲያዊው ባሕልም በሕዝብ የተፈጠረ ሲሆን የሚያድገውም በሰው ልጅ የተከማቸውን ቁስአካላዊና መንፈሳዊ እሴቶችን መሠረት

አድርጎ ነው። ስለሆነም ዴሞክራሲያዊ ባሕል ከዘመናዊው ሥልጣኔ የእድገት አቅጣጫ ያፈነገጠ ሳይሆን የጥንታዊው የባሕል ቅርስ ሕጋዊ ወራሽ መሆኑንና ለዘመናዊነት መሠረት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ዘመናዊነት ከነባሩ ባሕል ጋር ሳይያያዝና እሱም መሠረት ሳይሆነው፣ ከምንም ተነስቶ መዳበር አይችልም። ዴሞክራሲያዊ ባሕል የሰው ልጅ ባለፈባቸው ሥርዓቶች ውስጥ ያከማቻቸውን ነባር እውቀቶች መሠረት አድርጎ የሚያድግ ነው። ባሕል ስንል ከሁሉ አስቀድመን መረዳት ያለብን ነገር በሰው ልጆች የሥራ ሂደት የተገኘ፣ የተለወጠ፣ የተሠራ፣ ማለታችን ነው። የምርት መሣሪያዎች፣ የትራንስፖርትና የቋንቋ መገናኛዎች፣ ሳይንሳዊና ሥነ- ጥበባዊ ዕውቀቶች ወዘተ… ማለት የሳይንስና የቴክኖሎጂ የሥራ ውጤቶች በሙሉ ከሕዝብ ንብረትነታቸው ባሻገር፣ በኀብረተሰቡ ታሪካዊ የሥራ ሂደት ወቅት አዲስ የተፈጠሩ፣ ቀደም ከነበሩት የተለወጡ፣ ወይም የተስተካከሉ ናቸው። ሥራና እውቀት ተባብረው ሁለተኛን ተፈጥሮ በመገንባት የተገኙ ናቸው። የዚህም “ሁለተኛ ተፈጥሮ” ቀጥተኛና ግልጽ ትርጉሙ “ባሕል” ነው።



123

በመሆኑም የባሕል እድገት መሠረቱ የሰው ልጅ ሥራ፣ ከሁሉም በፊት ቁሳዊው የማምረቻ ወይም የማፍሪያ መሣሪያው ነው። በሰው ልጅ ሥራ አማካኝነት የሚገኘውን ታሪካዊ የባሕል እድገትም ሆነ የሰው ልጅ ከተፈጥሮና ከኀብረተሰቡ አካባቢ ጋር ያለውን ሕብራዊ ግንኙነት፣ አገር በቀሉን ዕውቀት መሠረት አድርጎ የሚገነባው ዘመናዊው ትምህርት ሊያጠናክረውና ዕድገቱን ሊያፋጥነው ይችላል። የሰው ልጅ የፈጠራ ተሳትፎውና የሥልጣኔ ጣዕሙ፣ በየትውልዱ ባሰገናቸው የባሕል የሥራ ፍሬ ውጤቶች ብቻ ሳይረካ፣ እንደገና በይበልጥ ሲያጠና፣ በይበልጥ ሲመራመር፣ የቀድሞውን ደካማና ጎታች የሆነውን ሁሉ እያፈረሰ በአዳዲስ ጠንካራ ፈጠራ ሲገነባ፣ ከባሕል ግንባታ ሂደቱ ጋር ተነጥሎ የማይታይ አንድ ዐቢይ ነጥብ እንመለከታለን። ይኸውም የሕዝቦች የሥልጣኔ ቅርስ ጥበቃና የባሕሎች መወራረስ የሚያስከትለው ለውጥ ለባሕል እድገት ታላቅ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ነው። በአንድ ፊት የሕዝቦች ባሕላዊ ልውውጥና የሥልጣኔ ቅርስ ጥበቃ፣ ወዘተ… በሌላ ፊት የየትውልድ አዳዲስ ቁሳዊና መንፈሳዊ የፈጠራ ተሳትፎአቸው በየአንፃራቸው የባሕልን እድገት በአፋጣኝ እያካሔዱ ሀብትነቱንም

ያረጋግጣሉ። በተለይ አንድን ባሕል ከሌሎች አጉልቶ የሚያጎለምሰው ፈጣን የፈጠራ ውጤት ሲኖር ነው። ይህ የባሕል የፈጠራ ሂደት፣ ሁልጊዜም ጥንታዊውን ቅርስ ከማጥናትና አዲሱንም የፈጠራ ኃይል ከማሰባሰብ ጋር በስልት ይጣመራል። ጥንታዊው ለዘመናዊው ጽኑ መሠረት ይሆናል። የሰው ልጅ የአንድ ኀብረተሰብ አባል ለመሆን በአንድ ፊት አስቀድሞ ከነበረው ባሕላዊ ቅርስ ጋር ራሱን በወራሽነት ማዋሀድ ሲኖርበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ አሁን ላለበት ኀብረተሰብ ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች በመሥራት በወቅቱ በሚካሄደው ባሕላዊ ፈጠራ አባል ሆኖ ተሳታፊ መሆን አለበት። ባሕል ማለት በአጭሩ የሰው ልጆች ቁሳዊና መንፈሳዊ ጣምራ የዕድገትና የፈጠራ ፍሬ ማለት ሲሆን፣ ይህም ቁሳዊና መንፈሳዊ የዕድገት ፋና ከግለሰብ፣ ከቡድን፣ ከመደብ፣ ከብሔርና በአጠቃላይም ከኀብረተሰብ መንጭቶ ወደ ዓለም ሰፊ ሕዝቦች ባሕላዊ ሀብትነት የሚደመር ነው። ኀብረተሰብ የጋራ ባሕልን ከቀደምት እየተረከበ የማይበጀውን እየጣለ የሚጠቅመውን እያሻሻለ፣ አዲስ የሚፈጥረውን ከቆየው



124

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ጋር እያስማማ ለሚቀጥለው ትውልድ ያስተላልፋል። እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆኑ የባሕል እሴቶች ከሕዝቡ በወጡት ግለሰቦች በቀጥታ ይፈጠራሉ ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይህም እውነታ ከዓለም ታላላቅ የሥነ-ጽሁፍ፣ የኪነ-ጥበብ፣ የሙዚቃ፣ የሥዕል ወዘተ.. ሰዎች ሥራ አንፃር በግልጽ ሊገናዘብ ይገባል። እነዚህ የፈጠራ ሰዎች ታላቅና እውቅ ሊሆኑ የቻሉት በሕዝቦቻቸው ቱባ ባሕልና በአገር በቀል ጥበብ ላይ እጅግ የጠለቀ እውቀት ስላላቸውና የሕዝቡንም የተከማቹ እሴቶች መሠረት ስላደረጉ ነው። የባሕልና የኀብረተሰብ የባሕል

እድገት ጥያቄ በዘመናችን አንገብጋቢ ጥያቄ ሆኖ አያሌ ውይይቶች ይካሄዱበታል። የሞቀ የርዕዮተ ዓለም የትግል መድረክ ከሆነም ቆይቷል። ይህም ያለምክንያት አይደለም። የተለያዩ ዘርፎች ያሉትን የባሕልን ጥያቄ ለመፍታት ከዚያም ለማበልጸግ ያለው አማራጭ መንገድ አንድ ነው። ይህም መንገድ በአገር በቀል እውቀት ላይ የተመሠረተ ሳይንሳዊ አመለካከት ያለው የባሕል ጽንሰ ሐሳብ /ቲዎሪ/ ማዳበር ነው። የዚህ ጽንሰ ሐሳብ ምንጭ ደግሞ ነባሩ አስተምህሮት ነው። ባሕል ከሕዝቦች ሥራ ጋር የተያያዘ ነው። የባሕል ትርጉም አንድም

መሬትን ማረስ ማለስለስ ሲሆን፣ ሌላኛው ትርጉሙ ደግሞ የሰውን ልጅ ማስተማር፣ ማሠልጠን፣ በግብረገብ ማነጽ በአጠቃላይ የሕዝቦች የሥራ ውጤት ነው። የሰው ልጅ የአንድ ኀብረተሰብ አካል ለመሆን፣ አስቀድሞ ባለው ኀብረተሰብ የባሕል ሂደት ውስጥ ራሱን ማስተዋወቅና ማዋሀድ አለበት። ስለሆነም አንድ ሰው የአንድ ኀብረተሰብ አካል ሆነ ሲባል፣ ባለው የባሕል ሂደት ውስጥ ራሱን አዋሀደ ማለት ነው። ስለሆነም ባሕል ማለት የሰው ልጆች መንፈሳዊና ቁሳዊ የሆኑ ፈጣን የፈጠራ ሥራዎች ማለት ነው። ይህ ቁሳዊና መንፈሳዊ



125

የፈጠራ ሥራ የግለሰብ፣ የቡድን፣ የመደብ፣ የብሔር፣ በአጠቃላይ የኀብረተሰብ ሊሆን ይችላል። የሰው ልጆች ተፈጥሮን በቁጥጥራቸው ሥር ለማድረግ የሚጠብቁት፣ የሚያዳብሩት፣ የሚያፈልቁት፣ የሚያከፋፍሉትና ለሕብረተሰቡ የሚያውሉት ዋጋ ያላቸው መንፈሳዊና ቁሳዊ ባሕሎች እንዲሁም የእነዚህ ሥራዎች ፍሬ፣ በአጠቃላይ የሀሳብ የፈጠራ ሥራዎች ናቸው። ባሕል የአንድ ኀብረተሰብ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ይዘት ነፀብራቅ ነው። የኀብረተሰቡን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ይዘት የሚያንፀባርቀውም መደባዊ አቋም ይዞ መሆኑን መረዳት ይቻላል። የአሁኑ የሰው ልጅም ሆነ ያለፈው ኀብረተሰብ የኖረውና ያለው በብዙ ጐሣዎች ወይም ዘርፎች ተከፋፍሎ ነው። አንዱ ጐሣ ከአንደኛው የሚለይባቸው አያሌ ጠባዮች ቢኖሩትም ሁሉም የሚገናኙባቸውም መስኮች አሉ። ጎሣዎች የራሳቸውን ባሕል ፈጥረው በአንድ ላይ ለመኖር ከቻሉበት ምክንያቶች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ሆነው እናገኛቸዋለን። • በአንድ ዓይነት ዳር ድንበር

መከለላቸው፣ • ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ አንድ

ዐይነት ታሪክ ስላላቸው፣

• በአንድ ዓይነት የኢኮኖሚ ሕይወት ላይ ኑሯቸውን ስለገነቡ፣

• በአንድ ዓይነት ቁሳዊና መንፈሳዊ ባሕል ስለተያያዙ፣

• አንድ ዓይነት ቋንቋ ስለሚናገሩና

• አንድ ዓይነት ንቃተ ኀሊናና ሥነ-ልቦና ስላላቸው።

እያንዳንዱ ሕዝብ ከሁሉ አስቀድሞ የራሱ ጐሣ የሆነውን ባሕል ያሳድጋል፣ ይንከባከባልም። የራሱም ጐሣ የሆነውን ባሕሉንም ጠብቆ ለራሱ ትውልድ ያስተላልፋል። የእያንዳንዱ ሕዝብ ባሕል ከሌላው የተለየ የራሱ የሆነ ጠባይና ውበት አለው። ይህም ልዩ ባህርይ በአንድ አካባቢ አንዴ ብቻ ብልጭ ብሎ የሚጠፋ፣ የማይደገም የሚሆንበት ጊዜም አለ። “የተለያዩ ሕዝቦች የተለያየ ባሕል አላቸው” ቢባልም፤ አንዱ ሕዝብ ከአንደኛው ፈጽሞ የተለየ ነው ማለት አይደለም። ባለፋት የታሪክ ዘመናት ሁሉ ሕዝቦችና ባሕላቸው ያለማቋረጥ በአንድነት ተግባራቸውን ሲያካሄዱ ቆይተዋል። የሕዝብ ባሕሎች እርስ በርሳቸው ግንኙነት በመፍጠር በእነዚህ የኀብረተሰብ የታሪክ ዘመናት ሁሉ ወደፊት መራመዳቸውን ዓለም አቀፋዊው የባሕል ታሪክ

ያወሳናል። (በአገራችንም ማረሻው፣ ”ነጩ እጀጠባብና ቀሚስ፣ እንጀራው፣ የሙዚቃ ቅኝቱና መሣሪያው፣ ዜማው፣ ለሥነ-ምግባር እነፃው ብቻ ሳይሆን ለአገር ግንባታም ውሏል) የሕዝቦች አንድነት በባሕሎቻቸው ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ካለም የባሕላዊ ታሪክ ሀብት ፈለግ እንጂ ሌላ አይደለም እንላለን። ስለሆነም በእያንዳንዱ ሕዝብ ባሕል ላይ በትንሹም ሆነ በብዛት የሌላው ሕዝብ ባሕል ነፀብራቅ ይታይበታል። ከዚህም ሌላ የአንዱ ሕዝብ ባሕል በይዘቱ ከሌሎች ሕዝቦች ባሕል የተለየና የራሱ የሆነ ወጥነት ያለው ቢሆንም፣ በአንፃሩ ደግሞ ከሌሎች ሕዝቦች የተወሰደ ወይም የተደባለቀ መሠረታዊ የሆነ ውህደት በውስጡ እናገኝበታለን። በዚህም ወቅት በአንድ ባሕል ውስጥ “የአካባቢውን”፣ “ከውጭ የመጣውን“ ወይም “የተዳቀለውን” ባሕል ለይቶ ማውጣቱ ቀላል የማይሆንበት ጊዜ አለ። ከዚህም ጋር አብሮ ከአንድ ባሕል ዕድገት ጋር በውስጥና በውጭ ስለተያያዙት አንዳንድ ሁኔታዎችና ስላላቸው ግንኙነቶች በዛ ያሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ። ባሕል የአዕምሮና የጉልበት የአንድነት ሥራ ውጤት ነው። መንፈሳዊና ቁሳዊ ባሕሎች



126

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

በአንድነት ተጣምረው አንድ ኀብረተሰብ የደረሰበትን የእድገት ደረጃ ያሳያሉ። ባሕል በአንድ ኀብረተሰብ ውስጥ ያሉትን ልዩ ልዩ ዘርፎች የሚያጠቃልል ሲሆን ሁለት ታላላቅ ክፍሎች እንዳሉት እንረዳለን። እነዚህም መንፈሳዊና ቁሳዊ ተብለው ይጠራሉ። የባሕል ቁስ አካላዊ እሴቶች በስልተምርቱ ውስጥ የሚከተሉትን ነጥቦች ያጠቃልላሉ። የምርቱ የቴክኒክ ዕድገት ደረጃ፣ የሣይንስና የቴክኖሎጂ እርምጃዎች በምርቱ ውስጥ ያላቸው ሰፋትና ጥልቀት፣ ቴክኖሎጂን ለመጠቀም ሰዎች ያሏቸው ችሎታና እውቀት፣ በጉልበትና በአዕምሮ ሥራ፣ በየመስኩ ያለው ሳይንሳዊ የሥራ ግንኙነትና ቅርበት፣ በከተማና በገጠር መካከል ያለው ልዩነት ወይም አንድነት፣ የግለሰቦች ሁለገብ የሙያ ትምህርት የእድገት ደረጃ፣ በኢንዱስትሪው ውስጥ የሳይንሳዊ ሥራ ቅንብር፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከሰዎች ከቀን-ተቀን ኑሯቸው ጋር መጣጣምና ቁስአካላዊ ፍላጐቶቻቸውን የማርካት፣ በኢንዱስትሪ ውስጥ አዲስ ሳይንሳዊና ቴክኖሌጂያዊ የቴክኒክ እርምጃዎችን የመጠቀም ወዘተ... ሁሉ በቁስ አካላዊ መስክ የሚገኙ የባሕል እሴቶች ናቸው።

የባሕል መንፈሳዊ ሕይወት አቅጣጫዎች የሚያጠቃልሉት፤ የኪነ-ጥበብ እና የሥነ-ጽሁፍ ሥራዎችን ሲሆን፣ እነርሱ በሕዝቡ ዘንድ ያላቸው ሥርጭት፣ የሕብረተሰቡ የትምህርት ደረጃ፣ እውቀት በሕዝቡ ውስጥ ያለው ስርፀት፣ የእምነት ተቋማትና ትሩፋት፣ የምሁራን ሚና ወዘተ…. ነው። ኪነ-ጥበባት ሊቁ ተሰማ ሀብተ ሚካኤል ግጽው፤ ከሣቴብርሃን ተሰማ በ’የአማርኛ መዝገበ ቃላት’ መጽሐፋቸው ገጽ 815 ላይ፤ ኪነ-ጥበብ ለሚለው ጽንሰ ሐሳብ የሰጡት ትርጉም እንዲህ ይላል “ኪነ-ጥበብ በብረታብረት ወይም በጠርብና በድንጋይ ሠሌዳ ላይ ልዩ ልዩ ሥዕልና ቅርጽ፣ ንቅስም፣ በግንብ ሥራ፣ በሥዕል ሥራ፣ በሐረግ ሥራ፣ በአንጥረኝነት፣ በስፌት፣ በልዩልዩ ተግባረ ዕድ ተሠርቶ የሚታይ የእጅ ሥራ ጥበብ” ካሉ በኋላ በመቀጠል፤ “ኪነ- ጥበብ የአዕምሮ ትምህርት የሚሆን ኪነ-ጥበብ…” በማለት ይቋጩታል። ቀጥለውም “ኪነት” ለሚለው ቃል ሠፊ ብያኔ ይሰጣሉ። ኪነት ይላሉ ሊቁ፤ “ልዩልዩ የእጅ ጥበብን፣ ከአዕምሮ እያፈለቁ በልዩልዩ ዐይነት መሥራት፣ ብረታብረትን፣ ድንጋይንና ጠርብ ልዩልዩ ንቅስና ቅርጽ የሚቀርጽ፣ የሰውን፣

የእንስሳ መልክን እየመሰለ የሚሳል፣ ሱሳን ወርድ፣ አበባን እንደ ሐረግ፣ እየሳበ የሚያፈነዳ ወይም በልዩልዩ ንቅስ ዘውድን፣ አክሊልን፣ ዕርባን ሥራ ቀለበትን መሥራት ኪነት ይባላል” ይሉናል። በአንፃሩ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በአስኳላ ምሁራን የተዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ በገጽ 385 ላይ ስለ ኪነ-ጥበብ እንዲህ ይላል። ”ኪነ-ጥበብ እንደ ስዕል፣ ቅርፃቅርጽ ያለ የእጅ ጥበብ ሥራ ነው” ካለ በኋላ “ኪነት” ለሚለው ቃል የሰጠው ብያኔ” ኪነት፤ 1-ኪነ-ጥበብ፣ 2-የሙዚቃ፣ የዘፈን፣ የውዝዋዜ ጥበብ...” ነው ይላል። እነዚህን ግንዛቤዎች በአዕምሯችን ቋጥረን ሠፋ ብሎ የቀረበውን የኪነ-ጥበብ ውሳኔ እንዝለቀው። የባሕል ምንጭ ሰፊው ሕዝብ መሆኑን አስቀድመን ገልፀናል። ታሪክንም የምንመለከተው ከታሪክ ፈጣሪው አንፃር ነው። ታሪክ ፈጣሪዎች በአሁኑ ወቅት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ናቸው። የሕዝቦችን ንቃተ ኀሊና ለማዳበር ደግሞ የኪነ-ጥበባት ውጤቶች ዓብይ ሚና ይጫወታሉ። የሰፊው ሕዝብ የትግል መሳሪያ የሆኑት የኪነ-ጥበባት ውጤቶች ፖለቲካዊ አቋም ደግሞ ሕዝባዊነት፣ ወገናዊነት፣



127

ገላጭ ውሁዳዊነት፣ ቅርብነት፣ ሃቃዊነት፣ የሚሉ ናቸው። እነዚህም አንዱ ከአንደኛው ተለይተው የሚታዩ አይደሉም። ኪነ-ጥበባት በሰፊው ሕዝብ የተፈጠሩ ሀብቶች ናቸው። መሠረታቸውን በሰፊው ሕዝብ ውስጥ ማድረግና የእርሱም አገልጋይ መሆን አለባቸው። ስለሆነም ሰፊውን ሕዝብ ዘልቀው በመግባት ለሕብረተሰቡ መዳረስ ይኖርባቸዋል። የሰው ልጅ የሐሳቡና የተግባሩ ውጤቶች የሆኑ ማንኛውም ነገሮች ሁሉ የባሕል ማንፀባረቂያ ገጽታዎች ናቸው። ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል፤ ቋንቋ፣ ሥነ-ቃል፣ እምነት/ ፍልስፍና/ የኅብረተሰብ

አደረጃጀት ሥርዓት፣ የኪነ- ጥበብ ውጤቶች፤ /ሥነ-ጽሑፋ፣ ሙዚቃ፣ ሥዕል፣ ቅርፃ ቅርፅ፣ ዳንስና ውዝዋዜ፣ ቴአትር፣ ስፖርት/፣ ሥርዓተ ትምህርት፣ የፖለቲካ መዋቅር፣ የኢኮኖሚ መዋቅር፣ የጤና አጠባበቅ ዘዴ፣ የመጓጓዣና የመገናኛ ዘዴዎች፣ የቤት አሠራር፣ አለባበስ፣ አመጋገብ፣ የመዝናኛ ዘዴዎች፣ ዕለታዊ የሥራ ሥምሪት ወዘተ ናቸው። ከላይ ከተጠቀሱት የባሕል መከሰቻ ገጽታዎች መካከል ዋነኛው ኪነ¬¬-ጥበብ ነው። ኪነ-ጥበብ እንደ ባሕል ዓቢይ ክፍልነቱ በመደብ በተከፋፈለ ኅብረተሰብ ውስጥ የገዥው መደብ መሣሪያ ነው። ኪነ-

ጥበብ የሰፊው ሕዝብ አገልጋይ የሚሆነው ደግሞ የሰው- በሰው ብዝበዛ በከሰመበት፣ የኅብረተሰቡ መብትና ነፃነት በሚከበርበት ዴሞክራቲክ ሥርዓት ብቻ ነው። ኪነ-ጥበብ የሕዝብ ሐብት ነው። በሕዝቡ ውስጥ ሥሩን መትከል አለበት፣ ፈጠራውን ሕዝብ ሊረዳውና ሊያፈቅረው ይገባል። የሕዝቡን ስሜት፣ አስተሳሰብና ፍላጐት መቀስቀስ መቻል ዓቢይ ዓላማው ነው። ለተግባርም ያነሣሣዋል፣ ከሕዝቡም ቱባ ባሕል ውስጥ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን ማፍለቅና በነባር ዕውቀት ተንከባክቦ የማሳደግ ኃላፊነት አለበት። ኪነ-ጥበብ የሕዝብ የፈጠራ



128

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ውጤት እንደመሆኑ መጠን፣ መልሶ የሕዝቡን ሕይወት ማጉላትና ባሕላዊ ፍላጐቱን ማርካት ይጠበቅበታል። የኪነ- ጥበብ ውጤቶች በሰፊው ሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ ለመሆን የሚችሉት ለሰፊው ሕዝብ ግልጽና መልዕክታቸው የጠራ ሆነው ሲቀርቡ ነው። (የፈጠራ ሰው ከሕብረተሰቡ አንድ ጋት ወደፊት የቀደመ መሆን አለበት። ከጋት አልፎ ከሄደ ተስፈንጣሪ ይሆናል። ከጋት ወደኋላ ከቀረም በሕዝቡ የሚሳብ ተጎታች ይሆናል…) ኪነ-ጥበባት የሰፊውን ሕዝብ ስሜት፣ ፍላጐት፣ ሀሳብ በማዋሀድ ሕዝቡን ለልማት፣ ለዕድገት፣ ለትግል የመቀስቀስ ኃላፊነት አለባቸው። በመሠረቱ የኪነ-ጥበባት ዓቢይ አላማ፤ ሰፊውን ሕዝብ ማገልገል

መሆኑ ከላይ ተገልጿል። የኪነ- ጥበብ ባለሙያም ታላቅ ተግባር በአገሪቱ በሚካሔደው እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቶ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ነው። የኪነ-ጥበብ ውጤቶች ደግሞ እውነታን እንዳለ ማንፀባረቅና ሕይወትን ተቀብሎ መሳል ብቻ ሳይሆን መግለጽም አለባቸው። የሕይወትን ተሞክሮና ክስተት ማወያየትና ፍቺ መስጠት መቻል ይኖርባቸዋል። ከያኒው እራሱ የሚያስበውም ሆነ የሚመራመረው የኅብረተሰብ አካል ሆኖ እንጂ ከኅብረተሰቡ ውጪ በአየር ላይ ተንሳፎ አይደለም። የኪነ-ጥበብ ሰው በዘመኑ በሚካሄው የሕዝብ ትግል ውስጥ ወደደም ጠላም ከኅብረተሰቡ ጋር እኩል ይካፈላል። ከያኒው በኅብረተሰቡ

ትግል ውስጥ በሚካፈልበት ወቅት መርጦ የሚቆምለትና ጥቅሙን የሚያስጠብቅለት የራሱ ጎራ ይኖረዋል። ስለሆነም በዘውግ በተከፋፈለ ኀብረተሰብ ውስጥ ነፃ ከያኒም ሆነ ኪነ- ጥበብ ፈጽሞ አይኖርም፤ ሊኖርም አይችልም። ማንኛቸውም የኪነ-ጥበባት ሥራዎች ሕዝቡ ለፍትሕ መስፈን፣ ለዴሞከራሲ ግንባታ፣ ለአገር አንድነት፣ ለብልፅግና የሚያደርገውን ትግል መደገፍና ማንፀባረቅ ይጠበቅባቸዋል። ዓላማቸውም ሕዝቡ የራሱን መንግሥት ዴሞክራሲዊ በሆነ ሠላማዊ ምርጫ ለመመሥረት የሚያደርገው ትግል ግብ እንዲመታ ከጐኑ ቆመው ማታገልና መታገል ነው።



129

የኅብረተሰቡ ንቃተ ሕሊና በሙያ ሳይዳብር፤ ሰፊው ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ሊገነባ ከቶም አይችልም። ሕዝብ ሁሉን ነገር ሲያውቅ ብቻ ነው የማይበገር ኃይል የሚሆነው፤ ስለማንኛውም መፍረድ የሚችለው። የኪነ- ጥበብ ባለሙያው ወደ ሕዝቡ ለመግባት መንገድ ከመጀመሩ በፊት የሕብረተሰቡ የንቃተ ሕሊና ያለበትን የዕድገት ደረጃ በጥልቀት ማወቅ ይጠበቅበታል። ሕብረተሰብን በጥበብ ማንቃትና ለልማት ማደራጀት ብዙ ድካም አለበት። ከፍተኛ ትዕግሥትና የጊዜ መስዋዕትን ይጠይቃል። የሕዝብ ወዳጆች ከጥበቡ ጎን የሚቆሙትን ያህል አፍራሽ ኃይሎችም በተፃራሪው ተሰልፈው ይፋለማሉ። ያም ሆኖ ማንኛውንም ችግር ታግሎ ድል ማድረግ የሕዝባዊው ኪነ-ጥበብ ወሳኝ ተልዕኮ ነው። ኪነ-ጥበብ ከቀን ወደ ቀን የበለጠ የድል ባለቤት እንዲሆን መሠረቱን አገር በቀል ዕውቀት ሊያደርግ የግድ ይላል። የሕዝቦችን ምንጊዜም ድል አድራጊነት ቀደም ብለው የሚረዱ ደራሲያን፤ ኪነ-ጥበባት የኅብረተሰቡን እንቅስቃሴ እንዲያግዝ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። እነዚህ የፈጠራ ሰዎች ሕዝባዊና ሀቀኛ አቋማቸውን ለማራመድ የሚፈልጉት፣

መጀመሪያ የውስጥ ትግላቸውን አካሔደው የጠራ ሕዝባዊ አቋም ከያዙ በኋላ ነው። በዘመነ ዴሞክራሲ ኪነ- ጥበባት ሀቀኛ የፖለቲካ አቋም ሊኖራቸው ይገባል። በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠረውን ሕዝብ የኪነ-ጥበባት አዳማጭ ብቻ ማድረግ አይቻልም። ያለፉትን የኪነ-ጥበባት የፈጠራ ውጤቶች ብቻ ዝም ብለህ ተቀበል ማለትም ያስቸግራል። ሕዝብ ተቀባይ ብቻ ሳይሆን ሰጪም ጭምር ነው። አድማጭ ከሆነው ሚሊዮን ሕዝብ መካከል አዳዲስ ፈጣሪዎችን ማውጣት አስፈላጊ ነው። ለሕዝብ ማሰብ ማለት ሕዝብ እንዲማር መርዳት ነው፤ ለሕዝባዊ ኪነ-ጥበባት ማበብ የሚደረገው ትግል የዘመኑ መሠረታዊ አቋም ሊሆን ይገባል። ይህም ትግል ከባሕል ዕድገት፣ ከዴሞክራሲ መስፈን፣ መሀይምነትን ለመዋጋት ኀብረተሰቡ ከሚያካሂደው ዘመቻና እንዲሁም ሰፊው ሕዝብ ለዚህ ወሳኝ ትግል ከሚከፍለው መስዋዕትነት ጋር መያያዝ አለበት። ለዚህም ተልዕኮ እውን መሆን፤ የሕዝቡ ኪነ-ጥበባዊ የፈጠራ ኃይል በከፍተኛ ደረጃ መዳበር አለበት። ኀብረተሰቡም በአዲስ መንፈስ እንደገና መነሳሳት ይኖርበታል። በኪነ-ጥበብ ዙሪያ ያሉ የሀገሪቷ ምሁራንም አዳዲስ

የኪነ-ጥበብ ውጤቶችን ማፍለቅ ይጠበቅባቸዋል። በፈጠራ ሰዎቻችን ስም የአደባባዮች ስያሜና የሐውልቶች መቆም፤ በሕይወት ላሉት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ታላቅ የመንፈስ ሞራልና ብርታት ይሰጣቸዋል። ከዘመናዊው ኪነ-ጥበብ ጎን የሚሰለፉት ባለሙያዎች በአገር በቀል ዕውቀት ከታነጹ፣ የፈጠራ ሥራዎቻቸው ኢትዮጵያዊ ቅርጽ ይይዛሉ። ከውጭ የኪነ-ጥበብ ወረራም ፈጠራቸውን በከፊል ሊታደጉ ይችላሉ። ሕዝባዊ ባሕልን በመገንባት፣ የሕዝብን ፍላጎትና ስሜት በማስተጋባት፣ በየወቅቱ በሚካሔደው የባሕል እንቅስቃሴ ላይ የማይናቅ ሚና በመጫወት፣ የኪነ-ጥበብ ሥራዎችን በተፈለገው ደረጃ እንዲያብቡ ተጋድሎ በማድረግ፣ እነዚህ በኪነጥበብ ፈጠራ ላይ የተሠማሩ ባለሙዎች በእጅጉ አስፈላጊዎች ናቸው። አስፈላጊነታቸውም የባሕልን ዕድገት ለማጠናከር ብቻ ሳይሆን የኪነ-ጥበብ ውጤቶችን በዓይነትና በብዛት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ጭምር ነው። ይህም ታሪክ የሚጥልባቸው ኃላፊነት ይሆናል።



130

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ማኅበራዊ

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ እና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ትብብር የተዘጋጀ

የተገልጋይ እርካታን ለማሳደግ



131

የተገልጋይ እርካታን ለማሳደግ

በፍቅርተ ባልቻ

ምስረታው በ1961 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አማካኝነት በአውቶቡስ ተራ አካባቢ እንደሆነ ይነገርለታል፤ ብዙም ሳይቆይ ከጥቅምት 1962 ዓ.ም ጀምሮ ቋሚ አድራሻውን አሁን በሚገኝበት ስፍራ አድርጓል። ተቋሙ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ለማሻሻል፣ ለማሳደግና የተገልጋዮቹን ፍላጎት ለማሟላት የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ አሁናዊ ደረጃው ላይ መድረሱን ታሪኩ ያስረዳል። በ4 ሺህ 857 ባለሙያዎቹ እና በ700 አልጋዎች ክሊኒካል፣ አካዳሚክ፣ ምርምር እና የማኅበረሰብ አገልግሎቶችን የሚሰጥበት አቅም አጎልብቷል። ከ300 በላይ ከፍተኛ የሕክምና ባለሙያዎች (Senior medical specialists) ያሉት ሲሆን ከ80 በላይ የሕክምና ዓይነቶችን



132

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

(Clinical services) ለተመላላሽ ታካሚዎች ይሰጣል። በ2016 ዓ.ም ብቻ የሕክምና አገልግሎት ያገኙ ታካሚዎች ቁጥር 698 ሺህ 910 መሆኑን የተቋሙ መረጃ ያስረዳል፤ አሃዙ የአገልግሎቱን ስፋት ያመላክታል። ይህ ተቋም የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ነው። በዚህ ጽሑፍ ኮሌጁ የመማር ማስተማሩንና የሕክምና አገልግሎት ጥራቱን የሚያስጠብቁ አሠራሮችን በመፈተሽ ሥራ ላይ ለማዋል፤ በጥራት ላይ የሚሰራ የሕክምና ጥራትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት (Quality Improvement and Clinical Governance) አቋቁሞ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ተዳሰዋል። የሕክምና ጥራትና አስተዳደር እንደ መፍትሔ … የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የሕክምና ጥራትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት (Quality Im- provement and Clinical Governance) ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱ አደም በአገሪቷ ትልልቅ የጥራት ዳይሬክቶሬት ወይም አደረጃጀት ካላቸው ሆስፒታሎች መካከል አንደኛው እንደሆነና በሥራ ክፍሉ ውስጥ በተለያዩ የሙያ መስኮች የትምህርት ዝግጅት ያላቸው 24 ባለሙያዎች

መኖራቸውን ነግረውናል። በየሥራ ክፍሎች የሚገኙ መረጃዎችን የሚመዘግቡና ለዳይሬክቶሬቱ ባለሙያዎች በሚያቀርቡ የጥራት ሥራውን በሚከታተሉ ተወካዮች (fo- cal persons) የተሰባሰቡ መረጃዎች ለውሳኔ በሚጠቅም መልኩ በዳይሬክቶሬቱ ተተንትነው ለሥራ ክፍሎች (ዳይሬክቶሬቶች)፣ ለተቋሙ እንዲሁም ለባለድርሻ አካላት ይቀርባሉ። ጥራትን ማስጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት በምን መልኩ ይከናወናሉ የሚለውን ሲያብራሩም ”በተቋሙ ሥራ ክፍሎች የተለያዩ ተግባራት ይከናወናሉ፤ የሥራዎቹን ባሕሪይ የሚያውቀው ደግሞ በዚያ ያለው ኃላፊ እና ባለሙያ (የሥራው ባለቤት) ነው። በየሥራ ክፍሎቹ ጥራትን የሚከታተሉ የጥራት ባለሙያዎች እና የጥራት ምክትል ኃላፊዎች እንዲኖሩ ተደርጓል። ስለዚህ እኛ ለእነዚህ የጥራት ሥራዎች ተወካዮች ድጋፍ፣ ምክር እና የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየሰጠን በጋራ እየሰራን ነው” ነው ያሉት። ይህ በተቋሙ የሚሰጡ አገልግሎቶች እና የሕክምና ትምህርት ጥራትን ለመጠበቅ የሕክምና ጥራትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት መቋቋም እንደ



133

አንድ መፍትሔ ተወስዶ ላለፉት ስምንት ዓመታት እየተሰራበት ይገኛል። ጥራት ምንድን ነው? ጥራት (Quality) ሳይንስ ነው። ጥራት እስከ ፒኤችዲ የሚደርስ ትምህርት የሚሰጥበት እና ትልልቅ መጽሐፍት የተጻፉበት ጽንሰ ሀሳብ ነው። ይሁንና አብዛኛውን ምሁር የሚያስማማው፤ ተገልጋይ ጥራት ያለው አገልግሎት አገኘሁ፣ ተቋምም ጥራት ያለው አገልግሎት ሰጠሁ ለማለት የሚችለው ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ሰባት መለኪያዎች (Param- eters) ሲያሟላ ነው የሚሉት ዶ/ር አብዱ የጥራትን ምንነት ለመግለጽ ብሎም ለመመዘን ያገለግላሉ ያሏቸውን ነጥቦች እንዲህ አብራርተዋቸዋል። የተገልጋዮችን ደህንነት መጠበቅ (Safety) የመጀመሪያው ነጥብ ነው፤ ይህም በግድየለሽነት ምክንያት ሊከሰቱ ከሚችሉ አደጋዎች የፀዳ አገልግሎት መስጠትን ያጠቃልላል። ሌላው የጥራት መለኪያ በዓለም አቀፍ ደረጃ፤ እንደ አገርም እንደ ተቋምም ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው በሕክምና መርሆዎች እና መመሪያዎች መሰረት ውጤታማ አገልግሎት መስጠት (Effectiveness) ነው። ተገልጋይ ወደ ሕክምና ተቋማት



134

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ሲመጣ የሚፈልጋቸውን ነገሮች በተቻለ መጠን (በሆስፒታሉ፣ በአገር አቅም መሠረት) ለማቅረብ ጥረት ማድረግን ያጠቃልላል። ሌሎች ተጓዳኝ ሕመሞች እና ሕመምተኛውን ያጋጠሙት ተያያዥ ችግሮችን በሙሉ ለማከም መስራትም (Patient centered) ሌላው የጥራት መርህ ነው። በሌላ በኩል ታካሚው ሊረዳ በሚቻልበት ወቅት ጊዜውን የጠበቀ ሕክምና

ወይም አገልግሎት (Timely) ሲሰጥ ጥራቱን ጠብቋል ይባላል። የሰው እና የግብዓት መጠን (Resource) ከግንዛቤ ያስገባ አሰራር መከተል (Efficient) ሌላው ጥራት ያለው አገልግሎት ስለመሰጠቱ የሚያመላክት መመዘኛ ነው። አንድ የእጅ ጓንት መጠቀም እያለብን አስር የምንጠቀም ከሆነ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት አልሰጠንም እንደማለት ነው። ይህ የሕመምተኛውን አላስፈላጊ ወጪዎች መቀነስን ይጨምራል። ሌላው የጥራት መመዘኛ የሕክምና ተቋማቱን ለአካል ጉዳተኞች ተስማሚ እና ምቹ ማድረግ (Equitable) ነው። እነዚህ ሁሉ አገልግሎቶች በአንድ እና በተሟላ መልኩ (Integra- tion) በጣም በቅርብ ርቀት መስጠት ያስፈልጋል። ይህም እውን የሚሆነው የሥራ ክፍሎች በጋራ አገልግሎት የሚሰጡበትን አሰራር ሲተገብሩ ነው። እነዚህ ነጥቦች ጥራትን ለመግለጽ ብቻ ሳይሆን ጥራትን ለመለካት እንደመመዘኛ የምንጠቀማቸው ናቸው። እነዚህን የጥራት መገለጫ እና መመዘኛዎች ወደ ተግባር ለመቀየር የዓለም ጤና ድርጅትን ጨምሮ በሌሎችም ዓለም አቀፍ ተቋማት አማካኝነት ትልልቅ ሰነዶች እና መጽሐፍት



135

ተዘጋጅተውላቸው በዝርዝር ተተንትነው መቀመጣቸውን “እነዚህ ሁሉ ዓላማቸውና ግባቸው ሰባቱን የጥራት መገለጫዎች በማሟላት ታካሚው የሚረካበትን አገልግሎት መስጠት ነው“ ሲሉ ዶ/ር አብዱ ያስረዳሉ። ሰባቱ መመዘኛዎች የሚለኩባቸው በርካታ ስልቶች እንዳሉ፣ አንደኛው የጥራት ዳይሬክቶሬት ሥራም ይኸው እንደሆነ አክለዋል። አበይት ክንውኖች የጤና ሥርዓት ውስብስብ ባሕሪይ እንዳለው ይነገራል። የዚህ ምክንያትም ሰውን የሚያክመው ራሱ የሰው ፍጡር ስለሆነ፣ ሰውን ተረድቶ ሕመሙን ማከም በራሱ ከባድ እና ውስብስብ በመሆኑ . . . ሲሉ በመስኩ የተሰማሩ ባለሙያዎች ይጠቅሳሉ። የነርሲንግ፣ የሕክምና፣ የፋርማሲ፣ የላቦራቶሪ ወዘተ … ሙያ ያላቸው ሰዎች በአንድነት ሆነው ውስብስብ አፈጣጠር ያለውን የሰው ልጅ በሽታ ለማዳን ደፋ ቀና ይላሉ። በዚህ የሕክምና ሂደት ውስጥ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ”ምን ያህሎቹ ሥራዎች ደረጃቸውን ጠብቀዋል?” የሚለው ጥያቄ ጥራትን ከመጠበቅ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው።

ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት አሠራር መዘርጋት ወሳኝ ነው። ሆኖም አሠራር ስለተዘረጋ ብቻ ለውጥ አይኖርም፤ ጥራትን ባሕል (Quality Culture) ለማድረግ ግንዛቤ መፍጠሩ ወሳኝ ነው። ባሕሉን ለማዳበር በጣም ትልቅ ትግል እና ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም የሕክምና ጥራትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬቱ እንደ ግብ ይዞ እየሰራበት ይገኛል። ”ሰዎች በሚገባቸው መልኩ ግንዛቤ እንዲያዳብሩ በየሥራ ክፍሉ እየሄድን የገጽ ለገጽ ማብራሪያ እየሰጠን ነው” ይላሉ ዳይሬክተሩ። ከዚህ ባሻገር በሣምንት፣ በ15 ቀን፣ በወር ከየሥራ ክፍሎች ጋር የውይይት መድረኮች ይካሄዳሉ፤ ሁልጊዜ ጠዋት ጠዋትም (ከእሁድ በስተቀር) የተቋሙ ውሎ እና አዳር የሚገመገምበት (Morn- ing meeting) መርሃ ግብር ይከናወናል። እንደ ተቋምና እንደ ሥራ ክፍል ጥራትን ባሕል ለማድረግ፣ ግንዛቤ ለመፍጠር እና እርስ በእርስ ለመማማር ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል አንደኛውና ትልቁ በየዓመቱ የሚዘጋጀው የጥራት ጉባዔ (Quality Sum- mit) ነው። ይህ የጥራት ጉባዔ ከነሐሴ 20 እስከ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ለሦስተኛ ጊዜ ለተከታታይ ሦስት ቀናት በተለያዩ መርሃ

ግብሮች ተካሂዷል። በሦስቱ የጉባዔው ቀናት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የፓናል ውይይቶች ተካሂደዋል። የኮሌጁን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚያስረዱ መረጃዎች በጉባዔው ተሳታፊዎችና እንግዶች እንዲሁም በኮሌጁ ባለሙያዎች ተጎብኝተዋል። ከዓመታዊው ጉባዔ ዓላማዎች የመጀመሪያው ባለሙያዎች በሥራ ክፍሎቻቸው ውስጥ ሆነው የሚሠሯቸው የማሻሻያ (Improvement) ሥራዎችን በማጋራት መማማር እና ስለ ጥራት ያለውን እውቀት ለማሳደግ ብሎም ጥራትን ባሕል ለማድረግ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ማገዝ ሲሆን፤ ሁለተኛው በዳይሬክቶሬቶችና በሥራ ክፍሎች መካከል በጎ የሆነ ፉክክር እንዲኖር የሚያስችል መነሳሳት መፍጠር ነው። ከጥራት ጋር በተያያዘ እየተከናወነ ያለው ሌላው ተግባር የተገልጋይ እርካታን ለመለካት የሚሠራው ጥናት ነው። በሁሉም የሥራ ክፍሎች (ከተመላላሽና ተኝተው ከሚታከሙ) ናሙና እየተወሰደ በዓመት አራት ጊዜ ጥናት እንደሚሰራ ገልጸዋል። “የጥናቱ ግኝት የተገልጋዩ እርካታ የወረደ እንደሆነ የሚያሳይ ከሆነ ለምን ዝቅተኛ ሆነ ብለን እናያለን፣ ምክንያቱን እንፈትሻለን፣ የማስተካከያ እርምጃዎች



136

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

እንዲወሰዱ እናደርጋለን“ ይላሉ ዶ/ር አብዱ። በተቋሙ ጥራትን ለማስጠበቅ ትኩረት የሚደረግባቸውን አገልግሎቶችና ሥራዎች የትኞቹ ናቸው? ለምንስ ተመረጡ? የሚለውን ዶ/ር አብዱ ሲያብራሩ “በተቋሙ ውስጥ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በሙሉ አካተን እንሰራለን። ትኩረት የማናደርግባቸው ሕሙማን የሚደርሱባቸው የሥራ ክፍሎች የሉንም። ይህ ጥራት አያስፈልገውም ብለን የምንተወው የሥራ ክፍል የለንም፤ ሁሉም የምንሰጣቸው አገልግሎቶች ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሰራ ቢሆንም በቂ ግን አይደሉም“ ነው ያሉት። ስህተትን መቀነስ የሚያስችል ሥርዓት የማበጀትና ተግባራዊ የማድረግ አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም። ይህን አስመልክቶ ዳይሬክተሩ ሲያብራሩ “ለስህተት ተጋላጭ የሆኑ አገልግሎቶች አሉ። እነሱ ላይ በጣም በልዩ ትኩረት ነው የምንሰራባቸው። የቀዶ ሕክምና ክፍል ከእነዚህ መካከል ነው“ ብለዋል። ስህተቶችን ለመቆጣጠር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ አሠራሮች አሉ። እኛ ይህንን “ሰርጂካል ሴፍቲ ቼክ ሊስት“ እንለዋለን ይላሉ ዶ/ር አብዱ።

ይህ ቼክ ሊስት ሳይሞላ ማንም ሰው የቀዶ ሕክምና አይደረግለትም። ስለሆነም ይህ ቼክ ሊስት ስህተቶች እንዳይፈጠሩ ለመቆጣጠር የሚረዳ አንዱ ዘዴ ነው። ስኬቶች . . . የሕክምና ጥራትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት በኮሌጁ የሚሰጡ አገልግሎቶች እና የማስተማር ሂደቱ ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ የተገበራቸው የተለያዩ አሠራሮች እና ስልቶች ውጤት እየተገኘባቸው ስለመሆኑ መረጃዎች ያመላክታሉ። ዳይሬክተሩ እንደሚገልጹት፤ በተቋሙ የአገልግሎት ጥራትን ለማስጠበቅ በየሥራ ክፍሉ ቁጥጥር እና ክትትል ይደረጋል፣ አሠራሮች ይዘረጋሉ፣ አፈጻጸማቸው ይመዘናል፣ የሚስተዋሉ ክፍተቶች ይለያሉ፣ ግብረ መልስ ይሰጣል። ከእነዚህ ሁሉ ሥራዎች ጎን ለጎን በክትትል ወቅት የሚገኙ ክፍተቶችን ለማስተካከል የሚረዳ እና የማሻሻያ አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት (Quality Improvement Proj- ect) አሰራር ስለመኖሩ ኃላፊው ይጠቅሳሉ። ይህ ፕሮጀክት በችግሮች ዙሪያ ከየሥራ ክፍሎች ጋር በመሆን የመፍትሔ አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት እና የሚተገበሩበት ነው። በዚህ ፕሮጀክት አማካኝነት ከተሠሩና

ውጤት ከተገኘባቸው መካከል ማሳያ ያሏቸውን ዶ/ር አብዱ ያነሳሉ። አንድ ታካሚ ወደ ተቋሙ ሲመጣ የመጀመሪያ ተግባሩ የሚሆነው ከካርድ ክፍል ካርድ ማውጣት ነው። እንደ ዶ/ር አብዱ ገለጻ፤ በካርድ ክፍሉ ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ለዓመታት የተጠራቀሙ የማይፈለጉ ካርዶች ተከማችተው ቦታ ከመያዛቸው ባሻገር የሚፈለጉትን በፍጥነት ለማግኘት አዳጋች፣ ለማስተዳደርም አዳጋች በመሆኑ የሚፈለጉ እና የማይፈለጉ ካርዶችን የካይዘን ፍልስፍናን በመተግበር ማስወገድ ተችሏል። ከዚህ ቀደም አንድ ታካሚ አልትራ ሳውንድ ቢታዘዝለት ከሁለት ቀን በኋላ ነበር ውጤቱ የሚደርስለት። ይህ በተቋሙም ሆነ በታካሚው ላይ የሚያሳድረው ጫና እና እንግልት ቀላል አልነበረም። ስለሆነም ሁለት ቀን የሚቆይበትን ምክንያት በመፈተሽ መፍትሔ ተበጅቶለታል። ይህም በመሆኑ ከሁለት ዓመት ወዲህ ባሉት ጊዜያት አንድ ታካሚ በሆስፒታሉ አልትራ ሳውንድ ከታዘዘለት ሳይውል ሳያድር የምርመራ ውጤቱ እየተሰጠው ነው ይህም ሌላው እልባት የተሰጠው የአልትራ ሳውንድ አገልግሎት ነው።



137

የቀዶ ሕክምና ቀጠሮ ከተያዘ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች እንደሚሰረዝ በተደረገ ክትትል በመታወቁ ምክንያቱ ሲጠና ለቀዶ ሕክምና ቀጠሮ የሚሰጣቸው ታካሚዎች የደም ግፊት እና የስኳር ሕመም ካላቸው እንዲቆጣጠሩት ባለመደረጉ እና ምክር ባለመሰጠቱ፣ መድኃኒት በአግባቡ ባለመውሰድ እና አስቀድሞ በሚደረጉ ምርመራዎች አለመሟላት መሆኑ ተለይቷል። ለችግሮቹ መፍትሔ ለማበጀት እንዲቻል የቅድመ ሰመመን (Pre-anesthesia) ክሊኒክ

ተቋቋመ፤ ክሊኒኩ አንድ ሰው ወደ ቀዶ ሕክምና ክፍል ከመግባቱ በፊት መሠራት የሚገባቸውን ሥራዎች ይከታተላል። ይህም በተቋሙና በታካሚው ላይ ይደርስ የነበረውን እንግልት፣ አላስፈላጊ ውጣውረዶችና የሐብት ብክነት መቀነስ አስችሏል። ዶ/ር አብዱ የተጠቀሱትን ዓይነት ማሻሻያዎች ካደረግን በኋላ ልምድና ዕውቀቱ እኛ ጋር ብቻ መቅረት ስለሌለበት ሌሎች ተቋማት እንዲማሩበት ተሞክሮዎቻችንን እናካፍላለን ብለዋል።



138

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ማኅበራዊ

“ትውልድ ይማር፣ ይሠልጥን



139

ከዓለም ይፎካከር”

በምህረቱ ሞላልኝ

መንደርደሪያ.... ኢትዮጵያ ዜጎችን በየደረጃው ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችሉ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ተግባራትን በማከናወን ላይ ትገኛለች። ዘላቂ ልማት የተረጋገጠባት፣ ሰላም የሰፈነባት፣ ጠንካራ እና የሕዝቦች አንድነት የተገነባባት የበለጸገች አገር መገንባት የሚያስችሉት እነዚህ ተግባራት በርካታ ቢሆኑም መንግሥት ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ጋር በመሆን እየተገበረ ያለውን አምሥት ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግና በኦን ላይን የሚሰጥ ነጻ የኮደርስ ሥልጠና ስምምነት ምንነትና ፋይዳ የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ቅኝት ነው። ዜጎች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና ዘመኑ የሚሻውን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥልጠና በነፃ የሚያገኙበትን ዕድል የፈጠረው



140

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ይህ ስምምነት የኢትዮጵያ መንግሥት ካስመዘገባቸው የዲፕሎማሲ ስኬቶች አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል። ይህ ሥልጠና በጣም ውድ በመሆኑ የአገር ሐብት ተጠቅሞ ትምህርቱን በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች መስጠት እጅግ በጣም ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መልካም ግንኙነት ከመሰረቱባቸው አገራት ቀዳሚዋ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ነች። በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገ የሦስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ተጀምሮ፤ ባለፉት አምሥት ዓመታት በቀጠለው ተከታታይ ጥረት የሁለትዮሽ ግንኙንቱ ወደ ከፍተኛ የወዳጅነትና የትብብር መስክ አድጓል። የሁለቱም አገራት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተለያዩ ጊዜያት እየተገናኙ የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን በመፈትሽና በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ እና በኢኮኖሚያዊ መስኮች የሚያደርጉትን የትብብር ማዕቀፍ ዘርፎች በማበራከት የአገራቱን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ ችለዋል። በነሐሴ 12 ቀን 2015 ዓ.ም የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ፕሬዚዳንት መሐመድ ቢን ዛይድ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ባላቸው ቅርበት

ለኢትዮጵያዊያን ወጣቶች የተለያዩ የትምህርት ዕድሎችን በመስጠት ይታወቃሉ። ለአብነት በ2014 ዓ.ም ከፍተኛ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያስመዘገቡ 273 ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች በተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች የቅድመ ምረቃ መርሃ-ግብር ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝተው በአገሪቱ በሚገኙ አሥር ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ የትምህርት መስኮች እንዲገቡ መደረጉን መጥቀስ ይቻላል። የነፃ ትምህርት ዕድሉ የተገኘው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተነሳሽነትና ጥረት ነው። ይህንኑ ጥረት በማሳደግ ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም አምስት ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነፃ የዲጂታል ትምህርት ስምምነት ይፋ ተደርጓል። የአምሥት ሚሊዮን ኮዶሮች ኢኒሼቲቭ በዓለማችን ላይ ያለው ሁለንተናዊ ነገር እጅግ ተለዋዋጭ ነው። መላውን ዓለም ጠባብ መንደር ያደረገው የዘመኑ የዲጂታል ቴክኖሎጂ እጅግ የላቀ ደረጃ ላይ ከመድረሱ ባሻገር ተለዋዋጭነቱም እየበዛ መምጣቱ ከማንም የተሰወረ አይደለም። በመሆኑም ከዚህ ፈጣን ለውጥ ጋር ዜጎችን እያበቁ አገር መገንባት ለነገ ሊባል

የማይችል ወሳኝ ጉዳይ ነው። ይህንን ከግምት ውስጥ ማስገባት የቻለው የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎች ዘመኑ የሚጠይቀውን እውቀትና ክህሎት ቀስመው በዓለም መድረክ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ የቆየ ሲሆን ይህንኑ በማጠናከር የአምሥት ሚሊዮን ኮዶሮቸ ኢኒሼቲቭ የሥልጠና ዕድል እንዲፈጠር አድርጓል። የወጣቶችን ክህሎት ዘመኑ በሚዋጀው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማጎልበት ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ጋር የተደረገው የአምሥት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ስምምነት በአዲስ አበባ ሳይንስ



141

ሙዚየም ያስጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት ኢኒሼቲቩ “የዲጂታል ክህሎት ክፍተትን ለመቅረፍ ያለመ ሀገራዊ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ አካል” ነው ሲሉ ገልጸዋል። በፕሮጀክቱ የሚሰጠው መርሃ ግብር አምሥት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ወጣቶችን በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ አንድሮይድ ዴቨሎፕመንት፣ ዳታ ሳይንስ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሰረታዊ የዲጂታል ክህሎት እንዲኖራቸው ለማድረግ ያለመ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የኢትዮጵያ የወደፊት ተስፋ የሚመሰረተው ወጣቶች

ላይ በመሆኑ ዛሬ የጀመርነው ኢኒሼቲቭ ትልቅ ዕድል ነው” ብለዋል። ወጣቶች ለፕሮግራሙ ተመዝግበው ክህሎታቸውን በማዳበርና የምስክር ወረቀት (Certificate) በመያዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ አሳስበው በዚህ ፕሮጀክት የሚሠለጥኑ ኮደሮች ለአገራችው የዲጂታል ችግር አዳዲስ መፍትሄዎችን ከማምጣት ባሻገር ለአህጉራቸው የተስፋ ብርሃን ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል። መንግሥት የአገሪቷንና የሕዝቦቿን ብልጽግና እውን ለማድረግ ያነገበውን ሰፊ ራዕይ ማሳካት የግድ ይለዋል። ይህንን ለመፈጸም ከሚጠቀምባቸው

መንገዶች አንዱ ደግሞ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ነው። ዲጂታልን ማንበብና መጻፍ እንደዚሁም ክህሎትን ማጎልበት ወጣቶች ተወዳዳሪና አካታች ኢኮኖሚ ለመገንባት በምታደርገው ጥረት የሚኖራቸው ሚና ወሳኝ ነው። በመሆኑም በጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ የተጀመረው የአምሥት ሚሊዮን ወጣቶችን ሕይወት የሚቀይረው የኦንላይን የኮዲንግ ሥልጠና በዋናነት በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዳታ ሳይንስ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት ላይ ትኩረት ያደረገ በመሆኑ ወጣቶች ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ



142

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ወሳኝ ከሆኑት መሰረቶች አንዱ የዲጂታል ሥነ-ምህዳርን ማስፋት ነው። የዲጂታል ሥነ-ምህዳሩን ከሚያሰፉ ተግባራት አንዱ የክህሎት ግንባታ በመሆኑ በዘርፉ እውቀትና ክህሎት ያለውን የሰው ኃይል ለማፍራት መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት ይገኛል፡፡ ኢኒሼቲቩ ወጣቶች በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ

እንዲኖራቸውና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ የሚያስችል ክህሎት የሚያገኙበት ነው። ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ መስክ በቂ አቅም እንዲኖራት፣ ወጣቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ የፈጠራ ሥራ ችሎታቸውን እንዲያጎለብቱ እንዲሁም የዲጂታል ቴክኖሎጂን በዕለት ተዕለት ሥራዎቻቸው መጠቀም የሚያስችል እንደሆነ ይታመናል። ናርዶስ አባይ በአዲስ አበባ ከሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶቸ በአንዱ በመምህርነት በማገልገል



143

ላይ ትገኛለች። የሁለት ልጆች እናት ስትሆን ባለቤትዋን በሞት ካጣች ሦስት ዓመታት ተቆጥረዋል። በጂኦግራፊ ትምህርት ዲፕሎማዋን ከያዘች በኋላ ትምህርቷን ለመቀጠል አልያም የሥራ መስክ ለመቀየር ፍላጎት ቢኖራትም የገንዘብ አቅም በማጣቷ ምክንያት ሳይሳካላት ቆይታለች። በየወሩ የምታገኘው ደመወዝ ከልጆቿና ከራስዋ የዕለት ጉርስ የሚያልፍ አልሆነም። “የተሻለ ክፍያ የሚያስገኝ ሥራ ለማግኘት የትምህርት ደረጃዬን ለማሻሻል

ወይም የትምህርት መስክ ለመቀየር ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖረኝም ይህንን ለማድረግ ግን አቅም አልፈቀደልኝም” ትላለች። በዚህ ምክንያት ዲፕሎማዋን ከያዘች በርካታ ዓመታት ቢቆጠሩም የትምህርት ደረጃዋን ማሻሻል አልቻለችም። አሁን ናርዶስ ትምህርቷን ለመቀጠል ለነበራት ከፍተኛ ምኞች ምላሽ አግኝታለች። የአምሥት ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ተጠቃሚ ከሆኑ ወጣቶች መካከል መሆን ችላለች። ‘ዳታ ሳይንስ’ን በኦንላይን እያጠናች ትገኛለች። “ይህ ዕድል መቼም ላገኘው የማልችል ዕድል ነበር፤ ምክንያቱም በገንዘብ ችግር ምክንያት ለረጅም ዓመታት መማር አልቻልኩም ነበር። አሁን ግን በነጻ የኮዲንግ ሥልጠና ማግኘት በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ መንግሥትንም በጣም አመሰግናለሁ” ነው ያለችው። የናርዶስ ቀጣይ ፍላጎትና ምኞች የጀመረችውን ከጨረሰችና የምስክር ወረቀት ካገኘች በኋላ ሌላ ተጨማሪ ፕሮግራም ማጥናት ነው። ያገኘችውን ዕድል በመጠቀም ሕይወትዋን መቀየር እንደምትችል ተስፋ እንዳደረገች ትናገራለች። እንደ ናርዶስ ተመሳሳይ የገንዘብ አቅም ችግር ከህልማቸው እንዳይደርሱ ያደረጋቸው ወጣቶች ቁጥር

የትየለሌ ነው። የመማርም ሆን የሥራ ዕድል ያጡ ዜጎችም በርካቶች ናቸው። ይሁንና አሁን ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ወጣቶች ነፃ የኮዲንግ ሥልጠና መከታተል መጀመራቸው ትልቅ ተስፋ አሳድሯል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው እስካሁን ባለው ሂደት በአገር አቀፍ ደረጃ ከአንድ መቶ ሺህ በላይ ወጣቶች የዲጂታል ሥራ ክህሎት የማሳደጊያ ሥልጠናውን በተለያዩ ዘርፎቸ በመከታተል ላይ ይገኛሉ፡፡ “ትውልድ ይማር፣ ትውልድ ይሠልጥን፣ ከዓለም ጋር ይፎካከር” በሚል እሳቤ ወጣቶች የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን በማዳበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ብቁ እንዲሆኑ የሚያስችለው ፕሮጀክት በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት አምሥት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያንን መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት እንዲጨብጡ የሚያስችል ነው። መርሃ ግብሩ ትውልድ የመገንባት አካል በመሆኑ የግሉም ዘርፍ ለመርሃ ግብሩ ውጤታማነት የበኩሉን ድጋፍ የማድረግ አገራዊ ግዴታ አለበት፡፡ ወጣቶችም ዘመኑ የሚፈልገው ብቁ ዜጋ ለመሆን የሚያስችላቸውን ይህን ሥልጠና በመውሰድ አገራቸውንና መላውን ሕዝብ



144

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ሊደግፉና ለተግባራዊነቱ ሊተጋገዙ ይገባል። ከተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች መንግሥት ጋር በመተባበር የተጀመረውና ዓለም አቀፍ እውቅና ካለው ተቋም የምስክር ወረቀት የሚገኝበት ይህ የሥልጠና መርሃ ግብር ዩዳሲቲ በተሰኘ ተቋም እየተሰጠ ይገኛል። ዩዳሲቲ ከአጀማመሩ የስታንፎርድ መምህራን ነጻ የኦንላይን ትምህርት ለመስጠት በማሰብ “የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ” ኮርሶችን ለሁሉም ሰው በነጻ ለማቅረብ ዓላማ ያደረገ መሆኑን የተቋሙ የበይነ- መረብ መረጃ ያሳያል። እንደመረጃው ከሆነ በወቅቱ ከ190 በላይ አገራት ከ160 ሺህ በላይ ተማሪዎች መመዝገባቸውን ያሳያል። ሥራውን እያሰፋ በመምጣትና ትምህርቱንም የበለጠ ፍትሃዊ እና አካታች በማድረግ ተልዕኮውን ለማሳካት ባደረገው ጥረት ዕድሎችን እያሰፋ መጥቷል። ዩዳሲቲ አሁን ከ240 በላይ አገራት ውስጥ ከ16 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ የተመዘገቡ ተጠቃሚዎች፣ ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ፕሮጀክቶች የሚሰሩ፣ ከ205 ሺህ በላይ የምስክር ወረቀት ያገኙ ሠልጣኞችን በማስተናገድ ላይ ይገኛል። ዩዳሲቲ በቴክኖሎጂ ውስጥ የወደፊት ጊዜዎችን የመፍጠር ተልዕኮ ላይ አተኩሮ

እየሰራ ነው። ቀጣይ አዳዲስ ነገሮችን ማሳደግ ከሚሹ ግለሰቦች፣ ድርጅቶች እና መንግሥታት ጋር በጋራ እየሰራ እንደሆነም መረጃው ያሳያል። ይህንን ከፍተኛ ገንዘብ (ዶላር) እየተከፈለበት የሚሰጥ ሥልጠና ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አምሥት ሚሊዮን ዜጎች ዕድሉን በነጻ እንዲያገኙ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራ ያከናወኑት። የኢኒሼቲቩ ፋይዳ የአምሥት ሚሊዮን ኮደሮች ኢኒሼቲቭን ፋይዳ በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በማኅበረሰብ እና በአገር ደረጃ ከፋፍሎ ማየት ይቻላል። በአገር ደረጃ መንግሥት ባለፉት ስድስት ዓመታት ሥራ አጥነትን ለማቃለል የተለያዩ መርሃ ግብሮችን በመዘርጋት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ አድርጓል። አምሥት ሚሊዮን ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርገው ይህ ኢኒሼቲቭም የዚሁ አካል ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ከዚህ አንጻር ኢኒሼቲቩ በርካታ ፋይዳዎች አሉት። ከእነዚህም መካከል ዘመኑ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ በአግባቡ ለመረዳት፣ በየወቅቱ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ችሎታና ብቃት ለማጎልበት፣ የተለያዩ መረጃዎችን

ለማጠናቀር፣ የፈጠራ ክህሎትን የበለጠ ለማሳደግ፣ ሁለንተናዊ ቋንቋን ለማሻሻል፣ የኅብረተሰብ አገልግሎትን ለማቀላጠፍ እና የሥራ ዕድልን የበለጠ ለማስፋት የሚሉት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። ኮዲንግ (ኮድ ማድረግ) በሁሉም ዓይነት ኢንዱስትሪዎች ተፈላጊ ክህሎት ነው። እንደ ሶፍትዌር ልማት እና ቴክኒካል ኦፕሬሽኖች የመሳሰሉ የረቀቁ የተለያዩ የሙያ ዘርፎችን የሚያጠቃልል በመሆኑ ተፈላጊነቱ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። በመሆኑም የኮዲንግ ክህሎት የገቢ አቅምን ለማሳደግ እጅግ ጠቃሚ ነው። ኮዲንግን መማር በርካታ ጥቅሞችን እና ሰፊ የሥራ ዕድሎችን ያስገኛል። በማደግ ላይ ያሉ የበርካታ አገራት መሰረታዊ ችግር የሆነውን ሥራ አጥነት በማቃለል የማህበረሰብን ችግር ለማስወገድ መንግሥታት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ይሰራሉ። በአገራችንም በተመሳሳይ መልኩ ሥራ አጥነትን ማስቀረት ከዋና ዋና አገራዊ አጀንዳዎች መካከል አንዱ ነው። ኢኒሼቲቩ ቀደም ሲል ሲሰራ ከነበረው ሥራ አጥነትን የማቃለል እንቅስቃሴ በተጨማሪ አምሥት ሚሊዮን ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ነው። ወጣቶች ዘመኑ የሚጠይቀውን የቴክኖሎጂ ክህሎት በመታጠቅ



145

በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆነው በትላልቅ የውጭ እና የአገር ውስጥ ተቋማት የሥራ ዕድል እንዲከፈትላቸው የሚያስችል በመሆኑ ፋይዳው ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። መንግሥታዊም ሆኑ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በየወቅቱ ከፍተኛ የሰው ኃይል የሚፈልጉ ቢሆኑም አብዛኞቹ የሥራ መስኮች ከሚጠይቁት ክህሎትና ብቃት አንጻር የወጣቶች ተጠቃሚነት ተረጋግጧል ማለት አያስደፍርም። በተለይ ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ሥልጠናዎች የሚጠይቁት ክፍያ ቀላል ባለመሆኑ በዘርፉ

የሠለጠኑ ዜጎች ቁጥር ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጎታል። ከዚህ ባሻገር ከቴክኖሎጂ ሥልጠና ጋር ተያይዘው የሚሰጡ ሥልጠናዎች አንድም ዋጋቸው ውድ በመሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ ሥልጠናውን በበቂ ሁኔታ ለመስጠት የተቋማት የአቅም ውስንነት በመኖሩ መማርና ራሳቸውን መቀየር እየቻሉ በገንዘብ እጦት ምክንያት መማር ያልቻሉ ወጣቶች ቁጥር አሻቅቧል። ኢኒሼቲቩ ይህንን ችግር በመፍታት ረገድ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነው። ኮድ በመስጠት የችግሮች አፈታት ላይ አዲስ እይታ እንዲኖረን በማገዝ የሎጂክ



146

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

የአስተሳሰብ ችሎታን ማሻሻል፤ ውስብስብ የኮድ ፕሮጀክቶችን ለማከናወንም ሆነ አዳዲስ የአሰራር ዘዴዎችን ለማፍለቅ የሚያጋጥምን ማንኛውንም ፈተና ለመቋቋምና ለመፍታት ማስቻሉም ሌላው የኢኒሼቲቩ ፋይዳ ነው። ዜጎች በገንዘብ ማጣት ምክንያት ሊያገኙት የማይችሉት ለሕይወታቸው እጅግ ጠቃሚ የሆነን የትምህርት ዘርፍ በነጻ ተጠቃሚ በማድረግ፤ ናርዶስን የመሳሰሉ በርካታ ወጣቶችን አገሪቷ እየተጓዘችበት የምትገኘውን የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ ዘመኑ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ በማስታጠቅ ከፍተኛ ጥቅም ይኖረዋል። የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን በስፋት ለማቀጣጠል የሚረዳ ፕሮግራም በመሆኑ በአገሪቷ ያለውን የዲጂታል ክህሎት ክፍተት በማጥበብ ረገድም ቁልፍ ሚና አለው። ሚሊዮኖች ኮደሮች ያላት አገር ከቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ ሊፈጠር የሚችልን ችግር በቀላሉ ለመፍታት ስለምትችል የኢኒሼቲቩ አገራዊ ጠቀሜታ እጅግ በጣም የላቀ ነው። በመሆኑም የዲጂታል ኮደርስ ሥልጠና የሚወስዱ ወጣቶች ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ክህሎት በመቅሰም በሠለጠኑበት መስክ አገራቸውን

እያገለገሉ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችላችው ልዩ ዕድል ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢኒሼቲቩ ለአገርና ለሠልጣኞች ከሚኖረው ፋይዳ አንጻር በአገር ውስጥና በውጭ አገራት በጎ ተጽዕኖ ለመፍጠር ጉጉት ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች፣ ተማሪዎችና ባለሙያዎች ዕድሉን እንዲጠቀሙ ጥሪ በማቅረብ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የክህሎት አበልጻጊዎች፣ አሳዳጊዎችና ዩኒቨርሲቲዎች ፕሮጀክቱን መደገፍ እንዳለባቸው ያሳሰቡት። በምንኖርባት ዓለም ቴክኖሎጂ በሚያስደንቅ ፍጥነት ማደጉን ቀጥሏል። ኮድ መስጠት መቻል ደግሞ በዚህ የቴክኖሎጂ ለውጥ ውስጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ከአዳዲስ ሮቦቲክስ እና አውቶሜትድ ቴክኖሎጂዎች አንፃር በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ ይሆናል። ኮድ ማድረግ ትምህርት መማርን ለመቀጠል የሚያስፈልጉ ክህሎቶችን ይሰጣል። ይህ ደግሞ ለዓለም አቀፍ ባንኮች፣ የጤና ድርጅቶች፣ አውቶማቲክ አሰራሮች እና የተሽከርካሪዎችን ቴክኖሎጂ ለማሻሻል ይጠቅማል። ይህ ብቻ አይደለም መረጃን ለማጠናቀርና ለመተንተን የተዋቀረ የመጠይቅ ቋንቋ



147

Structured query lan- guage (SQL) ካሉ በኮዲንግ ቋንቋዎችን ተገንዝቦ ለመስራት ልምድ ይሰጣል። SQL በተዛማጅ ዳታቤዝ ውስጥ መረጃ ለማከማቸትና ለማስኬድ የሚጠቅም የፕሮግራሚንግ ቋንቋ ነው። ተዛማጅ መረጃዎችን በሰንጠረዥ መልክ ያከማቻል፣ ረድፎች እና አምዶች በተለያዩ የመረጃ እሴቶች መካከል ያሉ ግንኙነቶችን ለማወቅ ያግዛል። እነዚህ ክህሎቶች ውስብስብ ዳሽቦርዶችን እና ሪፖርቶችን ለመንደፍ ጠቃሚ ናቸው። መረጃን የበለጠ ተደራሽ እና ቀላል ለማድረግ የሚያገለግል ክህሎት ነው። የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሲባል መረጃን ለማግኘት ዲጂታልን ለማንበብና ለመጻፍ፣ ለመገምገም፣ ለመፍጠር እና ለማስተላለፍ የመረጃና የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም ችሎታ ማለት ነው። ይህ በመሰረታዊነት በአገር አቀፍ ደረጃ በ2018 ዓ.ም ለአምሥት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች የዲጂታል ማንበብና መፃፍ ሥልጠናን በመስጠት ለሕይወታቸው እና ለሥራቸው አስፈላጊ የሆነውን ክህሎት እንዲያገኙ ማድረግን ዓላማ አድርጓል። ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና በምታደርገው ጉዞ ዜጎች

በተለይ ደግሞ ወጣቶች የዲጂታል ዕውቀት ባለቤት እንዲሆኑ ማብቃት ወሳኝ ጉዳይ ነው። ይህ መጠነ ሰፊ መርሃ ግብር ለወጣቶች የመሠረተ ዲጂታል ክህሎት ሥልጠና በነጻ በመስጠት በአገራቸው ልማት ንቁ ተሳትፎና አስተዋጾ እንዲያደርጉ ተጠቃሚም እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው። ኮድ ማድረግ እንደ ግራፊክ ዲዛይን፣ ድረ ገጽ ወይም መተግበሪያዎችንና ሌሎች የፈጠራ መስኮች ላይ ብዙ ዕድሎችን ሊከፍት ይችላል። ለጸሐፊያንም በብሎግ አቀማመጥ ላይ አርትዖቶችን ማድረግ ወይም የኦንላይን ጋዜጣ ወይም የዳሰሳ ጥናት የማከናወን ክህሎትን ያሳድጋል። ኮድ ሁለንተናዊ ቋንቋ ነው፤ በዓለም ዙሪያም አንድ ነው። መተርጎም አያስፈልገውም። ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር በሚንቀሳቀስበት ጊዜ በሌላ የትምህርት ዘርፍ ከሆነ ሙያዊ የቋንቋ እንቅፋት ሊያጋጥመን ይችላል። በኮዲንግ ግን ይህ አይታሰብም። በኮድ የሚደረጉ ቋንቋዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ ዓይነት በመሆናቸው ወደ የትኛውም አገር ከእኛ ጋር ይዘነው የምንጓዘው ክህሎት ነው። እንደ ኮድ አቀንቃኝ፣ የፕሮግራሚንግ ወይም የኮድ

ማኅበረሰብን መቀላቀል በርካታ ጥቅማጥቅሞችም አሉት። ተመሳሳይ አስተሳሰብ ካላቸው ሰዎች ጋር እውቀትን፣ ምክርን እና ክህሎትን ለመለዋወጥ ዕድል ይሰጣል። ለማጠቃለል የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ከሥራ ፈጠራ ባሻገር ለአገልግሎት ዘርፍ ኢንቨስትመንት መጎልበት ሚናው የጎላ ነው:: አሁናዊ የኢኒሼቲቩ ሂደት ከፕሮግራሙ መጀመር ጋር ተያይዞ በመንግሥት በኩል ወጣቶች የዚህ ትልቅ ፕሮጀክት ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ለማስቻል ቀላል የማይባል ጥረት እየተደረገ ነው። ከእነዚህ መካከል መገናኛ ብዙሃንን መጠቀም አንዱ ሲሆን ስለ ኢኒሼቲቩ ሁሉም ኅብረተሰብ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማስቻል በስፋት እየተሰራበት መሆኑ ነው። በተጨማሪም በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ሥልጠናውን መውሰድ ለሚሹ ወጣቶች እገዛ እየተደረገላቸው ይገኛል። ፕሮጀክቱን ወደ መሬት ለማውረድ እንደዚሁም በመላ አገሪቷ የሚገኙ ወጣቶች የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የማነቃቂያ ሥልጠናዎች እየተሰጡ ይገኛሉ። በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሰሩ ካሉ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ



148

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

በሆነው የአምሥት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ 134 ሺህ ሠልጣኞች በያሉበት ሆነው በበይነ-መረብ አማራጭ ሥልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ። ይህ ሥልጠና ክህሎትን ለማሳደግም ሆነ አዲስ ነገር ለማወቅ ለሚሹ ዜጎች በሙሉ ሰፊ የዕድል በር የከፈተ በመሆኑ ሥልጠናውን በመከታተል ዓለም አቀፍ የብቃት ማረጋገጫ ማግኘት እንደሚቻል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። ሥልጠናው በዋና ዋና ከተሞች ብቻ ታጥሮ እንዳይቀር በገጠር ከተሞችም አጠቃቀሙን በተመለከተ ሥልጠና በመሰጠት ላይ ይገኛል። በምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የማነቃቂያ ሥልጠና 139 ሺህ ወጣቶችን ተሳታፊ መሆናቸውን አብነት መጥቀስ ይቻላል። በተመሳሳይ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 198 ሺህ 284 ወጣቶችን ለማሠልጠን ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ወጣቶችን በዲጂታል ዓለም ይበልጥ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ግንዛቤ በመፍጠር ወደ ሥልጠና ለማስገባት እንቅስቃሴው ተጠናክሮ ቀጥሏል። በአዳማ ከ110 ሺህ በላይ ወጣቶች እንደሚሳተፉ የከተማዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የስማርት አዳማ

ኢንሼቲቭ አስተባባሪ ኢንጂነር ሙክታር ጄይላን የገለጹ ሲሆን፤ በተመሳሳይ በአፋር ክልል ከ53 ሺህ በላይ ወጣቶች በሥልጠና ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተነግሯል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት 62 ሺህ ሠልጣኞች ዲጂታል ሥልጠናውን መውሰድ የሚያችሉ የተለያዩ የማንቂያ ሥልጠናዎች እየተሰጡ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ በ2017 በጀት ዓመት 75 ሺህ ወጣቶች ሥልጠናውን እንዲከታተሉ ዕቅድ ይዞ እየሰራ ይገኛል። በአጠቃላይ እስካሁን ባለው ሂደት በአገር አቀፍ ደረጃ ከ100 ሺህ በላይ ወጣቶች ሥልጠናውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ታውቋል። ይህ የተቀናጀ እንቅስቃሴ በኢኒሼቲቩ የተያዙ ግቦች እንዲሳኩ ጉልህ ሚና እንዳለው መገመት አያዳግትም፡፡ የአምሥት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ከ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ጋር የሚጣጣም መሆኑን በከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተለያየ ጊዜ ተገልጿል። ማጠቃለያ በርካታ ወጣቶችን የሚያሳትፍና የጎላ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለው የኢትዮጵያዊያን ኮደርስ

ዲጂታል ሥልጠና ለሚቀጥሉት ተከታታይ ሦስት ዓመታት ወጣቶችን በዲጂታል ሙያ ለማፍራት ያለመ ፕሮግራም በመሆኑ ወጣቶች የዚህ ዕድል ተጠቃሚ በመሆን ራሳቸውን ጠቅመው አገራቸውን የሚያገለግሉበት መልካም አጋጣሚ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኮደር ኢኒሼቲቭን በይፋ ሲያስጀምሩ ከመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች መካከል ቢያንስ 50 በመቶ የሚሆኑት ወጣት ሴቶች እንዲሆኑ፤ ፕሮጀክቱ ከሁሉም ክልሎች ወጣቶችን ማስታጠቅ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ገልፀዋል። ይህ ዘመኑ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ክህሎት የማግኘት ዕድል የሚፈጥር ዲጂታል የክህሎት ማበልጸጊያና በዓይነቱ ልዩ የሆነ የነፃ የትምህርት ዕድል “ትውልድ ይማር፣ ትውልድ ይሰልጥን፣ ከዓለም ጋር ይፎካከር” በሚል እሳቤ ይፋ ሲሆን ዜጎች የቴክኖሎጂ ዕውቀታቸውን በማዳበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑም ተነግሯል።



149



150

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 28 ጥቅምት 2017 ዓ.ም


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም